በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ክርስቲያኖች—በማንነታችሁ ልትኮሩ ይገባል!

ክርስቲያኖች—በማንነታችሁ ልትኮሩ ይገባል!

ክርስቲያኖች—በማንነታችሁ ልትኮሩ ይገባል!

“የሚመካ በጌታ [“በይሖዋ፣” Nw] ይመካ።”—1 ቆሮንቶስ 1:31

1. ሰዎች ለሃይማኖት ምን ዝንባሌ ይታይባቸዋል?

 “ግዴለሽነት።” ስለ ሃይማኖታዊ ጉዳዮች የሚዘግብ አንድ ጋዜጠኛ ብዙ ሰዎች ስለ እምነታቸው የሚያሳዩትን ዝንባሌ ለመግለጽ በቅርቡ ይህን ቃል ተጠቅሞ ነበር። “በዘመናችን ባሉ ሃይማኖቶች ውስጥ ተንሰራፍቶ የሚገኘው ዝንባሌ ሃይማኖተኝነት ሳይሆን ‘ግዴለሽነት’ ነው” በማለት ተናግሯል። ከዚያም ሐሳቡን ሲያብራራ ‘ግዴለሽነት’ ብሎ የጠራውን ይህን ዝንባሌ “ለገዛ ሃይማኖት ፈጽሞ ደንታቢስ መሆን” የሚል ፍቺ ሰጥቶታል። እርሱ እንደተናገረው ብዙ ሰዎች “በአምላክ ያምናሉ . . .፤ ሆኖም ስለ እርሱ መጨነቅ አይፈልጉም።”

2. (ሀ) ሰዎች ለመንፈሳዊ ነገሮች ግዴለሽ መሆናቸው የሚያስደንቅ ያልሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ግዴለሽነት በእውነተኛ ክርስቲያኖች ላይ ምን አደጋ ሊያስከትል ይችላል?

2 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች እንዲህ ያለ የግዴለሽነት ዝንባሌ መስፈኑ አያስደንቃቸውም። (ሉቃስ 18:8) ሃይማኖትን በአጠቃላይ የተመለከትን እንደሆነ በዚህ ረገድ ሰዎች ግዴለሽ መሆናቸው የሚጠበቅ ነገር ነው። ምክንያቱም የሐሰት ሃይማኖት ለረጅም ዘመናት የሰው ልጆችን ሲያስት የኖረ ከመሆኑም በላይ ከናካቴው ተስፋ እንዲቆርጡ አድርጓቸዋል። (ራእይ 17:15, 16) ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው የግዴለሽነት መንፈስ በእውነተኛ ክርስቲያኖች ላይ መንጸባረቅ ከጀመረና ቅንዓታቸው እየቀዘቀዘ ከሄደ በጣም አደገኛ ነው። ለእምነታችን ቸልተኞች ከሆንን እንዲሁም ለአገልግሎትና ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ያለን ቅንዓት ከቀዘቀዘ ከባድ መዘዝ ሊያስከትልብን ይችላል። ኢየሱስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን በሎዶቅያ ለነበሩ ክርስቲያኖች “ቀዝቃዛ ወይም ትኵስ እንዳልሆንህ . . . ዐውቃለሁ፤ ቀዝቃዛ ወይም ትኵስ ብትሆን በወደድሁ ነበር። . . . ለብ ያልህ ብቻ [ነህ]” ሲል በሰጠው ምክር ላይ መንፈሳዊ ለብታ አደገኛ መሆኑን አስጠንቅቋል።—ራእይ 3:15-18

ማንነታችንን መገንዘብ

3. ክርስቲያኖች የሚኮሩት በየትኞቹ መለያዎቻቸው ነው?

3 ክርስቲያኖች መንፈሳዊ ግዴለሽነትን ለመዋጋት ማንነታቸውን በግልጽ መገንዘብ እንዲሁም በማንነታቸው መኩራት ይገባቸዋል። የይሖዋ አገልጋዮች እንዲሁም የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንደመሆናችን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ማንነታችንን የሚጠቁሙ የተለያዩ መግለጫዎችን ማግኘት እንችላለን። ለሰዎች ‘ወንጌልን’ በቅንዓት የምንሰብክ እንደመሆናችን መጠን “ከእግዚአብሔር ጋር አብረን የምንሠራ” የይሖዋ ‘ምሥክሮች’ ነን። (ኢሳይያስ 43:10፤ 1 ቆሮንቶስ 3:9፤ ማቴዎስ 24:14) በተጨማሪም ‘እርስ በርስ የምንዋደድ’ ሰዎች ነን። (ዮሐንስ 13:34) እውነተኛ ክርስቲያኖች ‘መልካሙን ከክፉው ለመለየት ራሳቸውን ያስለመዱ’ ሰዎች ናቸው። (ዕብራውያን 5:14) እንዲሁም ‘እንደ ከዋክብት በዓለም ሁሉ እናበራለን።’ (ፊልጵስዩስ 2:15) ‘በአሕዛብ መካከል በመልካም ሕይወት ለመኖር’ ብርቱ ጥረት እናደርጋለን።—1 ጴጥሮስ 2:12፤ 2 ጴጥሮስ 3:11, 14

4. አንድ የይሖዋ አምላኪ፣ ሊርቀው የሚገባውን ነገር ማወቅ የሚችለው እንዴት ነው?

4 በአንጻሩ ደግሞ እውነተኛ የይሖዋ አምላኪዎች ሊርቁት የሚገባውን ነገር ጠንቅቀው ያውቃሉ። መሪያቸው ኢየሱስ ክርስቶስ የዚህ ዓለም ክፍል እንዳልነበረ ሁሉ “እነርሱም ከዓለም አይደሉም።” (ዮሐንስ 17:16) ‘ልቦናቸው ከጨለመባቸውና ከእግዚአብሔር ሕይወት ተለይተው’ ከሚኖሩት “አሕዛብ” ጋር አይቀራረቡም። (ኤፌሶን 4:17, 18) በዚህም ምክንያት የኢየሱስ ተከታዮች ‘በኀጢአት መኖርንና ዓለማዊ ምኞትን ክደው፣ በአሁኑ ዘመን ራሳቸውን በመግዛትና በጽድቅ፣ በእውነተኛ መንፈሳዊ ሕይወት ይኖራሉ።’—ቲቶ 2:12

5. በይሖዋ ‘መመካት’ ሲባል ምን ማለት ነው?

5 ስለ ክርስቲያናዊ መለያችን ያለን ግልጽ ግንዛቤና ከአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዥ ጋር የመሠረትነው ዝምድና በይሖዋ ‘እንድንመካ’ ይገፋፋናል። (1 ቆሮንቶስ 1:31) ይሁንና በይሖዋ እንመካለን ሲባል ምን ማለት ነው? እውነተኛ ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ይሖዋ አምላካችን በመሆኑ እንኮራለን ማለት ነው። “የሚመካ ግን፣ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ በማወቁና፤ በምድር ላይ ምሕረትን፣ ፍትሕንና ጽድቅን የማደርግ መሆኔን በመረዳቱ፣ በዚህ ይመካ” የሚለውን ማሳሰቢያ እንከተላለን። (ኤርምያስ 9:24) አምላክን የማወቅ እንዲሁም ሌሎችን ለመርዳት በእርሱ የመመረጥ ልዩ መብት በማግኘታችን ‘እንመካለን’ ወይም እንኮራለን።

ማንነታችንን እንድንዘነጋ የሚያጋጥመን ፈታኝ ሁኔታ

6. አንዳንድ ክርስቲያኖች መለያቸው እንዳይጠፋ ጥንቃቄ ማድረግ ፈታኝ የሆነባቸው ለምንድን ነው?

6 ክርስቲያናዊ መለያችን እንዳይጠፋ ጥንቃቄ ማድረግ ሁልጊዜ ቀላል እንዳልሆነ የማይካድ ነው። በክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ ያደገ አንድ ወጣት በመንፈሳዊ በተዳከመበት ወቅት ተሰምቶት የነበረውን ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “ለምን የይሖዋ ምሥክር እንደሆንኩ እንኳ የሚጠፋብኝ ጊዜ ነበር። ከሕፃንነቴ አንስቶ እውነትን ስማር ቆይቻለሁ። ያለሁበት ሃይማኖት ከሌሎቹ ሃይማኖቶች ተለይቶ እንደማይታይ የሚሰማኝ ጊዜ ነበር።” ሌሎች ደግሞ ክርስቲያናዊ መለያቸው በመዝናኛው ዓለም፣ በመገናኛ ብዙኃንና ሰዎች ለሕይወት ባላቸው የተሳሳተ አመለካከት እንዲቀረጽ ፈቅደው ሊሆን ይችላል። (ኤፌሶን 2:2, 3) አንዳንድ ክርስቲያኖች ማንነታቸውን የሚጠራጠሩበት እንዲሁም በአመለካከታቸውና በግቦቻቸው ላይ ተደጋጋሚ ለውጥ የሚያደርጉበት ጊዜ ይኖራል።

7. (ሀ) የአምላክ አገልጋዮች ሊያደርጉት የሚገባው ምርመራ ምን ዓይነት ነው? (ለ) ለአደጋ የምንጋለጠው ምን ካደረግን ነው?

7 አልፎ አልፎ ራሳችንን በጥንቃቄ መመርመራችን ስህተት ነው? በፍጹም። ሐዋርያው ጳውሎስ “በእምነት መሆናችሁን ለማወቅ ራሳችሁን መርምሩ፤ ራሳችሁን ፈትኑ” በማለት ክርስቲያኖች በየጊዜው ራሳቸውን እንዲመረምሩ አበረታቶ እንደነበር ታስታውስ ይሆናል። (2 ቆሮንቶስ 13:5) እዚህ ላይ ጳውሎስ መንፈሳዊ ድክመት ይኖርብን እንደሆነ ለማወቅ ምርመራ እንድናደርግ ማበረታታቱ ነበር። ይህን የምናደርግበት ዓላማ ድክመታችንን ለማሻሻል የሚያስችል ተገቢ እርምጃ ለመውሰድ ነው። አንድ ክርስቲያን በእምነት መሆን አለመሆኑን ለማወቅ ራሱን ሲፈትን ቃሉም ሆነ ተግባሩ ከሚያምነው ነገር ጋር የሚጣጣም መሆኑን ማረጋገጥ ይኖርበታል። ይሁን እንጂ “ማንነታችንን” ፍለጋ የምንነሳ ወይም ከይሖዋና ከክርስቲያን ጉባኤ ጋር ግንኙነት የሌላቸው መልሶች ለማግኘት የምንጥር ከሆነ ዓላማችንን የምንስት ከመሆኑም በላይ መንፈሳዊ ጉዳት ሊያጋጥመን ይችላል። a ‘እምነታችን ባሕር ላይ አደጋ ደርሶበት እንደሚጠፋ መርከብ’ እንዲሆን ፈጽሞ አንፈልግም!—1 ጢሞቴዎስ 1:19

ክርስቲያኖች ከችግር ነፃ አይደሉም

8, 9. (ሀ) ሙሴ ብቃት እንደሌለው የገለጸው ምን በማለት ነበር? (ለ) ይሖዋስ ምን ምላሽ ሰጠው? (ሐ) ይሖዋ ለሕዝቦቹ የሰጠው ማበረታቻ ምን ስሜት ያሳድርብሃል?

8 አልፎ አልፎ ማንነታቸውን በሚመለከት ጥርጣሬ የሚገባቸው ክርስቲያኖች ችግር አለባቸው ማለት ነው? በፍጹም! እንዲያውም እንዲህ ያለው ስሜት በእነርሱ እንዳልጀመረ ማወቃቸው ሊያጽናናቸው ይችላል። በጥንት ዘመን የኖሩ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮችም ተመሳሳይ ሁኔታ አጋጥሟቸው ነበር። ጠንካራ እምነት፣ ታማኝነትና ለአምላክ የማደር ባሕርይ ያሳየውን ሙሴን እንደምሳሌ እንውሰድ። ከአቅሙ በላይ የሆነ ኃላፊነት እንደተሰጠው በተሰማው ጊዜ “እኔ ማን ነኝ?” በማለት ኃላፊነቱን ለመቀበል አቅማምቶ ነበር። (ዘፀአት 3:11) ሙሴ እንዲህ ሲል ‘እዚህ ግባ የምባል ሰው አይደለሁም!’ ወይም ‘ብቃቱ የለኝም!’ ማለቱ እንደነበር ግልጽ ነው። ሙሴ ብቃት እንደሚጎድለው እንዲሰማው ያደረገው ከዚያ ቀደም ያሳለፈው ተሞክሮ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ያህል:- የተወለደው በባርነት ከሚማቅቅ ብሔር ነበር። በእስራኤላውያን ዘንድም ቢሆን ተቀባይነት አላገኘም። አንደበተ ርቱዕ አልነበረም። (ዘፀአት 1:13, 14፤ 2:11-14፤ 4:10) በግ ጠባቂ የነበረ ሲሆን ይህ ሥራ በግብፃውያን ዘንድ የተጠላ ነበር። (ዘፍጥረት 46:34) በእርግጥም በባርነት ቀንበር ሥር የሚማቅቀውን የአምላክ ሕዝብ ነፃ እንዲያወጣ ሲጠየቅ ብቃቱ እንደሚጎድለው ቢሰማው ምንም አያስገርምም!

9 ይሖዋ መፈጸማቸው የማይቀር ሁለት ተስፋዎችን በመስጠት ሙሴን አጽናናው:- “እኔ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ እኔ የላክሁህ ለመሆኑ ምልክቱ ይህ ነው፤ ሕዝቡን ከግብፅ ካወጣሃቸው በኋላ በዚህ ተራራ ላይ እግዚአብሔርን ታመልካላችሁ።” (ዘፀአት 3:12) አምላክ ይህን ሲል አቅማምቶ ለነበረው ለአገልጋዩ ለሙሴ ምንጊዜም ከእርሱ ጋር እንደሚሆን መግለጹ እንዲሁም ይሖዋ ሕዝቡን ከባርነት ነፃ ማውጣቱ እንደማይቀር መናገሩ ነበር። ባለፉት ዘመናት ሁሉ አምላክ ሕዝቡን ለመርዳት ተመሳሳይ ተስፋ ሰጥቷል። ለምሳሌ ያህል፣ እስራኤላውያን ተስፋይቱ ምድር ለመግባት ተቃርበው በነበረበት ወቅት በሙሴ በኩል “ብርቱና ደፋር ሁኑ፤ . . . አምላክህ እግዚአብሔር ካንተ ጋር ይሄዳልና፤ አይተውህም፤ አይጥልህምም” ብሏቸው ነበር። (ዘዳግም 31:6) እንዲሁም ለኢያሱ “በሕይወት በምትኖርበት ዘመን ሁሉ ማንም አይቋቋምህም፤ . . . ከአንተም ጋር እሆናለሁ፤ ከቶ አልጥልህም፤ አልተውህም” የሚል ማረጋገጫ ሰጥቶት ነበር። (ኢያሱ 1:5) ለክርስቲያኖችም “ከቶ አልተውህም፤ በፍጹም አልጥልህም” የሚል ቃል ገብቶላቸዋል። (ዕብራውያን 13:5) እንዲህ ያለ አስተማማኝ ድጋፍ ማግኘታችን በክርስቲያንነታችን እንድንኮራ ሊያደርገን ይገባል!

10, 11. ሌዋዊው አሳፍ ይሖዋን ማገልገል የሚያስገኘውን ጥቅም በተመለከተ ትክክለኛ አመለካከት እንዲይዝ የረዳው ምን ነበር?

10 ሙሴ ከሞተ ከአምስት መቶ ዓመታት ገደማ በኋላ የኖረው አሳፍ የሚባል ታማኝ ሌዋዊ የጽድቅን ጎዳና መከተሉ የሚያስገኘውን ፋይዳ በሚመለከት ጥርጣሬ አድሮበት እንደነበረ በግልጽ ጽፏል። አሳፍ አስቸጋሪና ተፈታታኝ በሆኑ ሁኔታዎች ሥር አምላክን ለማገልገል ደፋ ቀና እያለ ሳለ በአምላክ ላይ የሚዘብቱ አንዳንድ ሰዎች ኃይላቸው እየደረጀና በቁሳዊ እየበለጸጉ ሲሄዱ ተመለከተ። አሳፍ ምን ተሰምቶት ይሆን? “እኔ ግን እግሬ ሊሰናከል፣ አዳልጦኝም ልወድቅ ጥቂት ቀረኝ። ክፉዎች ሲሳካላቸው አይቼ፣ በዐመፀኞች ቀንቼ ነበርና” በማለት የተሰማውን በግልጽ ተናግሯል። አሳፍ የይሖዋ አምላኪ መሆን የሚያስገኘውን ጥቅም መጠራጠር ጀምሮ ነበር። “ለካ ልቤን ንጹሕ ያደረግሁት በከንቱ ነው፤ እጄንም በየዋህነት የታጠብሁት በከንቱ ኖሮአል! ቀኑን ሙሉ ተቀሠፍሁ” የሚል ሐሳብ መጥቶበት ነበር።—መዝሙር 73:2, 3, 13, 14

11 አሳፍ እንዲህ ያለ የስሜት መረበሽ ሲያጋጥመው ምን አደረገ? ስሜቱን አፍኖ ዝም አለ? በፍጹም። በ73ኛው መዝሙር ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው ስሜቱን ለይሖዋ በጸሎት ገልጿል። አሳፍ ወደ ይሖዋ ቤተ መቅደስ መሄዱ በአስተሳሰቡ ላይ ትልቅ ለውጥ እንዲያደርግ ረድቶታል። እዚያ ሲገባ ለአምላክ ከማደር የተሻለ አንዳች ነገር እንደሌለ ተገነዘበ። የአምላክ አገልጋይ እንዲሆን ለተሰጠው መብት ያለው አድናቆት እንደገና ሲቀጣጠል ይሖዋ ክፋትን እንደሚጠላና እርሱ በወሰነው ጊዜ ክፉዎችን እንደሚያጠፋ ተገነዘበ። (መዝሙር 73:17-19) በዚህ ጊዜ የይሖዋ አገልጋይ መሆኑን እንደ ልዩ መብት መቁጠር ጀመረ። አምላክን “ዘወትር ከአንተ ጋር ነኝ፤ አንተም ቀኝ እጄን ይዘኸኛል። በምክርህ መራኸኝ፤ ኋላም ወደ ክብር ታስገባኛለህ” ብሎታል። (መዝሙር 73:23, 24) አሳፍ እንደገና በአምላኩ መኩራት ጀመረ።—መዝሙር 34:2

ማንነታቸውን ፈጽሞ አልዘነጉም

12, 13. ከአምላክ ጋር በመሠረቱት ዝምድና ይኮሩ የነበሩ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ገጸ ባሕርያትን ጥቀስ።

12 ለክርስቲያናዊ መለያችን ያለንን አድናቆት ይበልጥ ማጠናከር የምንችልበት አንደኛው መንገድ መከራ ቢያጋጥማቸውም እንኳ ከአምላክ ጋር በመሠረቱት ዝምድና ይኮሩ የነበሩ ታማኝ አምላኪዎች ያሳዩትን እምነት መመርመርና ምሳሌያቸውን መኮረጅ ነው። በመጀመሪያ የያዕቆብን ልጅ ዮሴፍን እንመልከት። ገና ለጋ ወጣት ሳለ ለባርነት ተሸጦ ፈሪሃ አምላክ ካለው አባቱ እንዲሁም ፍቅርና እንክብካቤ ያገኝበት ከነበረው ቤተሰቡ በመለየት እጅግ ርቃ ወደምትገኘው ወደ ግብፅ ተወሰደ። ዮሴፍ በግብፅ ሳለ አምላካዊ ምክር የሚያካፍለው ሰው ያልነበረው ከመሆኑም በላይ የሥነ ምግባር አቋሙን የሚያበላሹና በአምላክ ላይ ያለውን ትምክህት የሚያዳክሙ ተፈታታኝ ሁኔታዎችን መጋፈጥ ነበረበት። ይሁን እንጂ የአምላክ አገልጋይ መሆኑን የሚያሳውቀው መለያ እንዳይጠፋበት ብርቱ ትግል አድርጎ እንደነበር ግልጽ ነው። እንዲሁም በታማኝነት ትክክል የሆነውን ማድረጉን ቀጥሏል። ለአምልኮቱ አመቺ ባልሆነ አካባቢ ይኖር የነበረ ቢሆንም የይሖዋ አምላኪ በመሆኑ ይኮራ ነበር። በተጨማሪም የሚሰማውን ከመናገር ወደኋላ አላለም።—ዘፍጥረት 39:7-10

13 ዮሴፍ ከሞተ ከስምንት መቶ ዓመታት በኋላ የኖረችውና በምርኮ ተወስዳ የሶርያዊው የጦር አዛዥ የንዕማን ባሪያ የሆነችው እስራኤላዊት ልጃገረድም የይሖዋ አምላኪ መሆኗን ፈጽሞ አልዘነጋችም። ባገኘችው አጋጣሚ ተጠቅማ ኤልሳዕ የእውነተኛው አምላክ ነቢይ መሆኑን በድፍረት በመናገር ስለ ይሖዋ ግሩም ምሥክርነት ሰጥታለች። (2 ነገሥት 5:1-19) ከበርካታ ዓመታት በኋላ ደግሞ ወጣቱ ንጉሥ ኢዮስያስ ብልሹ በሆነ ሥርዓት ውስጥ ይኖር የነበረ ቢሆንም ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ሃይማኖታዊ ተሃድሶ አካሂዷል፣ የአምላክን ቤተ መቅደስ አድሷል እንዲሁም ሕዝቡ ወደ ይሖዋ እንዲመለስ አድርጓል። ኢዮስያስ በእምነቱና በአምልኮቱ ይኮራ ነበር። (2 ዜና መዋዕል ምዕራፍ 34 እና 35) በባቢሎን ይኖሩ የነበሩት ዳንኤልና ሦስቱ ዕብራውያን ጓደኞቹ የይሖዋ አገልጋዮች መሆናቸውን ላፍታ እንኳ ዘንግተው አያውቁም። ተጽዕኖና ተፈታታኝ ሁኔታ ቢያጋጥማቸውም እንኳ ከአቋማቸው ዝንፍ አላሉም። የይሖዋ አገልጋዮች በመሆናቸው ይኮሩ እንደነበር ግልጽ ነው።—ዳንኤል 1:8-20

በማንነታችሁ ልትኮሩ ይገባል

14, 15. በክርስቲያናዊ መለያችን መኩራት ሲባል ምን ነገሮችን ይጨምራል?

14 እነዚህ የአምላክ አገልጋዮች እንዲህ ሊሳካላቸው የቻለው በአምላክ ፊት ስላላቸው አቋም ተገቢ ኩራት ይሰማቸው ስለነበረ ነው። እኛስ እንዴት ነን? በክርስቲያናዊ መለያችን መኩራት ሲባል ምን ነገሮችን ይጨምራል?

15 በመጀመሪያ ደረጃ፣ በይሖዋ ስም ከሚጠራው ሕዝብ መካከል በመሆናችን እንዲሁም የይሖዋን በረከትና ሞገስ ለማግኘት በመታደላችን ጥልቅ አድናቆት ሊሰማን ይገባል። አምላክ የእርሱ የሆኑትን በሚገባ ያውቃል። ሃይማኖታዊ ግራ መጋባት በነገሠበት ዘመን የኖረው ሐዋርያው ጳውሎስ “ጌታ [“ይሖዋ፣” NW] የእርሱ የሆኑትን ያውቃል” ሲል ጽፏል። (2 ጢሞቴዎስ 2:19፤ ዘኍልቍ 16:5) ይሖዋ ‘የእርሱ በሆኑት’ ይኮራል። እንዲያውም “የሚነካችሁ የዐይ[ኔ]ን ብሌን ይነካል” በማለት ተናግሯል። (ዘካርያስ 2:8) ይሖዋ እንደሚወደን ግልጽ ነው። ከእርሱ ጋር ያለን ዝምድናም ለእርሱ ባለን ጥልቅ ፍቅር ላይ የተመሠረተ መሆን ይኖርበታል። ጳውሎስ “እግዚአብሔርን የሚወድ ሰው ግን በእግዚአብሔር ዘንድ የታወቀ ነው” በማለት ተናግሯል።—1 ቆሮንቶስ 8:3

16, 17. ክርስቲያኖች ወጣትም ሆኑ አረጋዊ በመንፈሳዊ ውርሻቸው መኩራት የሚገባቸው ለምንድን ነው?

16 በይሖዋ ምሥክሮች ቤተሰብ ውስጥ ያደጉ ወጣቶች ክርስቲያናዊ ማንነታቸው ከአምላክ ጋር ባላቸው የግል ዝምድና ላይ ጥብቅ ሆኖ የተመሠረተ መሆኑን ለማወቅ ራሳቸውን በሚገባ መፈተን ይኖርባቸዋል። በወላጆቻቸው እምነት ብቻ መተማመን አይኖርባቸውም። ጳውሎስ እያንዳንዱን የአምላክ አገልጋይ በሚመለከት “እርሱ ቢወድቅ ወይም ቢቆም ለጌታው ነው” ሲል ጽፏል። አክሎም “እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን ለእግዚአብሔር መልስ እንሰጣለን” በማለት ተናግሯል። (ሮሜ 14:4, 12) በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው ከወላጆቻችሁ የወረሳችሁትን አምልኮ እንዲያው ለወጉ ያህል መከተል ከይሖዋ ጋር የጠበቀና ዘላቂነት ያለው ዝምድና ለመመሥረት አያስችላችሁም።

17 ይሖዋ በታሪክ ዘመናት ሁሉ ምሥክሮች የነበሩት ሲሆን ይህም ከ6,000 ዓመታት በፊት ከኖረው ከታማኙ አቤል አንስቶ በዘመናችን ያሉትን “እጅግ ብዙ” ምሥክሮች እንዲሁም ወደፊት ዘላለማዊ ሕይወት የመውረስ ተስፋ ያላቸውን ሥፍር ቁጥር የሌላቸው የይሖዋ አምላኪዎች ይጨምራል። (ራእይ 7:9፤ ዕብራውያን 11:4) በዚህ ዘመን እኛም ታማኝ አምላኪዎቹ የመሆን መብት አግኝተናል። በእርግጥም ታላቅ መንፈሳዊ ውርስ አግኝተናል!

18. አመለካከታችንና የአቋም ደረጃችን ከዓለም የሚለየን እንዴት ነው?

18 ክርስቲያናዊ መለያችን አመለካከታችንን እንዲሁም ክርስቲያናዊ ባሕርያችንንና አቋማችንን ያካትታል። በሕይወታችን ውስጥ ስኬት የምናገኝበትና አምላክን ማስደሰት የምንችልበት ብቸኛው “መንገድ” ይህ ነው። (የሐዋርያት ሥራ 9:2፤ ኤፌሶን 4:22-24) ክርስቲያኖች ‘ሁሉን ነገር ፈትነው መልካም የሆነውን ይይዛሉ።’ (1 ተሰሎንቄ 5:21) በክርስትና እምነትና ከአምላክ ርቆ በሚገኘው በዚህ ዓለም መካከል ሰፊ ልዩነት እንዳለ በሚገባ እናውቃለን። ይሖዋ በእውነተኛውና በሐሰተኛው አምልኮ መካከል ያለውን ልዩነት በግልጽ አሳውቆናል። በነቢዩ ሚልክያስ አማካኝነት “በዚያን ጊዜም እንደ ገና በጻድቁና በኀጢአተኛው መካከል፣ እግዚአብሔርን በሚያገለግለውና በማያገለግለው መካከል ያለውን ልዩነት ታያላችሁ” በማለት ተናግሯል።—ሚልክያስ 3:18

19. እውነተኛ ክርስቲያኖች የትኛው አደጋ አያሰጋቸውም?

19 ግራ በተጋባውና የሚይዘው የሚጨብጠው በጠፋው በዚህ ዓለም ውስጥ ስንኖር በይሖዋ መኩራት በጣም አስፈላጊ መሆኑን ተመልክተናል፤ ታዲያ በአምላካችን ተገቢ ኩራት እንዲሰማንና ክርስቲያናዊ ማንነታችንን ጠንቅቀን እንድናውቅ ምን ሊረዳን ይችላል? የሚቀጥለው ርዕስ በዚህ ጉዳይ ላይ ጠቃሚ ሐሳቦች ይሰጠናል። እነዚህን ሐሳቦች ስትመለከት እውነተኛ ክርስቲያኖች ፈጽሞ “የግዴለሽነት” ሰለባ እንደማይሆኑ ልትገነዘብ ትችላለህ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a እዚህ ላይ የተጠቀሰው ስለ መንፈሳዊ ማንነታችን ብቻ ነው። የአእምሮ መታወክ ያጋጠማቸው አንዳንድ ሰዎች የሕክምና እርዳታ ማግኘታቸው አስፈላጊ ሊሆን ይችላል።

ታስታውሳለህ?

• ክርስቲያኖች በይሖዋ ‘የሚመኩት’ እንዴት ነው?

• ከሙሴና ከአሳፍ ታሪክ ምን ትምህርት አግኝተሃል?

• የአምላክ አገልጋይ በመሆናቸው የኮሩ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ገጸ ባሕርያትን ጥቀስ።

• በክርስቲያናዊ ማንነታችን መኩራት ምን ነገሮችን ይጨምራል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሙሴ ለጊዜውም ቢሆን ስለማንነቱ ጥርጣሬ ገብቶት ነበር

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በጥንት ዘመን የኖሩ በርካታ የይሖዋ አገልጋዮች በማንነታቸው ኮርተዋል