በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በዘመናችን ትዳር የሰመረ ሊሆን ይችላል

በዘመናችን ትዳር የሰመረ ሊሆን ይችላል

በዘመናችን ትዳር የሰመረ ሊሆን ይችላል

“በፍጹም አንድነት የሚያስተሳስረውን ፍቅርን ልበሱት።”—ቈላስይስ 3:14

1, 2. (ሀ) በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ምን የሚያስደስት ሁኔታ ይታያል? (ለ) የተሳካ ትዳር የሚባለው ምን ዓይነት ነው?

 ክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ለ10, ለ20, ለ30 ወይም ከዚያ ለሚበልጡ ዓመታት ከትዳር ጓደኛቸው ጋር በታማኝነት የኖሩ ብዙ ባልና ሚስቶች መኖራቸውን ማወቁ አያስደስትም? እነዚህ ሰዎች በክፉውም በደጉም ጊዜ ከትዳር ጓደኛቸው ጋር በታማኝነት ጸንተዋል።—ዘፍጥረት 2:24

2 አብዛኞቹ በትዳራቸው ውስጥ ችግሮች ያጋጥሟቸው እንደነበረ አይሸሽጉም። በመስኩ ጥናት የሚያካሂዱ አንዲት ሴት እንዲህ ብለዋል:- “ደስታ የሰፈነበት ትዳር ችግር የለበትም ብለን ማሰብ አይኖርብንም። አስደሳችም ሆኑ አሳዛኝ ወቅቶች ያጋጥማሉ . . . ይሁንና . . . እነዚህ ሰዎች ኑሮ የሚያስከትለው [መከራ] እያለም በትዳር ዓለም አንድ ላይ መጽናት ችለዋል።” ትዳራቸው የሰመረላቸው ባልና ሚስቶች በተለይ ደግሞ ልጆች ያሳደጉ ከሆኑ ሕይወት በሚያስከትለው ጫና ሳቢያ የሚመጡ መከራዎችንና ችግሮችን እንዴት መወጣት እንደሚችሉ ከተሞክሮ ተምረዋል። እነዚህ ባልና ሚስቶች እውነተኛ ፍቅር ‘ከቶ እንደማይወድቅ’ በሕይወታቸው አይተዋል።—1 ቆሮንቶስ 13:8

3. በጋብቻና በፍቺ ዙሪያ የሚወጡ አኃዞች ምን ያሳያሉ? ይህስ የትኞቹን ጥያቄዎች ያስነሳል?

3 በአንጻሩ ደግሞ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ጋብቻዎች በአሳዛኝ ሁኔታ አክትመዋል። አንድ ሪፖርት እንዲህ ይላል:- “በዛሬው ጊዜ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ካሉት ጋብቻዎች መካከል ግማሽ የሚያህሉት በፍቺ እንደሚያከትሙ ይገመታል። ከእነዚህ [ፍቺዎች] መካከል ግማሽ የሚያህሉት የሚከሰቱት ጋብቻው ከተፈጸመበት ጊዜ አንስቶ እስከ 7.8 ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ነው . . . ለሁለተኛ ጊዜ ከሚያገቡት 75 በመቶ ከሚሆኑ ሰዎች መካከል 60 በመቶዎቹ በድጋሚ ይፋታሉ።” ሌላው ቀርቶ ከዚህ ቀደም አነስተኛ የፍቺ ቁጥር በነበራቸው አገሮች ውስጥ ያለው ሁኔታ እንኳ ተቀይሯል። ለምሳሌ ያህል፣ በጃፓን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የፍቺ ቁጥር በእጥፍ ጨምሯል። አንዳንድ ጊዜ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ሳይቀር እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ያጋጥማል። ታዲያ መንስኤ የሆኑት አንዳንድ ችግሮች ምንድን ናቸው? ሰይጣን የትዳርን መሠረት ለማናጋት ጥረት ቢያደርግም ትዳር የሰመረ እንዲሆን ምን ያስፈልጋል?

ልንርቃቸው የሚገቡ አደጋዎች

4. በትዳር ላይ ችግር ሊያስከትሉ የሚችሉ አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?

4 የአምላክ ቃል ለትዳር ፀር የሆኑ ነገሮችን እንድናስተውል ይረዳናል። ለምሳሌ ያህል፣ ሐዋርያው ጳውሎስ በመጨረሻው ዘመን የሚሆኑትን ነገሮች በተመለከተ ምን ብሎ እንደጻፈ ተመልከት:- “በመጨረሻው ዘመን የሚያስጨንቅ ጊዜ እንደሚመጣ ይህን ዕወቅ። ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉ፤ ገንዘብን የሚወዱ፣ ትምክሕተኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ ቅድስና የሌላቸው፣ ፍቅር የሌላቸው፣ ለዕርቅ የማይሸነፉ፣ ሐሜተኞች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ መልካም የሆነውን የማይወዱ፣ ከዳተኞች፣ ችኩሎች፣ በከንቱ በትዕቢት የተወጠሩ፣ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉና። ሃይማኖታዊ መልክ አላቸው፤ ኀይሉን ግን ክደዋል። ከእነዚህ ራቅ።”—2 ጢሞቴዎስ 3:1-5

5. ‘ራስ ወዳድ መሆን’ ለትዳር ፀር የሚሆነው ለምንድን ነው? በዚህ ረገድ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ምክር ይሰጣል?

5 ጳውሎስ የጠቀሳቸውን ጉዳዮች ልብ ብለን ካጤንናቸው ከዘረዘራቸው ነጥቦች መካከል አብዛኞቹ ትዳር እንዲፈርስ አስተዋጽኦ ሊያደርጉ የሚችሉ ነገሮች ናቸው። ለምሳሌ ያህል፣ “ራሳቸውን የሚወዱ” ሰዎች ራስ ወዳድ በመሆናቸው ለሌሎች አሳቢነት አያሳዩም። ራሳቸውን ብቻ የሚወዱ ባሎች ወይም ሚስቶች በመሰላቸው መንገድ ከመሄድ ወደኋላ አይሉም። ግትርና እኔ ያልኩት ካልሆነ ብለው ድርቅ የሚሉ ናቸው። እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ደስታ የሰፈነበት ትዳር ሊያስገኝ ይችላል? በፍጹም። ሐዋርያው ጳውሎስ ባለ ትዳሮችን ጨምሮ ክርስቲያኖችን እንዲህ ሲል በጥበብ መክሯል:- “ሌሎች ከእናንተ እንደሚሻሉ በትሕትና ቊጠሩ እንጂ፣ በራስ ወዳድነት ምኞት ወይም ከንቱ ውዳሴ ለማግኘት አንዳች አታድርጉ። እያንዳንዳችሁ ሌሎችን የሚጠቅመውንም እንጂ፣ ራሳችሁን የሚጠቅመውን ብቻ አትመልከቱ።”—ፊልጵስዩስ 2:3, 4

6. የገንዘብ ፍቅር የጋብቻ ዝምድናን ሊያዳክም የሚችለው እንዴት ነው?

6 የገንዘብ ፍቅር ባልና ሚስትን ሊያራርቅ ይችላል። ጳውሎስ እንዲህ ሲል አስጠንቅቋል:- “ባለጠጋ ለመሆን የሚፈልጉ ግን ወደ ፈተናና ወደ ወጥመድ፣ እንዲሁም ሰዎችን ወደ መፍረስና ወደ ጥፋት ወደሚያዘቅጠው ወደ ብዙ ከንቱና ክፉ ምኞት ይወድቃሉ። ምክንያቱም የገንዘብ ፍቅር የክፋት ሁሉ ሥር ነው፤ አንዳንዶች ባለጠጋ ለመሆን ካላቸው ጒጒት የተነሣ ከእምነት መንገድ ስተው ሄደዋል፤ ራሳቸውንም በብዙ ሥቃይ ወግተዋል።” (1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10) ጳውሎስ የተናገረው ነገር በዛሬው ጊዜ በብዙ ትዳሮች ላይ የደረሰ መሆኑ በጣም ያሳዝናል። ብዙ ባልና ሚስቶች ሀብት ሲያሳድዱ የትዳር ጓደኛቸውን ፍላጎት ችላ ያሉ ሲሆን ይህም መሠረታዊ የሆነ ስሜታዊ ድጋፍ አለመስጠትንና ዘወትር የጠበቀ ወዳጅነት አለማሳየትን ይጨምራል።

7. አንዳንዶች ለትዳር ጓደኛቸው ታማኝ እንዳይሆኑ ያደረጋቸው ምንድን ነው?

7 በተጨማሪም ጳውሎስ በዚህ የመጨረሻ ዘመን አንዳንዶች “ቅድስና የሌላቸው [“ታማኝነት የጎደላቸው፣” NW]፣ ፍቅር የሌላቸው፣ ለዕርቅ የማይሸነፉ” እንደሚሆኑ ተናግሯል። የጋብቻ መሐላ ዘላቂ አንድነት ማስገኘት ያለበት ትልቅ ትርጉም ያዘለ ቃል ኪዳን ስለሆነ በመካካድ መፍረስ የለበትም። (ሚልክያስ 2:14-16) ሆኖም አንዳንዶች የትዳር ጓደኛቸው ላልሆነ ሰው የፍቅር ስሜት ያሳያሉ። በ30ዎቹ ዕድሜ ክልል ውስጥ የምትገኝ ባሏ ጥሏት የሄደ አንዲት ሚስት ትቷት ከመሄዱ በፊት እንኳ ከሌሎች ሴቶች ጋር በጣም ይቀራረብ እንደነበረና ለእነርሱ የፍቅር ስሜት ያሳይ እንደነበር ተናግራለች። አድራጎቱ ባለ ትዳር ከሆነ ሰው የማይጠበቅ እንደሆነ መገንዘብ አልቻለም። ባለቤቱ ይህን ሁኔታ ስታይ በጣም የተጎዳች ከመሆኑም ሌላ አዝማሚያው አደገኛ እንደሆነ በዘዴ ልታስጠነቅቀው ሞከረች። ይሁን እንጂ ምንዝር ከመፈጸም አልተመለሰም። በደል የፈጸመው ወገን ደግነት የተሞላበት ማስጠንቀቂያ የተሰጠው ቢሆንም እንኳ ለጉዳዩ ትኩረት ለመስጠት አሻፈረኝ አለ። ይባስ ብሎም ዓይኑን ጨፍኖ ወጥመድ ውስጥ ገባ።—ምሳሌ 6:27-29

8. ምንዝር ወደመፈጸም የሚያደርሰው ምንድን ነው?

8 መጽሐፍ ቅዱስ ምንዝርን በተመለከተ የሚሰጠው ማስጠንቀቂያ በጣም ግልጽ ነው! “የሚያመነዝር ሰው ግን ማመዛዘን ይጐድለዋል፤ እንዲህ የሚያደርግ ሁሉ ራሱን ያጠፋል።” (ምሳሌ 6:32) አብዛኛውን ጊዜ ምንዝር እንዲያው በድንገት የሚፈጸም ነገር አይደለም። የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ያዕቆብ እንደጠቀሰው አንድ ሰው እንደ ምንዝር ያለ ኃጢአት የሚፈጽመው ጉዳዩን ወደ አእምሮው በማምጣት መልሶ መላልሶ ሲያስብበት ከቆየ በኋላ ነው። (ያዕቆብ 1:14, 15) በደሉን የሚፈጽመው ወገን፣ ከእርሱ ወይም ከእርሷ ጋር በሕይወት ዘመኔ ሁሉ በታማኝነት እኖራለሁ ብሎ ቃለ መሐላ ለገባለት ሰው ያለው ታማኝነት ቀስ በቀስ እየተዳከመ ይሄዳል። ኢየሱስ “‘አታመንዝር’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ሴትን በምኞት ዓይን የተመለከተ ሁሉ በልቡ ከእርሷ ጋር አመንዝሮአል” ሲል ተናግሯል።—ማቴዎስ 5:27, 28

9. ምሳሌ 5:18-20 ላይ ምን ጥበብ ያዘለ ምክር ይገኛል?

9 በምሳሌ መጽሐፍ ላይ ጥበብ ያለበትና ለታማኝነት የሚያበቃ አካሄድ ምን እንደሆነ ተገልጿል:- “ምንጭህ ቡሩክ ይሁን፤ በልጅነት ሚስትህም ደስ ይበልህ። እርሷ እንደ ተወደደች ዋላ፣ እንደ ተዋበች ሚዳቋ ናት፤ ጡቶቿ ዘወትር ያርኩህ፤ ፍቅሯም ሁልጊዜ ይማርክህ። ልጄ ሆይ፤ በአመንዝራ ሴት ፍቅር ለምን ትሰክራለህ? የሌላዪቱንስ ሴት ብብት ስለ ምን ታቅፋለህ?”—ምሳሌ 5:18-20

ለማግባት አትቸኩሉ

10. ልናገባው ያሰብነውን ሰው ለማወቅ ጊዜ መውሰድ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

10 አንድ ወንድና ሴት የተጋቡት በስሜት ተገፋፍተው ከሆነ በትዳራቸው ውስጥ ችግሮች ሊከሰቱ ይችላሉ። ባልና ሚስቱ በዕድሜ በጣም ለጋ ሊሆኑና ብስለት ሊጎድላቸው ይችላል። ወይም በቂ ጊዜ ወስደው የሚወዱትንና የሚጠሉትን ነገር፣ በሕይወታቸው ውስጥ ያሏቸውን ግቦች እንዲሁም የቤተሰብ ሕይወታቸውን ለማወቅ ጥረት አላደረጉ ይሆናል። ልታገቡት ያሰባችሁትን ሰው ለማወቅ በትዕግሥት የተወሰነ ጊዜ ማሳለፉ ጠቃሚ ነው። የይስሐቅ ልጅ የሆነውን የያዕቆብን ሁኔታ ተመልከት፤ ራሔልን እንዲድርለት ሲል አባቷን ሰባት ዓመት ማገልገል ነበረበት። ያዕቆብ በመልኳ ተማርኮ ሳይሆን ለእርሷ እውነተኛ ፍቅር ስለነበረው እንደዚያ ለማድረግ ፈቃደኛ ሆኗል።—ዘፍጥረት 29:20-30

11. (ሀ) በጋብቻ የተሳሰሩ ሰዎች ምን ልዩነቶች ሊኖሯቸው ይችላሉ? (ለ) በጋብቻ ውስጥ በአንደበት አጠቃቀም ረገድ ጠንቃቃ መሆን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

11 ትዳር እንዲያው በፆታ ፍቅር ላይ ብቻ የሚመሠረት ዝምድና አይደለም። ትዳር የተለያየ አስተዳደግና ባሕርይ፣ ስሜት እንዲሁም የትምህርት ደረጃ ያላቸው ሁለት ሰዎች የሚጣመሩበት ሕይወት ነው። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ሁለቱ ሰዎች በባሕልና በቋንቋ ሊለያዩ ይችላሉ። እነዚህ ልዩነቶች ባይኖሩ እንኳን በሌሎች ጉዳዮች ላይ የተለያየ አመለካከት ሊኖራቸው የሚችል ሁለት ሰዎች አንድ ላይ የሚጣመሩበት ዝግጅት ነው። የአመለካከት ልዩነት በጋብቻ ሕይወት ውስጥ መከሰቱ የማይቀር ነው። ባልና ሚስት ሐሳባቸውን የሚገልጹበት መንገድ ነቀፋና ቁጣ ያዘለ ወይም ደግሞ የሚያበረታታና የሚያንጽ ሊሆን ይችላል። በእርግጥም፣ የምንናገራቸው ቃላት የትዳር ጓደኛችንን ሊጎዱ ወይም ሊያስደስቱ ይችላሉ። እንዳመጣልን መናገር በትዳር ውስጥ ከባድ ውጥረት ሊያስከትል ይችላል።—ምሳሌ 12:18፤ 15:1, 2፤ 16:24፤ 21:9፤ 31:26

12, 13. ትዳርን በተመለከተ ሊኖረን የሚገባው ምክንያታዊ አመለካከት ምንድን ነው?

12 ስለዚህ የትዳር ጓደኛችን የሚሆነውን ሰው በቅርብ ለማወቅ በቂ ጊዜ መውሰዱ ጠቃሚ ነው። በትዳር ዓለም ብዙ ዓመት ያሳለፈች አንዲት እህት እንዲህ ብላለች:- “ለትዳር ያሰባችሁትን ሰው በአእምሯችሁ ይዛችሁ ግለሰቡ እንዲኖሩት የምትፈልጓቸውን አሥር የሚሆኑ አስፈላጊ ባሕርያት ለማሰብ ሞክሩ። ግለሰቡ ሰባቱን ብቻ የሚያሟላ ከሆነ ራሳችሁን እንዲህ ብላችሁ ጠይቁ፤ ‘የሚጎድሉትን ሦስት ባሕርያት ችላ ብዬ ለማለፍ ፈቃደኛ ነኝ? ጉድለቶቹን ነጋ ጠባ ችዬ መኖር እችላለሁ?’ ራሳችሁን ከተጠራጠራችሁ ጉዳዩን በሚገባ አጢኑት።” እርግጥ በዚህ ረገድ ሐቁን መቀበል ይኖርባችኋል። ማግባት የምትፈልጉ ከሆነ ፍጹም የሆነ የትዳር ጓደኛ አገኛለሁ ብላችሁ ተስፋ ማድረግ የለባችሁም። እናንተም ብትሆኑ ፍጹም የትዳር ጓደኛ ልትሆኑ እንደማትችሉ አስታውሱ።—ሉቃስ 6:41

13 ትዳር መሥዋዕትነት መክፈል ይጠይቃል። ጳውሎስ ይህን ጉዳይ ጎላ አድርጎ ገልጾታል:- “እኔስ ያለ ጭንቀት እንድትኖሩ እወዳለሁ። ያላገባ ሰው ጌታን ደስ ለማሰኘት ስለ ጌታ ነገር ያስባል፤ ያገባ ሰው ግን ሚስቱን ደስ ለማሰኘት የዚህን ዓለም ነገር ያስባል፤ በዚህም ልቡ ተከፍሎአል። ያላገባች ሴት ወይም ድንግል ስለ ጌታ ነገር ታስባለች፤ ዓላማዋም በሥጋና በመንፈስ ለጌታ መቀደስ ነው። ያገባች ሴት ግን ባሏን ደስ ለማሰኘት የዚህን ዓለም ነገር ታስባለች።”—1 ቆሮንቶስ 7:32-34

አንዳንድ ትዳሮች የሚፈርሱት ለምንድን ነው?

14, 15. የጋብቻ ሰንሰለት እንዲዳከም የሚያደርጉ አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?

14 በቅርቡ አንዲት እህት በትዳር ዓለም ለ12 ዓመታት ከቆየች በኋላ ባሏ ጥሏት ሄዶ ከሌላ ሴት ጋር ግንኙነት በመሠረተ ጊዜ ፍቺ የሚያስከትለው ሐዘን ደረሰባት። ከመፋታታቸው በፊት አዝማሚያውን አስተውላ ነበር? እንዲህ ትላለች:- “ከተወሰነ ጊዜ ወዲህ መጸለይ አቁሞ ነበር። በሰበብ በአስባቡ ከጉባኤ ስብሰባና ከአገልግሎት ይቀራል። ከእኔ ጋር ጊዜ ላለማሳለፍ ሲል ሥራ እንደበዛበት ወይም በጣም እንደደከመው ይናገራል። ፈጽሞ አያናግረኝም። መንፈሳዊ ነገሮች መነጋገር አቆምን። እንዲህ ተለውጦ ማየት በጣም የሚያሳዝን ነበር። ጭራሽ የማላውቀው ሰው ሆነብኝ።”

15 ሌሎች ክርስቲያኖችም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ጸሎት ወይም የጉባኤ ስብሰባዎችን ችላ ማለትን ጨምሮ ተመሳሳይ አዝማሚያዎችን ማየታቸውን ተናግረዋል። በሌላ አባባል ውሎ አድሮ የትዳር ጓደኛቸውን ትተው የሄዱ አብዛኞቹ ግለሰቦች ከይሖዋ ጋር ያላቸው ዝምድና እንዲዳከም ፈቅደዋል። ከዚህም የተነሳ መንፈሳዊ እይታቸው ይዳከማል። ይሖዋ ሕያው አምላክ ሆኖ አይታያቸውም። ጽድቅ የሰፈነበት አዲስ ዓለም እንደሚመጣ የተነገረው ተስፋ እውን ሆኖ መታየቱ ያከትማል። እንዲህ ያለው መንፈሳዊ ድክመት የትዳር ጓደኛውን የከዳው ግለሰብ ከጋብቻ ውጪ ግንኙነት ከመመሥረቱ በፊት እንኳ የተከሰተባቸው ወቅቶች አሉ።—ዕብራውያን 10:38, 39፤ 11:6፤ 2 ጴጥሮስ 3:13, 14

16. ለጠንካራ ትዳር አስተዋጽኦ የሚያደርገው ምንድን ነው?

16 በአንጻሩ ደግሞ በጣም ደስተኛ የሆኑ አንድ ባልና ሚስት ትዳራቸው ሊሰምር የቻለው መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችን በጋራ ስለሚያከናውኑ እንደሆነ ተናግረዋል። አብረው ይጸልያሉ እንዲሁም አብረው ያጠናሉ። ባልየው “መጽሐፍ ቅዱስን አብረን እናነባለን። አገልግሎት አብረን እንወጣለን። ሌሎች ነገሮችም አብረን እናደርጋለን” ሲል ተናግሯል። መልእክቱ ግልጽ ነው:- ከይሖዋ ጋር ጥሩ ዝምድና መመሥረት ባልና ሚስት አንድነት እንዲኖራቸው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል።

እውነታውን አትሽሹ እንዲሁም ተነጋገሩ

17. (ሀ) ለተሳካ ትዳር አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ሁለት ነገሮች ምንድን ናቸው? (ለ) ጳውሎስ ክርስቲያናዊ ፍቅርን የገለጸው እንዴት ነው?

17 ለተሳካ ትዳር አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ሌሎች ሁለት ነገሮች አሉ፤ እነርሱም ክርስቲያናዊ ፍቅርና መነጋገር ናቸው። አንድ ወንድና አንዲት ሴት አንዳቸው ከሌላው ጋር ፍቅር ከያዛቸው አንዱ የሌላውን ጉድለት ችላ ብሎ የማለፍ ዝንባሌ ይኖራቸዋል። እነዚህ ሰዎች ወደ ትዳር ዓለም የገቡት ምናልባትም በፍቅር ልብ ወለድ መጽሐፍ ላይ ያነበቡት ወይም በፊልም ያዩት ነገር ያሳደረባቸውን የተጋነነ አመለካከት ይዘው ይሆናል። ውሎ አድሮ ግን ባልና ሚስቱ ሐቁን ለመጋፈጥ ይገደዳሉ። ከዚያም ጥቃቅን ጉድለቶች ወይም ደስ የማይሉ ልማዶች ጉልህ ችግሮች ሊሆኑ ይችላሉ። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ከተፈጠረ ክርስቲያኖች ፍቅርን ጨምሮ የመንፈስ ፍሬዎችን ማፍራት ይኖርባቸዋል። (ገላትያ 5:22, 23) በእርግጥም ፍቅር ይኸውም በፆታ ላይ የተመሠረተ ሳይሆን ክርስቲያናዊ ፍቅር ከፍተኛ ኃይል አለው። ጳውሎስ ይህ ዓይነቱን ክርስቲያናዊ ፍቅር እንዲህ በማለት ገልጾታል:- “ፍቅር ታጋሽ ነው፤ ደግሞም ቸር ነው። . . . ራስ ወዳድ አይደለም፤ አይበሳጭም፤ በደልን አይቈጥርም። . . . ፍቅር ሁልጊዜ ይታገሣል፤ ሁልጊዜ ያምናል፤ ሁልጊዜ ተስፋ ያደርጋል፤ ሁልጊዜ ጸንቶ ይቆማል።” (1 ቆሮንቶስ 13:4-7) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው እውነተኛ ፍቅር ሰብዓዊ ድክመቶችን ግምት ውስጥ ያስገባል። ከሌሎች ፍጽምና አይጠብቅም።—ምሳሌ 10:12

18. መነጋገር ዝምድናን ሊያጠናክር የሚችለው እንዴት ነው?

18 ከዚህ በተጨማሪ መነጋገር በጣም አስፈላጊ ነገር ነው። በትዳር ዓለም ያሉ ሰዎች አንድ ላይ ያሳለፉት ዓመት ምንም ያህል ረጅም ቢሆን እርስ በርሳቸው መነጋገርና አንዳቸው ሌላውን ከልብ ማዳመጥ ይኖርባቸዋል። አንድ ባል “ስሜታችንን በግልጽ እንነጋገራለን፤ እንዲህ የምናደርገው ግን በፍቅር ነው” ሲል ተናግሯል። አንድ ባልና ሚስት ይበልጥ በተዋወቁ መጠን የትዳር ጓደኛቸው የሚናገረውን ማዳመጥ ብቻ ሳይሆን ስሜቱንም መረዳት ይችላሉ። በሌላ አባባል ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ደስተኛ ባልና ሚስት የትዳር ጓደኛቸውን ውስጣዊ ሐሳብና ስሜት መረዳት ይችላሉ። አንዳንድ ሚስቶች ባሎቻቸው በጥሞና እንደማያዳምጧቸው ተናግረዋል። አንዳንድ ባሎች ደግሞ ሚስቶቻቸው ሊያናግሯቸው የሚፈልጉት ፈጽሞ አመቺ ባልሆነ ሰዓት እንደሆነ ስሞታ ያሰማሉ። መነጋገር ርኅራኄና አሳቢነት ማሳየት ይጠይቃል። መግባባት የሰፈነበት ውይይት ለባልም ሆነ ለሚስት በጣም አስፈላጊ ነው።—ያዕቆብ 1:19

19. (ሀ) ይቅርታ መጠየቅ ከባድ ሊሆን የሚችለው ለምንድን ነው? (ለ) ይቅርታ እንድንጠይቅ የሚያነሳሳን ምንድን ነው?

19 በባልና ሚስት መካከል የሚደረግ ውይይት አንዳንድ ጊዜ ይቅርታ መጠየቅንም ይጨምራል። ይህ ደግሞ ከባድ የሚሆንበት ጊዜ አለ። ስህተትን አምኖ መቀበል ትሕትና ይጠይቃል። ይሁንና በትዳር ውስጥ ከፍተኛ ለውጥ ያመጣል! ከልብ ይቅርታ መጠየቅ ወደፊት ለግጭት መንስኤ የሚሆንን ነገር ለማስወገድ የሚያስችል ከመሆኑም ሌላ ከልብ ይቅር ለመባባልና ለችግሩ መፍትሄ ለማግኘት መንገድ ይጠርጋል። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “እርስ በርሳችሁ ተቻቻሉ፤ ከእናንተ አንዱ በሌላው ላይ ቅር የተሰኘበት ነገር ቢኖር ይቅር ተባባሉ፤ ጌታ ይቅር እንዳላችሁ እናንተም ሌላውን ይቅር በሉ። በእነዚህ ሁሉ ላይ ሁሉን በፍጹም አንድነት የሚያስተሳስረውን ፍቅርን ልበሱት።”—ቈላስይስ 3:13, 14

20. አንድ ክርስቲያን ለብቻቸውም ሆነ ከሌሎች ጋር በሚሆኑበት ጊዜ የትዳር ጓደኛውን እንዴት ሊይዝ ይገባል?

20 በተጨማሪም በትዳር ውስጥ አንዱ ሌላውን መደገፉ ወሳኝ ነው። አንድ ክርስቲያን ባልና ሚስት እርስ በርሳቸው መተማመንና መረዳዳት መቻል አለባቸው። አንደኛው የትዳር ጓደኛ ሌላኛው ወገን በእሱ ላይ ያለውን እምነት እንዲያጣ ወይም ጥርጣሬ እንዲያድርበት የሚያደርግ ነገር መፈጸም የለበትም። የትዳር ጓደኞቻችንን ከፍቅር ተነሳስተን ማመስገን ይኖርብናል እንጂ መንቀፍ የለብንም። (ምሳሌ 31:28ለ) ደግሞም በእነርሱ ላይ እያፌዝን ወይም እየቀለድን ክብራቸውን ከመንካት መቆጠብ ይኖርብናል። (ቈላስይስ 4:6) በየጊዜው የፍቅር ቃላት የሚለዋወጡ ከሆነ በመካከላቸው ያለው የመደጋገፍ መንፈስ እየተጠናከረ ይሄዳል። የትዳር ጓደኛን በፍቅር ስሜት መዳበስ ወይም የፍቅር ቃል መናገር “አሁንም እወድሃለሁ/ሻለሁ። አንተን/ቺን በማግኘቴ ደስተኛ ነኝ” የማለት ያህል ይሆናል። እነዚህ በጋብቻ ላይ ለውጥ ሊያመጡ ከሚችሉትና በዛሬው ጊዜ ትዳር የተሳካ እንዲሆን ከሚያደርጉት ነገሮች መካከል አንዳንዶቹ ናቸው። በዚህ ረገድ ሌሎች ነጥቦችም ያሉ ሲሆን የሚቀጥለው ርዕስ ጋብቻን የተሳካ ለማድረግ የሚያስችሉ ተጨማሪ ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያዎች ይዟል። a

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ተመልከት።

ልታብራራ ትችላለህ?

• ትዳርን ሊያናጉ የሚችሉ አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?

• ቸኩሎ ማግባት ጥሩ ያልሆነው ለምንድን ነው?

• መንፈሳዊነት በትዳር ላይ ምን ለውጥ ያመጣል?

• ትዳር ጠንካራ እንዲሆን የሚያስችሉት ነገሮች ምንድን ናቸው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ትዳር እንዲሁ በፆታ ፍቅር ላይ ብቻ የሚመሠረት ዝምድና አይደለም

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድ ባልና ሚስት ከይሖዋ ጋር ጠንካራ ዝምድና ካላቸው ትዳራቸው ሊሰምር ይችላል