በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሳምሶን ከይሖዋ ባገኘው ብርታት ድል አደረገ!

ሳምሶን ከይሖዋ ባገኘው ብርታት ድል አደረገ!

ሳምሶን ከይሖዋ ባገኘው ብርታት ድል አደረገ!

በበቀል ስሜት የተነሳሱት ጠላቶቹ ዓይኑን ካጠፉ በኋላ የጉልበት ሥራ እንዲሠራ አደረጉት። ከዚያም በቤተ ጣዖቱ የተሰበሰበውን ሕዝብ ለማዝናናት ከእስር ቤት አውጥተው ወደዚያ አመጡት። በሺህ በሚቆጠሩ ተመልካቾች ፊት በማዞር መቀለጃ አደረጉት። ይህ እስረኛ፣ ወንጀለኛ አሊያም የጠላት ሠራዊት ጦር አዛዥ አይደለም። የይሖዋ አምላኪና በእስራኤል ለ20 ዓመታት መስፍን ሆኖ ያገለገለ ሰው ነው።

እስከ ዛሬ በምድር ላይ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ በአካላዊ ጥንካሬው ተወዳዳሪ ያልተገኘለት ሳምሶን ይህን የመሰለ ውርደት እንዴት ሊደርስበት ቻለ? ይህ ለየት ያለ ጥንካሬው ያድነው ይሆን? የሳምሶን ጥንካሬ ምስጢሩ ምን ነበር? ከእርሱ የሕይወት ታሪክ የምንማረው ነገር ይኖር ይሆን?

‘እስራኤልን መታደግ ይጀምራል’

እስራኤላውያን በተደጋጋሚ ከእውነተኛው አምልኮ ዘወር ብለዋል። በአንድ ወቅት “እንደ ገና በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸሙ፤ ስለዚህም እግዚአብሔር በፍልስጥኤማውያን እጅ አርባ ዓመት እንዲገዙ አሳልፎ ሰጣቸው።”—መሳፍንት 13:1

የሳምሶን ታሪክ የሚጀምረው የይሖዋ መልአክ፣ መካን ለሆነችው ለእስራኤላዊው ለማኑሄ ሚስት ተገልጦ ወንድ ልጅ እንደምትወልድ ባበሰራት ወቅት ነው። መልአኩ “በራሱ ላይ ምላጭ አይድረስበት” ሲል መመሪያ ከሰጣት በኋላ “ልጁ ከእናቱ ማሕፀን ጀምሮ ናዝራዊ በመሆን ለእግዚአብሔር የተለየ ይሆናልና፤ እስራኤልንም ከፍልስጥኤማውያን እጅ መታደግ ይጀምራል” አላት። (መሳፍንት 13:2-5) ሳምሶን ከመጸነሱ አስቀድሞ አንድ ለየት ያለ ሥራ እንደሚሰጠው ይሖዋ ወስኗል። ከተወለደበት ጊዜ ጀምሮ ናዝራዊ ማለትም ለአንድ ቅዱስ አገልግሎት የተለየ ይሆናል።

‘ልቤን የማረከችው እርሷ ናት’

ሳምሶን እያደገ ሄደ፤ “እግዚአብሔርም ባረከው።” (መሳፍንት 13:24) አንድ ቀን ሳምሶን ወደ አባቱና እናቱ ቀርቦ “በተምና አንዲት ወጣት ፍልስጥኤማዊት አይቻለሁና አሁኑኑ አጋቡኝ” አላቸው። (መሳፍንት 14:2) ይህን ሲሰሙ ክው ብለው እንደቀሩ ልትገምት ትችላለህ። ልጃቸው እስራኤላውያንን ከጨቋኞቻቸው እጅ ነፃ ከማውጣት ይልቅ ከእነርሱ ጋር በጋብቻ ለመተሳሰር ፈለገ። ጣዖት አምላኪ ከሆነ ሕዝብ መካከል ሚስት ማግባት ከአምላክ ሕግ ጋር የሚጋጭ ድርጊት ነው። (ዘፀአት 34:11-16) በዚህም ምክንያት ወላጆቹ “ከዘመዶችህ ወይም ከሕዝባችን ሁሉ መካከል ለአንተ የምትሆን ሴት መች ታጣችና ነው ወዳልተገረዙት ፍልስጥኤማውያን ሚስት ፍለጋ የሄድኸው?” በማለት ተቃወሙት። ይሁንና ሳምሶን አባቱን “ልቤን የማረከችው እርሷ ናትና እርሷን ኣጋባኝ” በማለት በአቋሙ ጸና።—መሳፍንት 14:3

ይህች ፍልስጥኤማዊት የሳምሶንን ‘ልብ የማረከችው’ ወይም ለእርሱ ተስማሚ የሆነችው በምን መንገድ ነው? በማክሊንቶክ እና ስትሮንግ የተዘጋጀው ሳይክሎፒዲያ እርሷ ልቡን የማረከችው “ቆንጆ፣ ማራኪና ውብ ስለሆነች ሳይሆን ተስማሚ ሆኖ ያገኛት ከአንድ ዓላማ ወይም ግብ አንፃር ነው” የሚል ሐሳብ ይሰጣል። ዓላማው ምን ነበር? መሳፍንት 14:4 ሳምሶን “ከፍልስጥኤማውያን ጋር ጠብ እንዲፈጠር” አጋጣሚ ይፈልግ እንደነበር ይገልጻል። ሳምሶን ሴቲቱን የፈለጋት ለዚህ ዓላማ ነበር። ሳምሶን ሙሉ ሰው ሲሆን ‘የእግዚአብሔር መንፈስ ያነቃቃው ጀመር’ ወይም እርምጃ እንዲወስድ አነሳሳው። (መሳፍንት 13:25) ስለዚህ ያልተለመደ የጋብቻ ጥያቄ እንዲያነሳም ሆነ በእስራኤል ላይ መስፍን ሆኖ ያከናወናቸውን ሥራዎች እንዲሠራ ያስቻለው የይሖዋ መንፈስ ነበር። ታዲያ ሳምሶን ሲጠብቀው የነበረውን አጋጣሚ አገኘ? በመጀመሪያ ይሖዋ መለኮታዊ ድጋፍ እንደሚሰጠው እንዴት እንዳረጋገጠለት እንመልከት።

ሳምሶን ወደፊት ሚስቱ ወደምትሆነው ሴት የመኖሪያ ከተማ ወደ ተምና እየሄደ ሳለ ያጋጠመውን ሁኔታ የመጽሐፍ ቅዱሱ ዘገባ እንዲህ በማለት ይገልጻል:- “[በተምናም] ከአንድ የወይን አትክልት ቦታ እንደ ደረሱ፣ ድንገት አንድ የአንበሳ ደቦል እያገሣ መጣበት። በዚህ ጊዜ የእግዚአብሔር መንፈስ በኀይል ወረደበት፤ . . . አንበሳውን . . . ገነጣጠለው።” ይህ አስደናቂ የኃይል መግለጫ የታየው ሳምሶን ብቻውን እያለ ነበር። ሁኔታውን የተመለከቱ የዓይን ምሥክሮች አልነበሩም። ሳምሶን አምላክ የሰጠውን ተልእኮ ለመፈጸም ችሎታ እንዳለው እንዲገነዘብ ከይሖዋ የመጣለት ማረጋገጫ ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሰ ነገር የለም፤ ይሁን እንጂ ሳምሶን ይህ ያልተለመደ ኃይል የእርሱ እንዳልሆነ ተረድቶ እንደሚሆን የተረጋገጠ ነው። ኃይሉን ያገኘው ከአምላክ መሆን አለበት። ከፊት ለፊቱ ለሚጠብቀው ሥራ ይሖዋ እንደሚረዳው በእርሱ ላይ ትምክህት ሊጥል ይችላል። ሳምሶን አንበሳውን መግደሉ እምነቱን ስላጠናከረለት፣ “ወደ ሴቲቱም ወረደ፤ ከእርሷም ጋር ተነጋገረ፤ እጅግም ወደዳት።”—መሳፍንት 14:5-7

ከዚያም ሳምሶን ሴቲቱን ወደ ቤቱ ሊያመጣት ሲሄድ “የአንበሳውንም በድን ለማየት ከመንገድ ዘወር አለ፤ በበድኑም ውስጥ የንብ መንጋ ሰፍሮ ተመለከተ፤ ማርም ነበረበት።” ከዚያም በሠርጉ ላይ አጃቢ እንዲሆኑት ለተሰጡት ሠላሳ ፍልስጥኤማውያን ይህንን ክስተት እንቈቅልሽ አድርጎ አቀረበላቸው:- “ከበላተኛው መብል፣ ከብርቱም ጣፋጭ ነገር ወጣ።” የዚህን እንቈቅልሽ ትክክለኛ ፍቺ ካገኙ 30 በፍታ ቀሚስና 30 የክት ልብስ ሊሰጣቸው፤ ካላገኙ ደግሞ እነርሱ በተመሳሳይ ሊሰጡት ተስማሙ። ፍልስጥኤማውያኑ ለሦስት ቀናት ያህል በእንቈቅልሹ ግራ ተጋቡ። በአራተኛው ቀን ፍቺውን እንድትጠይቅላቸው ሴቲቱን ማስፈራራት ጀመሩ። እንዲህም አሏት:- “የእንቈቅልሹን ፍች እንዲነግረን ባልሽን እስቲ አግባቢልን፤ ያለዚያ አንቺንም የአባትሽንም ቤተ ሰብ በእሳት እናቃጥላችኋለን።” ፍልስጥኤማውያን የራሳቸው ወገን በሆኑ ሰዎች ላይ እንዲህ የሚጨክኑ ከሆነ ረግጠው በሚገዟቸው እስራኤላውያን ላይ የሚያደርሱትን መከራ መገመት አያዳግትም!—መሳፍንት 14:8-15

በማስፈራሪያው የተደናገጠችው ሴት ሳምሶን መልሱን እንዲነግራት ትነዘንዘው ጀመር። ፍቺውን ከነገራት በኋላ ወዲያውኑ ሄዳ ለአጃቢዎቹ ነገረቻቸው፤ ይህም ለእርሱ ፍቅርም ሆነ ታማኝነት እንደሌላት ያሳያል። የእንቈቅልሹን ፍቺ በነገሩት ጊዜ እንዴት እንዳወቁ ስለተረዳ እንዲህ አላቸው:- “በጊደሬ ባላረሳችሁ፣ እንቈቅልሼንም ባልፈታችሁ።” ሳምሶን ይጠብቀው የነበረው ያ አጋጣሚ ተከፈተለት። “የእግዚአብሔር መንፈስ በሳምሶን ላይ በኀይል ወረደበት፤ ወደ አስቀሎናም ወርዶ ከሰዎቻቸው መካከል ሠላሳውን ገደለ፤ ያላቸውን ከገፈፈ በኋላ ልብሶቻቸውን አምጥቶ እንቈቅልሹን ለፈቱት ሰዎች ሰጣቸው።”—መሳፍንት 14:18, 19

ሳምሶን በአስቀሎና ሰዎቹን የገደለው በበቀል ስሜት ተነሳስቶ ነበር? አልነበረም። ከዚህ ይልቅ አምላክ በመረጠው አዳኝ በኩል የወሰደው እርምጃ ነበር። ይሖዋ ሳምሶንን በመጠቀም ሕዝቦቹን እየጨቆኑ ባሉት ላይ ውጊያ እንዲጀመር አድርጓል። ይህ ጠላትን የማጥቃት ዘመቻ ደግሞ መቀጠል አለበት። ሳምሶን ሚስቱን ለመጎብኘት በሄደበት ወቅት ደግሞ ጥቃት ለመሰንዘር የሚያስችለው ተጨማሪ አጋጣሚ አገኘ።

ብቻውን ጦርነት የገጠመ ሰው

ተምና እንደ ደረሰም የሚስቱ አባት ሳምሶን ጠልቷታል ብሎ ስላሰበ ሴቲቱን ለሌላ ሰው እንደዳራት ተረዳ። ሳምሶንም በጉዳዩ የተናደደ መሰለ። ሦስት መቶ ቀበሮዎችን ከያዘ በኋላ ጥንድ ጥንድ አድርጎ በጅራታቸው ላይ ችቦ አሰረባቸው። ቀበሮዎቹን ሲለቃቸው የፍልስጥኤማውያንን የዓመቱን ዋና ዋና ሰብሎች ማለትም የእህል አዝመራውን፣ የወይኑንና የወይራውን ተክል አቃጠሉት። በዚህ በጣም የተቆጡት ፍልስጥኤማውያን የጭካኔ ተግባር ፈጸሙ። ለደረሰባቸው ኪሳራ ተጠያቂዎቹ የሳምሶን ሚስትና አባቷ ናቸው ብለው በእሳት አቃጠሏቸው። የእነርሱ ጭካኔ የተንጸባረቀበት ብቀላ ለሳምሶን ዓላማ መንገድ ከፈተ። ከዚያም በምላሹ ጥቃት ሰንዝሮ ብዙዎችን ገደለ።—መሳፍንት 15:1-8

እስራኤላውያን ይሖዋ ሳምሶንን እየባረከው እንዳለ ተረድተው የፍልስጥኤማውያንን የጭቆና ቀንበር ከላያቸው ለማስወገድ ከእርሱ ጋር ግንባር ይፈጥሩ ይሆን? በጭራሽ። የይሁዳ ሰዎች ችግር ውስጥ ላለመግባት ሲሉ 3,000 የሚያክሉ ሰዎችን በመላክ አምላክ የመረጠውን መሪያቸውንና ነፃ አውጪያቸውን አስረው ለጠላቶቹ አሳልፈው ሰጡት። ይሁንና የእነዚህ እስራኤላውያን ታማኝ አለመሆን ሳምሶን በጠላቶቹ ላይ ተጨማሪ ጥፋት ማድረስ የሚችልበት ሌላ አጋጣሚ አስገኘለት። ለፍልስጥኤማውያን አሳልፈው ሊሰጡት ሲሉ “የእግዚአብሔር መንፈስ በሳምሶን ላይ በኀይል ወረደበት። እጆቹ የታሰሩበትም ገመድ እሳት ውስጥ እንደ ገባ የተልባ እግር ፈትል ሆኖ ከእጆቹ ላይ ወደቀ።” ከዚያም የአህያ መንጋጋ አንስቶ አንድ ሺህ የሚያክሉ ጠላቶቹን ገደለበት።—መሳፍንት 15:10-15

ሳምሶን ይሖዋን እንዲህ ሲል ለመነ:- “እነሆ፤ ለአገልጋይህ ይህን ታላቅ ድል አጐናጽፈሃል፤ ታዲያ አሁን በውሃ ጥም ልሙት? እንዴትስ በእነዚህ ባልተገረዙ ፍልስጥኤማውያን እጅ ልውደቅ?” ይሖዋ የሳምሶንን ጸሎት ሰምቶ ምላሽ ሰጠው። “እግዚአብሔርም . . . ዐለት ሰነጠቀለት፤ ከዚያም ውኃ ወጣ፤ ሳምሶንም ያን ሲጠጣ በረታ፤ መንፈሱም ታደሰ።”—መሳፍንት 15:18, 19

ሳምሶን ትኩረቱ ሁሉ ያረፈው ከፍልስጥኤማውያን ጋር በሚያደርገው ውጊያ ላይ ነበር። በጋዛ አንዲት ሴተኛ አዳሪ ቤት ለማረፍ የገባው ከአምላክ ጠላቶች ጋር ለመዋጋት በማሰብ ነበር። በጠላት ከተማ የሚያድርበት ቦታ ያስፈልገው ነበር፤ ማግኘት የሚችለው ደግሞ የሴተኛ አዳሪ ቤት ነው። ሳምሶን የሥነ ምግባር ብልግና የመፈጸም ሐሳብ አልነበረውም። እኩለ ሌሊት ሲሆን ከሴቲቱ ቤት በመውጣት የከተማይቱን ቅጥር በር ከሁለት መቃኖቹ ጋር ነቅሎ 60 ኪሎ ሜትር ያህል ርቆ ወደሚገኝ ኬብሮን አጠገብ ያለ ኮረብታ ጫፍ ድረስ ተሸክሞ ተጓዘ። ይህን ያደረገው ከአምላክ ባገኘው ድጋፍና እርሱ በሰጠው ኃይል ነበር።—መሳፍንት 16:1-3

በወቅቱ በነበሩት ለየት ያሉ ሁኔታዎች የተነሳ መንፈስ ቅዱስ በሳምሶን ላይ የሠራበት መንገድ ያልተለመደ ዓይነት ነበር። በዛሬው ጊዜ ያሉ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ይኸው መንፈስ ኃይል እንደሚሰጣቸው እምነት ሊጥሉ ይችላሉ። ይሖዋ ‘ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስ እንደሚሰጣቸው’ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ አረጋግጦላቸዋል።—ሉቃስ 11:13

ይሖዋ ‘ሳምሶንን የተወው’ ለምንድን ነው?

ከጊዜ በኋላ ደግሞ ሳምሶን ደሊላ ከምትባል ሴት ጋር ፍቅር ያዘው። ሕብረት የፈጠሩት አምስቱ የፍልስጥኤማውያን ከተሞች ገዢዎች ሳምሶንን የማጥፋት ከፍተኛ ፍላጎት ስለነበራቸው እንድትረዳቸው ጠየቋት። ወደ ደሊላ ቀርበው “ልናሸንፈው እንዴት እንደምንችልና የብርታቱ ታላቅነት ምስጢር ምን እንደ ሆነ እንዲያሳይሽ እስቲ አባብዪው” አሏት። አምስቱ ገዢዎች እርሷን ለማማለል እያንዳንዳቸው “አንድ ሺህ አንድ መቶ ሰቅል ጥሬ ብር” ለመስጠት ቃል ገቡላት።—መሳፍንት 16:4, 5

የሚሰጧት ጉቦ የብር ሰቅል ከሆነ 5,500 ሰቅል ማለት በጣም ብዙ ብር ነው። አብርሃም ሚስቱን ለመቅበር የመቃብር ቦታውን የገዛው በ400 ሰቅል ሲሆን የአንድ ባሪያ ዋጋ ደግሞ 30 ሰቅል ነበር። (ዘፍጥረት 23:14-20፤ ዘፀአት 21:32) አምስቱ የፍልስጥኤማውያን ከተሞች ገዢዎች ደሊላን የመጡባት ለወገኖቿ ባላት ታማኝነት ሳይሆን በገንዘብ መሆኑ ምናልባት እስራኤላዊት ልትሆን እንደምትችል ይጠቁማል። ያም ሆነ ይህ ደሊላ በሐሳቡ ተስማምታለች።

ሳምሶን፣ ደሊላ ላቀረበችለት ጥያቄ ሦስት ጊዜ የተሳሳተ መልስ ሰጣት፤ እርሷም ሦስት ጊዜ ለጠላቶቹ አሳልፋ ለመስጠት ሞከረች። ሆኖም “በሕይወት መኖሩን እስኪጠላ ድረስ ዕለት ዕለት በመጨቅጨቅ አሰለቸችው።” በመጨረሻ ሳምሶን ጸጉሩን ተላጭቶ እንደማያውቅ፣ ቢላጭ ግን ኃይሉን እንደሚያጣና እንደ ማንኛውም ሰው እንደሚሆን በመግለጽ እውነቱን ነገራት።—መሳፍንት 16:6-17

ይህንን ምስጢር መግለጡ ለውድቀቱ ምክንያት ሆነ። ደሊላም ጸጉሩ እንዲላጭ ሁኔታዎችን አመቻቸች። እርግጥ የሳምሶን ኃይል ቃል በቃል በጸጉሩ ላይ ነው ማለት አይደለም። ጸጉሩ ለአምላክ የተለየ ናዝራዊ መሆኑን የሚያሳይ ነገር ብቻ ነበር። ሳምሶን ጸጉሩን በመላጨት የናዝራዊነት መብቱን የሚያሳጣ ድርጊት በመፈጸሙ ‘እግዚአብሔር ትቶት ነበር።’ በዚህ ጊዜ ሳምሶን ፍልስጥኤማውያንን መቋቋም ስላልቻለ ዓይኑን አውጥተው እስር ቤት አስገቡት።—መሳፍንት 16:18-21

ከዚህ ታሪክ ትልቅ ትምህርት እናገኛለን! ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና እንደ ውድ ነገር መመልከት አይኖርብንም? ክርስቲያናዊ አቋማችንን በሆነ መንገድ ብናላላ የአምላክ በረከት አይለየንም ብለን እንዴት መጠበቅ እንችላለን?

‘ከፍልስጥኤማውያን ጋር አብሬ ልሙት’

በደስታ የሰከሩት ፍልስጥኤማውያን ሳምሶንን በማሸነፋቸው ለአምላካቸው ለዳጎን ምስጋና አቀረቡ። ይህንን ድል ለማክበር ምርኮኛቸውን ዳጎን ወደ ተቀመጠበት ቤተ መቅደስ አመጡት። ሳምሶን ግን የሽንፈቱን ትክክለኛ ምክንያት ያውቅ ነበር። ይሖዋ ለምን እንደተወው አውቋል፤ በመሆኑም ለሠራው ጥፋት ንስሐ ገባ። ሳምሶን እስር ቤት በነበረበት ወቅት ጸጉሩ እንደገና ማደግ ጀምሮ ነበር። በሺህ በሚቆጠሩ ፍልስጥኤማውያን ፊት በቆመበት በዚህ ጊዜ ምን ዓይነት እርምጃ ይወስድ ይሆን?

ሳምሶን እንዲህ ብሎ ጸለየ:- “ልዑል እግዚአብሔር ሆይ፤ አስበኝ፤ አምላክ ሆይ፤ እባክህን አንድ ጊዜ ብቻ ብርታት ስጠኝና ስለ ጠፉት ዐይኖቼ ፍልስጥኤማውያንን አንዴ ልበቀላቸው።” ሕንፃውን ደግፈው የያዙትን ሁለት ምሰሶዎች አቅፎ ይዞ ‘ባለ ኀይሉ ገፋቸው።’ ውጤቱስ ምን ሆነ? “ቤተ ጣዖቱ በገዦቹና በውስጡ በነበሩት በሌሎቹ ሰዎች ሁሉ ላይ ወደቀባቸው፤ ስለዚህ በሕይወት ከኖረበት ጊዜ ይልቅ በሞቱ ጊዜ ብዙ ሰው ገደለ።”—መሳፍንት 16:22-30

አካላዊ ጥንካሬን በተመለከተ ሳምሶንን የሚወዳደረው አንዳች ሰው አልነበረም። የሠራቸው ታላላቅ ሥራዎች በእርግጥም በዓይነታቸው ልዩ ናቸው። ከሁሉም በላይ ግን የይሖዋ ቃል ሳምሶንን ጠንካራ እምነት ከነበራቸው ሰዎች መካከል ይመድበዋል።—ዕብራውያን 11:32-34

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሳምሶን ጥንካሬ ምስጢሩ ምን ነበር?