የቃላት ጦርነት ጎጂ የሆነው ለምንድን ነው?
የቃላት ጦርነት ጎጂ የሆነው ለምንድን ነው?
“በእናንተ መካከል ያለው ጦርነትና ጠብ ከየት የመጣ ነው?”—ያዕቆብ 4:1
የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ያዕቆብ ይህን ጥያቄ ያቀረበው አንድን ከተማ ድል ለማድረግ እየተዋጋ ለነበረ የሮም ጦር ሠራዊት አልነበረም፤ ወይም ደግሞ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት የአይሁድ የደፈጣ ተዋጊዎች ወይም ነፍሰ ገዳዮች ዓላማቸው ምን እንደሆነ መጠየቁም አይደለም። ከዚህ ይልቅ ያዕቆብ እየተናገረ የነበረው በሁለት ሰዎች መካከል ስለተፈጠረ አለመግባባት ነበር። ያዕቆብ ስለዚህ ጉዳይ መናገር ያስፈለገው ለምንድን ነው? ምክንያቱም የግል ግጭቶች የትላልቅ ጦርነቶችን ያህል አጥፊ ስለሆኑ ነው። እስቲ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎችን እንመልከት።
የፓትርያርኩ የያዕቆብ ልጆች ለወንድማቸው ለዮሴፍ የነበራቸው ከፍተኛ ጥላቻ እርሱን ለባርነት አሳልፈው እስከመሸጥ አድርሷቸዋል። (ዘፍጥረት 37:4-28) ከዚያም ቆየት ብሎ የእስራኤል ንጉሥ የነበረው ሳኦል ዳዊትን ለመግደል ሞክሮ ነበር። ለምን? ምክንያቱም በዳዊት ይቀና ስለነበረ ነው። (1 ሳሙኤል 18:7-11፤ 23:14, 15) ኤዎድያንና ሲንጤኪን በተባሉ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖሩ በነበሩ ክርስቲያን ሴቶች መካከል በተፈጠረው አለመግባባት ምክንያት ጉባኤው ሰላም አጥቶ ነበር።—ፊልጵስዩስ 4:2
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሰዎች በመካከላቸው የሚፈጠረውን አለመግባባት የሚፈቱት በሰይፍ ወይም በሽጉጥ ፍልሚያ በመግጠም ሆኗል። ብዙውን ጊዜ ከተፋላሚዎቹ አንዱ ይገደላል ወይም ክፉኛ ይቆስላል። ዛሬ ዛሬ ግን እርስ በርስ የተቃቃሩ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ የሚጠቀሙበት የጦር መሣሪያ አሽሙርና ሸካራ ቃላት ሆነዋል። እንደዚህ ባለው ፍልሚያ ደም ባይፈስም እንኳ የሰዎቹ ስሜት ሊጎዳና ስማቸው ሊጎድፍ ይችላል። ብዙውን ጊዜ በዚህ “ጦርነት” ንጹሐን ሰዎች ይሠቃያሉ።
ከጥቂት ዓመታት በፊት አንድ የአንግሊካን ቄስ፣ የቤተ ክርስቲያኗን ገንዘብ አላግባብ ተጠቅሞበታል በሚል ሌላኛውን ቄስ በወነጀለው ጊዜ ምን እንደተፈጠረ እንመልከት። በሁለቱ ቄሶች መካከል የተፈጠረው ግጭት አደባባይ ሲወጣ ምዕመኖቻቸው በሁለት ወገን ተከፈሉ። አንዳንድ ምዕመናን የሚቃወሙት ቄስ ፕሮግራሙን ሲመራ ላለመገኘት ወሰኑ። በሁለት ወገን የተከፈሉት ምዕመናን በጣም ከመካረራቸው የተነሳ ለአምልኮ ቤተ ክርስቲያን ሄደውም እንኳ አይነጋገሩም ነበር። በዚህ ላይ ባልደረባውን
የወነጀለው ቄስ ራሱ በጾታ ብልግና ሲወነጀል ደግሞ ግጭቱ ይበልጥ ተፋፋመ።የካንተርበሪው ሊቀ ጳጳስ በሁለቱ ቄሶች መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት “ካንሰር” እንዲሁም “የጌታችንን ስም ያዋረደ አሳፋሪ ቅሌት” ብለው የጠሩት ሲሆን ለችግሩ መቋጫ እንዲያበጁለት ሁለቱን ቄሶች ለምነዋቸዋል። በ1997 አንደኛው ቄስ ሥራውን ለመልቀቅ ተስማማ። ሌላኛው ግን ሥልጣኑን መልቀቅ ስላልፈለገ ዕድሜው ለጡረታ ደርሶ ቦታውን መልቀቅ ግድ እስኪሆንበት ድረስ ቆየ። የጡረታ ጊዜው ከደረሰ በኋላም እንኳ ነሐሴ 7, 2001፣ 70ኛ ዓመቱን እስከያዘበት ቀን ድረስ ሥልጣኑን ይዞ ቆይቷል። ዘ ቸርች ኦቭ ኢንግላንድ ኒውስ ፔፐር ይህ ቄስ ጡረታ የወጣበት ቀን “የቅዱስ” ቪክትሪሽየስ በዓል እንደሆነ ገልጿል። “ቅዱስ” ቪክትሪሽየስ ማን ነበሩ? በአራተኛው መቶ ዘመን የኖሩ በጦር ሠራዊት ውስጥ አልዋጋም በማለታቸው እንደተገረፉ የሚነገርላቸው ጳጳስ ነበሩ። ጋዜጣው “በቅዱስ” ቪክትሪሽየስና ጡረታ በወጣው ቄስ መካከል ያለውን የአመለካከት ልዩነት ሲገልጽ ‘“ቅዱስ” ቪክትሪሽየስ ከተዉት ምሳሌ በተቃራኒ ጡረታ የወጣው ቄስ ከባልደረባው ጋር ለመዋጋት ፈቃደኛ ነበረ’ ብሏል።
እነዚህ ሁለት ቄሶች የሮሜ 12:17, 18ን ምክር ቢሠሩበት ኖሮ ራሳቸውንም ሆነ ሌሎችን አይጎዱም ነበር። ጥቅሱ እንዲህ ይላል:- “ለማንም ክፉን በክፉ አትመልሱ፤ በሰው ሁሉ ፊት በጎ የሆነውን ነገር ለማድረግ ትጉ። ቢቻላችሁስ በበኩላችሁ ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ።”
አንተ በዚህ በኩል እንዴት ነህ? አንድ ሰው ሲያስቀይምህ ወዲያውኑ ቅር ተሰኝተህ የቃላት ጦርነት ትፈጥራለህ? ወይስ ሸካራ ቃላቶችን አስወግደህ ሰላም ለመፍጠር አመቺ ሁኔታ እንዲኖር ታደርጋለህ? አንድን ሰው ብታስቀይም ጊዜ ባለፈ መጠን ችግሩን እየረሳው ይሄዳል ብለህ ግለሰቡን ችላ ትለዋለህ? ወይስ ወዲያውኑ ይቅርታ ትጠይቃለህ? አንተ ራስህ ይቅርታ በመጠየቅም ሆነ ሌሎችን ይቅር በማለት ሰላም ለመፍጠር የምታደርገው ጥረት እርካታና ደስታ እንድታገኝ አስተዋጽኦ ያደርጋል። የሚቀጥለው ርዕስ እንደሚያሳየው የቆየ አለመግባባት ቢኖርም እንኳ በመጽሐፍ ቅዱስ ምክር አማካኝነት መፍትሔ ሊያገኝ ይችላል።