የአንባቢያን ጥያቄዎች
የአንባቢያን ጥያቄዎች
በ2 ሳሙኤል 12:31 እና በ1 ዜና መዋዕል 20:3 ላይ ከሚገኘው ዘገባ በመነሳት አንዳንዶች እንደሚሉት አምላክ እንደልቤ ያለው ዳዊት በምርኮ በያዛቸው ሰዎች ላይ ጭካኔ ፈጽሞባቸዋል?
በፍጹም። ዳዊት አሞናውያን ምርኮኞቹን የጉልበት ሥራ እንዲሠሩ ወሰነባቸው እንጂ የፈጸመባቸው ግፍ የለም። ነገር ግን አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች እነዚህን ጥቅሶች የተረጎሙበት መንገድ ሰዎች የዳዊትን ድርጊት በተሳሳተ መንገድ እንዲረዱ አድርጓቸዋል።
እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ዳዊት አሞናውያንን የቀጣበትን መንገድ የገለጹት ጨካኝና አረመኔ እንደሆነ አድርገው ነው። ለምሳሌ በ1879 የታተመው የአማርኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም 2 ሳሙኤል 12:31ን እንዲህ በማለት ተርጉሞታል:- “በውሥጥዋም የነበረውን ሕዝብ አውጥቶ በመጋዝ በታች በብረት መንኰራኲርና በብረት መጥረቢያ በታች አስቀመጣቸው ከጡብ እቶንም አገባቸው። በዓሞንም ልጆች አገር ሁሉ እንዴህ አደረገ።” በ1 ዜና መዋዕል 20:3 ላይ የሚገኘው ዘገባም የተተረጎመው በተመሳሳይ መንገድ ነው።
ይህንን አስመልክተው ሳሙኤል ሮልስ ድራይቨር የተባሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑር “የዳዊትን ባሕርይና አስተሳሰብ እስከምናውቀው ድረስ [ጭካኔ] የሚባል ነገር ታይቶበት አያውቅም” ሲሉ ተናግረዋል። በመሆኑም ዚ አንከር ባይብል የተባለው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ያሰፈረውን ሐሳብ ተመልከት:- “ዳዊት የኢኮኖሚ ጥቅም ለማግኘት ሲል ድል አድርጎ በያዛቸው አካባቢዎች የሚኖሩትን ምርኮኞች በተለያየ የሥራ መስክ አሰማርቷቸዋል፤ በጦርነት ድል ያደረጉ ነገሥታት ደግሞ እንዲህ የማድረግ ልማድ ነበራቸው።” ከዚሁ ጋር በሚስማማ መንገድ አዳም ክላርክ የተባሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑር እንዲህ ብለዋል:- “በመሆኑም የጥቅሱ ሐሳብ ዳዊት ምርኮኞቹን በባርነት በመግዛት እንጨት እንዲቆርጡ፣ የብረት መሣሪያዎችን እንዲሠሩ፣ ማዕድን እንዲያወጡ፣ . . . እንጨት እንዲጠርቡ እንዲሁም ጡብ እንዲሠሩ ያደርግ እንደነበረ ይጠቁማል። ጥቅሱ ሰዎችን በመጋዝ መሰንጠቅን፣ መፍለጥን፣ መቁረጥንና መጥረብን አያሳይም። በተጨማሪም ዳዊት በአሞናውያን ላይ ከፈጸመው ሁኔታ ጋር የሚስማማ አይደለም።”
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የተዘጋጁ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ይህን የተሻለ ግንዛቤ መሠረት በማድረግ ጥቅሱን ያሰፈሩበት መንገድ ዳዊት ሰብዓዊነት በጎደለው ድርጊት መወንጀል እንደሌለበት በግልጽ ያሳያል። a አዲሱ መደበኛ ትርጉም (1993) ምን እንደሚል ተመልከት:- “እዚያ የነበሩትንም ሕዝብ አውጥቶ መጋዝ፣ የብረት መቈፈሪያና መጥረቢያ ተጠቅመው ሥራ እንዲሠሩ አደረጋቸው፣ እንዲሁም የሸክላ ጡብ አሠራቸው። እንዲህ ያለውም ሥራ በሌሎቹ የአሞናውያን ከተሞች ሁሉ እንዲፈጸም አደረገ።” (2 ሳሙኤል 12:31) “በዚያ የነበረውን ሕዝብ አውጥቶ መጋዝ፣ ዶማና መጥረቢያ ይዘው እንዲሠሩ አደረጋቸው። ዳዊት በሌሎቹም የአሞን ከተሞች ሁሉ ይህንኑ አደረ[ገ]።” (1 ዜና መዋዕል 20:3) የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑራን አሁን ካላቸው ግንዛቤ ጋር በሚስማማ መንገድ በ1954 የታተመው የአማርኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ጥቅሱን እንዲህ በማለት ይተረጉመዋል:- “በውስጥዋም የነበሩትን ሕዝብ አውጥቶ በመጋዝና በብረት መቈፈሪያና በብረት መጥረቢያ እንዲሠሩ አደረጋቸው፤ የሸክላ ጡብም እንዲያቃጥሉ አደረጋቸው፤ በአሞን ልጆች ከተሞች ሁሉ እንዲህ አደረገ።” (2 ሳሙኤል 12:31) “በውስጥዋም የነበረውን ሕዝብ አውጥቶ በመጋዝና በብረት መቈፈሪያ በመጥረቢያም እንዲሠሩ አደረጋቸው። እንዲሁም ዳዊት በአሞን ልጆች ከተሞች ሁሉ አደረገ።”—1 ዜና መዋዕል 20:3
ዳዊት ሽንፈት የደረሰባቸውን አሞናውያን በጭካኔ አላሰቃያቸውም ወይም አሰቃቂ በሆነ መንገድ አልገደላቸውም። በዘመኑ የነበሩትን አሰቃቂና ዘግናኝ የጦርነት ልማዶች አልተከተለም።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a አንድ ሆሄ ብቻ ቢቀየር የዕብራይስጡ ጥቅስ “በመጋዝ እንዲቆርጡ አደረጋቸው” በሚለው ፋንታ “በመጋዝ ቆራረጣቸው” የሚል ትርጉም ይኖረዋል። በተጨማሪም በዕብራይስጡ “የጡብ እቶን” ለማመልከት የተሠራበት ቃል “የጡብ ቅርጽ ማውጫ” የሚል ትርጉም ሊኖረው ይችላል። ስለዚህ በአንድ ጠባብ የጡብ ቅርጽ ማውጫ ውስጥ ሰው ያልፋል ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው።