‘በዋጋ ተገዝታችኋል’
‘በዋጋ ተገዝታችኋል’
“በዋጋ ተገዝታችኋልና፤ ስለዚህ በሰውነታችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ።”—1 ቆሮንቶስ 6:20
1, 2. (ሀ) በሙሴ ሕግ መሠረት እስራኤላውያን ባሮች ምን ሊደረግላቸው ይገባ ነበር? (ለ) ጌታውን የሚወድ አንድ ባሪያ ምን ምርጫ ነበረው?
“በጥንቱ ዓለም ሰዎችን ባሪያ አድርጎ መግዛት የተለመደና ከፍተኛ ተቀባይነት ያለው ድርጊት ነበር” በማለት ሆልመን ኢለስትሬትድ ባይብል ዲክሽነሪ ገልጿል። በመቀጠልም እንዲህ ይላል:- “የግብጽ፣ የግሪክና የሮም ኢኮኖሚ የተመሠረተው በባሪያ ጉልበት ላይ ነበር። ክርስትና በተቋቋመበት በመጀመሪያው መቶ ዘመን ኢጣሊያ ውስጥ ከሦስት ሰዎች መካከል አንዱ፣ በሌሎች አገሮች ደግሞ ከአምስት ሰዎች አንዱ ባሪያ ነበር።”
2 በጥንቷ እስራኤል ባርነት የነበረ ቢሆንም እንኳ የሙሴ ሕግ ዕብራውያን ባሮች ግፍ እንዳይፈጸምባቸው ያዝዝ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ሕጉ አንድ እስራኤላዊ ከስድስት ዓመት በላይ በባርነት ማገልገል እንደሌለበት ያዝዛል። በሰባተኛው ዓመት ላይ ባሪያው “ያለምንም ክፍያ በነጻ” መሄድ ይችላል። ሆኖም ለባሮች ሊደረግላቸው የሚገባውን ነገር በተመለከተ የወጣው ደንብ በጣም ፍትሐዊና ሰብዓዊነት የሚንጸባረቅበት በመሆኑ የሙሴ ሕግ የሚከተለውን መመሪያ ይዟል:- “አገልጋዩ፤ ‘ጌታዬን፤ ሚስቴንና ልጆቼን እወዳለሁ ነጻ ሆኜ አልሄድም’ ቢል፣ ጌታው ወደ ዳኞች ይውሰደው፤ ወደ በር ወይም ወደ በሩ መቃን ወስዶ ጆሮውን በወስፌ ይብሳው፤ ከዚያም ዕድሜ ዘመኑን የእርሱ አገልጋይ ይሆናል።”—ዘፀአት 21:2-6፤ ዘሌዋውያን 25:42, 43፤ ዘዳግም 15:12-18
3. (ሀ) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች የተቀበሉት ባርነት ምን ዓይነት ነበር? (ለ) አምላክን እንድናገለግል የሚያነሳሳን ምንድን ነው?
3 በፈቃደኝነት የሌላ ሰው አገልጋይ ለመሆን የሚያስችለው ዝግጅት እውነተኛ ክርስቲያኖች የሚገዙበትን የባርነት ዓይነት የሚያሳይ ጥላ ነበር። ለምሳሌ ያህል የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆኑት ጳውሎስ፣ ያዕቆብ፣ ጴጥሮስና ይሁዳ የአምላክና የክርስቶስ ባሮች ወይም አገልጋዮች እንደሆኑ ተናግረዋል። (ቲቶ 1:1፤ ያዕቆብ 1:1፤ 2 ጴጥሮስ 1:1፤ ይሁዳ 1) ጳውሎስ የተሰሎንቄ ክርስቲያኖች “ሕያውና እውነተኛ የሆነውን አምላክ ለማገልገል ከጣዖታት ወደ እግዚአብሔር” የተመለሱ መሆናቸውን አስታውሷቸዋል። (1 ተሰሎንቄ 1:9) እነዚህ ክርስቲያኖች በፈቃደኝነት የአምላክ ባሪያ እንዲሆኑ ያደረጋቸው ምን ነበር? እስራኤላዊው ባሪያ ነፃ መውጣት አልፈልግም እንዲል የሚያደርገው ውስጣዊ ግፊት ምን ነበር? ለጌታው የነበረው ፍቅር አይደለም? በተመሳሳይ ክርስቲያናዊ ባርነት የተመሠረተው ለአምላክ ባለን ፍቅር ላይ ነው። እውነተኛና ሕያው የሆነውን አምላክ ስናውቀውና ስናፈቅረው እርሱን ‘በፍጹም ልባችንና በፍጹም ነፍሳችን’ ለማገልገል እንነሳሳለን። (ዘዳግም 10:12, 13) ይሁንና የአምላክና የክርስቶስ ባሪያ መሆን ምን ነገሮችን ያካትታል? ይህ በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ላይ ምን ለውጥ ያመጣል?
“ሁሉንም ነገር ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት”
4. የአምላክና የክርስቶስ ባሮች የምንሆነው እንዴት ነው?
4 ባሪያ የሚለው ቃል “የአንድ ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ግለሰቦች ሕጋዊ ንብረት የሆነና የታዘዘውን ሁሉ የመፈጸም ግዴታ ያለበት ሰው” የሚል ፍቺ ተሰጥቶታል። ሕይወታችንን ለይሖዋ ወስነን ስንጠመቅ የእርሱ ሕጋዊ ንብረት እንሆናለን። ሐዋርያው ጳውሎስ “እናንተም የራሳችሁ አይደላችሁም፤ በዋጋ ተገዝታችኋልና” ሲል ገልጿል። (1 ቆሮንቶስ 6:19, 20) ይህ ዋጋ የኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት እንደሆነ ግልጽ ነው። በመንፈስ የተቀባን ክርስቲያኖችም ሆን ምድራዊ ተስፋ ያለን፣ አምላክ አገልጋዮቹ አድርጎ የተቀበለን በዚህ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ነው። (ኤፌሶን 1:7፤ 2:13፤ ራእይ 5:9) በመሆኑም ከተጠመቅንበት ጊዜ አንስቶ “የይሖዋ ነን።” (ሮሜ 14:8 NW) የተገዛነው በኢየሱስ ክርስቶስ ክቡር ደም ስለሆነ የእርሱም ባሮች እንሆናለን። ከዚህም በተጨማሪ ትእዛዛቱን የማክበር ግዴታ አለብን።—1 ጴጥሮስ 1:18, 19
5. የይሖዋ ባሮች እንደመሆናችን መጠን ተቀዳሚ ግዴታችን ምንድን ነው? ይህን መወጣት የምንችለውስ እንዴት ነው?
5 አንድ ባሪያ ጌታውን የመታዘዝ ግዴታ አለበት። ባርነታችን ከፈቃደኝነት መንፈስና ለጌታ ካለን ፍቅር የሚመነጭ ነው። አንደኛ ዮሐንስ 5:3 “እግዚአብሔርን መውደድ ትእዛዛቱን መፈጸም ነውና። ትእዛዛቱም ከባድ አይደሉም” ይላል። ስለዚህ ታዛዥ መሆናችን ይሖዋን እንደምንወድና ለእርሱ በፈቃደኝነት እንደምንገዛ ያሳያል። ይህም በምናደርገው ነገር ሁሉ በግልጽ ይታያል። ጳውሎስ “ስትበሉም ሆነ ስትጠጡ፣ ወይም ማንኛውንም ነገር ስታደርጉ ሁሉንም ነገር ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት” ብሏል። (1 ቆሮንቶስ 10:31) በዕለት ተዕለት ሕይወታችን፣ በትንንሽ ነገሮች ጭምር ‘ጌታን እንደምናገለግል’ ማሳየት እንፈልጋለን።—ሮሜ 12:11
6. የአምላክ ባሪያዎች መሆናችን በሕይወታችን በምናደርጋቸው ውሳኔዎች ላይ ለውጥ የሚያመጣው እንዴት ነው? በምሳሌ አስረዳ።
6 ለምሳሌ ያህል ውሳኔ ስናደርግ በሰማይ የሚኖረውን የጌታችንን የይሖዋን ፈቃድ ግምት ውስጥ ለማስገባት ጠንቃቆች መሆን እንፈልጋለን። (ሚልክያስ 1:6) ከባድ ውሳኔዎች ሲያጋጥሙን ለአምላክ ያለን ታዛዥነት ሊፈተን ይችላል። በዚህ ጊዜ “ተንኰለኛ” እና “ክፉ” የሆነውን የልባችንን ዝንባሌ ከመከተል ይልቅ አምላክ የሚሰጠንን ምክር እንሰማለን? (ኤርምያስ 17:9 የ1954 ትርጉም) ነጠላ ክርስቲያን የሆነችው ሜሊሳ ከተጠመቀች ብዙም ሳይቆይ አንድ ወጣት የፍቅር ስሜት ያሳያት ጀመር። ይህ ወጣት ሲያዩት ጨዋ ይመስላል፤ ደግሞም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ያጠናል። ይሁን እንጂ አንድ የጉባኤ ሽማግሌ የምናገባው ሰው “በጌታ መሆን” እንዳለበት ይሖዋ የሰጠውን መመሪያ መከተል ጥበብ እንደሆነ ለሜሊሳ ነገራት። (1 ቆሮንቶስ 7:39፤ 2 ቆሮንቶስ 6:14) ሜሊሳ “ምክሩን በሥራ ማዋል በጣም ከብዶኝ ነበር” ስትል በግልጽ ተናግራለች። “ሆኖም የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ቃል የገባሁ በመሆኔ የእርሱን ግልጽ መመሪያ መታዘዝ እንዳለብኝ ወሰንኩ።” ከጊዜ በኋላ የተከሰተውን ሁኔታ በማስታወስ እንዲህ ትላለች:- “ምክሩን ተግባራዊ በማድረጌ በጣም ደስተኛ ነኝ። ያ ወጣት ብዙም ሳይቆይ ጥናቱን አቋረጠ። ከእርሱ ጋር የነበረኝን ግንኙነት ቀጥዬበት ቢሆን ኖሮ በአሁኑ ወቅት በይሖዋ የማያምን ባል ይኖረኝ ነበር።”
7, 8. (ሀ) ሰዎችን ስለማስደሰት ከልክ በላይ መጨነቅ የሌለብን ለምንድን ነው? (ለ) የሰውን ፍርሃት እንዴት ማሸነፍ እንደሚቻል ግለጽ።
7 የአምላክ ባሪያዎች ስለሆንን የሰዎች ባሪያ መሆን የለብንም። (1 ቆሮንቶስ 7:23) እርግጥ ማናችንም ብንሆን በሰዎች ዘንድ መጠላት አንፈልግም። ሆኖም የክርስቲያኖች የአቋም ደረጃ ዓለም ከሚከተለው የተለየ መሆኑን መዘንጋት የለብንም። ጳውሎስ “ጐሽ ለመባል የምሻው በሰዎች ዘንድ ነው?” ሲል ጠይቋል። ከዚያም “ሰዎችን ደስ ለማሰኘት የምጥር ብሆን ኖሮ፣ የክርስቶስ አገልጋይ ባልሆንሁ ነበር” የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሷል። (ገላትያ 1:10) እኩዮቻችን ለሚያሳድሩብን ጫና ተሸንፈን ሰዎችን ደስ ማሰኘት አንፈልግም። ታዲያ ሌሎችን መስለን እንድንኖር ጫና ሲደረግብን ምን ማድረግ እንችላለን?
8 በስፔይን የምትኖረውን የወጣቷ ኤሌናን ምሳሌ ተመልከት። በርካታ የክፍል ጓደኞቿ ደም ለጋሾች ነበሩ። የይሖዋ ምሥክር የሆነችው ኤሌና ደም እንደማትሰጥም ሆነ እንደማትወስድ ያውቃሉ። ለክፍሉ ተማሪዎች በሙሉ አመለካከቷን የምታስረዳበት አጋጣሚ ስታገኝ ንግግር ለማቅረብ ፈቃደኛ ሆነች። ኤሌና እንዲህ ትላለች:- “እውነቱን ለመናገር ነገሩን ሳስበው በጣም ተጨነቅሁ። ሆኖም ጥሩ ዝግጅት አደረግሁ፤ በውጤቱም እጅግ ተደሰትኩ። አብረውኝ የሚማሩ ብዙ ልጆች በአክብሮት ይመለከቱኝ ጀመር፤ አስተማሪዬም የማከናውነውን ሥራ እንደሚያደንቅ ነገረኝ። ከሁሉ በላይ የይሖዋን ስም በማስከበሬና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ አቋሜን በግልጽ ማስረዳት በመቻሌ ውስጣዊ እርካታ ተሰማኝ።” (ዘፍጥረት 9:3, 4፤ የሐዋርያት ሥራ 15:28, 29) በእርግጥም የአምላክና የክርስቶስ ባሪያዎች በመሆናችን ከሌሎች እንለያለን። ይሁን እንጂ ስለ እምነታችን በአክብሮት ለመናገር ዝግጁ ከሆንን አብዛኛውን ጊዜ የሌሎችን አክብሮት እናተርፋለን።—1 ጴጥሮስ 3:15
9. ለሐዋርያው ዮሐንስ ከተገለጠለት መልአክ ምን እንማራለን?
9 በተጨማሪም የአምላክ ባሪያዎች መሆናችንን ማስታወሳችን ትሑት እንድንሆን ሊረዳን ይችላል። በአንድ ወቅት ሐዋርያው ዮሐንስ ስለ ሰማያዊቷ ኢየሩሳሌም ባየው አስገራሚ ራእይ በአድናቆት ከመዋጡ የተነሳ የአምላክ ቃል አቀባይ ሆኖ ባገለገለው መልአክ ፊት ለመስገድ እግሩ ሥር ተደፋ። መልአኩ “ተው!፤ ይህን አታድርግ! እኔ ከአንተና ከወንድሞችህ ከነቢያት እንዲሁም የዚህን መጽሐፍ ቃል ከሚጠብቁት ሁሉ ጋር አገልጋይ ነኝ፤ ለእግዚአብሔር ስገድ” አለው። (ራእይ 22:8, 9) ይህ መልአክ ለአምላክ ባሮች በሙሉ ግሩም ምሳሌ ትቷል! አንዳንድ ክርስቲያኖች በጉባኤ ውስጥ ልዩ የኃላፊነት መብቶች ይኖሯቸው ይሆናል። ይሁንና ኢየሱስ “ከእናንተ ትልቅ መሆን የሚፈልግ አገልጋያችሁ ይሁን፤ የበላይ ለመሆን የሚሻም የእናንተ የበታች ይሁን” ብሏል። (ማቴዎስ 20:26, 27) የኢየሱስ ተከታዮች እንደመሆናችን መጠን ሁላችንም ባሮች ነን።
“ልናደርገው የሚገባንን ተግባር ፈጽመናል”
10. ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች አንዳንድ ጊዜ የአምላክን ፈቃድ ማድረግ ይከብዳቸው እንደነበር የሚያሳዩ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምሳሌዎች ተናገር።
10 ፍጽምና የሚጎድላቸው ሰዎች አንዳንድ ጊዜ የአምላክን ፈቃድ ማድረግ ሊከብዳቸው ይችላል። ይሖዋ ነቢዩ ሙሴን ወደ ግብጽ ሄዶ በባርነት ቀንበር ሥር የነበሩትን እስራኤላውያን ነፃ እንዲያወጣ ሲነግረው ለመታዘዝ አቅማምቶ ነበር። (ዘፀአት 3:10, 11፤ 4:1, 10) ዮናስ ለነነዌ ሕዝብ የፍርድ መልእክት እንዲያውጅ ተልእኮ ሲሰጠው “ከእግዚአብሔር ፊት ኰበለለ፤ ወደ ተርሴስም ለመሄድ ተነሣ።” (ዮናስ 1:2, 3) የነቢዩ ኤርምያስ ጸሐፊ የነበረው ባሮክ ሥራው እንደሰለቸው በምሬት ገልጿል። (ኤርምያስ 45:2, 3) የግል ፍላጎታችን ወይም ምርጫችን የአምላክን ፈቃድ እንዳናደርግ የሚያግደን ከሆነ ምን ማድረግ ይኖርብናል? የዚህን ጥያቄ መልስ ኢየሱስ ከተናገረው አንድ ምሳሌ ላይ ማግኘት እንችላለን።
11, 12. (ሀ) ሉቃስ 17:7-10 ላይ የሚገኘውን የኢየሱስን ምሳሌ በአጭሩ ተናገር። (ለ) ኢየሱስ ከተናገረው ምሳሌ የምናገኘው ትምህርት ምንድን ነው?
11 ኢየሱስ የጌታውን በጎች ቀኑን ሙሉ መስክ ላይ ሲያግድ ስለዋለ አንድ ባሪያ ተናገረ። ባሪያው ለ12 ሰዓት ያህል ከባድ ሥራ ሲሠራ ውሎ ድክም ብሎት ቤት ሲደርስ ጌታው ቁጭ ብለህ እራት ብላ አላለውም። ከዚህ ይልቅ ጌታው “እራቴን እንድበላ አዘጋጅልኝ፣ እኔ እስክበላና እስክጠጣ ድረስ ታጥቀህ አገልግለኝ፤ ከዚያ በኋላ አንተ ደግሞ ትበላለህ” አለው። ባሪያው የራሱን ፍላጎት ማሟላት የሚችለው ጌታውን አገልግሎ ከጨረሰ በኋላ ነው። ኢየሱስ ምሳሌውን የደመደመው “ስለዚህ እናንተም የታዘዛችሁትን ሁሉ ባደረጋችሁ ጊዜ፣ ‘ከቊጥር የማንገባ አገልጋዮች ነን፤ ልናደርገው የሚገባንን ተግባር ፈጽመናል’ በሉ” በማለት ነበር።—ሉቃስ 17:7-10
12 ኢየሱስ ይህን ምሳሌ የተናገረው ይሖዋ እርሱን ለማገልገል የምናከናውነውን ሥራ አቅልሎ እንደሚመለከት ለማሳየት አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር ዐመፀኛ አይደለም፤ እርሱ ሥራችሁን እንዲሁም . . . ስለ ስሙ ያሳያችሁትን ፍቅር አይረሳም” በማለት በግልጽ ይናገራል። (ዕብራውያን 6:10) ስለዚህ ኢየሱስ የተናገረው ምሳሌ የሚያስተላልፈው መልእክት አንድ ባሪያ ራሱን የማስደሰት ወይም የራሱን ፍላጎት የማስቀደም መብት የለውም የሚል ነው። ራሳችንን ለአምላክ በወሰንንበትና የእርሱ ባሪያዎች ለመሆን በመረጥንበት ወቅት የእርሱን ፈቃድ ከእኛ ፍላጎት ለማስቀደም ተስማምተናል። ከእኛ ፈቃድ ይልቅ የአምላክን ፈቃድ ማስቀደም ይኖርብናል።
13, 14. (ሀ) ከራሳችን ስሜት ጋር መታገል የሚኖርብን የትኞቹ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ነው? (ለ) ለአምላክ ፈቃድ በደስታ መገዛት ያለብን ለምንድን ነው?
13 የአምላክን ቃልና “ታማኝና ልባም ባሪያ” የሚያዘጋጃቸውን ጽሑፎች አዘውትሮ ማጥናት ከፍተኛ ጥረት ይጠይቅብን ይሆናል። (ማቴዎስ 24:45 የ1954 ትርጉም) በተለይ ማንበብ የማንወድ ከሆነ ወይም የምናነበው ጽሑፍ የሚያብራራው “የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር” ከሆነ ራሳችንን ማስገደድ ሊኖርብን ይችላል። (1 ቆሮንቶስ 2:10) በመሆኑም የግል ጥናት የምናደርግበት ጊዜ መመደብ አይኖርብንም? አርፎ ለመቀመጥና የምናጠናውን ጽሑፍ በቂ ጊዜ ወስደን ለማንበብ ራሳችንን ማስለመድ ያስፈልገን ይሆናል። እንዲህ ሳናደርግ ‘የበሰሉ ሰዎች የሚመገቡትን ጠንካራ ምግብ’ የመመገብ ፍላጎት እንዴት ልናዳብር እንችላለን?—ዕብራውያን 5:14
14 ወደ ቤታችን የመጣነው ቀኑን ሙሉ ስንሠራ ውለን ደክሞን ቢሆንስ? ከጉባኤ ስብሰባ ላለመቅረት ራሳችንን ማስገደድ ይኖርብን ይሆናል። ወይም ደግሞ ለማናውቃቸው ሰዎች መስበክ ደስ ላይለን ይችላል። ጳውሎስ እንኳ አንዳንድ ጊዜ ምሥራቹን የምንሰብከው ‘በፈቃደኝነት ላይሆን’ እንደሚችል ተገንዝቧል። (1 ቆሮንቶስ 9:17) ይሁን እንጂ የምንወደው ጌታችን ይሖዋ እነዚህን ነገሮች ማድረግ እንዳለብን ስለነገረን ከማድረግ ወደኋላ አንልም። ጥረት ቢጠይቅብንም እንኳ አጥንተን ስንጨርስ እንዲሁም ስብሰባ ተገኝተንና አገልግሎት ወጥተን ስንመለስ ሁልጊዜ እርካታና ደስታ አይሰማንም?—መዝሙር 1:1, 2፤ 122:1፤ 145:10-13
“ወደ ኋላ” አትመልከቱ
15. ኢየሱስ ለአምላክ በመገዛት ረገድ ምን ምሳሌ ትቷል?
15 ኢየሱስ ክርስቶስ በሰማይ ለሚኖረው አባቱ ተገዥነቱን በላቀ መንገድ አሳይቷል። ለደቀ መዛሙርቱ “ከሰማይ የወረድሁት የራሴን ፈቃድ ለማድረግ ሳይሆን፣ የላከኝን የእርሱን ፈቃድ ለመፈጸም ነውና” ሲል ነግሯቸዋል። (ዮሐንስ 6:38) በጌቴሴማኒ መናፈሻ በጣም ተጨንቆ በነበረበት ወቅት “አባቴ ሆይ፤ ቢቻል ይህ ጽዋ ከእኔ ይለፍ፤ ነገር ግን እኔ እንደምፈልገው ሳይሆን አንተ እንደምትፈልገው ይሁን” በማለት ጸልዮአል።—ማቴዎስ 26:39
16, 17. (ሀ) ትተናቸው ለመጣነው ነገሮች ምን አመለካከት ሊኖረን ይገባል? (ለ) ጳውሎስ በዓለም ሊያገኝ የሚችለውን ክብር “እንደ ጒድፍ” መቁጠሩ ትክክል የነበረው ለምን እንደሆነ ግለጽ።
16 ኢየሱስ ክርስቶስ የአምላክ ባሮች ለመሆን ባደረግነው ውሳኔ እንድንጸና ይፈልጋል። “ዕርፍ ጨብጦ ወደ ኋላ የሚመለከት ሰው ለእግዚአብሔር መንግሥት የተገባ አይደለም” ብሏል። (ሉቃስ 9:62) የይሖዋ አገልጋዮች ከሆንን በኋላ ትተነው ስለመጣነው ነገር ነጋ ጠባ ማሰብ ተገቢ አይደለም። ከዚህ ይልቅ የአምላክ ባሮች ለመሆን በመምረጣችን ያገኘነውን ጥቅም በአድናቆት መመልከት ይኖርብናል። ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች “ለእርሱ ብዬ ሁሉን ነገር የተውሁለትን፣ ወደር የሌለውን ጌታዬን ክርስቶስ ኢየሱስን ከማወቅ ታላቅነት ጋር ሳነጻጽር፣ ሁሉንም ነገር እንደ ጒድለት እቈጥረዋለሁ፤ ለእርሱ ስል ሁሉን አጥቻለሁ፤ ክርስቶስን አገኝ ዘንድ ሁሉን እንደ ጒድፍ እቈጥራለሁ” ሲል ጽፏል።—ፊልጵስዩስ 3:8
17 ጳውሎስ የአምላክ ባሪያ በመሆን ለሚያገኛቸው መንፈሳዊ በረከቶች ሲል እንደ ጉድፍ ቆጥሮ የተዋቸውን ነገሮች አስብ። በዓለም ላይ ሊያገኝ የሚችለውን የተመቻቸ ኑሮ ብቻ ሳይሆን ወደፊት የአይሁድ እምነት መሪ የመሆን አጋጣሚውን ጭምር ትቷል። ጳውሎስ የአይሁድ እምነቱን እንደያዘ ቢቀጥል ኖሮ የአስተማሪው የገማልያል ልጅ ስምዖን ያገኘው ዓይነት ሥልጣን ሊይዝ ይችል ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 22:3፤ ገላትያ 1:14) ስምዖን የፈሪሳውያን መሪ ለመሆን በቅቶ ነበር። ከዚህም በላይ አንዳንድ ወደኋላ ያለባቸው ጉዳዮች የነበሩ ቢሆንም ከ66-70 ከክርስቶስ ልደት በኋላ አይሁዶች በሮም ላይ ባስነሱት ዓመጽ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል። በዚያ ግጭት ላይ በአክራሪ አይሁዳውያን አሊያም በሮማውያን ሠራዊት እጅ ተገድሏል።
18. መንፈሳዊ ነገሮችን ማስቀደም በረከት እንዳለው የሚያሳይ አንድ ምሳሌ ተናገር።
18 የጳውሎስን ምሳሌ የተከተሉ ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች አሉ። ጄን እንዲህ ትላለች:- “ትምህርት ከጨረስኩ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ለንደን ውስጥ ለአንድ የታወቀ ጠበቃ ዋና ጸሐፊ ሆኜ ተቀጠርኩ። ሥራውን የወደድኩት ከመሆኑም ሌላ ብዙ ገንዘብም አገኝ ነበር። ልቤ ግን በይሖዋ አገልግሎት ብዙ መሥራት እንደምችል ይነግረኝ ስለነበር በመጨረሻ ሥራውን ለቅቄ በአቅኚነት ማገልገል ጀመርኩ። ከ20 ዓመት ገደማ በፊት ይህን እርምጃ በመውሰዴ በጣም አመስጋኝ ነኝ! የሙሉ ጊዜ አገልግሎት፣ የትኛውም የጸሐፊነት ሥራ ሊያስገኝልኝ ከሚችለው በላይ ሕይወቴን አስደሳች አድርጎልኛል። የይሖዋ ቃል የአንድን ሰው ሕይወት እንዴት እንደሚለውጥ ከማየት የበለጠ የሚያስደስት ነገር የለም። በዚህ ሥራ ድርሻ ማበርከት መቻል ትልቅ መብት ነው። ለይሖዋ የምንሰጠው ነገር ከእርሱ ከምንቀበለው ጋር ሲወዳደር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።”
19. ቁርጥ ውሳኔያችን ምን መሆን አለበት? ለምንስ?
19 ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ሁኔታችን ይለወጥ ይሆናል። ይሁን እንጂ ለአምላክ የገባነው ቃል ፈጽሞ አይለወጥም። የይሖዋ ባሮች መሆናችን እንደተጠበቀ ሆኖ ጊዜያችንን፣ ጉልበታችንን፣ ችሎታችንንና ያሉንን ሌሎች ነገሮች ከሁሉ በተሻለ መንገድ እንዴት እንደምንጠቀምባቸው የመወሰን ነፃነት ሰጥቶናል። በመሆኑም በዚህ ረገድ የምናደርጋቸው ውሳኔዎች ለአምላክ ያለንን ፍቅር ሊያሳዩ ይችላሉ። እንዲሁም ምን ያህል መሥዋዕት ለመክፈል ፈቃደኞች እንደሆንን ያሳያሉ። (ማቴዎስ 6:33) ያለንበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን ለይሖዋ ምርጣችንን ለመስጠት ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ አይኖርብንም? ጳውሎስ “ለመስጠት በጎ ፈቃድ ካለን ስጦታው ተቀባይነት የሚያገኘው ባለን መጠን ስንሰጥ እንጂ፣ በሌለን መጠን ለመስጠት ስንሞክር አይደለም” ሲል ጽፏል።—2 ቆሮንቶስ 8:12
‘የምትሰበስቡት ፍሬ’
20, 21. (ሀ) የአምላክ ባሮች የሚያፈሩት ፍሬ ምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ ምርጣቸውን የሚሰጡትን ሰዎች የሚክሳቸው እንዴት ነው?
20 የአምላክ ባሪያ መሆን ለጭቆና አይዳርግም። ከዚህ በተቃራኒ ደስታ ከሚያሳጣን ጎጂ የባርነት ዓይነት እንድናመልጥ ያስችለናል። ጳውሎስ “ከኀጢአት ነጻ ወጥታችሁ የእግዚአብሔር ባሮች ሆናችኋል፤ የምትሰበስቡትም ፍሬ ወደ ቅድስና ያመራል፤ መጨረሻውም የዘላለም ሕይወት ነው” ሲል ጽፏል። (ሮሜ 6:22) የአምላክ ባሮች መሆናችን በቅድስና መንገድ ፍሬ ያስገኛል የሚለው አነጋገር ቅዱስ ወይም በሥነ ምግባር ንጹሕ የሆነ ኑሮ መኖራችን ጥቅም እንደሚያስገኝልን ያሳያል። ከዚህ በተጨማሪ ወደፊት የዘላለም ሕይወት ያስገኝልናል።
21 ይሖዋ ለባሮቹ ልግስና ያሳያቸዋል። እርሱን ለማገልገል አቅማችን የፈቀደውን ስናደርግ “የሰማይን መስኮት” ከፍቶ ‘ማስቀመጫ እስክናጣ ድረስ የተትረፈረፈ በረከት’ ያፈስልናል። (ሚልክያስ 3:10) የይሖዋ ባሪያ ሆኖ እርሱን ለዘላለም ማገልገል በጣም ያስደስታል!
ታስታውሳለህ?
• የአምላክ ባሮች ለመሆን ራሳችንን የምናቀርበው ለምንድን ነው?
• ለአምላክ ፈቃድ እንደምንገዛ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
• ከእኛ ፍላጎት ይልቅ የይሖዋን ፈቃድ ለማስቀደም ዝግጁ መሆን ያለብን ለምንድን ነው?
• ‘ወደ ኋላ መመልከት’ የሌለብን ለምንድን ነው?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በእስራኤል የነበረው በፈቃደኝነት ባሪያ ለመሆን የሚያስችለው ዝግጅት ለክርስቲያናዊ ተገዥነት ጥላ ነበር
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ስንጠመቅ የአምላክ ባሮች እንሆናለን
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ክርስቲያኖች የአምላክን ፈቃድ ያስቀድማሉ
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሙሴ የተሰጠውን ተልእኮ ለመቀበል አቅማምቶ ነበር