በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሕይወት ውድ ነው ወይስ ርካሽ?

ሕይወት ውድ ነው ወይስ ርካሽ?

ሕይወት ውድ ነው ወይስ ርካሽ?

“የሰው ልጅ የተፈጠረው በአምላክ መልክ በመሆኑ ሰውን መግደል የምድራችንን እጅግ ክቡርና ቅዱስ የሆነ ነገር ማጥፋት ነው።”—ዘ ፕሌይን ማንስ ጋይድ ቱ ኤቲክስ፣ በዊልያም ባርክሌይ የተዘጋጀ

 ‘የምድራችን እጅግ ክቡር ነገር።’ አንተስ ለሕይወት እንዲህ ያለ አመለካከት አለህ? የሰዎችን አድራጎት በመመልከት ብዙዎች ከላይ በተጠቀሱት ደራሲ ሐሳብ እንደማይስማሙ በግልጽ ለመረዳት ይቻላል። ስለ ሌላው ደኅንነት ምንም ደንታ የሌላቸው ዓመጸኛ ሰዎች የራስ ወዳድነት ፍላጎታቸውን ለማሳካት ሲሉ የበርካታ ሰዎችን ሕይወት በጭካኔ ይቀጥፋሉ።—መክብብ 8:9

አንዳንዶች የሰውን ሕይወት ከአሮጌ እቃ ለይተው አያዩትም

አንደኛው የዓለም ጦርነት ለዚህ ዓይነተኛ ምሳሌ ይሆነናል። ታሪክ ጸሐፊው አላን ጆን ቴይለር እንደገለጹት ይህ አሰቃቂ ጦርነት ተጀምሮ እስከሚያልቅ ድረስ “የሰዎች ሕይወት በከንቱ ተሰውቷል።” የጦር አዛዦች ወታደሮቻቸው ዋጋ ቢስና ምንም እርባና የሌላቸው ይመስል ክብርና ዝና የማግኘት ፍላጎታቸውን ለማሳካት ተጠቅመውባቸዋል። ፈረንሳይ ውስጥ ቨርዳን የምትባለውን ከተማ ለመያዝ ተደርጎ በነበረው ጦርነት ላይ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች ቆስለዋል ወይም ሞተዋል። ቴይለር “በዚህ ጦርነት ላይ ሰዎች ከመሞታቸውና ድል አድራጊው ወገን ክብር ከማግኘቱ በስተቀር ውጊያው ለሁለቱም ወገኖች [ምንም ዓይነት ወታደራዊ ጠቀሜታ] አላስገኘም” በማለት ጽፈዋል።—ዘ ፈርስት ወርልድ ዎር

እንዲህ ያለው ሕይወትን እንደ ርካሽ ነገር የመመልከት አዝማሚያ አሁንም ድረስ በስፋት ይታያል። ኬቨን ቤልዝ የተባሉ ምሑር እንደጠቆሙት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ “የሕዝብ ብዛት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ ዓለማችን ድሃ በሆነና ለጥቃት በተጋለጠ ሠራተኛ ኃይል እንድትጥለቀለቅ ምክንያት ሆኗል።” እነዚህ ሰዎች “ሕይወት በረከሰበት” ጨቋኝ የንግድ ሥርዓት ውስጥ ሕይወታቸውን

ለማቆየት ዕድሜ ልካቸውን ደፋ ቀና ይላሉ። ምሑሩ ቤልዝ በዝባዦቹ የሚበዘብዟቸውን ሰዎች ከባሪያ ለይተው እንደማያዩአቸው ይኸውም “ገንዘብ ለማግኘት ከተጠቀሙባቸው በኋላ እንደሚጣሉ እቃዎች” እንደሚቆጥሯቸው ተናግረዋል።—ዲስፖዘብል ፒፕል

‘ነፋስን እንደ መከተል ነው’

በርካታ ሰዎች ሕይወታቸው ዋጋ ቢስ እንደሆነ እንዲሰማቸው የሚያደርጓቸውና ተስፋ የሚያስቆርጧቸው ሌሎች ብዙ ምክንያቶች አሉ፤ ብዙዎች ይኑሩ ይሙቱ ማንም ደንታ አይሰጠውም። ከጦርነትና ከፍትሕ መጓደል ባሻገር ድርቅ፣ ረሃብ፣ በሽታ፣ የሚወዱትን ሰው በሞት መነጠቅና ሌሎች ቁጥር ስፍር የሌላቸው ችግሮች መላውን የሰው ልጅ አስጨንቀውታል። እንዲሁም ‘መኖር ምን ዋጋ አለው?’ እንዲል አድርገውታል።—መክብብ 1:8, 14

እርግጥ ነው፣ በሕይወታቸው ውስጥ ከመጠን በላይ ችግር የሚያጋጥማቸውና የሚጨነቁት ሁሉም ሰዎች አይደሉም። ነገር ግን ብዙም የኑሮ ጭንቀት የሌለባቸው በርካታ ሰዎች የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ ሰሎሞን አንስቶት በነበረው ጥያቄ ይስማማሉ:- “ሰው ከፀሓይ በታች በሚደክምበት ጥረትና ልፋት ሁሉ ትርፉ ምንድን ነው?” ብዙዎች ነገሩን በጥልቅ ካሰቡበት በኋላ ሲያደርጉ የቆዩት ነገር “ከንቱ፣ ነፋስንም እንደ መከተል” እንደሆነ ተገንዝበዋል።—መክብብ 2:22, 26

በርካታ ሰዎች ያሳለፉትን ሕይወት መለስ ብለው ይመለከቱና “በቃ? ሕይወት ማለት ይሄ ነው?” በማለት ይጠይቃሉ። በእውነት እንደ አብርሃም ‘ዕድሜ እንደጠገቡ’ የሚሰማቸው ምን ያህል ሰዎች ናቸው? (ዘፍጥረት 25:8) ብዙዎች ለረጅም ጊዜያት የሚዘልቅ የዋጋ ቢስነት ስሜት ይሰማቸዋል። ሆኖም ሕይወት ከንቱ አይደለም። አምላክ የእያንዳንዱን ሰው ሕይወት ውድ አድርጎ የሚመለከት ከመሆኑም በላይ ሁላችንም የተሟላና አርኪ የሆነ እውነተኛ ሕይወት እንድንመራ ይፈልጋል። ይህ እንዴት ሊፈጸም ይችላል? እስቲ በዚህ ጉዳይ ላይ የሚቀጥለው ርዕስ ምን ሐሳብ እንደሚሰጥ ተመልከት።