በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወደ ሳባ ደሴት የተደረገ ጉዞ

ወደ ሳባ ደሴት የተደረገ ጉዞ

ወደ ሳባ ደሴት የተደረገ ጉዞ

የሆላንድ ግዛት የሆነችው የሳባ ደሴት በአንድ ወቅት በካሪቢያን ባሕር ላይ ዝርፊያ ለሚያካሂዱ ሽፍቶች መደበቂያ ነበረች። በዛሬው ጊዜ ይህች ትንሽ ደሴት ከፖርቶ ሪኮ በስተ ምስራቅ 240 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ስትሆን በውስጧ 1,600 የሚያክሉ ነዋሪዎች አሉ፤ ከእነዚህ መካከል አምስቱ የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው። እነዚህ ደፋር አገልጋዮች በዝርፊያ ከሚገኝ ነገር እጅግ የላቀ ዋጋ ያለው ሀብት ለማግኘት በፍለጋ ላይ ናቸው። አዎ፣ ‘ለዘላለም ሕይወት የተዘጋጁ’ ሰዎችን በትጋት እየፈለጉ ናቸው።—የሐዋርያት ሥራ 13:48

የአምላክ መንግሥት ምሥራች ወደ ደሴቲቱ የደረሰው 18 ሜትር ርዝመት ያላት ሲቢያ ተብላ የምትጠራው የይሖዋ ምሥክሮች የሚገለገሉባት መለስተኛ መርከብ ሰኔ 22, 1952 ላይ መልሕቋን በሳባ የባሕር ዳርቻ በጣለችበት ጊዜ ነበር። (ማቴዎስ 24:14) ገስት ማኪ እና ስታንሊ ካርተር የተባሉ ሚስዮናውያን ወንድሞች 500 የድንጋይ ደረጃዎች ያሉትን ጠመዝማዛ አቀበት በመውጣት ዘ ቦተም ተብላ ወደምትጠራው የደሴቲቱ ዋና ከተማ ደረሱ። a ለብዙ ዘመናት ወደ ደሴቲቱ ነዋሪዎች ለመድረስ ያለው ብቸኛ አማራጭ ይህ ጠባብ መንገድ ነበር።

በሳባ ደሴት የተደረገውን የስብከት ሥራ አስመልክቶ ለመጀመሪያ ጊዜ ሪፖርት የወጣው በ1966 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ ላይ ነበር። ይህ ሪፖርት በወቅቱ በደሴቲቱ ላይ የነበረው አንድ የይሖዋ ምሥክር ብቻ እንደነበር ይገልጻል። በኋላም ከካናዳ የመጡ አንድ ቤተሰብ ለበርካታ ዓመታት የመንግሥቱን ምሥራች በዚያ ሰብከዋል። በቅርቡ ደግሞ ረስልና ካቲ የተባሉ ጡረታ የወጡ ባልና ሚስት ከአሜሪካ ወደ ሳባ ሄደው በስብከቱ ሥራ ተካፍለዋል። እስቲ በዚያ ያጋጠማቸውን ተመልከት።

በሳባ ያደረግነው ጉብኝት

እኔና ባለቤቴ ከአውሮፕላን ስንወርድ በእንግድነት የተቀበለን በ1990ዎቹ አብዛኞቹ ዓመታት በደሴቲቱ የነበረው ብቸኛ የይሖዋ ምሥክር ወንድም ሮነልድ ነበር። ወንድም በአውሮፕላን ማረፊያው እየጠበቀን ነበር። በደሴቲቱ ላይ ለሽያጭ ተብሎ የሚለማ እርሻ ስለሌለ በአንዲት ትንሽ ሣጥን በስጦታ መልክ ይዘንለት የመጣነውን አትክልት ሲመለከት በጣም ደስ አለው። ከዚያም በአንዲት አነስተኛ የጭነት መኪና በመሳፈር ጠመዝማዛውን መንገድ ተከትለን ሲነሪ ወደተባለው ተራራ ጫፍ መውጣት ጀመርን።

ሄልስ ጌት የተባለችው መንደር ስንደርስ መኪናችንን አቆምንና ሮነልድ የእሁዱ የሕዝብ ስብሰባ ፕሮግራም እንደተለጠፈ ለማየት መንደሩ ውስጥ ወዳለው የሕዝብ ማስታወቂያ ሰሌዳ ሄደ። ተመልሶ መጥቶ መለጠፉን ሲነግረን በጣም ደስ አለን። ከዚያ በኋላ ዳገቱን ይዘን ዊንድዋርድሳይድ (ወደ ነፋሱ አቅጣጫ ማለት ነው) ወደ ተባለችው የደሴቲቱ ትልቅ መንደር አቀናን። የስሟ ትርጉም እንደሚያመለክተው ይህች ዓይነ ገብ መንደር የተቆረቆረችው ወደ ደሴቲቱ ነፋስ በሚነፍስበት አቅጣጫ ከባሕር ወለል በላይ 400 ሜትር ከፍ ብላ ነው። ወደ ሮነልድ ቤት ስንቃረብ በረንዳው ላይ የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ የሚል ምልክት ተመለከትን።

ምሳ እየተመገብን እያለ “በሳባ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪ የሆንከው እንዴት ነው?” ስል ጠየቅሁት፤ ወደዚያ ለመሄድ ያነሳሳን ዋናው ምክንያት ይህ ነበር።

ሮነልድ እንዲህ አለን:- “በፖርቶ ሪኮ ይገነባ የነበረው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ በ1993 ሲጠናቀቅ እኔና ባለቤቴ ውጭ አገር በማገልገል ለመቀጠል ፈለግን። ቀደም ብሎ ከአንድ ባልና ሚስት አቅኚዎች ጋር ሳባን በጎበኘንበት ወቅት ደሴቲቱ 1,400 ነዋሪዎች ያሏት ቢሆንም አንድም የይሖዋ ምሥክር እንደማይገኝባት አወቅን። ስለዚህ ፖርቶ ሪኮ ለሚገኘው ቅርንጫፍ ኮሚቴ ወደዚህ መጥተን የማገልገል ፍላጎት እንዳለን አሳወቅን።

“ሁሉም ነገር ተሳክቶልን በመጨረሻ ወደዚያ እንድንሄድ ተፈቀደልን። የሚያሳዝነው ግን ከሁለት ዓመት በኋላ ባለቤቴ በጠና ታመመችና ወደ ካሊፎርኒያ ተመለስን። ከእርሷ ሞት በኋላ ወደ ሳባ ተመለስሁ። አያችሁ አንድ ነገር ጀምሮ መተው አይሆንልኝም።”

በሳባ ከቤት ወደ ቤት መመሥከር

የሮነልድ ቤት አንድ መቶ ዓመት ያስቆጠረ ሲሆን ሳሎኑ የመንግሥት አዳራሽ ሆኖም ያገለግላል። b ቁርሳችንን በልተን ወደ አገልግሎት ለመውጣት እየተዘጋጀን ሳለ ድንገት የጣለው ዝናብ ከላይ ክፍት የሆነውን ማዕድ ቤት አረጠበው። ከቁርስ በኋላ ዘ ቦተም በተባለችው መንደር ከቤት ወደ ቤት ማገልገል ጀመርን። በእያንዳንዱ ቤት የምናገኛቸውን ሰዎች ሮነልድ በስም ያውቃቸዋል። ውይይታችን የሚያተኩረው በቅርቡ በአካባቢው በቀረበ የዜና ርዕሰ ጉዳይ ላይ ነበር። አብዛኞቹ ሰዎች ለሮነልድና ለሚያከናውነው አገልግሎት እንግዳ አይደሉም፤ ብዙዎቹም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በደስታ ይወስዳሉ።

አንድ ሰው በመንደሩ ውስጥ ካሉት ነዋሪዎች ጋር በደንብ የሚተዋወቅ ካልሆነ በስተቀር ለመንግሥቱ ምሥራች ፍላጎት ያሳዩትን መዝግቦ መያዝ አስቸጋሪ ነው። ለምን? ምክንያቱን ሮነልድ እንደነገረን “ሁሉም ቤቶች ተመሳሳይ ቀለም እንዲቀቡ ሕጉ ያዝዛል።” እኔም ግራና ቀኝ ስመለከት በሳባ ያሉ ቤቶች ሁሉ ግድግዳቸው ነጭ፣ ጣሪያቸው ደግሞ ቀይ ቀለም የተቀባ መሆኑን አስተዋልኩ።

መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይታችንን ስንጨርስ የቤቱን ባለቤቶች እሁድ በመንግሥት አዳራሽ በሚሰጠው የሕዝብ ንግግር ላይ እንዲገኙ እንጋብዛቸዋለን። ሮነልድ ከደሴቲቱ ርቆ ካልሄደ በስተቀር በየሳምንቱ የሕዝብ ንግግር ያቀርባል። በአሁኑ ወቅት በሳባ 17 የሚያክሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች አሉ። በ2004 በተከበረው የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ ላይ 20 ሰዎች ተገኝተው ነበር። ይህ ቁጥር ትንሽ ሊመስል ቢችልም ከጠቅላላው የደሴቷ ነዋሪዎች መካከል አንድ በመቶውን የሚወክል ነው!

በእርግጥም የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክን የመዳን መልእክት በተቻለ መጠን ለብዙ ሰው ለማሰማት ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ። የይሖዋ ምሥክሮች ሳባን በመሰለ ትንሽ ደሴት ላይም ሆነ በአንድ ትልቅ አኀጉር ውስጥ ‘ሕዝቦችን ሁሉ ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉ’ የተሰጣቸውን ተልእኮ በታማኝነት እየተወጡ ነው።—ማቴዎስ 28:19

የሚያሳዝነው ጉብኝታችን በፍጥነት አለቀብን። አስተናጋጃችንን ተሰናብተን ወደ አውሮፕላናችን አመራን። በሳባ ያደረግነውን ጉብኝትና ዘ ቦተም ለመድረስ የወጣነውን ዳገት መቼም አንረሳውም!

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a ከተማዋ ፈንድቶ ባበቃለት እሳተ ገሞራ ሥር ስለተቆረቆረች የባሕር ላይ ዘራፊዎቹ ዘ ቦተም የሚለውን ስም እንደሰጧት ይታሰባል።

b መስከረም 28, 2003 ከዩናይትድ ስቴትስ፣ ፍሎሪዳ የመጡ ፈቃደኛ ሠራተኞች በዚያ አቅራቢያ የሚገኝ አንድ ሕንፃ በአዲስ መልክ ሠርተው አሁን የመንግሥት አዳራሽ ሆኖ ያገለግላል።

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፖርቶ ሪኮ

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ከበስተጀርባ ያለው ሥዕል:- www.sabatourism.com