በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለባለ ትዳሮች የሚሆን ጥበብ ያዘለ መመሪያ

ለባለ ትዳሮች የሚሆን ጥበብ ያዘለ መመሪያ

ለባለ ትዳሮች የሚሆን ጥበብ ያዘለ መመሪያ

“ሚስቶች ሆይ፤ ለጌታ እንደምትገዙ ለባሎቻችሁም ተገዙ። ባሎች ሆይ . . . ሚስቶቻችሁን ውደዱ።”—ኤፌሶን 5:22, 25

1. ስለ ጋብቻ ሊኖረን የሚገባው ትክክለኛ አመለካከት ምንድን ነው?

 ኢየሱስ ጋብቻ አንድ ወንድና አንዲት ሴት ተጣምረው “አንድ ሥጋ” የሚሆኑበት መለኮታዊ ዝግጅት እንደሆነ ተናግሯል። (ማቴዎስ 19:5, 6) ጋብቻ ተመሳሳይ ፍላጎቶችን ለማዳበር የሚጥሩና የጋራ ግቦችን ዳር ለማድረስ አብረው የሚሠሩ የተለያየ ባሕርይ ያላቸው ሁለት ሰዎች ጥምረት ነው። ጋብቻ የዕድሜ ልክ ቃል ኪዳን እንጂ በቀላሉ የሚፈርስ ጊዜያዊ ስምምነት አይደለም። በብዙ አገሮች ውስጥ ፍቺ በቀላሉ ሊፈጸም የሚችል ቢሆንም በክርስቲያኖች ዓይን ግን ጋብቻ ቅዱስ ዝምድና ነው። ትዳር የሚፈርሰው አንድ ከባድ ችግር ከተፈጠረ ብቻ ነው።—ማቴዎስ 19:9

2. (ሀ) ባልና ሚስት እርዳታ ማግኘት የሚችሉባቸው ዝግጅቶች የትኞቹ ናቸው? (ለ) ትዳር የተሳካ እንዲሆን ጥረት ማድረግ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

2 አንዲት የጋብቻ አማካሪ “የተሳካ ትዳር አዳዲስ ክስተቶች የሚስተናገዱበት፣ ችግሮች እንደ አመጣጣቸው መፍትሄ የሚያገኙበት እንዲሁም ለትዳር የሚረዱ ነገሮች ሁሉ ጥቅም ላይ የሚውሉበት ቀጣይነት ያለው የለውጥ ሂደት ነው” ብለዋል። ክርስቲያን ባልና ሚስቶች ሊጠቀሙባቸው ከሚችሉ ዝግጅቶች መካከል መጽሐፍ ቅዱስ የያዘው ጥበብ ያዘለ ምክር፣ ከክርስቲያን ባልንጀሮቻቸው የሚያገኙት እርዳታ እንዲሁም በጸሎት አማካኝነት ከይሖዋ ጋር የሚመሠርቱት የጠበቀ ዝምድና ይገኙበታል። የተሳካ ትዳር ጸንቶ የሚቀጥል ከመሆኑም ሌላ ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ባልና ሚስቱ በትዳራቸው ተደስተውና ረክተው ይኖራሉ። ከሁሉ በላይ ደግሞ የጋብቻ መሥራች ለሆነው ለይሖዋ አምላክ ክብር ያመጣለታል።—ዘፍጥረት 2:18, 21-24፤ 1 ቆሮንቶስ 10:31፤ ኤፌሶን 3:15፤ 1 ተሰሎንቄ 5:17

ኢየሱስንና ጉባኤውን ምሰሉ

3. (ሀ) ጳውሎስ ላገቡ ሰዎች የሰጠው ምክር ፍሬ ሐሳብ ምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ ምን ጥሩ ምሳሌ ትቷል?

3 ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት ሐዋርያው ጳውሎስ ለክርስቲያን ባልና ሚስቶች ይህን ጥበብ ያዘለ ምክር ጽፏል:- “ቤተ ክርስቲያን ለክርስቶስ እንደምትገዛ፣ ሚስቶችም ለባሎቻቸው በማንኛውም ነገር እንደዚሁ መገዛት ይገባቸዋል። ባሎች ሆይ፤ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳትና ራሱንም ስለ እርሷ አሳልፎ እንደ ሰጠ፣ እናንተም ሚስቶቻችሁን ውደዱ።” (ኤፌሶን 5:24, 25) እዚህ ላይ የቀረበው ንጽጽር ነጥቡን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል! ለባሎቻቸው በትሕትና የሚገዙ ክርስቲያን ሚስቶች የራስነትን መሠረታዊ ሥርዓት በመቀበልና በማክበር ረገድ ጉባኤውን ይመስላሉ። በጥሩም ሆነ በአስቸጋሪ ጊዜያት ሚስቶቻቸውን የሚወድዱ አማኝ የሆኑ ባሎች ክርስቶስ ጉባኤውን በመውደድና በመንከባከብ ረገድ የተወውን ምሳሌ በጥብቅ እንደሚከተሉ ያሳያሉ።

4. ባሎች የኢየሱስን ምሳሌ መከተል የሚችሉት እንዴት ነው?

4 ክርስቲያን ባሎች የቤተሰባቸው ራስ ናቸው። ይሁንና እነርሱም ራስ አላቸው፤ እርሱም ኢየሱስ ነው። (1 ቆሮንቶስ 11:3) ስለዚህ ኢየሱስ ጉባኤውን ይንከባከብ እንደነበረ ሁሉ ባሎችም መሥዋዕት መክፈል የሚጠይቅባቸው ቢሆንም እንኳ የቤተሰባቸውን መንፈሳዊም ሆነ ቁሳዊ ፍላጎት በፍቅር ተነሳስተው ማሟላት ይኖርባቸዋል። የቤተሰባቸውን ደኅንነት ከራሳቸው ፍላጎትና ምርጫ ያስቀድማሉ። ኢየሱስ “ሌሎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ነገር እናንተም አድርጉላቸው” ብሏል። (ማቴዎስ 7:12) ይህ መሠረታዊ ሥርዓት በትዳር ውስጥ ትልቅ ቦታ አለው። ጳውሎስ “ባሎችም እንደዚሁ ሚስቶቻቸውን እንደ ገዛ ሥጋቸው መውደድ ይገባቸዋል። . . . የገዛ ሥጋውን የሚጠላ ማንም የለም፤ ይመግበዋል፤ ይንከባከበዋል” ብሎ በጻፈ ጊዜ ይህን አሳይቷል። (ኤፌሶን 5:28, 29) አንድ ሰው ራሱን ለመመገብና ለመንከባከብ የሚተጋውን ያህል ሚስቱንም መመገብና መንከባከብ ይኖርበታል።

5. ሚስቶች ክርስቲያን ጉባኤን መምሰል የሚችሉት እንዴት ነው?

5 አምላክን የሚያከብሩ ሚስቶች ክርስቲያን ጉባኤን አርዓያ አድርገው ይመለከታሉ። ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት ተከታዮቹ ሥራቸውን በደስታ ትተው ተከትለውታል። ኢየሱስ ከሞተ በኋላም እርሱን መታዘዛቸውን የቀጠሉ ከመሆኑም ሌላ ላለፉት 2,000 ዓመታት ገደማ እውነተኛው የክርስቲያን ጉባኤ ለኢየሱስ ሥልጣን ሲገዛና በማንኛውም ነገር የእርሱን አመራር ሲከተል ቆይቷል። በተመሳሳይ ክርስቲያን ሚስቶች ባሎቻቸውን በንቀት አይመለከቱም ወይም በጋብቻ ውስጥ ያለውን ቅዱስ ጽሑፋዊ የራስነት ዝግጅት አቅልለው አይመለከቱም። ከዚህ ይልቅ ባሎቻቸውን የሚደግፉና ለሥልጣናቸው የሚገዙ ከመሆኑም በተጨማሪ ከእነርሱ ጋር ተባብረው ስለሚሠሩ የብርታት ምንጭ ይሆኑላቸዋል። ባሎችም ሆኑ ሚስቶች እንዲህ በፍቅር የሚመሩ ከሆነ ትዳራቸው የሰመረ ይሆናል፤ እንዲሁም ሁለቱም በትዳራቸው ተደስተው ይኖራሉ።

አብራችኋቸው ኑሩ

6. ጴጥሮስ ለባሎች ምን ምክር ሰጥቷል? ምክሩ አስፈላጊ የሆነውስ ለምንድን ነው?

6 ሐዋርያው ጴጥሮስም ለባልና ሚስቶች ምክር የሰጠ ሲሆን በተለይ ለባሎች የሰጠው ሐሳብ ጠንከር ያለ ነው። “ጸሎታችሁ እንዳይደናቀፍ በኑሮአችሁ ሁሉ ለሚስቶቻችሁ አስቡላቸው፣ ደካሞች ስለሆኑና የሕይወትንም በረከት አብረዋችሁ ስለሚወርሱ አክብሯቸው” ብሏል። (1 ጴጥሮስ 3:7) ጥቅሱ ላይ የሚገኙት የመጀመሪያዎቹ ቃላት ጴጥሮስ የሰጠው ምክር ምን ያህል አሳሳቢ እንደሆነ ያሳያሉ። አንድ ባል ሚስቱን በአክብሮት መያዝ ካልቻለ ከይሖዋ ጋር ያለው ዝምድና ይበላሽበታል። ጸሎቱ ይደናቀፋል ወይም ተሰሚነት ያጣል።

7. አንድ ባል ለሚስቱ አክብሮት ማሳየት ያለበት እንዴት ነው?

7 ታዲያ ባሎች ሚስቶቻቸውን በክብር መያዝ የሚችሉት እንዴት ነው? ሚስትን ማክበር ሲባል ከፍ በማድረግና የላቀ ግምት በመስጠት እርሷን በፍቅር መያዝ ማለት ነው። ሚስትን እንዲህ በደግነት መያዝ በወቅቱ ለብዙዎች አዲስ ነገር ሊሆንባቸው ይችላል። አንድ ግሪካዊ ምሑር እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “በሮማውያን ሕግ ሥር አንዲት ሴት ምንም መብት አልነበራትም። በሕጉ መሠረት ከልጆች የተለየ መብት አልነበራትም። . . . ሙሉ በሙሉ ለባሏ ሥልጣን የምትገዛ ከመሆኑም ሌላ እንዳሻው ሊያደርጋት ይችል ነበር።” ይህ ሁኔታ ከክርስትና ትምህርት በጣም የተለየ ነው! አንድ ክርስቲያን ባል ለሚስቱ አክብሮት ያሳያል። ከእርሷ ጋር ያለው ግንኙነት የሚመራው በክርስቲያናዊ መሠረታዊ ሥርዓት እንጂ በወረት ስሜት አይደለም። ከዚህ በተጨማሪ ሚስቱ ደካማ ዕቃ መሆኗን ግምት ውስጥ በማስገባት ‘ያስብላታል።’

“ደካሞች” የሚባሉት ከምን አንጻር ነው?

8, 9. ሴቶች ከወንዶች ጋር እኩል የሆኑት በየትኞቹ መንገዶች ነው?

8 ጴጥሮስ ሚስት ‘ደካማ’ ነች ሲል ሴቶች በአስተሳሰብ ወይም በመንፈሳዊነት ከወንዶች ያንሳሉ ማለቱ አልነበረም። እርግጥ፣ ብዙ ክርስቲያን ወንዶች በጉባኤ ውስጥ የአገልግሎት መብት ያላቸው ሲሆን እህቶች ግን እነዚህን መብቶች ለማግኘት አይጠብቁም፤ በቤተሰብ ክልል ውስጥ ደግሞ ሴቶች ለባሎቻቸው ሥልጣን ይገዛሉ። (1 ቆሮንቶስ 14:35፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:12) ይሁን እንጂ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች እምነትና ጽናት እንዲያሳዩ እንዲሁም ከፍተኛ የሥነ ምግባር ደረጃ እንዲከተሉ ይጠበቅባቸዋል። ደግሞም ጴጥሮስ እንዳለው ባሎችም ሆኑ ሚስቶች ‘የሕይወትን በረከት አብረው ይወርሳሉ።’ መዳንን በተመለከተ በይሖዋ አምላክ ፊት ሁለቱም እኩል ቦታ አላቸው። (ገላትያ 3:28) ጴጥሮስ ደብዳቤውን የጻፈው በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ነበር። ስለዚህ ‘ከክርስቶስ ጋር አብረው ወራሾች’ እንደመሆናቸው መጠን እነርሱም ሆኑ ሚስቶቻቸው ተመሳሳይ ሰማያዊ ተስፋ እንዳላቸው ክርስቲያን ባሎችን አስታውሷቸዋል። (ሮሜ 8:17) አንድ ቀን ሁለቱም በሰማይ በተቋቋመው የአምላክ መንግሥት ካህናትና ነገሥታት ሆነው የሚያገለግሉበት ጊዜ ይመጣል!—ራእይ 5:10

9 በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያን ሚስቶች በመንፈስ ከተቀቡ ክርስቲያን ባሎቻቸው በምንም መንገድ አያንሱም። በመሠረታዊ ሥርዓት ደረጃ ደግሞ ይኸው ሐሳብ ምድራዊ ተስፋ ላላቸውም ይሠራል። ‘የእጅግ ብዙ ሕዝብ’ ክፍል የሆኑ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ልብሳቸውን በበጉ ደም አጥበው ንጹሕ አድርገዋል። ወንዶችም ሆኑ ሴቶች በዓለም ዙሪያ ለይሖዋ በሚቀርብ ውዳሴ “ቀንና ሌሊት” ይካፈላሉ። (ራእይ 7:9, 10, 14, 15) ወንዶችም ሆኑ ሴቶች “እውነተኛ የሆነውን ሕይወት” አግኝተው “ለእግዚአብሔር ልጆች ወደ ሆነው ወደ ከበረው ነጻነት” ለመድረስ ይናፍቃሉ። (ሮሜ 8:21፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:19) ቅቡዓንም ሆኑ ሌሎች በጎች ሁሉም ክርስቲያኖች ‘በአንድ እረኛ’ ሥር ‘አንድ መንጋ’ ሆነው ይሖዋን በኅብረት ያገለግላሉ። (ዮሐንስ 10:16) በእርግጥም ይህ፣ አንድ ክርስቲያን ባልና ሚስት አንዳቸው ለሌላው ተገቢውን አክብሮት እንዲያሳዩ የሚያስገድድ አጥጋቢ ምክንያት ነው!

10. ሴቶች ‘ደካማ’ ናቸው የሚባለው ከምን አንጻር ነው?

10 ታዲያ ሴቶች “ደካሞች” የተባሉት ከምን አንጻር ነው? ምናልባት ጴጥሮስ በጥቅሉ ሲታይ ሴቶች በሰውነትም ሆነ በአካላዊ ጥንካሬ ከወንዶች እንደሚያንሱ ማመልከቱ ሊሆን ይችላል። ከዚህ በተጨማሪ ሰዎች ፍጽምና የሚጎድለን ከመሆኑ የተነሳ ሴቶች ያላቸው ልጆች የመውለድ አስደናቂ ችሎታ በአካላዊ ጤንነታቸው ላይ ጉዳት ያስከትላል። ልጅ መውለድ በሚችሉበት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሴቶች በየጊዜው የጤና መታወክ ሊያጋጥማቸው ይችላል። እንዲህ ዓይነት የጤና መታወክ ሲያጋጥማቸው ወይም ከእርግዝናና ልጅ ከመውለድ ጋር በተያያዘ ድካም ሲሰማቸው ልዩ እንክብካቤና አሳቢነት ሊያገኙ ይገባል። የሚያስፈልጋትን ስሜታዊ ድጋፍ ተገንዝቦ ሚስቱን በክብር የሚይዝ ባል ለትዳራቸው መሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል።

በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤተሰብ ውስጥ

11. አንድ ባልና ሚስት የተለያየ ሃይማኖት ቢኖራቸውም ትዳራቸው ሰምሯል የሚባለው ከምን አንጻር ነው?

11 የትዳር ጓደኛሞች ከተጋቡ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ አንዳቸው እውነትን በመቀበላቸው የተነሳ ሃይማኖታዊ አመለካከታቸው ቢለያይስ? እንዲህ ዓይነቱ ትዳር የሰመረ ሊሆን ይችላል? በብዙዎች ላይ እንደታየው አዎ፣ ሊሰምር ይችላል። የተለያየ ሃይማኖታዊ አመለካከት ያላቸው አንድ ባልና ሚስት ትዳራቸው እስከዘለቀና ሁለቱም ደስተኞች እስከሆኑ ድረስ ጋብቻቸው የሰመረ ነው ሊባል ይችላል። ከዚህ በተጨማሪ አሁንም “አንድ ሥጋ” ስለሆኑ ጋብቻቸው በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት አለው። ስለዚህ አማኝ ያልሆነው ወገን አብሮ ለመኖር ፈቃደኛ ከሆነ ክርስቲያን ባሎች ወይም ሚስቶች አብረው እንዲኖሩ ተመክረዋል። ልጆች ያሏቸው ከሆነ ክርስቲያን የሆነው ወላጅ የሚያሳየው ታማኝነት ልጆቹን ሊጠቅማቸው ይችላል።—1 ቆሮንቶስ 7:12-14

12, 13. ክርስቲያን ሚስቶች የጴጥሮስን ምክር በመከተል አማኝ ያልሆኑ ባሎቻቸውን መርዳት የሚችሉት እንዴት ነው?

12 ጴጥሮስ በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤት ውስጥ ለሚኖሩ ክርስቲያን ሴቶች ደግነት የተሞላበት ምክር ሰጥቷቸዋል። ለሚስቶች የሰጠው ምክር በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ ክርስቲያን ባሎችም በመሠረታዊ ሥርዓት ደረጃ ይሠራል። ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ሚስቶች ሆይ፤ እናንተም እንደዚሁ ለባሎቻችሁ ተገዙ፤ አንዳንድ ለቃሉ የማይታዘዙ ቢኖሩ፣ ያለ ቃል በሚስቶቻቸው አኗኗር ተማርከው ይመለሳሉ፤ ይህም የሚሆነው ንጹሕና ፍጹም አክብሮት የተሞላውን ኑሮአችሁን ሲመለከቱ ነው።”—1 ጴጥሮስ 3:1, 2

13 አንዲት ሚስት ለባሏ እምነቷን በዘዴ ማስረዳት ከቻለች ጥሩ ነው። እርሱ ግን መስማት ባይፈልግስ? ይህ ምርጫው ነው። ይሁንና ክርስቲያናዊ አኗኗር ከፍተኛ ምሥክርነት ሊሰጥ ስለሚችል ነገሩ አበቃለት ማለት አይደለም። በፊት ለመልእክቱ ፍላጎት ያልነበራቸው ይባስ ብሎም የሚስቶቻቸውን እምነት ይቃወሙ የነበሩ ብዙ ባሎች የሚስቶቻቸውን መልካም አኗኗር ከተመለከቱ በኋላ ‘ለዘላለም ሕይወት የተዘጋጁ’ ለመሆን በቅተዋል። (የሐዋርያት ሥራ 13:48) አንድ ባል የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ባይቀበል እንኳ የሚስቱ አኗኗር በጎ አመለካከት ሊያሳድርበትና ከዚህም የተነሳ ትዳራቸው ሊጠናከር ይችላል። ሚስቱ የይሖዋ ምሥክር የሆነች አንድ ባል የይሖዋ ምሥክሮችን ከፍተኛ የሥነ ምግባር ደረጃ መከተል እንደሚከብደው በግልጽ ተናግሯል። ሆኖም ለአንድ ጋዜጣ በጻፈው ደብዳቤ ላይ “ጥሩ ሚስት ያለችኝ ደስተኛ ባል ነኝ” ያለ ከመሆኑም በላይ ባለቤቱንና የእምነት ባልንጀሮቿን ከልብ አመስግኗቸዋል።

14. ባሎች አማኝ ያልሆኑ ሚስቶቻቸውን መርዳት የሚችሉት እንዴት ነው?

14 ጴጥሮስ በሰጠው ምክር ላይ የሚገኘውን መሠረታዊ ሥርዓት በተግባር ያዋሉ ክርስቲያን ባሎችም በአኗኗራቸው ሚስቶቻቸውን አሸንፈዋል። አማኝ ያልሆኑ ሚስቶች ባሎቻቸው በማጨስ፣ በመጠጣትና ቁማር በመጫወት ገንዘብ ማባከን ትተው ኃላፊነት የሚሰማቸው ሰዎች ሲሆኑ እንዲሁም ክፉ ቃል መናገራቸውን ሲያቆሙ ተመልክተዋል። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ ከሌሎች የክርስቲያን ጉባኤ አባላት ጋር በቅርብ የመተዋወቅ አጋጣሚ አግኝተዋል። ፍቅር የሰፈነበት ክርስቲያናዊው የወንድማማች ማኅበር አድናቆት ያሳደረባቸው ከመሆኑም በተጨማሪ በወንድሞች መካከል የተመለከቱት ነገር ወደ ይሖዋ እንዲሳቡ አድርጓቸዋል።—ዮሐንስ 13:34, 35

“የውስጥ ሰውነት”

15, 16. አማኝ ያልሆነ አንድ ባል ክርስቲያን ሚስቱ የምታሳየው የትኛው ባሕርይ ሊማርከው ይችላል?

15 አንድን ባል ሊማርከው የሚችለው ምን ዓይነት ባሕርይ ነው? ክርስቲያን ሴቶች እንዲያዳብሩ የሚጠበቅባቸው ባሕርይ እንደሆነ የታወቀ ነው። ጴጥሮስ እንዲህ ብሏል:- “ውበታችሁ በውጫዊ ነገሮች በመሽሞንሞን ይኸውም ሹሩባ በመሠራት፣ በወርቅ በማጌጥና በልብስ አይሁን፤ ነገር ግን ውበታችሁ በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ፣ ገርና ጭምት መንፈስ ያለበት፣ ምንጊዜም የማይጠፋ የውስጥ ሰውነት ውበት ይሁን። ተስፋቸውን በእግዚአብሔር ላይ የጣሉ የቀድሞ ቅዱሳት ሴቶች ራሳቸውን ያስዋቡት በዚህ ዐይነት ለባሎቻቸው በመገዛት ነበርና። ሣራም አብርሃምን ‘ጌታዬ’ እያለች ትታዘዘው ነበር፣ እናንተም ምንም ሳትፈሩ መልካም ብታደርጉ የእርሷ ልጆች ናችሁ።”—1 ጴጥሮስ 3:3-6

16 ጴጥሮስ አንዲት ክርስቲያን ሴት በውጫዊ ውበቷ እንዳትመካ ምክር ሰጥቷል። ከዚህ ይልቅ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በውስጣዊ ሰውነቷ ላይ ያመጣውን ለውጥ ባሏ እንዲያስተውል ማድረግ መቻል አለባት። አዲሱን ሰው መልበሷን እንዲያይ ማድረግ አለባት። ምናልባትም ሚስቱ ያደረገችውን ለውጥ በፊት ከነበራት ባሕርይ ጋር ያነጻጽር ይሆናል። (ኤፌሶን 4:22-24) “ገርና ጭምት” መሆኗ እንደሚያስደስተውና እንደሚማርከው ምንም ጥርጥር የለውም። እንዲህ ዓይነቱ ባሕርይ ባሏን የሚያስደስት ከመሆኑም በተጨማሪ “በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ” ነው።—ቈላስይስ 3:12

17. ሣራ ለክርስቲያን ሚስቶች ግሩም ምሳሌ የሆነችው እንዴት ነው?

17 ሣራ ባሎቻቸው አማኝም ሆኑ አልሆኑ ለክርስቲያን ሚስቶች ምሳሌ ተደርጋ የተጠቀሰች ሴት ናት። ሣራ ምንም ሳታንገራግር አብርሃም ራሷ መሆኑን ተቀብላለች። በልቧ እንኳ ሳይቀር ‘ጌታዬ’ ብላ ጠርታዋለች። (ዘፍጥረት 18:12) ይህ ግን ክብሯን አልቀነሰባትም። በይሖዋ ላይ ጽኑ እምነት የነበራት በመንፈሳዊ ጠንካራ ሴት እንደሆነች ግልጽ ነው። በእርግጥም ‘በፊታችን ያለውን ሩጫ በጽናት እንድንሮጥ’ ሊያነሳሱን ከሚችሉ ‘እንደ ደመና ካሉ ብዙ ምስክሮች’ መካከል አንዷ ናት። (ዕብራውያን 11:11፤ 12:1) አንዲት ክርስቲያን ሚስት የሣራን አርዓያ መከተሏ ክብሯን አይቀንስባትም።

18. በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤተሰብ ውስጥ የትኞቹን መሠረታዊ ሥርዓቶች ማክበር ያስፈልጋል?

18 የትዳር ጓደኛሞች የተለያየ ሃይማኖት በሚከተሉበት ቤተሰብ ውስጥ የባል ራስነት እንደተጠበቀ ነው። ባልየው አማኝ ከሆነ ከራሱ እምነት ጋር በተያያዘ አቋሙን የማያላላ ቢሆንም እንኳ የሚስቱን እምነት ያከብርላታል። አማኝ የሆነችው ሚስቲቱ ከሆነች እርሷም ሃይማኖታዊ አቋሟን ማላላት አይኖርባትም። (የሐዋርያት ሥራ 5:29) በሌላ በኩል ደግሞ የባልዋን የራስነት ሥልጣን አትጋፋም። ሥልጣኑን የምታከብርለት ከመሆኑም ሌላ ‘በጋብቻ ሕግ’ ሥር ትኖራለች።—ሮሜ 7:2

መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ጥበብ ያዘለ መመሪያ

19. በትዳር ላይ ውጥረት የሚፈጥሩ አንዳንድ ጫናዎች ምንድን ናቸው? ይሁንና እነዚህን ጫናዎች እንዴት መቋቋም ይቻላል?

19 በዛሬው ጊዜ በትዳር ላይ ውጥረት ሊያስከትሉ የሚችሉ ብዙ ነገሮች አሉ። አንዳንድ ወንዶች ኃላፊነቶቻቸውን በአግባቡ ሳይወጡ ይቀራሉ። አንዳንድ ሴቶች የባላቸውን ራስነት ለመቀበል አሻፈረኝ ይላሉ። በአንዳንድ ትዳሮች ውስጥ አንደኛው ወገን በሌላው ግፍ ይፈጸምበታል። ለክርስቲያኖች ደግሞ የኢኮኖሚ ችግር፣ አለፍጽምና እንዲሁም የሥነ ምግባር ብልግና የተንሰራፋበትና ውሉ የጠፋበት ይህ ዓለም የሚያንጸባርቀው መንፈስ ታማኝነታቸውን ሊፈታተን ይችላል። ሆኖም የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች የሚከተሉ ወንዶችና ሴቶች ያሉበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን የይሖዋን በረከት ያገኛሉ። በትዳር ውስጥ ቢያንስ አንዱ እንኳ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ቢከተል ሁኔታውን የተሻለ ያደርገዋል። ከዚህ በተጨማሪ ይሖዋ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ሥር ሆነውም የትዳር ቃለ መሐላቸውን በታማኝነት ለመጠበቅ የሚጥሩ አገልጋዮቹን ይወዳቸዋል እንዲሁም ይደግፋቸዋል። ያሳዩትን ታማኝነት ፈጽሞ አይረሳም።—መዝሙር 18:25፤ ዕብራውያን 6:10፤ 1 ጴጥሮስ 3:12

20. ጴጥሮስ ለሁሉም ክርስቲያኖች የሰጠው ምክር ምንድን ነው?

20 ሐዋርያው ጴጥሮስ ላገቡ ወንዶችና ሴቶች የሰጠውን ምክር የደመደመው የማበረታቻ ቃላት በመናገር ነው። “በመጨረሻም ሁላችሁ በአንድ ሐሳብ ተስማሙ፤ እርስ በርሳችሁ ተሳሰቡ፤ እንደ ወንድማማቾች ተዋደዱ፤ ርኅሩኆችና ትሑታን ሁኑ። ክፉን በክፉ ወይም ስድብን በስድብ ፈንታ አትመልሱ፤ በዚህ ፈንታ ባርኩ፤ ምክንያቱም እናንተ የተጠራችሁት እንደነዚህ ያሉትን ነገሮች እያደረጋችሁ በረከትን ለመውረስ ነው” ብሏል። (1 ጴጥሮስ 3:8, 9) ይህ በእርግጥም ለሁላችንም በተለይ ደግሞ ላገቡ ሰዎች ጥበብ ያዘለ ምክር ነው!

ታስታውሳለህ?

• ክርስቲያን ባሎች ኢየሱስን መምሰል የሚችሉት እንዴት ነው?

• ክርስቲያን ሚስቶች ጉባኤውን መምሰል የሚችሉት እንዴት ነው?

• ባሎች ሚስቶቻቸውን ማክበር የሚችሉት እንዴት ነው?

• ባሏ አማኝ ያልሆነ አንዲት ክርስቲያን ሚስት ልታደርገው የምትችለው ከሁሉ የተሻለ ነገር ምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ክርስቲያን ባል ሚስቱን ያፈቅራል እንዲሁም ይንከባከባል

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ክርስቲያን ሚስት ባሏን በአክብሮትና በአድናቆት ትመለከታለች

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከሮማውያን ሕግ በተለየ የክርስትና ትምህርት ባል ሚስቱን እንዲያከብር ያዝዛል

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

‘የእጅግ ብዙ ሕዝብ’ ክፍል የሆኑ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች በገነት ውስጥ ለዘላለም ለመኖር ተስፋ ያደርጋሉ

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሣራ አብርሃምን እንደ ጌታዋ ቆጥራዋለች