በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በየጊዜው የሚያጋጥመንን ለውጥ ራቅ ባሉ አካባቢዎች ለመስበክ ተጠቅመንበታል

በየጊዜው የሚያጋጥመንን ለውጥ ራቅ ባሉ አካባቢዎች ለመስበክ ተጠቅመንበታል

የሕይወት ታሪክ

በየጊዜው የሚያጋጥመንን ለውጥ ራቅ ባሉ አካባቢዎች ለመስበክ ተጠቅመንበታል

ሪካርዶ ማሊክሲ እንደተናገረው

በክርስቲያናዊ የገለልተኝነት አቋሜ ምክንያት ሥራዬን ባጣሁ ጊዜ ከቤተሰቤ ጋር ሆነን የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ እቅድ በማውጣት ረገድ ይሖዋ እንዲረዳን ጸለይን። በጸሎታችን ላይ አገልግሎታችንን በሰፊው ማከናወን እንደምንፈልግ ጨምረን ጠቅሰን ነበር። ብዙም ሳይቆይ ከዘላኖች ኑሮ ጋር የሚመሳሰል ሕይወት መምራት የጀመርን ሲሆን ከዚያ በኋላ በነበሩት ጊዜያት በሁለት አሕጉሮች ወደሚገኙ ስምንት አገሮች ሄደናል። ይህም ምሥራቹን ከፊሊፒንስ ርቀው በሚገኙ ቦታዎች እንድንሰብክ አስችሎናል።

 የተወለድኩት በ1933 ፊሊፒንስ ውስጥ ሲሆን ቤተሰባችን የፊሊፒንስ ኢንዲፔንደንት ቤተ ክርስቲያን አባል ነበር። አሥራ አራቱም ቤተሰቦቼ የዚህ ቤተ ክርስቲያን ተከታዮች ነበሩ። የ12 ዓመት ልጅ ሳለሁ አምላክ ወደ እውነተኛው እምነት እንዲመራኝ እጸልይ ነበር። አንዱ አስተማሪዬ የሃይማኖት ትምህርት በሚሰጥበት ክፍል ውስጥ እንድማር መዘገበኝና ከዚያ በኋላ አጥባቂ ካቶሊክ ሆንኩ። ቅዳሜ ይከናወን የነበረው የኑዛዜ ፕሮግራምም ሆነ የእሁዱ ቅዳሴ አምልጦኝ አያውቅም ነበር። ይሁን እንጂ ውሎ አድሮ አንዳንድ ነገሮችን መጠራጠርና ቅር መሰኘት ጀመርኩ። ‘ሰዎች ከሞቱ በኋላ ምን ይሆናሉ’ የሚለው ጥያቄ እንዲሁም ‘ሲኦል የማቃጠያ ስፍራ ነው’ እና ‘አምላክ ሥላሴ ነው’ የሚሉት ትምህርቶች በጣም ያስጨንቁኝ ጀመር። የሃይማኖት መሪዎች መሠረት የሌለውና አጥጋቢ ያልሆነ መልስ ይሰጡኝ ነበር።

አጥጋቢ መልስ አገኘሁ

ኮሌጅ እማር በነበረበት ወቅት የአንድ ቡድን አባል በመሆኔ ምክንያት መደባደብ፣ ቁማር መጫወት፣ ማጨስና ሌሎች ተገቢ ያልሆኑ ድርጊቶችን መፈጸም ጀመርኩ። አንድ ቀን ምሽት የይሖዋ ምሥክር ከነበረችው የአንዱ የክፍል ጓደኛዬ እናት ጋር ተገናኘሁ። አባል ለነበርኩበት ሃይማኖት መሪዎች የጠየቅኩትን ጥያቄ ለእርሷም አቀረብኩላት። ለሁሉም ጥያቄዎቼ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ መልስ የሰጠችኝ ሲሆን የነገረችኝ በሙሉ እውነት መሆኑን አመንኩ።

መጽሐፍ ቅዱስ ገዝቼ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ማጥናትና ብዙም ሳይቆይ በሁሉም ስብሰባዎቻቸው ላይ መገኘት ጀመርኩ። “መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን ጠባይ ያበላሻል” በሚለው ጥበብ ያዘለ የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር መሠረት ከምግባረ ብልሹ ጓደኞቼ ተለየሁ። (1 ቆሮንቶስ 15:33) ይህም በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቴ እድገት እንዳደርግና በመጨረሻም ራሴን ለይሖዋ እንድወስን ረድቶኛል። በ1951 ከተጠመቅኩ በኋላ ለጥቂት ጊዜ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ (አቅኚ) ሆንኩ። ከዚያም በ1953 ከአውሬየ ሜንዶዛ ክሩስ ጋር ተጋባን፤ አውሬየ የዕድሜ ልክ አጋሬና የአገልግሎት ጓደኛዬ ሆናለች።

ለጸሎታችን መልስ አገኘን

አቅኚ ሆነን የማገልገል ጠንካራ ፍላጎት ነበረን። ይሁን እንጂ ይሖዋን በይበልጥ የማገልገል ምኞታችን ወዲያውኑ አልተሳካም። ቢሆንም እርሱን ለማገልገል የሚያስችሉንን አጋጣሚዎች እንዲከፍትልን ይሖዋን ከመለመን አልቦዘንም ነበር። ኑሮ በጣም ከባድ ነበር። እንዲህም ሆኖ መንፈሳዊ ግቦች ነበሩን፤ በ25 ዓመቴ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ አገልጋይ (በአሁኑ ጊዜ ሰብሳቢ የበላይ ተመልካች የሚባለው ነው) ሆኜ እንዳገለግል ተሾምኩ።

የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀቴ እየጎለበተ ሄዶ ይሖዋ ያወጣቸውን መሠረታዊ ሥርዓቶች በይበልጥ መገንዘብ ስጀምር የተሰማራሁበት ሥራ ከገለልተኝነት አቋሜ ጋር እንደማይጣጣም በማስተዋሌ ኅሊናዬን ይቆረቁረኝ ጀመር። (ኢሳይያስ 2:2-4) በመሆኑም ሥራዬን ለመልቀቅ ወሰንኩ። ይህም እምነታችንን የሚፈትን ነበር። ለቤተሰቤ የሚያስፈልገውን ነገር እንዴት ማቅረብ እችላለሁ? በዚህም ጊዜ ቢሆን ወደ ይሖዋ አምላክ ጸለይን። (መዝሙር 65:2) በጸሎታችን የሚያስጨንቁንንና የሚያስፈሩንን ነገሮች ለይሖዋ ገለጽን፤ በተጨማሪም የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ሄደን ማገልገል እንደምንፈልግ ነገርነው። (ፊልጵስዩስ 4:6, 7) በዚህ ጊዜ የተለያዩ አጋጣሚዎች ከፊታችን እንደሚጠብቁን ፈጽሞ አላወቅንም ነበር!

ጉዟችንን ጀመርን

በሚያዝያ ወር 1965 ላኦስ በሚገኘው ቪየንቲያን ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የእሳት አደጋ መከላከያ ተቆጣጣሪ ሆኜ ተቀጠርኩና ወደዚያው አመራን። በቪየንቲያን ከተማ 24 የይሖዋ ምሥክሮች የነበሩ ሲሆን ከሚስዮናውያንና ከጥቂት የአገሪቱ ተወላጅ ወንድሞች ጋር ሆነን እንሰብክ ነበር። ከዚያም ታይላንድ ወደሚገኘው ኡዶን ታኒ አውሮፕላን ማረፊያ ተቀየርኩ። በወቅቱ በኡዶን ታኒ ከተማ የነበርነው የይሖዋ ምሥክሮች እኛ ብቻ በመሆናችን ሁሉንም ሳምንታዊ ስብሰባዎቻችንን ብቻችንን እናካሂድ ነበር። ከቤት ወደ ቤት እየሄድን እንሰብክ እንዲሁም ተመላልሶ መጠየቆችን እናደርግ ነበር፤ መጽሐፍ ቅዱስን የምናስጠናቸው ሰዎችም ነበሩ።

ኢየሱስ ‘ብዙ ፍሬ ማፍራት’ እንዳለባቸው ለደቀ መዛሙርቱ የሰጣቸውን ማሳሰቢያ እናስታውስ ነበር። (ዮሐንስ 15:8) እኛም የእነርሱን ምሳሌ ለመከተል ቁርጥ ውሳኔ በማድረግ ምሥራቹን መስበካችንን ቀጠልን። ብዙም ሳይቆይ አንዳንድ ውጤቶችን ማግኘት ጀመርን። አንዲት ታይላንዳዊት ልጃገረድ እውነትን ተቀብላ መንፈሳዊ እህታችን ሆነች። ሁለት የሰሜን አሜሪካ ተወላጆችም እንዲሁ እውነትን ተቀብለው በኋላ የጉባኤ ሽማግሌዎች ሆኑ። በሰሜን ታይላንድ ከአሥር ዓመት በላይ ምሥራቹን ሰብከናል። በአሁኑ ጊዜ በኡዶን ታኒ ከተማ ጉባኤ እንዳለ ስንሰማ በጣም ተደሰትን! ከዘራነው የእውነት ዘር ውስጥ ጥቂቱ እስከ አሁን ድረስ ፍሬ እያፈራ ነው።

የሚያሳዝነው አሁንም እንደገና ወደ ሌላ አካባቢ ልንዛወር ነው፤ በዚህም ጊዜ ቢሆን “የመከሩ ጌታ” በስብከቱ ሥራ መካፈላችንን እንድንቀጥል እንዲረዳን በጸሎት ጠየቅነው። (ማቴዎስ 9:38) የኢራን ዋና ከተማ ወደሆነችው ቴራን ተቀየርን። ኢራን በወቅቱ በልዑል ትገዛ ነበር።

በአስቸጋሪ ክልሎች ውስጥ መስበክ

ቴራን እንደደረስን ከመንፈሳዊ ወንድሞቻችን ጋር ተገናኘን። ከዚያም የ13 አገር ዜጎችን ካቀፈው አነስተኛ የይሖዋ ምሥክሮች ቡድን ጋር ተቀላቀልን። ኢራን ውስጥ ምሥራቹን ለመስበክ አንዳንድ ማስተካከያዎችን ማድረግ ነበረብን። ቀጥተኛ ተቃውሞ ባያጋጥመንም እንኳን ጥንቃቄ ማድረግ አስፈልጎናል።

የማጥናት ፍላጎት ባላቸው ሰዎች የሥራ ሰዓት ምክንያት አልፎ አልፎ እኩለ ሌሊት ላይ ወይም ከዚያ በኋላ እስኪነጋጋ ድረስ ለማስጠናት ተገድደን ነበር። ይሁን እንጂ እንደዚህ ጠንክረን መሥራታችን ፍሬያማ ለመሆን ስላስቻለን በጣም ደስተኞች ነን! በርካታ ፊሊፒናውያንና ኮሪያውያን ቤተሰቦች እውነትን ተቀብለው ራሳቸውን ለይሖዋ ወስነዋል።

የሚቀጥለው ምድቤ ደግሞ ዳካ፣ ባንግላዴሽ ሲሆን በታኅሣሥ ወር 1977 እዚያ ደረስን። ይህ አገር የስብከት ሥራችንን ለመፈጸም አስቸጋሪ ከሆኑብን ቦታዎች አንዱ ነው። የሆነ ሆኖ በስብከቱ ሥራ ሁልጊዜ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለብን ይሰማን ነበር። በይሖዋ መንፈስ እርዳታ የሕዝበ ክርስትና አባላት የሆኑ ቤተሰቦችን ለማግኘት ቻልን። አንዳንዶቹ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ለሚገኘው መንፈስን የሚያድስ የእውነት ውኃ ጥማት ነበራቸው። (ኢሳይያስ 55:1) በመሆኑም በርካታ ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናት ጀመርን።

የአምላክ ፈቃድ “ሰዎች ሁሉ እንዲድኑ” መሆኑን ሁልጊዜ እናስታውሳለን። (1 ጢሞቴዎስ 2:4) ደስ የሚለው ማንም ሰው አላስቸገረንም ነበር። ለእኛ ከሩቁ ጥላቻ እንዳያድርባቸው ለማድረግ ስንል ወዳጃዊ በሆነ መንገድ እንቀርባቸው ነበር። ልክ እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ‘ከሁሉም ጋር ሁሉንም ነገር ለመሆን’ እንጥር ነበር። (1 ቆሮንቶስ 9:22) ለምን እንደመጣን ሲጠይቁን በደግነት መልስ እንሰጣቸው ነበር፤ አብዛኞቹ በጣም ተግባቢ እንደሆኑ ማስተዋል ችለናል።

በዳካ ውስጥ የአገሪቱ ተወላጅ የሆነች የይሖዋ ምሥክር አግኝተን ስብሰባ እንድትመጣ በኋላም አብራን በስብከቱ ሥራ እንድትካፈል አበረታታናት። ትንሽ ቆይቶ ደግሞ ባለቤቴ የልጅቷን ቤተሰቦች መጽሐፍ ቅዱስ ታስጠናቸው ጀመር፤ በስብሰባዎቻችንም ላይ እንዲገኙ ጋበዘቻቸው። በይሖዋ ቸርነት መላው ቤተሰብ እውነትን ተቀበለ። ከጊዜ በኋላ ሁለት ሴት ልጆቻቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ወደ ቤንጋሊ ቋንቋ በመተርጎም ሥራ ይረዱ ነበር፤ በርካታ ዘመዶቻቸውም እንዲሁ የይሖዋ አምላኪዎች ሆነዋል። ሌሎች በርከት ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችም እውነትን ተቀብለዋል። በአሁኑ ጊዜ አብዛኞቹ ሽማግሌዎችና አቅኚዎች ሆነው ያገለግላሉ።

ዳካ ሕዝብ የሚበዛባት ከተማ በመሆኗ አንዳንድ ዘመዶቻችን መጥተው በስብከቱ ሥራ እንዲረዱን እንጋብዛቸው ነበር። አብዛኞቹ ግብዣችንን በመቀበል ባንግላዴሽ መጥተው አብረውን አገልግለዋል። በዚህች አገር ምሥራቹን የመስበክ አስደሳች አጋጣሚ በማግኘታችን ይሖዋን በጣም እናመሰግነዋለን! አንድ ሰው ብቻ በነበረበት በባንግላዴሽ አሁን ሁለት ጉባኤዎች አሉ።

በሐምሌ ወር 1982 ከባንግላዴሽ እንድንወጣ ስለታዘዝን ከወንድሞች ጋር ተላቅሰን ተለያየን። ብዙም ሳይቆይ ኡጋንዳ በሚገኘው ኢንቴቤ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የተቀጠርኩ ሲሆን እዚያም አራት ዓመት ከሰባት ወር ቆየን። በዚህ አገር የይሖዋን ታላቅ ስም ማክበር የቻልነው እንዴት ነው?

በምሥራቅ አፍሪካ ይሖዋን ማገልገል

እኔና ባለቤቴ ኢንቴቤ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እንደደረስን አንድ ሹፌር ተቀብሎን ወደ ማረፊያችን መጓዝ ጀመርን። ከአውሮፕላን ማረፊያው እንደወጣን ለሹፌሩ ስለ አምላክ መንግሥት መስበክ ስጀምር “የይሖዋ ምሥክር ነህ እንዴ?” ብሎ ጠየቀኝ። “አዎን” ብዬ መልስ ስሰጠው “አንዱ ወንድማችሁ የአውሮፕላን መቆጣጠሪያ ማማ ላይ ይሠራል” አለኝ። ወዲያውኑ ወደዚያው እንዲወስደኝ ጠየቅኩት። ወንድም ሲያገኘን በጣም ተደሰተ፤ ከዚያ በኋላ በስብሰባዎች ለመገኘትና በመስክ አገልግሎት ለመካፈል የሚያስፈልገንን ዝግጅት አደረግን።

በወቅቱ ኡጋንዳ ውስጥ 228 አስፋፊዎች ብቻ ይገኙ ነበር። በመጀመሪያው ዓመት በኢንቴቤ ከነበሩ ሁለት ወንድሞች ጋር ሆነን የእውነትን ዘር ስንተክል ቆየን። ነዋሪዎቹ የማንበብ ፍላጎት ስለነበራቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ መጽሔቶችና ሌሎች በርካታ ጽሑፎች ማበርከት ቻልን። በዋና ከተማዋ በካምፓላ የሚገኙ ወንድሞች ቅዳሜና እሁድ ወደ ኢንቴቤ መጥተው በስብከቱ ሥራ እንዲረዱን እንጋብዛቸው ነበር። ለመጀመሪያ ጊዜ የሕዝብ ንግግር ባቀረብኩበት ወቅት የተገኘነው ተሰብሳቢዎች እኔን ጨምሮ አምስት ነበርን።

ከሦስት ዓመት በኋላ፣ እውነትን ያስተማርናቸው ሰዎች በጎ ምላሽ በመስጠት ፈጣን እድገት ሲያደርጉ በማየታችን በጣም ተደሰትን። (3 ዮሐንስ 4) በአንድ የወረዳ ስብሰባ ላይ ስድስት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን ተጠመቁ። አብዛኞቹ ጥናቶቻችን እኛ ሙሉ ቀን ዓለማዊ ሥራ ብንሠራም እንኳን አቅኚ ሆነን ማገልገላችን እነርሱም በሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንዲካፈሉ እንዳበረታታቸው ይነግሩን ነበር።

የሥራ ቦታችንም እንዲሁ ፍሬያማ የአገልግሎት ክልል እንደሆነ ተገንዝበን ነበር። በአንድ አጋጣሚ በአውሮፕላን ማረፊያው ውስጥ ወደ አንድ የእሳት አደጋ መከላከያ ሠራተኛ ቀረብኩና ገነት በሆነች ምድር ላይ ስለምናገኘው ሕይወት የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ነገርኩት። ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች በሰላምና በስምምነት እንደሚኖሩ እንዲሁም በድህነት፣ በቤት ችግር፣ በጦርነትና በሞት ምክንያት መሠቃየት እንደሚቀር ከራሱ መጽሐፍ ቅዱስ አውጥቼ አሳየሁት። (መዝሙር 46:9፤ ኢሳይያስ 33:24፤ 65:21, 22፤ ራእይ 21:3, 4) ይህን ከራሱ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ማንበቡ ፍላጎቱን ቀሰቀሰው። ወዲያውኑ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናትና በሁሉም ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመረ። ብዙም ሳይቆይ ራሱን ለይሖዋ ወስኖ ተጠመቀና በኋላ ላይ አብሮን በአቅኚነት ማገልገል ጀመረ።

ኡጋንዳ እያለን ሁለት ጊዜ ሕዝባዊ ዓመጽ ተቀስቅሶ የነበረ ቢሆንም ብጥብጡ ለመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎቻችን እንቅፋት አልሆነብንም። በዚህ ጊዜ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ሠራተኛ ቤተሰቦች ለስድስት ወር ወደ ናይሮቢ፣ ኬንያ ሄደው እንዲቆዩ ተደረገ። በኡጋንዳ የቀረነው በጣም መጠንቀቅ ይገባን የነበረ ቢሆንም በስብሰባዎች ላይ መገኘታችንንና በስብከቱ ሥራ መካፈላችንን ቀጥለን ነበር።

በሚያዝያ ወር 1988 በኡጋንዳ የነበረኝን ሥራ አጠናቀቅኩና እንደገና ወደ ሌላ ቦታ ተጓዝን። በኢንቴቤ በነበረው መንፈሳዊ እድገት ጥልቅ እርካታ እየተሰማን ጉባኤውን ለቅቀን ሄድን። በሐምሌ ወር 1997 በድጋሚ ወደ ኢንቴቤ የመሄድ አጋጣሚ አግኝተን ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ስናስጠናቸው ከነበሩት ውስጥ አንዳንዶቹ በወቅቱ ሽማግሌዎች ሆነው ማገልገል ጀምረው ነበር። በሕዝብ ንግግር ላይ 106 ተሰብሳቢዎች መገኘታቸውን ስናይ በጣም ተደሰትን!

ጨርሶ ወዳልተነካ ክልል ተጓዝን

አሁንስ አዲስ አጋጣሚ ይከፈትልን ይሆን? አዎን፣ የሚቀጥለው የሥራ ቦታዬ በሶማሊያ የሚገኘው ሞቃዲሾ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሆነ። ጨርሶ ባልተነካ ክልል የማገልገል አጋጣሚያችንን ጥሩ አድርገን ልንጠቀምበት ቆረጥን።

በአብዛኛው የምንሰብከው የኤምባሲ ሠራተኞች ለሆኑ ፊሊፒናውያንና ለሌሎች የውጭ አገር ዜጎች ነበር። ብዙ ጊዜ እነዚህን ሰዎች የምናገኛቸው በገበያ ቦታ ነበር። በጥየቃ መልክም ቤታቸው እንሄድ ነበር። በብልሃት፣ በዘዴና በጥንቃቄ እንዲሁም ሙሉ በሙሉ በይሖዋ ላይ በመታመን የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ልናካፍላቸው ችለን ነበር፤ ይህም የተለያየ አገር ዜግነት ያላቸው ሰዎች እውነትን እንዲያውቁ ለመርዳት አስችሎናል። ከሁለት ዓመት በኋላ ልክ ጦርነት ሊጀምር ሲል ሞቃዲሾን ለቅቀን ወጣን።

ከዚህ በመቀጠል ዓለም አቀፍ ሲቪል አቪየሽን ድርጅት ያንጎን፣ ማያንማር መደበኝ። አሁንም ቢሆን ልበ ቅን የሆኑ ሰዎች የአምላክን ዓላማ እንዲማሩ የመርዳት አጋጣሚ አገኘን። ከማያንማር በኋላ ዳሬ ሰላም፣ ታንዛንያ ተመደብን። በዳሬ ሰላም እንግሊዝኛ ተናጋሪ ሰዎች ስለነበሩ ከቤት ወደ ቤት መስበክ ብዙም አይከብድም ነበር።

በሠራንባቸው አገሮች በአብዛኛው የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ ታግዶ የነበረ ቢሆንም የገጠሙን ችግሮች በጣት የሚቆጠሩ ናቸው። የሥራዬ ሁኔታ ብዙውን ጊዜ ከመንግሥትና ከሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር ያገናኘኝ ስለነበር ሰዎች ስለ ስብከት ሥራችን አይጠይቁኝም ነበር።

በዓለማዊ ሥራዬ ምክንያት እኔና ባለቤቴ ለሦስት አሥርተ ዓመታት የዘላን ዓይነት ኑሮ ኖረናል። ይሁን እንጂ ሥራዬን ዋነኛውን ግባችንን ለመፈጸም እንዳስቻለን አድርገን እንቆጥረዋለን። ምንጊዜም ቢሆን ዋናው ዓላማችን የአምላክን መንግሥት ፍላጎቶች ማራመድ ነበር። ይሖዋ በየጊዜው ያጋጠመንን የሥራ ቦታ ለውጥ ጥሩ አድርገን እንድንጠቀምበት ስለረዳንና ምሥራቹን ከፊሊፒንስ ርቀው በሚገኙ ቦታዎች ጭምር የመስበክ ድንቅ አጋጣሚ ስለሰጠን በጣም እናመሰግነዋለን።

ወደተነሳንበት ተመለስን

ሃምሳ ስምንት ዓመት ሲሆነኝ የጡረታ ዕድሜዬ ሳይደርስ ጡረታ ለመውጣትና ፊሊፒንስ ለመመለስ ወሰንኩ። ወደ ፊሊፒንስ ስንመለስ ማድረግ የሚገባንን በተመለከተ መመሪያ እንዲሰጠን ወደ ይሖዋ ጸለይን። በከቪቲ አውራጃ ውስጥ ባለችው ትሬሴ ማርቲሬስ ከተማ በሚገኝ ጉባኤ ውስጥ ማገልገል ጀመርን። እዚህች ከተማ በደረስንበት ጊዜ 19 የመንግሥቱ አስፋፊዎች ብቻ ይገኙ ነበር። በየዕለቱ መስበክ የምንችልበት ዝግጅት ተደረገና በርካታ ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናት ጀመርን። ከዚያ በኋላ ጉባኤው እድገት ያደርግ ጀመር። በአንድ ወቅት ባለቤቴ ወደ 19 የሚጠጉ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች የነበሯት ሲሆን እኔ ደግሞ 14 ጥናቶች እመራ ነበር።

ብዙም ሳይቆይ የመንግሥት አዳራሻችን ስለጠበበን ይህን ጉዳይ በተመለከተ ወደ ይሖዋ ጸለይን። አንድ መንፈሳዊ ወንድማችንና ሚስቱ ከመሬታቸው ትንሽ ከፍለው ሰጡን፤ ቅርንጫፍ ቢሮውም አዲስ የመንግሥት አዳራሽ ለመሥራት የሚያስችል ብድር ፈቀደልን። አዲሱ ሕንጻ በስብከቱ ሥራ ላይ በጎ ተጽዕኖ አድርጓል፤ በመሆኑም የተሰብሳቢዎች ቁጥር ከሳምንት ወደ ሳምንት ይጨምር ነበር። በአሁኑ ጊዜ 17 አስፋፊዎች የሚገኙበትን ሌላ ጉባኤ ከአንድ ሰዓት በላይ ተጉዘን በመሄድ እየረዳን ነው።

እኔም ሆንኩ ባለቤቴ ያገኘነውን በተለያዩ አገሮች ውስጥ የማገልገል መብት ከፍ አድርገን እንመለከተዋለን። ያሳለፍነውን የዘላንነት ኑሮ መለስ ብለን ስናስበው ከሁሉ በተሻለ መንገድ ማለትም ሌሎችን ስለ ይሖዋ ለማስተማር ስለተጠቀምንበት ትልቅ እርካታ ይሰማናል!

[በገጽ 24 እና 25 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ታንዛንያ

ኡጋንዳ

ሶማሊያ

ኢራን

ባንግላዴሽ

ማያንማር

ላኦስ

ታይላንድ

ፊሊፒንስ

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከባለቤቴ ከአውሬየ ጋር