በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የወደፊት ዕጣህን መወሰን ትችላለህ?

የወደፊት ዕጣህን መወሰን ትችላለህ?

የወደፊት ዕጣህን መወሰን ትችላለህ?

 የመጨረሻው ዕጣ ፈንታችን አስቀድሞ ተወስኗል? በሕይወታችን ውስጥ የምናደርጋቸው ምርጫዎች ወደፊት በሚያጋጥመን ነገር ላይ ለውጥ ያመጣሉ?

የሰው ልጅ የራሱን ዕድል መወሰን ይችላል እንበል። ይህ ቢሆን ማንኛውም ሰው የተለየ ሥራ ለመሥራት ወይም የተወሰነ የኃላፊነት ቦታ ለመያዝ አስቀድሞ ሊወስን ይችላል ማለት ነው? ሰዎች የወደፊት ዕጣቸውን የመወሰን ነፃነት ካላቸው አምላክ ለምድር ያለውን ዓላማ እንዴት ከግቡ ማድረስ ይችላል? መጽሐፍ ቅዱስ ለእነዚህ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ ይሰጠናል።

ዕድል ተወስኗል የሚለው እምነትና ነፃ ምርጫ—ሁለቱም አመለካከቶች ትክክል ሊሆኑ ይችላሉ?

እስቲ ይሖዋ አምላክ እንዴት እንደፈጠረን እንመልከት። መጽሐፍ ቅዱስ “[ሰውን] በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው” ይላል። (ዘፍጥረት 1:27) በአምላክ አምሳል በመፈጠራችን እንደ ፍቅር፣ ፍትሕ፣ ጥበብና ኃይል የመሳሰሉ ባሕርያቱን የማንጸባረቅ ችሎታ አለን። እንዲሁም አምላክ ነፃ ምርጫ ወይም በሌላ አነጋገር የፈለግነውን የመምረጥ ነፃነት ሰጥቶናል። ይህም ከሌሎች የአምላክ ምድራዊ ፍጥረታት ሁሉ የተለየን እንድንሆን አድርጎናል። የአምላክን የሥነ ምግባር መመሪያ ለመጠበቅ ወይም ላለመጠበቅ የመወሰን መብት አለን። ነቢዩ ሙሴ እንደሚከተለው ብሎ የተናገረው በዚህ ምክንያት ነው:- “ሕይወትንና ሞትን፣ በረከትንና ርግማንን በፊትህ እንዳስቀመጥሁ ዛሬ ሰማይንና ምድርን ምስክር አድርጌ እጠራብሃለሁ። እንግዲህ አንተና ልጆችህ በሕይወት እንድትኖሩ ሕይወትን ምረጥ፤ ይኸውም አምላክህን እግዚአብሔርን እንድትወድ፣ ቃሉን እንድታደምጥና ከእርሱ ጋር እንድትጣበቅ ነው።”—ዘዳግም 30:19, 20

ሆኖም የፈለግነውን የመምረጥ ነፃነት አለን ሲባል ሙሉ በሙሉ ነፃ ነን ማለት አይደለም። ይህ ነፃነታችን አምላክ አጽናፈ ዓለም የተረጋጋና ሰላማዊ እንዲሆን ለማስቻል ካወጣቸው ተፈጥሯዊና ሥነ ምግባራዊ ሕጎች ነፃ አያደርገንም። እነዚህ ሕጎች ለእኛው ጥቅም ታስበው የተዘጋጁ ሲሆን ሕጎቹን መጣስ ከባድ መዘዝ ያስከትላል። ለምሳሌ ያህል የስበትን ሕግ ችላ ብለን ከአንድ ትልቅ ሕንጻ ጣራ ላይ ብንዘል ምን ሊፈጠር እንደሚችል አስብ!—ገላትያ 6:7

በተጨማሪም የመምረጥ ነፃነታችን ይህ ስጦታ ካልተሰጣቸው ሌሎች ፍጥረታት የተለየ ኃላፊነት ያስከትልብናል። ደራሲው ኮርለስ ላሞንት “የሰዎች ምርጫና የሚያከናውኑት ተግባር አስቀድሞ እንደተወሰነ . . . አምነን ከተቀበልን፣ እንዴት ሥነ ምግባራዊ ደንብ ማውጣትና ሰዎች ስህተት ሲፈጽሙ መቅጣት እንችላለን?” የሚል ጥያቄ አቅርበዋል። እውነት ነው፤ እንዲህ ማድረግ አንችልም። በደመ ነፍስ የሚንቀሳቀሱ እንስሳት ለሚያደርጉት ነገር ሥነ ምግባራዊ ተጠያቂነት የለባቸውም፤ ኮምፒውተሮችም በተገጠመላቸው ፕሮግራም መሠረት ለሚያከናውኑት ሥራ በኃላፊነት አይጠየቁም። እኛ ያገኘነው የፈለግነውን የመምረጥ ነፃነት ግን ከባድ ኃላፊነት የሚያስከትልብን ሲሆን ለምናደርጋቸው ነገሮችም ተጠያቂዎች ነን።

ይሖዋ ገና ከመወለዳችን በፊት በኋላ የምንፈጽመውን ድርጊት ቢወስንና ባደረግነው ነገር ተጠያቂ ቢያደርገን ኖሮ አፍቃሪና ፍትሐዊ አምላክ ነው ለማለት ይቸግር ነበር! እርሱ ግን ‘ፍቅር በመሆኑ’ እና ‘መንገዱ ሁሉ ትክክል’ ወይም ፍትሐዊ ስለሆነ እንዲህ አያደርግም። (1 ዮሐንስ 4:8፤ ዘዳግም 32:4) አምላክ በአንድ በኩል ነፃ ምርጫ ሰጥቶ በሌላ በኩል ደግሞ የሰው ዕድል አስቀድሞ እንደተወሰነ የሚያምኑ ሰዎች እንደሚሉት ‘ማንን እንደሚያድንና ማንን እንደሚያጠፋ አስቀድሞ’ ሊወስን አይችልም። ነፃ ምርጫና ዕድል አብረው ሊሄዱ አይችሉም።

መጽሐፍ ቅዱስ የምናደርጋቸው ምርጫዎች የወደፊት ዕጣችንን እንደሚወስኑት በግልጽ ይናገራል። ለምሳሌ አምላክ ለክፉ አድራጊዎች እንዲህ ብሏቸዋል:- “እንግዲህ ሁላችሁ ከክፉ መንገዳችሁና ከክፉ ሥራችሁ ተመለሱ፤ . . . እኔም ክፉ አላደርግባችሁም።” (ኤርምያስ 25:5, 6) አምላክ የእያንዳንዱን ሰው ዕጣ አስቀድሞ የሚወስን ከሆነ ይህን ማለቱ ምንም ትርጉም አይኖረውም። ከዚህም በተጨማሪ የአምላክ ቃል “እንግዲህ ኀጢአታችሁ እንዲደመሰስ ንስሓ ግቡ፤ ከመንገዳችሁም ተመለሱ፤ ከጌታም ዘንድ የመታደስ ዘመን ይመጣላችኋል” ይላል። (የሐዋርያት ሥራ 3:19) ይሖዋ የሰው ልጆች በጭራሽ ዕጣ ፈንታቸውን መቀየር እንደማይችሉ እያወቀ እንዴት ንስሐ እንዲገቡና እንዲመለሱ ይጠይቃል?

መጽሐፍ ቅዱስ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በሰማይ እንዲነግሡ አምላክ ስለጋበዛቸው ጥቂት ሰዎች ይናገራል። (ማቴዎስ 22:14፤ ሉቃስ 12:32) ነገር ግን እነዚህ ሰዎች እስከ መጨረሻው ካልጸኑ ይህን ድንቅ አጋጣሚ እንደሚያጡ ይገልጻል። (ራእይ 2:10) አምላክ ለቦታው እንደማይመርጣቸው አስቀድሞ ከወሰነ ቀድሞውንስ ቢሆን ይህን ግብዣ ለምን ያቀርባል? እንዲሁም ሐዋርያው ጳውሎስ ለእምነት ባልንጀሮቹ የተናገራቸውን ቃላት ልብ በል። “የእውነትን ዕውቀት ከተቀበልን በኋላ ሆን ብለን በኀጢአት ጸንተን ብንመላለስ፣ ከእንግዲህ ለኀጢአት የሚሆን ሌላ መሥዋዕት አይኖርም” ሲል ጽፏል። (ዕብራውያን 10:26) አምላክ የእነዚህን ሰዎች ዕድል አስቀድሞ ቢወስን ኖሮ እንዲህ ያለውን ማስጠንቀቂያ መስጠቱ ዋጋ ቢስ በሆነ ነበር። ይሁንና አምላክ ቢያንስ ቢያንስ አንዳንድ ግለሰቦች ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር እንዲገዙ አስቀድሞ አልወሰነም?

አስቀድመው የተወሰኑት በግለሰብ ደረጃ ነው ወይስ በቡድን?

ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ብሎ ጽፏል:- “በሰማያዊ ስፍራ በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ በክርስቶስ የባረከን [አምላክ] . . . ዓለም ከመፈጠሩ አስቀድሞ በእርሱ መርጦናልና። . . . በኢየሱስ ክርስቶስ ልጆቹ እንሆን ዘንድ . . . አስቀድሞ ወሰነን።” (ኤፌሶን 1:3-5) አምላክ አስቀድሞ የወሰነው ምንድን ነው? ጳውሎስ ‘ዓለም ከመፈጠሩ አስቀድሞ መርጦናል’ ሲል ምን ማለቱ ነበር?

ይህ ጥቅስ አምላክ ከመጀመሪያው ሰው ከአዳም ዘሮች መካከል ጥቂት ሰዎችን ከክርስቶስ ጋር በሰማይ እንዲገዙ እንደመረጠ ይገልጻል። (ሮሜ 8:14-17, 28-30፤ ራእይ 5:9, 10) ሆኖም ይሖዋ አምላክ ጥቂት ግለሰቦች ከመወለዳቸው በሺዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት ይህን መብት እንዲቀበሉ አስቀድሞ ወስኗል የሚለው ግምታዊ ሐሳብ የሰው ልጆች የፈለጉትን የመምረጥ ነፃነት ተሰጥቷቸዋል ከሚለው እውነት ጋር ይጋጫል። አምላክ አስቀድሞ የወሰነው በቡድን ደረጃ እንጂ ግለሰቦችን አይደለም።

ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል መንግሥት አንድ ድርጅት ለማቋቋም አቀደ እንበል። ድርጅቱ ምን እንደሚሠራ፣ ምን ያህል ሥልጣን እንደሚኖረውና ስፋቱን አስቀድሞ ይወስናል። ድርጅቱ ከተቋቋመ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሥራውን ጀመረ፤ ከዚያም የድርጅቱ አባላት የሚከተለውን መግለጫ አወጡ:- “መንግሥት ከዓመታት በፊት ምን መሥራት እንዳለብን ወስኖ ነበር። እንድንሠራው የሚጠበቅብንን ሥራ አሁን መሥራት ጀምረናል።” ከዚህ መግለጫ በመነሳት መንግሥት የድርጅቱ አባላት እነማን እንደሚሆኑ ከጥቂት ዓመታት በፊት በግለሰብ ደረጃ አስቀድሞ ወስኗል ብለህ ትደመድማለህ? እንደማትደመድም የተረጋገጠ ነው። በተመሳሳይ ይሖዋ የአዳም ኃጢአት ላስከተለው ችግር መፍትሔ የሚያመጣ ልዩ ድርጅት ለማቋቋም አስቀድሞ ወስኗል። እንዲሁም አንድ ቡድን በዚህ ድርጅት ውስጥ እንዲያገለግል አስቀድሞ የወሰነ ቢሆንም በግለሰብ ደረጃ ግን ምርጫ አላደረገም። የሚመረጡት ወደፊት የነበረ ሲሆን በመጨረሻ ተቀባይነት ማግኘታቸው ወይም አለማግኘታቸው የተመካው በሕይወታቸው ውስጥ በሚያደርጓቸው ምርጫዎች ላይ ነው።

ሐዋርያው ጳውሎስ “ዓለም ከመፈጠሩ አስቀድሞ በእርሱ መርጦናልና” ብሎ በጻፈበት ጊዜ በአእምሮው ይዞ የነበረው የትኛውን ዓለም ነው? እዚህ ላይ የጠቀሰው አምላክ አዳምና ሔዋንን በፈጠረበት ጊዜ የተገኘውን ዓለም አይደለም። ያ ዓለም ከኃጢአትና ከመጥፎ ሥነ ምግባር ነፃ የሆነ “እጅግ መልካም” ዓለም ነበር። (ዘፍጥረት 1:31) ስለዚህ የኃጢአት “ይቅርታ” ማግኘት አያስፈልገውም ነበር።—ኤፌሶን 1:7

ጳውሎስ የጠቀሰው፣ አዳምና ሔዋን በኤድን ገነት ውስጥ ካመጹ በኋላ የተፈጠረውንና አምላክ አስቦት ከነበረው በጣም የተለየ የሆነውን ዓለም ነው። ይህ ዓለም የተፈጠረው አዳምና ሔዋን ልጅ በወለዱ ጊዜ ሲሆን ከአምላክ የራቁ እንዲሁም የኃጢአትና የመጥፎ ሥነ ምግባር ባሪያ የሆኑ የሰው ልጆችን አቅፎ ይዟል። በተጨማሪም ዓለም የሚለው ቃል እንደ አዳምና ሔዋን በራሱ ፈቃድ ሳይሆን ሳይወድ በግዱ የኃጢአት ባሪያ በመሆኑ ምክንያት ቤዛ ሊከፈልለት የሚገባውን የሰው ዘር ያመለክታል።—ሮሜ 5:12፤ 8:18-21

ይሖዋ አምላክ በኤድን የተነሳው ዓመጽ ያስከተለውን ችግር ወዲያውኑ የመፍታት ችሎታ ነበረው። ይህን ማድረግ ባስፈለገው ጊዜ አንድ ልዩ ድርጅት ለማቋቋም ወዲያውኑ ወሰነ፤ ይህ ድርጅት በኢየሱስ ክርስቶስ የሚመራው መሲሐዊ መንግሥት ሲሆን ይሖዋ በዚህ መንግሥት አማካኝነት የሰው ዘሮችን ከአዳማዊ ኃጢአት ነፃ ከማውጣት ጋር የተያያዙ ነገሮችን ያከናውናል። (ማቴዎስ 6:10) አምላክ ይህን ያቀደው ቤዛ ሊከፈልለት የሚገባው የሰው ዘር “ዓለም ከመፈጠሩ አስቀድሞ” ማለትም ዓመጸኞቹ አዳምና ሔዋን ልጆች ከመውለዳቸው በፊት ነው።

ሰዎች ማድረግ የሚፈልጉትን ለማከናወን ብዙውን ጊዜ የሥራ ዕቅድ ማውጣት ያስፈልጋቸዋል። የዕድል ጽንሰ ሐሳብ አምላክ ጽንፈ ዓለምን ለመፍጠር አስቀድሞ ዝርዝር ዕቅድ አውጥቶ መሆን አለበት ከሚለው እምነት ጋር ተያያዥነት አለው። ሮይ ዌዘርፈርድ የተባሉት ደራሲ “በርካታ ፈላስፎች ባልተሟላ ዕቅድ የሚከናወን እያንዳንዱ ተግባር ከአምላክ ሉዓላዊ ገዥነት ጋር የሚቃረን ይመስላቸዋል” በማለት ጽፈዋል። በእርግጥ አምላክ ለማከናወን ላቀደው ነገር አስቀድሞ ዝርዝር ንድፍ ማውጣት ያስፈልገዋል?

ወሰን የሌለው ኃይልና አቻ የማይገኝለት ጥበብ ያለው ይሖዋ ፍጥረታቱ ነፃ ምርጫቸውን መጠቀማቸው ምንም ዓይነት ድንገተኛ ወይም ያልታሰበ ሁኔታ ቢያስከትል በተሳካ መንገድ ሊወጣው ይችላል። (ኢሳይያስ 40:25, 26፤ ሮሜ 11:33) ይህንንም አስቀድሞ ዝርዝር ዕቅድ ማውጣት ሳያስፈልገው በአንድ አፍታ ሊያከናውነው ይችላል። የአቅም ገደብ ካለባቸው ኃጢአተኛ የሰው ልጆች ፈጽሞ የተለየ የሆነው ሁሉን ቻይ አምላክ በምድር ላይ ለሚኖረው ለእያንዳንዱ ግለሰብ በዝርዝር የተቀመጠ ድርቅ ያለ ዕቅድ አስቀድሞ ማውጣት አያስፈልገውም። (ምሳሌ 19:21) በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች በኤፌሶን 3:11 ላይ እንደሚገልጹት አምላክ ዘላለማዊ ዓላማ እንጂ ድርቅ ያለ ደንብ የለውም።

በወደፊት ሕይወትህ ላይ ተጽዕኖ ልታደርግ የምትችለው እንዴት ነው?

አምላክ አስቀድሞ ለምድር ያወጣው ዓላማ አለው። ራእይ 21:3, 4 እንዲህ ይላል:- “እነሆ፤ የእግዚአብሔር ማደሪያ በሰዎች መካከል ነው፤ እርሱ ከእነርሱ ጋር ይኖራል፤ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ፤ እግዚአብሔር ራሱም ከእነርሱ ጋር ይኖራል፤ አምላካቸውም ይሆናል። እንባን ሁሉ ከዐይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት ወይም ሐዘን ወይም ልቅሶ ወይም ሥቃይ አይኖርም፤ የቀድሞው ሥርዐት ዐልፎአልና።” አዎን፣ ምድራችን በአምላክ የመጀመሪያ ዓላማ መሠረት ገነት ትሆናለች። (ዘፍጥረት 1:27, 28) አሁን የሚነሳው ጥያቄ ‘አንተስ በዚያ ትገኝ ይሆን?’ የሚለው ነው። ይህ የተመካው አሁን በምታደርገው ምርጫ ላይ ነው። ይሖዋ ዕጣ ፈንታህን አስቀድሞ አልወሰነም።

የአምላክ ልጅ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት የሚያምኑ ሁሉ የዘላለም ሕይወት ያገኛሉ። (ዮሐንስ 3:16, 17፤ የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35) መጽሐፍ ቅዱስ “በወልድ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት አለው፤ በወልድ የማያምን ግን . . . ሕይወትን አያይም” ይላል። (ዮሐንስ 3:36) ስለ አምላክ፣ ስለ ልጁና ስለ አምላክ ፈቃድ ከመጽሐፍ ቅዱስ በመማር እንዲሁም የተማርከውን በሥራ ላይ በማዋል ሕይወትን መምረጥ ትችላለህ። በአምላክ ቃል ውስጥ በሚገኘው እውነተኛ ጥበብ የሚመራ ሰው “በሰላም ይኖራል፤ ክፉን ሳይፈራ ያለ ሥጋት ይቀመጣል” የሚል ማረጋገጫ ተሰጥቶታል።—ምሳሌ 1:20, 33

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሰዎች ከእንስሳት በተለየ መልኩ ለሚፈጽሟቸው ድርጊቶች ሥነ ምግባራዊ ተጠያቂነት አለባቸው

[ምንጭ]

ንስር:- ፎቶ: Cortesía de GREFA