“ፒም” የመጽሐፍ ቅዱስን ታሪክ እውነተኝነት አረጋገጠ
“ፒም” የመጽሐፍ ቅዱስን ታሪክ እውነተኝነት አረጋገጠ
“ፒም” የሚለው ቃል በጥንቱ የዕብራይስጥ ቅዱስ ጽሑፍ ውስጥ የሚገኘው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። በንጉሥ ሳኦል ዘመን እስራኤላውያን የብረት መሣሪያዎቻቸውን የሚያስሉት ፍልስጥኤማውያን ዘንድ ወዳሉት ቀጥቃጮች በመሄድ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ “ማረሻና ዶማ ለማሾል የሚከፈለው ዋጋ ሁለት ሦስተኛ ሰቅል (በዕብራይስጡ “ፒም” ) ሲሆን፣ መንሽና ጠገራ እንዲሁም የበሬ መንጃ ለማሾል ደግሞ አንድ ሦስተኛ ሰቅል ነበር” ይላል።—1 ሳሙኤል 13:21—የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።
ፒም ምንድን ነው? በ1907 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በጥንቷ የጂዘር ከተማ በተደረገ ቁፋሮ የፒም መለኪያ የሆነ ድንጋይ ለመጀመሪያ ጊዜ እስኪገኝ ድረስ የፒም ምንነት አይታወቅም ነበር። ቀደም ባሉት ዘመናት የነበሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች “ፒም” የሚለውን ቃል መተርጎም ያስቸግራቸው ነበር። ለአብነት ያህል፣ የኪንግ ጄምስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም 1 ሳሙኤል 13:21ን ሲተረጉም “ዶማውን፣ ሞፈሩን፣ መንሹን፣ መጥረቢያውንና የበሬ መንጃውን ለማሾል በሞረድ ይጠቀሙ ነበር” ብሏል።
በዛሬው ጊዜ ያሉ ምሑራን ፒም በአማካይ 7.82 ግራም ወይም ዋነኛው የዕብራውያን የክብደት መለኪያ የሆነው የሰቅል ሁለት ሦስተኛ ገደማ ያህል የሚመዝን መለኪያ እንደነበረ ያውቃሉ። ፍልስጥኤማውያን የእስራኤላውያንን መሣሪያዎች ለመሳል የሚያስከፍሏቸው የፒም ክብደት ያለው የብር ቁርጥራጭ ነበር። በ607 ከክርስቶስ ልደት በፊት የይሁዳ መንግሥት ሲወድቅና ዋና ከተማዋ ኢየሩሳሌም ስትጠፋ ሰቅል የክብደት መመዘኛ መሆኑ ቀረ። ታዲያ ፒም የዕብራይስጡን ቅዱስ ጽሑፍ ታሪካዊ ትክክለኝነት የሚያረጋግጠው እንዴት ነው?
አንዳንድ ምሑራን የአንደኛ ሳሙኤልን መጽሐፍ ጨምሮ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች የተጻፉት በግሪካውያንና በሮማውያን ዘመን፣ እንዲያውም ከሁለተኛው እስከ መጀመሪያው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት አካባቢ ባለው ጊዜ ውስጥ እንደሆነ ይናገራሉ። በመሆኑም “እነዚህ መጻሕፍት . . . ‘ጥንታዊ እንዳልሆኑ፣’ ‘በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለተገለጸችው’ ወይም ስለ ‘ጥንቷ እስራኤል’ እውነተኛ ታሪካዊ ዘገባ በማቅረብ ረገድ ብዙም ፋይዳ እንደሌላቸው ወይም ጨርሶ እንደማይጠቅሙና በዘመናዊው የአይሁድና የክርስትና ኅብረተሰብ የተዘጋጁ ጽሑፎች” እንደሆኑ ይነገር ነበር።
ይሁን እንጂ በመካከለኛው ምሥራቅ አካባቢ የአርኪኦሎጂና የአንትሮፖሎጂ ፕሮፌሰር የሆኑት ዊልያም ዴቨር በ1 ሳሙኤል 13:21 ላይ ስለተጠቀሰው የፒም መለኪያ እንዲህ ብለዋል:- “በግሪካውያንና በሮማውያን ዘመን ይኖሩ የነበሩ ጸሐፊዎች እነዚህ መለኪያዎች ከጠፉና ከተረሱ ከበርካታ መቶ ዓመታት በኋላ ስለ እነሱ ‘ፈጥረው’ ሊጽፉ አይችሉም። እንዲያውም በ20ኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት መባቻ ላይ በዕብራይስጥ ፒም የሚለው ቃል የተጻፈባቸው ነገሮች በቁፋሮ እስከተገኙበት ጊዜ ድረስ . . . ይህንን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ መረዳት አይቻልም ነበር።” ፕሮፌሰሩ ቀጥለውም እንዲህ ብለዋል:- “በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት ታሪኮች በሙሉ በግሪካውያንና በሮማውያን ዘመን የተጻፉ ‘የፈጠራ ሥራዎች’ ከሆኑ ይህ [ስለ ፒም የሚናገረው] ታሪክ እንዴት በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ሊገኝ ቻለ? እርግጥ ነው፣ አንድ ሰው ስለ ፒም የሚናገረው ሐሳብ ተጨማሪ መረጃ ለመስጠት የገባ ‘ዝርዝር ጉዳይ’ ነው ሊል ይችላል። ይህ እውነት ቢሆንም ‘ታሪክ የጥቃቅን ዝርዝር ጉዳዮች ስብስብ’ መሆኑ በብዙዎች ዘንድ የታወቀ ነው።”
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የፒም የክብደት መለኪያ የሰቅል ሁለት ሦስተኛ ያህል ነበር