የተሟላ ምሥክርነት ለመስጠት ሠልጥነዋል
የተሟላ ምሥክርነት ለመስጠት ሠልጥነዋል
“በኢየሩሳሌም፣ በይሁዳና በሰማርያ ሁሉ፣ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ።”—የሐዋርያት ሥራ 1:8
1, 2. ጴጥሮስ ምን ተልእኮ ተሰጥቶታል? ሰጪውስ ማን ነበር?
‘የናዝሬቱ ኢየሱስ ለሕዝቡ እንድንሰብክና በሕያዋንና በሙታንም ላይ እንዲፈርድ እግዚአብሔር የሾመው እርሱ መሆኑን የተሟላ ምሥክርነት እንድንሰጥ እርሱ ራሱ አዘዘን።’ (የሐዋርያት ሥራ 10:38, 42) ሐዋርያው ጴጥሮስ ወንጌላዊ ሆኖ እንዲያገለግል ኢየሱስ የሰጠውን ተልእኮ በሚመለከት ለቆርኔሌዎስና ለቤተሰቡ የገለጸው እንዲህ በማለት ነበር።
2 ይሁንና ኢየሱስ ይህን ተልእኮ የሰጠው መቼ ነበር? ጴጥሮስ ይህን ያለው ኢየሱስ ከሞት ተነስቶ ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት የተናገረውን አስታውሶ መሆን አለበት። በዚያ ጊዜ ኢየሱስ ታማኝ ደቀ መዛሙርቱን “በኢየሩሳሌም፣ በይሁዳና በሰማርያ ሁሉ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ” ብሏቸው ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 1:8) ይሁን እንጂ፣ ጴጥሮስ ከዚያ ቀደም ብሎም የኢየሱስ ደቀ መዝሙር እንደመሆኑ መጠን በጌታው ላይ ስላለው እምነት ለሌሎች መናገር እንዳለበት ተገንዝቦ ነበር።
ሦስት ዓመት የፈጀ ሥልጠና
3. ኢየሱስ ምን ተአምር ፈጸመ? ለጴጥሮስና ለእንድርያስስ ምን ግብዣ አቀረበላቸው?
3 ኢየሱስ በ29 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ከተጠመቀ ከተወሰኑ ወራት በኋላ ጴጥሮስና ወንድሙ እንድርያስ ዓሣ ወደሚያጠምዱበት ወደ ገሊላ ወንዝ አካባቢ ሄዶ ሰበከ። ጴጥሮስና እንድርያስ ሌሊቱን ሙሉ ዓሣ ለማጥመድ ሲደክሙ ቢያድሩም ምንም አልተሳካላቸውም ነበር። ይሁንና ኢየሱስ “ወደ ጥልቁ ውሃ ፈቀቅ በልና ዓሣ ለመያዝ መረባችሁን ጣሉ” አላቸው። ኢየሱስ እንዳላቸው ሲያደርጉ “እጅግ ብዙ ዓሣ ያዙ፤ መረባቸውም ይበጣጠስ ጀመር።” ጴጥሮስ ይህን ተአምር ሲመለከት በጣም ፈራ፤ ኢየሱስ ግን “አትፍራ፤ ከእንግዲህ ሰውን የምታጠምድ ትሆናለህ” በማለት አረጋጋው።—ሉቃስ 5:4-10
4. (ሀ) ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ለአገልግሎት ያዘጋጃቸው እንዴት ነበር? (ለ) የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የሚያከናውኑት አገልግሎት እርሱ ካከናወነው ጋር ሲወዳደር ምን ይመስላል?
4 ወዲያውኑ ጴጥሮስና እንድርያስ እንዲሁም የዘብዴዎስ ልጆች የሆኑት ያዕቆብና ዮሐንስ ዓሣ ማጥመጃ ጀልባቸውን ትተው ኢየሱስን ተከተሉት። ለሦስት ዓመት ገደማ፣ ኢየሱስ ለስብከት ወደሚሄድባቸው ቦታዎች አብረውት በመጓዝ የወንጌላዊነት ሥልጠና አግኝተዋል። (ማቴዎስ 10:7፤ ማርቆስ 1:16, 18, 20, 38፤ ሉቃስ 4:43፤ 10:9) በሥልጠናው መገባደጃ ላይ ይኸውም ኒሳን 14, 33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ኢየሱስ “በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ሥራ ይሠራል፤ እንዲያውም እኔ ወደ አብ ስለምሄድ፣ ከእነዚህም የሚበልጥ ያደርጋል” አላቸው። (ዮሐንስ 14:12) የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ልክ እንደ እርሱ የተሟላ ምሥክርነት ይሰጣሉ፤ ሆኖም ይህን የሚያደርጉት እርሱ ካደረገው በበለጠ ስፋት ይሆናል። ብዙም ሳይቆይ እንደተገነዘቡት እነርሱም ሆኑ ወደፊት ደቀ መዛሙርት የሚሆኑት ሰዎች እስከ “ዓለም ፍጻሜ” ድረስ ‘ለሕዝቦች ሁሉ’ ምሥክርነት መስጠት ይኖርባቸዋል።—ማቴዎስ 28:19, 20
5. ኢየሱስ ለተከታዮቹ ከሰጠው ሥልጠና ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?
5 የምንኖረው ‘በዓለም መጨረሻ’ ዘመን ላይ ነው። (ማቴዎስ 24:3) በመሆኑም እንደ መጀመሪያዎቹ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ከኢየሱስ ጋር መጓዝና ለሰዎች ሲሰብክ መመልከት አንችልም። ያም ሆኖ ግን እንዴት እንደሰበከና ለተከታዮቹ ምን መመሪያዎችን እንደሰጠ የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ በማንበብ እርሱ ከሰጠው ሥልጠና ጥቅም ማግኘት እንችላለን። (ሉቃስ 10:1-11) በተጨማሪም፣ በዚህ ርዕስ ውስጥ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ በተግባር ያሳያቸው በጣም አስፈላጊ የሆነ ነገር ይኸውም ለስብከቱ ሥራ ሊኖረን ስለሚገባው ትክክለኛ አመለካከት ይብራራል።
ለሰዎች አሳቢነት ማሳየት
6, 7. ኢየሱስ አገልግሎቱን ውጤታማ ያደረገለት የትኛው ባሕርይው ነው? እኛስ በዚህ ረገድ ልንኮርጀው የምንችለው እንዴት ነው?
6 ኢየሱስ እንዲህ ያለ ውጤታማ ምሥክርነት እንዲሰጥ ያስቻለው ምንድን ነው? አንደኛው ነገር ለሰዎች ከልብ ያዝንና ያስብላቸው ስለነበረ ነው። መዝሙራዊው፣ ስለ ኢየሱስ “ለድኾችና ለችግረኞች ይራራል” በማለት ትንቢት ተናግሯል። (መዝሙር 72:13) ኢየሱስ ይህን ትንቢት እንደፈጸመ ምንም ጥርጥር የለውም። መጽሐፍ ቅዱስ በአንድ ወቅት የሆነውን ሲናገር “ሕዝቡም እረኛ እንደሌለው በግ ተጨንቀውና ተመልካች የለሽ ሆነው ባየ ጊዜ አዘነላቸው” ይላል። (ማቴዎስ 9:36) ሌላው ቀርቶ ከባድ ኃጢአት የሠሩ ሰዎች እንኳ አሳቢ መሆኑን ተገንዝበው ወደ እርሱ ይቀርቡ ነበር።—ማቴዎስ 9:9-13፤ ሉቃስ 7:36-38፤ 19:1-10
7 እኛም ለሰዎች ተመሳሳይ አሳቢነት የምናሳይ ከሆነ እንደ ኢየሱስ ውጤታማ ልንሆን እንችላለን። ወደ አገልግሎት ከመውጣትህ በፊት ሰዎች አንተ የምትናገረው መልእክት ምን ያህል እንደሚያስፈልጋቸው ለምን ጊዜ ሰጥተህ አታስብበትም? በአምላክ መንግሥት ሥር ብቻ መፍትሔ የሚያገኙ ምን ችግሮች እንዳሉባቸው ቆም ብለህ ለማሰብ ሞክር። ለምትናገረው መልእክት ማን ጆሮ እንደሚሰጥ ስለማታውቅ ለሰዎች ሁሉ አዎንታዊ አመለካከት ይኑርህ። ማን ያውቃል፣ እንደ አንተ ያለ ሰው መጥቶ እንዲረዳው ሲጸልይ ከነበረ ሰው ጋር ትገናኝ ይሆናል!
በፍቅር ተነሳስቶ ማገልገል
8. የኢየሱስ ተከታዮች ምሥራቹን ልክ እንደ እርሱ እንዲሰብኩ የሚገፋፋቸው ምንድን ነው?
8 ኢየሱስ ይሰብከው የነበረው ምሥራች ከይሖዋ ፈቃድ መፈጸም፣ ከስሙ መቀደስና ከሉዓላዊነቱ መረጋገጥ ጋር ቀጥተኛ ተዛምዶ አለው። እነዚህ ደግሞ በመላው የሰው ልጆች ፊት የተደቀኑ አንገብጋቢ ጥያቄዎች ናቸው። (ማቴዎስ 6:9, 10) ኢየሱስ አባቱን ይወድድ ስለነበር የአቋም ጽናቱን እስከ መጨረሻው የመጠበቅ እንዲሁም ለእነዚህ ጥያቄዎች የማያዳግም ምላሽ ስለሚያስገኘው የአምላክ መንግሥት የተሟላ ምሥክርነት የመስጠት ከፍተኛ ፍላጎት ነበረው። (ዮሐንስ 14:31) በዛሬው ጊዜ ያሉ የኢየሱስ ተከታዮችም ተመሳሳይ ፍላጎት ስላላቸው በትጋት ያገለግላሉ። ሐዋርያው ዮሐንስ “እግዚአብሔርን መውደድ ትእዛዛቱን መፈጸም ነውና” በማለት ተናግሯል። ትእዛዛቱ ምሥራቹን እንድንሰብክና ደቀ መዛሙርት እንድናደርግ የተሰጠንን ተልእኮ ይጨምራሉ።—1 ዮሐንስ 5:3፤ ማቴዎስ 28:19, 20
9, 10. ለአምላክ ካለን ፍቅር ሌላ የተሟላ ምሥክርነት እንድንሰጥ የሚገፋፋን ለማን ያለን ፍቅር ነው?
9 ኢየሱስ “ብትወዱኝ ትእዛዜን ትጠብቃላችሁ። የሚወደኝ ትእዛዜን ተቀብሎ የሚጠብቅ ነው” በማለት ለተከታዮቹ ነግሯቸዋል። (ዮሐንስ 14:15, 21) በመሆኑም ለኢየሱስ ያለን ፍቅር ስለ እውነት እንድንመሠክርና እርሱ ያዘዛቸውን ሌሎች ነገሮች እንድንጠብቅ ሊገፋፋን ይገባል። ኢየሱስ ከትንሣኤው በኋላ ለሰዎች ከተገለጠላቸው አጋጣሚዎች መካከል በአንዱ ላይ ጴጥሮስን “ጠቦቶቼን መግብ . . . በጎቼን ጠብቅ . . . በጎቼን መግብ” በማለት በጥብቅ አሳስቦት ነበር። ጴጥሮስን እንዲህ እንዲያደርግ የሚገፋፋው ምንድን ነው? ኢየሱስ “ትወደኛለህን? . . . በእውነት ትወደኛለህን? . . . ትወደኛለህን?” ሲል በተደጋጋሚ ያቀረበለት ጥያቄ መልሱን እንድናገኝ ይረዳናል። አዎን፣ ጴጥሮስ የተሟላ ምሥክርነት እንዲሰጥ፣ የኢየሱስን ‘በጎች’ እንዲፈልግ አልፎ ተርፎም መንፈሳዊ እረኛ በመሆን እንዲጠብቃቸው የሚገፋፋው ለኢየሱስ ያለው ፍቅር ነው።—ዮሐንስ 21:15-17
10 በዛሬው ጊዜ እንደ ጴጥሮስ ኢየሱስን በአካል እንደማናውቀው እሙን ነው። ያም ሆኖ ግን ኢየሱስ ስላደረገልን ነገሮች የጠለቀ ግንዛቤ አለን። ልባችን ‘ስለ ሰው ሁሉ ሞትን እንዲቀምስ’ በገፋፋው ታላቅ ፍቅር ተነክቷል። (ዕብራውያን 2:9፤ ዮሐንስ 15:13) እኛም “የክርስቶስ ፍቅር ግድ ይለናልና፤ . . . በሕይወት ያሉትም ለሞተላቸውና ከሙታን ለተነሣላቸው እንጂ ከእንግዲህ ለራሳቸው እንዳይኖሩ እርሱ ስለ ሁሉ ሞተ” በማለት እንደጻፈው እንደ ጳውሎስ ይሰማናል። (2 ቆሮንቶስ 5:14, 15) የተሟላ ምሥክርነት እንድንሰጥ የሰጠንን ተልእኮ በቁም ነገር በመመልከት ኢየሱስ ላሳየን ፍቅር ከፍተኛ አድናቆት እንዳለን እንዲሁም እኛም እርሱን እንደምንወደው በተግባር ማሳየት እንችላለን። (1 ዮሐንስ 2:3-5) የኢየሱስን ቤዛዊ መሥዋዕት እንደ ተራ ነገር የምንመለከት ይመስል ለስብከቱ ሥራ ፈጽሞ የግዴለሽነት መንፈስ ማሳየት አንፈልግም።—ዕብራውያን 10:29
ትኩረታችሁ በምንም ነገር አይከፋፈል
11, 12. ኢየሱስ ወደዚህ ዓለም የመጣበት ዓላማ ምን ነበር? ዓላማውን እንዳልሳተስ ያሳየው እንዴት ነው?
11 ኢየሱስ ለፍርድ በጳንጥዮስ ጲላጦስ ፊት በቀረበ ጊዜ “የተወለድሁት፣ ወደዚህም ዓለም የመጣሁት ስለ እውነት ለመመስከር ነው” በማለት ተናግሮ ነበር። (ዮሐንስ 18:37) ኢየሱስ ምንም ነገር ለእውነት ከመመሥከር እንቅፋት እንዲሆንበት አልፈቀደም። ይህ አምላክ ለእርሱ ያለው ፈቃድ ነበር።
12 ሰይጣን በዚህ ረገድ ኢየሱስን እንደፈተነው ምንም ጥርጥር የለውም። ኢየሱስ ከተጠመቀ ከተወሰኑ ቀናት በኋላ ሰይጣን “የዓለምንም መንግሥታት ከነክብራቸው” በመስጠት እርሱን ታላቅ ሰው የማድረግ ፍላጎት እንዳለው ገልጾለት ነበር። (ማቴዎስ 4:8, 9) ከጊዜ በኋላ ደግሞ አይሁዳውያን ንጉሥ ሊያደርጉት ፈለጉ። (ዮሐንስ 6:15) አንዳንዶች ኢየሱስ ሰብዓዊ ንጉሥ ቢሆን ለሰው ልጆች በርካታ መልካም ነገሮች ሊያከናውን እንደሚችል በማሰብ ግብዣውን ቢቀበል ጥሩ ይሆን እንደነበር ይሰማቸው ይሆናል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ እንደዚያ ያለ አስተሳሰብ አልነበረውም። እርሱ በዋነኝነት ያተኮረው ስለ እውነት እንዲመሠክር በተሰጠው ተልእኮ ላይ ነበር።
13, 14. (ሀ) ኢየሱስ የመጣበትን ዋነኛ ዓላማ እንዳይፈጽም ምን ነገር እንቅፋት አልሆነበትም? (ለ) ኢየሱስ በቁሳዊ ነገሮች ረገድ ድሃ ቢሆንም ምን አከናውኗል?
13 ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ የመጣበትን ዓላማ በመሳት ሀብት ወደማሳደድ አላዘነበለም። የተንደላቀቀ ሕይወት ያልመራው በዚህ ምክንያት ነው። ሌላው ቀርቶ የራሱ ቤት እንኳ አልነበረውም። በአንድ አጋጣሚ “ቀበሮዎች ጕድጓድ፣ የሰማይ ወፎችም ጎጆ አላቸው፤ የሰው ልጅ ግን ራሱን የሚያስጠጋበት ቦታ የለውም” ሲል ተናግሯል። (ማቴዎስ 8:20) በመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ መሠረት ኢየሱስ በሞተ ጊዜ የነበረው ንብረት የሮም ወታደሮች እጣ የተጣጣሉበት ልብስ ብቻ ነበር። (ዮሐንስ 19:23, 24) ታዲያ ኢየሱስ ያልተሳካለት ሰው ነበር ማለት ነው? በፍጹም!
14 ኢየሱስ በዓለም ላይ እጅግ ሀብታም የሚባል በጎ አድራጊ ሊያከናውነው ከሚችለው በእጅጉ የሚበልጥ ሥራ አከናውኗል። ጳውሎስ “የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ጸጋ ታውቃላችሁና፤ በእርሱ ድኽነት እናንተ ባለጠጎች ትሆኑ ዘንድ እርሱ ሀብታም ሆኖ ሳለ ለእናንተ ሲል ድኻ ሆነ” በማለት ተናግሯል። (2 ቆሮንቶስ 8:9፤ ፊልጵስዩስ 2:5-8) ኢየሱስ በቁሳዊ ነገሮች ረገድ ድሃ ቢሆንም ትሑት የሆኑ ሰዎች ፍጽምና ተላብሰው የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ የሚያስችል አጋጣሚ ከፍቷል። ላደረገልን ነገር በጣም አመስጋኞች ነን! እንዲሁም በአምላክ ፈቃድ ላይ ብቻ በማተኮሩ ምክንያት ላገኘው ወሮታ በጣም ደስተኞች ነን!—መዝሙር 40:8፤ የሐዋርያት ሥራ 2:32, 33, 36
15. ከሀብት የበለጠ ዋጋ ያለው ምንድን ነው?
15 የኢየሱስን ምሳሌ ለመከተል ከፍተኛ ጥረት የሚያደርጉ በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖችም ሀብት ለማግኘት የሚደረገው ሩጫ ትኩረታቸውን እንዲከፋፍልባቸው አይፈቅዱም። (1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10) እነዚህ ክርስቲያኖች ሀብት የተደላደለ ሕይወት ለመምራት እንደሚያስችል አይክዱም፤ ሆኖም የዘላለም ሕይወት ማግኘታቸው የተመካው በሀብት ላይ እንዳልሆነ ያውቃሉ። የኢየሱስ ልብስ እርሱ በሞተ ጊዜ ምንም እንዳልረባው ሁሉ አንድ ክርስቲያንም ሲሞት ሀብቱ ምንም አይጠቅመውም። (መክብብ 2:10, 11, 17-19፤ 7:12) አንድ ክርስቲያን ሲሞት እውነተኛ ጥቅም የሚያስገኝለት ብቸኛው ነገር ከይሖዋና ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የመሠረተው ወዳጅነት ነው።—ማቴዎስ 6:19-21፤ ሉቃስ 16:9
ለተቃውሞ እጅ አልሰጠም
16. ኢየሱስ የደረሰበትን ተቃውሞ የተቋቋመው እንዴት ነው?
16 ኢየሱስ የደረሰበት ተቃውሞ ለእውነት እንዳይመሠክር እንቅፋት አልሆነበትም። ምድራዊ ሕይወቱ በመሥዋዕታዊ ሞት እንደሚደመደም ማወቁ እንኳ ተስፋ እንዲቆርጥ አላደረገውም። ጳውሎስ ኢየሱስን በሚመለከት “እርሱ በፊቱ ስላለው ደስታ መስቀሉን ታግሦ፣ የመስቀሉንም ውርደት ንቆ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአል” በማለት ተናግሯል። (ዕብራውያን 12:2) ኢየሱስ ‘ውርደትን እንደናቀ’ ልብ በል። ተቃዋሚዎቹ ስለ እርሱ የሚያስቡት ነገር አላስጨነቀውም። ትኩረቱ ሙሉ በሙሉ ያረፈው የአምላክን ፈቃድ በማድረግ ላይ ነበር።
17. ኢየሱስ ካሳየው ትዕግሥት ምን እንማራለን?
17 ጳውሎስ ክርስቲያኖች ኢየሱስ ካሳየው ትዕግሥት ወይም ጽናት ምን ትምህርት እንደሚያገኙ ሲናገር “ዝላችሁ ተስፋ እንዳትቆርጡ፣ ከኀጢአተኞች የደረሰበትን እንዲህ ያለውን ተቃውሞ የታገሠውን እርሱን ዐስቡ” በማለት አበረታቷቸዋል። (ዕብራውያን 12:3) በየዕለቱ የተቃውሞ ወይም የፌዝ ዒላማ ሆኖ መኖር አሰልቺ እንደሆነ እሙን ነው። ዓለም ማራኪ አድርጎ በሚያቀርባቸው ነገሮች ላለመሸነፍ መታገል ምናልባትም “ለራሳችን እንድናውቅበት” የሚያበረታቱንን የዘመዶቻችንን ጉትጎታ ተቋቁሞ መኖር አታካች ሊሆንብን ይችላል። ይሁን እንጂ በሕይወታችን ውስጥ የአምላክን መንግሥት ለማስቀደም የቆረጥን እንደመሆናችን መጠን ልክ እንደ ኢየሱስ ይሖዋ እንዲረዳን እንጠይቀዋለን።—ማቴዎስ 6:33፤ ሮሜ 15:13፤ 1 ቆሮንቶስ 2:4
18. ኢየሱስ ለጴጥሮስ ከሰጠው መልስ ምን ግሩም ትምህርት እናገኛለን?
18 ኢየሱስ በቅርቡ እንደሚገደል ለደቀ መዛሙርቱ መናገር በጀመረ ጊዜ የመጣበትን ዓላማ ከመፈጸም ምንም ነገር እንዲያግደው እንዳልፈቀደ በግልጽ ታይቷል። ጴጥሮስ ኢየሱስን “እንዲህ ያለ ነገር ከቶ አይድረስብህ” በማለት በራሱ እንዳይጨክን ሊያግባባው ሞከረ። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ የይሖዋን ፈቃድ ለመፈጸም ያለውን ቁርጥ አቋም ሊያዳክምበት የሚችል ምንም ነገር ማዳመጥ እንደማይፈልግ አሳይቷል። ኢየሱስ፣ ጴጥሮስ ላቀረበው ሐሳብ ቦታ ሳይሰጥ “አንተ ሰይጣን፣ ሂድ ከዚህ! የሰው እንጂ የእግዚአብሔር ነገር በሐሳብህ ስለ ሌለ መሰናክል ሆነህብኛል!” አለ። (ማቴዎስ 16:21-23) እኛም በተመሳሳይ የሰዎችን አስተሳሰብ ለመቃወም ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። ከዚህ ይልቅ ምንጊዜም በአምላክ አስተሳሰብ የምንመራ እንሁን።
የአምላክ መንግሥት ዘላቂ ጥቅሞች ያስገኛል
19. ኢየሱስ ብዙ ተአምራት የሠራ ቢሆንም በዋነኝነት ያከናወነው ጠቃሚ ሥራ ምን ነበር?
19 ኢየሱስ በእርግጥ መሲሕ መሆኑን ለማሳየት በርካታ ተአምራት ፈጽሟል። ሙታንን እንኳ ሳይቀር አስነስቷል። እነዚህ ተአምራት የሕዝቡን ትኩረት እንደሳቡ እሙን ነው፤ ሆኖም ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣበት ዋነኛው ምክንያት ለእውነት ለመመሥከር እንጂ ማኅበራዊ ሥራ ለማከናወን አልነበረም። እርሱ የሚሰጠው ማንኛውም ቁሳዊ ጥቅም ጊዜያዊ እንደሆነ ያውቅ ነበር፤ ከሞት ያስነሳቸው ሰዎች እንኳ እንደገና መሞታቸው አይቀርም። ሰዎች የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ መርዳት የሚችለው ስለ እውነት በመመሥከር ብቻ ነው።—ሉቃስ 18:28-30
20, 21. እውነተኛ ክርስቲያኖች መልካም ሥራ በመሥራት ረገድ ሚዛናዊ አመለካከት የሚይዙት እንዴት ነው?
20 በዛሬው ጊዜ አንዳንድ ግለሰቦች ድሆችን ለመርዳት ሆስፒታሎች በመክፈት ወይም ሌሎች የበጎ አድራጎት ተግባራት በማከናወን የኢየሱስን መልካም ሥራ ለመኮረጅ ጥረት ያደርጋሉ። አንዳንድ ጊዜ እንዲህ ማድረግ ከፍተኛ ወጪ ስለሚጠይቅባቸው በቅንነት ለሚያደርጉት ለዚህ ተግባር ሊመሰገኑ ይገባቸዋል። ሆኖም የሚሰጡት ማንኛውም እርዳታ የሚያስገኘው ጥቅም ጊዜያዊ ነው። ለማንኛውም ችግር ዘላቂ መፍትሔ የሚያመጣው የአምላክ መንግሥት ብቻ ነው። በመሆኑም የይሖዋ ምሥክሮች ልክ እንደ ኢየሱስ ስለ መንግሥቱ የሚናገረውን እውነት ለሌሎች በመመሥከሩ ሥራ ላይ ያተኩራሉ።
21 እርግጥ ነው፣ እውነተኛ ክርስቲያኖች መልካም ሥራዎችንም ይሠራሉ። ጳውሎስ “ዕድሉ ካለን ለሰው ሁሉ፣ በተለይም ለእምነት ቤተ ሰቦች መልካም እናድርግ” ሲል ጽፏል። (ገላትያ 6:10) ድንገተኛ አደጋዎች በሚከሰቱበት ወይም አንድ ሰው ችግር ላይ በሚወድቅበት ጊዜ ለሰው ሁሉ ወይም ለክርስቲያን ወንድሞቻችን ‘መልካም ከማድረግ’ ወደኋላ አንልም። የሆነ ሆኖ በዋነኝነት ልክ እንደ ኢየሱስ እውነትን በመመሥከሩ ሥራ ላይ እናተኩራለን።
ከኢየሱስ ምሳሌ ተማሩ
22. ክርስቲያኖች ምሥራቹን ለሰዎች የሚሰብኩት ለምንድን ነው?
22 ጳውሎስ “ወንጌልን ባልሰብክ ግን ወዮልኝ” ሲል ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 9:16) ወንጌሉን ወይም ምሥራቹን የመስበኩ ሥራ ለእርሱም ሆነ ለሚሰሙት ሰዎች ሕይወት የሚያስገኝ በመሆኑ የግዴለሽነት መንፈስ አላሳየም። (1 ጢሞቴዎስ 4:16) እኛም ለአገልግሎታችን ተመሳሳይ አመለካከት አለን። ሰዎችን መርዳትና ለይሖዋ ያለንን ፍቅር ማሳየት እንፈልጋለን። እንዲሁም ለኢየሱስ ያለንን ፍቅርና እርሱ ላሳየን ታላቅ ፍቅር ያለንን አድናቆት በተግባር መግለጽ እንፈልጋለን። በመሆኑም ምሥራቹን በመስበክ “እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እንጂ እንደ ሥጋ ምኞት” እንደማንኖር እናሳያለን።—1 ጴጥሮስ 4:1, 2
23, 24. (ሀ) ኢየሱስ ዓሣ ከማጥመድ ጋር በተያያዘ ከፈጸመው ተአምር ምን ትምህርት እናገኛለን? (ለ) በዛሬው ጊዜ የተሟላ ምሥክርነት በመስጠት ላይ የሚገኙት እነማን ናቸው?
23 እንደ ኢየሱስ ሁሉ እኛም ሰዎች ሲሰድቡን ወይም መልእክታችንን እንደማይፈልጉ በቁጣ ሲነግሩን ዋነኛውን ሥራችንን ከማከናወን ወደኋላ አንልም። ኢየሱስ ጴጥሮስንና እንድርያስን እንዲከተሉት በጋበዛቸው ጊዜ ካከናወነው ተአምር ትምህርት እናገኛለን። ኢየሱስ የሚለንን ሰምተን በምሳሌያዊ ሁኔታ ምንም ዓሣ የሌለበት በሚመስልበት ውኃ ውስጥ መረባችንን የምንጥል ከሆነ መንፈሳዊ ዓሣ የማጥመድ ሥራችን ውጤት ሊያስገኝ ይችላል። በመንፈሳዊ ዓሣ የማጥመድ ሥራ ላይ የተሰማሩ በርካታ ክርስቲያኖች ጠፍ በሚመስልበት አካባቢ ለበርካታ ዓመታት ከሠሩ በኋላ ግሩም ውጤት አግኝተዋል። ሌሎች ደግሞ ምሳሌያዊው ዓሣ የማጥመድ ሥራ ይበልጥ ውጤታማ ወደሆነባቸው አካባቢዎች ተዛውረው በማገልገላቸው ጥሩ ውጤት አግኝተዋል። እስከ አሁን ያከናወንነው ሥራ ምንም ያህል ይሁን መረባችንን መጣላችንን አናቆምም። ኢየሱስ በየትኛውም የምድር ክፍል ላይ የስብከቱ ሥራ መጠናቀቁን እንዳልተናገረ እናውቃለን።—ማቴዎስ 24:14
24 በዛሬው ጊዜ ከስድስት ሚሊዮን የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮች ከ230 በላይ በሆኑ አገሮች ውስጥ ምሥራቹን በመስበክ ላይ ናቸው። በየካቲት 1, 2005 መጠበቂያ ግንብ እትም ላይ በ2004 የአገልግሎት ዓመት በዓለም ዙሪያ ስላከናወኑት እንቅስቃሴ የሚያሳይ ዓመታዊ ሪፖርት ይወጣል። ይህ ሪፖርት ይሖዋ የስብከቱን ሥራ በእጅጉ እንደባረከው ያሳያል። ይህ ሥርዓት እስከሚጠፋበት ጊዜ ድረስ ጳውሎስ “ቃሉን ስበክ” በማለት የሰጠውን ምክር ልብ ማለታችንን እንቀጥል። (2 ጢሞቴዎስ 4:2) ይሖዋ ሥራው መጠናቀቁን እስከሚያስታውቅበት ጊዜ ድረስ የተሟላ ምሥክርነት መስጠታችንን እንቀጥል።
በጥር 1 መጠበቂያ ግንብ እትም ላይ ይወጣ የነበረው የይሖዋ ምሥክሮች ዓመታዊ የአገልግሎት ሪፖርት ከዚህ ዓመት ጀምሮ በየካቲት 1 እትም ላይ የሚወጣ መሆኑን እንገልጽላችኋለን።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ከሰጠው ሥልጠና ምን ጥቅም ማግኘት እንችላለን?
• ኢየሱስ ለሚሰብክላቸው ሰዎች ምን አመለካከት ነበረው?
• የተሟላ ምሥክርነት እንድንሰጥ የሚገፋፋን ምንድን ነው?
• እንደ ኢየሱስ ሁሉ እኛም የአምላክን ፈቃድ በማድረጉ ሥራ ላይ ትኩረት ማድረግ የምንችለው በየትኞቹ መንገዶች ነው?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እኛም እንደ ኢየሱስ ለሰዎች አሳቢነት የምናሳይ ከሆነ በአገልግሎታችን ውጤታማ እንሆናለን
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣበት ዋናው ዓላማ ስለ እውነት ለመመሥከር ነው
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የይሖዋ ምሥክሮች የተሟላ ምሥክርነት በመስጠቱ ሥራ ላይ ያተኩራሉ