ለአምላክ ቃል ፍቅር የነበረው ትሑት አፍሪካዊ
ለአምላክ ቃል ፍቅር የነበረው ትሑት አፍሪካዊ
አፍሪካን የሚጎበኙ ብዙዎች ከአገሬው ሰዎች ጋር በቀላሉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት መጀመር እንደሚቻል ሲያውቁ ይገረማሉ። “የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው?” ወይም “የምግብ እጥረት፣ በሽታ፣ ጦርነት እንዲሁም ወንጀል ዘላቂ መፍትሄ ይኖራቸው ይሆን?” እንደሚሉት ያሉ ጥያቄዎች በቀላሉ ሰሚ ጆሮ ያገኛሉ። ብዙዎቹ አንድ የማያውቁት ሰው መልሶቹን ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ቢያሳያቸው ደስ ይላቸዋል። ይህ ደግሞ ብዙውን ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመጀመር መንገድ ይከፍታል። ከዚያም ግለሰቡ መንፈሳዊ እድገት በማድረግ የተጠመቀ ክርስቲያን ይሆናል።
ይህን የመሰለ ምላሽ ከሰጡት አፍሪካውያን መካከል አንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በሐዋርያት ሥራ 8:26-40 ላይ ተጠቅሷል። ይህ ሰው ለእውነተኛው አምላክ ለይሖዋ አምልኮ ለማቅረብ ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዞ የነበረ ኢትዮጵያዊ ነው።
ከታች ባለው ሥዕል ላይ እንደሚታየው በሰረገላ ወደ አገሩ እየተመለሰ የነበረው ኢትዮጵያዊ የያዘውን ጥቅልል ያነብባል። በዚህን ጊዜ አንድ የማያውቀው ሰው ወደ እርሱ ቀርቦ “ለመሆኑ፣ የምታነበውን ታስተውለዋለህን?” ሲል ጠየቀው። ኢትዮጵያዊው እርዳታ እንደሚያስፈልገው በትሕትና በማመን ሰውየውን ማለትም ክርስቲያኑን ወንጌላዊ ፊልጶስን ወደ ሰረገላው ወጥቶ አብሮት እንዲቀመጥ ለመነው። ከዚያም እያነበበ ያለው የቅዱሳን ጽሑፎች ክፍል ምን ትርጉም እንዳለው እንዲያብራራለት ጠየቀው። ፊልጶስ በቅርቡ ስለሞተው መሲሕ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚናገር ትንቢት መሆኑን ገለጸለት። በተጨማሪም “ስለ ኢየሱስ ወንጌል” ሌሎች ነገሮችን ነገረው፤ ይህ ወንጌል ወይም ምሥራች ትንሣኤውን እንደሚጨምር ምንም ጥርጥር የለውም።
ኢትዮጵያዊው እነዚህን አስደናቂ እውነቶች ከሰማ በኋላ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ለመሆን በመፈለጉ “እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምን ነገር አለ?” በማለት ጠየቀ። በጣም የተደሰተው ይህ ትሑት አፍሪካዊ ከተጠመቀ በኋላ ወደ አገሩ የሚያደርገውን ጉዞ ቀጠለ፤ መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ሰው ከዚህ በላይ የሚናገረው ነገር የለም።
በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ይህንን ተመሳሳይ ምሥራች እንዲያውቁ በመርዳት ላይ ናቸው። በአሁኑ ወቅት ስድስት ሚሊዮን ለሚያክሉ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን በነፃ ያስተምራሉ።