በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“በፈተና ወቅት ያሳዩት ጽናት”

“በፈተና ወቅት ያሳዩት ጽናት”

“በፈተና ወቅት ያሳዩት ጽናት”

በ1951 ሚያዝያ ወር መጀመሪያ አካባቢ ኃያሉ የሶቪዬት ሕብረት መንግሥት በአገሪቱ ምዕራባዊ ግዛት በሚገኙና የይሖዋ ምሥክሮች ተብለው በሚጠሩ ንጹሐን ዜጎች ላይ ድንገተኛ ጥቃት ከፈተ። ሕፃናትን፣ ነፍሰ ጡሮችን እና አረጋውያንን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ቤተሰቦች ወደ ሳይቤሪያ ለሚደረገው ሃያ ቀን የሚፈጅ አድካሚ ጉዞ የባቡር ፉርጎዎች ውስጥ ታጨቁ። ለመኖር አመቺ ባልሆነና ሥልጣኔ ባልገባበት አካባቢ ለዘለቄታው እንዲኖሩ ተፈረደባቸው።

በሚያዝያ 2001 የዚህ የማይረሳ ክንውን 50ኛ ዓመት በሞስኮ በተከበረበት ወቅት የይሖዋ ምሥክሮች በቀድሞዋ ሶቪዬት ሕብረት ለአሥርተ ዓመታት የደረሰባቸውን ጭቆና የሚያሳይ የቪዲዮ ፊልም ወጥቶ ነበር። በፊልሙ ላይ የታሪክ ምሑራንና የዓይን ምሥክሮች፣ እነዚህ ክርስቲያኖች የደረሰባቸውን ከባድ ችግር እንዴት እንደተቋቋሙና ብሎም እንዴት በቁጥር እየበዙ እንደሄዱ ተርከዋል።

በሶቪዬት ሕብረት ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች በፈተና ወቅት ያሳዩት ጽናት የተባለውን ይህን የቪዲዮ ፊልም በአሁኑ ጊዜ በሩሲያና በሌሎች አገሮች የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የተመለከቱት ከመሆኑም ሌላ ከታሪክ ምሑራንም ሆነ በአጠቃላይ ከተመልካቾች ከፍተኛ አድናቆት ተችሮታል። አብዛኞቹ የይሖዋ ምሥክሮች በተሰደዱበት አካባቢ የሚኖሩ ሁለት የሩሲያ የታሪክ ምሑራን የሰጡት አስተያየት ቀጥሎ ቀርቧል።

“ፊልሙን በጣም ወድጄዋለሁ። ድሮም ቢሆን የእናንተን ሃይማኖት ሰዎች እወዳቸዋለሁ፤ ፊልሙን ከተመለከትኩ በኋላ ደግሞ ለእናንተ ያለኝ አድናቆት በጣም ጨምሯል። ፊልሙ የላቀ ሞያዊ ጥበብ ተንጸባርቆበታል! በተለይ ደግሞ ሰዎቹን በቅርብ እንድናውቃቸው አድርጋችሁ ያቀረባችሁበት መንገድ አስደስቶኛል። የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታይና ሃይማኖቴን የመቀየር ሐሳብ የሌለኝ ሰው ብሆንም እንኳ ምሥክሮቹን ግን እወዳቸዋለሁ። የታሪክ ፋኩልቲው የዚህ የቪዲዮ ፊልም ቅጂ እንዲኖረው እፈልጋለው። እኔና የሥራ ባልደረቦቼ ፊልሙን ለተማሪዎቻችን ለማሳየትና በሥርዓተ ትምህርቱ ውስጥ ለማካተት ተስማምተናል።”—በሩሲያ፣ ኢርኩትስክ በሚገኘው ዘ ስቴት ፔዳጎጂካል ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ፋኩልቲ ዲን የሆኑት ፕሮፌሰር ሰርጌይ ኒከሌይቪች ሩብትሶፍ።

“የፊልሙ መውጣት አስደስቶኛል። መብት ረገጣን የሚያሳይ ፊልም ሲዘጋጅ ታሪኩን ባልተዛባ መንገድ ማዘጋጀት ምንጊዜም ቢሆን በጣም አስቸጋሪ ነው፤ እናንተ ግን ተሳክቶላችኋል። እባካችሁ፣ ሌሎች ፊልሞችም ብታመጡልኝ ደስ ይለኛል።”—በሩሲያ፣ ኢርኩትስክ በሚገኘው ስቴት ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ፋኩልቲ ዲን የሆኑት ፕሮፌሰር ሰርጌይ ኢሊች ኩዝኔትሶፍ።

በሳይቤሪያ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮችም ፊልሙን ከልብ አድንቀዋል። ከሰጡት አስተያየት መካከል የሚከተሉትን ለናሙና ያህል እንመልከት።

“በፊልሙ ላይ የቀረቡት ሁኔታዎች በተፈጸሙበት ወቅት በሩሲያ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮችን እንቅስቃሴ በተመለከተ የተዛባ መረጃ ይቀርብላቸው ነበር። ይሁንና ፊልሙን ከተመለከቱ በኋላ ድርጅታችን ከዚህ በፊት ያስቡት እንደነበረው አንድ የኑፋቄ ቡድን አለመሆኑን መረዳት ችለዋል። በቅርቡ የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ወንድሞችና እህቶች ደግሞ ‘አብረውን የሚያገለግሉት ክርስቲያን ወንድሞች ይህን ያህል ከባድ መከራ እንዳሳለፉ አስበን አናውቅም ነበር!’ ብለዋል። አንድ ወንድም ፊልሙን ከተመለከተ በኋላ የዘወትር አቅኚ የመሆን ፍላጎት እንዳደረበት ተናግሯል።”—በግዞት ወደ ሳይቤሪያ ተወስዳ የነበረችው አና ቮቭቹክ።

“ፊልሙ ላይ አንድ የሕዝብ ደኅንነት ፖሊስ የይሖዋ ምሥክሮችን ቤት ሲያንኳኳ ስመለከት በድንጋጤ ክው አልኩ። የእኛን ቤት ያንኳኩበት ጊዜና እናቴ ‘ምናልባት የሆነ ቦታ ቃጠሎ ተነስቶ ይሆናል’ ብላ የተናገረችው ትዝ አለኝ። ይሁንና ፊልሙ ከእኔ የባሰ ሥቃይ የደረሰባቸው ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች እንዳሉ እንዳስተውልም አድርጎኛል። ፊልሙ ላይ የተመለከትናቸው ነገሮች ሁሉ ይሖዋን ማገልገላችንን እንድንቀጥል የበለጠ ጥንካሬና ቅንዓት ጨምሮልናል።”—በግዞት ወደ ሳይቤሪያ ተወስዶ የነበረው ስቲፓን ቮቭቹክ።

“ወላጆቼ በግዞት ከተወሰዱት ምሥክሮች መካከል ናቸው። በመሆኑም በዚያን ጊዜ ስለደረሰው ነገር ብዙ የማውቅ ይመስለኝ ነበር። ይሁንና ይህንን ፊልም ካየሁ በኋላ ምንም ነገር እንደማላውቅ ተረዳሁ። ወንድሞች የደረሰባቸውን ሁኔታ ሲናገሩ ስሰማ ዓይኖቼ እንባ አቀረሩ። አሁን ተሞክሮዎቹ ለእኔ ሕያው ማስረጃዎች እንጂ ታሪክ ብቻ አይደሉም። ፊልሙ ከአምላክ ጋር ያለኝ ዝምድና እንዲጠናከር ከመርዳቱም ሌላ ከፊት ለፊቴ የሚያጋጥሙኝን ፈተናዎች በጽናት ለመወጣት እንድችል አዘጋጅቶኛል።”—የኢርኩትስክ ነዋሪ የሆነው ቭላድሚር ኮቫሽ።

“ታሪኩን ከማንበብ ይልቅ በፊልም ማየት መቻሌ ስሜቴን በጥልቅ ነክቶታል። ወንድሞች የደረሰባቸውን ነገር ሲናገሩ ስመለከትና ስሰማ ያን ሁሉ ከባድ መከራ እኔም ከእነርሱ ጋር ያሳለፍኩ ያህል ሆኖ ተሰማኝ። እስር ቤት ውስጥ እያለ ለሴቶች ልጆቹ ካርድ ላይ ሥዕል ስሎ ይልክላቸው የነበረው አባት ያደረገው ነገር እኔም በመጽሐፍ ቅዱስ እውነት አማካኝነት የልጆቼን ልብ ለመንካት ጥረት ማድረግ እንዳለብኝ አስተምሮኛል። በጣም አመሰግናችኋለሁ! ይህ ፊልም በሩሲያ የምንገኝ የይሖዋ ምሥክሮች ዓለም አቀፍ ስፋት ያለው የይሖዋ ድርጅት አካል መሆናችንን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ እንድንረዳ አስችሎናል።”—ታትያና ካሊና የተባለች የኢርኩትስክ ነዋሪ።

‘መቶ ጊዜ ከመስማት አንድ ጊዜ ማየት’ የሚለው አባባል በእርግጥ ለዚህ ፊልም ይሠራል። ነገሮችን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ፣ ሕያውና ከእኛ ሕይወት ጋር ዝምድና ያለው ፊልም ነው! ፊልሙን ከተመለከትኩ በኋላ በሁኔታው ላይ ለማሰላሰል ሰፋ ያለ ጊዜ መመደብ አስፈልጐኛል። እንዲሁም ራሴን በእነዚያ ግዞተኛ ምሥክሮች ቦታ አድርጌ እንድመለከት አስችሎኛል። አሁን እኔ ያለሁበትን ሁኔታ እነርሱ ካሳለፉት ጋር ሳወዳድር፣ ዛሬ ስለሚያጋጥሙን ችግሮች የተለየ አመለካከት እንዲኖረኝ አስችሎኛል።”—ሊዲያ ቢኤዳ የተባለች የኢርኩትስክ ነዋሪ።

በፈተና ወቅት ያሳዩት ጽናት የተሰኘው ይህ የቪዲዮ ፊልም በ25 ቋንቋዎች የሚገኝ ሲሆን በዓለም ዙሪያም ጥሩ ተቀባይነት እያገኘ ነው። a በሩሲያ ውስጥ በሚገኙት በሴይንት ፒተርስበርግ፣ በኦምስክ እና በሌሎች ከተሞች እንዲሁም ዩክሬይን ውስጥ በሚገኙት በቪነኔትሳ፣ ኬርሽ፣ ሜሊቶፖል እና በለቪፍ ክልል ፊልሙ በቴሌቪዥን ተላልፏል። ከዚህም በተጨማሪ በዓለም አቀፉ የፊልም ገምጋሚ ቦርድ ተሸላሚ ለመሆን በቅቷል።

የዚህ ፊልም ዋና መልእክት፣ ለረጅም ዓመታት የዘለቀ ስደት ቢያጋጥማቸውም የሚያስገርም ድፍረትና መንፈሳዊ ጥንካሬ ባሳዩ በሺዎች በሚቆጠሩ ተራ ሰዎች የሕይወት ተሞክሮ ላይ የተመሠረተ ነው። በሶቪዬት ሕብረት የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች በፈተና ወቅት ታማኝ መሆናቸውን በእርግጥ አስመስክረዋል። አንተም ይህንን ፊልም ማየት ከፈለግህ በአካባቢህ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮችን ብትጠይቃቸው ሊያመጡልህ ፈቃደኞች ናቸው።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ይህ የቪዲዮ ፊልም በካንቶኒዝ፣ በቼክ፣ በደች፣ በእንግሊዝኛ፣ በፈረንሳይኛ፣ በጀርመንኛ፣ በግሪክኛ፣ በጣሊያንኛ፣ በጃፓንኛ፣ በሊቱዋንያ፣ በማንደሪን፣ በፖሊሽ፣ በስሎቫክ፣ በስፓንኛ እንዲሁም በቡልጋሪያ፣ በፊንላንድ፣ በዴንማርክ፣ በሀንጋሪ፣ በስዊድን፣ በስሎቫንያ፣ በኢንዶኔዥያ፣ በኮሪያ፣ በሩማንያ፣ በሩሲያ እና በኖርዌይ ቋንቋ ይገኛል።

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ስታሊን:- U.S. Army photo

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ስታሊን:- U.S. Army photo