በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

በሐዋርያት ሥራ 7:59 ላይ እስጢፋኖስ ያቀረበው ልመና ጸሎቶቻችንን ማቅረብ ያለብን ለኢየሱስ እንደሆነ ያሳያል?

የሐዋርያት ሥራ 7:59 እንዲህ ይላል:- “እስጢፋኖስም እየወገሩት ሳለ፣ ‘ጌታ ኢየሱስ ሆይ፤ ነፍሴን ተቀበላት’ ብሎ ጸለየ።” መጽሐፍ ቅዱስ ‘ጸሎትን የሚሰማው’ ይሖዋ እንደሆነ ስለሚናገር ከላይ ያሉት ቃላት በአንዳንዶች አእምሮ ውስጥ ጥያቄ አስነስተዋል። (መዝ. 65:2) እስጢፋኖስ በእርግጥ ጸሎቱን ያቀረበው ለኢየሱስ ነበር? ከሆነስ ይህ ኢየሱስና ይሖዋ አንድ አካል መሆናቸውን ያመለክታል?

የኪንግ ጄምስ ቨርሽን መጽሐፍ ቅዱስ እስጢፋኖስ “አምላክን እየጠራ” እንደነበር ይናገራል። በመሆኑም ማቲው ሄንሪ የተባሉ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑር “እስጢፋኖስ ለኢየሱስ እየጸለየ ነበር፤ ስለዚህ እኛም ለእርሱ መጸለይ አለብን” ብለው በተናገሩት ሐሳብ ብዙዎች ይስማማሉ። ይሁን እንጂ ይህ መደምደሚያ የተሳሳተ ነው። ለምን?

ባርንዝ ኖትስ ኦን ዘ ኒው ቴስታመንት የተባለው መጽሐፍ እንደሚከተለው በማለት ሐቁን ተናግሯል:- “አምላክ የሚለው ቃል በመጀመሪያው ቅጂ ላይ ስለማይገኝ በትርጉሙም ላይ መጨመር አልነበረበትም። በጥንታዊ [የብራና ቅጂዎች] ወይም ትርጎሞች ላይም አይገኝም።” ታዲያ “አምላክ” የሚለው ቃል በጥቅሱ ውስጥ እንዴት ገባ? አቤል አቦት ሊቨርሞር የተባሉት ምሑር ይህ “የተርጓሚዎቹ ሃይማኖታዊ አመለካከት በሥራቸው ላይ ያሳደረውን ተጽዕኖ የሚያሳይ ምሳሌ” እንደሆነ ተናግረዋል። በመሆኑም አብዛኞቹ ዘመናዊ ትርጉሞች ይህን የተሳሳተ ሐሳብ አውጥተውታል።

ሆኖም ብዙ ትርጉሞች እስጢፋኖስ ለኢየሱስ ‘እንደጸለየ’ ይናገራሉ። እንዲሁም በአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ ላይ “ልመና አቀረበ” የሚለው ቃል “ምልጃን፤ ጸሎትን” ሊያመለክት እንደሚችል ተገልጿል። ታዲያ ይህ ኢየሱስ ሁሉን ቻይ አምላክ እንደሆነ አያመለክትም? በፍጹም። ቫይንስ ኤክስፖዚተሪ ዲክሽነሪ ኦቭ ኦልድ ኤንድ ኒው ቴስታመንት ዎርድስ እንደሚለው በመጀመሪያው የግሪክኛ ቅጂ ላይ የሚገኘው ኢፒካሊዮ የሚለው የግሪክኛ ቃል በዚህ አገባቡ “መጥራትን፣ መለመንን፤ . . . ለባለ ሥልጣን አቤቱታ ማቅረብን” ያመለክታል። ጳውሎስ “ወደ ቄሳር ይግባኝ ብያለሁ” ለማለት የተጠቀመው ተመሳሳይ ቃል ነው። (የሐዋርያት ሥራ 25:11) በመሆኑም የ1954 ትርጉም እስጢፋኖስ ኢየሱስን ‘እንደጠራ’ በመግለጽ በትክክል አስቀምጦታል።

እስጢፋኖስ እንዲህ ዓይነቱን ልመና እንዲያቀርብ ያነሳሳው ምን ነበር? የሐዋርያት ሥራ 7:55, 56 “እስጢፋኖስ ግን በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ወደ ሰማይ ትኩር ብሎ ሲመለከት፣ የእግዚአብሔርን ክብር፣ እንዲሁም ኢየሱስ በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ” እንዳየ ይናገራል። እስጢፋኖስ ከዚያ በፊት ልመናውን ለይሖዋ የሚያቀርበው በኢየሱስ ስም ይሆናል። ከሞት የተነሳውን ኢየሱስን በራእይ ሲመለከተው ግን “ጌታ ኢየሱስ ሆይ፣ ነፍሴን ተቀበላት” በማለት ልመናውን በቀጥታ ለኢየሱስ ማቅረብ እንደሚችል ሳይሰማው አይቀርም። ለኢየሱስ ሙታንን የማስነሳት ሥልጣን እንደተሰጠው እስጢፋኖስ ያውቅ ነበር። (ዮሐንስ 5:27-29) ስለዚህ ኢየሱስ ከሞት አስነስቶ በሰማይ የማይሞት ሕይወት እስከሚሰጠው ድረስ መንፈሱን ወይም ሕይወት እንዲኖረው ያስቻለውን ኃይል እንዲጠብቅለት ጠይቆታል።

እስጢፋኖስ የተናገራቸው እነዚህ አጭር ቃላት ወደ ኢየሱስ መጸለይ እንደሚቻል ያሳያሉ? በፍጹም። በመጀመሪያ ደረጃ እስጢፋኖስ በይሖዋ እና በኢየሱስ መካከል ያለውን ልዩነት በሚገባ ያውቃል፤ ምክንያቱም ዘገባው ኢየሱስን “በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ” እንደተመለከተው ይናገራል። ከዚህም በላይ እነዚህ ለየት ባለ አጋጣሚ የተፈጠሩ ሁኔታዎች ናቸው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለኢየሱስ ልመና እንዳቀረበ የተዘገበው ሌላው ብቸኛ ሰው ሐዋርያው ዮሐንስ ሲሆን እርሱም በቀጥታ ለኢየሱስ የተናገረው ከእስጢፋኖስ ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ በራእይ በተመለከተው ወቅት ነበር።—ራእይ 22:16, 20

ምንም እንኳን በዛሬው ጊዜ የሚኖሩ ክርስቲያኖች ጸሎታቸውን የሚያቀርቡት ለይሖዋ አምላክ ብቻ ቢሆንም ኢየሱስ “ትንሣኤና ሕይወት” እንደሆነ ሙሉ እምነት አላቸው። (ዮሐንስ 11:25) ኢየሱስ ተከታዮቹን ከሞት ለማስነሳት ችሎታ እንዳለው ማመናችን እስጢፋኖስን በመከራ ወቅት በታማኝነት ለመጽናት እንዳስቻለው ሁሉ እኛንም ሊረዳን ይችላል።