በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከእንግዲህ ለራሳችን አንኖርም

ከእንግዲህ ለራሳችን አንኖርም

ከእንግዲህ ለራሳችን አንኖርም

“በሕይወት ያሉትም . . . ከእንግዲህ ለራሳቸው እንዳይኖሩ [ክርስቶስ] ስለ ሁሉ ሞተ።”—2 ቆሮንቶስ 5:15

1, 2. በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ የኢየሱስ ተከታዮች ራስ ወዳድነትን እንዲያሸንፉ የረዳቸው የትኛው ቅዱስ ጽሑፋዊ ትእዛዝ ነው?

 ጊዜው ኢየሱስ በምድር ላይ ያሳለፈው የመጨረሻው ምሽት ነበር። ከጥቂት ሰዓታት በኋላ በእርሱ ለሚያምኑ ሁሉ ሕይወቱን አሳልፎ ይሰጣል። በዚያ ምሽት ኢየሱስ ለታማኝ ሐዋርያቱ ብዙ ቁም ነገሮች አካፈላቸው። ከነገራቸው ነገሮች መካከል ተከታዮቹ ተለይተው እንዲታወቁ ምልክት ሆኖ የሚያገለግለውን ባሕርይ በተመለከተ የሰጠው ትእዛዝ ይገኝበታል። “አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ፤ ይኸውም እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ ነው፤ እንግዲህ እኔ እንደ ወደድኋችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ። እርስ በርሳችሁ ብትዋደዱ፣ ሰዎች ሁሉ የእኔ ደቀ መዛሙርት እንደ ሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ” ብሏል።—ዮሐንስ 13:34, 35

2 እውነተኛ ክርስቲያኖች አንዳቸው ለሌላው ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር እንዲያሳዩና ከራሳቸው ይልቅ የእምነት ባልንጀሮቻቸውን ጥቅም እንዲያስቀድሙ ይጠበቅባቸዋል። ሌላው ቀርቶ ‘ስለ ወዳጆቻቸው ሕይወታቸውን አሳልፈው ከመስጠት’ ወደኋላ ማለት የለባቸውም። (ዮሐንስ 15:13) የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ለዚህ አዲስ ትእዛዝ የሰጡት ምላሽ ምን ነበር? በሁለተኛው መቶ ዘመን የኖረው ተርቱሊያን የተባለ ጸሐፊ አፖሎጂ በተባለው ዝነኛ የጽሑፍ ሥራው ላይ ‘እርስ በርሳቸው እንዴት እንደሚዋደዱ፣ አልፎ ተርፎም አንዳቸው ለሌላው ለመሞት ምን ያህል ዝግጁ እንደሆኑ ተመልከቱ’ ብለው ሌሎች ስለ ክርስቲያኖች መናገራቸውን ጽፏል።

3, 4. (ሀ) ራስ ወዳድነትን መዋጋት ያለብን ለምንድን ነው? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንማራለን?

3 በዛሬው ጊዜ ያለን ክርስቲያኖችም ‘አንዳችን የሌላውን ከባድ ሸክም በመሸከም የክርስቶስን ሕግ መፈጸም’ ይኖርብናል። (ገላትያ 6:2) ይሁን እንጂ የክርስቶስን ሕግ እንዳንታዘዝ ብሎም ይሖዋ ‘አምላካችንን በፍጹም ልባችን፣ በፍጹም ነፍሳችን፣ በፍጹም ሐሳባችን እንዳንወድ እንዲሁም ጎረቤታችንን እንደ ራሳችን እንዳንወድ’ እንቅፋት የሚሆንብን ትልቁ ችግር ራስ ወዳድነት ነው። (ማቴዎስ 22:37-39) ፍጽምና የሚጎድለን ስለሆንን የራስ ወዳድነት ዝንባሌ ያጠቃናል። በዚህ ላይ ኑሮ የሚያስከትለው ውጥረት፣ በትምህርት ቤት ወይም በሥራ ቦታ የሚታየው የፉክክር መንፈስ እንዲሁም ለመኖር የሚያስፈልጉ ነገሮችን ለማግኘት የሚደረገው ትግል ሲጨመርበት ይህ ችግር ይባባሳል። ይህ የራስ ወዳድነት ዝንባሌ እየቀነሰ ሲሄድ አይታይም። ሐዋርያው ጳውሎስ “በመጨረሻው ዘመን . . . ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉ” ሲል አስጠንቅቋል።—2 ጢሞቴዎስ 3:1, 2

4 ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ መጨረሻ አካባቢ ደቀ መዛሙርቱ የራስ ወዳድነትን ባሕርይ ማሸነፍ እንዲችሉ የሚረዳ ሦስት ነጥቦችን ያካተተ መመሪያ ሰጥቷቸዋል። መመሪያው ምንድን ነው? እኛስ ከትምህርቱ ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?

ፍቱን ማርከሻ!

5. ኢየሱስ በስተ ሰሜን ገሊላ እየሰበከ ሳለ ለደቀ መዛሙርቱ ምን ገለጸላቸው? ይህስ ለእነርሱ አስደንጋጭ የሆነባቸው ለምንድን ነው?

5 ኢየሱስ በስተ ሰሜን ገሊላ በምትገኘው ፊልጶስ ቂሣርያ አቅራቢያ ምሥራቹን እየሰበከ ነበር። ይህ ጸጥታ የሰፈነበት የሚያምር አካባቢ ይበልጥ የሚያመቸው ለመዝናናት እንጂ ራስን ስለ መካድ ለመማር ላይመስል ይችላል። ሆኖም በዚያ እያሉ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ “ወደ ኢየሩሳሌም ይሄድ ዘንድ፣ በዚያም በሽማግሌዎች፣ በካህናት አለቆችና በኦሪት ሕግ መምህራን እጅ መከራን ይቀበልና ይገደል ዘንድ፣ በሦስተኛው ቀን ከሞት ይነሣ ዘንድ እንደሚገባው” ይገልጽላቸው ጀመር። (ማቴዎስ 16:21) የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እስከዚህ ጊዜ ድረስ መሪያቸው በምድር ላይ መንግሥት እንደሚያቋቁም ይጠባበቁ ስለነበር ይህን ሲሰሙ በጣም ሳይደነግጡ አልቀረም!—ሉቃስ 19:11፤ የሐዋርያት ሥራ 1:6

6. ኢየሱስ ለጴጥሮስ ጠንካራ ተግሣጽ የሰጠው ለምን ነበር?

6 ጴጥሮስ ወዲያውኑ “ኢየሱስን ወደ ጐን ሳብ አድርጎ፣ ‘ጌታ ሆይ፤ እንዲህ ያለ ነገር ፈጽሞ አይድረስብህ’ እያለ ይገሥጸው ጀመር።” ኢየሱስ ምን ምላሽ ሰጠ? “ኢየሱስም ወደ ጴጥሮስ ዘወር ብሎ፣ ‘አንተ ሰይጣን፣ ሂድ ከዚህ! የሰው እንጂ የእግዚአብሔር ነገር በሐሳብህ ስለ ሌለ መሰናክል ሆነህብኛል’ አለው።” በሁለቱ መካከል ትልቅ የአመለካከት ልዩነት ነበር! ኢየሱስ፣ አምላክ የመረጠለትን የራስን ጥቅም የመሠዋት አኗኗር ለመከተል ፈቃደኛ የነበረ ሲሆን ይህም ከጥቂት ወራት በኋላ በመከራ እንጨት ላይ መሞትን ይጠይቅበታል። ጴጥሮስ “እንዲህ ያለ ነገር ፈጽሞ አይድረስብህ” በማለት ራሱን ማስጨነቅ እንደሌለበት ነገረው። ጴጥሮስ እንዲህ ያለው በጥሩ ዓላማ እንደሆነ ምንም ጥያቄ የለውም። ይሁንና ጴጥሮስ በዚህ ወቅት የተናገረው በሰይጣን ተጽዕኖ ተሸንፎ ስለነበር ኢየሱስ ገስጾታል። ጴጥሮስ ‘የሰው እንጂ የእግዚአብሔር ነገር በሐሳቡ’ አልነበረም።—ማቴዎስ 16:22, 23

7. በማቴዎስ 16:24 ላይ ኢየሱስ ተከታዮቹ ምን ዓይነት አኗኗር እንዲከተሉ ተናግሯል?

7 በዛሬው ጊዜም ሰዎች የጴጥሮስ ዓይነት አስተሳሰብ አላቸው። አብዛኛውን ጊዜ ይህ ዓለም ሰዎች ‘ራሳቸውን እንዳይጎዱ’ ወይም ‘ቀላሉን አማራጭ እንዲጠቀሙ’ ያበረታታል። በአንጻሩ ደግሞ ኢየሱስ ከዚህ የተለየ አስተሳሰብ እንዲኖረን አሳስቦናል። ደቀ መዛሙርቱን “ሊከተለኝ የሚወድ ራሱን ይካድ፣ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ” በማለት ነግሯቸዋል። (ማቴዎስ 16:24) “ይህ አባባል ሌሎች ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ የቀረበ ጥሪ ሳይሆን የክርስቶስን ጥሪ ተቀብለው ለመጡ ሰዎች ደቀ መዝሙርነት ምን ማለት እንደሆነ እንዲያስቡበት የተነገረ ሐሳብ ነው” በማለት ዘ ኒው ኢንተርፕሪተርስ ባይብል ገልጿል። ክርስትናን የተቀበሉ ሰዎች ኢየሱስ በዚህ ጥቅስ ላይ የተናገራቸውን ሦስት ነጥቦች በሥራ ሊያውሏቸው ይገባል። እስቲ ሦስቱንም አንድ በአንድ እንመልከት።

8. ራስን መካድ ሲባል ምን ማለት እንደሆነ አብራራ።

8 በመጀመሪያ ደረጃ ራሳችንን መካድ ይኖርብናል። “ራሱን ይካድ” ለማለት የተሠራበት ግሪክኛ ቃል የራስ ወዳድነት ፍላጎቶችን ወይም የግል ጥቅሞችን ገሸሽ ለማድረግ ፈቃደኛ መሆንን ያመለክታል። ራስን መካድ አልፎ አልፎ አንዳንድ አስደሳች ነገሮችን የመተው ጉዳይ ብቻ አይደለም። በሌላ በኩል ደግሞ መናኝ እንሆናለን ወይም ራሳችንን እንጎዳለን ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ‘የራሳችን’ መሆናችን ያከትማል፤ ይህም ሲባል መላ ሕይወታችንንም ሆነ ከሕይወታችን ጋር ግንኙነት ያላቸውን ነገሮች በፈቃደኝነት ለይሖዋ እንሰጣለን ማለት ነው። (1 ቆሮንቶስ 6:19, 20) ስለ ራሳችን ብቻ ከማሰብ ይልቅ ሕይወታችን አምላክን በማገልገል ላይ ያተኮረ ይሆናል። ራስን መካድ ሲባል ደካማ ሥጋችን ወደ ሌላ አቅጣጫ የሚመራን ቢሆንም እንኳ የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ቆርጦ መነሳትን ያመለክታል። ራሳችንን ለአምላክ ስንወስንና ስንጠመቅ ሙሉ በሙሉ ለእርሱ ያደርን መሆናችንን እናሳያለን። ከዚህ በኋላ በቀረው የሕይወት ዘመናችን ሁሉ ከውሳኔያችን ጋር ተስማምተን ለመኖር እንጥራለን።

9. (ሀ) ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት የመከራ እንጨት ምን ያመለክት ነበር? (ለ) የመከራ እንጨት የምንሸከመው እንዴት ነው?

9 ሁለተኛው ነጥብ ደግሞ መስቀሉን ማለትም የመከራውን እንጨት መሸከም ያለብን መሆኑ ነው። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የመከራ እንጨት መሰቃየትን፣ መዋረድንና መሞትን ያመለክት ነበር። በአብዛኛው፣ የመከራ እንጨት ላይ የሚሰቀሉት ወይም ደግሞ አስከሬናቸው በእንጨት ላይ እንዲሰቀል የሚደረጉት ወንጀለኞች ብቻ ነበሩ። ኢየሱስ እንዲህ ሲል አንድ ክርስቲያን የዓለም ክፍል ባለመሆኑ ምክንያት ስደት፣ ጥላቻ ይባስ ብሎም ሞት ለመቀበል ዝግጁ መሆን እንዳለበት መግለጹ ነበር። (ዮሐንስ 15:18-20) ክርስቲያናዊ አቋማችን ከሌሎች የተለየን ስለሚያደርገን ዓለም ‘ሊሰድበን’ ይችላል። (1 ጴጥሮስ 4:4) እንዲህ ዓይነት ሁኔታ በትምህርት ቤት፣ በሥራ ቦታችን ወይም ከቤተሰባችን አባላት ሊደርስብን ይችላል። (ሉቃስ 9:23) ይሁንና ለራሳችን መኖር ስላቆምን ከዓለም የሚደርስብንን ጥላቻ ችለን ለማለፍ ፈቃደኞች ነን። ኢየሱስ “ሰዎች በእኔ ምክንያት ቢሰድቧችሁ፣ ቢያሳድዷችሁና ክፉውን ሁሉ በሐሰት ቢያስወሩባችሁ፤ ብፁዓን ናችሁ። በሰማይ የምትቀበሉት ዋጋ ታላቅ ስለ ሆነ ደስ ይበላችሁ፤ ሐሤት አድርጉ” ብሏል። (ማቴዎስ 5:11, 12) በእርግጥም፣ ትልቅ ቦታ የሚይዘው የአምላክን ሞገስ ማግኘት ነው።

10. ኢየሱስን መከተል ምን ማድረግን ይጨምራል?

10 ሦስተኛው ነጥብ ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ ልንከተለው እንደሚገባ የተናገረው ነው። በዊልያም ቫይን የተዘጋጀው አን ኤክስፖዚተሪ ዲክሽነሪ ኦቭ ኒው ቴስታመንት ወርድስ የተባለው መዝገበ ቃላት እንደሚያሳየው መከተል ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል የጉዞ ጓደኛን ማለትም “በተመሳሳይ አቅጣጫ የሚሄድን ሰው” ያመለክታል። አንደኛ ዮሐንስ 2:6 “ማንም [በአምላክ] እኖራለሁ የሚል፣ ኢየሱስ እንደ ተመላለሰ ሊመላለስ ይገባዋል” ይላል። ኢየሱስ የተመላለሰው ወይም የሄደው እንዴት ነበር? ኢየሱስ በሰማይ ለሚኖረው አባቱና ለደቀ መዛሙርቱ የነበረው ፍቅር ራስ ወዳድ እንዳይሆን አስችሎታል። ጳውሎስ “ክርስቶስ ራሱን ደስ አላሰኘምና” ሲል ጽፏል። (ሮሜ 15:3) ኢየሱስ ተርቦና ተጠምቶ በነበረበት ጊዜም እንኳ ከራሱ ይልቅ የሌሎችን ጥቅም ያስቀድም ነበር። (ማርቆስ 6:31-34) የመንግሥቱን ምሥራች በመስበኩና በማስተማሩ ሥራም በሙሉ ኃይሉ ተካፍሏል። ‘ኢየሱስ ያዘዛቸውን ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማርን ሕዝቦችን ሁሉ ደቀ መዛሙርት እንድናደርግ’ የተሰጠንን ተልእኮ በቅንዓት ስንወጣ እርሱን መምሰል የለብንም? (ማቴዎስ 28:19, 20) ኢየሱስ በአኗኗሩ ሁሉ ምሳሌ የተወልን ሲሆን እኛም ‘የእርሱን ፈለግ መከተል’ ይኖርብናል።—1 ጴጥሮስ 2:21

11. ራሳችንን መካዳችን፣ የመከራውን እንጨት መሸከማችንና ኢየሱስ ክርስቶስን መከተላችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

11 ራሳችንን መካዳችን፣ የመከራውን እንጨት መሸከማችንና ምሳሌያችን የሆነውን ኢየሱስን መከተላችን በጣም አስፈላጊ ነው። እንዲህ ማድረጋችን ሌሎችን ከራሳችን አስበልጠን እንዳንወድ እንቅፋት የሚሆንብንን ራስ ወዳድነት እንድናሸንፍ ያስችለናል። ከዚህ በተጨማሪ ኢየሱስ እንዲህ ብሏል:- “ነፍሱን ሊያድን የሚፈልግ ሁሉ ያጠፋታል፤ ነገር ግን ነፍሱን ስለ እኔ የሚያጠፋት ያድናታል። ሰው ዓለምን ሁሉ ቢያተርፍ፣ ነፍሱን ግን ቢያጣ ምን ይጠቅመዋል? ወይስ ሰው በነፍሱ ምትክ ሊከፍለው የሚችለው ዋጋ ምንድን ነው?”—ማቴዎስ 16:25, 26

ሁለት ጌቶችን ማገልገል አንችልም

12, 13. (ሀ) ኢየሱስን ምክር የጠየቀው ጐልማሳ ያሳሰበው ነገር ምን ነበር? (ለ) ኢየሱስ ለጐልማሳው ምን ምክር ሰጠው? ለምንስ?

12 ኢየሱስ ራስን የመካድን አስፈላጊነት ለደቀ መዛሙርቱ ካስተማራቸው ከተወሰኑ ወራት በኋላ አንድ ሀብታም ጐልማሳ ወደ እርሱ መጥቶ “መምህር ሆይ፤ የዘላለምን ሕይወት አገኝ ዘንድ ምን መልካም ነገር ልሥራ?” ብሎ ጠየቀው። ኢየሱስ “ትእዛዛቱን ጠብቅ” ብሎ የነገረው ከመሆኑም ሌላ አንዳንዶቹን ትእዛዛት ጠቀሰለት። ጐልማሳው “እነዚህንማ ጠብቄአለሁ” አለ። ሰውየው እንዲህ ብሎ የመለሰው ከልቡ የነበረ ሲሆን በሕጉ ውስጥ የታቀፉትን ትእዛዛት ለማክበርም የተቻለውን ሁሉ አድርጓል። ስለዚህ “ከዚህ ሌላ የሚጐድለኝ ምን አለ?” ሲል ጠየቀ። ኢየሱስ በሰጠው መልስ ላይ ለዚህ ጐልማሳ በዓይነቱ ልዩ የሆነ ግብዣ አቀረበለት:- “ፍጹም ለመሆን [“ሁሉን ለማሟላት፣” ኒው አሜሪካን ስታንዳርድ ባይብል] ከፈለግህ፣ ሄደህ ንብረትህን ሁሉ ሸጠህ፣ ገንዘቡን ለድኾች ስጥ፤ በሰማይም ሀብት ታገኛለህ። ከዚያም መጥተህ ተከተለኝ።”—ማቴዎስ 19:16-21

13 ይህ ጐልማሳ ይሖዋን በሙሉ ነፍሱ ማገልገል እንዲችል በሕይወቱ ውስጥ ትልቅ መሰናክል የሚሆንበትን ቁሳዊ ንብረቱን ማስወገድ እንዳለበት ኢየሱስ ተረድቷል። አንድ እውነተኛ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ሁለት ጌቶችን ማገልገል አይችልም። አዎ፣ “እግዚአብሔርንና ገንዘብን በአንድነት ማገልገል” አይችልም። (ማቴዎስ 6:24) ትኩረቱ በመንፈሳዊ ጉዳዮች ላይ ያነጣጠረ ‘ጤናማ ዐይን’ ያስፈልገዋል። (ማቴዎስ 6:22) አንድ ሰው ንብረቱን ሸጦ ገንዘቡን ለድኾች መስጠቱ የራሱን ጥቅም መሠዋቱን ያሳያል። በቁሳዊ ንብረቱ ምትክ ይህ ጐልማሳ በሰማይ ሀብት የማከማቸት በዋጋ የማይተመን አጋጣሚ እንደሚያገኝ ኢየሱስ ነገረው። ይህ ሀብት የዘላለም ሕይወት የማግኘትና በመጨረሻም ከክርስቶስ ጋር በሰማይ የመግዛት ተስፋ ያስገኝለታል። ጐልማሳው ራሱን ለመካድ ዝግጁ አልነበረም። “ብዙ ሀብት ስለ ነበረው እያዘነ ሄደ።” (ማቴዎስ 19:22) ይሁን እንጂ ሌሎች የኢየሱስ ተከታዮች ከዚህ የተለየ ምላሽ ሰጥተዋል።

14. አራቱ ዓሣ አጥማጆች ኢየሱስ እርሱን እንዲከተሉ ላቀረበላቸው ጥሪ ምን ምላሽ ሰጡ?

14 ከሁለት ዓመት ገደማ በፊት ኢየሱስ ዓሣ አጥማጆች ለሆኑት ለጴጥሮስ፣ ለእንድርያስ፣ ለያዕቆብና ለዮሐንስ ተመሳሳይ ግብዣ አቅርቦላቸው ነበር። በወቅቱ ከእነርሱ መካከል ሁለቱ ዓሣ እያጠመዱ የነበሩ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ መረባቸውን እያበጁ ነበር። ኢየሱስ “ኑ፣ ተከተሉኝ፤ ሰዎችን አጥማጆች አደርጋችኋለሁ” አላቸው። ከጊዜ በኋላ አራቱም ዓሣ የማጥመድ ሥራቸውን ትተው በቀሪው የሕይወት ዘመናቸው በሙሉ የኢየሱስ ተከታዮች ሆኑ።—ማቴዎስ 4:18-22

15. በዘመናችን አንዲት የይሖዋ ምሥክር ኢየሱስን ለመከተል መሥዋዕት የከፈለችው እንዴት ነው?

15 በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙ ክርስቲያኖች የሀብታሙን ጐልማሳ ሳይሆን የአራቱን ዓሣ አጥማጆች ምሳሌ ተከትለዋል። ይሖዋን ለማገልገል ሲሉ በዚህ ዓለም ሊያገኙ የሚችሉትን ሀብትና ክብር መሥዋዕት አድርገዋል። ዴብራ እንዲህ ትላለች:- “የ22 ዓመት ወጣት ሳለሁ አንድ ትልቅ ውሳኔ ተደቀነብኝ። መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ከጀመርኩ ወደ ስድስት ወር ገደማ ቢሆነኝ ነበር፤ ሕይወቴን ለይሖዋ የመወሰን ፍላጎትም ነበረኝ። ቤተሰቦቼ ግን በጣም ይቃወሙኝ ነበር። ቤተሰቦቼ ሚሊየነሮች ስለነበሩ የእኔ የይሖዋ ምሥክር መሆን በኅብረተሰቡ ዘንድ እንዲናቁ እንደሚያደርጋቸው ተሰማቸው። ከተንደላቀቀ ሕይወት አሊያም ከእውነት የቱን እንደምመርጥ በ24 ሰዓት ውስጥ እንዳሳውቃቸው ነገሩኝ። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ያለኝን ግንኙነት እርግፍ አድርጌ ካልተውኩ አንዳች ውርስ እንደማላገኝ ነገሩኝ። ይሖዋ ትክክለኛ ውሳኔ ላይ እንድደርስ የረዳኝ ከመሆኑም ሌላ በዚያው እንድጸና ብርታት ሰጠኝ። ላለፉት 42 ዓመታት በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ተካፍያለሁ፤ ደግሞም አንዳች የምቆጭበት ነገር የለም። በተድላ ላይ ያተኮረ የራስ ወዳድነት ኑሮ ለመኖር ፈቃደኛ ባለመሆኔ በቤተሰቤ አባላት ላይ ከማየው የከንቱነት ስሜትና ደስታ የራቀው ሕይወት ልተርፍ ችያለሁ። ከባለቤቴ ጋር ሆኜ ከአንድ መቶ በላይ የሚሆኑ ሰዎች እውነትን እንዲማሩ ረድቻለሁ። እነዚህ መንፈሳዊ ልጆቼ ከማንኛውም ቁሳዊ ሀብት እጅግ ይበልጡብኛል።” በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሌሎች የይሖዋ ምሥክሮችም የእርሷን አመለካከት ይጋራሉ። የአንተስ አመለካከት ምንድን ነው?

16. ለራሳችን እንደማንኖር እንዴት ማሳየት እንችላለን?

16 በሺዎች የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች ለራሳቸው የመኖር ፍላጎት የሌላቸው መሆኑ አቅኚዎች ማለትም የሙሉ ጊዜ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሆነው እንዲያገለግሉ አነሳስቷቸዋል። በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመካፈል ሁኔታቸው የማይፈቅድላቸው ሌሎች ደግሞ የአቅኚነት መንፈስ ያዳበሩ ከመሆኑም ሌላ አቅማቸው በፈቀደላቸው መጠን የመንግሥቱን ምሥራች ለመስበኩ ሥራ ድጋፍ ይሰጣሉ። ወላጆች ለልጆቻቸው መንፈሳዊ ሥልጠና ለመስጠት አብዛኛውን ጊዜያቸውን በማዋልና የግል ፍላጎቶቻቸውን መሥዋዕት በማድረግ ተመሳሳይ መንፈስ ያሳያሉ። ሁላችንም በሕይወታችን ውስጥ የአምላክን መንግሥት እንደምናስቀድም ማሳየት የምንችልባቸው የተለያዩ መንገዶች አሉ።—ማቴዎስ 6:33

ግድ የሚለን የማን ፍቅር ነው?

17. መሥዋዕት እንድንከፍል የሚያነሳሳን ምንድን ነው?

17 የራስን ጥቅም መሥዋዕት የሚያደርግ ፍቅር ማሳየት ቀላል አይደለም። ሆኖም ለዚህ የሚያነሳሳን ምን እንደሆነ አስብ። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “የክርስቶስ ፍቅር ግድ ይለናልና፤ ምክንያቱም አንዱ ስለ ሁሉ እንደ ሞተ እርግጠኞች ሆነናል . . . በሕይወት ያሉትም ለሞተላቸውና ከሙታን ለተነሣላቸው እንጂ ከእንግዲህ ለራሳቸው እንዳይኖሩ እርሱ ስለ ሁሉ ሞተ።” (2 ቆሮንቶስ 5:14, 15) ለራሳችን እንዳንኖር የሚያስገድደን የክርስቶስ ፍቅር ነው። ይህ ለተግባር የሚያነሳሳ ከፍተኛ ኃይል ነው! ክርስቶስ ለእኛ ብሎ እስከሞተልን ድረስ ለእርሱ የመኖር የሞራል ግዴታ እንዳለብን ሊሰማን አይገባም? በእርግጥም፣ አምላክና ክርስቶስ ላሳዩን ጥልቅ ፍቅር ያለን አመስጋኝነት ሕይወታችንን ለአምላክ እንድንወስንና የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንድንሆን አስገድዶናል።—ዮሐንስ 3:16፤ 1 ዮሐንስ 4:10, 11

18. የራስን ጥቅም የመሠዋት አኗኗር የማያስቆጭ የሆነው ለምንድን ነው?

18 ለራስ አለመኖር የሚያስገኘው ጥቅም አለ? ሀብታሙ ጐልማሳ፣ ክርስቶስ ያቀረበለትን ግብዣ ረግጦ ከሄደ በኋላ ጴጥሮስ “እኛ ሁሉን ትተን ተከትለንሃል፤ ታዲያ ምን እናገኝ ይሆን?” ሲል ኢየሱስን ጠየቀው። (ማቴዎስ 19:27) ጴጥሮስና ሌሎች ሐዋርያት በእርግጥ ራሳቸውን የካዱ ሰዎች ነበሩ። ታዲያ ወሮታቸው ምን ይሆን? ኢየሱስ በመጀመሪያ በሰማይ ከእርሱ ጋር ገዢዎች በመሆን ስለሚያገኙት መብት ጠቀሰ። (ማቴዎስ 19:28) በዚያው ወቅት ኢየሱስ ተከታዮቹ የሆኑ ሁሉ ስለሚያገኟቸው በረከቶች ተናግሯል። “ስለ እኔና ስለ ወንጌል ሲል ቤቱን ወይም ወንድሞቹን ወይም እኅቶቹን ወይም እናቱን ወይም አባቱን ወይም ልጆቹን ወይም ዕርሻውን የተወ ሁሉ፣ አሁን በዚህ ዘመን . . . መቶ ዕጥፍ የማይቀበል፣ በሚመጣውም ዓለም የዘላለም ሕይወት የማይወርስ የለም” ብሏል። (ማርቆስ 10:29, 30) መሥዋዕት ካደረግነው እጅግ የሚበልጥ በረከት እናገኛለን። በመንፈሳዊ ሁኔታ ያገኘናቸው አባቶቻችን፣ እናቶቻችን፣ ወንድሞቻችን፣ እህቶቻችንና ልጆቻችን ለአምላክ መንግሥት ስንል ከሠዋነው ከማንኛውም ነገር እጅግ አይበልጡብንም? ከጴጥሮስና ከሀብታሙ ጐልማሳ በጣም አስደሳች ሕይወት የኖረው ማን ነው?

19. (ሀ) እውነተኛ ደስታ በምን ላይ የተመካ ነው? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን እንማራለን?

19 ኢየሱስ ደስታ የሚገኘው ራስ ወዳድ በመሆን ሳይሆን ከመስጠትና ከማገልገል መሆኑን በቃልም ሆነ በተግባር አሳይቷል። (ማቴዎስ 20:28፤ የሐዋርያት ሥራ 20:35) ለራሳችን መኖር ትተን ክርስቶስን ስንከተል በአሁኑ ጊዜ በሕይወታችን ከፍተኛ ደስታ የምናገኝ ከመሆኑም ሌላ ወደፊት የዘላለም ሕይወት ተስፋ ይኖረናል። እርግጥ ነው፣ ራሳችንን ስንክድ ይሖዋ የሕይወታችን ባለቤት ይሆናል። በዚህ መንገድ የአምላክ ባሪያዎች እንሆናለን። እንዲህ ዓይነቱ ባርነት መልሶ ይክሳል የምንለው ለምንድን ነው? በሕይወታችን በምናደርጋቸው ውሳኔዎች ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል? እነዚህ ጥያቄዎች በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ይብራራሉ።

ታስታውሳለህ?

• የራስ ወዳድነት ዝንባሌዎቻችንን መዋጋት ያለብን ለምንድን ነው?

• ራስን መካድ፣ የመከራውን እንጨት መሸከምና ኢየሱስን መከተል ሲባል ምን ማለት ነው?

• ከእንግዲህ ለራሳችን እንዳንኖር የሚያነሳሳን ምንድን ነው?

• የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ ጥቅም ያስገኛል የምንለው ለምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ጌታ ሆይ፤ እንዲህ ያለ ነገር ፈጽሞ አይድረስብህ”

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሀብታሙ ጐልማሳ ኢየሱስን እንዳይከተል ያገደው ምንድን ነው?

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የይሖዋ ምሥክሮች ቀናተኛ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሆነው እንዲያገለግሉ የሚያስገድዳቸው ፍቅር ነው