የአንደኛ ሳሙኤል መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
የይሖዋ ቃል ሕያው ነው
የአንደኛ ሳሙኤል መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
ወቅቱ 1117 ከክርስቶስ ልደት በፊት ሲሆን ኢያሱ ተስፋይቱን ምድር ከተቆጣጠረ ሦስት መቶ ያህል ዓመታት አልፈዋል። በዚህ ጊዜ የእስራኤል ሽማግሌዎች ወደ ይሖዋ ነቢይ መጡና ለየት ያለ ጥያቄ አቀረቡለት። ነቢዩ ስለ ጉዳዩ ወደ ይሖዋ ጸለየ፤ ይሖዋም የፈለጉትን እንዲፈጽሙ ፈቀደላቸው። በዚህ መልኩ በእስራኤል የመሳፍንት ዘመን አበቃና ሰብዓዊ ነገሥታት መግዛት ጀመሩ። የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው አንደኛ ሳሙኤል ከዚህ ትልቅ ለውጥ ጋር በተያያዘ በእስራኤል የተከናወኑ ነገሮችን ይተርካል።
አንደኛ ሳሙኤልን የጻፉት ሳሙኤል፣ ናታንና ጋድ ሲሆኑ መጽሐፉ ከ1180 እስከ 1078 ከክርስቶስ ልደት በፊት ያሉትን የ102 ዓመታት ታሪክ ይዟል። (1 ዜና መዋዕል 29:29) እንደዚሁም በእስራኤል መሪ ስለነበሩ አራት ሰዎች ያወሳል። ከእነዚህ መሪዎች ሁለቱ መሳፍንት ሲሆኑ ሁለቱ ደግሞ ነገሥታት ነበሩ። ሁለቱ ለይሖዋ ሲታዘዙ ሁለቱ ግን አልታዘዙም። በዚሁ መጽሐፍ ውስጥ አርዓያ የሚሆኑ የሁለት ሴቶች እንዲሁም የአንድ ደፋርና ደግነትን የተላበሰ ጦረኛ ታሪክ ይገኛል። እነዚህ ምሳሌዎች ልንኮርጃቸው እንዲሁም ልናስወግዳቸው የሚገቡ ዝንባሌዎችንና ድርጊቶችን በተመለከተ ጠቃሚ ትምህርት ይሰጡናል። በመሆኑም የአንደኛ ሳሙኤል መጽሐፍ በአስተሳሰባችንና በድርጊታችን ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል።—ዕብራውያን 4:12
ሳሙኤል ዔሊን ተክቶ ፈራጅ ሆነ
በእስራኤል የመከር በዓል የሚከበርበት ጊዜ ተቃርቧል። በራማ የምትኖረው ሐና ይሖዋ ጸሎቷን ሰምቶ ወንድ ልጅ ስለሰጣት በጣም ተደስታለች። a ሐና ስዕለቷን ለመፈጸም ስትል ልጅዋን ሳሙኤልን በዚያ እንዲያገለግል “ወደ እግዚአብሔር ቤት አመጣችው።” በዚያም ብላቴናው ሳሙኤል “በካህኑ በዔሊ ፊት እግዚአብሔርን ያገለግል” ጀመር። (1 ሳሙኤል 1:24፤ 2:11) ሳሙኤል ገና ትንሽ ልጅ እያለ ይሖዋ ያነጋገረው ሲሆን በዔሊ ቤተሰብ ላይ ፍርድ እንደሚያመጣ ነገረው። ሳሙኤል እያደገ ሲሄድ የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ የይሖዋ ነቢይ አድርጎ ተቀበለው።
ከጊዜ በኋላ ፍልስጥኤማውያን በእስራኤል ላይ ጦርነት ከፈቱ። በጦርነቱም የይሖዋ ታቦት የተማረከ ሲሆን ሁለቱ የዔሊ ወንዶች ልጆችም ተገደሉ። “ለአርባ ዓመት በእስራኤል ላይ ፈራጅ” የነበረው አረጋዊው ዔሊ ይህን ዜና ሲሰማ ሕይወቱ አለፈ።(1 ሳሙኤል 4:18) ፍልስጥኤማውያን ታቦቱን ማርከው መውሰዳቸው ጥፋት ስላስከተለባቸው ወደ እስራኤላውያን መለሱት። ከዚህ በኋላ ሳሙኤል የእስራኤል ፈራጅ ሆነ፤ ምድሪቱም ሰላም አገኘች።
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-
2:10—ሐና በእስራኤል ሰብዓዊ ንጉሥ ባልነበረበት ወቅት ይሖዋ “ለንጉሡ ኀይልን ይሰጣል” በማለት የጸለየችው ለምንድን ነው? እስራኤላውያን ሰብዓዊ ንጉሥ እንደሚኖራቸው በሙሴ ሕግ ውስጥ አስቀድሞ ተነግሮ ነበር። (ዘዳግም 17:14-18) ያዕቆብም ሊሞት ሲቃረብ “በትረ መንግሥት [የንጉሣዊ ሥልጣን ምልክት] ከይሁዳ እጅ አይወጣም” በማለት ተንብዮ ነበር። (ዘፍጥረት 49:10) ከዚህም በላይ ይሖዋ የእስራኤላውያን ቅድመ አያት ስለሆነችው ስለ ሣራ ሲናገር “የሕዝቦችም ነገሥታት ከእርሷ ይወጣሉ” ብሎ ነበር። (ዘፍጥረት 17:16) ስለዚህ ሐና የጸለየችው ወደፊት ስለሚመጣው ንጉሥ ነበር።
3:3—ሳሙኤል የተኛው በቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ ነበር? አልነበረም። ሳሙኤል ሌዋዊ ቢሆንም የክህነት መብት የሌለው የቀዓት ዝርያ ነበር። (1 ዜና መዋዕል 6:33-38) በመሆኑም በሕጉ መሠረት “ንዋየ ቅዱሳቱን ለአንድ አፍታ እንኳን ለማየት” አይፈቀድለትም። (ዘኍልቍ 4:17-20) ሳሙኤል መግባት የሚፈቀድለት ወደ መገናኛ ድንኳኑ ቅጥር ግቢ ብቻ ነበር። የተኛውም እዚያ መሆን አለበት። ዔሊም ቢሆን የሚተኛው እዚያው መገናኛ ድንኳኑ ግቢ ውስጥ ሳይሆን አይቀርም። “የእግዚአብሔር ታቦት ባለበት” የሚለው አገላለጽ የመገናኛ ድንኳኑን አካባቢ የሚያመለክት መሆን አለበት።
7:7-9, 17—መሥዋዕት በቋሚነት መቅረብ ያለበት ይሖዋ በመረጠው ስፍራ ብቻ ሆኖ እያለ ሳሙኤል በምጽጳ የሚቃጠል መሥዋዕት ያቀረበውና በራማ b መሠዊያ የሠራው ለምንድን ነው? (ዘዳግም 12:4-7, 13, 14፤ ኢያሱ 22:19) ቅዱሱ ታቦት በሴሎ ከነበረው የማደሪያ ድንኳን ከተወሰደ በኋላ በዚያ ቦታ ይሖዋ እንደሚገኝ የሚጠቁም ነገር አልነበረም። በመሆኑም የአምላክ ወኪል የሆነው ሳሙኤል በምጽጳ የሚቃጠል መሥዋዕት ከማቅረቡም በላይ በአርማቴም መሠዊያ አቁሟል። በዚህ ድርጊቱ ይሖዋም የተስማማ ይመስላል።
ምን ትምህርት እናገኛለን?
1:11, 12, 21-23፤ 2:19፦ ሐና የጸሎት ሰው በመሆኗ፣ በትሕትናዋ፣ ለይሖዋ ደግነት ባላት አድናቆትና ለልጅዋ ባላት ጊዜ የማይሽረው ፍቅር አምላክን ለሚፈሩ ሴቶች ሁሉ አርዓያ ትሆናለች።
1:8፦ ሕልቃና ሌሎችን የሚያበረታታ ነገር በመናገር ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቷል። (ኢዮብ 16:5) መጀመሪያ ልቧ በሐዘን የተደቆሰውን ሐናን ‘ልብሽ ለምን ያዝናል?’ በማለት አሳቢነት የተንጸባረቀበት ጥያቄ አቀረበላት። ይህም ሐና ስሜቷን አውጥታ እንድትነግረው አነሳሳት። ከዚያም ሕልቃና “ከዐሥር ወንዶች ልጆች እኔ አልበልጥብሽምን?” በማለት ለእርሷ ያለውን ጥልቅ ፍቅር ገለጸላት።
2:26፤ 3:5-8, 15, 19፦ አምላክ የሰጠንን ሥራ በትጋት በማከናወን፣ መንፈሳዊ ሥልጠና ልናገኝ የምንችልባቸውን አጋጣሚዎች በሚገባ በመጠቀም እንዲሁም ትሑቶችና ሰው አክባሪዎች በመሆን በአምላክም ሆነ በሰዎች ዘንድ ‘ሞገስ’ ማግኘት እንችላለን።
4:3, 4, 10፦ እንደ ኪዳኑ ታቦት ያለ ቅዱስ ነገር እንኳ ምትሐታዊ ኃይል ስለሌለው ጥበቃ ሊያስገኝ አልቻለም። ‘ራሳችንን ከጣዖቶች መጠበቅ’ ይኖርብናል።—1 ዮሐንስ 5:21
የመጀመሪያው የእስራኤል ንጉሥ ስኬታማ ነበር?
ሳሙኤል ዕድሜውን ሙሉ ይሖዋን በታማኝነት ቢያገለግልም ልጆቹ ግን በአምላካዊ ጎዳና አልሄዱም። የእስራኤል ሽማግሌዎች ሰብዓዊ ንጉሥ እንዲነግሥላቸው ሲጠይቁ ይሖዋ የፈለጉትን እንዲያደርጉ ፈቀደ። ሳሙኤልም የይሖዋን መመሪያ በመከተል ሳኦል የተባለውን መልከ ቀና ብንያማዊ ንጉሥ አድርጎ ቀባው። ሳኦል አሞናውያንን ድል በማድረግ የንግሥና ሥልጣኑን አጠናከረ።
ደፋር የሆነው የሳኦል ልጅ ዮናታን የፍልስጥኤማውያንን ጦር ሰፈር ድል በማድረጉ ፍልስጥኤማውያን ብዛት ያለው ሠራዊት ሰብስበው ከእስራኤል ጋር ጦርነት ለመግጠም ተሰለፉ። በዚህ ጊዜ ሳኦል በፍርሃት ስለተዋጠ የይሖዋን ትእዛዝ በመጣስ እርሱ ራሱ የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረበ። በሌላ ጊዜም ደፋሩ ዮናታን ጋሻ ጃግሬውን ብቻ በማስከተል በሌላ የፍልስጥኤማውያን ጦር ሰፈር ላይ ጥቃት ሰነዘረ። ሆኖም ሳኦል በስሜታዊነት በፈጸመው መሐላ ምክንያት ድሉ የተሟላ ሊሆን አልቻለም። ከዚያ በኋላ ባሉት ጊዜያትም ሳኦል በዙሪያው ያሉትን ጠላቶቹን በሙሉ “ወጋቸው።” (1 ሳሙኤል 14:47) ይሁን እንጂ ሳኦል አማሌቃውያንን ካሸነፈ በኋላ ‘እንዲጠፋ የተወሰነውን’ ነገር ሳያጠፋ በመቅረቱ የይሖዋን ትእዛዝ ጣሰ። (ዘሌዋውያን 27:28, 29) በዚህም ምክንያት ይሖዋ ሳኦል ንጉሥ እንዳይሆን ናቀው።
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው፦
9:9—“ዛሬ ነቢይ የሚባለው በዚያ ጊዜ ባለ ራእይ ይባል ነበር” የሚለው አገላለጽ ምን ትርጉም አለው? ይህ ዓረፍተ ነገር በሳሙኤል ጊዜና በእስራኤል ነገሥታት ዘመን ነቢያት ይበልጥ እየታወቁ ሲመጡ “ባለ ራእይ” የሚለው አጠራር “ነቢይ” በሚለው መተካቱን ለመግለጽ የገባ ሊሆን ይችላል። ከነቢያት መካከል የመጀመሪያው ሳሙኤል ነው።—የሐዋርያት ሥራ 3:24
14:24-32, 44, 45—ዮናታን የሳኦልን መሐላ በመጣስ ማር መብላቱ የይሖዋን ሞገስ አሳጥቶታል? ዮናታን እንዲህ ማድረጉ የይሖዋን ሞገስ እንዲያጣ ያደረገው አይመስልም። በመጀመሪያ ደረጃ ዮናታን አባቱ ሕዝቡን ስለ ማስማሉ የሚያውቀው ነገር አልነበረም። ደግሞም ሳኦል ተገቢ ባልሆነ ቅንዓት ወይም ለንግሥና ሥልጣኑ የተሳሳተ አመለካከት በመያዙ ምክንያት የወሰደው ይህ እርምጃ ሕዝቡን ችግር ላይ ጥሎታል። እንዲህ ያለው መሐላ በአምላክ ዘንድ እንዴት ተቀባይነት ሊያገኝ ይችላል? ዮናታን መሐላውን መጣሱ የሚያስከትለውን ቅጣት ለመቀበል ፈቃደኛ የነበረ ቢሆንም ሕዝቡ ሕይወቱን አትርፎለታል።
15:6—ሳኦል ለቄናውያን ለየት ያለ ደግነት ያደረገላቸው ለምንድን ነው? ቄናውያን የሙሴ አማት ልጆች ሲሆኑ እስራኤላውያንን ከሲና ተራራ ተነስተው በተጓዙበት ወቅት ረድተዋቸዋል። (ዘኍልቍ 10:29-32) ከነዓን ከደረሱ በኋላም ቄናውያን ለተወሰነ ጊዜ ያህል ከይሁዳ ሰዎች ጋር ኖረዋል። (መሳፍንት 1:16) ምንም እንኳ ከጊዜ በኋላ ከአማሌቃውያንና ከሌሎች የተለያዩ ሕዝቦች ጋር ቢኖሩም ቄናውያን ከእስራኤላውያን ጋር ጥሩ ግንኙነት ነበራቸው። ከዚህ አንጻር ሳኦል ለቄናውያን ደግነት ማሳየቱ ተገቢ ነበር።
ምን ትምህርት እናገኛለን?
9:21፤ 10:22, 27፦ ሳኦል ንጉሥ ሆኖ በተሾመበት ወቅት ያሳየው ልክን የማወቅና የትሕትና ባሕርይ አንዳንድ “ምናምንቴ ሰዎች” ንግሥናውን በናቁ ጊዜ በችኰላ እርምጃ ከመውሰድ ጠብቆታል። እንዲህ ያለው አመለካከት ተገቢ ያልሆነ እርምጃ እንዳንወስድ ጥበቃ ይሆነናል!
12:20, 21፦ በሰዎች አሊያም በከፍተኛ ወታደራዊ ኃይል እንደመታመን ወይም እንደ ጣዖት አምልኮ ያሉት “ከንቱ” ነገሮች ከይሖዋ አምልኮ ዘወር እንዲያደርጉን ፈጽሞ መፍቀድ የለብንም።
12:24፦ በጥንት ጊዜያትም ሆነ ዛሬ ይሖዋ ለሕዝቡ ያደረጋቸውን “ታላላቅ ነገሮች” ማስታወሳችን ለእርሱ ያለንን አክብሮታዊ ፍርሃት እንዳናጣ እንዲሁም እርሱን በሙሉ ልባችን ለማገልገል እንድንችል ትልቅ እርዳታ ያበረክታል።
13:10-14፤ 15:22-25, 30፦ ታዛዥ ባለመሆንም ይሁን የኩራት መንፈስ በማሳየት የሚገለጸው ትዕቢተኝነት እንዳይጠናወተን መጠንቀቅ ይኖርብናል።—ምሳሌ 11:2
አንድ ትንሽ እረኛ ንጉሥ እንዲሆን ተመረጠ
ሳሙኤል የይሁዳ ነገድ አባል የሆነውን ዳዊትን ከሳኦል ቀጥሎ ንጉሥ እንዲሆን ቀባው። ይህ ከሆነ ብዙም ሳይቆይ ዳዊት ግዙፉን ፍልስጥኤማዊ ጎልያድን አንድ ጊዜ በወነጨፋት ድንጋይ ገደለው። በዚህም የተነሳ በዳዊትና በዮናታን መካከል የጠበቀ ወዳጅነት ተመሠረተ። ሳኦልም ዳዊትን የሠራዊቱ አዛዥ አድርጎ ሾመው። ዳዊት በተደጋጋሚ ጊዜያት ድል ይቀዳጅ ስለነበር የእስራኤል ሴቶች “ሳኦል ሺህ ገደለ፤ ዳዊት ግን ዐሥር ሺህ ገደለ” በማለት ዘፈኑለት። (1 ሳሙኤል 18:7) በዚህ ጊዜ በቅናት የበገነው ሳኦል ዳዊትን ለመግደል ፈለገ። ሳኦል ሦስት ጊዜ ያህል ሊገድለው ከሞከረ በኋላ ዳዊት ከእርሱ ሸሽቶ ስደተኛ ሆነ።
ዳዊት በስደት ባሳለፋቸው ዓመታት ውስጥ ከአንዴም ሁለት ጊዜ ሳኦልን መግደል የሚችልበት አጋጣሚ ቢያገኝም እንዲህ ሳያደርግ ቀርቷል። በዚህ ጊዜ አቢግያ ከተባለችው ውብ ሴት ጋር የተገናኘ ሲሆን ከጊዜ በኋላ ሚስቱ አደረጋት። ፍልስጥኤማውያን እስራኤልን ለመውጋት ሲመጡ ሳኦል መመሪያ ለማግኘት ይሖዋን ጠየቀ። ሆኖም ይሖዋ ትቶት ነበር። ሳሙኤል ደግሞ ሞቷል። የሚያደርገው የጠፋው ሳኦል ወደ መናፍስት ጠሪ ቢሄድም ከፍልስጥኤማውያን ጋር በሚያደርገው ውጊያ እንደሚገደል ተነገረው። በጦርነቱ ወቅት ሳኦል ከባድ ጉዳት ሲደርስበት ወንዶች ልጆቹ ተገደሉ። መጽሐፉ በሳኦል ውድቀት ዘገባውን ይደመድማል። ዳዊትም ከስደት ኑሮው አልተላቀቀም።
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው፦
16:14—ሳኦልን ያሠቃየው ክፉ መንፈስ ምንድን ነው? ሳኦል የአእምሮ ሰላም እንዲያጣ ያደረገው መጥፎ መንፈስ ክፉ የሆነው የልብና የአእምሮ ዝንባሌው ይኸውም መጥፎ እንዲያደርግ የሚገፋፋው ውስጣዊ ስሜቱ ነበር። የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ከሳኦል ሲርቅ ሳኦል ከአምላክ ያገኝ የነበረውን ጥበቃ ስላጣ የራሱ ክፉ መንፈስ ተቆጣጠረው። ይህ ክፉ መንፈስ በአምላክ ቅዱስ መንፈስ ምትክ በሳኦል ላይ እንዲያድር የፈቀደው ይሖዋ በመሆኑ “ከእግዚአብሔር ዘንድ የታዘዘ ክፉ መንፈስ” ተብሎ ተጠርቷል።
17:55—ከ1 ሳሙኤል 16:17-23 አንጻር ሳኦል፣ ዳዊት የማን ልጅ እንደሆነ የጠየቀው ለምን ነበር? ሳኦል ይህንን ጥያቄ ያቀረበው የዳዊትን አባት ስም ለማወቅ ብቻ ብሎ አልነበረም። ግዙፉን ፍልስጥኤማዊ በመግደል አስደናቂ ነገር ያከናወነው ወጣት አባት ምን ዓይነት ሰው እንደሆነ ለማወቅ ፈልጎ መሆን አለበት።
ምን ትምህርት እናገኛለን?
16:6, 7፦ ለሰዎች ውጫዊ ገጽታ ትኩረት ከመስጠት ወይም ከዚህ በመነሳት ምን ዓይነት ሰዎች እንደሆኑ ለመገምገም ከመቸኮል ይልቅ ሰዎችን በይሖዋ ዓይን ለማየት መጣር ይኖርብናል።
17:47-50፦ “ሰልፉ የእግዚአብሔር ስለ ሆነ” እንደ ጎልያድ ያሉ አስፈሪ ጠላቶቻችን የሚያደርሱብንን ተቃውሞ ወይም ስደት በድፍረት መጋፈጥ እንችላለን።
18:1, 3፤ 20:41, 42፦ ይሖዋን ከሚወድዱ ሰዎች መካከል እውነተኛ ጓደኞች ማግኘት ይቻላል።
21:12, 13፦ ይሖዋ በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙንን ችግሮች ለመወጣት፣ በማሰብ ችሎታችንና ባለን ተሰጥኦ እንድንጠቀም ይጠብቅብናል። ማስተዋል፣ እውቀትና ልባምነትን ወይም የማሰብ ችሎታን ማግኘት እንድንችል በመንፈሱ ያስጻፈውን ቃሉን ሰጥቶናል። (ምሳሌ 1:4) ከዚህም በላይ ከክርስቲያን ሽማግሌዎች እርዳታ ማግኘት እንችላለን።
24:6፤ 26:11፦ ዳዊት ይሖዋ ለቀባው ሰው ልባዊ አክብሮት በማሳየት ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል!
25:23-33፦ አቢግያ በአስተዋይነቷ አርዓያ ትሆናለች።
28:8-19፦ ክፉ መናፍስት ሰዎችን ለማሳሳት ወይም ለመጉዳት ሲሉ የሞቱ ሰዎችን መስለው ሊቀርቡ ይችላሉ። ከማንኛውም ዓይነት መናፍስታዊ ድርጊት ልንርቅ ይገባል።—ዘዳግም 18:10-12
30:23, 24፦ ዳዊት ዘኍልቍ 31:27ን መሠረት በማድረግ ያስተላለፈው ውሳኔ ይሖዋ በጉባኤው ውስጥ ረዳት ሆነው የሚሠሩትንም ከፍ አድርጎ እንደሚመለከታቸው ያሳያል። እንግዲያው የምናደርገውን ሁሉ ‘ለሰው ሳይሆን ለይሖዋ እንደምናደርገው ቆጥረን በሙሉ ልባችን እናድርገው።’—ቆላስይስ 3:23
‘ከመሥዋዕት የሚበልጥ’ ነገር
ስለ ዔሊ፣ ሳሙኤል፣ ሳኦልና ዳዊት የሚተርከው ዘገባ የትኛውን መሠረታዊ ሐቅ አጎልቶ ያሳያል? “መታዘዝ ከመሥዋዕት፣ ማዳመጥም ከአውራ በግ ሥብ ይበልጣል። ዐመፅ እንደ ጥንቆላ ያለ ኀጢአት፣ እልኸኝነትም እንደ ጣዖት አምልኮ ያለ ክፉ ነገር ነው” የሚለው ነጥብ ጎልቷል።—1 ሳሙኤል 15:22, 23
በዓለም ዙሪያ ስለ አምላክ መንግሥት የመስበክና ደቀ መዛሙርት የማድረግ ግሩም መብት ተሰጥቶናል። ለይሖዋ ‘የከንፈራችንን ፍሬ’ ስናቀርብ በቃሉ እንዲሁም በምድራዊ ድርጅቱ አማካኝነት የሚሰጠንን መመሪያ ለመታዘዝ የምንችለውን ሁሉ ማድረግ ይኖርብናል።—ሆሴዕ 14:2፤ ዕብራውያን 13:15
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በአንደኛ ሳሙኤል መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሱ የተለያዩ ቦታዎች የት እንደሚገኙ ለማወቅ በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ‘መልካሚቱን ምድር ተመልከት’ የተባለውን ብሮሹር ገጽ 18-19 ተመልከት።
b አርማቴም መሴፋ በአጭሩ ሲጠራ ራማ ይባላል።—1 ሳሙኤል 1:19
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ትሑትና ልኩን የሚያውቅ ሰው የነበረው የእስራኤል የመጀመሪያው ንጉሥ ከጊዜ በኋላ ኩሩና እብሪተኛ ሆኗል
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እንደ ጎልያድ ከመሰሉ ጠላቶች ተቃውሞ ሲደርስብን ስለምን ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን?