በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ በጥብቅ ተከተል

ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ በጥብቅ ተከተል

ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ በጥብቅ ተከተል

“እኔ እንዳደረግሁላችሁ እናንተም እንደዚሁ እንድታደርጉ ምሳሌ ትቼላችኋለሁ።”—ዮሐንስ 13:15

1. ክርስቲያኖች ኢየሱስን ምሳሌያቸው አድርገው የሚመለከቱት ለምንድን ነው?

 በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ኃጢአት ሳይሠራ ያለፈው አንድ ሰው ብቻ ነው። እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ከኢየሱስ በስተቀር ‘ኀጢአት የማይሠራ ሰው የለም።’ (1 ነገሥት 8:46፤ ሮሜ 3:23) በዚህም ምክንያት እውነተኛ ክርስቲያኖች ኢየሱስን ሊኮርጁት የሚገባ ፍጹም ምሳሌ አድርገው ይመለከቱታል። ኢየሱስ ራሱ ኒሳን 14, 33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ከመሞቱ ትንሽ ቀደም ብሎ “እኔ እንዳደረግሁላችሁ እናንተም እንደዚሁ እንድታደርጉ ምሳሌ ትቼላችኋለሁ” በማለት ተከታዮቹ ምሳሌውን እንዲከተሉ ነግሯቸው ነበር። (ዮሐንስ 13:15) ለምድራዊ ሕይወቱ የመጨረሻ በሆነችው በዚያች ምሽት ኢየሱስ ክርስቲያኖች እርሱን ሊመስሉ የሚችሉባቸውን የተለያዩ መንገዶች ዘርዝሮላቸዋል። በዚህ ርዕስ ውስጥ ከእነዚህ መንገዶች መካከል አንዳንዶቹን እንመረምራለን።

የትሕትና አስፈላጊነት

2, 3. በትሕትና ረገድ ኢየሱስ ፍጹም ምሳሌ የተወው እንዴት ነው?

2 ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ እርሱ የተወውን ምሳሌ እንዲከተሉ ሲያበረታታቸው በተለይ ትሕትናውን እንዲኮርጁ መናገሩ ነበር። ተከታዮቹ ትሑት እንዲሆኑ በተደጋጋሚ ምክር ሰጥቷቸው የነበረ ሲሆን ኒሳን 14 ምሽት ላይ ደግሞ የሐዋርያቱን እግር በማጠብ እርሱም ራሱ ትሑት መሆኑን በተግባር አሳይቷቸዋል። ከዚያም “እኔ ጌታችሁና መምህራችሁ ሆኜ ሳለሁ እግራችሁን ካጠብሁ፣ እናንተም እንደዚሁ እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ልትተጣጠቡ ይገባችኋል” አላቸው። (ዮሐንስ 13:14) ሐዋርያቱ እርሱ የተወውን ምሳሌ እንዲከተሉ የነገራቸው ከዚህ በኋላ ነበር። በእርግጥም ኢየሱስ በትሕትና ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቷል!

3 ኢየሱስ ሰው ሆኖ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት “በባሕርዩ አምላክ ሆኖ” ይኖር እንደነበር ሐዋርያው ጳውሎስ ተናግሯል። የሆነ ሆኖ ራሱን ባዶ በማድረግ ተራ ሰው ሆነ። ከዚህም በላይ “ራሱን ዝቅ አደረገ፤ እስከ ሞት፣ ያውም በመስቀል ላይ እስከ መሞት ድረስ ታዛዥ ሆነ።” (ፊልጵስዩስ 2:6-8) እስቲ አስበው በጽንፈ ዓለም ውስጥ ሁለተኛውን ከፍተኛ ሥልጣን የያዘው ኢየሱስ ከመላእክት ያነሰ ለመሆን፣ የሌሎች እርዳታ የሚያስፈልገው ሕፃን ሆኖ ለመወለድ፣ ፍጹም ባልሆኑ ወላጆች እጅ ለማደግና ለእነርሱ ለመታዘዝ በመጨረሻም እንደ ወንጀለኛ ተቆጥሮ ለመሞት ፈቃደኛ ሆኗል። (ቆላስይስ 1:15, 16፤ ዕብራውያን 2:6, 7) በእርግጥም የላቀ ትሕትና አሳይቷል! ይሁንና እንዲህ ያለውን “አስተሳሰብ” በመኮረጅ ‘ትሕትናን’ ማዳበር ይቻላል? (ፊልጵስዩስ 2:3-5) አዎን ይቻላል፤ ሆኖም ቀላል አይደለም።

4. ሰዎችን እንዲኮሩ የሚያደርጓቸው አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው? ኩራት አደገኛ የሆነውስ ለምንድን ነው?

4 ኩራት የትሕትና ተቃራኒ ነው። (ምሳሌ 6:16-19) ሰይጣንን ለውድቀት የዳረገው ይህ ባሕርይ ነበር። (1 ጢሞቴዎስ 3:6) ኩራት በሰዎች ልብ ውስጥ በቀላሉ ሥር ሊሰድ ይችላል፤ አንድ ጊዜ ልብ ውስጥ ከገባ ደግሞ ነቅሎ ማውጣት በጣም አስቸጋሪ ነው። ሰዎች በአገራቸው፣ በዘራቸው፣ በሀብታቸው፣ በእውቀታቸው፣ ባገኙት ስኬት፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ ባላቸው ሥልጣን፣ በመልካቸው፣ በስፖርት ችሎታቸውና በሌሎች በርካታ ነገሮች ይኮራሉ። ሆኖም ይሖዋ ከእነዚህ ነገሮች መካከል ለአንዱም ክብደት አይሰጥም። (1 ቆሮንቶስ 4:7) እነዚህ ነገሮች አሉን ብለን የምንኮራ ከሆነ ከእርሱ ጋር ያለን ዝምድና ይበላሽብናል። “እግዚአብሔር በከፍታ ስፍራ ቢሆንም፣ ዝቅ ያለውን ይመለከተዋል፤ ትዕቢተኛውን ከሩቅ ያውቀዋል።”—መዝሙር 138:6፤ ምሳሌ 8:13

ለወንድሞቻችን ትሕትና ማሳየት

5. ሽማግሌዎች ትሑት መሆናቸው በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

5 በይሖዋ አገልግሎት ያበረከትነው አስተዋጽዖና ያገኘነው ውጤት አልፎ ተርፎም በጉባኤ ውስጥ ያሉን ኃላፊነቶች እንድንኮራ ሊያደርጉን አይገባም። (1 ዜና መዋዕል 29:14፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:17, 18) እንዲያውም ኃላፊነታችን እየጨመረ በመጣ መጠን የዚያኑ ያህል ትሑት መሆን ይኖርብናል። ሐዋርያው ጴጥሮስ ሽማግሌዎች ‘በዐደራ ለተሰጣቸው መንጋ መልካም ምሳሌ እንዲሆኑ እንጂ በላያቸው እንዳይሠለጥኑ’ በጥብቅ አሳስቧቸዋል። (1 ጴጥሮስ 5:3) ሽማግሌዎች የሚሾሙት ጌታና አዛዥ እንዲሆኑ ሳይሆን ጉባኤውን እንዲያገለግሉና ለመንጋው ምሳሌ እንዲሆኑ ነው።—ሉቃስ 22:24-26፤ 2 ቆሮንቶስ 1:24

6. ክርስቲያኖች ትሕትናን እንዲያንጸባርቁ የሚጠበቅባቸው በየትኞቹ የሕይወታቸው ዘርፎች ነው?

6 ትሕትና እንዲያሳዩ የሚጠበቅባቸው ሽማግሌዎች ብቻ አይደሉም። ጴጥሮስ አንዳንድ ጎልማሶች፣ በዕድሜ ከገፉት አንጻር ሲታዩ ፈጣን አእምሮና ብርቱ ሰውነት ያላቸው በመሆኑ ምክንያት ኩራት ስለተሰማቸው ሊሆን ይችላል “ሁላችሁም እርስ በርስ በመከባበር ትሕትናን ልበሱ፤ ምክንያቱም፣ ‘እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል’” በማለት ጽፎላቸዋል። (1 ጴጥሮስ 5:5) አዎን፣ ሁላችንም የክርስቶስን ዓይነት ትሕትና ማንጸባረቃችን በጣም አስፈላጊ ነው። ግዴለሽነት ወይም ተቃውሞ በሚበዛበት አካባቢ ምሥራቹን መስበክ በእርግጥ ትሕትና ይጠይቃል። የሚሰጠንን ምክር ለመቀበል ወይም በአገልግሎት የምናደርገውን ተሳትፎ ከፍ ለማድረግ ስንል ቀላል ሕይወት መምራት ትሕትና ይጠይቃል። በተጨማሪም የሐሰት ወሬ ሲናፈስብን፣ በሕግ ስም ተጽዕኖ ሲደረግብን ወይም ከባድ ስደት ሲደርስብን ትሕትና አልፎ ተርፎም ድፍረትና እምነት ማሳየት ያስፈልገናል።—1 ጴጥሮስ 5:6

7, 8. ትሕትና ማዳበር የምንችልባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው?

7 አንድ ሰው ኩራትን ማሸነፍና ‘ሌሎች ከእርሱ እንደሚሻሉ በትሕትና ማሰብ’ የሚችለው እንዴት ነው? (ፊልጵስዩስ 2:3) ራሱን በይሖዋ ዓይን በመመልከት ነው። ኢየሱስ “እናንተም የታዘዛችሁትን ሁሉ ባደረጋችሁ ጊዜ፣ ‘ከቁጥር የማንገባ አገልጋዮች ነን፤ ልናደርገው የሚገባንን ተግባር ፈጽመናል’ በሉ” በማለት አንድ ሰው ስለ ራሱ ሊኖረው የሚገባውን ትክክለኛ አመለካከት ገልጿል። (ሉቃስ 17:10) ምንም ነገር ብናደርግ ኢየሱስ ካደረገው ጋር ሊወዳደር እንደማይችል አስታውስ። ሆኖም ኢየሱስ ትሑት ሰው ነበር።

8 ከዚህም በላይ፣ ስለ ራሳችን ተገቢውን አመለካከት እንድናዳብር እንዲረዳን ይሖዋን መለመን እንችላለን። እንደ መዝሙራዊው ሁሉ እኛም “በትእዛዛትህ አምናለሁና፣ በጎ ማስተዋልንና ዕውቀትን አስተምረኝ” ብለን መጸለይ እንችላለን። (መዝሙር 119:66) ይሖዋ ስለ ራሳችን ጤናማና ሚዛናዊ አመለካከት እንድናዳብር የሚረዳን ከመሆኑም በላይ የትሕትና መንፈስ በማሳየታችንም ይባርከናል። (ምሳሌ 18:12) ኢየሱስ “ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ይዋረዳል፣ ራሱን የሚያዋርድ ግን ይከበራል” በማለት ተናግሯል።—ማቴዎስ 23:12

መልካምና ክፉን በሚመለከት ሊኖረን የሚገባው ትክክለኛ አመለካከት

9. ኢየሱስ መልካምና ክፉ ለሆኑ ነገሮች ምን አመለካከት ነበረው?

9 ኢየሱስ ፍጽምና በጎደላቸው ሰዎች መካከል ለ33 ዓመታት የኖረ ቢሆንም እንኳ “ምንም ኀጢአት አልሠራም።” (ዕብራውያን 4:15) እንዲያውም መዝሙራዊው፣ መሲሑን በሚመለከት ትንቢት ሲናገር “ጽድቅን ወደድህ፤ ዐመፃን ጠላህ” ብሏል። (መዝሙር 45:7፤ ዕብራውያን 1:9) ክርስቲያኖች በዚህ ረገድም የኢየሱስን ምሳሌ ለመኮረጅ ይጣጣራሉ። መልካሙን ከክፉው ለይተው ማወቅ ብቻ ሳይሆን ክፉውን ይጠላሉ፤ መልካሙን ይወድዳሉ። (አሞጽ 5:15) እንዲህ ማድረጋቸው በውርስ ያገኙትን የኃጢአት ዝንባሌ እንዲዋጉ ይረዳቸዋል።—ዘፍጥረት 8:21፤ ሮሜ 7:21-25

10. “ክፉ” ነገሮችን መሥራት ልማድ ከሆነብን ምን ዓይነት ዝንባሌ እያሳየን ነው?

10 ኢየሱስ ፈሪሳዊ ለሆነው ለኒቆዲሞስ እንዲህ ብሎት ነበር:- “ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላል፤ አድራጎቱም እንዳይገለጥበት ወደ ብርሃን አይመጣም። በእውነት የሚመላለስ ግን ሥራው በእግዚአብሔር የተሠራ መሆኑ በግልጽ ይታይ ዘንድ ወደ ብርሃን ይመጣል።” (ዮሐንስ 3:20, 21) ዮሐንስ ኢየሱስን “ለሰው ሁሉ ብርሃን ሰጪ የሆነው እውነተኛው ብርሃን” ብሎ እንደጠራው ልብ በል። (ዮሐንስ 1:9, 10) በሌላ በኩል ኢየሱስ “ክፉ” ነገሮች ማለትም ከሥነ ምግባር ውጪ የሆኑና አምላክ የሚጠላቸውን ነገሮች የምናደርግ ከሆነ ብርሃንን እንደምንጠላ ተናግሯል። ይሁንና ኢየሱስንም ሆነ እርሱ ያወጣውን መሥፈርት መጥላት የማይታሰብ ነገር ነው። ኃጢአት መሥራት ልማድ የሆነባቸው ንስሐ የማይገቡ ሰዎች ግን እያደረጉ ያሉት ይህንኑ ነው። እነርሱ ኢየሱስንም ሆነ መሥፈርቶቹን እንደሚጠሉ አያስቡ ይሆናል። ኢየሱስ ግን አድራጎታቸውን ከዚያ ለይቶ አያየውም።

መልካምና ክፉን በሚመለከት የኢየሱስ ዓይነት አመለካከት ማዳበር

11. ኢየሱስ መልካሙንና ክፉውን በሚመለከት ያለውን አመለካከት ለመኮረጅ የምንፈልግ ከሆነ ምን ማድረጋችን ወሳኝ ነው?

11 መልካምና ክፉ የሆኑ ነገሮችን በሚመለከት ይሖዋ ያለው ዓይነት አመለካከት ለማዳበር ትክክለኛ ግንዛቤ ማግኘት ያስፈልገናል። እንዲህ ያለውን ግንዛቤ ማግኘት የምንችለው የአምላክ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ብቻ ነው። ቃሉን በምናጠናበት ጊዜ ልክ እንደ መዝሙራዊው “እግዚአብሔር ሆይ፤ አካሄድህን እንዳውቅ አድርገኝ፤ መንገድህንም አስተምረኝ” ብለን መጸለይ ይኖርብናል። (መዝሙር 25:4) ሆኖም ሰይጣን አታላይ መሆኑን ፈጽሞ አትዘንጋ። (2 ቆሮንቶስ 11:14) ሰይጣን አንድ ክርስቲያን ካልተጠነቀቀ ክፉ የሆነው ነገር ጥሩ መስሎ እንዲታየው ሊያደርግ ይችላል። በመሆኑም በተማርናቸው ነገሮች ላይ በጥልቀት ማሰላሰልና “ታማኝና ልባም ባሪያ” የሚሰጠንን ምክር በጥብቅ መከተል ይኖርብናል። (ማቴዎስ 24:45-47 የ1954 ትርጉም) ማጥናታችን፣ መጸለያችንና በተማርናቸው ነገሮች ላይ ማሰላሰላችን እንድንጎለምስ ብሎም ‘መልካሙን ከክፉው ለመለየት ራሳቸውን ያስለመዱ’ ሰዎች የደረሱበት ደረጃ ላይ እንድንደርስ ይረዳናል። (ዕብራውያን 5:14) በዚህ መንገድ ክፉውን መጥላትና መልካም የሆነውን መውደድ እንችላለን።

12. ዓመጽን የማድረግ ልማድ እንዳይጠናወተን የትኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ይረዳናል?

12 ክፉውን የምንጠላ ከሆነ በውስጣችን መጥፎ የሆኑ ነገሮችን የመሥራት ፍላጎት አያድርብንም። ሐዋርያው ዮሐንስ ኢየሱስ ከሞተ ከበርካታ ዓመታት በኋላ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ዓለምን ወይም በዓለም ያለውን ማናቸውንም ነገር አትውደዱ፤ ማንም ዓለምን ቢወድ፣ የአብ ፍቅር በእርሱ ዘንድ የለም፤ ምክንያቱም በዓለም ያለው ሁሉ:- የሥጋ ምኞት፣ የዐይን አምሮትና የኑሮ ትምክሕት ከዓለም እንጂ ከአብ የሚመጣ አይደለም።”—1 ዮሐንስ 2:15, 16

13, 14. (ሀ) ክርስቲያኖች በዓለም ያሉ ነገሮችን መውደዳቸው አደገኛ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) በዓለም ያሉ ነገሮችን ከመውደድ መራቅ የምንችለው እንዴት ነው?

13 አንዳንዶች በዓለም ላይ ያሉ ነገሮች ሁሉ መጥፎ ናቸው ማለት አይቻልም ብለው ያስቡ ይሆናል። ይህ እውነት ቢሆንም እንኳ ዓለምም ሆነ ዓለም ማራኪ አስመስሎ የሚያቀርባቸው ነገሮች ከይሖዋ አገልግሎት ትኩረታችንን በቀላሉ ሊሰርቁብን ይችላሉ። ዓለም ወደ አምላክ እንድንቀርብ እኛን ለመርዳት ብሎ የሚያዘጋጀው ነገር የለም። በመሆኑም በራሳቸው ምንም ስሕተት የሌለባቸው ነገሮች ቢሆኑም እንኳ በዓለም ያሉ ነገሮችን መውደድ ከጀመርን አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ገብተናል ማለት ነው። (1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10) ከዚህም በላይ በዓለም ያለው አብዛኛው ነገር መጥፎ ከመሆኑም ሌላ አቋማችንን ሊያበላሽብን ይችላል። ዓመጽ፣ ፍቅረ ነዋይ ወይም የጾታ ብልግና የሚንጸባረቅባቸውን ፊልሞችና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች የምንመለከት ከሆነ እነዚህን ነገሮች ልንቀበላቸው ብሎም ተመሳሳይ ነገር ለማድረግ ልንፈተን እንችላለን። የኑሮ ደረጃቸውን ለማሻሻል ወይም የንግድ እንቅስቃሴያቸውን ለማስፋት ከሚሯሯጡ ሰዎች ጋር የምንወዳጅ ከሆነ እኛም ለእነዚህ ነገሮች ከፍተኛ ትኩረት መስጠት ልንጀምር እንችላለን።—ማቴዎስ 6:24፤ 1 ቆሮንቶስ 15:33

14 በሌላ በኩል በይሖዋ ቃል ደስ የምንሰኝ ከሆነ “የሥጋ ምኞት፣ የዐይን አምሮትና የኑሮ ትምክሕት” ወጥመድ አይሆኑብንም። በተጨማሪም የአምላክን መንግሥት ከሚያስቀድሙ ሰዎች ጋር የምንወዳጅ ከሆነ እኛም እንደ እነርሱ እንሆናለን፤ ይኸውም የሚወዱትን እንወዳለን የሚጠሉትን ደግሞ እንጠላለን።—መዝሙር 15:4፤ ምሳሌ 13:20

15. ከኢየሱስ ምሳሌ እንደምንረዳው ጽድቅን መውደድና ዓመጻን መጥላት የብርታት ምንጭ የሚሆንልን እንዴት ነው?

15 ኢየሱስ ዓመጻን መጥላቱና ጽድቅን መውደዱ ‘በፊቱ ያለውን ደስታ’ ትኩር ብሎ እንዲመለከት ረድቶታል። (ዕብራውያን 12:2) እኛም እንደ እርሱ ማድረግ እንችላለን። ‘ዓለምና ምኞቱ እንደሚያልፉ’ እናውቃለን። ይህ ዓለም የሚያስገኘው ደስታ ጊዜያዊ ነው። “የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚፈጽም ግን ለዘላለም ይኖራል።” (1 ዮሐንስ 2:17) ኢየሱስ የአምላክን ፈቃድ ስለፈጸመ ሰዎች የዘላለም ሕይወት የሚያገኙበትን አጋጣሚ ከፍቶላቸዋል። (1 ዮሐንስ 5:13) እንግዲያው ሁላችንም የእርሱን ምሳሌ በመኮረጅ ጽኑ አቋም ጠባቂነቱ ከሚያስገኘው ጥቅም ተቋዳሽ እንሁን።

ስደትን ተቋቁሞ መኖር

16. ኢየሱስ ተከታዮቹ እርስ በርሳቸው እንዲዋደዱ በጥብቅ ያሳሰባቸው ለምን ነበር?

16 ኢየሱስ “ትእዛዜ ይህች ናት፤ እኔ እንደ ወደድኋችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ” ብሎ በተናገረ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ምሳሌውን ሊኮርጁ የሚችሉበትን ሌላም መንገድ ጠቁሟል። (ዮሐንስ 15:12, 13, 17) ክርስቲያኖች የእምነት ወንድሞቻቸውን የሚወዱበት በርካታ ምክንያቶች አሏቸው። በዚህ ጊዜ ግን ኢየሱስ ይህን ትእዛዝ የሰጣቸው ዓለም የጥላቻ ዒላማ እንደሚያደርጋቸው በማሰብ ነበር። እንዲህ አላቸው:- “ዓለም ቢጠላችሁ፣ ከእናንተ በፊት እኔን እንደ ጠላኝ ዕወቁ። . . . ‘አገልጋይ ከጌታው አይበልጥም’ . . . እኔን አሳደውኝ ከሆነ፣ እናንተንም ያሳድዷችኋል።” (ዮሐንስ 15:18, 20) አዎን፣ ክርስቲያኖች ስደትን በመቀበል ረገድ እንኳ ኢየሱስን ይመስላሉ። የሚያጋጥማቸውን ጥላቻ መቋቋም እንዲችሉ ፍቅር የሰፈነበት የጠበቀ አንድነት መፍጠር ይኖርባቸዋል።

17. ዓለም እውነተኛ ክርስቲያኖችን የሚጠላው ለምንድን ነው?

17 ይሁንና ዓለም ክርስቲያኖችን የሚጠላው ለምንድን ነው? እንደ ኢየሱስ እነርሱም “ከዓለም ባለመሆናቸው” ነው። (ዮሐንስ 17:14, 16) ከወታደራዊና ከፖለቲካዊ ጉዳዮች ፍጹም ገለልተኞች ናቸው፤ እንዲሁም የሕይወትን ቅድስና በማክበርና ከፍተኛ የሥነ ምግባር ሕጎችን በመጠበቅ ረገድ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ይከተላሉ። (የሐዋርያት ሥራ 15:28, 29፤ 1 ቆሮንቶስ 6:9-11) በሕይወታቸው ውስጥ ዋነኛው ግባቸው በመንፈሳዊ እንጂ በቁሳዊ ነገሮች ላይ ያተኮረ አይደለም። የሚኖሩት በዓለም ውስጥ ቢሆንም እንኳ ጳውሎስ እንዳለው ዓለምን ሙሉ በሙሉ አይጠቀሙበትም። (1 ቆሮንቶስ 7:31) እውነት ነው፣ አንዳንዶች የይሖዋ ምሥክሮች ለሚከተሉት ከፍተኛ የሥነ ምግባር አቋም አድናቆት እንዳላቸው ገልጸዋል። ሆኖም የይሖዋ ምሥክሮች የሌሎችን አድናቆት ለማትረፍ ወይም ተቀባይነት ለማግኘት ብለው አቋማቸውን አያላሉም። ከዚህም የተነሳ አብዛኞቹ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች አቋም ግራ ያጋባቸዋል፤ ብዙዎች ደግሞ ይጠሏቸዋል።

18, 19. ክርስቲያኖች ተቃውሞና ስደት ሲያጋጥማቸው የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል ምን ያደርጋሉ?

18 የኢየሱስ ሐዋርያት ጌታቸው በተያዘና በተገደለ ጊዜ ዓለም ምን ያህል ከባድ ጥላቻ እንዳለው ተመልክተዋል። እንዲሁም ኢየሱስ የደረሰበትን ጥላቻ እንዴት እንዳሳለፈው አይተዋል። ኢየሱስን የሚቃወሙት የሃይማኖት ሰዎች እርሱን ለመያዝ ወደ ጌቴሴማኒ የአትክልት ቦታ መጡ። በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ በሰይፍ ሊያስጥለው ሞክሮ ነበር። ኢየሱስ ግን ጴጥሮስን “በል ሰይፍህን ወደ ሰገባው መልስ፤ ሰይፍን የሚመዝዙ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉ” አለው። (ማቴዎስ 26:52፤ ሉቃስ 22:50, 51) በጥንት ጊዜያት እስራኤላውያን ጠላቶቻቸውን በሰይፍ ተዋግተዋል። አሁን ግን ሁኔታዎች ተቀይረዋል። የአምላክ መንግሥት “ከዚህ ዓለም” ካለመሆኑም ሌላ ጥበቃ የሚያስፈልገው ብሔራዊ ድንበር የለውም። (ዮሐንስ 18:36) ብዙም ሳይቆይ ጴጥሮስ የአንድ መንፈሳዊ ብሔር አባል የሚሆን ሲሆን የዚህ ብሔር አባላት አገራቸው በሰማይ ነው። (ገላትያ 6:16፤ ፊልጵስዩስ 3:20, 21) በመሆኑም የኢየሱስ ተከታዮች ከዚያን ጊዜ አንስቶ የሚደርስባቸውን ጥላቻና ስደት ልክ እንደ ኢየሱስ ያለ አንዳች ፍርሃት ሆኖም በሰላማዊ መንገድ ይጋፈጣሉ። በዚህ አቋማቸው ሳቢያ የሚያጋጥማቸው ፈተና የሚኖረውን የመጨረሻ ውጤት ለይሖዋ በመተው ለመጽናት የሚያስፈልጋቸውን ብርታት እንዲሰጣቸው በእርሱ ይታመናሉ።—ሉቃስ 22:42

19 ጴጥሮስ ከዓመታት በኋላ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ክርስቶስ ስለ እናንተ መከራን የተቀበለው የእርሱን ፈለግ እንድትከተሉ ምሳሌን ሊተውላችሁ ነው። . . . ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም፤ መከራ ሲደርስበት አልዛተም፤ ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ።” (1 ጴጥሮስ 2:21-23) ኢየሱስ አስቀድሞ እንዳስጠነቀቀው ክርስቲያኖች ባለፉት ዘመናት ሁሉ መራራ ስደት አጋጥሟቸዋል። በመጀመሪያው መቶ ዘመንም ይሁን በዘመናችን ክርስቲያኖች የኢየሱስን ምሳሌ የተከተሉ ሲሆን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ታማኝነታቸውን እንደሚጠብቁ የሚያሳይ ድንቅ ታሪክ አስመዝግበዋል። (ራእይ 2:9, 10) ሁላችንም እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥመን በግለሰብ ደረጃ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ታማኝነታችንን እንጠብቅ።—2 ጢሞቴዎስ 3:12

“ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ልበሱት”

20-22. ክርስቲያኖች ‘ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን የሚለብሱት’ እንዴት ነው?

20 ጳውሎስ ሮም ለሚገኘው ጉባኤ “ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ልበሱት፤ ምኞቱንም ይፈጽም ዘንድ ለሥጋ በሐሳባችሁ አትመቻቹለት” ሲል ጽፎ ነበር። (ሮሜ 13:14) ክርስቲያኖች በምሳሌያዊ አነጋገር ኢየሱስን እንደ ልብስ ይለብሱታል። ፍጽምና የሚጎድላቸው ሰዎች ቢሆኑም እንኳ ጌታቸውን በሚገባ እስኪመስሉ ድረስ ባሕርዩንና ተግባሩን ለመኮረጅ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ።—1 ተሰሎንቄ 1:6

21 ስለ ጌታ ሕይወት ጠንቅቀን የምናውቅና እርሱ በኖረበት መንገድ ለመኖር ጥረት የምናደርግ ከሆነ ‘ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን በመልበስ’ ረገድ ሊሳካልን ይችላል። የትሕትና ባሕርይውን፣ ለጽድቅ የነበረውን ፍቅር፣ ለዓመጽ የነበረውን ጥላቻ፣ ለወንድሞቹ የነበረውን ፍቅር፣ ከዓለም የተለየ በመሆን የነበረውን አቋምና መከራ ሲደርስበት ያሳየውን ጽናት እንኮርጃለን። ‘ምኞቱን ይፈጽም ዘንድ ለሥጋችን አንመቻችለትም፤’ ይህም ሲባል በሕይወታችን ውስጥ ዋነኛው ግባችን ዓለማዊ ነገሮችን ማሳደድ ወይም ሥጋዊ ምኞቶችን ማርካት አይሆንም ማለት ነው። ከዚህ ይልቅ ውሳኔ ስናደርግ ወይም ለደረሰብን ችግር መፍትሔ ስንፈልግ ‘ኢየሱስ ቢሆን ኖሮ ምን ያደርግ ነበር? እኔስ ምን እንዳደርግ ይጠብቅብኛል?’ ብለን ራሳችንን እንጠይቃለን።

22 በመጨረሻ፣ ‘የምሥራቹን በመስበኩ’ ሥራ ራሳችንን በማስጠመድ የኢየሱስን ምሳሌ እንኮርጃለን። (ማቴዎስ 4:23፤ 1 ቆሮንቶስ 15:58) ክርስቲያኖች በዚህ ረገድም ቢሆን ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ የሚኮርጁ ሲሆን የሚቀጥለው ርዕስ በዚህ ላይ ያተኮረ ይሆናል።

ልታብራራ ትችላለህ?

• አንድ ክርስቲያን ትሑት መሆኑ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

• መልካሙንና ክፉውን በሚመለከት ተገቢውን አመለካከት ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው?

• ክርስቲያኖች ለሚደርስባቸው ተቃውሞና ስደት በሚሰጡት ምላሽ ረገድ የኢየሱስን ምሳሌ መኮረጅ የሚችሉት እንዴት ነው?

• ‘ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን መልበስ’ የሚቻለው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ በትሕትና ረገድ ፍጹም ምሳሌ ትቷል

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የስብከቱን ሥራ ጨምሮ የክርስትና ሕይወት በአጠቃላይ ትሕትና ይጠይቃል

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሰይጣን አንድን መጥፎ መዝናኛ ለአንድ ክርስቲያን ጥሩ አስመስሎ ሊያቀርብለት ይችላል

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወንድሞቻችን ለእኛ ያላቸው ፍቅር በተቃውሞ ጊዜ ያጠነክረናል