በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክን መውደድ የሚያስገኘው አንድነት

አምላክን መውደድ የሚያስገኘው አንድነት

አምላክን መውደድ የሚያስገኘው አንድነት

 በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ የክርስቲያን ጉባኤ ሲመሠረት አንድ ለየት የሚያደርገው ነገር ነበር። አባላቱ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የመጡ ቢሆኑም አንድነት ነበራቸው። እነዚህ የእውነተኛው አምላክ አገልጋዮች በእስያ፣ በአውሮፓና በአፍሪካ ከሚገኙ አገራት የመጡ ሲሆኑ በመካከላቸው ካህናት፣ ወታደሮች፣ ባሪያዎች፣ ስደተኞች፣ የእጅ ባለሞያዎች፣ የመንግሥት ሠራተኞችና ነጋዴዎች የነበሩ ሰዎች ይገኙ ነበር። አንዳንዶቹ አይሁዳውያን ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ አሕዛብ ነበሩ። ብዙዎቹ ቀደም ሲል አመንዝሮች፣ ግብረ ሰዶማውያን፣ ሰካራሞች፣ ሌቦች ወይም ዘራፊዎች የነበሩ ቢሆንም ክርስቲያን ሲሆኑ ግን መጥፎ ድርጊታቸውን ትተው በእምነት አንድ ሆኑ።

በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው የክርስቲያን ጉባኤ እነዚህ ሁሉ ሰዎች አንድነት እንዲኖራቸው ማድረግ የቻለው እንዴት ነው? እነዚህ ሰዎች እርስ በርሳቸውም ሆነ ከሌሎች ጋር በሰላም መኖር የቻሉት ለምንድን ነው? ዓመጽ ሲቀሰቀስ ወይም ግጭት ሲፈጠር ገለልተኛ የሆኑት ለምን ነበር? የጥንቱ የክርስቲያን ጉባኤ ዛሬ ካሉት ታላላቅ ሃይማኖቶች በጣም የተለየ የሆነው ለምንድን ነው?

የጉባኤው አባላት አንድነት እንዲኖራቸው ያደረገው ምን ነበር?

በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች እርስ በርስ አንድነት እንዲኖራቸው አስተዋጽኦ ካደረጉት ነገሮች መካከል ዋነኛው ለአምላክ የነበራቸው ፍቅር ነው። እነዚህ ክርስቲያኖች ተቀዳሚ ግዴታቸው እውነተኛ አምላክ የሆነውን ይሖዋን በፍጹም ልባቸው፣ በፍጹም ነፍሳቸውና በፍጹም ሐሳባቸው መውደድ እንደሆነ ተገንዝበው ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ አይሁዳዊ የነበረው ሐዋርያው ጴጥሮስ ወደ አንድ የባዕድ አገር ሰው እንዲሄድ ታዝዞ ነበር። እንደ አስተዳደጉ ቢሆን ኖሮ ጴጥሮስ ከዚህ ሰው ጋር መቀራረብ አይፈልግም ነበር። በዚህ ወቅት የታዘዘውን እንዲፈጽም የገፋፋው ዋነኛው ምክንያት ለአምላክ የነበረው ፍቅር ነው። እርሱና በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ሌሎች ክርስቲያኖች ከአምላክ ጋር የተቀራረበ ዝምድና የነበራቸው ሲሆን ለዚህም መሠረት የሆናቸው ስለ ባሕርያቱ እንዲሁም ስለሚወዳቸውና ስለሚጠላቸው ነገሮች ትክክለኛ እውቀት ማካበታቸው ነው። ከጊዜ በኋላ ሁሉም ክርስቲያኖች የይሖዋ ፈቃድ አገልጋዮቹ “አንድ ልብ፣ አንድ ሐሳብ” እንዲኖራቸው መሆኑን ተገነዘቡ።—1 ቆሮንቶስ 1:10፤ ማቴዎስ 22:37፤ የሐዋርያት ሥራ 10:1-35

እነዚህ አማኞች አንድነት እንዲኖራቸው ያስቻላቸው ሌላው ነገር ደግሞ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የነበራቸው እምነት ነው። የእርሱን ፈለግ መከተል ይፈልጉ ነበር። ኢየሱስ የሚከተለውን ትእዛዝ ሰጥቷቸዋል:- “እኔ እንደ ወደድኋችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ። እርስ በርሳችሁ ብትዋደዱ፣ ሰዎች ሁሉ የእኔ ደቀ መዛሙርት እንደ ሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ።” (ዮሐንስ 13:34, 35) እዚህ ላይ የተገለጸው ፍቅር አላፊ የሆነ የወረት ፍቅር ሳይሆን ራስን ለሌሎች መሥዋዕት እስከማድረግ የሚደርስ ፍቅር ነው። እንደዚህ ዓይነት ፍቅር ማሳየታቸው ምን ውጤት ያስገኛል? ኢየሱስ በእርሱ የሚያምኑትን ሰዎች አስመልክቶ “አባት ሆይ፣ አንተ በእኔ፣ እኔም በአንተ እንዳለሁ ሁሉም አንድ እንዲሆኑ” በማለት ጸልዮአል።—ዮሐንስ 17:20, 21፤ 1 ጴጥሮስ 2:21

ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ ቅዱስ መንፈሱን ወይም ኃይሉን በእውነተኛ አገልጋዮቹ ላይ ያፈሰሰ ሲሆን ይህ መንፈስ በመካከላቸው አንድነት እንዲኖር አድርጓል። መንፈስ ቅዱስ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ሲገልጥላቸው ጉባኤዎቹ በሙሉ ይህንን እውነት ተቀበሉት። የይሖዋ አምላኪዎች በሰማይ ሆኖ በመላው የሰው ዘር ላይ የሚገዛው መሲሐዊ መንግሥት የአምላክን ስም እንደሚያስቀድስ የሚናገረውን አንድ ዓይነት መልእክት ይሰብኩ ነበር። የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ‘ከዚህ ዓለም መሆን’ እንደሌለባቸው ያውቁ ስለነበር በሕዝባዊ ዓመጽ ወይም በጦርነት አልተካፈሉም። ከሁሉም ጋር በሰላም ኖረዋል።—ዮሐንስ 14:26፤ 18:36፤ ማቴዎስ 6:9, 10፤ የሐዋርያት ሥራ 2:1-4፤ ሮሜ 12:17-21

በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ሁሉም ክርስቲያኖች አንድነታቸውን የማጠናከር ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል። እንዴት? ከመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓቶች ጋር ተስማምተው በመኖር ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች ሲጽፍ ‘በቀድሞ ሕይወታቸው የነበራቸውን አሮጌውን ሰውነት አውልቀው አዲሱን ሰውነት እንዲለብሱ’ የመከራቸው ለዚህ ነው።—ኤፌሶን 4:22-32

አንድነታቸውን ጠብቀዋል

በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች ፍጹማን ስላልነበሩ አንድነታቸውን ሊያናጉ የሚችሉ ሁኔታዎች ተፈጥረው እንደነበረ አይካድም። ለምሳሌ በሐዋርያት ሥራ 6:1-6 ላይ ግሪክኛ ተናጋሪ በሆኑት አይሁዳውያን ክርስቲያኖችና ዕብራይስጥ በሚናገሩት አይሁዳውያን መካከል አለመግባባት ተፈጥሮ እንደነበረ ተዘግቧል። ለዚህም ምክንያት የሆነው ግሪክኛ ተናጋሪ የሆኑት አይሁዳውያን ክርስቲያኖች መድሎ እንደተደረገባቸው ስለተሰማቸው ነበር። ሆኖም ጉዳዩ ሐዋርያት ጆሮ እንደደረሰ ከአድልዎ ነፃ በሆነ መንገድ አፋጣኝ መፍትሔ አግኝቷል። ቆየት ብሎ ደግሞ በጉባኤው ውስጥ የሚገኙ አይሁዳዊ ያልሆኑ ክርስቲያኖች ያለባቸውን ግዴታ አስመልክቶ የተነሳው የመሠረተ ትምህርት ጥያቄ ውዝግብ አስከተለ። በዚህም ወቅት ቢሆን በመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ላይ የተመሠረተ ውሳኔ የተሰጠ ሲሆን ሁሉም ጉባኤዎች ውሳኔውን ተቀብለውታል።—የሐዋርያት ሥራ 15:1-29

ከእነዚህ ምሳሌዎች መመልከት እንደሚቻለው በመጀመሪያው መቶ ዘመን በነበረው የክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የተፈጠሩት አለመግባባቶች የጎሣ መከፋፈል ወይም አንዱ ወገን ድርቅ ያለ አቋም በመያዙ ምክንያት የሚፈጠር የመሠረተ ትምህርት ልዩነት እንዲኖር አላደረጉም። ለዚህ ምክንያቱ ምን ነበር? መጀመሪያውኑ አንድነት እንዲኖራቸው ያደረጉት ነገሮች ይኸውም ለይሖዋ የነበራቸው ፍቅር፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ማመናቸው፣ አንዳቸው ለሌላው ራሳቸውን መሥዋዕት እስከማድረግ የሚደርስ ፍቅር ማዳበራቸው፣ የመንፈስ ቅዱስን መመሪያ መቀበላቸው፣ የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርቶች በአንድ ዓይነት መንገድ መረዳታቸውና አኗኗራቸውን ለመለወጥ ፈቃደኞች መሆናቸው ሰላማቸውንና ኅብረታቸውን ጠብቀው እንዲኖሩ አስችሏቸዋል።

የአምልኮ አንድነት በዘመናችን

ዛሬስ በዚሁ መንገድ አንድነት መፍጠር ይቻላል? ከላይ የተዘረዘሩት ነጥቦች ዛሬም ቢሆን የአንድ እምነት አባላት አንድነት እንዲኖራቸውና በዓለም ዙሪያ ከሚገኙ የተለያየ ዝርያ ካላቸው ሰዎች ጋር በሰላም እንዲኖሩ ማድረግ ይችላሉ? አዎን፣ ይችላሉ! የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ዙሪያ ከ230 በሚበልጡ አገሮች፣ ደሴቶችና ግዛቶች ከሚኖሩ ወንድሞቻቸው ጋር አንድነት ያላቸው ሲሆን ለዚህም አስተዋጽኦ ያደረጉት በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩትን ክርስቲያኖች አንድነት እንዲኖራቸው የረዷቸው ነገሮች ናቸው።

በይሖዋ ምሥክሮች መካከል አንድነት በማስፈን ረገድ በዋነኝነት ተጠቃሽ የሚሆነው ለይሖዋ ያደሩ መሆናቸው ነው። ይህም ሲባል በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ለእርሱ ታማኝ ለመሆን ይጥራሉ ማለት ነው። የይሖዋ ምሥክሮች በኢየሱስ ክርስቶስ እና በትምህርቶቹ ላይም እምነት አላቸው። እነዚህ ክርስቲያኖች የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት በማድረግ ለእምነት ባልንጀሮቻቸው ፍቅር የሚያሳዩ ከመሆኑም በላይ በሚኖሩባቸው አገሮች ሁሉ ስለ አምላክ መንግሥት የሚናገረውን ተመሳሳይ ምሥራች ይሰብካሉ። ከየትኛውም ዓይነት ሃይማኖት፣ ዘር፣ አገር ወይም ማኅበረሰብ ለመጡ ሰዎች ስለ አምላክ መንግሥት ለመናገር ፈቃደኞች ናቸው። የይሖዋ ምሥክሮች ከዚህ ዓለም ጉዳዮች ገለልተኞች በመሆናቸው የሰውን ዘር የሚከፋፍሉትን ከፖለቲካ፣ ከባሕል፣ ከማኅበራዊ ሕይወትና ከንግድ ጋር የተያያዙ ተጽዕኖዎች መቋቋም ችለዋል። ሁሉም የይሖዋ ምሥክሮች ከመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ጋር ተስማምተው በመኖር በመካከላቸው አንድነት የማስፈን ኃላፊነት እንዳለባቸው ይገነዘባሉ።

አንድነት ሌሎችንም ይማርካል

በይሖዋ ምሥክሮች መካከል የሚታየው ይህ አንድነት አብዛኛውን ጊዜ የሌላ ሃይማኖት ተከታዮች የሆኑ ሰዎችን ይማርካል። በጀርመን በሚገኝ ገዳም ውስጥ የካቶሊክ መነኩሲት የነበረችውን ኢልዘን a እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር እንድትተባበር ያነሳሳት ምንድን ነበር? ኢልዘ እንዲህ ትላለች:- “ካየኋቸው ሰዎች ሁሉ የተሻሉ ናቸው። ወደ ጦርነት የማይዘምቱ ከመሆኑም በላይ ሌሎችን የሚጎዳ አንዳችም ነገር አያደርጉም። ሰዎች በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር ገነት በሆነች ምድር ላይ በደስታ መኖር እንዲችሉ ለመርዳት ይፈልጋሉ።”

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ወደ ፈረንሳይ ተልኮ የነበረ ጉንተር የተባለ የጀርመን ወታደርም ሌላ ምሳሌ ነው። አንድ ቀን አንድ የፕሮቴስታንት ቄስ በጉንተር ክፍለ ጦር ውስጥ ለነበሩት ወታደሮች ቃለ ቡራኬ ሲሰጥ አምላክ እንዲባርካቸው፣ ጥበቃ እንዲያደርግላቸውና ድል እንዲያጎናጽፋቸው ጸለየ። ሃይማኖታዊ ሥርዓቱ ካበቃ በኋላ ጉንተር በጥበቃ ቦታው ላይ እያለ አቅርቦ በሚያሳይ መነጽር አሻግሮ ሲመለከት አንድ ቄስ በተቃራኒው ወገን ላሉት የጠላት ወታደሮችም ቡራኬ ሲሰጥ ተመለከተ። ጉንተር በኋላ ላይ እንዲህ ብሏል:- “በዚያኛው ወገን ያለው ቄስም አምላክ እንዲባርካቸው፣ ጥበቃ እንዲያደርግላቸውና ድል እንዲያጎናጽፋቸው ይጸልይ ይሆናል። ሁለት የክርስትና አብያተ ክርስቲያናት በአንድ ጦርነት ላይ የተለያየ ጎራ ይዘው የሚፋለሙ መሆናቸው አስገረመኝ።” ይህ ጉዳይ በአእምሮው ውስጥ ተቀርጾ ቆየ። ከጊዜ በኋላ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ሲገናኝና በጦርነት እንደማይካፈሉ ሲገነዘብ የዚህ ዓለም አቀፋዊ የወንድማማች ማኅበር አባል ሆነ።

አሾክና ፊማ የሩቅ ምሥራቅ ሃይማኖት ተከታዮች ስለነበሩ ቤታቸው ውስጥ ለአምላካቸው የተዘጋጀ የአምልኮ ቦታ ነበራቸው። እነዚህ ባልና ሚስት በቤተሰባቸው ውስጥ ከባድ ሕመም ሲከሰት ሃይማኖታቸውን እንደገና መመርመር ጀመሩ። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ከተወያዩ በኋላ በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችና በምሥክሮቹ መካከል በተመለከቱት ፍቅር ተማረኩ። አሾክና ፊማ አሁን የአምላክን መንግሥት የምሥራች በቅንዓት ይሰብካሉ።

ኢልዘ፣ ጉንተር፣ አሾክና ፊማ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮችን ባቀፈ የወንድማማች ማኅበር ውስጥ አንድ ሆነዋል። ዛሬ እነርሱ አንድነት እንዲኖራቸው ያደረጓቸው ነገሮች በቅርቡ ታዛዥ የሰው ልጆችን በሙሉ አንድ እንደሚያደርጓቸው በሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ያምናሉ። ከዚያ በኋላ በሃይማኖት ስም የሚፈጸም ግፍ፣ መከፋፈልና መለያየት አይኖርም። መላው ዓለም በእውነተኛው አምላክ በይሖዋ አምልኮ አንድ ይሆናል።—ራእይ 21:4, 5

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀምንባቸው አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

[በገጽ 4 እና 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ከበርካታ የዓለም ክፍሎች የመጡና የተለያየ አኗኗር የነበራቸው ቢሆኑም አንድነት ነበራቸው