“የሰርዲኖን ዕንቁ ይመስል ነበር”
“የሰርዲኖን ዕንቁ ይመስል ነበር”
ሐዋርያው ዮሐንስ በሰማይ ያለ አንድ ክብራማ ዙፋን በራእይ ተመልክቶ ነበር። በዙፋኑ ላይ የተቀመጠው “የኢያስጲድንና የሰርዲኖን ዕንቁ [ቀይ ቀለም ያለው የከበረ ድንጋይ] ይመስል ነበር።” (ራእይ 4:2, 3) እነዚህ ዕንቁዎች ምን ዓይነት ነበሩ?
እነዚህ ዕንቁዎች እንዲያው ከላይ የሚያንጸባርቁና በውስጣቸው ብርሃን የማያሳልፉ ድንጋዮች አልነበሩም። “ኢያስጲድ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል በጥንት ጊዜ የተለያዩ ቀለማት ያላቸውን የከበሩ ድንጋዮችና በውስጣቸው ብርሃን የሚያስተላልፉ ውድ ዕንቁዎችን ለማመልከት ይሠራበት ነበር። አርኪባልድ ቶማስ ሮበርትሰን በአዲስ ኪዳን ውስጥ የሚገኙ ምሳሌያዊ ቃላት (እንግሊዝኛ) በተባለው መጽሐፋቸው ላይ በራእይ 4:3 ላይ የተጠቀሰው ‘የኢያስጲድ ዕንቁ’ “በጊዜያችን ኢያስጲድ በመባል የሚታወቀውና በርካሽ ዋጋ የሚገኘው ድንጋይ እንዳልሆነ ምንም ጥርጥር የለውም” ብለዋል። እንዲሁም ዮሐንስ በራእይ መጽሐፍ መደምደሚያ አካባቢ ስለ ሰማያዊቷ ከተማ ስለ ኢየሩሳሌም ሲናገር “የብርሃኗም ድምቀት እጅግ እንደ ከበረ ድንጋይ እንደ ኢያስጲድ፣ እንደ መስተዋት የጠራ ነበር” ብሏል። (ራእይ 21:10, 11) ከዚህ ለመረዳት እንደሚቻለው ዮሐንስ የጠቀሳቸው የከበሩ ድንጋዮች ብርሃን በውስጣቸው ማሳለፍ የሚችሉ ዕንቁዎች ነበሩ።
በዮሐንስ ራእይ ውስጥ በዙፋኑ ላይ እንደተቀመጠ ተደርጎ የተገለጸው በጽንፈ ዓለሙ ውስጥ ከማንም በላይ ክብር ያለው ይሖዋ አምላክ ነው። በንጽሕናውም ሆነ በቅድስናው ወደር የለውም። ከዚህ ጋር በሚስማማ ሁኔታ ሐዋርያው ዮሐንስ “እግዚአብሔር ብርሃን ነው፤ ጨለማም በእርሱ ዘንድ ከቶ የለም” በማለት ጽፏል። (1 ዮሐንስ 1:5) በመሆኑም ዮሐንስ የእምነት ባልንጀሮቹን ‘እርሱ ንጹሕ እንደ ሆነ ራሳቸውን እንዲያነጹ’ አበረታቷቸዋል።—1 ዮሐንስ 3:3
በአምላክ ዘንድ ንጹሕ ሆነን ለመታየት ምን ማድረግ ይኖርብናል? የፈሰሰው የክርስቶስ ደም ኃጢአታችንን እንደሚያስተሰርይልን ማመናችን የግድ አስፈላጊ ነው። እንዲሁም አዘውትረን መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናትና በውስጡ ከያዛቸው ትምህርቶች ጋር በሚስማማ መንገድ በመኖር ‘በብርሃን መመላለስ’ ይኖርብናል።—1 ዮሐንስ 1:7