በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በዛሬው ጊዜ “እጅግ ውድ የሆነ ዕንቊ” ለማግኘት የተደረገ ጥረት

በዛሬው ጊዜ “እጅግ ውድ የሆነ ዕንቊ” ለማግኘት የተደረገ ጥረት

በዛሬው ጊዜ “እጅግ ውድ የሆነ ዕንቊ” ለማግኘት የተደረገ ጥረት

“ለሕዝብ ሁሉ ምስክር እንዲሆን፣ ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል።”—ማቴዎስ 24:14

1, 2. (ሀ) በኢየሱስ ዘመን የነበሩ አይሁዳውያን ስለ አምላክ መንግሥት የነበራቸው ግንዛቤ ምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት በትክክል እንዲገባቸው ምን አድርጓል? ውጤቱስ ምን ነበር?

 ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት የአምላክ መንግሥት በእስራኤላውያን ዘንድ ዓቢይ የመነጋገሪያ ርዕስ ሆኖ ነበር። (ማቴዎስ 3:1, 2፤ 4:23-25፤ ዮሐንስ 1:49) መጀመሪያ ላይ ግን አብዛኞቹ ሰዎች ግዛቱ ምን ያህል ስፋት እንደሚኖረውና ምን ዓይነት አገዛዝ እንደሚሆን እንዲሁም በሰማይ ያለ መስተዳደር መሆኑን በሚገባ አልተረዱም ነበር። (ዮሐንስ 3:1-5) አንዳንድ የኢየሱስ ተከታዮች እንኳ ሳይቀሩ የአምላክ መንግሥት ሲባል ምን ማለት እንደሆነና ከክርስቶስ ጋር ተባባሪ ገዥዎች የመሆን መብት ለማግኘት ምን ማድረግ እንዳለባቸው በትክክል አልገባቸውም ነበር።—ማቴዎስ 20:20-22፤ ሉቃስ 19:11፤ የሐዋርያት ሥራ 1:6

2 በጊዜ ሂደት ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ በፊተኛው ርዕስ ላይ የተመለከትነውን እጅግ ውድ ስለሆነ ዕንቁ የሚናገረውን ምሳሌ ጨምሮ ብዙ ትምህርቶች በማስተማር መንግሥተ ሰማይን ለመውረስ ከፍተኛ ተጋድሎ ማድረግ እንዳለባቸው ገለጸላቸው። (ማቴዎስ 6:33፤ 13:45, 46፤ ሉቃስ 13:23, 24) የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ በሰፊው እንደሚያሳየው በአጭር ጊዜ ውስጥ ትጉና ደፋር የመንግሥቱ ምሥራች አዋጅ ነጋሪዎች በመሆን መልእክቱን እስከ ምድር ዳር ድረስ በማሰራጨታቸው ትምህርቱ ልባቸውን በጥልቅ እንደነካው መረዳት ይቻላል።—የሐዋርያት ሥራ 1:8፤ ቈላስይስ 1:23

3. ኢየሱስ የእኛን ዘመን አስመልክቶ ስለ አምላክ መንግሥት ምን ብሏል?

3 ዛሬስ ሁኔታው ምን ይመስላል? በአምላክ መንግሥት ሥር ምድር ገነት ስትሆን የሚኖረው አስደሳች ሕይወት በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች እየተሰበከ ነው። ኢየሱስ ‘ስለ ዓለም መጨረሻ’ በተናገረው ትንቢት ላይ “ለሕዝብ ሁሉ ምስክር እንዲሆን፣ ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል” በማለት በግልጽ ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:3, 14፤ ማርቆስ 13:10) ከዚህ በተጨማሪ ይህ መጠነ ሰፊ ሥራ የሚከናወነው ከፍተኛ እንቅፋትና ፈተና ብሎም ስደት እያለ እንደሆነ ገልጿል። ይሁን እንጂ “እስከ መጨረሻ የሚጸና . . . እርሱ ይድናል” የሚል ዋስትና ሰጥቷል። (ማቴዎስ 24:9-13) ይህ ሁሉ ነገር ኢየሱስ በተናገረው ምሳሌ ውስጥ የተጠቀሰው ነጋዴ ያሳየው ዓይነት የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስና የዓላማ ጽናት ይጠይቃል። በዛሬው ጊዜ መንግሥቱን ለማግኘት እንዲህ ዓይነት እምነትና ቅንዓት የሚያሳዩ ግለሰቦች ይገኛሉ?

እውነትን ማወቅ የሚያስገኘው ደስታ

4. የመንግሥቱ እውነት በዛሬው ጊዜ ሰዎችን ምን የማድረግ ኃይል አለው?

4 ኢየሱስ በተናገረው ምሳሌ ውስጥ የተጠቀሰው ነጋዴ “እጅግ ውድ የሆነ ዕንቊ” ሲያገኝ በጣም ተደስቶ ነበር። እንዲያውም እጅግ ከመደሰቱ የተነሳ ዕንቁውን እጁ ለማስገባት ሲል የሚቻለውን ሁሉ አድርጓል። (ዕብራውያን 12:1) ዛሬም ቢሆን ስለ አምላክና ስለ መንግሥቱ የሚነገረው እውነት ሰዎችን ይማርካቸዋል እንዲሁም ለተግባር ያነሳሳቸዋል። ይህ ደግሞ ወንድም አሌክሳንደር ማክሚላን ስለ አምላክና እርሱ ለሰው ልጆች ስላለው ዓላማ ለማወቅ ያደረገውን ጥረት በሚመለከት ፌዝ ኦን ዘ ማርች በተባለው መጽሐፉ ላይ ያሰፈረውን ሐሳብ ያስታውሰናል:- “እኔ ያገኘሁትን ነገር በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በማግኘት ላይ ናቸው። እነዚህ ሰዎች ደግሞ ከተለያየ ብሔር፣ ዘር፣ የኑሮ ደረጃና ዕድሜ የተውጣጡ በመሆናቸው እንደ እኔና እንደ እናንተ ያሉ ሰዎች ናቸው። እውነት ከሰው ሰው አይለይም። ሁሉንም ዓይነት ሰዎች ይስባል።”

5. የ2004 የአገልግሎት ዓመት ሪፖርት እንደሚያሳየው ምን ግሩም ውጤት ተገኝቷል?

5 በየዓመቱ ቅን ልብ ያላቸው በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ስለ አምላክ መንግሥት ምሥራች ሰምተው ሕይወታቸውን ለይሖዋ ለመወሰንና ፈቃዱን ለማድረግ መነሳሳታቸው የዚህን አባባል እውነተኝነት ያረጋግጣል። በመስከረም 2003 ጀምሮ በነሐሴ 2004 የተደመደመው የ2004 የአገልግሎት ዓመትም ቢሆን ተመሳሳይ ውጤት ተገኝቶበታል። በእነዚያ 12 ወራት ውስጥ 262,416 ሰዎች በሕዝብ ፊት በውኃ በመጠመቅ ራሳቸውን ለይሖዋ መወሰናቸውን አሳይተዋል። ይህ የተከናወነው በ235 አገሮች ውስጥ ሲሆን የይሖዋ ምሥክሮች በእነዚህ አገሮች ውስጥ የተለያየ የኑሮ ሁኔታ ያላቸው ከሕዝብ፣ ከነገድና ከቋንቋ የተውጣጡ 6,085,387 የሚያህሉ ሰዎች በአምላክ ቃል ውስጥ የሠፈረውንና ሕይወት የሚያሰጠውን እውነት እንዲያገኙ ለመርዳት በየሳምንቱ መጽሐፍ ቅዱስን በማስጠናት ላይ ይገኛሉ።—ራእይ 7:9

6. ባለፉት ዓመታት ቀጣይ እድገት እንዲኖር ያስቻለው ምንድን ነው?

6 ይህ እድገት እንዴት ሊገኝ ቻለ? ይሖዋ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸውን እነዚህን ሰዎች ወደ ራሱ እንደሳባቸው ምንም ጥያቄ የለውም። (ዮሐንስ 6:65፤ የሐዋርያት ሥራ 13:48) ይሁንና መንግሥቱን ለመውረስ በሚያደርጉት ጥረት ራሳቸውን ምንም ሳይቆጥቡ ያቀረቡና ያለ አንዳች መታከት በሥራው የተሳተፉ ክርስቲያኖች ያከናወኑት ተግባር ሳይጠቀስ የሚታለፍ አይደለም። ወንድም ማክሚላን በ79 ዓመት ዕድሜው እንዲህ ሲል ጽፎ ነበር:- “ታማሚና ሟች ለሆነው የሰው ዘር የተዘረጋለትን ተስፋ መጀመሪያ ከሰማሁበት ጊዜ አንስቶ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኘው በዚህ ትምህርት ላይ ያለኝ እምነት ፈጽሞ አልተዳከመም። ከዚያን ጊዜ አንስቶ ሁሉን ቻይ ስለሆነው ስለ ይሖዋ አምላክና ለሰው ልጆች ስላለው በጎ ዓላማ እንደ እኔ ማወቅ ለሚፈልጉ ሰዎች መንገር እንድችል መጽሐፍ ቅዱስ ስለሚያስተምረው ነገር ይበልጥ ለማወቅ ቆርጬ ተነሳሁ።”

7. የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ያገኙ ሰዎች የሚሰማቸውን ደስታና ጉጉት የሚያሳየው የትኛው ተሞክሮ ነው?

7 በዛሬው ጊዜ ባሉ የይሖዋ ምሥክሮችም ዘንድ ተመሳሳይ ግለት ይታያል። ለምሳሌ ያህል በኦስትሪያ፣ ቬይና የምትኖረውን የዳንየላን ተሞክሮ ተመልከት። እንዲህ ትላለች:- “ከልጅነቴ አንስቶ አምላክ የቅርብ ወዳጄ ሆኖ ቆይቷል። ‘አምላክ’ የሚለው ስም ፈጣሪ እውን ሆኖ እንዲታየኝ ስለማያደርግ ስሙን የማወቅ ጉጉት ነበረኝ። ይሁንና በ17 ዓመቴ የይሖዋ ምሥክሮች ቤታችን እስከመጡበት ጊዜ ድረስ ስሙን ሳላውቅ ቆየሁ። ከእነርሱ ጋር ከተገናኘሁ በኋላ ስለ አምላክ ማወቅ የምፈልገውን ነገር ሁሉ ነገሩኝ። በመጨረሻ እውነትን አገኘሁ፤ እውነትን ማወቅ በጣም ያስደስታል! እንዲያውም ከደስታዬ የተነሳ ላገኘሁት ሰው ሁሉ መስበክ ጀመርኩ።” ዳንየላ በጋለ ስሜት መስበኳ ብዙም ሳይቆይ ከትምህርት ቤት ጓደኞቿ ፌዝ አስከተለባት። በመቀጠል እንዲህ ትላለች:- “እኔ ግን ኢየሱስ ተከታዮቹ ለስሙ ሲሉ እንደሚጠሉና እንደሚሰደዱ እንደተናገረ ቀደም ብዬ ስለተማርኩ ነገሩን የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜ አድርጌ ቆጠርኩት። ከፍተኛ በሆነ የደስታና የመገረም ስሜት ተዋጥሁ።” ዳንየላ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሕይወቷን ለይሖዋ ወስና የተጠመቀች ከመሆኑም ሌላ ሚስዮናዊ ለመሆን ጥረት ማድረግ ጀመረች። ትዳር ከመሠረተች በኋላ ከባለቤቷ ከሄልሙት ጋር ሆና ቬይና ውስጥ ለሚኖሩ አፍሪካውያን፣ ቻይናውያን፣ ፊሊፒናውያንና ሕንዶች ምሥራቹን መስበክ ጀመረች። በአሁኑ ጊዜ ዳንየላና ሄልሙት በደቡብ ምዕራብ አፍሪካ ሚስዮናዊ ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ።

ተስፋ አልቆረጡም

8. ብዙዎች ለአምላክ ያላቸውን ፍቅርና ለመንግሥቱ ያላቸውን ታማኝነት ያሳዩበት አንድ አስደሳች መንገድ የትኛው ነው?

8 በእርግጥም የሚስዮናዊነት አገልግሎት በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ሕዝቦች ለአምላክ ያላቸውን ፍቅርና ለመንግሥቱ ያላቸውን ታማኝነት የሚያሳዩበት አንደኛው መንገድ ነው። ኢየሱስ በተናገረው ምሳሌ ላይ እንደተጠቀሰው ነጋዴ ሚስዮናዊ የሚሆኑ ክርስቲያኖችም ለአምላክ መንግሥት ሲሉ ሩቅ ወደሆኑ ቦታዎች ለመጓዝ ፈቃደኛ ናቸው። እርግጥ ነው፣ ሚስዮናውያኑ የሚጓዙት የመንግሥቱን ምሥራች ለማግኘት ብለው ሳይሆን ርቀው በሚገኙ የምድር ክፍሎች የሚኖሩ ሰዎች የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ ለማስተማርና ለመርዳት ነው። (ማቴዎስ 28:19, 20) በብዙ አገሮች ውስጥ አይተው የማያውቁትን ችግር ለመቋቋም ይገደዳሉ። ሆኖም ጽናታቸው ከፍተኛ በረከት ያስገኝላቸዋል።

9, 10. ሚስዮናውያን እንደ መካከለኛው አፍሪካ ሪፑብሊክ በመሳሰሉ ርቀው በሚገኙ አገሮች ምን አስደሳች ተሞክሮዎች አግኝተዋል?

9 ለምሳሌ ያህል፣ ባለፈው ዓመት በተከበረው የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ ላይ በአገሪቱ ካሉት የመንግሥቱ አስፋፊዎች ቁጥር ወደ ሰባት እጥፍ ገደማ ማለትም 16,184 ሰዎች የተገኙባትን የመካከለኛው አፍሪካ ሪፑብሊክን ተመልከት። በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍል የኤሌክትሪክ መብራት ስለማይገኝ አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች የዕለት ተዕለት ተግባራቸውን የሚያከናውኑት ከቤት ውጪ ዛፍ ጥላ ሥር ሆነው ነው። በመሆኑም ሚስዮናውያኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻቸውን የሚያስጠኑት ከቤት ውጪ ዛፍ ሥር ተቀምጠው ነው። ውጪ ማጥናታቸው የተሻለ ብርሃንና ቀዝቀዝ ያለ አየር የሚያስገኝላቸው ከመሆኑም በተጨማሪ ሌላም ጥቅም አለው። ሕዝቡ በተፈጥሮው ለመጽሐፍ ቅዱስ ፍቅር አለው፤ እንዲሁም በሃይማኖታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መወያየት በአንዳንድ አገሮች ስለ ስፖርትና ስለ አየር ጠባይ የማውራት ያህል የተለመደ ነገር ነው። አብዛኛውን ጊዜ ጥናት ሲካሄድ የሚመለከቱ መንገደኞች ከፈለጉ መጥተው ያዳምጣሉ።

10 በመሆኑም አንድ ሚስዮናዊ ውጪ መጽሐፍ ቅዱስ እያስጠና ሳለ ከመንገዱ ባሻገር የሚኖር አንድ ወጣት ቀረብ ብሎ እርሱን ቤቱ መጥቶ ያነጋገረው ሰው ስለሌለ ሚስዮናዊው እርሱ ጋር መጥቶ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያስጠናው እንደሚፈልግ ነገረው። እንደሚጠበቀው ሁሉ ሚስዮናዊው ለማስጠናት ደስተኛ መሆኑን ገለጸለት፤ ወጣቱም ፈጣን እድገት በማድረግ ላይ ይገኛል። በዚያ አገር ብዙ ጊዜ ፖሊሶች የይሖዋ ምሥክሮችን መንገድ ላይ ያስቆሟቸዋል። እንዲህ የሚያደርጉት ግን የክስ ወይም የቅጣት ወረቀት ሊሰጧቸው ሳይሆን በቅርብ የወጡ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔት እንዲሰጧቸው ለመጠየቅ አሊያም ጠቃሚ ሆኖ ያገኙትን ርዕስ በተመለከተ ምስጋናቸውን ለመግለጽ ነው።

11. የተለያዩ ፈተናዎች ቢኖሩም ለረጅም ጊዜ በሚስዮናዊነት ያገለገሉ ወንድሞች ስለ አገልግሎታቸው ምን ይሰማቸዋል?

11 ከዛሬ 40 ወይም 50 ዓመታት በፊት የሚስዮናዊነት አገልግሎት የጀመሩ አብዛኞቹ የይሖዋ ምሥክሮች አሁንም በታማኝነት እያገለገሉ ናቸው። በእምነትና በጽናት ረገድ ለሁላችንም ግሩም ምሳሌ ይሆኑናል! አንድ ባልና ሚስት ላለፉት 42 ዓመታት በሦስት አገሮች ውስጥ በሚስዮናዊነት አገልግለዋል። ባልየው እንዲህ ይላል:- “አንዳንድ ችግሮች ለመጋፈጥ ተገድደናል። ለምሳሌ ያህል፣ ለ35 ዓመታት ከወባ በሽታ ጋር ስንታገል ቆይተናል። ሆኖም ሚስዮናዊ ለመሆን ባደረግነው ውሳኔ ፈጽሞ ተቆጭተን አናውቅም።” ባለቤቱ ደግሞ እንዲህ ትላለች:- “ምንጊዜም አመስጋኝ እንድንሆን የሚያስችሉ ብዙ ነገሮች ያጋጥሙናል። አገልግሎት በጣም ያስደስታል፤ ደግሞም በቀላሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ማስጀመር ይቻላል። መጽሐፍ ቅዱስ የምናስጠናቸው ሰዎች ወደ ስብሰባ ሲመጡና አንዳቸው ከሌላው ጋር ሲተዋወቁ ማየት ዘመድ አዝማድ የተሰባሰበ ነው የሚመስለው።”

“ሁሉንም ነገር እንደ ጉድለት” ይቆጥራሉ

12. አንድ ሰው የአምላክን መንግሥት እንደ ውድ ሀብት እንደሚቆጥር ማሳየት የሚችለው እንዴት ነው?

12 ነጋዴው እጅግ ውድ የሆነ ዕንቁ ባገኘ ጊዜ “ሄዶ ያለውን ሁሉ ሸጦ ገዛው።” (ማቴዎስ 13:46) ነጋዴው የሚጠቅመውን ነገር መሥዋዕት ለማድረግ ያሳየው ይህ ዓይነቱ የፈቃደኝነት መንፈስ የአምላክን መንግሥት ዋጋማነት ከልብ የሚያደንቁ ሰዎች የሚታወቁበት ባሕርይ ነው። ከክርስቶስ ጋር በመንግሥቱ ክብር የመካፈል አጋጣሚ የነበረው ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ብሏል:- “ለእርሱ ብዬ ሁሉን ነገር የተውሁለትን፣ ወደር የሌለውን ጌታዬን ክርስቶስ ኢየሱስን ከማወቅ ታላቅነት ጋር ሳነጻጽር፣ ሁሉንም ነገር እንደ ጒድለት እቈጥረዋለሁ፤ ለእርሱ ስል ሁሉን አጥቻለሁ፤ ክርስቶስን አገኝ ዘንድ ሁሉን እንደ ጒድፍ እቈጥራለሁ።”—ፊልጵስዩስ 3:8

13. በቼክ ሪፑብሊክ የሚኖሩ አንድ ግለሰብ ለአምላክ መንግሥት ያላቸውን ፍቅር ያሳዩት እንዴት ነው?

13 በተመሳሳይ በዛሬው ጊዜ ብዙዎች የአምላክ መንግሥት የሚያመጣውን በረከት ለማግኘት ሲሉ በሕይወታቸው ውስጥ መሠረታዊ ለውጦች ለማድረግ ፈቃደኛ ሆነዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በጥቅምት 2003 ቼክ ሪፑብሊክ ውስጥ የአንድ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር የሆኑ የ60 ዓመት ሰው ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተባለውን መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት የተዘጋጀ መጽሐፍ አገኙ። መጽሐፉን አንብበው ከጨረሱ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስጠናቸው ሰው ለማግኘት ወዲያውኑ በአካባቢያቸው ካሉ የይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኙ። ጥሩ መንፈሳዊ እድገት አድርገው በአጭር ጊዜ ውስጥ በሁሉም የጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመሩ። ታዲያ ለከተማው ከንቲባነት ከዚያም አልፎ ለምክር ቤት አባልነት ለመወዳደር የነበራቸውን ዕቅድ ምን አደረጉት? ይህን ትተው የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪ በመሆን የሕይወትን ሩጫ ለመጀመር ወሰኑ። “ለተማሪዎቼ ብዙ ጽሑፎች ማበርከት ችያለሁ” ሲሉ ተናግረዋል። በሐምሌ 2004 በተደረገ የአውራጃ ስብሰባ ላይ ራሳቸውን ለይሖዋ መወሰናቸውን በውኃ ጥምቀት አሳዩ።

14. (ሀ) የመንግሥቱ ምሥራች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ምን እንዲያደርጉ አነሳስቷቸዋል? (ለ) እያንዳንዳችን ራሳችንን የትኞቹን አሳሳቢ ጥያቄዎች መጠየቅ እንችላለን?

14 በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለመንግሥቱ ምሥራች ተመሳሳይ ምላሽ ሰጥተዋል። ከክፉው ዓለም ወጥተዋል፣ አሮጌውን ሰው አስወግደዋል፣ የቀድሞ ባልንጀሮቻቸውን እርግፍ አድርገው ትተዋል እንዲሁም ዓለማዊ ግቦችን ማሳደድ አቁመዋል። (ዮሐንስ 15:19፤ ኤፌሶን 4:22-24፤ ያዕቆብ 4:4፤ 1 ዮሐንስ 2:15-17) ይህን ሁሉ ያደረጉት ለምንድን ነው? የአምላክ መንግሥት የሚያመጣላቸውን በረከት ይህ ሥርዓት ሊሰጣቸው ከሚችለው ከማንኛውም ጥቅም እጅግ አስበልጠው ስለተመለከቱ ነው። አንተስ ለአምላክ መንግሥት ምሥራች ተመሳሳይ አመለካከት አለህ? አኗኗርህን፣ በሕይወትህ ውስጥ ከፍተኛ ግምት የምትሰጣቸውን ነገሮችና ግቦችህን ከይሖዋ ፈቃድ ጋር ለማስማማት አስፈላጊውን ለውጥ እንድታደርግ ያነሳሳሃል? እንዲህ ማድረግህ አሁንም ሆነ ለዘላለም ብዙ በረከት እንድታገኝ ያስችልሃል።

መከሩ ወደ ፍጻሜው ተዳርሷል

15. በፍጻሜው ዘመን የአምላክ ሕዝቦች ምን እንደሚያደርጉ በትንቢት ተነግሯል?

15 መዝሙራዊው “ለጦርነት በምትወጣበት ቀን፣ ሰራዊትህ በገዛ ፈቃዱ በጐንህ ይቆማል” ሲል ጽፏል። ራሳቸውን በፈቃደኝነት ካቀረቡት መካከል ‘እንደ ጠል ያሉ ጎልማሶች’ እና ‘ዜናውን የሚያሰራጩ ብዙ ሴቶች’ ይገኙበታል። (መዝሙር 68:11 የ1980 ትርጉም፤ 110:3) በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ወንዶችም ሆኑ ሴቶች እንዲሁም ወጣቶችም ሆኑ አረጋውያን የይሖዋ ምሥክሮች ያሳዩት ትጋትና የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ ምን አስገኝቷል?

16. የአምላክ አገልጋዮች ሌሎች ስለ አምላክ መንግሥት እንዲማሩ ለመርዳት ምን ጥረት እያደረጉ እንዳሉ የሚያሳይ አንድ ምሳሌ ተናገር።

16 በሕንድ የምትኖር አንዲት አቅኚ ወይም የሙሉ ጊዜ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪ በአገሪቱ የሚኖሩት ከሁለት ሚሊዮን የሚበልጡ መስማት የተሳናቸው ሰዎች ምሥራቹን እንዲያውቁ እንዴት ሊረዱ ይችላሉ የሚለው ጉዳይ ያሳስባት ነበር። (ኢሳይያስ 35:5) የምልክት ቋንቋ ለመማር ወደ አንድ ተቋም ሄዳ ለመመዝገብ ወሰነች። በዚያም መስማት ለተሳናቸው ብዙ ሰዎች የመንግሥቱን ምሥራች መመሥከር ቻለች። እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቡድኖች ተቋቋሙ። በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ከአሥራ ሁለት የሚበልጡ ሰዎች በመንግሥት አዳራሹ በሚካሄዱት ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመሩ። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ደግሞ በአንድ የሠርግ ግብዣ ላይ አቅኚዋ ከካልካታ ከመጣ መስማት የተሳነው ወጣት ጋር ተገናኘች። ይህ ወጣት በርካታ ጥያቄዎች የነበሩት ከመሆኑም ሌላ ስለ ይሖዋ ተጨማሪ እውቀት የማግኘት ከፍተኛ ጉጉት አደረበት። ይሁንና መፍትሄ የሚያሻው አንድ ችግር ነበር። ወጣቱ ኮሌጅ ለመግባት 1,600 ኪሎ ሜትር ርቆ ወደሚገኘው ወደ ካልካታ መመለስ የነበረበት ሲሆን በዚያ ደግሞ የምልክት ቋንቋ የሚችሉ የይሖዋ ምሥክሮች የሉም። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱን መቀጠል ስለፈለገ በባንጋሎር ከተማ በሚገኝ ትምህርት ቤት ለመግባት እንዲፈቅድለት አባቱን እንደ ምንም ብሎ አሳመነው። ግሩም መንፈሳዊ እድገት አድርጎ ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ ሕይወቱን ለይሖዋ ወሰነ። እርሱ ደግሞ በተራው የልጅነት ጓደኛውን ጨምሮ በርከት ያሉ መስማት የተሳናቸውን ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ በማስጠናት ላይ ይገኛል። በሕንድ የሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ አቅኚዎች በዚህ የአገልግሎት መስክ መካፈል እንዲችሉ የምልክት ቋንቋ እንዲማሩ ዝግጅት እያደረገ ነው።

17. ከገጽ 19 እስከ 22 ካለው የ2004 የአገልግሎት ዓመት ሪፖርት በጣም አበረታች ሆኖ ያገኘኸውን ነጥብ ተናገር።

17 በዚህ መጽሔት ከገጽ 19 እስከ 22 ላይ የይሖዋ ምሥክሮች በ2004 የአገልግሎት ዓመት በዓለም ዙሪያ ያደረጉትን የአገልግሎት እንቅስቃሴ የሚያሳይ ሪፖርት ወጥቷል። ጥቂት ጊዜ ወስደህ ሪፖርቱን በማጤን በምድር ዙሪያ ያሉ የይሖዋ ሕዝቦች በዛሬው ጊዜ “እጅግ ውድ የሆነ ዕንቊ” ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ለመሆናቸው ማስረጃውን ተመልከት።

‘አስቀድማችሁ የአምላክን መንግሥት እሹ’

18. ኢየሱስ ስለ ነጋዴው በተናገረው ምሳሌ ላይ ያልጠቀሰው ሐሳብ ምንድን ነው? ለምንስ?

18 ከዚህ በፊት የተጠቀሰውን ኢየሱስ ስለ ነጋዴው የተናገረውን ምሳሌ በድጋሚ ካነሳን ነጋዴው ያለውን ሁሉ ከሸጠ በኋላ በምን እንደሚተዳደር ኢየሱስ የተናገረው ነገር እንደሌለ እንገነዘባለን። አንዳንዶች ‘ነጋዴው ለክፉ ቀን ያስቀመጠው ምንም ነገር ስለሌለ ምግብ፣ ልብስና መጠለያ ከየት ያገኛል? በውድ ዋጋ የገዛው ዕንቁ ምን ሊያደርግለት ይችላል?’ ብለው መጠየቃቸው አይቀርም። ጉዳዩን በሥጋዊ ዓይን ከተመለከትነው ጥያቄዎቹ አግባብነት ያላቸው ይመስላሉ። ሆኖም ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “ከሁሉ አስቀድማችሁ . . . የእግዚአብሔርን መንግሥትና ጽድቁን እሹ፤ እነዚህ ሁሉ ይጨመሩላችኋል” በማለት አሳስቧቸው አልነበረም? (ማቴዎስ 6:31-33) የምሳሌው ዋና መልእክት ለአምላክ በሙሉ ልብ የማደርንና መንግሥቱን በቅንዓት የመደገፍን አስፈላጊነት ማስገንዘብ ነው። እኛ ከዚህ የምናገኘው ትምህርት ይኖራል?

19. ኢየሱስ እጅግ ውድ ስለሆነ ዕንቁ ከተናገረው ምሳሌ ምን ዓቢይ ትምህርት እናገኛለን?

19 አስደናቂውን ምሥራች የሰማነው በቅርቡም ሆነ የአምላክን መንግሥት በመጠባበቅና የሚያመጣቸውን በረከቶች ለሌሎች በመንገር በርካታ አሥርተ ዓመታት ያሳለፍን ቢሆን ልባችንና ትኩረታችን በመንግሥቱ ላይ እንዳነጣጠረ መቀጠል ይኖርብናል። ያለንበት ዘመን በጣም አስቸጋሪ ነው፤ ይሁንና ለማግኘት የምንጣጣረው ነገር እውነተኛና ተወዳዳሪ የማይገኝለት ሀብት እንደሆነ የሚያሳምነን ጠንካራ ምክንያት አለን። እንዲያውም ነጋዴው ባገኘው ዕንቁ ልንመስለው እንችላለን። በዓለም ላይ የሚታዩ ክስተቶችና ፍጻሜያቸውን ያገኙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች የምንኖረው ‘በዓለም መጨረሻ’ ላይ እንደሆነ አሳማኝ ማስረጃ ይሰጡናል። (ማቴዎስ 24:3) እንደ ነጋዴው ሁሉ እኛም የአምላክን መንግሥት በሙሉ ልባችን እንደምንደግፍ እናሳይ፤ እንዲሁም ምሥራቹን ለማወጅ ባገኘነው መብት እንደሰት።—መዝሙር 9:1, 2

ታስታውሳለህ?

• ባለፉት ዓመታት የእውነተኛ አምላኪዎች ቁጥር እንዲጨምር አስተዋጽኦ ያደረገው ምንድን ነው?

• ሚስዮናዊ ሆነው የሚያገለግሉ ወንድሞች ምን ዓይነት መንፈስ አላቸው?

• ሰዎች የመንግሥቱን ምሥራች በመስማታቸው ምን ዓይነት ለውጥ አድርገዋል?

• ኢየሱስ እጅግ ውድ ስለሆነ ዕንቁ ከተናገረው ምሳሌ ምን ጠቃሚ ትምህርት እናገኛለን?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[ከገጽ 19-22 የሚገኝ ሰንጠረዥ]

የ2004 የአገልግሎት ዓመት የይሖዋ ምሥክሮች ዓለም አቀፍ ሪፖርት

(መጽሔቱን ተመልከት)

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“እውነት . . . ሁሉንም ዓይነት ሰዎች ይስባል።”—አሌክሳንደር ማክሚላን

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዳንየላና ሄልሙት በቬይና ለውጭ አገር ቋንቋ ተናጋሪ ሲሰብኩ

[በገጽ 16 እና 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በዛሬው ጊዜ ሚስዮናውያን እንደ ነጋዴው ብዙ በረከት አግኝተዋል

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ሰራዊትህ በገዛ ፈቃዱ በጐንህ ይቆማል”