በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ክርስቲያናዊ መለያችን እንዳይጠፋ እንጠንቀቅ

ክርስቲያናዊ መለያችን እንዳይጠፋ እንጠንቀቅ

ክርስቲያናዊ መለያችን እንዳይጠፋ እንጠንቀቅ

“‘እናንተ ምስክሮቼ . . . ናችሁ’ ይላል እግዚአብሔር።”—ኢሳይያስ 43:10

1. ይሖዋ ወደ ራሱ የሚስበው ምን ዓይነት ሰዎችን ነው?

 በጉባኤ ስብሰባ ላይ ስትገኝ እስቲ በዙሪያህ የተቀመጡትን ልብ ብለህ ተመልከት። በዚህ የአምልኮ ቦታ ላይ እነማንን ትመለከታለህ? የሚቀርበውን ቅዱስ ጽሑፋዊ የጥበብ ቃል በቁም ነገር የሚከታተሉ ወጣቶችን ትመለከት ይሆናል። (መዝሙር 148:12, 13) ለቤተሰብ ሕይወት ጠንቅ በሆነ ዓለም ውስጥ ቢኖሩም እንኳ አምላክን ለማስደሰት ከፍተኛ ጥረት የሚያደርጉ የቤተሰብ ራሶችንም መመልከትህ አይቀርም። ምናልባትም የዕድሜ መግፋት የሚያስከትላቸው የተለያዩ ችግሮች ቢኖሩባቸውም ራሳቸውን ለአምላክ ሲወስኑ የገቡትን ቃል ለመጠበቅ ብርቱ ጥረት የሚያደርጉ አረጋውያን ዓይንህ ይገቡ ይሆናል። (ምሳሌ 16:31) እነዚህ ሁሉ ለይሖዋ ጥልቅ ፍቅር አላቸው። እርሱ ደግሞ ወደ ራሱ ስቦ ወዳጆቹ እንዲሆኑ አጋጣሚውን ሰጥቷቸዋል። የአምላክ ልጅ “የላከኝ አብ ካልሳበው በቀር ማንም ወደ እኔ መምጣት አይችልም” ሲል ሐቁን በግልጽ ተናግሯል።—ዮሐንስ 6:37, 44, 65

2, 3. ክርስቲያናዊ መለያችንን ጠብቆ መኖር ፈታኝ የሆነው ለምንድን ነው?

2 ይሖዋ ሞገሱንና በረከቱን ከሰጣቸው ሰዎች መካከል መገኘታችን አያስደስተንም? ይሁንና በዚህ ‘የሚያስጨንቅ ዘመን’ ውስጥ ስንኖር ስለ ክርስቲያናዊ መለያችን ያለን ግንዛቤ እንዳይዛባ መጠንቀቅ በጣም ተፈታታኝ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) በተለይ ደግሞ በክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ ያደጉ ወጣቶች እንደዚያ ማድረጉ ሊከብዳቸው ይችላል። በክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ ያደገ አንድ ወጣት “በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ እገኝ የነበረ ቢሆንም ግልጽ የሆነ መንፈሳዊ ግብ እንዲያውም ሐቁን ለመናገር ይሖዋን የማገልገል ልባዊ ፍላጎት አልነበረኝም” በማለት የተሰማውን ተናግሯል።

3 አንዳንድ ክርስቲያኖች ይሖዋን የማገልገል ልባዊ ፍላጎት ቢኖራቸውም እንኳ እኩዮቻቸው የሚያሳድሩባቸው ከባድ ጫና፣ ዓለማዊ ተጽዕኖዎችና የኃጢአት ዝንባሌዎች እንቅፋት ሊሆኑባቸው ይችላሉ። ጫናው ሲበረታብን ክርስቲያናዊው መለያችን ቀስ በቀስ ይጠፋ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ጊዜ ያለፈባቸው ወይም በዚህ ዘመናዊ ዓለም ውስጥ የማይሠሩ እንደሆኑ አድርገው ያስባሉ። (1 ጴጥሮስ 4:4) እንዲሁም አንዳንዶች አምላክን እርሱ ባዘዘው መንገድ ማምለክ አስፈላጊ እንዳልሆነ ይሰማቸዋል። (ዮሐንስ 4:24) ጳውሎስ ለኤፌሶን ጉባኤ በጻፈው ደብዳቤ ላይ ዓለም አንድ ዓይነት “መንፈስ” ወይም በሰፊው ተንሰራፍቶ የሚታይ ዝንባሌ እንዳለው ተናግሯል። (ኤፌሶን 2:2) ይህ መንፈስ ይሖዋን የማያውቀው ሰብዓዊ ኅብረተሰብ ባለው አስተሳሰብ እንዲመሩ በሰዎች ላይ ጫና ያሳድራል።

4. ኢየሱስ ማንነታችንን በግልጽ የሚያሳውቀው ክርስቲያናዊ መለያ እንዳይጠፋብን መጠንቀቃችን አስፈላጊ መሆኑን ያጎላው እንዴት ነው?

4 ይሁን እንጂ ራሳችንን የወሰንን የይሖዋ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን ወጣትም ሆን አረጋዊ ሁላችንም ክርስቲያናዊ መለያችን እንዲበላሽ ከፈቀድን ከባድ ኪሳራ እንደሚደርስብን እናውቃለን። ስለ ክርስቲያናዊ መለያችን ያለን ትክክለኛ አመለካከት መመሥረት የሚገባው ይሖዋ ባወጣው መሥፈርትና እርሱ ለእኛ ባለው ፈቃድ ላይ ብቻ ነው። ደግሞም የተፈጠርነው በእርሱ መልክ ነው። (ዘፍጥረት 1:26፤ ሚክያስ 6:8) መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያናዊ መለያችንን ሰዎች ሁሉ በግልጽ ከሚያዩት ልብስ ጋር ያመሳስለዋል። ኢየሱስ ያለንበትን ዘመን በሚመለከት “እነሆ፤ እንደ ሌባ እመጣለሁ፤ ዕራቊቱን እንዳይሆን ኀፍረቱም እንዳይታይ ነቅቶ ልብሱን የሚጠብቅ ሰው ብፁዕ ነው” በማለት አስጠንቅቋል። a (ራእይ 16:15) በልብስ የተመሰሉትን ክርስቲያናዊ ባሕርያችንንና የሥነ ምግባር መሥፈርቶቻችንን አውልቀን የሰይጣን ዓለም በራሱ መልክ እንዲቀርጸን አንፈልግም። እንደዚያ ከሆነ ግን ‘ልብሳችንን’ እናጣለን። እንዲህ ያለው ሁኔታ የኋላ ኋላ የሚያስቆጭና ለውርደት የሚዳርግ ነው።

5, 6. በመንፈሳዊ ጥብቅ አቋም መያዝ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

5 አንድ ክርስቲያን ስለ ማንነቱ ያለው ጠንካራ ግንዛቤ በአኗኗሩ ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣል። እንዴት? አንድ የይሖዋ አምላኪ ስለ ማንነቱ ያለው ግንዛቤ ከተዛባ ሐሳቡ ሊከፋፈል ይኸውም በግልጽ የተቀመጠ የሕይወት አቅጣጫ ወይም ግብ ሊያጣ ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ያለው የመወላወል ስሜት አደገኛ መሆኑን በተደጋጋሚ ያስጠነቅቃል። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “የሚጠራጠር ሰው በነፋስ እንደሚገፋና እንደሚናወጥ የባሕር ማዕበል ነው። ያ ሰው፣ ከጌታ አንዳች ነገር አገኛለሁ ብሎ አያስብ፤ እርሱ በሁለት ሐሳብ የተያዘና በመንገዱ ሁሉ የሚወላውል ነው” ሲል አስጠንቅቋል።—ያዕቆብ 1:6-8፤ ኤፌሶን 4:14፤ ዕብራውያን 13:9

6 ክርስቲያናዊ መለያችን እንዳይበላሽ መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው? የሉዓላዊው ጌታ አምላኪዎች መሆን እጅግ ታላቅ መብት ስለመሆኑ ያለንን ግንዛቤ እንድናሰፋ ምን ሊረዳን ይችላል? እስቲ የሚከተሉትን መንገዶች እንመልከት።

ክርስቲያናዊ መለያችሁ ጽኑ መሠረት ይኑረው

7. ይሖዋ እንዲመረምረን መማጸናችን ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?

7 ከይሖዋ ጋር የመሠረትከውን ዝምድና በየጊዜው አጠናክር። አንድ ክርስቲያን አለኝ ከሚለው ሀብት ሁሉ እጅግ የላቀው ከይሖዋ ጋር የመሠረተው ወዳጅነት ነው። (መዝሙር 25:14፤ ምሳሌ 3:32) ክርስቲያናዊ መለያችንን በሚመለከት አእምሯችንን የሚረብሹ ጥያቄዎች ቢፈጠሩብን ከይሖዋ ጋር ያለን ወዳጅነት ምን ያህል የጠበቀ እንደሆነ መመርመራችን አስፈላጊ ነው። መዝሙራዊው “እግዚአብሔር ሆይ፤ ፈትነኝ፤ መርምረኝም፤ ልቤንና ውስጤን መርምር” በማለት አምላክን መማጸኑ የተገባ ነበር። (መዝሙር 26:2) እንዲህ ያለው ምርመራ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ውስጣዊ ግፊታችንንና ዝንባሌያችንን እኛ ራሳችን በትክክል መመርመር ስለማንችል ነው። ውስጣዊ ማንነታችንን ማለትም የልብ ዝንባሌያችንን፣ ሐሳባችንንና ስሜታችንን በሚገባ መረዳት የሚችለው ይሖዋ ብቻ ነው።—ኤርምያስ 17:9, 10

8. (ሀ) በይሖዋ መፈተናችን ሊጠቅመን የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) በክርስትና ሕይወት እድገት እንድታደርግ ምን እርዳታ አግኝተሃል?

8 ይሖዋ እንዲመረምረን መጸለያችን እርሱ እንዲፈትነን ፈቃደኛ መሆናችንን ያሳያል። እርሱም ውስጣዊ ግፊታችንና የልባችን ሁኔታ በግልጽ እንዲታይ ለማድረግ አንዳንድ ሁኔታዎች ወይም ፈተናዎች እንዲደርሱብን ሊፈቅድ ይችላል። (ዕብራውያን 4:12, 13፤ ያዕቆብ 1:22-25) እንዲህ ያለው ፈተና ለይሖዋ ምን ያህል ታማኞች እንደሆንን ለማሳየት ስለሚያስችለን በጸጋ ልንቀበለው ይገባል። እንዲህ ያሉ አጋጣሚዎች ‘ምንም የማይጐድለን ፍጹማንና ምሉኣን’ መሆን አለመሆናችንን ሊያሳዩ ይችላሉ። (ያዕቆብ 1:2-4) እንዲሁም በፈተና ውስጥ ማለፋችን መንፈሳዊ እድገት እንድናደርግ ይረዳናል።—ኤፌሶን 4:22-24

9. እያንዳንዳችን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች እውነት መሆናቸውን ማረጋገጣችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? አብራራ።

9 በመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ላይ ያለህ እምነት በእውቀት ላይ የተመሠረተ ይሁን። የይሖዋ አገልጋዮች መሆናችንን የሚያሳውቀው መለያ በመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ላይ በጽኑ ካልተመሠረተ ሊጠፋ ይችላል። (ፊልጵስዩስ 1:9, 10) ወጣት አረጋዊ ሳይል እያንዳንዱ ክርስቲያን የሚያምንበት ነገር በመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ላይ የተመሠረተ ለመሆኑ ለራሱ አጥጋቢ ማስረጃ ማግኘት ይኖርበታል። ጳውሎስ የእምነት ባልንጀሮቹን “ሁሉን ነገር ፈትኑ፤ መልካም የሆነውን ያዙ” በማለት አሳስቧቸዋል። (1 ተሰሎንቄ 5:21) ፈሪሃ አምላክ ባላቸው ቤተሰቦች ውስጥ ያደጉ ወጣት የይሖዋ ምሥክሮች ወላጆቻቸው አማኞች ስለሆኑ ብቻ እውነተኛ ክርስቲያኖች ሊሆኑ እንደማይችሉ ማወቅ ይገባቸዋል። ዳዊት ራሱ ልጁን ሰሎሞንን “የአባትህን አምላክ ዕወቅ፤ በፍጹም ልብና በበጎ ፈቃድ አገልግለው” በማለት በጥብቅ አሳስቦት ነበር። (1 ዜና መዋዕል 28:9) በወቅቱ ወጣት የነበረው ሰሎሞን አባቱ ዳዊት በይሖዋ ላይ ያለውን እምነት ሲያጠናክር ማየቱ ብቻውን በቂ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ በራሱ ተነሳስቶ ይሖዋን ማወቅ ነበረበት፤ ደግሞም እንደዚያ አድርጓል። “ይህን ሕዝብ ለመምራት እንድችል፣ ጥበብና ዕውቀትን ስጠኝ” በማለት አምላክን ተማጽኗል።—2 ዜና መዋዕል 1:10

10. በቅን ልቦና ተነሳስቶ ጥያቄዎችን መጠየቅ ስህተት ያልሆነው ለምንድን ነው?

10 ለጠንካራ እምነት መሠረቱ እውቀት ነው። ጳውሎስ “እምነት የሚገኘው መልእክቱን ከመስማት ነው” ሲል ተናግሯል። (ሮሜ 10:17) እንዲህ ሲል ምን ማለቱ ነበር? የአምላክን ቃል በመመገብ በይሖዋ፣ እርሱ በሰጣቸው ተስፋዎች እንዲሁም በድርጅቱ ላይ ያለንን እምነትና ትምክህት ማጠናከር እንችላለን ማለቱ ነበር። በቅን ልቦና ተነሳስተን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎች መጠየቃችን እምነት የሚያጠናክር መልስ ሊያስገኝልን ይችላል። ከዚህም በላይ ጳውሎስ በሮሜ 12:2 ላይ “መልካም፣ ደስ የሚያሰኝና ፍጹም የሆነውን የእግዚአብሔር ፈቃድ ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ [እወቁ]” የሚል ምክር ሰጥቶናል። ታዲያ ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ትክክለኛውን “የእውነት ዕውቀት” በማግኘት ነው። (ቲቶ 1:1) የይሖዋ መንፈስ በጣም ከባድ የሆኑ ትምህርቶችን እንኳ ሳይቀር እንድንገነዘብ ሊረዳን ይችላል። (1 ቆሮንቶስ 2:11, 12) አንድን ትምህርት መረዳት አስቸጋሪ ከሆነብን አምላክ እንዲረዳን በጸሎት ልንጠይቀው ይገባል። (መዝሙር 119:10, 11, 27) ይሖዋ ቃሉን እንድንረዳ፣ እንድናምንና እንድንታዘዝ ይፈልጋል። በቅን ልቦና ተነሳስተን የምናቀርባቸውን ጥያቄዎች ለማስተናገድ ፈቃደኛ ነው።

አምላክን ለማስደሰት ቁርጥ ውሳኔ አድርጉ

11. (ሀ) ወጥመድ ሊሆንብን የሚችለው የትኛው የተፈጥሮ ፍላጎታችን ነው? (ለ) የእኩዮችን ተጽዕኖ ለመቋቋም የሚያስችል ድፍረት ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?

11 ሰውን ሳይሆን አምላክን ለማስደሰት ጣር። በተወሰነ ደረጃ የአንድ ቡድን አባል በመሆን ማንነታችንን ለማሳየት መፈለጋችን ያለ ነገር ነው። ሁሉም ሰው ቢሆን ጓደኞች ያስፈልጉታል፤ በሌሎች ዘንድ ተቀባይነት ማግኘታችን ደግሞ ጥሩ ስሜት ያሳድርብናል። በጉርምስና ወቅትም ሆነ ከዚያ በኋላ ባሉት ዓመታት የእኩዮች ተጽዕኖ በጣም የሚያይል ሲሆን ይህ ተጽዕኖ ወጣቶች ሌሎችን የመምሰል ወይም የማስደሰት ከፍተኛ ፍላጎት እንዲያድርባቸው ያደርጋል። ሆኖም ጓደኞቻችንና እኩዮቻችን ሁልጊዜ ለደኅንነታችን ያስባሉ ማለት አይቻልም። አንዳንድ ጊዜ እነርሱ የሚፈልጉት ክፉ ነገር ለመሥራት የሚተባበራቸው ሰው ማግኘት ብቻ ነው። (ምሳሌ 1:11-19) አንድ ክርስቲያን በእኩዮች ተጽዕኖ ሲሸነፍ ብዙውን ጊዜ ማንነቱን ለመደበቅ ይሞክራል። (መዝሙር 26:4) ሐዋርያው ጳውሎስ “የዚህ ዓለም ሰዎች ጠባይ እንዲቀርጻችሁ አትፍቀዱ” በማለት አስጠንቅቋል። (ሮሜ 12:2 ዘ ጀሩሳሌም ባይብል) ይሖዋ ዓለምን እንድንመስል የሚደረግብንን ማንኛውንም ግፊት እንድንቋቋም የሚያስፈልገንን ውስጣዊ ጥንካሬ ይሰጠናል።—ዕብራውያን 13:6

12. በይሖዋ ላይ ያለን ትምክህት ሲፈተን ጽኑ አቋም እንድንይዝ የሚረዳን የትኛው መሠረታዊ ሥርዓትና ምሳሌ ነው?

12 ከውጭ የሚደረግብን ተጽዕኖ ክርስቲያናዊ መለያችንን ሊያበላሽብን እንደሚችል ከተሰማን የላቀ ቦታ ያለው የሕዝቡ አመለካከት ወይም የብዙኃኑ ዝንባሌ ሳይሆን ለአምላክ ያለን ታማኝነት እንደሆነ ፈጽሞ መዘንጋት አይኖርብንም። በዘፀአት 23:2 ላይ የሚገኘው “ክፉ በማድረግ ብዙዎችን አትከተል” የሚለው ምክር አስተማማኝ መሠረታዊ ሥርዓት ሆኖ ሊያገለግለን ይችላል። ካሌብ አብዛኞቹ እስራኤላውያን ይሖዋ የገባውን ቃል ለመፈጸም ያለውን ችሎታ በተጠራጠሩ ጊዜ የብዙኃኑን አመለካከት ለመቀበል ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል። አምላክ የሰጠው ተስፋ እምነት የሚጣልበት መሆኑን እርግጠኛ የነበረ ሲሆን ይህ አቋሙም ከፍተኛ በረከት አስገኝቶለታል። (ዘኍልቍ 13:30፤ ኢያሱ 14:6-11) አንተስ ከአምላክ ጋር የመሠረትከው ዝምድና እንዳይበላሽ ለመከላከል ስትል የብዙኃኑን አመለካከት ለመቋቋም እንዲህ ያለ አቋም ትወስዳለህ?

13. ሌሎች ክርስቲያን መሆናችንን እንዲያውቁ ማድረጋችን የጥበብ እርምጃ የሆነው ለምንድን ነው?

13 ክርስቲያን መሆንህን አሳውቅ። አስቀድሞ ማጥቃት ከሁሉ የላቀው የመከላከል ዘዴ ነው የሚለው አባባል ክርስቲያናዊ መለያችን እንዳይበላሽ ለምናደርገው ትግልም በሚገባ ይሠራል። በዕዝራ ዘመን የነበሩ ታማኝ እስራኤላውያን የይሖዋን ፈቃድ እንዳያደርጉ ተቃውሞ ባጋጠማቸው ጊዜ “እኛ የሰማይና የምድር አምላክ አገልጋዮች ነን” በማለት ተናግረው ነበር። (ዕዝራ 5:11) ለእኛ ጥላቻ ያላቸው ሰዎች የሚወስዱት እርምጃና የሚሰነዝሩት ትችት የሚያሸማቅቀን ከሆነ የሰው ፍርሃት ሊያሽመደምደን ይችላል። ሁሉን ሰው ማስደሰት እንዳለብን የሚሰማን ከሆነ በሥራችን ውጤታማ መሆን አንችልም። ስለሆነም በፍርሃት አትሸበር። ምንጊዜም ቢሆን የይሖዋ ምሥክር መሆንህን ለሌሎች በግልጽ ማሳወቅህ በጣም ጥሩ ነው። ስለ ሥነ ምግባራዊ አቋምህ፣ ስለምታምንባቸው ነገሮችና ስለ ክርስቲያናዊ አመለካከትህ በአክብሮት ሆኖም በጥብቅ ልትገልጽላቸው ትችላለህ። ሌሎች ሰዎች ይሖዋ ያወጣውን ከፍተኛ የሥነ ምግባር መሥፈርት ለመጠበቅ መቁረጥህን እንዲያውቁ አድርግ። ክርስቲያናዊ አቋምህ ለድርድር እንደማይቀርብ በግልጽ አሳውቅ። በምትመራበት የሥነ ምግባር መሥፈርት እንደምትኮራ አሳይ። (መዝሙር 64:10) በክርስቲያናዊ አቋምህ ጸንተህ መቆምህ ሊያበረታህና ጥበቃ ሊሆንልህ ይችላል፤ እንዲያውም አንዳንድ ሰዎች ስለ ይሖዋና ስለ ሕዝቦቹ ለማወቅ ጥያቄዎችን እንዲያነሱ ያደርጋቸው ይሆናል።

14. የሰዎች ፌዝ ወይም ተቃውሞ ተስፋ ሊያስቆርጠን ይገባል? አብራራ።

14 አንዳንዶች የይሖዋ ምሥክር መሆንህን ሲያውቁ ያፌዙብህ ወይም ይቃወሙህ ይሆናል። (ይሁዳ 18) ሥነ ምግባራዊ አቋምህን አሳውቀህ በጎ ውጤት ሳታገኝ ብትቀር ተስፋ አትቁረጥ። (ሕዝቅኤል 3:7, 8) ምንም ያህል ቆራጥ አቋም ቢኖርህ ማመን የማይፈልጉ ሰዎችን ማሳመን አትችልም። ለምሳሌ ያህል ፈርዖንን አስታውስ። የትኛውም መቅሰፍት ወይም ተአምር ሌላው ቀርቶ የበኩር ልጁን ማጣቱ እንኳ ሙሴ የይሖዋ ወኪል መሆኑን አምኖ እንዲቀበል ሊያደርገው አልቻለም። በመሆኑም የሰው ፍርሃት እንዲያሽመደምድህ አትፍቀድ። በአምላክ ላይ ያለን ትምክህትና እምነት ፍርሃትን እንድንቋቋም ሊረዳን ይችላል።—ምሳሌ 3:5, 6፤ 29:25

ካለፈው ተማሩ፤ ለወደፊቱ ጊዜ መሠረት ጣሉ

15, 16. (ሀ) መንፈሳዊ ውርሻችን ምን ነገሮችን ይጨምራል? (ለ) በአምላክ ቃል ታግዘን በመንፈሳዊ ውርሻችን ላይ ማሰላሰላችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል?

15 መንፈሳዊ ውርሻህን እንደ ውድ ሀብት ተመልከት። ክርስቲያኖች በአምላክ ቃል ብርሃን እየታገዙ ውድ በሆነው መንፈሳዊ ውርሻ ላይ በማሰላሰል ጥቅም ማግኘት ይችላሉ። ይህ ውርሻ በይሖዋ ቃል ውስጥ የሚገኘውን እውነት፣ የዘላለም ሕይወት ተስፋን እንዲሁም የምሥራቹ አዋጅ ነጋሪ በመሆን አምላክን ወክሎ የመቅረብን ልዩ መብት ይጨምራል። ሕይወት አድን የሆነውን መንግሥቱን የመስበኩን ሥራ የማከናወን መብት በተሰጣቸው የይሖዋ ሕዝቦች መካከል አንተም የራስህ ድርሻ እንዳለህ ትገነዘባለህ? ሕዝቦቹን “እናንተ ምስክሮቼ . . . ናችሁ” ያላቸው ይሖዋ ራሱ እንጂ ሌላ ማንም እንዳልሆነ አስታውስ።—ኢሳይያስ 43:10

16 እንዲህ እያልህ ራስህን መጠየቅ ትችላለህ:- ‘ይህን መንፈሳዊ ውርሻ እንደ ውድ ነገር እመለከተዋለሁ? ይህ አመለካከቴ በሕይወቴ ውስጥ ለአምላክ ፈቃድ ቅድሚያ እንድሰጥ አድርጎኛል? ለዚህ መንፈሳዊ ውርሻ ያለኝ አድናቆት ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ አቅልዬ እንድመለከተው የሚያጋጥመኝን ፈተና እንድቋቋም አስችሎኛል?’ ከዚህም በተጨማሪ መንፈሳዊው ውርሻችን በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ብቻ የሚገኘው መንፈሳዊ ደኅንነት እንዲሰማን ሊያደርግ ይችላል። (መዝሙር 91:1, 2) በዚህ ዘመን የይሖዋ ምድራዊ ድርጅት ያሳለፈውን አስደናቂ ታሪክ መለስ ብለን መከለሳችን ማንም ሰው ወይም ምንም ዓይነት ነገር ቢሆን የይሖዋን ሕዝብ ከምድር ገጽ ሊያጠፋ እንደማይችል እንድንገነዘብ ያደርገናል።—ኢሳይያስ 54:17፤ ኤርምያስ 1:19

17. ከመንፈሳዊ ውርሻ በተጨማሪ ምን ያስፈልገናል?

17 ይህ ሲባል ግን መንፈሳዊ ውርሻ እስካለን ድረስ ሌላ ምንም ነገር አያስፈልገንም ማለት አይደለም። እያንዳንዳችን ከአምላክ ጋር የቅርብ ዝምድና መመሥረት ይኖርብናል። ጳውሎስ በፊልጵስዩስ የሚገኙ ክርስቲያኖች እምነታቸውን እንዲገነቡ ለመርዳት ብርቱ ጥረት ካደረገ በኋላ “ስለዚህ፣ ወዳጆቼ ሆይ፤ ሁልጊዜም ታዛዦች እንደ ነበራችሁ ሁሉ፣ አሁንም እኔ በአጠገባችሁ ሳለሁ ብቻ ሳይሆን፣ ይልቁንም አሁን በሌለሁበት ጊዜ በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ” ሲል ጽፎላቸው ነበር። (ፊልጵስዩስ 2:12) መዳናችን የተመካው በሌሎች ሳይሆን በራሳችን ጥረት ላይ ነው።

18. ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች ስለ ክርስቲያናዊ መለያችን ያለንን ግንዛቤ የሚያሰፉልን እንዴት ነው?

18 ራስህን በክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች አስጠምድ። “ሥራ በአንድ ሰው ማንነት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራል” ተብሎ ይነገራል። በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች በሰማይ ስለተቋቋመው የአምላክ መንግሥት የሚገልጸውን ምሥራች እንዲሰብኩ ከፍተኛ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል። ጳውሎስ “የአሕዛብ ሐዋርያ እንደ መሆኔ መጠን አገልግሎቴን በትጋት እፈጽማለሁ” በማለት ተናግሯል። (ሮሜ 11:13) የስብከቱ ሥራችን ከዓለም ለይቶ የሚያሳውቀን ሲሆን በሥራው ላይ የምናደርገው ተሳትፎ የክርስቲያናዊ መለያችን ጉልህ ገጽታ ነው። በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘትን፣ የአምልኮ ቦታዎችን መገንባትንና ችግረኞችን መርዳትን በመሳሰሉ ቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች ራሳችንን ማስጠመዳችን ስለ ክርስቲያናዊ መለያችን ያለንን ግንዛቤ ሊያሰፋልን ይችላል።—ገላትያ 6:9, 10፤ ዕብራውያን 10:23, 24

መለያችን ግልጽ መሆኑ ተጨባጭ በረከቶች ያስገኛል

19, 20. (ሀ) ክርስቲያን መሆንህ ምን ጥቅሞች አስገኝቶልሃል? (ለ) ለእውነተኛ መለያችን መሠረት የሚሆነን ምንድን ነው?

19 እውነተኛ ክርስቲያን መሆናችን ስላስገኘልን በርካታ ጥቅሞችና በረከቶች ቆም ብለህ አስብ። በግለሰብ ደረጃ በይሖዋ የመታወቅ ልዩ መብት አግኝተናል። ነቢዩ ሚልክያስ “እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ፤ እግዚአብሔር አዳመጠ፤ ሰማቸውም፤ እግዚአብሔርን ለሚፈሩና ስሙን ለሚያከብሩ በእርሱ ፊት የመታሰቢያ መጽሐፍ ተጻፈ” ብሏል። (ሚልክያስ 3:16) አምላክ እንደ ወዳጆቹ አድርጎ ይመለከተናል። (ያዕቆብ 2:23) ሕይወታችን ዓላማና ትርጉም ያለው ከመሆኑም በላይ ትክክለኛና ውጤታማ የሆኑ ግቦች ማውጣት ችለናል። ከዚህም በተጨማሪ ለዘላለም የመኖር ተስፋ አግኝተናል።—መዝሙር 37:9

20 እውነተኛ መለያህና ዋጋማነትህ የሚመዘነው አምላክ ለአንተ ባለው ግምት እንጂ ሌሎች ሰዎች ስለ አንተ ባላቸው አመለካከት እንዳልሆነ አስታውስ። ሌሎች ትክክለኛ ባልሆነ ሰብዓዊ መሥፈርት ሊመዝኑን ይሞክሩ ይሆናል። ሆኖም አምላክ ለእኛ ያለው ፍቅርና በግል የሚያስብልን መሆኑ የእርሱ እንደሆንን እንዲሰማን ያደርጋል። ደግሞም ትክክለኛ ዋጋማነታችን የሚለካው በዚህ ነው። (ማቴዎስ 10:29-31) እኛም በአጸፋው ለአምላክ የሚያድርብን ፍቅር በክርስቲያናዊ መለያችን እንድንኮራና ለሕይወታችን ግልጽ የሆነ መመሪያ እንድናገኝ ያደርገናል። “እግዚአብሔርን የሚወድ ሰው . . . በእግዚአብሔር ዘንድ የታወቀ ነው።”—1 ቆሮንቶስ 8:3

[የግርጌ ማስታወሻ]

a እነዚህ ቃላት ኢየሩሳሌም በነበረው ቤተ መቅደስ ውስጥ አለቃው ያሉበትን ኃላፊነቶች በተዘዋዋሪ መንገድ የሚጠቁሙ ሊሆኑ ይችላሉ። አለቃው ሌሊት ላይ ቤተ መቅደሱ ውስጥ እየተዘዋወረ ሌዋውያን ጠባቂዎች በተመደቡበት ቦታ ነቅተው ይጠብቁ እንደሆነና እንዳልሆነ ይመለከታል። አንድ ጠባቂ ተኝቶ ከተገኘ በበትር ይመታል፤ እንዲሁም እፍረት እንዲከናነብ ሲባል ልብሱ እንዲቃጠል ይደረግ ይሆናል።

ታስታውሳለህ?

• ክርስቲያኖች መንፈሳዊ መለያቸው እንዳይበላሽ መጠበቃቸው በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

• ክርስቲያናዊ መለያችን በጽኑ መሠረት ላይ እንዲገነባ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

• ማስደሰት ያለብን ማንን ነው የሚል ጥያቄ ሲደቀንብን ትክክለኛ ውሳኔ እንድናደርግ ምን ሊረዳን ይችላል?

• ስለ መለያችን ያለን ግልጽ ግንዛቤ የወደፊቱን ክርስቲያናዊ ጎዳናችንን አቅጣጫ የሚያስይዝልን እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ራሳችንን በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ማስጠመዳችን ክርስቲያናዊ መለያችን ጎልቶ እንዲታይ ያደርጋል