እውነት በምታስተምራቸው ሰዎች ልብ ውስጥ ፍሬ እያፈራ ነው?
እውነት በምታስተምራቸው ሰዎች ልብ ውስጥ ፍሬ እያፈራ ነው?
ወጣቱ ኤሪክ የይሖዋ ምሥክር መሆን እንደማይፈልግ በነገራቸው ጊዜ ወላጆቹ ቅስማቸው ተሰበረ። ጉዳዩ ፈጽሞ ያልጠበቁት ነገር ነበር። ኤሪክ ልጅ እያለ በቤተሰቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ላይ ይሳተፍ፣ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ይገኝ እንዲሁም ከጉባኤው ጋር አገልግሎት ይወጣ ነበር። ለተመልካች በእውነት ውስጥ ይመላለስ የነበረ ይመስላል። ከቤት ከወጣ በኋላ ግን ወላጆቹ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የራሱ አለማድረጉን ተገነዘቡ። ይህ ደግሞ ለድንጋጤና ለሐዘን ዳረጋቸው።
ሌሎች ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻቸው በድንገት ጥናታቸውን ሲያቋርጡ ተመሳሳይ ስሜት ተሰምቷቸዋል። በዚህ ወቅት ብዙዎች ራሳቸውን ‘ይህ እንደሚመጣ እንዴት ማወቅ አቃተኝ?’ ብለው ይጠይቃሉ። ይሁንና ጥናቶቻችን በመንፈሳዊ ከመውደቃቸው በፊት እውነት ለውጥ እንዲያደርጉ እየረዳቸው መሆን አለመሆኑን ማወቅ እንችላለን? እንዲያውም እኛም ሆን ጥናቶቻችን በእውነት ውስጥ እየተመላለስን መሆኑን እርግጠኛ መሆን የምንችለው እንዴት ነው? ኢየሱስ ስለ ዘሪው በሚናገረው ምሳሌ ላይ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ የምናገኝበት ፍንጭ ሰጥቶናል።
እውነት ልብን ሊለውጥ ይገባል
ኢየሱስ “ዘር የተባለው የእግዚአብሔር ቃል ነው” በማለት ካስረዳ በኋላ ቀጥሎም “በመልካም መሬት ላይ የወደቀውም ቃሉን ቅንና በጎ በሆነ ልብ ሰምተው የሚጠብቁ፣ ታግሠውም በመጽናት ፍሬ የሚያፈሩ ናቸው” ብሏል። (ሉቃስ 8:11, 15) ስለዚህ የመንግሥቱ እውነት በተማሪዎቻችን ሕይወት ላይ አንድ ዓይነት ለውጥ ከማምጣቱ በፊት በምሳሌያዊው ልባቸው ውስጥ ሥር መስደድ ይኖርበታል። ኢየሱስ፣ በመልካም መሬት ላይ እንደወደቀው ዘር ሁሉ መለኮታዊ እውነትም ጥሩ ልብ ላይ ካረፈ ግለሰቡ በፍጥነት ለውጥ እንዲያደርግና ፍሬ እንዲያፈራ እንደሚያደርገው ማረጋገጫ ሰጥቶናል። እንዲያፈሩ የምንጠብቀው ምን ዓይነት ፍሬ ነው?
የሰዎችን ውጫዊ አቋም ብቻ ሳይሆን የልባቸውን ዝንባሌ በትኩረት መከታተል ይገባናል። በዘልማድ የሚዘወተሩ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች የአንድን ሰው የልብ ዝንባሌ በትክክል ላይገልጹ ይችላሉ። (ኤርምያስ 17:9, 10፤ ማቴዎስ 15:7-9) ስለዚህም ነገሮችን በጥልቀት ለማየት መሞከሩ አስፈላጊ ነው። ግለሰቡ በፍላጎቶቹ፣ በግቦቹና ቅድሚያ በሚሰጣቸው ነገሮች ረገድ በግልጽ የሚታይ ለውጥ ማድረግ አለበት። ግለሰቡ ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚስማማውን አዲሱን ሰው መልበስ ይኖርበታል። (ኤፌሶን 4:20-24) ለምሳሌ ያህል በተሰሎንቄ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ምሥራቹን በሰሙበት ወቅት የአምላክ ቃል ነው ብለው መልእክቱን በደስታ እንደተቀበሉ ጳውሎስ ተናግሯል። ነገር ግን እውነት “[በእነርሱ] እንደሚሠራ” እንዲያምን ያደረገው ቃሉን ከተቀበሉ በኋላ ያሳዩትን ጽናት፣ ታማኝነትና ፍቅር ማየት መቻሉ ነው።—1 ተሰሎንቄ 2:13, 14፤ 3:6
የኤሪክ ሁኔታ እንደሚያሳየው በተማሪዎቻችን ልብ ውስጥ ያለው ነገር ፈጥኖም ይሁን ዘግይቶ በጠባያቸው ላይ መታየቱ አይቀርም። (ማርቆስ 7:21, 22፤ ያዕቆብ 1:14, 15) ክፋቱ ግን አንዳንድ መጥፎ ባሕርያት በድርጊት የሚገለጹት ሥር ከሰደዱ በኋላ ስለሚሆን ግለሰቡን ለመርዳት አስቸጋሪ ይሆናል። ተፈታታኙ ነገር አንዳንድ ድክመቶች ከጊዜ በኋላ መንፈሳዊ ውድቀት የሚያስከትሉ መሰናክሎች ከመሆናቸው በፊት አስቀድሞ ማወቅ መቻሉ ነው። ስለዚህም ምሳሌያዊውን ልብ ማየት የምንችልበት ዘዴ ሊኖረን ይገባል። ይህንን እንዴት ማድረግ እንችላለን?
ከኢየሱስ መማር
እርግጥ ነው፣ ኢየሱስ የሰዎችን ልብ በትክክል የማንበብ ችሎታ ነበረው። (ማቴዎስ 12:25) ከእኛ አንዳችንም ብንሆን ይህንን ማድረግ አንችልም። ይሁንና ኢየሱስ የሰዎችን ፍላጎት፣ አስተሳሰብና ቅድሚያ የሚሰጡትን ነገር እኛም ማስተዋል እንደምንችል አሳይቶናል። አንድ ብቃት ያለው ሐኪም የበሽተኛውን የልብ ችግር ለማወቅ የተለያዩ የምርመራ ዘዴዎችን እንደሚጠቀም ሁሉ ኢየሱስም ከሰው እይታ የተሰወረ ቢሆንም እንኳ የግለሰቡን ችግር ‘ቀድቶ ለማውጣት’ እና “የልብንም ሐሳብና ምኞት” ለማወቅ የአምላክን ቃል ተጠቅሟል።—ምሳሌ 20:5፤ ዕብራውያን 4:12
ለምሳሌ ኢየሱስ፣ ወደፊት እንቅፋት የሚሆንበትን ድክመት እንዲያስተውል በአንድ ወቅት ጴጥሮስን ረድቶታል። ኢየሱስ ጴጥሮስ ከልቡ እንደሚወደው ያውቃል። እንዲያውም ከጥቂት ጊዜ በፊት “የመንግሥተ ሰማይን መክፈቻዎች” በአደራ ሰጥቶት ነበር። (ማቴዎስ 16:13-19) ይሁን እንጂ ሰይጣን ሐዋርያቱን የጥቃት ኢላማው እንዳደረጋቸውና ብዙም ሳይቆይ አቋማቸውን እንዲያላሉ የሚያደርግ ፈተና እንደሚያመጣባቸውም ያውቃል። ኢየሱስ አንዳንድ ደቀ መዛሙርቱ በእምነት ረገድ ድክመት እንደሚታይባቸው በግልጽ አስተውሏል። ስለዚህ ሊሠሩበት የሚገባቸውን ነገር ከመናገር ወደኋላ አላለም። ጉዳዩን አንስቶ እንዴት እንዳወያያቸው እስቲ እንመልከት።
ማቴዎስ 16:21 እንደሚነግረን “ኢየሱስ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ . . . መከራን ይቀበልና ይገደል ዘንድ . . . እንደሚገባው ለደቀ መዛሙርቱ ይገልጽላቸው ጀመር።” ኢየሱስ በእርሱ ላይ የሚደርሰውን ነገር በመናገር ብቻ ሳይወሰን ይገልጽላቸው እንደነበር ልብ ማለት ይገባል። መሲሑ መከራ እንደሚደርስበትና እንደሚገደል ለማብራራት እንደ መዝሙር 22:14-18 ወይም እንደ ኢሳይያስ 53:10-12 ያሉትን ጥቅሶች ሳይጠቀም አይቀርም። ኢየሱስ ከመጽሐፍ ቅዱስ በማንበብም ይሁን በቀጥታ ጠቅሶ በመናገር ለጴጥሮስም ሆነ ለሌሎቹ ደቀ መዛሙርት በልባቸው ያለውን አውጥተው የሚናገሩበት አጋጣሚ ሰጥቷቸዋል። ታዲያ ስደት እንደሚጠብቃቸው ቢሰሙ ምላሻቸው ምን ይሆናል?
የሚያስገርመው፣ ጴጥሮስ ደፋርና ቀናተኛ መሆኑን ያሳየ ቢሆንም በዚህ ወቅት የሰጠው የችኮላ መልስ በጣም የተሳሳተ አመለካከት እንደነበረው በግልጽ አሳይቷል። ኢየሱስን “ጌታ ሆይ፤ እንዲህ ያለ ነገር ፈጽሞ አይድረስብህ” አለው። የጴጥሮስ አስተሳሰብ የተሳሳተ እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። ከዚህም የተነሳ ኢየሱስ ‘የሰው እንጂ የእግዚአብሔር ነገር በሐሳብህ የለም’ አለው። ይህ ወደ ከባድ መዘዝ የሚያደርስ ትልቅ ስሕተት ነበር። ታዲያ ኢየሱስ ምን አደረገ? ጴጥሮስን ከገሰጸው በኋላ ለእርሱም ሆነ ለሌሎቹ ደቀ መዛሙርት “ሊከተለኝ የሚወድ ራሱን ይካድ፣ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ” በማለት ነገራቸው። መዝሙር 49:8 እና 62:12 ላይ የሚገኙትን ሐሳቦች በመጥቀስ ዘላለማዊ ተስፋቸው የተመካው በአምላክ ላይ እንጂ ማዳን በማይችሉ በሰው ልጆች ላይ አለመሆኑን በደግነት አስታወሳቸው።—ማቴዎስ 16:22-28
ከጥቂት ቀናት በኋላ ጴጥሮስ ለጊዜው በፍርሃት ተሸንፎ ኢየሱስን ሦስት ጊዜ የካደ ቢሆንም ከእርሱ ጋር ያደረገው ይህም ሆነ ሌሎች ውይይቶች በመንፈሳዊ ቶሎ እንዲያንሰራራ እንደረዱት ምንም ጥርጥር የለውም። (ዮሐንስ 21:15-19) ከ50 ቀናት በኋላ ጴጥሮስ በኢየሩሳሌም ተሰብስበው ለነበሩት ሰዎች ስለ ኢየሱስ ትንሣኤ በድፍረት ምሥክርነት ሰጥቷል። በቀጣዮቹም ሳምንታት፣ ወራትና ዓመታት በተደጋጋሚ የታሰረና የተደበደበ እንዲሁም ወኅኒ ቤት የተጣለ ቢሆንም ፈተናውን በድፍረት ተወጥቷል። በመሆኑም በቆራጥነት በመጽናት ረገድ ለሌሎች የላቀ ምሳሌ ትቷል።—የሐዋርያት ሥራ 2:14-36፤ 4:18-21፤ 5:29-32, 40-42፤ 12:3-5
ከዚህ ምን እንማራለን? ኢየሱስ በጴጥሮስ ልብ ውስጥ ያለውን ነገር ለማግኘትና ለማውጣት ምን እንዳደረገ አስተዋልክ? በመጀመሪያ የጴጥሮስ ትኩረት ወደ ተፈላጊው አቅጣጫ እንዲመጣ ለማድረግ ተስማሚ የሆኑ ጥቅሶች መረጠ። ቀጥሎም ኢየሱስ፣ ጴጥሮስ በልቡ
ያለውን አውጥቶ እንዲናገር አጋጣሚ ሰጠው። በመጨረሻም አመለካከቱንና አስተሳሰቡን እንዲያስተካክል ለመርዳት ተጨማሪ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ሰጠው። ምናልባት ይህ የማስተማር ጥበብ ከእኔ አቅም በላይ ነው ብለህ ታስብ ይሆናል። ነገር ግን ጥሩ ዝግጅት ማድረግና በይሖዋ ላይ መመካት ሁላችንም የኢየሱስን ምሳሌ መከተል እንድንችል እንደሚረዳን የሚያሳዩ ሁለት ምሳሌዎችን እንመልከት።የልባቸውን አውጥተው እንዲናገሩ ማድረግ
የአንደኛና የሁለተኛ ክፍል ተማሪ የሆኑ ሁለት ልጆች ያሉት የይሖዋ ምሥክር የሆነ አንድ አባት ልጆቹ ከአስተማሪያቸው ጠረጴዛ ላይ ከረሜላ እንደሰረቁ ሲሰማ ቁጭ አድርጎ አወያያቸው። አባትየው ነገሩን እንደ ተራ የልጆች ጨዋታ አድርጎ ከመመልከት ይልቅ “እንዲህ ያለውን መጥፎ ድርጊት እንዲፈጽሙ ያነሳሳቸውን የልብ ዝንባሌ ለመረዳት ጥረት አደረግሁ” ብሏል።
አባትየው በኢያሱ ምዕራፍ 7 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን በአካን ላይ የደረሰውን ሁኔታ ያስታውሱ እንደሆነ ልጆቹን ጠየቃቸው። እነርሱም ወዲያውኑ ነጥቡ ስለገባቸው የሠሩትን ጥፋት በግልጽ ተናገሩ። አባትየው ሕሊናቸው እንደወቀሳቸው ካስተዋለ በኋላ ኤፌሶን 4:28ን አውጥቶ “ይሰርቅ የነበረ ከእንግዲህ አይስረቅ፤ ነገር ግን ለተቸገሩት የሚያካፍለው ነገር እንዲኖረው . . . እየሠራ ለማግኘት ይድከም” የሚለውን ጥቅስ አነበበላቸው። ከዚያም ከረሜላ ገዝቶ ለአስተማሪያቸው ወስደው እንዲሰጡ በማድረግ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሰጣቸውን ምክር በተግባር ደገፈው።
አባትየው “መጥፎ ዝንባሌ ካየንባቸው ከሥረ መሠረቱ ለማስወገድ ጥረት የምናደርግ ከመሆኑም ሌላ በምትኩ መልካምና ንጹሕ የሆነ የልብ ዝንባሌ እንዲኖራቸው አሳማኝ በሆነ መንገድ እናስተምራቸዋለን” ብሏል። እነዚህ ወላጆች የኢየሱስን ምሳሌ ተከትለው ልጆቻቸውን በማስተማራቸው ከጊዜ በኋላ ጥሩ ውጤት ሊያገኙ ችለዋል። በመጨረሻም ሁለቱ ልጆች ብሩክሊን በሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤት የቤቴል ቤተሰብ አባል እንዲሆኑ የተጋበዙ ሲሆን አንደኛው ከ25 ዓመታት በኋላም እዚያው በማገልገል ላይ ይገኛል።
አሁን ደግሞ፣ አንዲት እህት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዋን እንዴት እንደረዳቻት ተመልከት። ጥናቷ በስብሰባዎች ላይ ትገኛለች፣ በአገልግሎት ትሳተፋለች እንዲሁም ለመጠመቅ እንደምትፈልግ አሳውቃለች። ይሁንና በይሖዋ ከመታመን ይልቅ ከልክ በላይ በራሷ የመታመን ዝንባሌ ይታይባታል። አስጠኚዋ ሁኔታውን በማስታወስ እንዲህ ትላለች:- “ያላገባች ሴት በመሆኗ ከምታስበው በላይ በራስ የመመራት ዝንባሌ ይታይባት ነበር። አንድ ቀን ከባድ የጤና መቃወስ ወይም መንፈሳዊ ውድቀት እንዳይደርስባት እጨነቅ ነበር።”
ስለዚህ እህት ጥናቷን በማቴዎስ 6:33 ላይ በማወያየት ቅድሚያ በምትሰጣቸው ነገሮች ላይ ማስተካከያ እንድታደርግ፣ መንግሥቱን እንድታስቀድምና ማንኛውም ነገር እንዲሳካላት በይሖዋ እንድትታመን አበረታታቻት። ከዚያም በግልጽ እንዲህ ብላ ጠየቀቻት:- “ሕይወትሽን በራስሽ ዕቅድ የምትመሪ መሆንሽ በሌሎች እንዲሁም በይሖዋ ላይ ጭምር መታመንን አስቸጋሪ ያደርግብሻል?” ጥናቷ እንዲያውም መጸለይ ወደ ማቆሙ እንደደረሰች ነገረቻት። እህት 1 ጴጥሮስ 5:7 እንደሚለው ‘እርሱ ስለ እኛ ስለሚያስብ’ በመዝሙር 55:22 ላይ ያለውን ምክር ተግባራዊ በማድረግ ሸክሟን በይሖዋ ላይ እንድትጥል አበረታታቻት። እነዚህ ቃላት ልቧን ነኩት። እህትም ሁኔታውን በማስታወስ “ስታለቅስ ካየሁበት ጥቂት ጊዜያት ውስጥ አንዱ የዚያን ቀን ነበር” ብላለች።
እውነትን በሕይወትህ ውስጥ ተግባራዊ አድርግ
እያስጠናናቸው ያሉ ሰዎች ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጥሩ ምላሽ ሲሰጡ ማየት በጣም የሚያስደስት ነው። ሆኖም ሌሎችን ለመርዳት የምናደርገው ጥረት ውጤት እንዲኖረው እኛ ራሳችን ጥሩ ምሳሌ ሆነን መገኘት አለብን። ይሁዳ 22, 23) ሁላችንም ብንሆን ‘በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችንን መዳን መፈጸም’ ይገባናል። (ፊልጵስዩስ 2:12) ይህም ያለ ማቋረጥ የቃሉ ብርሃን በልባችን እንዲበራ በማድረግ በአስተሳሰባችን፣ በምኞታችንና በዝንባሌያችን ላይ ማስተካከያ ማድረግ በሚያስፈልግበት ጊዜ ማስተካከያ ማድረግን ይጨምራል።—2 ጴጥሮስ 1:19
(ለምሳሌ ያህል ለክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች የነበረህ ቅንዓት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየቀነሰ መጥቷል? ከሆነ ለምን? አንደኛው ምክንያት በራስህ ላይ ከልክ በላይ መታመንህ ይሆናል። ይህ መሆኑን እንዴት ማወቅ ትችላለህ? ሐጌ 1:2-11ን አንብብና ይሖዋ ከስደት የተመለሱትን አይሁዳውያን እንዴት አሳማኝ በሆነ መንገድ እንዳስረዳቸው ቆም ብለህ አሰላስል። ከዚያም ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ:- ‘የገንዘብ ችግር እንዳያጋጥመኝና ቁሳዊ ነገሮች እንዲሟሉልኝ ከልክ በላይ እጨነቃለሁ? ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ ከሰጠሁ ይሖዋ ቤተሰቤን እንደሚንከባከብልኝ እተማመናለሁ? ወይንስ እኔው ራሴ እንክብካቤ መስጠት እንዳለብኝ ይሰማኛል?’ በአስተሳሰብህም ሆነ በስሜትህ ላይ ማስተካከያ ማድረግ እንዳለብህ ከተሰማህ ዛሬ ነገ አትበል። በማቴዎስ 6:25-33፣ በሉቃስ 12:13-21 እና በ1 ጢሞቴዎስ 6:6-12 ላይ እንደሚገኙት ያሉ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክሮች ለቁሳዊ ፍላጎታችንና ለሀብት ሊኖረን የሚገባው አመለካከት ሚዛናዊ እንዲሆን ይረዱናል። እንደዚህ ዓይነት ዝንባሌ ካለን ደግሞ የይሖዋ በረከት እንደማይለየን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ሚልክያስ 3:10
በዚህ መንገድ ራስን መመርመር ከባድ ሊሆን ይችላል። በግልጽ የሚታዩ ድክመቶቻችን ሲነገሩን መቀበሉ ሊከብደን ይችላል። ይሁንና ነገሩ በጥንቃቄ መያዝ ያለበት የግል ጉዳይ ቢሆንም በፍቅር ተነሳስተህ ልጅህን፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትህን ወይም ደግሞ ራስህን ለመርዳት ስታስብ የእርሱን ወይም የአንተን ሕይወት ለማትረፍ የሚያስችለውን የመጀመሪያውን እርምጃ መውሰድህ ሊሆን ይችላል።—ገላትያ 6:1
ጥረትህ ወዲያውኑ ጥሩ ውጤት ባያስገኝስ? ቶሎ ብለህ ተስፋ አትቁረጥ። ፍጹም ያልሆነን ልብ መግራት አስቸጋሪና ጊዜ የሚወስድ ከመሆኑም በተጨማሪ አንዳንዴ ተስፋ አስቆራጭ ሊሆን ይችላል። ውጤቱ ግን ያማረ ነው።
ወጣቱ ኤሪክ ውሎ አድሮ ወደ ልቡ በመመለስ እንደገና ‘በእውነት ውስጥ መሄድ’ ጀምሯል። (2 ዮሐንስ 4) እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “ያጣሁት ነገር ምን እንደሆነ እስከተገነዘብኩበት ጊዜ ድረስ ወደ ይሖዋ የመመለስ ሐሳብ አልመጣልኝም ነበር።” ቤተሰቦቹ ባደረጉለት እርዳታ ኤሪክ አሁን አምላክን በታማኝነት ማገልገል ጀምሯል። ምንም እንኳን በአንድ ወቅት ወላጆቹ አቋሙን እንዲያጤን ለማስቻል ያደረጉትን ተደጋጋሚ ጥረት ለመቀበል አሻፈረኝ ያለ ቢሆንም አሁን ግን ያደረጉለትን ነገር በጣም ያደንቃል። “ቤተሰቦቼ በጣም የሚደነቁ ሰዎች ናቸው፤ ፍቅራቸውን ነፍገውኝ አያውቁም ነበር” ብሏል።
የምናስተምራቸው ሰዎች የአምላክ ቃል በልባቸው ውስጥ እንዲተከል መርዳት የፍቅራዊ ደግነት መግለጫ ነው። (መዝሙር 141:5) አዲሱ ሰው በልጆቻችሁና በመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችሁ ሕይወት ውስጥ ሥር እየሰደደ መሆኑን ለማወቅ ልባቸውን መመርመራችሁን አታቋርጡ። ‘የእውነትን ቃል በትክክል በማስረዳት’ እውነት በራሳችሁም ሆነ በሌሎች ሕይወት ውስጥ እንዲሠራ ጥረት አድርጉ።—2 ጢሞቴዎስ 2:15
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብ ጴጥሮስ ያለበት ድክመት እንዲወጣ አድርጓል
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በልብ ውስጥ ያለውን ለማውጣት በመጽሐፍ ቅዱስ ተጠቀም