በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘እጅግ ውድ የሆነ ዕንቁ ማግኘት’

‘እጅግ ውድ የሆነ ዕንቁ ማግኘት’

‘እጅግ ውድ የሆነ ዕንቁ ማግኘት’

“መንግሥተ ሰማያትን ለማግኘት የሚጋደሉ ብዙዎች ናቸው፤ በተጋድሏቸው የሚጸኑም ደግሞ ወራሽ ይሆናሉ።”—ማቴዎስ 11:12 Nw

1, 2. (ሀ) ኢየሱስ ስለ መንግሥተ ሰማይ ከተናገራቸው ምሳሌዎች በአንዱ ላይ ምን ያልተለመደ ባሕርይ ጠቅሷል? (ለ) ኢየሱስ እጅግ ውድ ስለሆነ ዕንቁ በተናገረው ምሳሌ ላይ ምን ብሏል?

 እጅግ ከፍተኛ ግምት የምትሰጠው ከመሆኑ የተነሳ አለኝ የምትለውን ነገር ሁሉ ሰጥተህ በእጅህ ልታስገባው የምትፈልገው ነገር አለ? ምንም እንኳ ሰዎች ገንዘብ፣ ታዋቂነት፣ ሥልጣን ወይም ማዕረግ ለማግኘት ቆርጠው የተነሱ መሆናቸውን ሲናገሩ መስማት የተለመደ ቢሆንም በጣም የሚፈልገውን ነገር አግኝቶ የራሱ ለማድረግ ሲል ያለውን ሁሉ ለመስጠት ፈቃደኛ የሆነ ሰው ግን እምብዛም አይገኝም። ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ አምላክ መንግሥት ከተናገራቸው አመራማሪ የሆኑ ምሳሌዎች መካከል በአንዱ ላይ ይህን ያልተለመደ ሆኖም የሚደነቅ ባሕርይ ጠቅሷል።

2 ምሳሌው ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ብቻ የነገራቸው እጅግ ውድ ስለሆነ ዕንቁ የሚናገረው ታሪክ ነው። ኢየሱስ “መንግሥተ ሰማይ ውብ ዕንቊ የሚፈልግ ነጋዴ ትመስላለች፤ እጅግ ውድ የሆነ ዕንቊ ባገኘም ጊዜ ሄዶ ያለውን ሁሉ ሸጦ ገዛው” በማለት ተናገረ። (ማቴዎስ 13:36, 45, 46) ኢየሱስ ይህን ምሳሌ የተናገረው አድማጮቹን ምን ለማስተማር ፈልጎ ነው? እኛስ ከዚህ ምሳሌ ትምህርት ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?

ውድ ዋጋ ያላቸው ዕንቁዎች

3. በጥንት ዘመን ጥራት ያለው ዕንቁ በጣም ውድ የነበረው ለምንድን ነው?

3 ከጥንት ዘመን አንስቶ ዕንቁ ጌጣ ጌጥ ለመሥራት የሚያገለግል በጣም ተፈላጊ ማዕድን ሆኖ ቆይቷል። አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ፣ ሮማዊው ምሑር ትልቁ ፕሊኒ ዕንቁ “ውድ ዋጋ አላቸው ከሚባሉ ነገሮች ሁሉ የመጀመሪያውን ደረጃ” ይይዛል ብሎ መናገሩን ገልጿል። ከወርቅ፣ ከብርና ከሌሎች በርካታ ውድ ማዕድናት በተለየ ዕንቁ የሚገኘው ከሕያዋን ፍጥረታት ነው። ኦይስተር ተብለው ከሚጠሩት የዓሣ ዝርያዎች አንዳንዶቹ እንደ ጠጠር ያሉ የሚቆረቁሯቸውን ነገሮች ከሰውነታቸው በሚመነጭ ኔከር በሚባል ፈሳሽ በመሸፈን የሚያብረቀርቅ ዕንቁ የመሥራት ችሎታ እንዳላቸው በሰፊው ይታወቃል። በጥንት ዘመን ጥራት ያላቸው ዕንቁዎች በአብዛኛው የሚገኙት ከቀይ ባሕር፣ ከፋርስ ባሕረ ሰላጤና ከሕንድ ውቅያኖስ ሲሆን እነዚህ ቦታዎች የሚገኙት ደግሞ ከእስራኤል ርቀው ነበር። ኢየሱስ “ውብ ዕንቊ የሚፈልግ ነጋዴ” በማለት የተናገረው ከዚህ የተነሳ እንደሚሆን ግልጽ ነው። እውነተኛ ዕንቁ ለማግኘት ብዙ ጥረት ይጠይቃል።

4. ኢየሱስ ዕንቁ ስለሚፈልግ ነጋዴ የተናገረው ምሳሌ የያዘው ዋና መልእክት ምንድን ነው?

4 ከረጅም ዘመን አንስቶ ውብ ዕንቁዎች ከፍተኛ ዋጋ የነበራቸው ቢሆንም ኢየሱስ ምሳሌውን የተናገረው ከዋጋ አንጻር እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ኢየሱስ በዚህ ምሳሌ ውስጥ የአምላክን መንግሥት እንዲያው ውድ ዋጋ ካለው ዕንቁ ጋር አዛምዶ ብቻ አላለፈም፤ ከዚህ ይልቅ ‘ውብ ዕንቊ የሚፈልገው ነጋዴ’ ዕንቁውን ሲያገኝ የወሰደውን እርምጃ ጎላ አድርጎ ገልጿል። ዕንቁ ከሚሸጥ ከአንድ ተራ ባለ ሱቅ በተለየ ዕንቁ ፍለጋ የሚጓዝ አንድ ነጋዴ በሙያው የተካነ እንደሆነ ይታመናል። ነጋዴው አንድን ዕንቁ በዓይነቱ ልዩ የሚያስብለውን ውበትና ጥራት መንጥሮ የማየት ችሎታ አለው። እውነተኛውን ዕንቁ ዓይቶ ማወቅ ስለሚችል ጥራት በሌለው ወይም አስመስለው በሠሩት የውሸት ዕንቁ አይታለልም።

5, 6. (ሀ) ኢየሱስ በተናገረው ምሳሌ ውስጥ የተጠቀሰው ነጋዴ ምን ለየት ያለ ባሕርይ አለው? (ለ) ስለተደበቀ ሀብት የሚናገረው ምሳሌ ስለ ነጋዴው ምን የሚገልጸው ነገር አለ?

5 ከዚህ አስተዋይ ነጋዴ የምንማረው ሌላም ቁም ነገር አለ። አብዛኞቹ ነጋዴዎች ከዕንቁው ሽያጭ የሚያገኙትን ትርፍ ለማወቅ ዕንቁውን ከመግዛታቸው በፊት ገበያ ላይ ያለውን የመሸጫ ዋጋ ያጣራሉ። በተጨማሪም ወዲያውኑ መሸጥ ስለሚፈልጉ፣ የሚገዙት ዕንቁ ገበያ ላይ ተፈላጊ መሆን አለመሆኑን ያጤናሉ። በሌላ አባባል የነጋዴዎቹ ፍላጎት ዕንቁውን ይዞ መቀመጥ ሳይሆን የገዙትን ዕንቁ በቶሎ ሸጦ ትርፍ ማግኘት ነው። ኢየሱስ በምሳሌው ላይ የጠቀሰው ነጋዴ አስተሳሰብ ግን የተለየ ነው። የእርሱ ፍላጎት ገንዘብ ወይም ሌላ ጥቅም ማግኘት አይደለም። እንዲያውም ሲፈልገው የነበረውን ነገር በእጁ ለማስገባት ሲል “ያለውን ሁሉ” ማለትም የግል ንብረቱንና ሀብቱን በሙሉ ለመሠዋት ፈቃደኛ ነበር።

6 በአብዛኞቹ ነጋዴዎች አስተሳሰብ ኢየሱስ በተናገረው ምሳሌ ውስጥ የተጠቀሰው ግለሰብ ያደረገው ነገር የቂል ሥራ ይመስል ይሆናል። አንድ ብልጥ ነጋዴ እንዲህ ዓይነት የማያዋጣ ነገር አያደርግም። በምሳሌው ውስጥ የተጠቀሰው ነጋዴ ግን ለሀብት ያለው አመለካከት የተለየ ነው። የእርሱ ፍላጎት ገንዘብ ማትረፍ ሳይሆን እጅግ የላቀ ዋጋ ያለውን ነገር እጁ በማስገባት ደስታና እርካታ ማግኘት ነው። ኢየሱስ በተናገረው በአንድ ተመሳሳይ ምሳሌ ላይ ይህን ነጥብ ግልጽ አድርጎታል። “መንግሥተ ሰማይ በዕርሻ ውስጥ የተደበቀ ሀብት ትመስላለች፤ አንድ ሰው ባገኛት ጊዜ መልሶ ሸሸጋት፤ ከመደሰቱም የተነሣ ሄዶ፤ ያለውን ሁሉ በመሸጥ ያንን የዕርሻ ቦታ ገዛ” ብሏል። (ማቴዎስ 13:44) አዎ፣ ሰውየው ያንን ሀብት ማግኘቱና የግሉ ማድረጉ የሚያስገኝለት ደስታ ያለውን ሁሉ እንዲሸጥ አነሳስቶታል። በዛሬው ጊዜ እንዲህ ዓይነት ሰዎች ይገኛሉ? ደግሞስ እንዲህ ዓይነት መሥዋዕት ሊከፈልለት የሚገባ ሀብት ይኖራል?

የአምላክን መንግሥት ዋጋማነት የተገነዘቡ ሰዎች

7. ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ያለውን የላቀ ዋጋ በሚገባ እንደተገነዘበ ያሳየው እንዴት ነው?

7 ኢየሱስ ምሳሌውን የተናገረው ስለ “መንግሥተ ሰማይ” ለማስረዳት ብሎ ሲሆን የአምላክ መንግሥት ትልቅ ዋጋ እንዳለውም በሚገባ ያውቅ ነበር። የወንጌል ዘገባዎች በዚህ ጉዳይ ላይ አሳማኝ ምሥክርነት ይሰጣሉ። ኢየሱስ በ29 ከክርስቶስ ልደት በኋላ እንደተጠመቀ “‘ንስሓ ግቡ፤ የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርባለችና’ እያለ መስበክ ጀመረ።” ለሦስት ዓመት ተኩል ያህል ብዙ ሰዎችን ስለ አምላክ መንግሥት አስተማረ። በመላው የይሁዳ ምድር እየተዘዋወረ “የእግዚአብሔርን መንግሥት የምሥራች ቃል እየሰበከ በየከተማውና በየመንደሩ አለፈ።”—ማቴዎስ 4:17፤ ሉቃስ 8:1

8. ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት የሚያከናውናቸውን ነገሮች ለማሳየት ምን አድርጓል?

8 ኢየሱስ የታመሙትን መፈወስን፣ የተራቡትን መመገብን፣ የተፈጥሮ ኃይሎችን መቆጣጠርንና ሙታንን ማስነሳትን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ተአምራት በመፈጸም የአምላክ መንግሥት የሚያከናውናቸውንም ነገሮች አሳይቷል። (ማቴዎስ 14:14-21፤ ማርቆስ 4:37-39፤ ሉቃስ 7:11-17) በመጨረሻም በመከራ እንጨት ላይ መሥዋዕታዊ ሞት በመሞት ለአምላክና በሰማይ ለተቋቋመው መንግሥት ያለውን ታማኝነት አረጋግጧል። ነጋዴው “እጅግ ውድ የሆነ ዕንቊ” ለማግኘት ሲል ያለውን ሁሉ ለመስጠት ፈቃደኛ እንደሆነ ሁሉ ኢየሱስም እስከ ሕይወቱ መጨረሻ ድረስ ለአምላክ መንግሥት በታማኝነት ቆሟል።—ዮሐንስ 18:37

9. የቀድሞዎቹ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ምን በዓይነቱ ልዩ የሆነ ባሕርይ አሳይተዋል?

9 ኢየሱስ ሕይወቱ በአምላክ መንግሥት ላይ እንዲያተኩር ከማድረጉም ሌላ ጥቂት ተከታዮች አፍርቷል። እነርሱም ቢሆኑ ይህ መንግሥት ከፍተኛ ዋጋ እንዳለው በጥልቅ ተገንዝበው ነበር። ቀደም ሲል የመጥምቁ ዮሐንስ ደቀ መዝሙር የነበረው እንድርያስ ከእነርሱ መካከል አንዱ ነው። እንድርያስና አንድ ሌላ የዮሐንስ ደቀ መዝሙር (ዮሐንስ የሚባለው የዘብዴዎስ ልጅ ሳይሆን አይቀርም) ኢየሱስ “የእግዚአብሔር በግ መሆኑን” መጥምቁ ዮሐንስ ሲመሰክር ሰምተው ወዲያውኑ ኢየሱስን መከተል ጀመሩ፤ በእርሱም አመኑ። ሆኖም ጉዳዩ በዚህ አላበቃም። እንድርያስ ምንም ጊዜ ሳያባክን የሥጋ ወንድሙ ስምዖን ጋር ሄዶ “መሲሑን አገኘነው” ብሎ ነገረው። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ስምዖን (ኬፋ ወይም ጴጥሮስ በሚል ስያሜ የሚታወቀው) እንዲሁም ፊልጶስና ጓደኛው ናትናኤል ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን ተገነዘቡ። እንዲያውም ናትናኤል ኢየሱስን “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ፤ አንተ የእስራኤል ንጉሥ ነህ” ብሎታል።—ዮሐንስ 1:35-49

ለተግባር ተነሳሱ

10. ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ከተወሰነ ጊዜ በኋላ በድጋሚ አግኝቶ እንዲከተሉት ሲነግራቸው ምን አደረጉ?

10 እንድርያስ፣ ጴጥሮስ፣ ዮሐንስና ሌሎች መሲሑን ባገኙ ጊዜ የተሰማቸውን ደስታ ነጋዴው እጅግ ውድ የሆነ ዕንቁ ባገኘ ጊዜ ከተሰማው ደስታ ጋር ማወዳደር ይቻላል። ታዲያ ምን ያደርጉ ይሆን? ለመጀመሪያ ጊዜ ኢየሱስን ካገኙት በኋላ ወዲያውኑ ምን እንዳደረጉ የወንጌል ዘገባዎች ብዙም የሚናገሩት ነገር የለም። አብዛኞቹ ወደ ወትሮ ኑሯቸው እንደተመለሱ ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። ይሁን እንጂ ከስድስት ወር እስከ አንድ ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ኢየሱስ እንድርያስን፣ ጴጥሮስን፣ ዮሐንስንና ወንድሙን ያዕቆብን በገሊላ ባሕር ላይ ዓሣ ሲያጠምዱ አገኛቸው። a በዚህ ጊዜ ኢየሱስ “ኑ፣ ተከተሉኝ፤ ሰዎችን አጥማጆች አደርጋችኋለሁ” አላቸው። ታዲያ ምን አደረጉ? የማቴዎስ ዘገባ “ወዲያው መረባቸውን ትተው ተከተሉት” በማለት ጴጥሮስና እንድርያስ ያደረጉትን ይገልጻል። ያዕቆብና ዮሐንስን በተመለከተ “ወዲያውኑ ጀልባቸውንም ሆነ አባታቸውን ትተው ተከተሉት” የሚል እናነባለን። ሉቃስ ያሰፈረው ዘገባ ደግሞ “ሁሉን ትተው ተከተሉት” የሚል ተጨማሪ ሐሳብ ይዟል።—ማቴዎስ 4:18-22፤ ሉቃስ 5:1-11

11. ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ እንዲከተሉት ሲጠራቸው አፋጣኝ ምላሽ የሰጡት ለምን ሊሆን ይችላል?

11 ደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ዓይነት ፈጣን ምላሽ የሰጡት በስሜት ተገፋፍተው ይሆን? በፍጹም! ምንም እንኳ ከኢየሱስ ጋር መጀመሪያ ከተገናኙ በኋላ በቤተሰብ መልክ ወደሚያከናውኑት ዓሣ የማጥመድ ሥራ የተመለሱ ቢሆንም በዚያን ጊዜ ያዩትና የሰሙት ነገር በልባቸውና በአእምሯቸው ላይ የማይረሳ ትዝታ ጥሎባቸው እንዳለፈ ግልጽ ነው። ከዚያ በኋላ የነበረው ወደ አንድ ዓመት የሚጠጋ ጊዜ በእነዚያ ጉዳዮች ላይ የሚያሰላስሉበት በቂ ጊዜ እንዲያገኙ አስችሏቸዋል። አሁን አንድ አቋም የሚወስዱበት ጊዜ ደርሷል። ደቀ መዛሙርቱ፣ ውድ የሆነ ዕንቁ ሲያገኝ ልቡ በደስታ ከመፈንደቁ የተነሳ ዕንቁውን ወዲያው “ሄዶ” ለመግዛት አስፈላጊውን ነገር እንዳደረገው ነጋዴ ተመሳሳይ እርምጃ ይወስዱ ይሆን? ምን ጥያቄ አለው፤ ባዩትና በሰሙት ነገር ልባቸው ተነክቷል። እርምጃ የሚወስዱበት ጊዜ መድረሱን ተገንዝበዋል። በመሆኑም ዘገባው እንደሚለው ምንም ሳያቅማሙ ያላቸውን ሁሉ እርግፍ አድርገው በመተው ኢየሱስን መከተል ጀምረዋል።

12, 13. (ሀ) የኢየሱስን ስብከት ያዳመጡ ብዙ ሰዎች የሰጡት ምላሽ ምን ነበር? (ለ) ኢየሱስ ታማኝ ደቀ መዛሙርቱን በተመለከተ ምን ብሏል? እንደዚያ ሲልስ ምን ማለቱ ነበር?

12 እነዚህ ታማኝ ሰዎች በወንጌል ዘገባዎች ውስጥ ከተጠቀሱ ሌሎች ሰዎች ፈጽሞ የተለየ አቋም ነበራቸው! ኢየሱስ የፈወሳቸውና የመገባቸው ሰዎች በጣም ብዙ ቢሆኑም ሁሉም ወደ ግል ጉዳያቸው ተመልሰዋል። (ሉቃስ 17:17, 18፤ ዮሐንስ 6:26) እንዲያውም አንዳንዶች ኢየሱስ ተከታዮቹ እንዲሆኑ ሲጠራቸው መምጣት የማይችሉበትን ሰበብ አቅርበዋል። (ሉቃስ 9:59-62) ከእነዚህ ፍጹም በተለየ ኢየሱስ ስለ ታማኝ ተከታዮቹ በሌላ ጊዜ እንዲህ ብሏል:- “ከመጥምቁ ዮሐንስ ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ ብዙዎች መንግሥተ ሰማያትን ለማግኘት ይጋደላሉ፤ በተጋድሏቸው የሚጸኑም ወራሽ ይሆናሉ።”—ማቴዎስ 11:12 NW

13 ‘መጋደል’ እና ‘በተጋድሎ መጽናት’ የሚሉት ቃላት ምን ሐሳብ ያስተላልፋሉ? እነዚህ ቃላት የተገኙበትን የግሪክኛውን ግስ በተመለከተ ቫይንስ ኤክስፖዚተሪ ዲክሽነሪ ኦቭ ኦልድ ኤንድ ኒው ቴስታመንት ወርድስ የተባለው መዝገበ ቃላት “ግሱ ከፍተኛ ጥረት ማድረግን ያመለክታል” ይላል። ይህን ጥቅስ በተመለከተ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑር የሆኑት ሃይነሪክ ሜየር እንዲህ ብለዋል:- “መምጫው የተቃረበውን መሲሐዊውን መንግሥት ለማግኘት የነበራቸው ጉጉት፣ ከፍተኛ ፍላጎትና ጥሮሽ የተገለጸው በዚህ መንገድ ነው . . . መንግሥቱን ይጠባበቁ የነበሩት (በለዘብተኝነትና በጥርጣሬ ሳይሆን) በከፍተኛ ጉጉትና በሙሉ ልብ ነበር።” በምሳሌው ላይ እንደተጠቀሰው ነጋዴ ሁሉ እነዚህ ጥቂት ግለሰቦችም እውነተኛ ዋጋ ያለው ነገር ምን እንደሆነ ወዲያውኑ የተገነዘቡ ከመሆኑም ሌላ የአምላክን መንግሥት ለማግኘት ሲሉ የነበራቸውን ሁሉ በፈቃደኝነት ሠውተዋል።—ማቴዎስ 19:27, 28፤ ፊልጵስዩስ 3:8

ሌሎችም በፍለጋው ተሰማሩ

14. ኢየሱስ ሐዋርያቱን ለስብከቱ ሥራ ያዘጋጃቸው እንዴት ነው? ውጤቱስ ምን ነበር?

14 ኢየሱስ አገልግሎቱን ባከናወነበት ወቅት ሌሎችም መንግሥቱን ማግኘት እንዲችሉ ሥልጠናና ድጋፍ ሰጥቷቸዋል። በመጀመሪያ ከደቀ መዛሙርቱ መካከል 12ቱን መርጦ ሐዋርያት (የተላኩ ማለት ነው) ብሎ ሾማቸው። ኢየሱስ ለሐዋርያቱ አገልግሎታቸውን እንዴት እንደሚያከናውኑ ዝርዝር መመሪያ የሰጣቸው ከመሆኑም ሌላ ወደፊት ስለሚጠብቃቸው አስቸጋሪ ሁኔታና መከራ አስጠንቅቋቸዋል። (ማቴዎስ 10:1-42፤ ሉቃስ 6:12-16) በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ገደማ ኢየሱስ በመላው ይሁዳ እየተዘዋወረ ሲሰብክ አብረውት በመሄድ ከእርሱ ጋር የቅርብ ዝምድና መመሥረት ችለዋል። የሰጣቸውን ትምህርቶች አዳምጠዋል፣ ተአምራዊ ሥራዎቹን አይተዋል እንዲሁም የተወውን ምሳሌ ተመልክተዋል። (ማቴዎስ 13:16, 17) እነዚህ ሁሉ ነገሮች በጥልቅ ስለነኳቸው እንደ ዕንቁ ነጋዴው እነርሱም የአምላክን መንግሥት ለማግኘት በቅንዓትና በሙሉ ልብ ተነሳስተዋል።

15. የኢየሱስን ተከታዮች ይበልጥ ደስ የሚያሰኛቸው እርሱ የተናገረው የትኛው ሐሳብ ነው?

15 ኢየሱስ ከ12ቱ ሐዋርያት በተጨማሪ “ሌሎች ሰባ . . . ሰዎችን መርጦ ሾመ፤ ወደሚሄድበትም ከተማና ቦታ ሁሉ እንዲቀድሙት፣ ሁለት ሁለት አድርጎ ላካቸው።” በተጨማሪም ወደፊት ስለሚጠብቃቸው ፈተናና መከራ የነገራቸው ከመሆኑም ሌላ ለሰዎች “የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ ቀርባለች” ብለው እንዲሰብኩ መመሪያ ሰጣቸው። (ሉቃስ 10:1-12) ሰባዎቹ ደቀ መዛሙርት ተመልሰው ሲመጡ በጣም ተደስተው የነበረ ሲሆን ኢየሱስን “ጌታ ሆይ፤ አጋንንት እንኳ በስምህ ተገዙልን” በማለት ያጋጠማቸውን ሁኔታ ነገሩት። ይሁንና ኢየሱስ የአምላክን መንግሥት በቅንዓት በመደገፋቸው የላቀ ደስታ እንደሚጠብቃቸው ሲነግራቸው ሳይገረሙ አይቀሩም። “መናፍስት ስለተገዙላችሁ በዚያ ደስ አይበላችሁ፤ ስማችሁ ግን በሰማይ ስለ ተጻፈ ደስ ይበላችሁ” አላቸው።—ሉቃስ 10:17, 20

16, 17. (ሀ) ኢየሱስ ከታማኝ ሐዋርያቱ ጋር ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት ምን ነገራቸው? (ለ) ኢየሱስ ለሐዋርያቱ ምን የሚያስደስትና የሚያበረታታ ነገር ነገራቸው?

16 በመጨረሻም ኢየሱስ ኒሳን 14, 33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ከሐዋርያቱ ጋር ባሳለፋት የመጨረሻ ምሽት የጌታ እራት የተባለውን በዓል ያቋቋመ ሲሆን ዕለቱን ለመታሰቢያው እንዲያከብሩለትም አዘዛቸው። በዚያ ምሽት ኢየሱስ አብረውት ለቆዩት ለአሥራ አንዱ ሐዋርያት እንዲህ አላቸው:- “እናንተም ሳትለዩኝ በመከራዬ ጊዜ በአጠገቤ የቆማችሁ ናችሁ፤ አባቴ እኔን እንደ ሾመኝ እኔም ደግሞ በመንግሥቴ እሾማችኋለሁ፤ ይኸውም በመንግሥቴ ከማእዴ እንድትበሉና እንድትጠጡ ደግሞም በዙፋን ላይ ተቀምጣችሁ በዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ላይ እንድትፈርዱ ነው።”—ሉቃስ 22:19, 20, 28-30

17 ኢየሱስ እንዲህ ሲላቸው ሐዋርያቱ በጣም ተደስተው መሆን አለበት! ማንኛውም ሰው ሊያገኘው ከሚችለው እጅግ የላቀ ክብርና መብት ተሰጣቸው። (ማቴዎስ 7:13, 14፤ 1 ጴጥሮስ 2:9) በምሳሌው ላይ እንደተጠቀሰው ዕንቁ ነጋዴ ሁሉ እነርሱም ኢየሱስን በመከተል መንግሥቱን ለማግኘት ባደረጉት ጥረት ብዙ ነገሮችን ሠውተዋል። ይሁንና እስከዚያን ጊዜ ድረስ የከፈሏቸው መሥዋዕቶች በከንቱ እንዳልቀሩ ማረጋገጫ ተሰጣቸው።

18. ከአሥራ አንዱ ሐዋርያት በተጨማሪ ጊዜው ሲደርስ ከአምላክ መንግሥት ጥቅም የሚያገኙት እነማን ናቸው?

18 ከአምላክ መንግሥት ጥቅም የሚያገኙት በዚያ ምሽት ከኢየሱስ ጋር የነበሩት ሐዋርያት ብቻ አይደሉም። ይሖዋ፣ በሰማይ በሚገኘው ክብራማ መንግሥት ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ተባባሪ ገዢዎች የሚሆኑና በመንግሥት ቃል ኪዳን ውስጥ የሚታቀፉ በጥቅሉ 144,000 ሰዎችን የመምረጥ ዓላማ ነበረው። ከዚህ በተጨማሪ ሐዋርያው ዮሐንስ “በዙፋኑና በበጉ ፊት ማንም ሊቈጥራቸው የማይችል . . . እጅግ ብዙ ሕዝብ ቆመው . . . ‘ማዳን በዙፋኑ ላይ የተቀመጠው፣ የአምላካችንና የበጉ ነው’” ሲሉ በራእይ ተመልክቷል። እነዚህ በምድር ላይ የሚኖሩ የአምላክ መንግሥት ተገዢዎች ናቸው። bራእይ 7:9, 10፤ 14:1, 4

19, 20. (ሀ) ለሕዝቦች ሁሉ ምን አጋጣሚ ተከፍቶላቸዋል? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ መልስ የሚያገኘው ጥያቄ ምንድን ነው?

19 ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከማረጉ ከጥቂት ጊዜ በፊት ታማኝ ተከታዮቹን እንዲህ ሲል አዟቸዋል:- “ስለዚህ ሂዱና ሕዝቦችን ሁሉ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ አስተምሯቸው፤ እኔም እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።” (ማቴዎስ 28:19, 20) በመሆኑም ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ሰዎች የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ይሆናሉ ማለት ነው። እነዚህም ውርሻቸው በሰማይ መኖርም ሆነ በምድር ልባቸውን በአምላክ መንግሥት ላይ ስለሚያኖሩ ነጋዴው ውብ ዕንቁ ሲያገኝ ያደረገውን ዓይነት እርምጃ ወስደዋል።

20 ይህ የኢየሱስ አነጋገር ደቀ መዝሙር የማድረጉ ሥራ “እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ” እንደሚቀጥል ያሳያል። ታዲያ በዘመናችን የአምላክን መንግሥት ለማግኘት ሲሉ ያላቸውን ሁሉ መሥዋዕት ለማድረግ ፈቃደኛ የሆኑ ነጋዴውን የሚመስሉ ግለሰቦች አሉ? ይህ ጥያቄ በሚቀጥለው ርዕስ ላይ መልስ ያገኛል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a የዘብዴዎስ ልጅ ዮሐንስ ኢየሱስ ያከናወናቸውን ነገሮች በወንጌል ዘገባው ላይ በግልጽ እንዲያሰፍር ያስቻለው ለመጀመሪያ ጊዜ ከኢየሱስ ጋር ከተገናኘ በኋላ ለተወሰነ ወቅት ከእርሱ ጋር በመሆን ያደረጋቸውን አንዳንድ ነገሮች ተመልክቶ ስለነበር ሳይሆን አይቀርም። (ዮሐንስ ምዕራፍ 2-5) ይሁን እንጂ ኢየሱስ እንዲከተለው እስከጠራው ጊዜ ድረስ ወደ ዓሣ ማጥመድ ሥራው ተመልሷል።

b ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች ከተዘጋጀው ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት ከተባለው መጽሐፍ ላይ ምዕራፍ 10ን ተመልከት።

ልታብራራ ትችላለህ?

• ስለ ነጋዴው የሚገልጸው ምሳሌ የያዘው ዋና መልእክት ምንድን ነው?

• ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ላለው የላቀ ዋጋ ልባዊ አድናቆት እንዳለው ያሳየው እንዴት ነው?

• እንድርያስ፣ ጴጥሮስ፣ ዮሐንስና ሌሎች ኢየሱስ እንዲከተሉት ሲጠራቸው ወዲያውኑ ምላሽ እንዲሰጡ ያደረጋቸው ምንድን ነው?

• ሕዝቦች ሁሉ ምን ግሩም አጋጣሚ ተከፍቶላቸዋል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

‘ሁሉን ትተው ኢየሱስን ተከትለውታል’

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት ተከታዮቹን ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉ አዟቸዋል