በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኢየሱስ ክርስቶስ በአንተ ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል?

ኢየሱስ ክርስቶስ በአንተ ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል?

ኢየሱስ ክርስቶስ በአንተ ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል?

ቀደም ባለው ርዕስ ውስጥ ከተመለከትናቸው ሐሳቦች አንጻር ስናየው የኢየሱስ ትምህርቶች በመላው ዓለም ላይ ተጽዕኖ ማሳደራቸው የሚያጠራጥር ነው? እንግዲያው እያንዳንዳችን “የኢየሱስ ትምህርቶች በእኔ ላይ ምን ተጽዕኖ አሳድረዋል?” ብለን ራሳችንን መጠየቅ ይገባናል።

የኢየሱስ ትምህርቶች በርካታ ርዕሰ ጉዳዮችን ይዳስሳሉ። ትምህርቶቹ የሚያስተላልፏቸው ጠቃሚ ሐሳቦች በሁሉም የሕይወትህ ዘርፍ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ። እስቲ ኢየሱስ በሕይወት ውስጥ ቅድሚያ ሊሰጠው ስለሚገባ ነገር፣ ከአምላክ ጋር ስለ መወዳጀት፣ ከሌሎች ጋር ጥሩ ወዳጅነት ስለመመሥረት፣ ችግር እንዲፈጠር ምክንያት የሚሆኑ ነገሮችን ማስወገድ ስለሚቻልበት መንገድና ከመጥፎ ድርጊቶች ስለመራቅ በሰጣቸው ትምህርቶች ላይ እናተኩር።

በሕይወት ውስጥ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ነገሮች

ያለንበት ሩጫ የበዛበት ዓለም በአብዛኛው ጊዜያችንንና ኃይላችንን የሚያሟጥጡ ነገሮች በማቅረብ መንፈሳዊ ጉዳዮችን ችላ እንድንል ያደርገናል። እስቲ አንድ በሃያዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኝ ወጣትን ሁኔታ እንመልከት። ይህ ወጣት ስለ መንፈሳዊ ጉዳዮች አንስቶ መጫወት የሚወድና ለሚሰማቸው መንፈሳዊ ነገሮች ጥልቅ አክብሮት ያለው ቢሆንም እንዲህ በማለት ምሬቱን ተናግሯል:- “አዘውትሬ መንፈሳዊ ጉዳዮችን የማከናውንበት ጊዜ የለኝም። በሳምንት ስድስት ቀን እሠራለሁ። የእረፍት ቀኔ እሁድ ብቻ ሲሆን ማድረግ ያሉብኝን ነገሮች ከፈጸምኩ በኋላ ድክም ይለኛል።” አንተም ተመሳሳይ ችግር ካለብህ ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ ካስተማረው ትምህርት ጥቅም ልታገኝ ትችላለህ።

ኢየሱስ ሊሰሙት ለተሰበሰቡት ሰዎች እንዲህ አላቸው:- “ስለ ኑሮአችሁ ምን እንበላለን? ምን እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? በማለት አትጨነቁ። ሕይወት ከምግብ፣ ሰውነትስ ከልብስ አይበልጥምን? እስቲ የሰማይ ወፎችን ተመልከቱ፤ አይዘሩም፤ አያጭዱም፤ በጐተራም አያከማቹም፤ ይሁን እንጂ የሰማዩ አባታችሁ ይመግባቸዋል። እናንተ ከእነርሱ እጅግ አትበልጡምን? . . . ስለዚህ፣ ‘ምን እንበላለን? ምን እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን?’ ብላችሁ አትጨነቁ፤ አሕዛብ እነዚህን ነገሮች ሁሉ ለማግኘት ይጨነቃሉና፤ የሰማዩ አባታችሁም እነዚህ ሁሉ ለእናንተ እንደሚያስፈልጓችሁ ያውቃል። ከሁሉ አስቀድማችሁ ግን የእግዚአብሔርን መንግሥትና ጽድቁን እሹ፤ እነዚህ ሁሉ ይጨመሩላችኋል።” (ማቴዎስ 6:25-33) ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን?

ኢየሱስ ለራሳችንም ሆነ ለቤተሰባችን አባላት የሚያስፈልጉትን ቁሳዊ ነገሮች ማሟላታችንን ችላ ማለት እንዳለብን መግለጹ አልነበረም። መጽሐፍ ቅዱስ “አንድ ሰው ዘመዶቹን፣ በተለይም የቅርብ ቤተ ሰቡን የማይረዳ ከሆነ ሃይማኖቱን የካደ፣ ከማያምንም ሰው ይልቅ የባሰ ክፉ ነው” በማለት ይናገራል። (1 ጢሞቴዎስ 5:8) ይሁን እንጂ መቅደም ያለባቸውን ነገሮች በተገቢው ቦታ ካስቀመጥንና ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ ከሰጠን አምላክ የሚያስፈልጉንን ነገሮች እንደሚያሟላልን ኢየሱስ ቃል ገብቷል። እነዚህ የኢየሱስ ቃላት ቅድሚያ ሊሰጣቸው ለሚገቡ ነገሮች እንዴት ቅድሚያ መስጠት እንዳለብን ያስተምሩናል። ‘ለመንፈሳዊ ፍላጎታቸው ንቁ የሆኑ ደስተኞች ስለሚሆኑ’ ይህንን የኢየሱስን ምክር መተግበር ደስታ ያስገኛል።—ማቴዎስ 5:3 NW

ከአምላክ ጋር መወዳጀት

ለመንፈሳዊ ፍላጎቶቻቸው ንቁ የሆኑ ሰዎች ከአምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና መመሥረት አስፈላጊ እንደሆነ ይገነዘባሉ። ከአንድ ሰው ጋር ጥሩ ወዳጅነት ለመመሥረት ምን ማድረግ አለብን? ያንን ሰው በደንብ ለማወቅ ጥረት አናደርግም? ስለ አመለካከቱ፣ ስለ አስተሳሰቡ፣ ስለ ችሎታዎቹ፣ ስላከናወናቸው ሥራዎች እንዲሁም ስለሚወዳቸውና ስለሚጠላቸው ነገሮች ለማወቅ እንጥራለን። ከአምላክ ጋር ወዳጅነት ለመመሥረትም ተመሳሳይ ነገሮችን ማድረግ ያስፈልጋል። ስለ እርሱ ትክክለኛ እውቀት ማግኘት ይገባናል። ኢየሱስ ተከታዮቹን በተመለከተ “እውነተኛ አምላክ የሆንኸውን አንተንና የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት” በማለት ወደ አምላክ ጸልዮአል። (ዮሐንስ 17:3) አዎን፣ ከይሖዋ ጋር ወዳጅነት ለመመሥረት እርሱን ማወቅ ያስፈልገናል። እርሱን ለማወቅ የሚረዳን ብቸኛው መሣሪያ ደግሞ በመንፈሱ አነሳሽነት ያስጻፈው ቃሉ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ጊዜ መመደብ ይገባናል።

ይሁን እንጂ እውቀት ብቻ በቂ አይደለም። ኢየሱስ ከላይ በተጠቀሰው ጸሎቱ ላይ “እነርሱም [ደቀ መዛሙርቱ] ቃልህን ጠብቀዋል” በማለት ጨምሮ ተናግሯል። (ዮሐንስ 17:6) ስለ አምላክ ማወቅ ብቻ ሳይሆን ካገኘነው እውቀት ጋር ተስማምተን መጓዝ ይገባናል። በእርግጥም የአምላክ ወዳጆች መሆን የምንችልበት ከዚህ የተሻለ መንገድ ይኖራል? ከአንድ ወዳጃችን አስተሳሰብና ከሚያምንበት ነገር ጋር የሚጋጭ ድርጊት ሆን ብለን እየፈጸምን ጓደኝነታችን እየጠነከረ ይሄዳል ብለን መጠበቅ እንችላለን? ስለዚህ ጠቅላላ አኗኗራችንን በአምላክ አስተሳሰብና መሠረታዊ ሥርዓቶች መምራት ይገባናል። አሁን ደግሞ ከሌሎች ሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት ረገድ ተግባራዊ ልናደርጋቸው የሚገቡ ሁለት መሠረታዊ ሥርዓቶችን እንመልከት።

ከሌሎች ጋር መልካም ግንኙነት መመሥረት

ኢየሱስ በአንድ ወቅት ሰዎች እርስ በርሳቸው ምን ዓይነት ግንኙነት ሊኖራቸው እንደሚገባ ለማስተማር አንድ አጭር ታሪክ ተናግሮ ነበር። ታሪኩ በአገልጋዮቹ እጅ የነበረውን ሒሳብ ለመተሳሰብ በፈለገ ንጉሥ ላይ ያተኩራል። ከአገልጋዮቹ አንዱ በምንም ዓይነት መንገድ ሊከፍለው በማይችለው ብዙ ዕዳ ውስጥ ተዘፍቆ ነበር። ስለዚህ ንጉሡ አገልጋዩ ራሱ እንዲሁም የአገልጋዩ ሚስትና ልጆች ተሽጠው ዕዳው እንዲከፈል አዘዘ። በዚህ ጊዜ ተበዳሪው ንጉሡ እግር ላይ ወድቆ “ታገሰኝ፣ ያለብኝን ዕዳ ሁሉ እከፍልሃለሁ” ብሎ ለመነው። ንጉሡም በአዘኔታ ዕዳውን ሰረዘለት። ይሁን እንጂ ይህ አገልጋይ ከንጉሡ ፊት ከወጣ በኋላ አነስተኛ ገንዘብ ያበደረውን ባልንጀራው የሆነ አገልጋይ አገኘና ዕዳውን እንዲከፍል ወጥሮ ያዘው። ይህ ባልንጀራው ዕዳውን እስኪከፍለው ድረስ እንዲታገሰው ቢማጸነውም እንኳን ብድሩን ሁሉ ከፍሎ እስኪጨርስ ድረስ እስር ቤት ወረወረው። ንጉሡ ይህን በሰማ ጊዜ ተበሳጨ። “እኔ እንደ ማርሁህ አንተም ባልንጀራህን ልትምረው አይገባህም ነበርን?” ብሎ አገልጋዩን ጠየቀው። ከዚያም ንጉሡ ምሕረት ያላደረገው አገልጋይ ዕዳውን ከፍሎ እስኪጨርስ ድረስ እስር ቤት አስገባው። ኢየሱስ ይህ ታሪክ ምን ትምህርት እንደሚሰጥ ሲገልጽ “ስለዚህ እያንዳንዳችሁ ወንድሞቻችሁን ከልባችሁ ይቅር ካላላችሁ፣ የሰማዩ አባቴም እንደዚሁ ያደርግባችኋል” አለ።—ማቴዎስ 18:23-35

ኃጢአተኞች እንደመሆናችን መጠን ብዙ ስህተቶች እንፈጽማለን። የእርሱን ሕግ በመጣሳችን ምክንያት የተከማቸብንን ከባድ ዕዳ ፈጽሞ ለአምላክ መክፈል አንችልም። ማድረግ የምንችለው ነገር ቢኖር የእርሱን ምሕረት መለመን ብቻ ነው። የበደሉንን ወንድሞቻችንን ይቅር የምንል ከሆነ ይሖዋ አምላክ እኛም የፈጸምነውን ስህተት ይቅር ለማለት ዝግጁ ነው። እንዴት ያለ ኃይለኛ ትምህርት ነው! ኢየሱስ ተከታዮቹ “እኛም ደግሞ የበደሉንን ይቅር እንደምንል፣ በደላችንን ይቅር በለን” ብለው እንዲጸልዩ አስተምሯቸዋል።—ማቴዎስ 6:12

ችግር እንዲፈጠር ምክንያት የሚሆኑ ነገሮችን ማስወገድ

ኢየሱስ ስለ ሰዎች ውስጣዊ ባሕርይ በሚገባ ያውቃል። በመሆኑም ችግሮችን ስለ መፍታት የሰጠው ምክር ለችግሮቹ መነሳት ምክንያት የሆኑ ነገሮችን ለማስወገድ የሚረዱ ናቸው። እስቲ ሁለት ምሳሌዎችን እንመልከት።

ኢየሱስ እንዲህ ብሎ ነበር:- “ለቀደሙት ሰዎች፣ ‘አትግደል፤ የገደለ ይፈረድበታል’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል፤ እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ወንድሙን ያለ አግባብ የሚቆጣ ይፈረድበታል።” (ማቴዎስ 5:21, 22) እዚህ ላይ ኢየሱስ ይበልጥ ያተኮረው በግድያው ላይ ሳይሆን ወንጀሉን ለመፈጸም ምክንያት በሆነው ጉዳይ ላይ ነው። ሰውን ለግድያ የሚያነሳሳው በልቡ ውስጥ የታመቀው ጥላቻ ነው። ሰዎች የቅሬታና የብስጭት ስሜት በውስጣቸው እንዲያድግ ካልፈቀዱ በስተቀር ሆን ብለው ወንጀል ወደ መፈጸም አያመሩም። ሰዎች ይህን ትምህርት በሥራ ላይ አውለው ቢሆን ኖሮ ብዙ የደም መፋሰስ ባልተከሰተ ነበር!

አሁን ደግሞ ኢየሱስ ከባድ ሐዘን ለሚያስከትል አንድ ችግር መሠረቱ ምን እንደሆነ የጠቀሰውን ልብ በል። ለተሰበሰበው ሕዝብ እንዲህ አለ:- “‘አታመንዝር’ እንደተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ሴትን በምኞት ዓይን የተመለከተ ሁሉ በልቡ ከእርሷ ጋር አመንዝሮአል። ቀኝ ዓይንህ የኀጢአት ሰበብ ቢሆንብህ፣ አውጥተህ ወዲያ ጣለው።” (ማቴዎስ 5:27-29) እዚህም ላይ ኢየሱስ ይበልጥ ያተኮረው በሥነ ምግባር ብልግናው ላይ ሳይሆን ድርጊቱን ለመፈጸም ምክንያት በሆነው ነገር ላይ ነው። የችግሩ መንስዔ መጥፎ ምኞት ነው። አንድ ሰው ተገቢ ያልሆኑ ምኞቶችን ለማስተናገድ ፈቃደኛ ባለመሆን ከአእምሮው ‘አውጥቶ ከጣላቸው’ ከሥነ ምግባር ውጪ የሆኑ ድርጊቶችን ከመፈጸም ሊታቀብ ይችላል።

“ሰይፍህን ወደ ሰገባው መልስ”

ኢየሱስ ክህደት በተፈጸመበትና በተያዘበት ምሽት ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ ሰይፉን መዝዞ ሊከላከልለት ሞክሮ ነበር። ኢየሱስ ግን “በል ሰይፍህን ወደ ሰገባው መልስ፤ ሰይፍን የሚመዝዙ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉ” በማለት አዘዘው። (ማቴዎስ 26:52) በማግስቱ ጠዋት ኢየሱስ ለጳንጥዮስ ጲላጦስ “የእኔ መንግሥት ከዚህ ዓለም አይደለም፤ ቢሆንማ ኖሮ አይሁድ እንዳይዙኝ ሎሌዎቼ በተከላከሉልኝ ነበር፤ አሁን ግን መንግሥቴ ከዚህ አይደለም” በማለት ነገረው። (ዮሐንስ 18:36) ይህ ትምህርት ምክንያታዊነት የጎደለው ነው?

የጥንት ክርስቲያኖች ኢየሱስ ዓመጽን እንደ መፍትሄ አድርገው እንዳይወስዱ ስለሰጣቸው ትምህርት ምን አመለካከት ነበራቸው? ዚ ኧርሊ ክሪስቸን አቲትዩድ ቱ ዎር የሚል ርዕስ ያለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “[የኢየሱስ ትምህርቶች] በምንም ዓይነት መንገድ በሌሎች ላይ ማመጽንም ሆነ ጉዳት ማድረስን ስለሚከለክሉ በተዘዋዋሪ መንገድ በጦርነት መካፈል እንደማይገባ የሚገልጹ [ነበሩ]። . . . የጥንት ክርስቲያኖች ኢየሱስ ያለውን ሙሉ በሙሉ ታዝዘዋል እንዲሁም የኢየሱስ ትምህርቶች ቃል በቃል ገሮች መሆን እንዳለባቸውና ጥቃትን በዓመጽ መከላከል እንደሌለባቸው እንደሚገልጹ አድርገው ተረድተዋቸዋል። ሃይማኖታቸውን በቀጥታ ከሰላም ጋር አዛምደውት ነበር፤ ደም አፋሳሽ ጦርነትን በጥብቅ ያወግዙ ነበር።” ክርስቲያን ነን የሚሉ ሁሉ ይህን ትምህርት በጥንቃቄ ቢከተሉ ኖሮ የታሪክ አቅጣጫ እንዴት በተቀየረ ነበር!

ከኢየሱስ ትምህርቶች በሙሉ ጥቅም ማግኘት ትችላለህ

እስከ አሁን የተመለከትናቸው የኢየሱስ ትምህርቶች የሚማርኩ፣ ያልተወሳሰቡና ኃይለኛ መልእክት ያዘሉ ናቸው። የሰው ልጆች ኢየሱስ ያስተማራቸውን ትምህርቶች በማወቅና በሥራ ላይ በማዋል ጥቅም ማግኘት ይችላሉ። a

በአካባቢህ የሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች ማንም ሌላ ሰው ያላስተማረው ጥበብ የሞላበት የኢየሱስ ትምህርት እንዴት ሊጠቅምህ እንደሚችል እንድታውቅ ለመርዳት ዝግጁ ናቸው። ከእነርሱ ጋር እንድትገናኝ ወይም ደግሞ በዚህ መጽሔት ገጽ 2 ላይ ባለው አድራሻ ተጠቅመህ ደብዳቤ እንድትጽፍ ሞቅ ያለ ግብዣ እናቀርብልሃለን።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ኢየሱስ ስላስተማራቸው ትምህርቶች ቀለል ያለ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የታተመውን እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው የሚል ርዕስ ያለውን መጽሐፍ ተመልከት።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“የሰማዩ አባታችሁ ይመግባቸዋል”

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የኢየሱስ ትምህርቶች በሕይወትህ ላይ በጎ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ