በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሐዋርያው ጴጥሮስ ለአንተ የላከው መልእክት

ሐዋርያው ጴጥሮስ ለአንተ የላከው መልእክት

ሐዋርያው ጴጥሮስ ለአንተ የላከው መልእክት

በዘመናችን የክርስትና ሕይወት ቀላል አይደለም። በርካታ ተጽዕኖዎች ያጋጥሙናል። በአንዳንድ አገሮች መንግሥታት ከክርስቲያናዊ ሕሊናችን ጋር የሚቃረኑ ድርጊቶችን እንድንፈጽም ሊያስገድዱን ይሞክራሉ። ከማያምኑ ባሎች ጋር የሚኖሩ ብዙ ክርስቲያን ሚስቶችም አሉ። የዚህ ዓለም “ጥበብና” የሚያብለጨልጩ ነገሮች የወጣቶችን ልብ ይማርካሉ። አንዳንዶች ደግሞ ለብዙ አሥርተ ዓመታት በትዕግሥት ሲጠባበቁ ከቆዩ በኋላ ‘አርማጌዶን ይመጣ ይሆን?’ የሚል ጥርጣሬ ሊያድርባቸው ይችላል።

እንደነዚህ ያሉ ችግሮች የማያጋጥሙት ክርስቲያን የለም ለማለት ይቻላል። አንተም እንዲህ ያሉ ችግሮች ካጋጠሙህ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት ከሐዋርያው ጴጥሮስ የተላኩ ሁለት ደብዳቤዎች ለአንተ በቀጥታ እንደተጻፉ ያህል ሊሆኑልህ ይችላሉ። ጴጥሮስ ደብዳቤውን የጻፈው ኢየሱስ ከሞተ ከ30 ብዙም ከማይበልጡ ዓመታት በኋላ ለነበሩት ጉባኤዎች ነበር። ይሁን እንጂ ክርስቲያኖችን በዚያን ጊዜ ያጋጥሟቸው የነበሩት ችግሮች አሁንም አሉ። የጴጥሮስ ምክር በዚያን ጊዜ ጠቃሚ የነበረውን ያህል አሁንም የሚሠራ ሲሆን ጴጥሮስም ቢሆን እንዲህ ዓይነቱን ምክር ለመስጠት የሚያስችል ብቃት ነበረው።

ብቃት ያለው እረኛ

የወንጌል ዘገባዎችንና የሐዋርያት ሥራን መጽሐፍ በማንበብ የገሊላ ሰው ስለነበረውና ከጊዜ በኋላ ሐዋርያው ጴጥሮስ ስለተባለው ዓሣ አጥማጅ ብዙ ማወቅ እንችላለን። ጴጥሮስ በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅ የሚያደርገው ሰብዓዊ ባሕርያቱ ጎልተው የሚታዩ መሆናቸው ነው። ለኢየሱስ የነበረው ታማኝነት ፈጽሞ የማያጠራጥር ቢሆንም ችኩል በመሆኑ አንዳንድ ጊዜ ስህተት ይሠራ ነበር። ምናልባትም ጴጥሮስ የፈጸማቸውን ስህተቶች ስንመለከት ከራሳችን ባሕርይ ጋር የሚመሳሰሉ ነገሮችን ማግኘት እንችላለን።

ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ በውኃ ላይ ሲራመድ ሲመለከት የተሰማውን ስሜት አስታውስ። በጣም ከመደነቁ የተነሳ እርሱም እንደዚያ ለማድረግ ፈልጎ ነበር። ይሁን እንጂ በውኃ ላይ መሄድ ከጀመረ በኋላ ፍርሃት ስለገባው እንዳይሰምጥ የኢየሱስ እርዳታ አስፈልጎት ነበር። እንዲሁም እርሱ ፈጽሞ እንደማይሰናከል በግትርነት የተናገረበትን ጊዜ አስታውስ። ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ግን ኢየሱስን ሦስት ጊዜ ክዶታል።—ማቴዎስ 14:23-34፤ 26:33, 34, 69-75

ይሁን እንጂ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሚገኙትን ሁለት ደብዳቤዎች የጻፈው ጴጥሮስ፣ ኢየሱስ “አንተ ሰይጣን፣ ሂድ ከዚህ! . . . መሰናክል ሆነህብኛል!” በማለት ከገሠጸው ወዲህ በጣም ተለውጧል። (ማቴዎስ 16:23) ኢየሱስ “በጎቼን መግብ” በማለት ያዘዘው እርሱን ነበር። (ዮሐንስ 21:17) ጴጥሮስ ለሠላሳ ዓመታት ‘በጎቹን በመመገብ’ ያካበተው ተሞክሮ በእጅጉ እንደለወጠው ከደብዳቤዎቹ መረዳት ይቻላል።

በመሆኑም “እርስ በርሳችሁም አጥብቃችሁ ከልብ ተዋደዱ” በማለት የጻፈውን ምክር ስናነብ በአንድ ወቅት እሱ ራሱ “ወንድሜ ቢበድለኝ ስንት ጊዜ ይቅር ልበለው? እስከ ሰባት ጊዜ ነውን?” በማለት ለኢየሱስ ያቀረበው ጥያቄ ወደ አእምሯችን ይመጣ ይሆናል። ጴጥሮስ ደብዳቤውን በጻፈበት ወቅት ክርስቲያኖች አንዳቸው ለሌላው ያላቸው ፍቅር ገደብ ሊኖረው እንደማይገባ ተገንዝቦ ነበር። (1 ጴጥሮስ 1:22፤ ማቴዎስ 18:21) እንዲሁም “መጸለይ እንድትችሉ ንቁ አእምሮ ይኑራችሁ” በማለት ለእምነት ባልንጀሮቹ የሰጠውን ማሳሰቢያ ስንመለከት በጌቴሴማኒ የአትክልት ስፍራ ውስጥ ኢየሱስ እንዲጸልዩ ነግሯቸው እነርሱ ግን በመተኛታቸው ከተፈጠረው ሁኔታ ትልቅ ትምህርት ማግኘቱን እንገነዘባለን።—1 ጴጥሮስ 4:7፤ ሉቃስ 22:39-46

አዎን፣ የገሊላው ዓሣ አጥማጅ በዚህ ወቅት የተዋጣለት እረኛ ሆኖ ነበር። በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት የጻፈው የእረኝነት ምክር በጊዜው ጠቃሚ እንደነበረ ሁሉ በዘመናችንም ይሠራል። እስቲ ከምክሮቹ መካከል አንዳንዶቹን እንመልከት።

ለእውነት አድናቆት ይኑራችሁ

በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው የአይሁዳውያንና የሮማውያን ኅብረተሰብ በብልጭልጭ ነገሮች የተሞላ ከመሆኑም በላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ቀላል አልነበረም። በጊዜው የነበሩት ክርስቲያኖች ዓለም በሚያቀርባቸው የሚስቡ ነገሮች ተማርከው ወይም በተጽዕኖዎቹ ተሸንፈው ከእውነት ጎዳና ላለመውጣት መጠንቀቅ ነበረባቸው። በመሆኑም ጴጥሮስ ማሳሰቢያውን የጀመረው “ልባችሁን አዘጋጁ፤ ራሳችሁንም ግዙ” በማለት ነበር። (1 ጴጥሮስ 1:13) እንዲህ ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው? ለመንፈሳዊ መብቶቻችን ያለን አድናቆት ምንጊዜም እንዳይጠፋ በመጠንቀቅ ነው።

ጴጥሮስ የጥንት ነቢያትና መላእክት እንኳን ሳይቀሩ አምላክ ለክርስቲያኖች የገለጠላቸውን ነገሮች ለማወቅ ይጓጉ እንደነበር አስታወሳቸው። በኢየሱስ ክርስቶስ ደም በመዋጀታቸው፣ በእግዚአብሔር ቃል አማካይነት ከማይጠፋ ዘር በመወለዳቸውና ‘የተመረጠ ትውልድ፣ የንጉሥ ካህናት፣ ቅዱስ ሕዝብና እግዚአብሔር ለራሱ የለያቸው ሕዝብ’ በመሆናቸው ምንኛ እንደተባረኩ ነገራቸው። (1 ጴጥሮስ 2:9) እንዲሁም ማንነታቸውን ማለትም ፈሪሃ አምላክ በሌለው ዓለም ውስጥ የሚኖሩ መጻተኞችና የይሖዋ አምላክን ታላቅ ምሕረት የቀመሱ ሰዎች መሆናቸውን መዘንጋት አይኖርባቸውም።

በዚያን ጊዜ የነበረው ዓለም ታሪክ ብቻ ሆኖ ቀርቷል። ይሁን እንጂ አሁንም የምንኖረው በፈተናዎች ሊያጠምደን ወይም በተጽዕኖዎች ሊያሸንፈን በሚሞክር ፈሪሃ አምላክ የሌለው ዓለም ውስጥ ነው። የጴጥሮስ ምክር ዛሬም ይሠራል። ያለንን ልዩ መብት ምንጊዜም መዘንጋት አይኖርብንም። በጊዜያችን ያለው በጥርጣሬ የተሞላና ለሃይማኖት ግዴለሽነት የተስፋፋበት ዓለም ለሚያሳድርብን ተጽዕኖ ተሸንፈን እጅ ሳንሰጥ ‘በድነታችን እንድናድግ፣ አዲስ እንደ ተወለዱ ሕፃናት ንጹሑን መንፈሳዊ ወተት መመኘት’ ይኖርብናል።—1 ጴጥሮስ 2:2

ችግሮች ቢኖሩም ደስተኛ መሆን

ፈሪሃ አምላክ በሌለው ዓለም ውስጥ መኖር በጴጥሮስ ዘመን አስቸጋሪ እንደነበረ ሁሉ በጊዜያችንም አብዛኛውን ጊዜ ችግሮች አሉት። ጴጥሮስ ሦስት ሁኔታዎችን የጠቀሰ ሲሆን እነዚህም (1) አንድ ክርስቲያን ለመንግሥት ያለበት ግዴታ፣ (2) አንድ ክርስቲያን ባሪያ ከጌታው ጋር የሚኖረው ግንኙነትና (3) አንዲት ክርስቲያን ሚስት ለራስነት ሥልጣን በመገዛት የማያምን ባሏን መርዳት የምትችልበት ሁኔታ ናቸው።

በዚያን ዘመን እነዚህ ነጥቦች የሕይወትና የሞት ጉዳይ ነበሩ። አብዛኛውን ጊዜ ገዢዎች ሮማዊ ያልሆኑ ሰዎችን የማሠቃየት ብሎም የመግደል ሥልጣን ነበራቸው። ባሪያዎችም ጌቶቻቸው በጭካኔ ቢያንገላቷቸው አቤት የሚሉበት አልነበራቸውም። ሚስቶች ደግሞ የባሎቻቸው ንብረት እንደሆኑ ተደርገው የሚታዩ ሲሆን የነበሯቸው መብቶችም ውስን ነበሩ።

ምንም እንኳን በጊዜያችን ሁኔታው ጥንት እንደነበረው የባሪያና የጌታ ግንኙነት የከፋ ባይሆንም ክርስቲያኖች “ከቄሳር” ወይም ከአሠሪዎቻቸው ጋር ባላቸው ግንኙነት ረገድ ችግሮች ያጋጥሟቸዋል። የማያምኑ ባሎች ያሏቸው በርካታ ክርስቲያን ሴቶችም ከባባድ ችግሮች አሉባቸው። በመሆኑም ሐዋርያው ጴጥሮስ የሰጠው የሚከተለው ምክር ለጊዜያችን በጣም ጠቃሚ ነው። ምን ብሎ ነበር?

በአጭሩ ሦስት ነገሮችን እንድናስታውስ መክሮናል። በመጀመሪያ ለሥልጣን መገዛትን በሚመለከት ተገቢ አመለካከት ሊኖረን ይገባል። ሁሉም ሰው ለባለ ሥልጣናት መገዛት አለበት፤ ሠራተኞች ለቀጣሪዎቻቸው መታዘዝ ይኖርባቸዋል እንዲሁም ሚስቶች ባሎቻቸውን ማክበርና መታዘዝ አለባቸው። እንዲህ የምናደርግ ከሆነ አማኝ ያልሆኑ ሰዎች ምግባራችንን በመመልከት ክርስትና ከሁሉ የተሻለ የሕይወት ጎዳና መሆኑን ይገነዘባሉ። (1 ጴጥሮስ 3:1፤ 4:15) በመጨረሻም በይሖዋ ዘንድ በጎ ሕሊና ሊኖረን የሚገባ ሲሆን አንዳንድ ነገሮችን የምናደርግበትን ምክንያት በየዋህነት ለማስረዳት ምንጊዜም ዝግጁዎች መሆን አለብን።—1 ጴጥሮስ 3:15, 16

ይሁን እንጂ ይህ ለችግሮቻችን ሁሉ መፍትሔ ያስገኛል ማለት ነው? ጴጥሮስ እንደዚያ እንዳልሆነ ያውቅ ነበር። የምንኖርበት ዓለም አንድ ክርስቲያን ሕሊናው የማይፈቅድለትን ነገር እንዲያደርግ የሚያስገድድበት ጊዜ ይኖራል። በመሆኑም ለጽድቅ ስንል መሰደድ ይኖርብን ይሆናል። ቢሆንም ጴጥሮስ “ስለ እግዚአብሔር ሲል የግፍ መከራን የሚቀበል ሰው ምስጋናን ያገኛል” ይላል።—1 ጴጥሮስ 2:19

እንዲያውም ከትክክለኛው አቅጣጫ ከተመለከትነው ለጽድቅ ሲባል መሰደድ ደስታ ያመጣል። ጴጥሮስ ይህን ከራሱ ተሞክሮ ያውቅ ነበር። ከብዙ ዓመታት በፊት ለእምነቱ ሲል ተገርፎ ነበር። እርሱና አብረውት የታሠሩት ከእስር ሲለቀቁ “ስለ ስሙ ውርደትን ለመቀበል በመብቃታቸው ደስ እያላቸው . . . ወጥተው ሄዱ።” (የሐዋርያት ሥራ 5:41) በመሆኑም ስደት ለሚደርስባቸው ክርስቲያኖች “የክርስቶስ መከራ ተካፋዮች በመሆናችሁ ደስ ይበላችሁ” በማለት ጽፎላቸዋል።—1 ጴጥሮስ 4:12, 13

ጴጥሮስ ለወንድሞች ከይሖዋ ሥልጠና እያገኙ እንደሆነ ነግሯቸዋል። “ስለዚህ . . . ከእግዚአብሔር ብርቱ እጅ በታች ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ” አላቸው። እርስ በርስ እንዲዋደዱ የመከራቸው ሲሆን ጉባኤውን የሚንከባከቡት ሽማግሌዎች ሊኖራቸው ስለሚገባው ትክክለኛ ዝንባሌም ነግሯቸዋል። በቅርቡ ‘የጸጋ ሁሉ አምላክ ራሱ መልሶ እንደሚያበረታቸው፤ አጽንቶም እንደሚያቆማቸው’ ተስፋ ሰጥቷቸዋል።—1 ጴጥሮስ 5:1-3, 6, 10

ይህ ምክር በጊዜው ወቅታዊ የነበረውን ያህል በዘመናችንም የሚሠራ አይደለም? ጴጥሮስ በቀጥታ ለአንተ እየተናገረ እንዳለ አልተሰማህም? በጴጥሮስ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች ይህን ደብዳቤ ሲያነብቡ ምን ያህል እንደተበረታቱ አስበው። ይሁን እንጂ በዕድሜ የገፋው ሐዋርያ በወንድሞቹ ላይ ስለተደቀነባቸው አሳሳቢ አደጋ ለማስጠንቀቅ ከዚህ ብዙም ሳይቆይ ሁለተኛ ደብዳቤ መጻፍ ነበረበት።

ከፊታቸው የሚጠብቃቸውን አደጋ መቋቋም

ጴጥሮስ የቀረው ዕድሜ በጣም ጥቂት በመሆኑ ለክርስቲያን ባልንጀሮቹ ማስጠንቀቂያ መጻፉ ለነገ የማይባል አጣዳፊ ጉዳይ እንደሆነ በሁለተኛ ደብዳቤው ላይ ተናግሯል። ክርስቲያኖች መንፈሳዊ ጥንካሬያቸውን ይዘው ለመቀጠል ሊያዳብሯቸው የሚገቡ ባሕርያትን የዘረዘረ ሲሆን መንፈሳዊነታቸውን ለማዳከም ከጉባኤው ውስጥ የሚነሱ ኃይሎች እንደሚኖሩ ተናግሯል።—2 ጴጥሮስ 1:5-8, 14, 16

ጴጥሮስ “በእናንተ መካከል ሐሰተኞች መምህራን ይነሣሉ” በማለት አስጠንቅቆ ነበር። (2 ጴጥሮስ 2:1, 2) እነዚህ ሐሰተኛ መምህራን የሥነ ምግባር ብልግናን የሚያስፋፉ ሲሆን “የፈጠራ ታሪኮችን” በማሰራጨት የተካኑ ይሆናሉ። ይሁን እንጂ አንድ ወሳኝ ነገር ይኸውም ‘ይሖዋ በእውነት እያመለኩት የሚኖሩትን ከፈተና እንዴት እንደሚያድናቸውና ዐመፀኞችን እየቀጣ ለፍርድ ቀን እንዴት ጠብቆ እንደሚያቆያቸው እንደሚያውቅ’ ይዘነጋሉ። (2 ጴጥሮስ 2:3, 9) እነዚህ ሰዎች ለአጭር ጊዜ ይሳካላቸው ይሆናል፤ ሆኖም ከፍርድ አያመልጡም።

ሌሎች ደግሞ “‘እመጣለሁ’ ያለው ታዲያ የት አለ? አባቶች ከሞቱበት ከፍጥረት መጀመሪያ አንሥቶ እስካሁን ድረስ ሁሉም ነገር እንዳለ ይኖራል” እያሉ ያፌዛሉ። እነዚህም ቢሆኑ የይሖዋ የጊዜ አቆጣጠር ከእኛ እንደሚለይና ታጋሽ አምላክ እንደሆነ ይዘነጋሉ። በኖኅ ዘመን መጨረሻው እንደመጣ ሁሉ የዚህ ሥርዓት መጨረሻም መምጣቱ አይቀርም።—2 ጴጥሮስ 3:4-10

በመጨረሻም፣ በጴጥሮስ ዘመን እንኳ በጉባኤው ውስጥ ያሉ አንዳንዶች ‘ቅዱሳት መጻሕፍትን ያጣምሙ’ እንደነበር ከደብዳቤው መረዳት ይቻላል። ይሁን እንጂ ይህ መጥፊያቸው ይሆናል።—2 ጴጥሮስ 3:16

ጴጥሮስ ከእነዚህ አደጋዎች አኳያ የወንድሞችን ‘ልቦና ማነቃቃት’ አስፈላጊ እንደሆነ ተሰምቶት ነበር። (2 ጴጥሮስ 3:1) ይሖዋ ክፉዎችን አጥፍቶ ጻድቃንን ማዳን እንደሚችል የሚያሳዩትን የተለያዩ ታሪካዊ ማስረጃዎች መርሳት የሌለባቸው ከመሆኑም በላይ ‘የእግዚአብሔርን ቀን መምጫ ሊያፋጥኑ ይገባል።’ (2 ጴጥሮስ 3:12) ይህ ቀን እውን ከመሆኑም በላይ እየቀረበ ነው። ይህን ማወቃቸው አሁን በሚያደርጓቸው ነገሮችም ሆነ በወደፊት እቅዶቻቸው ላይ ተጽዕኖ ማሳደር አለበት።—2 ጴጥሮስ 1:19-21

የምንኖረው መጨረሻው ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በቀረበበት ወቅት እንደመሆኑ “ያለ ነውርና ያለ ነቀፋ ከእርሱ ጋር በሰላም እንድትገኙ ትጉ” የሚለው የጴጥሮስ ማሳሰቢያ የበለጠ ኃይል ይኖረዋል። (2 ጴጥሮስ 3:14) አዎን፣ እነዚህ ቃላት በእኛም ላይ ይሠራሉ። ሐዋርያው ጴጥሮስ እነዚህን ቃላት የተናገረው ይሖዋ ቃል በገባው “አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር” ላይ ለመኖር ተስፋ ለሚያደርጉ ሰዎች ሁሉ ነው። በመሆኑም “ጸንታችሁ ከቆማችሁበት መሠረት በዐመፀኞች ስሕተት ተስባችሁ እንዳትወድቁ ተጠንቀቁ። ነገር ግን በጌታችንና በአዳኛችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ዕውቀት እደጉ” በማለት የሰጠው የመጨረሻ ማሳሰቢያ ከዘመናት በፊት እንደነበረው ሁሉ ዛሬም በሙሉ ኃይሉ ያስተጋባል።—2 ጴጥሮስ 3:13, 17, 18