በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክን ከማያስደስት ወግና ልማድ ራቅ

አምላክን ከማያስደስት ወግና ልማድ ራቅ

አምላክን ከማያስደስት ወግና ልማድ ራቅ

በአንዲት የአፍሪካ አገር አነስተኛ ግቢ ውስጥ በጠራራ ፀሐይ ላይ ያልተከደነ የሬሳ ሣጥን ተጋድሟል። ለቀስተኞቹ ሐዘናቸውን ለመግለጽ በሣጥኑ አጠገብ በሰልፍ እያለፉ ሳሉ አንድ በዕድሜ የገፉ ሰው ቆም አሉ። ቅስማቸው በሐዘን ስብር ብሎ ወደ ሟቹ ፊት ጠጋ ብለው “እንደምትሞት ለምን አልነገርከኝም? በዚህ ሁኔታ ላይ እያለሁ ለምን ጥለኸኝ ሄድክ? አሁን ወደ ቀድሞ ቦታህ ተመልሰሃል፤ እንደ ከዚህ በፊቱ ትረዳኛለህ?” አሉ።

በአንድ ሌላ የአፍሪካ አገር ደግሞ አንድ ሕፃን ተወለደ። ነገር ግን ከቤት ወጥቶ ሰዎች ሊያዩት የሚችሉት ከተወሰኑ ቀናት በኋላ ለልጁ ስም የማውጣት ሥነ ሥርዓት በሚከናወንበት ዕለት ነው።

አንዳንዶች የሞተን ሰው የማነጋገር ወይም ገና የተወለደን ሕፃን ከሰዎች እይታ የመደበቅ ባሕል ያላቸው ሰዎች እንዳሉ ሲሰሙ ይገርማቸው ይሆናል። ነገር ግን በአንዳንድ ባሕሎችና ኅብረተሰቦች ዘንድ ‘ሰዎች ሲሞቱ በውስጣቸው አንድ የማትሞት ነገር አለች፤ ሙታን ሁሉን ነገር ያውቃሉ’ የሚል ጠንካራ እምነት አለ፤ ይህ እምነት ሰዎች ለሙታንና ገና ለተወለደ ሕፃን ባላቸው አመለካከት ላይ ተጽዕኖ ያደርጋል።

ይህ እምነት በጣም ጠንካራ ከመሆኑ የተነሳ የሁሉም ልማዶችና ሥነ ሥርዓቶች ወሳኝ ክፍል ነው ለማለት ይቻላል። ለምሳሌ ያህል በርካታ ሰዎች እንደ መወለድ፣ ለአቅመ አዳምና ሔዋን መድረስ፣ ትዳር መያዝ፣ ልጅ መውለድና መሞት የመሳሰሉት በአንድ ሰው ሕይወት ውስጥ የሚከሰቱ ዋና ዋና ሂደቶች የቀድሞ አባቶች ወዳሉበት መንፈሳዊ ዓለም የሚያሸጋግሩ የተለያዩ ደረጃዎች እንደሆኑ ያምናሉ። በተጨማሪም ሟቹ በሕይወት ባሉት ሰዎች አኗኗር ላይ ትልቅ ሚና መጫወቱን ይቀጥላል የሚል እምነት አላቸው። እንዲሁም ከሞተ በኋላ እንደገና በመወለድ የሕይወት ዑደቱን ይቀጥላል ተብሎ ይታመናል።

ከአንዱ ደረጃ ወደ ሌላው ደረጃ የሚደረገው ሽግግር በጥሩ ሁኔታ እንዲካሄድ ለማስቻል በርካታ ልማዶችና ሥነ ሥርዓቶች ይፈጸማሉ። የእነዚህ ልማዶች ዋነኛ መንስኤ በውስጣችን የማትሞት ነገር አለች የሚለው እምነት ነው። እውነተኛ ክርስቲያኖች ከዚህ እምነት ጋር ግንኙነት ባላቸው ሥነ ሥርዓቶች ላይ አይካፈሉም። ለምን?

ሙታን በምን ሁኔታ ላይ ይገኛሉ?

መጽሐፍ ቅዱስ “ሕያዋን እንደሚሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን ምንም አያውቁምና፤ . . . ፍቅራቸው፣ ጥላቻቸው፣ ቅናታቸውም ከጠፋ ቈይቶአል፤ . . . ልትሄድበት ባለው መቃብር ውስጥ መሥራትም ሆነ ማቀድ፣ ዕውቀትም ሆነ ጥበብ የለም” በማለት ሙታን በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ግልጽና ቀላል በሆነ መንገድ ይናገራል። (መክብብ 9:5, 6, 10) እውነተኛ የይሖዋ አምላኪዎች ይህንን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሐቅ ከረጅም ጊዜ በፊት ጀምሮ ሲያምኑበት ቆይተዋል። ነፍስ ሟችና ጠፊ እንጂ ዘላለማዊ እንዳልሆነች ተገንዝበዋል። (ሕዝቅኤል 18:4) በተጨማሪም የሙታን መንፈስ የሚባል ነገር እንደሌለም አውቀዋል። (መዝሙር 146:4) ይሖዋ በጥንት ዘመን የነበሩ ሕዝቦቹ ሙታን ማሰብ ይችላሉ እንዲሁም በሕይወት ባሉ ሰዎች ላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉ ከሚለው እምነት ጋር ተዛማጅነት ባላቸው ልማዶችም ሆነ ሥነ ሥርዓቶች ላይ በጭራሽ እንዳይካፈሉ በጥብቅ አዟቸው ነበር።—ዘዳግም 14:1፤ 18:9-13፤ ኢሳይያስ 8:19, 20

በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖችም በተመሳሳይ ከሐሰት ሃይማኖት ትምህርት ጋር ግንኙነት ያለውን ማንኛውንም የአካባቢያቸውን ልማድ ወይም ሥነ ሥርዓት ከመከተል ተቆጥበዋል። (2 ቆሮንቶስ 6:15-17) ዛሬም ቢሆን የይሖዋ ምሥክሮች ምንም ዓይነት ዘር፣ ጎሳ ወይም አስተዳደግ ቢኖራቸው ነፍስ አትሞትም ከሚለው የሐሰት ትምህርት ጋር ግንኙነት ያላቸውን ባሕሎችና ልማዶች ከመከተል ይቆጠባሉ።

ክርስቲያን እንደመሆናችን መጠን አንዳንድ ልማዶች መፈጸምን በተመለከተ ለመወሰን ምን ሊረዳን ይችላል? ልማዱ ሙታን በሕያዋን ላይ ተጽዕኖ ያደርጋሉ እንደሚሉት ካሉ ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ ከሌላቸው እምነቶች ጋር ተዛምዶ እንዳለውና እንደሌለው በጥንቃቄ ማጤን ይኖርብናል። በተጨማሪም በእነዚህ ልማዶች ወይም ሥነ ሥርዓቶች ላይ በመካፈላችን የይሖዋ ምሥክሮች የሚያምኑትንና የሚያስተምሩትን ለሚያውቁ ሌሎች ተመልካቾች እንቅፋት እንዳንሆን ማሰብ ያስፈልገናል። እነዚህን ሐሳቦች በአእምሯችን ይዘን ከመውለድና ከሞት ጋር ተያይዘው የሚፈጸሙ ልማዶችን እንመርምር።

መወለድና ለሕፃኑ ስም የማውጣት ሥነ ሥርዓት

ልጅ ከመውለድ ጋር በተያያዘ የሚከናወኑት አብዛኞቹ ልማዶች ምንም ችግር የለባቸውም። ይሁን እንጂ መወለድ የቀድሞ አባቶች ካሉበት መንፈሳዊ ዓለም ወደ ሰብዓዊ ኅብረተሰብ መሸጋገሪያ መንገድ እንደሆነ ተደርጎ በሚታይባቸው ቦታዎች ያሉ እውነተኛ ክርስቲያኖች ጥንቃቄ ማድረግ ይገባቸዋል። ለምሳሌ በአንዳንድ የአፍሪካ አገሮች ገና የተወለደ ሕፃን ከቤት የማይወጣ ከመሆኑም በላይ እስከተወሰነ ጊዜ ድረስ ስም አይወጣለትም። የጊዜው ርዝመት ከቦታ ቦታ ቢለያይም የተወሰነው ወቅት ሲያበቃ ስም የሚወጣበት ሥነ ሥርዓት ይከናወናል፤ በዚያን ዕለት ልጁ ከቤት ይወጣና ወዳጅ ዘመዶች እንዲያዩት ይፈቀድላቸዋል። እንዲሁም በቦታው ለተገኙት ሰዎች የልጁ ስም ይፋ ይደረጋል።

ጋና—አንደርስታንዲንግ ዘ ፒፕል ኤንድ ዜር ካልቸር የተባለው መጽሐፍ ይህ ልማድ የሚከናወንበትን ምክንያት ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “ሕፃኑ ከተወለደ በኋላ ባሉት ሰባት ቀናት ‘በእንግድነት’ ላይ እንዳለና ከመናፍስት ዓለም ወደ ምድራዊው ሕይወት እየተሸጋገረ እንደሆነ ተደርጎ ይታሰባል። . . . በእነዚህ ቀናት ሕፃኑ ከቤት ካለመውጣቱም በላይ የቤተሰቡ አባል ያልሆኑ ሰዎች እንዲያዩት አይፈቀድላቸውም።”

ልጁ ስም ሳይወጣለት የሚቆየው ለምንድን ነው? “የተወለደው ሕፃን እስከ ስምንተኛው ቀን ድረስ ሰው እንደማይሆን ይታመናል። ይብዛም ይነስም ከመጣበት መንፈሳዊ ዓለም ጋር ግንኙነት እያደረገ ነው” በማለት ጋና ኢን ሪትረስፔክት የተባለው መጽሐፍ ይገልጻል። መጽሐፉ በማከል እንዲህ ይላል:- “ልጁን ሰው የሚያደርገው ስሙ ስለሆነ ወላጆቹ እንዳይሞት በመፍራት በሕይወት እንደሚቆይ እርግጠኛ እስከሚሆኑበት ጊዜ ድረስ ስም አያወጡለትም። . . . ይህ የሽግግር ጊዜ ለልጁም ሆነ ለወላጆቹ እንደ ትልቅ የፈተና ወቅት ይታያል። ልጁን ወደ ሰው ልጆች ዓለም የሚያመጣው ስም የማውጣት ሥነ ሥርዓት ነው።”

አብዛኛውን ጊዜ ስም የማውጣቱን ሥነ ሥርዓት የሚመራው በቤተሰቡ ውስጥ በዕድሜ አንጋፋ የሆነው ሰው ነው። አከባበሩ ከቦታ ቦታ ቢለያይም ሥነ ሥርዓቱ በአብዛኛው የመጠጥ ቁርባን በማፍሰስ፣ ሕፃኑ በሰላም ስለደረሰ ለቀድሞ አባቶች መንፈስ በጸሎት ምስጋና በማቅረብና በመሳሰሉት መንገዶች ይከበራል።

በክብረ በዓሉ ላይ የጎላ ሥፍራ የሚሰጠው የልጁን ስም ለማሳወቁ ሥነ ሥርዓት ነው። ለልጁ ስም የማውጣት ኃላፊነት ያለባቸው ወላጆች ቢሆኑም ሌሎች ዘመዶችም በምርጫው ላይ ትልቅ ሚና ይጫወታሉ። አንዳንዶቹ ስሞች በአካባቢው ቋንቋ “ተመልሶ መጣ፣” “እናትየው በድጋሚ መጣች” ወይም ደግሞ “አባትየው እንደገና መጣ” እንደሚሉት ያሉ ትርጉሞች ሊኖራቸው ይችላል። ሌሎቹ ስሞች ደግሞ የቀድሞ አባቶች የተወለደውን ሕፃን ወደ ሙታን ዓለም መልሰው እንዳይወስዱት ተስፋ ለማስቆረጥ ታቅደው የሚወጡ ናቸው።

እርግጥ ልጅ በመወለዱ ምክንያት መደሰት ስህተት አይደለም። ልጁን በሌላ ሰው ስም መሰየምም ሆነ ከመወለዱ ጋር የተያያዙ አንዳንድ ክስተቶችን ተንተርሶ ስም ማውጣት ምንም ችግር የለውም፤ እንዲሁም ወላጆች በመረጡት ጊዜ ስም ሊያወጡለት ይችላሉ። ሆኖም አምላክን ለማስደሰት የሚፈልጉ ክርስቲያኖች ሕፃኑ የቀድሞ አባቶች ካሉበት መንፈሳዊ ዓለም ወደ ሰብዓዊው ኅብረተሰብ እንደመጣ “እንግዳ” አድርገው እንደሚያምኑ የሚያስመስሉ ልማዶችን ወይም ሥነ ሥርዓቶችን ከማክበር ይቆጠባሉ።

በተጨማሪም በርካታ ሰዎች ስም የማውጣቱን ሥነ ሥርዓት ለሽግግር አስፈላጊ የሆነ ወቅት አድርገው ይቆጥሩታል፤ በዚህ ጉዳይ ረገድ ክርስቲያኖች ለሌሎች ሕሊና መጠንቀቅ ያለባቸው ከመሆኑም በተጨማሪ ድርጊታቸው በማያምኑ ሰዎች ላይ ሊያሳድር የሚችለውን ስሜት ከግምት ውስጥ ማስገባት አለባቸው። ለምሳሌ ክርስቲያን ቤተሰቦች ስም የማውጣት ሥነ ሥርዓት እስከሚከናወን ድረስ ልጁን ከሰዎች እይታ ቢደብቁ ተመልካቾች ምን ብለው ይደመድማሉ? ለሕፃኑ ያወጡለት ስም ያስተምሩት ከነበረው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጋር ቢጋጭ ሰዎች ላይ ምን ስሜት ያሳድራል?

ስለዚህ ክርስቲያኖች ለልጆቻቸው ስም የሚያወጡበትን መንገድም ሆነ ጊዜ ሲወስኑ ‘ሁሉንም ነገር ለእግዚአብሔር ክብር ለማድረግ’ በመጣር ለሰዎች እንቅፋት እንዳይሆኑ ይጠነቀቃሉ። (1 ቆሮንቶስ 10:31-33) ለሙታን ክብር ለመስጠት የታቀዱ ‘ወጎችን ለመጠበቅ ሲሉ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ’ ገሸሽ አያደርጉም። በተቃራኒው ሕያው ለሆነው ይሖዋ አምላክ ክብር ይሰጣሉ።—ማርቆስ 7:9, 13

ከሞት ወደ ሕይወት መሸጋገር

ብዙዎች ሞት ልክ እንደ መወለድ ሁሉ መሸጋገሪያ እንደሆነ ያምናሉ፤ አንድ ሰው ሲሞት ከሚታየው ዓለም፣ ወደማይታየው የሙታን መናፍስት ዓለም ይዘዋወራል ይላሉ። ብዙ ሰዎች ለሟቹ ከቀብር ጋር የተያያዙ አንዳንድ ልማዶችና ሥነ ሥርዓቶች ካልተፈጸሙለት በስተቀር በሕይወት ያሉትን ሊጎዱ ወይም ሊጠቅሙ ይችላሉ ተብለው የሚታሰቡት የቀድሞ አባቶች መናፍስት ይቆጣሉ ብለው ያምናሉ። ይህ እምነት በቀብር ሥነ ሥርዓቶች ዝግጅትና ክንውን ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራል።

ሙታንን ለማስደሰት ተብለው የሚዘጋጁት የቀብር ሥነ ሥርዓቶች፣ በአብዛኛው በአስከሬኑ ፊት አምርሮ ማልቀስንና መጮህን እንዲሁም ከቀብር በኋላ የፈንጠዝያ ድግሶችን መደገስን ጨምሮ የተለያየ ዓይነት ስሜት የሚንጸባረቅባቸው ናቸው ለማለት ይቻላል። ከጥጋብ በላይ ይበላል፣ ከልክ በላይ ይጠጣል እንዲሁም ለቀብር ሥነ ሥርዓት ማጀቢያ በተዘጋጁ ጆሮ የሚያደነቁሩ ዘፈኖች ይጨፈራል። የቀብር ሥርዓቱ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ተደርጎ ስለሚታይ ድሃ የሆኑ ቤተሰቦች እንኳ “ተገቢውን የቀብር ሥነ ሥርዓት” ለማከናወን የሚያስችል በቂ ገንዘብ ለማግኘት ብርቱ ጥረት ያደርጋሉ፤ ይህም ችግር እንዲገጥማቸውና ዕዳ ውስጥ እንዲዘፈቁ ያደርጋቸዋል።

የይሖዋ ምሥክሮች ከዓመት እስከ ዓመት ቅዱስ ጽሑፋዊ ባልሆኑ የቀብር ልማዶች ላይ እንዲካፈሉ ፈተና ያጋጥማቸዋል። a ከእነዚህም መካከል አስከሬኑን መጠበቅ፣ የመጠጥ ቁርባን ማፍሰስ፣ የሞተውን ሰው ማናገር ወይም ጥያቄ መጠየቅ እንዲሁም የሞተውን ሰው መታሰቢያ ማክበርና የመሳሰሉት ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ ልማዶች ይገኙበታል። እነዚህ ሁሉ ልማዶች ከሞት በኋላ በሕይወት የምትቀጥል ነገር አለች በሚለው እምነት ላይ የተመሠረቱ ናቸው። እንደነዚህ ያሉት ለአምላክ ክብር የማይሰጡ ልማዶች “ርኵስ” የሆኑና “በሰዎች ልማድ” ላይ የተመሠረቱ ‘ከንቱ ማግባቢያዎች’ እንጂ በአምላክ ቃል ውስጥ በሚገኘው እውነት ላይ የተመሠረቱ አይደሉም።—ኢሳይያስ 52:11፤ ቆላስይስ 2:8

በሥነ ሥርዓቱ ላይ እንድትካፈል የሚደረግብህ ግፊት

በተለይ ለሙታን ትልቅ ክብር በሚሰጥበት አካባቢ የሚኖር ሰው ባሕላዊ የሆኑ ልማዶችን አለመፈጸሙ ተፈታታኝ እንደሚሆንበት የታወቀ ነው። የይሖዋ ምሥክሮች እነዚህን ልማዶች ባለመከተላቸው በጥርጣሬ ዓይን ይታያሉ ወይም ለማኅበረሰቡ ጸር እንደሆኑና ሙታንን እንደማያከብሩ ተደርገው ይታሰባሉ። አንዳንድ ክርስቲያኖች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እውነት ትክክለኛ ግንዛቤ ቢኖራቸውም እንኳን የሚመጣውን ነቀፌታና ተጽዕኖ በመፍራት ከአካባቢያቸው ሰዎች ጋር ተመሳስለው ለመኖር መርጠዋል። (1 ጴጥሮስ 3:14) ሌሎች ደግሞ እነዚህ ልማዶች ባሕላቸው ስለሆኑ ሙሉ በሙሉ ሊተዉአቸው እንደማይችሉ ተሰምቷቸዋል። እንዲሁም ባሕሉን ለመከተል ፈቃደኛ አለመሆን የአምላክ ሕዝቦች በኅብረተሰቡ ዘንድ እንዲጠሉ ያደርጋቸዋል ብለው የሚያስቡም አሉ።

እርግጥ ነው፣ ሳያስፈልግ ሌሎችን ማስቆጣት አንፈልግም። ነገር ግን ምንም ያህል ሌሎችን ላለማስቆጣት ብንጥር ለእውነት ለመቆም እስከቆረጥን ድረስ ከአምላክ የራቀው ዓለም እንደሚጠላን መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠነቅቀናል። (ዮሐንስ 15:18, 19፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:12፤ 1 ዮሐንስ 5:19) በመንፈሳዊ ጨለማ ውስጥ ካሉት ሰዎች የተለየን መሆን እንዳለብን ስለምናውቅ በአቋማችን ለመጽናት ፈቃደኞች መሆን ይገባናል። (ሚልክያስ 3:18፤ ገላትያ 6:12) ኢየሱስ፣ አምላክን የሚያሳዝን ነገር እንዲያደርግ ሰይጣን ያቀረበለትን ፈተና እንደተቋቋመ ሁሉ እኛም አምላክን የማያስደስቱ ነገሮች እንድናደርግ የሚደረግብንን ተጽዕኖ ማሸነፍ እንችላለን። (ማቴዎስ 4:3-7) እውነተኛ ክርስቲያኖች በሰዎች ፍርሃት ከመሸነፍ ይልቅ ከምንም በላይ የእውነት አምላክ የሆነውን ይሖዋን ለማስደሰትና ለማክበር ይጥራሉ። በሰዎች ተጽዕኖ ምክንያት መጽሐፍ ቅዱስ ለንጹሕ አምልኮ ያወጣውን የአቋም ደረጃ ከመጠበቅ ወደኋላ ባለማለት ይህን ተግባራዊ ያደርጋሉ።—ምሳሌ 29:25፤ የሐዋርያት ሥራ 5:29

ስለ ሙታን ትክክለኛ አመለካከት በመያዝ ይሖዋን ማክበር

የምንወደውን ሰው በሞት ስናጣ ስሜታችን መደቆሱና ማዘናችን ያለ ነገር ነው። (ዮሐንስ 11:33, 35) እንዲሁም በሞት ስላጣነው ወዳጃችን ያለንን ትዝታ ማውሳታችንና እንደምናከብረው የሚያሳይ የቀብር ሥነ ሥርዓት ማከናወናችን፣ ተስማሚና ተገቢ የሆነ የፍቅር መግለጫ ነው። ነገር ግን የይሖዋ ምሥክሮች የሚወዱት ሰው መሞቱ የፈጠረባቸውን ከባድ ሐዘን በሚገልጹበት ጊዜ አምላክን የማያስደስቱ ልማዶችን እንዳይከተሉ መጠንቀቅ አለባቸው። ይህ ጉዳይ ሙታን በጣም በሚፈሩበት አካባቢ ላደገ ሰው ሊከብድ ይችላል። በተለይ በጣም የምንቀርበው ሰው ሞቶ ስሜታችን በሚደቆስበት ጊዜ ሚዛናችንን መጠበቅ ሊከብደን ይችላል። የሆነ ሆኖ ‘የመጽናናት ሁሉ አምላክ’ የሆነው ይሖዋ ለታማኝ ክርስቲያኖች ብርታት ይሰጣቸዋል፤ የእምነት ወንድሞቻቸውም እንዲሁ ፍቅራዊ ድጋፍ ያደርጉላቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 1:3, 4) እውነተኛ ክርስቲያኖች በአምላክ ዝክር ውስጥ ያሉ የሞቱ ዘመዶቻቸው እንደገና ሕያው እንደሚሆኑ ጠንካራ እምነት አላቸው፤ ይህ እምነታቸው በትንሣኤ ተስፋ እውነተኝነት ላይ ጥርጣሬ በሚዘሩ ክርስቲያናዊ ያልሆኑ የቀብር ሥነ ሥርዓቶች ላይ ፈጽሞ እንዳይካፈሉ ያደርጋቸዋል።

ይሖዋ “ከጨለማ ወደ አስደናቂ ብርሃኑ” ስለጠራን ደስ አይለንም? (1 ጴጥሮስ 2:9) ልጅ ሲወለድ የሚገኘውን ደስታና በሞት ምክንያት የሚከተለውን ሐዘን ብንቀምስም በጎ የሆነውን ለማድረግ ያለን ጠንካራ ፍላጎትና ለይሖዋ አምላክ ያለን ጥልቅ ፍቅር ሁልጊዜ ‘እንደ ብርሃን ልጆች እንድንኖር’ ይርዳን። አምላክን በማያስደስቱ ክርስቲያናዊ ያልሆኑ ልማዶች ባለመካፈል ራሳችንን ከመንፈሳዊ ብክለት እንጠብቅ።—ኤፌሶን 5:8

[የግርጌ ማስታወሻ]

a የሙታን መናፍስት—ሊረዱህ ወይም ሊጎዱህ ይችላሉን? ደግሞስ በእርግጥ አሉን? እና ዘ ሮድ ቱ ኤቨርላስቲንግ ላይፍ—ሀቭ ዩ ፋውንድ ኢት? የሚል ርዕስ ያላቸውን በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁ ብሮሹሮች ተመልከት።