በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋ ምንጊዜም የሚያደርገው ትክክል የሆነውን ነው

ይሖዋ ምንጊዜም የሚያደርገው ትክክል የሆነውን ነው

ይሖዋ ምንጊዜም የሚያደርገው ትክክል የሆነውን ነው

“እግዚአብሔር በመንገዱ ሁሉ ጻድቅ . . . ነው።”—መዝሙር 145:17

1. አንድ ሰው ስለ አንተ የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ ቢደርስ ምን ይሰማሃል? ከእንዲህ ዓይነቱ ገጠመኝ ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?

 ተሟላ መረጃ ሳያገኝ ምናልባትም አድራጎትህን ወይም ዓላማህን በመጠራጠር ስለ አንተ የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ የደረሰ ሰው አጋጥሞህ ያውቃል? ከሆነ በነገሩ ሳትጎዳ አትቀርም፤ እንደዚያ ቢሰማህ አይፈረድብህም። ከዚህ አንድ ከፍተኛ ቁም ነገር እንማራለን:- ስለ አንድ ጉዳይ የተሟላ ግንዛቤ ሳይኖረን ቸኩሎ አንድ መደምደሚያ ላይ ከመድረስ መቆጠብ ጥበብ ነው።

2, 3. አንዳንዶች ለጥያቄዎቻቸው መልስ የሚሆን በቂ ማብራሪያ የሌላቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች በተመለከተ ምን ይሰማቸዋል? ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ይሖዋ ምን ይነግረናል?

2 ይሖዋ አምላክን በተመለከተ አንዳንድ ድምዳሜዎች ላይ ከመድረሳችን በፊት ይህን ነጥብ ማስታወስ ይኖርብናል። ለምን? ምክንያቱም መጀመሪያ ላይ ግራ የሚያጋቡ የሚመስሉ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ስላሉ ነው። ምናልባትም አንዳንድ የአምላክ አገልጋዮች ስላደረጉት ነገር ወይም አምላክ ከዚህ በፊት ስለወሰዳቸው የፍርድ እርምጃዎች የሚያወሱት እነዚህ ዘገባዎች በአእምሯችን ውስጥ ለሚፈጠሩብን ጥያቄዎች በሙሉ መልስ ለማግኘት ዝርዝር ማብራሪያ አልያዙ ይሆናል። የሚያሳዝነው አንዳንዶች ዘገባዎቹን የሚተቹ ከመሆኑም በላይ አምላክ ጻድቅና ፍትሐዊ ስለመሆኑ እስከመጠራጠር ደርሰዋል። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር በመንገዱ ሁሉ ጻድቅ” እንደሆነ ይናገራል። (መዝሙር 145:17) በተጨማሪም ቃሉ እርሱ ‘ክፋትን እንደማይሠራ’ ማረጋገጫ ይሰጠናል። (ኢዮብ 34:12፤ መዝሙር 37:28) ስለዚህ ሌሎች ስለ እርሱ የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ ሲደርሱ ምን እንደሚሰማው አስብ!

3 እስቲ የይሖዋን ፍርድ እንዳንጠራጠር የሚያደርጉንን አምስት ምክንያቶች እንመልከት። ከዚያም አምስቱን ነጥቦች በአእምሯችን ይዘን አንዳንዶች ለመረዳት አስቸጋሪ ሆነው የሚያገኟቸውን ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች እንመረምራለን።

የይሖዋን ፍርድ መጠራጠር የሌለብን ለምንድን ነው?

4. አምላክ ስለወሰደው እርምጃ ስናስብ አቅማችንን ማወቅ የሚኖርብን ለምንድን ነው? በምሳሌ አስረዳ።

4 በመጀመሪያ ደረጃ ይሖዋ ከአንድ ጉዳይ ጋር የተያያዙትን መረጃዎች በሙሉ ያውቃል፤ እኛ ግን እንዲህ ዓይነት እውቀት የለንም። በመሆኑም አምላክ ስለወሰደው እርምጃ ስናስብ የማናውቀው ነገር እንዳለ ማመን ይኖርብናል። ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል:- ከአድልዎ ነፃ የሆነ ውሳኔ በመስጠት ረገድ መልካም ስም ያተረፈ አንድ ዳኛ በአንድ የፍርድ ጉዳይ ላይ ብያኔ ሰጠ እንበል። አንድ ሰው የተሟላ መረጃ ሳይኖረው ወይም ከጉዳዩ ጋር የተያያዙትን ሕጎች ሳያውቅ የዳኛውን ውሳኔ ቢነቅፍ ምን ይሰማሃል? ሰውየው በአንድ ጉዳይ ላይ የተሟላ እውቀት ሳይኖረው ፍርድ መስጠቱ ቂልነት ይሆንበታል። (ምሳሌ 18:13) ታዲያ ደካማ የሆኑ ሰዎች “የምድር ሁሉ ዳኛ” የሆነው ይሖዋን መንቀፋቸው እንዴት ያለ ታላቅ ቂልነት ነው!—ዘፍጥረት 18:25

5. አምላክ በአንዳንድ ግለሰቦች ላይ ስለወሰደው የቅጣት ፍርድ የሚያወሱ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎችን ስናነብ መርሳት የሌለብን ነገር ምንድን ነው?

5 የአምላክን ፍርድ ሳንጠራጠር እንድንቀበል የሚያደርገን ሁለተኛው ምክንያት እርሱ ከሰዎች በተለየ መልኩ ልብን ማንበብ የሚችል መሆኑ ነው። (1 ሳሙኤል 16:7) ቃሉ “እኔ እግዚአብሔር ለሰው ሁሉ እንደ መንገዱ፣ እንደ ሥራው ፍሬ ለመስጠት፣ ልብን እመረምራለሁ፤ የአእምሮንም ሐሳብ እፈትናለሁ” ይላል። (ኤርምያስ 17:10) ስለዚህ አምላክ በአንዳንድ ግለሰቦች ላይ ስለወሰደው ፍርድ የሚያወሱ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎችን ስናነብ አንዳች ነገር ከዓይኑ ስለማያመልጥ በቃሉ ውስጥ ያልሰፈሩትን የግለሰቦቹን አስተሳሰብ፣ ውስጣዊ ዝንባሌና ዓላማ ግምት ውስጥ እንዳስገባ መዘንጋት የለብንም።—1 ዜና መዋዕል 28:9

6, 7. (ሀ) ይሖዋ ከፍተኛ መሥዋዕትነት ቢጠይቅበትም እንኳ የፍትሕና የጽድቅ መሥፈርቶቹን እንደማይጥስ ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) አምላክ የወሰደው እርምጃ ፍትሐዊ ወይም ትክክል መሆኑን እንድንጠይቅ የሚያደርግ ታሪክ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ብናነብ ምን ማስታወስ ይኖርብናል?

6 አሁን ደግሞ የይሖዋን ፍርድ እንዳንጠራጠር የሚያደርገንን ሦስተኛ ምክንያት ተመልከት:- ከፍተኛ መሥዋዕትነት ቢጠይቅበትም የጽድቅ መሥፈርቶቹን አይጥስም። ለዚህ አንድ ምሳሌ እንመልከት። ይሖዋ ታዛዥ የሰው ልጆችን ከኃጢአትና ከሞት ነፃ ለማውጣት ሲል ልጁን ቤዛ አድርጎ በመስጠት የፍትሕና የጽድቅ መሥፈርቱ እንዲሟላ አድርጓል። (ሮሜ 5:18, 19) ሆኖም የሚወድደው ልጁ በመከራ እንጨት ላይ ተሰቃይቶ ሲሞት ማየት ለይሖዋ ከምንገምተው በላይ ከባድ ስቃይ አስከትሎበት መሆን አለበት። ይህ ሁኔታ ስለ እርሱ ምን ያስገነዝበናል? መጽሐፍ ቅዱስ ‘በኢየሱስ ክርስቶስ ስለሆነው ቤዛነት’ ሲናገር “ጽድቁን [የአምላክን ጽድቅ] ለማሳየት ነው” ይላል። (ሮሜ 3:24-26) በሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ላይ ሮሜ 3:25 እንዲህ ይላል:- “ይህ እንደሚያሳየው አምላክ ምንጊዜም የሚያደርገው ትክክልና ፍትሐዊ የሆነውን ነገር ነው።” (ኒው ሴንቸሪ ቨርሽን) አዎ፣ ይሖዋ ቤዛውን ለማቅረብ ይህን ያህል ፈቃደኛ መሆኑ ‘ትክክልና ፍትሐዊ ለሆነ ነገር’ እጅግ የላቀ ግምት እንደሚሰጥ ያሳያል።

7 ስለዚህ አንዳንዶች አምላክ የወሰደው እርምጃ ፍትሐዊና ትክክል ስለመሆኑ ጥርጣሬ ያሳደረባቸውን አንድ ታሪክ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብናነብ ይሖዋ ለጽድቅና ለፍትሕ መሥፈርቶቹ ታማኝ ከመሆኑ የተነሳ የራሱን ልጅ አሰቃቂ ሞት ከመሞት እንዲያመልጥ እንዳላደረገው መዘንጋት አይኖርብንም። ታዲያ እነዚህን መሥፈርቶች ከሌሎች ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ይጥሳል? ሐቁ ይሖዋ የጽድቅና የፍትሕ መሥፈርቶቹን ፈጽሞ የማይጥስ መሆኑ ነው። በመሆኑም ይሖዋ የሚያደርገው ሁሉ ትክክልና ፍትሐዊ እንደሆነ የሚያሳምነን አጥጋቢ ምክንያት አለን።—ኢዮብ 37:23

8. ሰዎች ይሖዋ ፍትሕና ጽድቅ ሊጎድለው ይችላል ብለው ማሰባቸው ምክንያታዊ የማይሆነው ለምንድን ነው?

8 የይሖዋን ፍርድ ሳንጠራጠር እንድንቀበል የሚያደርገንን አራተኛ ምክንያት ተመልከት:- ይሖዋ ሰውን የፈጠረው በራሱ መልክ ነው። (ዘፍጥረት 1:27) በመሆኑም ሰዎች የተፈጠሩት ፍትሕንና ጽድቅን ጨምሮ አምላክ ያሉትን ባሕርያት እንዲያንጸባርቁ ተደርገው ነው። እኛ ያለን የፍትሕና የጽድቅ ባሕርይ እነዚሁ ባሕርያት በይሖዋ ዘንድ ላይገኙ ይችላሉ ብለን እንድናስብ ካደረገን ይህ እርስ በርሱ የሚጋጭ ጉዳይ ይሆናል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ግራ ካጋባን በወረስነው ኃጢአት የተነሳ ፍትሐዊና ትክክል ለሆነ ነገር ያለን አመለካከት የተዛባ መሆኑን ማስታወስ ይኖርብናል። በመልኩ የፈጠረን ይሖዋ አምላክ በፍትሕና በጽድቅ ረገድ ፍጹም ነው። (ዘዳግም 32:4) ሰዎች ከአምላክ የበለጠ ፍትሐዊና ጻድቅ ይሆናሉ ብሎ ማሰቡ በራሱ ሞኝነት ነው!—ሮሜ 3:4, 5፤ 9:14

9, 10. ይሖዋ አድራጎቱን በተመለከተ ለሰዎች ማብራሪያ ወይም ማስረጃ እንዲያቀርብ የማይገደደው ለምንድን ነው?

9 የይሖዋን ፍርድ እንዳንጠራጠር የሚያደርገን አምስተኛው ምክንያት እርሱ “በምድር ሁሉ ላይ ልዑል” መሆኑ ነው። (መዝሙር 83:18) በመሆኑም የሚያደርጋቸውን ነገሮች በተመለከተ ለሰዎች ማብራሪያ ወይም ማስረጃ የማቅረብ ግዴታ የለበትም። ይሖዋ ታላቁ ሸክላ ሠሪ ሲሆን እኛ ደግሞ እርሱ የፈቀደውን ዓይነት የሸክላ ዕቃ የሚያደርገን ጭቃዎች ነን። (ሮሜ 9:19-21) በእርሱ እጅ የተሠራን የሸክላ ዕቃዎች እስከሆንን ድረስ የእርሱን ውሳኔ ወይም ሥራ የምንቃወም እኛ ማን ነን? ኢዮብ ይሖዋ ከሰው ልጆች ጋር ያለውን ግንኙነት በተሳሳተ መንገድ በተረዳ ጊዜ “ፍርዴን ታቃልላለህን? ወይስ አንተ ጻድቅ ለመሆን እኔን ትኰንናለህ?” ብሎ በመጠየቅ አርሞታል። ኢዮብ የተናገረው ሳያስተውል መሆኑን በመገንዘብ በኋላ ላይ ንስሐ ገብቷል። (ኢዮብ 40:8፤ 42:6) በአምላክ ላይ እንከን በመፈላለግ ፈጽሞ ስህተት አንሥራ!

10 በግልጽ ማየት እንደምንችለው ይሖዋ ምንጊዜም ቢሆን የሚያደርገው ትክክል የሆነውን ነው ብለን እንድናምን የሚያደርጉ አሳማኝ ምክንያቶች አሉን። የይሖዋን መንገድ በተመለከተ ያገኘነውን ይህን ግንዛቤ በአእምሯችን ይዘን አንዳንዶችን ግራ የሚያጋቡ ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች እስቲ እንመርምር። የመጀመሪያው አንድ የአምላክ አገልጋይ ከወሰደው እርምጃ ጋር የተያያዘ ሲሆን ሌላው ደግሞ አምላክ ራሱ የወሰደው የቅጣት ፍርድ ነው።

ሎጥ ሴቶች ልጆቹን ለመስጠት ሐሳብ ያቀረበው ለምንድን ነው?

11, 12. (ሀ) አምላክ ሥጋ የለበሱ ሁለት መላእክትን ወደ ሰዶም በላከ ጊዜ የተከሰተውን ሁኔታ ተናገር። (ለ) ይህ ዘገባ በአንዳንዶች አእምሮ ውስጥ ምን ጥያቄዎች ፈጥሯል?

11 ዘፍጥረት ምዕራፍ 19 አምላክ ሥጋ የለበሱ ሁለት መላእክትን ወደ ሰዶም በላከ ጊዜ የተከሰተውን ሁኔታ ይገልጻል። ሎጥ እንግዶቹ በቤቱ እንዲያድሩ አጥብቆ ለመናቸው። ይሁን እንጂ በዚያ ምሽት በከተማዋ የሚኖሩ ወንዶች ቤቱን ከብበው ከሥነ ምግባር ውጪ የሆነ ተግባር ለመፈጸም እንግዶቹን እንዲያወጣላቸው ግድ አሉት። ሎጥ ሰዎቹን ሊያግባባቸው ቢሞክርም ምንም ሊሳካለት አልቻለም። ሎጥ እንግዶቹን ለማስጣል በማሰብ እንዲህ አለ:- “ወዳጆቼ ሆይ፤ እባካችሁ እንዲህ ያለውን ክፉ ነገር አታድርጉ። እነሆ፤ ወንድ የማያውቁ ሁለት ሴቶች ልጆች አሉኝ። እነርሱን ላውጣላችሁና የፈለጋችሁትን አድርጉባቸው። በእነዚህ ሰዎች ላይ ግን አንዳች ነገር አታድርጉባቸው፤ እኔን ብለው ወደ ቤቴ ገብተዋልና።” ዓመጸኞቹ ሰዎች ሐሳቡን ለመቀበል ፈቃደኞች አልሆኑም፤ እንዲያውም በሩን ሊሰብሩት ተቃረቡ። በመጨረሻ ወደ ቤቱ የመጡት መላእክት በፆታ ስሜት ያበዱትን ሰዎች ዓይን አሳወሩ።—ዘፍጥረት 19:1-11

12 ይህ ዘገባ በአንዳንዶች አእምሮ ውስጥ ጥያቄ መፍጠሩ ምንም አያስደንቅም። ‘ሎጥ እንግዶቹን ለማዳን ብሎ እንዴት ሴቶች ልጆቹን በፆታ ስሜት ለተቃጠሉ ሰዎች ይሰጣል? ይህ ተገቢ ያልሆነ ወይም የፍርሃት እርምጃ መውሰድ አይሆንበትም?’ ብለው ያስባሉ። ሎጥ እንዲህ ያደረገ ሰው ከሆነ ታዲያ አምላክ ጴጥሮስን በመንፈስ ገፋፍቶ ሎጥ “ጻድቅ ሰው” ነው ብሎ እንዲጽፍ ለምን ያደርገዋል? ሎጥ ያደረገው ነገር በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት አለው? (2 ጴጥሮስ 2:7, 8) የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ እንዳንደርስ እስቲ በዚህ ጉዳይ ላይ በጥሞና እናስብ።

13, 14. (ሀ) ሎጥ ስላደረገው ነገር የሚያወሳውን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ በተመለከተ መርሳት የሌለብን ጉዳይ ምንድን ነው? (ለ) ሎጥ አለመፍራቱን የሚያሳየው ምንድን ነው?

13 በመጀመሪያ ደረጃ መጽሐፍ ቅዱስ የሎጥን ድርጊት ከመደገፍ ወይም ከመኮነን ይልቅ የተከሰተውን ብቻ ገልጾ ማለፉን ማስተዋል ይገባል። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ሎጥ ምን አስቦ እንደነበር ወይም እንደዚያ ዓይነት እርምጃ እንዲወስድ ምን እንዳነሳሳው አይናገርም። ‘ጻድቃን ከሞት በሚነሡበት ጊዜ’ ሕይወት ሲያገኝ ሁኔታውን በዝርዝር ይናገር ይሆናል።—የሐዋርያት ሥራ 24:15

14 ሎጥን ፈሪ የሚያስብለው አንዳች ነገር የለም። ያጋጠመው ሁኔታ በጣም አስቸጋሪ ነበር። ሎጥ “እኔን ብለው ወደ ቤቴ ገብተዋልና” በማለት ስለ እንግዶቹ መናገሩ እነርሱን ከአደጋ የመጠበቅና መጠለያ የመስጠት ግዴታ እንዳለበት እንደተሰማው ያሳያል። ሆኖም እንዲህ ማድረጉ ቀላል አልነበረም። አይሁዳዊው ታሪክ ጸሐፊ ጆሴፈስ ሰዶማውያን “በሰዎች ላይ ግፍ የሚፈጽሙና አምላክን የማይፈሩ . . . እንግዶችን የሚጠሉ እንዲሁም በግብረ ሰዶም ድርጊቶች ራሳቸውን ያስነወሩ” መሆናቸውን ተናግሯል። ይሁንና ሎጥ በጥላቻ የተሞሉትን ሰዎች ፈርቶ አላፈገፈገም። ከዚህ በተቃራኒ ወደ ውጭ ወጥቶ በቁጣ ገንፍለው የነበሩትን ሰዎች ለማግባባት ሞክሯል። እንዲያውም ‘መዝጊያውን ከበስተ ኋላው ዘግቷል።’—ዘፍጥረት 19:6

15. ሎጥ እርምጃ የወሰደው በእምነት ሊሆን ይችላል የሚባለው ለምንድን ነው?

15 አንዳንዶች ‘ሎጥ ለሰዎቹ ሴቶች ልጆቹን ለመስጠት እንዴት ሐሳብ ያቀርባል?’ ብለው ይጠይቁ ይሆናል። መጥፎ ዓላማ እንደነበረው ከማሰብ ይልቅ ለምን አንዳንድ አማራጮችን አንመለከትም? በመጀመሪያ ደረጃ ሎጥ እንደዚያ ያደረገው በእምነት ሊሆን ይችላል። እንዴት? ሎጥ የአጎቱ የአብርሃም ሚስት የሆነችውን ሣራን ይሖዋ እንዴት እንደጠበቃት እንደሚያውቅ ምንም ጥያቄ የለውም። ሣራ በጣም ውብ ስለነበረች አብርሃም እርሷን ለመውሰድ ሲሉ እንዳይገድሉት በመፍራት ወንድሜ ነው እንድትል ነግሯት እንደነበር አስታውስ። a ከዚህም የተነሳ ሣራ ወደ ፈርዖን ቤት ተወሰደች። ይሁንና ይሖዋ ጣልቃ በመግባት ፈርዖን ሣራን እንዳይደፍራት ከለከለው። (ዘፍጥረት 12:11-20) ሎጥ ሴቶች ልጆቹ ተመሳሳይ ጥበቃ ሊያገኙ እንደሚችሉ እምነት አድሮበት ሊሆን ይችላል። የሚያስገርመው፣ ይሖዋ በመላእክቱ አማካኝነት ጣልቃ የገባ ሲሆን ሴቶቹም ከጉዳት ሊጠበቁ ችለዋል።

16, 17. (ሀ) ሎጥ ቤቱን የከበቡትን ወንዶች ለማስደንገጥ ወይም ግራ ለማጋባት የሞከረው እንዴት ነው? (ለ) ሎጥ ያሰበው ነገር ምንም ይሁን ምን እርግጠኛ መሆን የምንችልበት ጉዳይ ምንድን ነው?

16 ሌላም አማራጭ ተመልከት። ሎጥ ሰዎቹን ለማስደንገጥ ወይም ግራ ለማጋባት አስቦም ሊሆን ይችላል። ሰዎቹ ለግብረ ሰዶም ከነበራቸው ጥማት የተነሳ ሴቶች ልጆቹን ላይፈልጓቸው ይችላሉ የሚል እምነት አድሮበት ሊሆን ይችላል። (ይሁዳ 7) ከዚህ በተጨማሪ ሴቶቹ በከተማው ውስጥ ለሚኖሩ ወንዶች ታጭተው ስለነበር የአማቾቹ ዘመዶች፣ ጓደኞች ወይም በሥራ የሚገናኟቸው ሰዎች ደጃፉ ላይ ከተሰበሰቡት መካከል ሳይኖሩ አይቀሩም። (ዘፍጥረት 19:14) ሎጥ እዚያ ከመጡት ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ ዝምድናውን አስበልጠው ሴቶች ልጆቹን ለማስጣል ተቃውሞ ያሰማሉ ብሎ ተስፋ አድርጎ ሊሆን ይችላል። በዚህ መንገድ አንድነቱን ያጣ የዓመጸኞች ቡድን ያን ያህል አስጊ ሊሆን አይችልም። b

17 የሎጥ ሐሳብና ዓላማ ምንም ይሁን ምን ስለ አንድ ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን:- ይሖዋ ምንጊዜም የሚያደርገው ትክክል የሆነውን ስለሆነ ሎጥን “ጻድቅ ሰው” አድርጎ የቆጠረበት አጥጋቢ ምክንያት አለው። እንዲሁም የሚያደርጉትን የማያውቁ እነዚያ ዓመጸኛ ሰዶማውያን የፈጸሙትን ድርጊት የተመለከትን ከሆነ ይሖዋ በዚያች ክፉ ከተማ ውስጥ በሚኖሩ ሰዎች ላይ የቅጣት ፍርድ ለማምጣት አጥጋቢ ምክንያት እንደነበረው የምንጠራጠርበት ነገር ሊኖር ይችላል?—ዘፍጥረት 19:23-25

ይሖዋ ዖዛን የቀሰፈው ለምን ነበር?

18. (ሀ) ዳዊት ታቦቱን ወደ ኢየሩሳሌም ለማምጣት ጥረት ባደረገበት ወቅት ምን ተከሰተ? (ለ) ይህ ዘገባ ምን ጥያቄ ያስነሳል?

18 በአንዳንዶች ላይ ጥያቄ ሊፈጥር የሚችለው ሌላው ዘገባ ዳዊት የቃል ኪዳኑን ታቦት ወደ ኢየሩሳሌም ለማምጣት ካደረገው ጥረት ጋር የተያያዘ ነው። ታቦቱ ሠረገላ ላይ የተጫነ ሲሆን ሠረገላውን የሚነዱት ደግሞ ዖዛና ወንድሙ ነበሩ። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “ወደ ናኮን ዐውድማ ሲደርሱም በሬዎቹ ስለ ተደናቀፉ፣ ዖዛ እጁን ዘርግቶ የእስራኤልን ታቦት ያዘ። ዖዛ በድፍረት ይህን ስላደረገ፣ የእግዚአብሔር ቊጣ በላዩ ላይ ነደደ፤ ስለዚህም እግዚአብሔር ቀሠፈው፤ እርሱም በእግዚአብሔር ታቦት አጠገብ እዚያው ሞተ።” ከተወሰኑ ወራት በኋላ ታቦቱን አምላክ ባዘዘው መሠረት የቀዓት ወገን የሆኑ ሌዋውያን በትከሻቸው ተሸክመው ስላጓጓዙት ይህ ሁለተኛ ሙከራ ሊሳካ ችሏል። (2 ሳሙኤል 6:6, 7፤ ዘኁልቁ 4:15፤ 7:9፤ 1 ዜና መዋዕል 15:1-14) አንዳንዶች ‘ይሖዋ እንዲህ ዓይነት ከባድ እርምጃ የወሰደው ለምንድን ነው? ዖዛ እኮ እንዲህ ያደረገው ታቦቱን ለማዳን ሲል ነው’ ብለው ያስቡ ይሆናል። የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ እንዳንደርስ አንዳንድ ጠቃሚ ዝርዝር ነጥቦችን ልብ ማለታችን አስፈላጊ ነው።

19. ይሖዋ በደል ይፈጽማል ብሎ ማሰብ የማይመስል የሆነው ለምንድን ነው?

19 ይሖዋ በደል ይፈጽማል ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር መሆኑን መዘንጋት የለብንም። (ኢዮብ 34:10) እንዲህ ማድረግ ፍቅር የጎደለው ድርጊት ይሆንበታል፤ መጽሐፍ ቅዱስን ስናጠና ደግሞ “እግዚአብሔር ፍቅር” መሆኑን ተምረናል። (1 ዮሐንስ 4:8) ከዚህ በተጨማሪ ቅዱሳን ጽሑፎች “ጽድቅና ፍትሕ የዙፋንህ መሠረቶች ናቸው” በማለት ይገልጻሉ። (መዝሙር 89:14) ታዲያ ይሖዋ እንዴት በደል ሊፈጽም ይችላል? እንዲህ ቢያደርግ ሉዓላዊነቱ የቆመበትን መሠረት ማናጋት ይሆንበታል።

20. ዖዛ ታቦቱን በተመለከተ ያለውን ሕግ ማወቅ ነበረበት እንድንል የሚያደርጉን አንዳንድ ምክንያቶች የትኞቹ ናቸው?

20 ዖዛ ሕጉን ከማንም በተሻለ ሁኔታ ማወቅ እንደነበረበት መዘንጋት የለብንም። ታቦቱ የይሖዋን መገኘት ይወክል ነበር። ሕጉ፣ ያልተፈቀደላቸው ሰዎች ታቦቱን መንካት እንደሌለባቸው ያዛል፤ መመሪያውን የጣሱ ሰዎች ደግሞ በሞት እንደሚቀጡ በግልጽ ያስጠነቅቃል። (ዘኁልቁ 4:18-20፤ 7:89) ስለዚህ ታቦቱን ወደ ሌላ ቦታ ማጓጓዝ እንደ ቀላል ነገር የሚታይ ሥራ አይደለም። ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው ዖዛ ካህን ባይሆንም እንኳ ሌዋዊ ስለነበረ ሕጉን እንዲያውቅ ይጠበቅበት ነበር። በተጨማሪም ከበርካታ ዓመታት በፊት ታቦቱ በአስተማማኝ ቦታ እንዲቀመጥ ተብሎ ወደ አባቱ ቤት መጥቷል። (1 ሳሙኤል 6:20 እስከ 7:1) ዳዊት ከዚያ ለመውሰድ እስከወሰነበት ጊዜ ድረስ ለ70 ዓመታት ገደማ እዚያው ቆይቷል። በመሆኑም ዖዛ ከልጅነቱ አንስቶ ታቦቱን በተመለከተ ያለውን ሕግ ሳያውቅ አይቀርም።

21. ከዖዛ ጋር በተያያዘ ይሖዋ የልብን ዝንባሌ እንደሚመለከት ማስታወሳችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

21 ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ይሖዋ ልብን ማንበብ ይችላል። የአምላክ ቃል የዖዛ ድርጊት ‘በድፍረት የተደረገ’ መሆኑን ስለሚገልጽ ይሖዋ በዘገባው ላይ በግልጽ ያልሰፈረ አንድ ዓይነት የራስ ወዳድነት ስሜት አይቶበት ሊሆን ይችላል። ምናልባት ዖዛ ገደቡን የማያውቅ ትዕቢተኛ ሰው ይሆን? (ምሳሌ 11:2) አባቱ ቤት ተቀምጦ የነበረውን ታቦት በሕዝብ ፊት እየመራ መውሰዱ እንዲኩራራ አድርጎት ይሆን? (ምሳሌ 8:13) ዖዛ ከነበረው እምነት ማነስ የተነሳ ይሖዋ የእርሱን መገኘት የሚወክለውን ታቦት እንዳይወድቅ ለማድረግ ክንዱ አጭር እንደሆነ ተሰምቶት ይሆን? ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ይሖዋ ትክክለኛ እርምጃ እንደወሰደ እርግጠኞች መሆን እንችላለን? ይሖዋ ፈጣን እርምጃ እንዲወስድ ያደረገው በዖዛ ልብ ውስጥ አንድ ያየው ነገር ቢኖር ነው።—ምሳሌ 21:2

እምነት እንድንጥል የሚያደርግ አሳማኝ ምክንያት

22. የይሖዋ ቃል አንዳንድ ጊዜ የተወሰኑ ጉዳዮችን የማይጠቅስ መሆኑ የእርሱን ጥበብ የሚያሳየው እንዴት ነው?

22 የይሖዋ ቃል አንዳንድ ዝርዝር ጉዳዮችን ሳይጠቅስ ማለፉ የእርሱ ጥበብ አቻ የሌለው መሆኑን ያሳያል። በዚህ መንገድ ይሖዋ በእርሱ የምንታመን መሆናችንን እንድናሳይ አጋጣሚ ይሰጠናል። እስከ አሁን ከተመለከትነው የይሖዋን ፍርድ እንዳንጠራጠር የሚያደርጉ አጥጋቢ ምክንያቶች እንዳሉ ግልጽ አይደለም? አዎ፣ የአምላክን ቃል በቅን ልቦናና ባልተዛባ አእምሮ ካጠናን ይሖዋ ምንጊዜም ፍትሐዊና ትክክል የሆነውን ነገር እንደሚያደርግ በሙሉ ልብ እንድንታመን የሚያስችል ብዙ እውቀት እናገኛለን። ስለዚህ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ወዲያውኑ ግልጽ መልስ የማናገኝላቸው ጥያቄዎች ከፈጠሩብን ይሖዋ ያደረገው ትክክለኛውን ነገር እንደሆነ ሙሉ እምነት ይኑረን።

23. ይሖዋ ወደፊት የሚወስደውን እርምጃ በተመለከተ ምን ዓይነት እምነት ሊኖረን ይችላል?

23 ይሖዋ ወደፊት የሚወስዳቸውን እርምጃዎች በተመለከተም ተመሳሳይ እምነት ሊኖረን ይችላል። በመሆኑም እየቀረበ ባለው ታላቅ መከራ ወቅት ፍርድ ሲሰጥ ‘ጻድቁን ከኀጢአተኛው ጋር አብሮ እንደማያጠፋ’ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (ዘፍጥረት 18:23) ለጽድቅና ለፍትሕ ያለው ፍቅር እንዲህ እንዲያደርግ አያስችለውም። በተጨማሪም ወደፊት በሚመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ የሚያስፈልጉንን ነገሮች በሙሉ ከሁሉ በተሻለ መንገድ እንደሚያሟላልን ሙሉ እምነት ሊኖረን ይችላል።—መዝሙር 145:16

[የግርጌ ማስታወሻ]

a አንድ ጥንታዊ ፓፒረስ አንድ ፈርዖን፣ የታጠቁ ሰዎች ልኮ ባሏን ገድለው ውብ የሆነችውን ሚስቱን ይዘው እንዲመጡ እንዳደረገ ስለሚናገር አብርሃም ያደረበት ፍርሃት ተገቢ ነበር።

b ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት የታኅሣሥ 1, 1979 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 31ን ተመልከት።

ታስታውሳለህ?

• የይሖዋን ፍርድ መጠራጠር የሌለብን በየትኞቹ ምክንያቶች የተነሳ ነው?

• ሎጥ ሴቶች ልጆቹን ለዓመጸኞቹ ሰዎች ለመስጠት ማሰቡን በተመለከተ የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ እንዳንደርስ ምን ሊረዳን ይችላል?

• ይሖዋ ዖዛን የቀሰፈው ለምን እንደሆነ እንድንገነዘብ የሚረዱን የትኞቹ ነጥቦች ናቸው?

• ይሖዋ ወደፊት የሚወስደውን እርምጃ በተመለከተ ምን እምነት ሊኖረን ይችላል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]