በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘እርስ በርሳችሁ እንግድነት ተቀባበሉ’

‘እርስ በርሳችሁ እንግድነት ተቀባበሉ’

‘እርስ በርሳችሁ እንግድነት ተቀባበሉ’

 በመጀመሪያው መቶ ዘመን ትኖር የነበረችው ክርስቲያኗ ፌቤን አንድ ችግር አጋጥሟት ነበር። ከግሪክ፣ ክንክራኦስ ተነስታ ወደ ሮም በምትጓዝበት ጊዜ በሮም ካሉት የእምነት ባልደረቦቿ መካከል አንዳቸውንም አታውቃቸውም ነበር። (ሮሜ 16:1, 2) የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚ የሆኑት ኤድገር ጉድስፒድ “በወቅቱ የነበረው የሮማውያኑ ዓለም ክፉ እና ጨካኝ በሆኑ ሰዎች የተሞላ ነበር” ብለዋል። አክለውም “የእንግዳ ማረፊያዎቹም ቢሆኑ በሥነ ምግባር ዝቅጠታቸው የሚታወቁ ከመሆናቸውም ሌላ ለጨዋ ሴቶች በተለይም ለክርስቲያን ሴቶች ፈጽሞ የማይመቹ ቦታዎች ነበሩ” በማለት ተናግረዋል። ታዲያ ፌቤን የት ልታርፍ ትችላለች?

በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ሰዎች ከቦታ ቦታ በጣም ይጓዙ ነበር። ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ምሥራቹን በመላው ይሁዳና ገሊላ ለመስበክ ብዙ ተጉዘዋል። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ሐዋርያው ጳውሎስን የመሳሰሉ ወንጌላውያን የሮማ ግዛት ዋና ከተማ የሆነችው ሮምን ጨምሮ በሜድትራንያን ባሕር አካባቢ ወደሚገኙ የተለያዩ አገሮች ምሥራቹን አዳርሰዋል። የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች በአይሁዳውያን ግዛት ውስጥም ሆነ ከዚያ ውጭ በሚጓዙበት ወቅት የሚያርፉት የት ነበር? ማረፊያ ማግኘትን በተመለከተ ምን ዓይነት ችግሮች ያጋጥሟቸው ነበር? እንግዳ ተቀባይ በመሆን ረገድ ከእነሱ ምን እንማራለን?

ዛሬ አንተ ቤት መዋል ይገባኛል

እንግዳ ተቀባይነት የይሖዋ እውነተኛ አምላኪዎች ከጥንት ጀምሮ ተለይተው የሚታወቁበት ባሕርይ ነው። ለምሳሌ ያህል አብርሃም፣ ሎጥና ርብቃ የእንግዳ ተቀባይነት ባሕርይ አሳይተዋል። (ዘፍጥረት 18:1-8፤ 19:1-3፤ 24:17-20) ኢዮብ እንግዳ ለሆኑ ሰዎች የነበረውን አመለካከት ሲናገር “ነገር ግን ቤቴ ለመንገደኛው ዘወትር ክፍት ስለ ነበር፣ መጻተኛው በጐዳና ላይ አያድርም ነበር” ብሏል።—ኢዮብ 31:32

አንድ መንገደኛ ወገኖቹ የሆኑ እስራኤላውያን በእንግድነት እንዲቀበሉት ከፈለገ ማድረግ ያለበት ነገር ቢኖር ወደ ቤት የሚያስገባው ሰው እስኪያገኝ ድረስ በከተማው አደባባይ ላይ ቁጭ ብሎ መጠበቅ ነው። (መሳፍንት 19:15-21) አስተናጋጆቹ ለእንግዶቻቸው ምግብና ውኃ ያቀርቡ፣ እግራቸውን ያጥቡ እንዲሁም ለከብቶቻቸው እንኳ ሳይቀር ገፈራ ያቀርቡ ነበር። (ዘፍጥረት 18:4, 5፤ 19:2፤ 24:32, 33) በአስተናጋጆቻቸው ላይ ሸክም መሆን የማይፈልጉ እንግዶች የሚያስፈልጋቸውን ስንቅ ማለትም ለራሳቸው ዳቦና ወይን፣ ለአህያዎቻቸው ደግሞ ገለባና ገፈራ ይዘው ይጓዙ ነበር። የሚፈልጉት ነገር ማደሪያ ብቻ ነበር።

መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ለስብከቱ ሥራ በሚጓዝበት ወቅት የት ያርፍ እንደነበረ በዝርዝር ባይናገርም እርሱና ደቀ መዛሙርቱ የሆነ ቦታ ያርፉ እንደነበር ግልጽ ነው። (ሉቃስ 9:58) ለምሳሌ ኢያሪኮ በነበረበት ወቅት ለዘኬዎስ “ዛሬ አንተ ቤት መዋል ይገባኛል” ባለው ጊዜ እርሱም ‘በደስታ ተቀብሎ’ አስተናግዶታል። (ሉቃስ 19:5, 6) በቢታንያ ደግሞ በወዳጆቹ በማርታ፣ በማርያም እና በአልዓዛር ቤት በእንግድነት ያርፍ ነበር። (ሉቃስ 10:38፤ ዮሐንስ 11:1, 5, 18) በቅፍርናሆምም በስምዖን ጴጥሮስ ቤት ያርፍ የነበረ ይመስላል።—ማርቆስ 1:21, 29-35

ኢየሱስ አገልግሎቱን አስመልክቶ ለአሥራ ሁለት ሐዋርያቱ የሰጠው መመሪያ በእስራኤል ምን ዓይነት አቀባበል መጠበቅ እንዳለባቸው ይጠቁማል። እንዲህ አላቸው “በመቀነታችሁ ወርቅም ሆነ ብር ወይም መዳብ አትያዙ። ለመንገዳችሁም ከረጢት፣ ትርፍ እጀ ጠባብ ወይም ጫማ ወይም በትር አትያዙ፤ ለሠራተኛ የዕለት ጒርሱ ይገባዋልና። ወደ አንድ ከተማ ወይም መንደር ስትገቡ ሊቀበላችሁ ፈቃደኛ የሆነ ሰው ፈልጋችሁ በቤቱ ዕረፉ፤ እስክትወጡም ድረስ በዚያው ቈዩ።” (ማቴዎስ 10:9-11) ቅን ልብ ያላቸው ግለሰቦች ደቀ መዛሙርቱን በደስታ ተቀብለው ምግብና መጠለያ እንዲሁም ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን እንደሚያቀርቡላቸው ያውቅ ነበር።

ይሁን እንጂ ወንጌላውያኑ ከቦታ ወደ ቦታ በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ራሳቸው ለማሟላትና ወጪያቸውን ለመሸፈን የሚገደዱበት ጊዜ ይመጣል። ኢየሱስ በደቀ መዛሙርቱ ላይ የሚመጣውን ተቃውሞ እንዲሁም የስብከቱ ሥራ ከእስራኤል ምድር ውጭ በሚስፋፋበት ጊዜ የሚኖረውን ሁኔታ ከግምት በማስገባት “ኰረጆም፣ ከረጢትም ያለው ሰው ይያዝ” በማለት ነግሯቸዋል። (ሉቃስ 22:36) ምሥራቹን በተለያዩ አካባቢዎች ለማዳረስ መጓጓዣና የማረፊያ ቦታ ማግኘት የግድ አስፈላጊ ነገሮች መሆናቸው አይቀርም።

እንግዶችን ተቀበሉ

በአንደኛው መቶ ዘመን በመላው የሮም ግዛት አንፃራዊ ሰላም የሰፈነ መሆኑና ብዙ ጥርጊያ መንገዶች መኖራቸው ሰዎች እንደ ልባቸው ከቦታ ወደ ቦታ እንዲንቀሳቀሱ አስችሏቸዋል። a የተጓዦች ቁጥር መብዛቱ ደግሞ የማረፊያ ቦታዎች ተፈላጊነት እንዲጨምር አድርጓል። ይህ የማረፊያ ችግር ከዋናዎቹ አውራ ጎዳናዎች አጠገብ የአንድ ቀን የእግር መንገድ ያህል ተራርቀው በሚገኙ ትናንሽ ሆቴሎች ሊቀረፍ ችሏል። ይሁን እንጂ ዘ ቡክ ኦቭ አክትስ ኢን ኢትስ ግሪኮ-ሮማን ሴቲንግ የተባለው መጽሐፍ እንደዘገበው “ስለነዚህ ቦታዎች በጽሑፍ ሰፍሮ የሚገኘው ነገር ጥሩ አይደለም። የሥነ ጽሑፍ መረጃዎችና የአርኪዮሎጂ ምርምር ውጤቶች እንደሚያሳዩት ሆቴሎቹ ያረጁና የቆሸሹ፣ በውስጣቸው ምንም ዓይነት የመገልገያ ዕቃ የሌላቸው፣ አልጋዎቹ በትኋን የተሞሉ፣ ምግቡና መጠጡ ንጽሕናው ያልተጠበቀ፣ ባለቤቶቹም ሆኑ ሠራተኞቹ ታማኝነት የሚጎድላቸው፣ ደንበኞቻቸው መልካም ስም የሌላቸው እንዲሁም በአጠቃላይ የሥነ ምግባር ርኩሰት የሚፈጸምባቸው ቦታዎች ነበሩ።” መልካም ሥነ ምግባር ያለው አንድ መንገደኛ በእነዚህ ሆቴሎች ውስጥ ላለማረፍ የተቻለውን ሁሉ እንደሚያደርግ እሙን ነው።

ቅዱሳን ጽሑፎች ክርስቲያኖች እንግዳ ተቀባይ እንዲሆኑ በተደጋጋሚ ማሳሰባቸው ሊያስገርመን አይገባም። ጳውሎስ በሮም የነበሩትን ክርስቲያኖች “ችግረኛ ለሆኑ ቅዱሳን ካላችሁ አካፍሉ፤ እንግዶችን ተቀበሉ” ሲል አሳስቧቸዋል። (ሮሜ 12:13) አይሁዳውያን ክርስቲያኖችን “እንግዶችን መቀበል አትርሱ፤ አንዳንዶች ይህን ሲያደርጉ፣ ሳያውቁ መላእክትን አስተናግደዋል” በማለት አስታውሷቸዋል። (ዕብራውያን 13:2) ጴጥሮስ የእምነት ባልንጀሮቹን “እርስ በርሳችሁ ያለ ማጒረምረም እንግድነት ተቀባበሉ” ሲል አሳስቧቸዋል።—1 ጴጥሮስ 4:9

ይሁን እንጂ የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ማሳየት ተገቢ የማይሆንበት ጊዜ አለ። “በክርስቶስ ትምህርት የማይኖርና ከትምህርቱ የሚወጣ” ሰውን በተመለከተ ሐዋርያው ዮሐንስ “በቤታችሁ አትቀበሉት፤ ሰላምም አትበሉት፤ የሚቀበለው ሰው፣ የክፉ ሥራው ተባባሪ ይሆናልና” ሲል አስጠንቅቋል። (2 ዮሐንስ 9-11) ሐዋርያው ጳውሎስ ንስሐ የማይገቡ ኃጢአተኞችን በተመለከተ “‘ወንድም ነኝ’ እያለ ከሚሴስን ወይም ከሚስገበገብ ወይም ጣዖትን ከሚያመልክ ወይም ከሚሳደብ ወይም ከሚሰክር ወይም ከሚቀማ ጋር እንዳትተባበሩ ነው፤ ከእንደዚህ ዐይነቱ ሰው ጋር ምግብ እንኳ አትብሉ” ሲል ጽፏል።—1 ቆሮንቶስ 5:11

አንዳንድ አስመሳዮች እውነተኛ ክርስቲያኖች የሚያሳዩትን የደግነት መንፈስ ተገቢ ባልሆነ መንገድ ሊጠቀሙበት ሞክረዋል። በሁለተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ የተዘጋጀ ዘ ዲዳሂ ወይም የአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ትምህርት ተብሎ የሚታወቀው ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ የሆነ አንድ ሰነድ ተጓዥ ሰባኪን በተመለከተ እንዲህ ብሏል:- “ለአንድ ወይም አስፈላጊ ከሆነ ለሁለት ቀን” በቤትህ በእንግድነት ተቀበለው። ከዚያም በሚሄድበት ወቅት ደግሞ “ለመንገድ የሚሆነው ስንቅ ብቻ አስይዘው . . . ገንዘብ የሚጠይቅህ ከሆነ ግን ሐሰተኛ ነቢይ ነው።” ሰነዱ በመቀጠል እንዲህ ይላል:- “በቤትህ ከአንተ ጋር መቀመጥ ቢፈልግና አንድ ዓይነት ሙያ ካለው ሠርቶ ይብላ። ምንም ዓይነት ሙያ ከሌለው ግን ሁኔታውን አይተህ ልትረዳው ይገባል። በዚህ መንገድ ክርስቲያን ነኝ በሚል ሰበብ ሥራ ፈት በመካከላችሁ እንዳይኖር ማድረግ ትችላላችሁ። ይህንን መከተል የማይፈልግ ከሆነ ግን ክርስትናን የግል ጥቅም ማራመጃ ሊያደርግ ያሰበ ስለሆነ ጥንቃቄ አድርግ።”

ሐዋርያው ጳውሎስ በአንዳንድ ከተሞች ረዘም ላለ ጊዜ ቆይታ በሚያደርግበት ወቅት ለአስተናጋጆቹ ሸክም እንዳይሆንባቸው ይጠነቀቅ ነበር። ራሱን ችሎ ለመኖር ድንኳን ይሰፋ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 18:1-3፤ 2 ተሰሎንቄ 3:7-12) የጥንቶቹ ክርስቲያኖች በመካከላቸው መስተንግዶ የሚያስፈልጋቸውን በጉዞ ላይ ያሉ ወንድሞችና እህቶች ለመርዳት የድጋፍ ደብዳቤ የመጻፍ ልማድ እንደነበራቸው ከሁኔታዎቹ መረዳት ይቻላል። ለምሳሌ ሐዋርያው ጳውሎስ ፌቤንን አስመልክቶ “እኅታችንን ፌቤንን ዐደራ እላችኋለሁ። . . . በጌታ እንድትቀበሏትና ከእናንተም የምትፈልገውን ማንኛውንም ርዳታ እንድታደርጉላት አሳስባችኋለሁ” ሲል ጽፏል።—ሮሜ 16:1, 2

እንግዳ ተቀባይ መሆን የሚያስገኘው በረከት

የአንደኛው መቶ ዘመን ክርስቲያን ሚስዮናውያን ይሖዋ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ሁሉ እንደሚያሟላላቸው ሙሉ እምነት ነበራቸው። ይሁንና የእምነት ባልንጀሮቻቸው በእንግድነት እንዲቀበሏቸው መጠበቅ ይችሉ ነበር? ልድያ ጳውሎስና አብረውት የነበሩት ሌሎች ወንድሞች በቤቷ እንዲያርፉ አድርጋለች። ጳውሎስ በቆሮንቶስ በነበረበት ወቅት አቂላና ጵርስቅላ ቤት ተቀምጧል። በፊልጵስዩስ የሚኖር አንድ የወህኒ ቤት ጠባቂ ጳውሎስና ሲላስን እቤቱ ወስዶ ምግብ አቅርቦላቸዋል። በተጨማሪም ጳውሎስ በተሰሎንቄ ኢያሶን፣ በቂሳርያ ደግሞ ፊልጶስ በእንግድነት ተቀብለውታል። ከቂሳርያ ወደ ኢየሩሳሌም በተጓዘበት ወቅት ምናሶን አስተናግዶታል። ወደ ሮም ሲያቀና ደግሞ በፑቲዮሉስ የሚኖሩ ወንድሞች ጥሩ መስተንግዶ አድርገውለታል። ጳውሎስን በእንግድነት የተቀበሉት ክርስቲያኖች በመንፈሳዊ ብዙ ጥቅም አግኝተው መሆን አለበት!—የሐዋርያት ሥራ 16:33, 34፤ 17:7፤ 18:1-3፤ 21:8, 16፤ 28:13, 14

ፍሬድሪክ ብሩስ የተባሉት የሃይማኖት ምሑር እንዲህ ብለዋል:- “የጳውሎስ ወዳጆችና የሥራ ባልደረቦች እንዲሁም በቤታቸው ያስተናገዱት ወንድሞችና እህቶች ያን ያህል ጥሩ አቀባበል እንዲያደርጉለት ያነሳሳቸው ዋነኛው ምክንያት ለጳውሎስና እርሱ ለሚያገለግለው ጌታ ከፍተኛ ፍቅር ስለነበራቸው ነው። ለጳውሎስ የሚያደርጉትን ነገር ለኢየሱስ እንዳደረጉት ይቆጥሩት ነበር።” እንግዳ ተቀባይ ለመሆን የሚያነሳሳ ትክክለኛ ዝንባሌ ይህ ነው።

እንግዳ የመቀበል አስፈላጊነት ዛሬም አልቀነሰም። በሺህ የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች ተጓዥ ተወካዮችን ወንድሞቻቸው በጥሩ ሁኔታ ተቀብለው ያስተናግዷቸዋል። አንዳንድ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ደግሞ ምሥራቹ እምብዛም ወዳልተዳረሰባቸው አካባቢዎች ሄደው ለማገልገል በራሳቸው ወጪ ይጓዛሉ። ትልቅ ቤት ባይኖረንም እንኳ እነዚህን ወንድሞች በቤታችን ማሳረፋችን ከፍተኛ በረከት ያስገኝልናል። ሞቅ ያለ የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ማሳየትና ከተቻለም ቀለል ያለ ምግብ መጋበዝ ‘እርስ በርስ ለመበረታታት’ እንዲሁም ለወንድሞቻችንና ለአምላካችን ያለንን ፍቅር ለማሳየት ግሩም አጋጣሚ ይከፍትልናል። (ሮሜ 1:11, 12) ‘ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ደስተኛ’ ስለሆነ እነዚህን የመሳሰሉ አጋጣሚዎች በተለይ ለእንግዳ ተቀባዮቹ ብዙ በረከት ያስገኛሉ።—የሐዋርያት ሥራ 20:35

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በ100 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ሮም 80,000 ኪሎ ሜትር የሚሸፍኑ በድንጋይ የተነጠፉ መንገዶች እንደነበሯት ይገመታል።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ክርስቲያኖች ‘እንግዳ ተቀባዮች’ ናቸው