በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አለመግባባቶችን መፍታት የሚያስገኛቸው ጥቅሞች

አለመግባባቶችን መፍታት የሚያስገኛቸው ጥቅሞች

አለመግባባቶችን መፍታት የሚያስገኛቸው ጥቅሞች

ኤድዋርድ ሊሞት እያጣጣረ ነው፤ ቢል ግን በዚህ ጊዜም እንኳ ለኤድዋርድ ያለው ጥላቻ አልቀነሰም። ኤድዋርድ ከሁለት አሥርተ ዓመታት በፊት ያደረገው ውሳኔ ቢልን ከሥራ ገበታው ያፈናቀለው ሲሆን በአንድ ወቅት የቅርብ ጓደኛሞች የነበሩት እነዚህ ሁለት ሰዎችም በዚሁ ሳቢያ ተቃቅረዋል። ኤድዋርድ የአእምሮ ሰላም አግኝቶ መሞትን ስለፈለገ ይቅርታ ቢጠይቀውም ቢል ግን ለመስማት ፈቃደኛ አልሆነም።

ወደ ሠላሳ የሚጠጉ ዓመታት ካለፉ በኋላ፣ ቢል መሞቻው እየተቃረበ ሲሄድ በዚያን ጊዜ ለወዳጁ ለምን ይቅርታ እንዳላደረገለት እንዲህ በማለት ገልጿል:- “ኤድዋርድ በቅርብ ጓደኛው ላይ ማድረግ የሌለበትን ነገር አድርጓል። ከሃያ ዓመታት በኋላ ደግሞ መታረቁን አልፈለግኩትም። . . . ምናልባት ተሳስቼ ሊሆን ይችላል፤ በወቅቱ ግን ይቅርታ ማድረግ እንደሌለብኝ ተሰምቶኝ ነበር።” a

አብዛኛውን ጊዜ የግል አለመግባባት ይህን የመሰለ አሳዛኝ ውጤት ባይኖረውም የብዙዎችን ስሜት ሊጎዳ ወይም ምሬት እንዲያድርባቸው ሊያደርግ ይችላል። አንድ ሰው ልክ የኤድዋርድ ዓይነት ስሜት ተሰማው እንበል። ባደረገው ውሳኔ ወዳጁን እንደጎዳው በመገንዘቡ ሕይወቱን ሙሉ የጸጸት ስሜት የሚያሠቃየው ከመሆኑም በላይ የቅርብ ጓደኛውን ቢልን ማጣቱ ያንገበግበዋል። ያም ሆኖ ግን ቅር የተሰኘው ጓደኛው ወዳጅነታቸውን ከምንም ባለመቁጠር እንደ ቀላል ነገር እንደተወው ሲያስብ ደግሞ ስሜቱ ይጎዳል።

በሌላ በኩል ደግሞ የቢል ዓይነት አመለካከት ያለው ሰው በየዋህነቱ እንደተጠቃ አድርጎ በማሰብ ወዳጁን ሊቀየመው ወይም አጥብቆ ሊጠላው ይችላል። ቢል የቀድሞ ጓደኛው ሆነ ብሎ እንደጎዳው ይሰማዋል። አብዛኛውን ጊዜ በሁለት ሰዎች መካከል አለመግባባት ሲፈጠር ሁለቱም ወገኖች ራሳቸው ትክክለኛ እንደሆኑና ጥፋቱ የሌላኛው ወገን እንደሆነ አድርገው ያስባሉ። ከዚህም የተነሳ ቀደም ሲል ወዳጆች የነበሩ ሁለት ሰዎች እርስ በርሳቸው ጦርነት የከፈቱ ያህል ይጣላሉ።

ውጊያውን የሚያካሂዱት በድምጽ አልባ የጦር መሣሪያ ይሆናል፤ አንደኛው ሲያልፍ ሌላኛው ፊቱን ያዞራል እንዲሁም በሰዎች መሃል ሲሆኑ እርስ በርሳቸው አይነጋገሩም። ከሩቁ ሲሆኑ አንዳቸው ሌላኛውን በስርቆት ይመለከታሉ ወይም ወዳጃዊ ባልሆነና ጥላቻ በተሞላበት መንገድ ይተያያሉ። በሚነጋገሩበት ጊዜም የአሽሙር ወይም ልክ እንደ ጩቤ የሚወጋ የዘለፋ ንግግር ይጠቀማሉ።

እርስ በርሳቸው ፈጽሞ የማይግባቡ ቢመስሉም በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ መስማማታቸው አይቀርም። ከበድ ያሉ ችግሮች እንዳሉባቸውና ከቅርብ ጓደኛ ጋር መለያየት ምን ያህል አሳዛኝ እንደሆነ ሊገልጹ ይችላሉ። እያንዳንዳቸው እንደሚያመረቅዝ ቁስል ውስጣዊ ሕመም ሊሰማቸው ይችላል፤ ቁስሉን ለማዳን ደግሞ አንድ ነገር መደረግ እንዳለበት ሁለቱም ያውቃሉ። ሆኖም የሻከረውን ግንኙነት ለማስተካከልና ሰላም ለመፍጠር ማን ቅድሚያውን ይውሰድ? ይህንን ለማድረግ ሁለቱም ፈቃደኞች አይደሉም።

ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት በኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት መካከል አንዳንድ ጊዜ የጋለ ክርክር ይፈጠር ነበር። (ማርቆስ 10:35-41፤ ሉቃስ 9:46፤ 22:24) በአንድ ወቅት በመካከላቸው ግጭት ከተፈጠረ በኋላ ኢየሱስ “በመንገድ ላይ የምትከራከሩት ስለ ምን ነበር?” ብሎ ጠየቃቸው። ሁሉም አፍረው ዝም አሉ። (ማርቆስ 9:33, 34) የኢየሱስ ትምህርቶች አለመግባባቶቻቸውን እንዲፈቱ ረድተዋቸዋል። እርሱም ሆነ አንዳንድ ደቀ መዛሙርቱ የሰጧቸው ምክሮች ሰዎች በመካከላቸው የሚፈጠሩ ቅራኔዎችን እንዲያስወግዱና ከወዳጆቻቸው ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዲያድሱ ረድተዋቸዋል። ይህ እንዴት ሊሆን እንደቻለ እንመልከት።

አለመግባባቶችን ለመፍታት ጥረት አድርግ

“ያንን ሰው ከአሁን በኋላ ላናግረውም ሆነ ላየው አልፈልግም።” አንድን ሰው በተመለከተ እንዲህ በማለት ተናግረህ ከነበረ የሚከተለው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል እንደሚያሳየው እርምጃ መውሰድ ያስፈልግሃል።

ኢየሱስ እንዲህ ሲል አስተምሯል:- “ስለዚህ መባህን በመሠዊያው ላይ ለእግዚአብሔር በምታቀርብበት ጊዜ ወንድምህ የተቀየመብህ ነገር መኖሩ ትዝ ቢልህ፣ መባህን በዚያው በመሠዊያው ፊት ተወው፤ በመጀመሪያ ሄደህ ከወንድምህ ጋር ተስማማ፤ ከዚያም ተመልሰህ መባህን ለእግዚአብሔር አቅርብ።” (ማቴዎስ 5:23, 24) በተጨማሪም “ወንድምህ ቢበድልህ ሄደህ አንተና እርሱ ብቻ ሆናችሁ ጥፋቱን ንገረው” ብሏል። (ማቴዎስ 18:15) አንድን ሰው አስቀይመህ ወይም ሌላ ሰው አስቀይሞህ ከሆነ ጉዳዩን አንተ ራስህ ከግለሰቡ ጋር ወዲያውኑ ልትነጋገርበት እንደሚገባ ኢየሱስ የተናገራቸው ቃላት ጎላ አድርገው ይገልጻሉ። ይህንንም ማድረግ ያለብህ “በየውሃት መንፈስ” መሆን አለበት። (ገላትያ 6:1 የ1954 ትርጉም) እንደዚህ ያለው ውይይት ዓላማ የራስህን ድርጊት ተገቢ በማስመሰል ሰዎች ለአንተ ያላቸው አመለካከት እንዳይቀየር ለማድረግ ወይም ደግሞ ሌላኛው ሰው ይቅርታ እንዲጠይቅ ለማስገደድ ሳይሆን ሰላም ለመፍጠር መሆን አለበት። ታዲያ ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ይሠራል?

ኧርነስት በአንድ ትልቅ መሥሪያ ቤት ውስጥ ኃላፊ ሆኖ የሚሠራ ሰው ነው። b ለብዙ ዓመታት ከሥራው ጋር በተያያዘ ከተለያዩ ሰዎች ጋር የሚያገናኙ ጥንቃቄ የሚሹ ጉዳዮችን ሲያከናውን የኖረ ሲሆን ይህም ከሥራ ባልደረቦቹ ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖረው ማድረግን ይጠይቅበት ነበር። በግለሰቦች መካከል በቀላሉ ቅራኔ ሊፈጠር እንደሚችል ከተሞክሮ ተመልክቷል። ኧርነስት እንዲህ ይላል:- “አንዳንድ ጊዜ ከሌሎች ጋር አለመግባባት ይፈጠር ነበር። በዚህ ጊዜ ከግለሰቡ ጋር ቁጭ ብዬ ችግሩን እንወያይበት ነበር። ሰላም ለመፍጠር በማሰብ በቀጥታ ሄጄ አነጋግራቸዋለሁ። በዚህ በኩልም ተሳክቶልኛል።”

አሊስያ የተለያየ ባሕል ያላቸው ጓደኞች አሏት። እንዲህ ትላለች:- “አንዳንድ ጊዜ አንድ ነገር ከተናገርኩ በኋላ አንድ ሰው እንዳስቀየምኩ ይሰማኛል። ግለሰቡ ጋር ሄጄ ይቅርታ እጠይቃለሁ። ምናልባት ግለሰቡ ቅሬታ አልተሰማው ይሆናል፤ እኔ ግን እንዲህ በማድረጌ ጥሩ ስሜት ስለሚሰማኝ አስፈላጊ ላይሆን ቢችልም ብዙ ጊዜ ይቅርታ እጠይቃለሁ። እንዲህ ሳደርግ በመካከላችን አለመግባባት እንዳልተፈጠረ ለማወቅም ያስችለኛል።”

እንቅፋቶችን ማሸነፍ

ሆኖም የግል አለመግባባቶችን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት በሚደረገው ጥረት አብዛኛውን ጊዜ እንቅፋቶች አይጠፉም። “ያጠፋው እርሱ ሆኖ እያለ ሰላም ለመፍጠር እኔ ቅድሚያውን የምወስደው ለምንድን ነው?” ብለህ ታውቃለህ? ወይም ደግሞ ችግሩን ለመፍታት ሄደህ “እኔ በበኩሌ ምንም የምልህ ነገር የለም” የሚል መልስ አጋጥሞህ ያውቃል? አንዳንድ ሰዎች እንዲህ ዓይነት መልስ የሚሰጡት ስሜታቸው ስለተጎዳ ነው። ምሳሌ 18:19 እንዲህ ይላል:- “የተበደለ ወንድም ከተመሸገ ከተማ ይበልጥ የማይበገር ነው፤ ጠቡም እንደ ጠንካራ የግንብ መዝጊያ ነው።” የሌላኛውን ወገን ስሜት ከግምት ለማስገባት ሞክር። ሊያነጋግርህ ፈቃደኛ ካልሆነ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ እንደገና ሞክር። ምናልባት ‘የተመሸገው ከተማና መዝጊያው’ ለእርቅ ሊከፈት ይችላል።

ክብሬ ይነካል የሚል ስሜት ደግሞ ሌላኛው እንቅፋት ነው። አንዳንድ ሰዎች ይቅርታ መጠየቅን እንዲያውም ከተቀያየሙት ሰው ጋር መነጋገርን እንኳ ልክ እንደ ውርደት ይቆጥሩታል። ለራሳችን ጥሩ ግምት እንዲኖረን መፈለጋችን ተገቢ ነው። ሆኖም ሰላም ለመፍጠር እምቢ ማለት ግን አንድ ሰው ለራሱ ያለውን አክብሮት ሊጨምርለት ወይም ሊቀንስበት ይችላል? ምናልባትም የተደበቀ ኩራት ይኖረን ይሆን?

የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ያዕቆብ የጠበኝነት መንፈስና ኩራት ተዛማጅነት እንዳላቸው አሳይቷል። በአንዳንድ ክርስቲያኖች መካከል ያለውን “ጦርነትና ጠብ” ካጋለጠ በኋላ እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል።” (ያዕቆብ 4:1-3, 6) ትዕቢት ወይም ኩራት ሰላምን ለመፍጠር ጋሬጣ የሚሆነው እንዴት ነው?

ኩራት ሰዎችን ከሌሎች የተሻሉ እንደሆኑ እንዲሰማቸው ስለሚያደርጋቸው ይታለላሉ። እብሪተኛ የሆኑ ሰዎች ሌላውን ጥሩ ወይም መጥፎ ሰው ብለው መፈረጅ እንደሚችሉ ይሰማቸዋል። በምን መንገድ? አለመግባባት በሚነሳበት ጊዜ የሚቃወማቸውን ሰው ሊሻሻል እንደማይችል አድርገው ይመለከቱታል። ኩራት ያለባቸው አንዳንድ ሰዎች ከእነሱ ጋር የማይስማሙ ሰዎችን ይቅርታ ሊጠይቋቸው ቀርቶ ትኩረት ሊሰጣቸው እንደማይገባ ይሰማቸዋል። ከዚህ የተነሳ ኩሩ የሆኑ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ችግሩን በአግባቡ ከመፍታት ይልቅ ግጭቱ እንዲቀጥል ያደርጋሉ።

በአንድ አውራ ጎዳና ላይ ተጋርጦ መኪኖች እንዳይተላለፉ እንደሚያግድ እንቅፋት ሁሉ ኩራትም ብዙውን ጊዜ ሰላም ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት ያደናቅፋል። ስለዚህ ከአንድ ሰው ጋር ሰላም ለመፍጠር ብትፈልግም ይህን እንዳታደርግ ከውስጥህ የሚታገልህ ስሜት ካለ ምናልባት የኩራት ችግር ይኖርህ ይሆናል። ኩራትን እንዴት ልታሸንፈው ትችላለህ? የኩራት ተቃራኒ የሆነውን ትሕትናን በማዳበር ነው።

ተቃራኒውን አድርግ

መጽሐፍ ቅዱስ ትሕትና ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ባሕርይ እንደሆነ ይገልጻል። “ትሕትናና እግዚአብሔርን መፍራት፣ ሀብትን፣ ክብርንና ሕይወትን ያስገኛል።” (ምሳሌ 22:4) አምላክ ለትዕቢተኞችና ለትሑታን ያለውን አመለካከት ሲገልጽ መዝሙር 138:6 እንዲህ ይላል:- “እግዚአብሔር በከፍታ ስፍራ ቢሆንም፣ ዝቅ ያለውን ይመለከተዋል፤ ትዕቢተኛውን ከሩቅ ያውቀዋል።”

አብዛኞቹ ሰዎች ትሕትናን ከውርደት ጋር ያመሳስሉታል። የዓለም መሪዎችም የሚሰማቸው እንደዚህ ነው። የፖለቲካ መሪዎች ሕዝቡ በአጠቃላይ ለፈቃዳቸው ተገዥ ቢሆንም እንኳን ስህተታቸውን በትሕትና አምነው ለመቀበል አይፈልጉም። አንድ መሪ “ይቅርታ” ከጠየቀ ትልቅ ዜና ይሆናል። ቀደም ሲል የመንግሥት ባለ ሥልጣን የነበረ አንድ ሰው ከፍተኛ አደጋ በደረሰበት ወቅት ለፈጸመው ስህተት በቅርቡ ይቅርታ በመጠየቁ ምክንያት ጉዳዩ በጋዜጦች ላይ ዋና ዜና ሆኗል።

አንድ መዝገበ ቃላት ትሕትና ለሚለው ቃል “አለመኩራት፣ ራስን አለማስቀደም. . . ትሑትነት፣ ዝቅታ፣ የፈቃድ ውርደት” የሚል ፍቺ ሰጥቶታል። ስለዚህ ትሕትና የሚለው ቃል አንድ ሰው ስለራሱ ያለውን አመለካከት የሚያሳይ እንጂ ሌሎች ስለ እርሱ ያላቸውን አመለካከት የሚገልጽ አይደለም። ጥፋትን አምኖ መቀበልና ከልብ ይቅርታ መጠየቅ አንድን ሰው አያዋርደውም፤ ከዚህ ይልቅ መልካም ስም ያተርፍለታል። መጽሐፍ ቅዱስ “ከውድቀቱ በፊት ሰው ልቡ ይታበያል፤ ትሕትና ግን ክብርን ትቀድማለች” ይላል።—ምሳሌ 18:12

አንድ ታዛቢ ስህተታቸውን አምነው ይቅርታ ስለማይጠይቁ ፖለቲከኞች ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል:- “ስህተትን ማመን የድክመት ምልክት እንደሆነ አድርገው የሚያስቡ መሆኑ ያሳዝናል። ደካማና በራሳቸው የማይተማመኑ ሰዎች ‘ይቅርታ’ የሚለው ቃል ፈጽሞ አይወጣቸውም። ልበ ሰፊዎችና ደፋሮች የሆኑ ሰዎች ግን ‘ተሳስቻለሁ’ በማለታቸው ክብራቸው እንደቀነሰ አይሰማቸውም።” ፖለቲከኛ ባትሆንም ይህ አባባል ለአንተም ይሠራል። ኩራትን በትሕትና ለመተካት የተቻለህን ጥረት ካደረግክ ግጭት በሚፈጠርበት ጊዜ ሰላም ለማስፈን የተሻለ አጋጣሚ ይኖርሃል። አንድ ቤተሰብ የዚህን ምክር እውነተኝነት እንዴት እንደተገነዘቡ እንመልከት።

ጁሊ እና ወንድሟ ዊልያም በመካከላቸው በተፈጠረው አለመግባባት የተነሳ ተቀያየሙ። ከዚያም ዊልያም በጁሊና በባሏ በጆሴፍ በጣም በመናደዱ ከእነርሱ ጋር የነበረውን ግንኙነት ሙሉ በሙሉ አቋረጠ። እንዲያውም ጁሊና ጆሴፍ ከዚያ በፊት በተለያዩ ጊዜያት የሰጡትን ስጦታዎች በጠቅላላ መለሰላቸው። ወራት ባለፉ ቁጥር እነዚህ ወንድምና እህት በአንድ ወቅት የነበራቸው ወዳጅነት በጥላቻ ተተካ።

ሆኖም ጆሴፍ ማቴዎስ 5:23, 24ን በተግባር ለማዋል ወሰነ። የሚስቱን ወንድም በለዘበ መንፈስ ለመቅረብ ጥረት አደረገ፤ ስላስቀየመው ይቅርታ ለመጠየቅ በግሉ ደብዳቤዎችን ይልክለት ነበር። ሚስቱም ብትሆን ወንድሟን ይቅር እንድትለው ያበረታታት ነበር። ዊልያምም ጁሊና ጆሴፍ ሰላም ለመፍጠር ከልባቸው እንደሚፈልጉ ከጊዜ በኋላ በመገንዘቡ አመለካከቱን ቀየረ። ዊልያምና ሚስቱ ከጁሊና ከጆሴፍ ጋር ሲገናኙ ሁሉም ተቃቅፈው ይቅርታ ተጠያየቁ፤ በዚህ መንገድ የቀድሞ ወዳጅነታቸውን አደሱት።

ከሌላ ሰው ጋር ያለህን ቅራኔ ለማስወገድ የምትፈልግ ከሆነ የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርቶች በትዕግሥት ተግባራዊ እያደረግህ ከግለሰቡ ጋር ሰላም ለመፍጠር ጥረት አድርግ። ይሖዋም ይረዳሃል። አምላክ “ትእዛዜን ሰምተህ ብቻ ቢሆን ኖሮ፣ ሰላምህ እንደ ወንዝ . . . በሆነ ነበር” በማለት ለጥንቶቹ እስራኤላውያን የሰጠው ምክር ለአንተም እውነት ይሆንልሃል።—ኢሳይያስ 48:18

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በስታንሊ ክላውድና ሊን ኦልሰን ከተዘጋጀው ዘ ሙሮው ቦይስ—ፓዮኒርስ ኦን ዘ ፍሮንት ላየንስ ኦቭ ብሮድካስት ጆርናሊዝም ከተባለው መጽሐፍ የተወሰደ።

b አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አብዛኛውን ጊዜ ይቅርታ መጠየቅ የሻከረውን ግንኙነት አድሶ ሰላም ለመፍጠር ይረዳል