በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

ሳምሶን የገደላቸውን እንስሳትና ሰዎች በድን ከነካ እንዴት በናዝራዊነቱ ሊቀጥል ይችላል?

በጥንቷ እስራኤል አንድ ሰው በራሱ ፈቃድ ለተወሰነ ጊዜ ናዝራዊ ለመሆን ስእለት መግባት ይችል ነበር። a የተሳለው ሰው ከተጣሉበት እገዳዎች አንዱ እንደሚከተለው ተገልጿል:- “ራሱን ለእግዚአብሔር በለየበት ጊዜ ሁሉ ወደ ሬሳ አይቅረብ። . . . አባቱም ይሁን እናቱ፣ ወንድሙም ይሁን እኅቱ ቢሞቱ ለእነርሱ ሲል እንኳ ራሱን አያርክስ።” አንድ ሰው ‘ድንገት አጠገቡ ቢሞትስ?’ እንዲህ ባለው አጋጣሚ በድኑን ቢነካ ናዝራዊነቱ ይረክስበታል። በመሆኑም “ያለፉት ቀኖች አይቈጠሩም” ተብሎ ተገልጿል። በዚህ ጊዜ የመንጻት ሥርዓት መፈጸምና የናዝራዊነቱን ዘመን እንደ አዲስ መጀመር ይኖርበታል።—ዘኍልቍ 6:6-12

የሳምሶን ናዝራዊነት ግን ለየት ያለ ነበር። ከመወለዱ በፊት አንድ የይሖዋ መልአክ ለእናቲቱ “ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ። በራሱ ላይ ምላጭ አይድረስበት፤ ልጁ ከእናቱ ማሕፀን ጀምሮ ናዝራዊ በመሆን ለእግዚአብሔር የተለየ ይሆናልና፤ እስራኤልንም ከፍልስጥኤማውያን እጅ መታደግ ይጀምራል” ብሏት ነበር። (መሳፍንት 13:5) ሳምሶን ናዝራዊ ለመሆን አልተሳለም ነበር። ዕድሜ ልኩን ናዝራዊ እንዲሆን የሾመው አምላክ ራሱ ነው። የሳምሶን ዓይነት ናዝራዊነት በድን መንካትን የሚከለክል ደንብ ሊያካትት አይችልም። ይህ ሕግ በሳምሶን ላይ የሚሠራ ቢሆንና ድንገት አስከሬን ቢነካ፣ ሲወለድ የጀመረውን የዕድሜ ልክ ናዝራዊነት እንዴት እንደገና ሊጀምር ይችላል? ከዚህ መረዳት እንደምንችለው ዕድሜ ልካቸውን ናዝራዊ ከሚሆኑ ሰዎችና በገዛ ፈቃዳቸው ናዝራዊ ከሆኑ ሰዎች የሚጠበቀው ብቃት በአንዳንድ መንገዶች ይለያያል።

እስቲ ይሖዋ ዕድሜ ልካቸውን ናዝራውያን ለሚሆኑት ለሳምሶን፣ ለሳሙኤልና ለመጥምቁ ዮሐንስ የሰጣቸውን ትእዛዛት ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንመልከት። ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ሳምሶን የራስ ፀጉሩን እንዳይቆረጥ ተነግሮት ነበር። ሐና ገና ሳሙኤልን ከመጸነሷ በፊት “በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ለእግዚአብሔር እሰጠዋለሁ፤ ምላጭም በራሱ ላይ አይደርስም” በማለት ተስላ ነበር። (1 ሳሙኤል 1:11) የይሖዋ መልአክ መጥምቁ ዮሐንስን በተመለከተ ሲናገር “የወይን ጠጅም ሆነ ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አይጠጣም” ብሏል። (ሉቃስ 1:15) በተጨማሪም “የዮሐንስ ልብስ የግመል ጠጒር ሲሆን፣ ወገቡንም በጠፍር ይታጠቅ ነበር። ምግቡም አንበጣና የበረሃ ማር ነበር።” (ማቴዎስ 3:4) ሆኖም ሦስቱም ግለሰቦች ወደ በድን እንዳይደርሱ አልታዘዙም።

ሳምሶን ከናዝራዊነቱም በተጨማሪ ይሖዋ እስራኤላውያንን ከወራሪዎች እጅ ለማዳን ካስነሳቸው መሳፍንት አንዱ ነበር። (መሳፍንት 2:16) ይህን ተልእኮውን በሚወጣበት ጊዜ በድን ነክቷል። በአንድ ወቅት ሳምሶን 30 ፍልስጥኤማውያንን ከገደለ በኋላ ልብሳቸውን ገፍፎ ወስዷል። ከዚያ በኋላ ጠላቶቹን “ጭን ጭናቸውን ብሎ በታላቅ አገዳደል መታቸው።” በተጨማሪም ከሞተ ብዙም ባልቆየ የአህያ መንጋጋ አንድ ሺህ ሰው ገድሏል። (መሳፍንት 14:19፤ 15:8, 15 የ1954 ትርጉም) ሳምሶን ይህን ሁሉ ያከናወነው በይሖዋ እርዳታና ድጋፍ ነው። ቅዱሳን ጽሑፎች ሳምሶን በእምነት ረገድ ምሳሌ እንደሆነ ይገልጻሉ።—ዕብራውያን 11:32፤ 12:1

ሳምሶን “የፍየል ጠቦት እንደሚገነጣጠል” ያህል አንድ አንበሳ እንደቆራረጠ የሚገልጸው ዘገባ በዚያን ዘመን የፍየል ጠቦት መገነጣጠል የተለመደ ነገር መሆኑን ያመለክታል?

በእስራኤል መሳፍንት ዘመን ሰዎች የፍየል ጠቦት የመቆራረጥ ልማድ እንደነበራቸው የሚያሳይ ማስረጃ አናገኝም። መሳፍንት 14:6 “የእግዚአብሔር መንፈስ [በሳምሶን ላይ] በኀይል ወረደበት፤ ስለዚህ የፍየል ጠቦት እንደሚገነጣጠል አንበሳውን ያለ ምንም መሣሪያ በባዶ እጁ ገነጣጠለው” በማለት ይናገራል። ይህ አባባል ምሳሌያዊ ይመስላል።

“ገነጣጠለው” የሚለው ቃል ሁለት ዓይነት ትርጉም ሊኖረው ይችላል። ሳምሶን የአንበሳውን መንገጭላ ለሁለት ሰንጥቆ አሊያም አንበሳውን በሆነ መንገድ በብልት በብልት ቆራርጦት ሊሆን ይችላል። ሳምሶን አንበሳውን ከመንገጭላው ሰንጥቆ ገድሎት ከሆነ፣ በፍየል ጠቦት ላይ ተመሳሳይ ነገር ማድረግ ለማንኛውም ሰው እንደማይከብድ ሁሉ ለእርሱም በባዶ እጁ አንበሳን ማሸነፍ የዚያን ያህል ቀልሎት ነበር ማለት ነው። ይሁንና ሳምሶን አንበሳውን የገደለው በብልት በብልት ቆራርጦ ከሆነስ? ይህ ከሆነ ስለ አገዳደሉ የተሰጠው መግለጫ ከንጽጽር የአነጋገር ዘይቤ ያለፈ ሊሆን አይችልም። በመሆኑም ሳምሶን በይሖዋ መንፈስ እገዛ ከተለመደው አካላዊ ጥንካሬ የበለጠ ኃይል የሚጠይቅ ተግባር ማከናወን እንደቻለ ለማስረዳት የተሠራበት የአነጋገር ዘይቤ ነው። ያም ሆነ ይህ በመሳፍንት 14:6 ላይ የቀረበው ንጽጽር፣ አንድ ተራ ሰው የፍየል ጠቦት እንደማይፈራ ሁሉ ሳምሶንም በይሖዋ እርዳታ ኃይለኛ የሆነውን አንበሳ ከምንም እንዳልቆጠረው ያሳያል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ናዝራዊ የሚሆንበትን የጊዜ ርዝመት የሚወስነው ስእለቱን የሚሳለው ሰው ነው። ይሁን እንጂ በአይሁዳውያን ልማድ መሠረት የስእለቱ ጊዜ ከ30 ቀናት ማነስ የለበትም። ከዚህ ካነሰ ስእለቱ እንደ ተራ ነገር ይቆጠራል የሚል እምነት ነበራቸው።