በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሕይወትህ ምን ያህል ውድ ነው?

ሕይወትህ ምን ያህል ውድ ነው?

ሕይወትህ ምን ያህል ውድ ነው?

 በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በአውሮፓ ቁጥር ስፍር የሌለው ሕይወት እየረገፈ በነበረበት ጊዜ በአንታርክቲካ አህጉር አስደናቂ የሆነ ሕይወት አድን ተግባር እየተከናወነ ነበር። ኧርነስት ሻክልተን የተባለ ብሪታኒያዊ አሳሽና አብረውት የነበሩ ተጓዦች ኢንዱራንስ የተባለችው መርከባቸው ተሰብራ በበረዶ ግግር ውስጥ በመቀርቀሯ ከባድ ችግር ገጠማቸው። ሻክልተን በእርሱ መሪነት ይጓዙ የነበሩት ሰዎች በአንጻራዊ ሁኔታ ሻል ወዳለውና በደቡብ አትላንቲክ ውቅያኖስ ላይ ወደሚገኘው ኤሌፋንት ደሴት መድረስ እንዲችሉ አደረገ። ሆኖም ገና ከባድ ችግር ይጠብቃቸው ነበር።

ሻክልተን፣ በደቡብ ጆርጂያ ደሴት ላይ ወደሚገኘው የዓሣ ነባሪ ማስገሪያ ጣቢያ ጥቂት ሰዎች ልኮ እርዳታ ካላገኙ በስተቀር የመትረፍ ተስፋ እንደማይኖራቸው ተገንዝቦ ነበር። ደቡብ ጆርጂያ የተባለው ደሴት ካሉበት ቦታ 1,100 ኪሎ ሜትር ርቆ የሚገኝ ሲሆን የሚጓዙት ኢንዱራንስ ከተባለችው መርከብ ላይ በወሰዱት 7 ሜትር ርዝመት ባለው ሕይወት አድን ጀልባ ነበር። ተስፋቸው በጣም የመነመነ ነበር።

ይሁን እንጂ ለአሥራ ሰባት ቀናት በጣም አስቸጋሪ ጉዞ ካደረጉ በኋላ ግንቦት 10, 1916 ሻክልተንና አብረውት የነበሩት ጥቂት ሰዎች ደቡብ ጆርጂያ ደረሱ፤ ነገር ግን ምቹ ያልነበረው የባሕሩ ሁኔታ በተቃራኒ አቅጣጫ እንዲወርዱ አስገደዳቸው። ወደሚፈልጉበት ቦታ ለመድረስ በበረዶ በተሸፈኑ ተራሮች ላይ 30 ኪሎ ሜትር ያህል መጓዝ ነበረባቸው። በጣም ኃይለኛው ቅዝቃዜም ሆነ ተራራ ለመውጣት የሚያገለግሉ መሣሪያዎች አለመያዛቸው ሻክልተን እና አብረውት የነበሩት ሰዎች ወዳሰቡበት ቦታ ከመድረስ አላገዷቸውም። በኋላም ሻክልተን ተመልሶ ከኤሌፋንት ደሴት መንቀሳቀስ ያልቻሉትን የተቀሩትን የቡድኑን አባላት ሕይወት ለማትረፍ ቻለ። ይሁንና ሻክልተን ይህን ያህል ትልቅ ጥረት ያደረገው ለምንድን ነው? “ትልቁ ምኞቱ አብረውት ከነበሩት ሰዎች የአንዱም ሕይወት እንዳይጠፋ” እንደነበር ታሪክ ጸሐፊው ሮለንድ ኸንትፎርድ ዘግበዋል።

“አንዳቸውም አይጠፉም”

ሰዎቹ “ከጫፍ እስከ ጫፍ 30 ኪሎ ሜትር በሚሸፍነው፣ ለመድረስ አስቸጋሪ በሆነው እንዲሁም ባገጠጠ ንብርብር አለትና በበረዶ በተሸፈነው ቦታ” ላይ ተስፋ ሳይቆርጡ ተኮራምተው ሻክልተንን እንዲጠባበቁት የረዳቸው ምንድን ነው? መሪያቸው ሕይወታቸውን ለማዳን የገባውን ቃል እንደሚፈጽም በመተማመናቸው ነው።

በዛሬው ጊዜ የሰው ልጅ በኤሌፋንት ደሴት ላይ በአደገኛና ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ውስጥ ሆነው መሪያቸውን ሲጠብቁ ከቆዩት ሰዎች ጋር ይመሳሰላል። በርካታ ሰዎች በከፋ ድህነት እየማቀቁ ሲሆን በሕይወት ለመቆየት ያህል ብቻ ብርቱ ትግል ያደርጋሉ። ሆኖም እነዚህ ሰዎች አምላክ በጭቆናና በችግር ‘የሚሠቃዩትን እንደሚያድን’ ሙሉ በሙሉ ሊተማመኑ ይችላሉ። (ኢዮብ 36:15) የእያንዳንዱ ሰው ሕይወት በአምላክ ዓይን ውድ መሆኑን አትጠራጠር። ፈጣሪያችን ይሖዋ አምላክ “በመከራ ጊዜ ወደ እኔ ጩህ፤ አድንሃለሁ” ብሏል።—መዝሙር 50:15

ፈጣሪ በምድር ላይ ካሉት በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መካከል አንተን በግል ውድ አድርጎ እንደሚመለከትህ አምኖ መቀበሉ ከብዶሃል? እንግዲያው ነቢዩ ኢሳይያስ ዳርቻ በሌለው አጽናፈ ዓለም ውስጥ ባሉ በቢሊዮን በሚቆጠሩ ጋላክሲዎች ውስጥ የሚገኙትን በቢሊዮን የሚቆጠሩ ከዋክብት በተመለከተ ምን እንደጻፈ ልብ በል። ጥቅሱ እንዲህ ይላል:- “ዐይናችሁን አንሡ፤ ወደ ሰማይ ተመልከቱ፤ እነዚህን ሁሉ የፈጠረ ማን ነው? የከዋክብትን ሰራዊት አንድ በአንድ የሚያወጣቸው፣ በየስማቸው የሚጠራቸው እርሱ ነው። ከኀይሉ ታላቅነትና ከችሎታው ብርታት የተነሣ፣ አንዳቸውም አይጠፉም።”—ኢሳይያስ 40:26

ይህ ምን ማለት እንደሆነ ገብቶሃል? የእኛን ሥርዓተ ፀሐይ በያዘው ፍኖተ ሐሊብ በሚባለው ጋላክሲ ውስጥ ብቻ እንኳ ቢያንስ 100 ቢሊዮን ከዋክብት ይገኛሉ። በጽንፈ ዓለም ውስጥ ምን ያህል ጋላክሲዎች አሉ? ማንም በእርግጠኝነት ሊናገር ባይችልም አንዳንዶች ቁጥሩ 125 ቢሊዮን ሊደርስ እንደሚችል ይገምታሉ። ከዋክብት እንዴት ያለ አስደናቂ ብዛት አላቸው! ነገር ግን ፈጣሪ እያንዳንዳቸውን በስማቸው እንደሚጠራቸው መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል።

‘የራስ ጠጉራችሁ አንድ ሳይቀር የተቆጠረ ነው’

ምናልባት አንዳንዶች ‘ግን እኮ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ከዋክብትን ወይም ሰዎችን በስም ማወቁ ብቻ በግል እንደሚያስብላቸው ያሳያል ለማለት አያስችልም’ ብለው የተቃውሞ ሐሳብ ያቀርቡ ይሆናል። በርካታ ነገሮችን የማስታወስ ችሎታ ያለው ኮምፒውተር እንኳን በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ስም መዝግቦ መያዝ ይችላል። ይሁንና ማንም ሰው ቢሆን ኮምፒውተር ያስብልኛል ብሎ አይጠብቅም። ነገር ግን ይሖዋ አምላክ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ስም ማወቅ ብቻ ሳይሆን በግለሰብ ደረጃ እንደሚያስብላቸው መጽሐፍ ቅዱስ ያሳያል። ሐዋርያው ጴጥሮስ “እርሱ ስለ እናንተ ስለሚያስብ የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት” በማለት ጽፏል።—1 ጴጥሮስ 5:7

ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ብሎ ተናግሯል:- “በአንድ ሳንቲም ከሚሸጡት ሁለት ድንቢጦች አንዲቷ እንኳ ያለ አባታችሁ ፈቃድ ምድር ላይ አትወድቅም። የራስ ጠጉራችሁ እንኳ አንድ ሳይቀር የተቆጠረ ነው። ስለዚህ አትፍሩ፤ ከብዙ ድንቢጦች ይልቅ ዋጋችሁ የከበረ ነው።” (ማቴዎስ 10:29-31) ኢየሱስ ድንቢጦችና ሰዎች የሚያጋጥማቸውን ነገር አምላክ በንቃት ይከታተላል ብቻ እንዳላለ ልብ በል። “ከብዙ ድንቢጦች ይልቅ ዋጋችሁ የከበረ ነው” ብሏል። ከብዙ ድንቢጦች ይልቅ ክቡር የሆንከው ለምንድን ነው? ምክንያቱም የማሰብ ችሎታ እንዲኖርህ፣ መልካም ሥነ ምግባርንና መንፈሳዊ ባሕርያትን እያዳበርክና እየተገበርክ መሄድ እንድትችል ሆነህ “በእግዚአብሔር መልክ” በመፈጠርህ ነው።—ዘፍጥረት 1:26, 27

“የማሰብ ችሎታ ያለው አካል የሥራ ውጤት”

ፈጣሪ መኖሩን የሚክዱ ሰዎች በሚናገሩት ሐሳብ እንዳትሳሳት ተጠንቀቅ። እነዚህ ሰዎች የማሰብ ችሎታ በሌለው የተፈጥሮ ኃይል እንደተፈጠርክ ይናገራሉ። “በእግዚአብሔር መልክ” የተፈጠርክ ሳትሆን ድንቢጦችን ጨምሮ በዚህ ምድር ላይ ካሉት ከማናቸውም ሌሎች እንስሳት ምንም የማትለይ ፍጡር እንደሆንህ ይናገራሉ።

ሕይወት የተገኘው እንዲያው በአጋጣሚ ወይም ደግሞ የማሰብ ችሎታ በሌለው ኃይል ነው የሚለው ሐሳብ ይዋጥልሃል? ማይክል ጄ ቢሂ የተባሉ ባዮሎጂስት እንደተናገሩት ለሕይወት መሠረት የሆኑት “በጣም ውስብስብ ባዮኬሚካላዊ ሂደቶች” ይህን ሐሳብ ሙሉ በሙሉ መሠረተ ቢስ ያደርጉታል። እንዲሁም ሳይንሳዊው ማስረጃ “በምድር ላይ የሚገኘው ሕይወት ከጅምሩ አንስቶም ቢሆን . . . የማሰብ ችሎታ ያለው አካል የሥራ ውጤት ነው” ወደሚለው እርግጠኛ መደምደሚያ እንደሚያደርሰን ተናግረዋል።—ዳርዊንስ ብላክ ቦክስ—ዘ ባዮኬሚካል ቻሌንጅ ቱ ኢቮሉሽን

መጽሐፍ ቅዱስ በዚህች ምድር በማንኛውም ደረጃ ላይ የሚገኘው ሕይወት የማሰብ ችሎታ ያለው አካል የሥራ ውጤት እንደሆነ ይነግረናል። እንዲሁም የእነዚህ ድንቅ የሥራ ውጤቶች ሁሉ ምንጭ የጽንፈ ዓለሙ ፈጣሪ ይሖዋ አምላክ እንደሆነ ይገልጻል።—መዝሙር 36:9፤ ራእይ 4:11

ችግርና ሥቃይ በተሞላ ዓለም ውስጥ መኖራችን ምድርን እንዲሁም በላይዋ ላይ ያለውን ሕይወት ሁሉ የፈጠረና ንድፍ ያወጣ አምላክ መኖሩን እንድንክድ ሊያደርገን እንደማይገባ ማስታወስ ይኖርብሃል። ሁለት መሠረታዊ እውነቶችን አስታውስ። አንደኛው፣ አምላክ አለፍጽምና በውስጣችን እንዲኖር እቅድ አልነበረውም። ሌላው ደግሞ ፈጣሪያችን አለፍጽምና ለጊዜው እንዲኖር የፈቀደበት በቂ ምክንያት አለው። ይህ መጽሔት በተደጋጋሚ ሲገልጽ እንደነበረው ይሖዋ አምላክ ክፋትን ዝም ብሎ የሚመለከተው ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ነው፤ ዓላማውም የሰው ልጆች ለመጀመሪያ ጊዜ ለአምላክ ሉዓላዊነት ለመገዛት አሻፈረን ባሉበት ወቅት ለተነሱት ሥነ ምግባር ነክ ጥያቄዎች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እልባት ማስገኘት ነው። aዘፍጥረት 3:1-7፤ ዘዳግም 32:4, 5፤ መክብብ 7:29፤ 2 ጴጥሮስ 3:8, 9

‘ችግረኛው በጮኸ ጊዜ ይታደገዋል’

በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች የመከራ ኑሮ መግፋት ግድ ቢሆንባቸውም ሕይወት አሁንም ድንቅ ስጦታ ነው። በመሆኑም ሕይወታችንን ለመጠበቅ የተቻለንን ጥረት ማድረግ አለብን። አምላክ ወደፊት ሊሰጠን ቃል የገባልን ሕይወት ልክ በኤሌፋንት ደሴት ላይ ሻክልተንን ሲጠባበቁ እንደነበሩት ሰዎች፣ እንዲያው ለመቆየት ያህል ትግል የሚደረግበት በችግርና በሰቆቃ የተሞላ አይደለም። የአምላክ ዓላማ እኛን በአሁኑ ጊዜ ካለው ሥቃይና የዋጋ ቢስነት ስሜት በመገላገል ለሰብዓዊ ፍጥረታቱ መጀመሪያ ሊሰጣቸው ያሰበውን ‘እውነተኛውን ሕይወት እንድናገኝ’ ነው።—1 ጢሞቴዎስ 6:19

አምላክ ይህንን ሁሉ የሚያደርገው እያንዳንዳችንን ውድ አድርጎ ስለሚመለከተን ነው። አምላክ እኛን ከመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ከአዳምና ከሔዋን ከወረስነው ኃጢአት፣ አለፍጽምናና ሞት ነጻ ለማውጣት ሲል ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ሆኖ እንዲቀርብ አድርጓል። (ማቴዎስ 20:28) “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው . . . እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስከ መስጠት ድረስ ዓለምን እንዲሁ ወዶአልና” በማለት ኢየሱስ ክርስቶስ ተናግሯል።—ዮሐንስ 3:16

አምላክ እየተሰቃዩና እየተጨቆኑ ለሚኖሩ ሰዎች ምን ያደርግላቸዋል? በመንፈሱ አነሳሽነት የተጻፈው ቃሉ ልጁን በተመለከተ እንዲህ ይለናል:- “ችግረኛው በጮኸ ጊዜ፣ ምስኪኑንና ረዳት የሌለውን ይታደገዋል። ለድኾችና ለችግረኞች ይራራል፤ ምስኪኖችንም ከሞት ያድናል። ሕይወታቸውን ከጭቆናና ከግፍ ያድናል።” አምላክ እንዲህ የሚያደርገው ለምንድን ነው? “ደማቸውም [ወይም ሕይወታቸው] በእርሱ ፊት ክቡር ” ስለሆነ ነው።—መዝሙር 72:12-14

የሰው ልጅ ለበርካታ መቶ ዘመናት በኃጢአትና በአለፍጽምና ምክንያት ሲማቅቅ እንዲሁም በብዙ ሥቃይና ችግር ‘ሲቃትት’ ኖሯል። አምላክ ይህ እንዲሆን የፈቀደው ችግሩ የሚያስከትለውን ጥፋት ማስተካከል እንደሚችል ስለሚያውቅ ነው። (ሮሜ 8:18-22) አምላክ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ንጉሥ በሆነበት መንግሥቱ በኩል በቅርቡ ‘ሁሉን ነገር ያድሳል።’—የሐዋርያት ሥራ 3:21፤ ማቴዎስ 6:9, 10

ይህም ባለፉት ዘመናት ሥቃይ የደረሰባቸውን በሞት ያንቀላፉ ሰዎችን ማስነሳትን ይጨምራል። እነዚህን ሙታን አምላክ አይረሳቸውም። (ዮሐንስ 5:28, 29፤ የሐዋርያት ሥራ 24:15) በቅርቡ በገነት ውስጥ ከችግርና ከሥቃይ የጸዳ ‘የተትረፈረፈ’ ፍጹም ሕይወት ይሰጣቸዋል። (ዮሐንስ 10:10፤ ራእይ 21:3-5) በዚያን ጊዜ የሚኖር ሰው ሁሉ የተሟላ ሕይወት በማግኘት የሚደሰት ከመሆኑም በላይ “በእግዚአብሔር መልክ” የተፈጠረ መሆኑን የሚያንጸባርቁ ድንቅ ባሕርያትንና ችሎታዎችን ያዳብራል።

አንተስ ይሖዋ ቃል በገባው አስደሳች ጊዜ በሕይወት ትኖር ይሆን? ምርጫው ለአንተ የተተወ ነው። አምላክ እነዚህን በረከቶች ሁሉ ለማምጣት ካደረገው ዝግጅት እንድትጠቀም እናበረታታሃለን። የዚህ መጽሔት አዘጋጆች ይህን ማድረግ እንድትችል ሊረዱህ ፈቃደኞች ናቸው።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ስለዚህ ነጥብ ዝርዝር ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች በተዘጋጀው ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተባለ መጽሐፍ ምዕራፍ 8 ላይ የሚገኘውን “አምላክ ሥቃይና መከራ እንዲኖር ለምን ፈቀደ?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ካሉበት መንቀሳቀስ ያልቻሉት ሰዎች ሻክልተን ሕይወታቸውን ለማዳን የገባውን ቃል እንደሚፈጽም እምነት ነበራቸው

[ምንጭ]

© CORBIS

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ከብዙ ድንቢጦች ይልቅ ዋጋችሁ የከበረ ነው”