በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሳውል ስብከት ተቃውሞ ቀሰቀሰ

የሳውል ስብከት ተቃውሞ ቀሰቀሰ

የሳውል ስብከት ተቃውሞ ቀሰቀሰ

 በደማስቆ የሚኖሩ አይሁዳውያን ነገሩ ግራ አጋብቷቸዋል። ሲወርድ ሲዋረድ ለመጣው ሃይማኖት በቅንዓት ይከራከር የነበረ ሰው እንዴት ከሃዲ ሊሆን ቻለ? ይህ ሰው በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን የኢየሱስ ተከታዮች ሲያሳድድ የነበረው ሳውል ነው። ወደ ደማስቆም የሄደው በዚያ የሚገኙትን ደቀ መዛሙርት ለማሳደድ ነበር። አሁን ግን አምላክን ሰድቧል ተብሎ እንደ ከባድ ወንጀለኛ ተቆጥሮ በአሳፋሪ ሁኔታ የተሰቀለው ሰው መሲሕ መሆኑን ራሱ መስበክ ጀምሯል! ሳውል አእምሮውን ስቶ ይሆን?—የሐዋርያት ሥራ 9:1, 2, 20-22

ሳውል እንዲህ ያደረገበት በቂ ምክንያት ነበረው። ከሳውል ጋር ለተመሳሳይ ዓላማ ከኢየሩሳሌም ተነስተው ሲጓዙ የነበሩ ሰዎችም በመንገድ ላይ ስለተከሰተው ሁኔታ ለሌሎች ሳያወሩ አልቀሩም። ወደ ደማስቆ ሲቃረቡ በድንገት ደማቅ ብርሃን በዙሪያቸው ካበራባቸው በኋላ ሁሉም መሬት ላይ ወደቁ። ከዚህም በላይ የሆነ ድምፅ ሰምተዋል። በዚህ ክስተት ሳቢያ ጉዳት የደረሰበት ሳውል ብቻ በመሆኑ መሬት ላይ ተዘርሮ ቆየ። በመጨረሻ ከወደቀበት ሲነሳ ማየት ተስኖት ስለነበር ሌሎቹ ተጓዦች ወደ ደማስቆ እየመሩ ወሰዱት።—የሐዋርያት ሥራ 9:3-8፤ 26:13, 14

ተቃዋሚው ደጋፊ ሆነ

ሳውል ወደ ደማስቆ እየተጓዘ ሳለ ያጋጠመው ምንድን ነው? ረጅሙ ጉዞ ወይም የቀትሩ ንዳድ አቅም አሳጥቶት ይሆን? በዘመናችን ያሉ መጽሐፍ ቅዱስን የሚጠራጠሩ ሰዎች ሳውል ትኩሳት ይዞት፣ ቅዠት ውስጥ ገብቶ፣ በኅሊና ጸጸት ምክንያት ከባድ ሥነ ልቦናዊ ሥቃይ ደርሶበት፣ የአእምሮ ወይም የስሜት መቃወስ አጋጥሞት አሊያም ድሮም የሚጥል በሽታ ኖሮበት ሊሆን ይችላል በማለት ሁኔታውን ከተለመዱ የጤና እክሎች አንጻር ለማብራራት ይሞክራሉ።

እውነታው ግን፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ዓይን በሚያሳውር ደማቅ ብርሃን ለሳውል ተገልጦለት መሲሕ መሆኑን ያሳመነው መሆኑ ነው። አንዳንድ ሥዕላዊ መግለጫዎች ሳውል ከፈረስ ላይ እንደወደቀ አድርገው ያሳያሉ። ነገሩ እንዲህ ሊሆን ቢችልም መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ግን ‘ምድር ላይ እንደወደቀ’ ብቻ ነው። (የሐዋርያት ሥራ 22:6-11) ሳውል በምንም መልኩ ቢወድቅ ከዚያ የከፋው ቀድሞ የነበረውን ሥልጣን በአሳፋሪ ሁኔታ ማጣቱ ነው። የኢየሱስ ተከታዮች የሚሰብኩት እውነት መሆኑን አምኖ ለመቀበል ተገድዷል። ሳውል የነበረው ብቸኛ አማራጭ ከእነርሱ ጋር ሆኖ ይህን ሥራ ማከናወን ነው። የኢየሱስን ትምህርት አጥብቆ ይቃወም የነበረው ሳውል ተቀይሮ የምሥራቹ ታማኝ ደጋፊ ከሆኑት ሰዎች አንዱ ሆነ። ሳውል ዓይኑ ከበራለትና ከተጠመቀ በኋላ “እየበረታ ሄደ፤ በደማስቆ ለሚኖሩትም አይሁድ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ መሆኑን ማስረጃ እያቀረበ አፋቸውን ያስይዛቸው ነበር።”—የሐዋርያት ሥራ 9:22

የግድያ ሴራው ከሸፈ

በኋላ ላይ ጳውሎስ የሚል ስም የተሰጠው ሳውል ክርስትናን ከተቀበለ በኋላ የተጓዘው ወዴት ነበር? “ወዲያው ወደ ዐረብ አገር ሄድሁ፤ በኋላም ወደ ደማስቆ ተመለስሁ” በማለት ለገላትያ ሰዎች በጻፈላቸው ደብዳቤ ላይ ገልጿል። (ገላትያ 1:17) “ዐረብ አገር” የሚለው አባባል የአረብ ባሕረ ገብ ምድር ክፍል ከሆነው ወደ አንዱ መሄዱን ሊያመለክት ይችላል። አንዳንድ ምሑራን ጳውሎስ ምናልባት ወደ ሶርያ በረሃ ወይም ደግሞ የንጉሥ አርስጦስዮስ አራተኛ፣ ግዛት ወደሆነው ወደ ናባቲያ ሄዷል የሚል አስተያየት ይሰጣሉ። ኢየሱስ ከተጠመቀ በኋላ ወደ በረሃ እንደሄደ ሁሉ ሳውልም ከጥምቀቱ በኋላ ለማሰላሰል ጸጥታ ወዳለበት ቦታ ሳይሄድ አይቀርም ብሎ ማሰቡ በጣም አሳማኝ ነው።—ሉቃስ 4:1

ሳውል ወደ ደማስቆ ሲመለስ ‘አይሁድ ሊገድሉት አሤሩ።’ (የሐዋርያት ሥራ 9:23) በደማስቆ ያለው የንጉሥ አርስጦስዮስ እንደ ራሴ ሳውልን ለማስያዝ ከተማዋን ያስጠብቅ ነበር። (2 ቆሮንቶስ 11:32) ጠላቶቹ ሳውልን ለመግደል አሲረው የነበረ ቢሆንም የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የሚያመልጥበትን መንገድ አመቻቹለት።

ሳውል እንዲያመልጥ ከረዱት መካከል ሐናንያና ክርስቲያን ከሆነ በኋላ አብረውት የነበሩ ሌሎች ደቀ መዛሙርት ይገኙበታል። a (የሐዋርያት ሥራ 9:17-19) ሳውል በደማስቆ ባካሄደው የስብከት ሥራ የተነሳ አማኝ የሆኑ አንዳንድ ሰዎችም ማምለጥ እንዲችል ሳይረዱት አልቀሩም፤ ይህን በተመለከተ የሐዋርያት ሥራ 9:25 እንዲህ ይላል:- “የእርሱ ተከታዮች ግን በሌሊት በከተማዋ ቅጥር ቀዳዳ አሹልከው በቅርጫት አወረዱት።” “የእርሱ ተከታዮች” የተባሉት ሳውል ያስተማራቸው ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ። የሆነ ሆኖ ሳውል በአገልግሎቱ ያገኘው ስኬት ቀደም ሲል ተነስቶበት የነበረው ጥላቻ ይበልጥ እንዲቀጣጠል ያደረገ ይመስላል።

ምን ትምህርት እናገኛለን?

ሳውል ክርስትናን ሲቀበልና ሲጠመቅ የተፈጠሩትን አንዳንድ ሁኔታዎች ስንመለከት፣ ሌሎች ስለ እርሱ ላላቸው አመለካከት ከልክ በላይ እንደማይጨነቅ በግልጽ መረዳት እንችላለን። ከዚህም በላይ ከባድ ተቃውሞ እንኳን ሥራውን አላስቆመውም። ሳውልን ያሳስበው የነበረው ዐቢይ ጉዳይ የተቀበለው የስብከት ተልእኮ ነው።—የሐዋርያት ሥራ 22:14, 15

አንተስ ምሥራቹን የመስበኩን አስፈላጊነት የተገነዘብከው በቅርቡ ነው? ከሆነ ሁሉም እውነተኛ ክርስቲያኖች የመንግሥቱ ምሥራች ሰባኪዎች መሆን እንዳለባቸው ታውቃለህ ማለት ነው። በምትሰብክበት ጊዜ አልፎ አልፎ ተቃውሞ ቢያጋጥምህ ሊያስደንቅህ አይገባም። (ማቴዎስ 24:9፤ ሉቃስ 21:12፤ 1 ጴጥሮስ 2:20) ሳውል ተቃውሞ ሲያጋጥመው የሰጠው ምላሽ ምሳሌ ይሆነናል። ተስፋ ሳይቆርጡ በፈተናዎች የሚጸኑ ክርስቲያኖች የአምላክን ሞገስ ያገኛሉ። ኢየሱስ ለተከታዮቹ “ስለ ስሜም በሰዎች ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ” ብሏቸዋል። ነገር ግን “ጸንታችሁም በመቆም ነፍሳችሁን ታተርፋላችሁ” የሚል ማረጋገጫም ሰጥቷቸዋል።—ሉቃስ 21:17-19

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ክርስትና ወደ ደማስቆ የገባው ኢየሱስ በገሊላ መስበኩን ተከትሎ አሊያም በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ከተከበረው የጰንጠቆስጤ በዓል በኋላ ሊሆን ይችላል።—ማቴዎስ 4:24፤ የሐዋርያት ሥራ 2:5

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሳውል ኢየሱስ በተገለጠለት ጊዜ ‘ምድር ላይ ወደቀ’

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሳውል ደማስቆ ውስጥ ከተሸረበበት የግድያ ሴራ አምልጧል