በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ልጆቻችን ውድ ስጦታ ናቸው

ልጆቻችን ውድ ስጦታ ናቸው

ልጆቻችን ውድ ስጦታ ናቸው

“እነሆ፤ ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታ ናቸው፤ የማሕፀንም ፍሬ ከቸርነቱ የሚገኝ ነው።”—መዝሙር 127:3

1. የመጀመሪያው ሕፃን የተወለደው እንዴት ነው?

 ይሖዋ አምላክ የመጀመሪያዎቹን ወንድና ሴት ሲፈጥር ታላቅ ተአምር ሊከናወን የሚችልበትን ሁኔታ እንዴት እንዳዘጋጀ ተመልከት። አባትየው አዳምና እናቲቱ ሔዋን የየራሳቸውን ክፋይ አዋጥተው የተፈጠረው ሕዋስ በሔዋን ማሕጸን ውስጥ አድጎ ሙሉ አዲስ ሰው ሆነና የመጀመሪያው ልጅ ተወለደ። (ዘፍጥረት 4:1) እስከዚህ ዘመን ድረስ የአንድ ልጅ መፀነስና መወለድ በጣም ሲያስገርም የኖረ ጉዳይ ሲሆን ብዙዎች ይህ ክስተት ተአምር እንደሆነ ይናገራሉ።

2. በአንዲት ነፍሰ ጡር ማሕጸን ውስጥ የሚፈጸመው ክንውን ተዓምር ነው እንድትል የሚያደርግህ ምንድን ነው?

2 እናቲቱ ከአባትየው ጋር ባደረገችው ግንኙነት ምክንያት የተፈጠረው የመጀመሪያው ሕዋስ በ270 ቀናት ውስጥ አድጎ በብዙ ትሪሊዮኖች በሚቆጠሩ ሕዋሳት የተገነባ ሕፃን ይሆናል። በመጀመሪያው ሕዋስ ውስጥ ከ200 የሚበልጡ የተለያዩ ዓይነት ሕዋሳትን ለመሥራት የሚያስችል መመሪያ አለ። በአስገራሚ ሁኔታ የተወሳሰቡት እነዚህ ሕዋሳት ከሰው ልጆች የመረዳት ችሎታ በላይ በሆነው በዚህ እጹብ ድንቅ መመሪያ መሠረት በተወሰነላቸው ቅደም ተከተልና ሥርዓት ተቀናጅተው አዲስ ሕያው አካል ያስገኛሉ!

3. ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ ያላቸው በርካታ ሰዎች ልጅ እንዲወለድ የሚያደርገው አምላክ መሆን እንዳለበት የሚስማሙት ለምንድን ነው?

3 ታዲያ የዚህ ሕፃን ፈጣሪ ማን ነው ትላለህ? የሕይወት ምንጭ የሆነው አምላክ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። የመጽሐፍ ቅዱሱ መዝሙራዊ “እግዚአብሔር እርሱ አምላክ እንደ ሆነ እወቁ፤ እርሱ ሠራን እኛም አይደለንም” በማለት ዘምሯል። (መዝሙር 100:3 የ1954 ትርጉም) ወላጆች፣ እንዲህ ያለ ውድ ሕፃን የወለዳችሁት የተለየ ችሎታ ስላላችሁ እንዳልሆነ አሳምራችሁ ታውቁታላችሁ። አንድ ሕፃን ልጅ ተአምራዊ በሆነ መንገድ እንዲፈጠር ሊያደርግ የሚችለው ለጥበቡ ዳርቻ የሌለው አምላክ ብቻ ነው። ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ ያላቸው ሰዎች አንድ ሕፃን በእናቱ ማሕጸን ውስጥ እንዲፈጠር የሚያደርገው ታላቁ ፈጣሪ መሆኑን በሺዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት ጀምሮ ሲያምኑበት ቆይተዋል። አንተስ?—መዝሙር 139:13-16

4. ይሖዋ የትኛው መጥፎ የሰዎች ባሕርይ ፈጽሞ አይታይበትም?

4 ይሁን እንጂ ይሖዋ ሰዎች ዘር መተካት የሚችሉበትን ባዮሎጂያዊ ሂደት ፈጥሮ ብቻ አሳቢነት በጎደለው ሁኔታ እርግፍ አድርጎ ትቷቸዋል? አንዳንድ ሰዎች አሳቢነት የጎደላቸው ናቸው፤ ይሖዋ ግን ፈጽሞ እንደዚያ አይደለም። (መዝሙር 78:38-40) መጽሐፍ ቅዱስ በመዝሙር 127:3 ላይ “እነሆ፤ ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታ ናቸው፤ የማሕፀንም ፍሬ ከቸርነቱ የሚገኝ ነው” በማለት ይናገራል። እስቲ በመጀመሪያ ስጦታ ምን እንደሆነና ምን እንደሚያረጋግጥልን እንመልከት።

ውርስ እና ችሮታ

5. ልጆች ውርስ ወይም ስጦታ ናቸው የምንለው ለምንድን ነው?

5 ውርስ እንደ ስጦታ ነው። ብዙውን ጊዜ ወላጆች ለልጆቻቸው በስጦታ መልክ ውርስ ለማውረስ ብዙ ይደክማሉ። ይህ ውርስ ወይም ስጦታ ገንዘብ፣ ንብረት አሊያም አንድ ዓይነት ውድ ሀብት ሊሆን ይችላል። ስጦታው ምንም ይሁን ምን ወላጆች ልጆቻቸውን እንደሚወዷቸው የሚያረጋግጥ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ በፍቅር ተገፋፍቶ ልጆችን ለወላጆች ስጦታ አድርጎ እንደሰጣቸው ይናገራል። ወላጅ ከሆንክ፣ ተግባርህ ልጆችህን ከጽንፈ ዓለሙ ፈጣሪ በአደራ እንዳገኘሃቸው ስጦታዎች አድርገህ እንደምትመለከታቸው የሚያሳይ ይመስልሃል?

6. ይሖዋ ለሰዎች ልጅ የመውለድ ችሎታ የሰጣቸው ለምንድን ነው?

6 ይሖዋ ለአዳምና ለሔዋን ልጅ የመውለድ ስጦታ የሰጠበት ዋነኛው ዓላማ ምድር በዘሮቻቸው እንድትሞላ ነበር። (ዘፍጥረት 1:27, 28፤ ኢሳይያስ 45:18) ይሖዋ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ መላእክት በቀጥታ ወደ ሕልውና እንዲመጡ እንዳደረገው እያንዳንዱን ሰው በግለሰብ ደረጃ አልፈጠረም። (መዝሙር 104:4፤ ራእይ 4:11) ከዚህ ይልቅ አምላክ ሰዎች መሰላቸውን የመውለድ ችሎታ እንዲኖራቸው አድርጎ ፈጥሯቸዋል። አንድ አባትና አንዲት እናት እንዲህ ያለ ልጅ ወልደው የማሳደግ አጋጣሚ ማግኘታቸው እንዴት ያለ አስደናቂ መብት ነው! ወላጅ ከሆንክ እንዲህ ያለውን ውድ ስጦታ ማግኘት የምትችልበትን ችሎታ ስለሰጠህ ይሖዋን ታመሰግነዋለህ?

ኢየሱስ ከተወው ምሳሌ ተማር

7. ከአንዳንድ ወላጆች በተቃራኒ ኢየሱስ ‘ለሰው ልጆች’ አሳቢነትና ርኅራኄ ያሳየው እንዴት ነው?

7 የሚያሳዝነው ግን ልጆቻቸውን ከይሖዋ እንደተገኙ በረከቶች አድርገው የሚመለከቱት ሁሉም ወላጆች አይደሉም። በርካታ ወላጆች ለልጆቻቸው ርኅራኄ የላቸውም። እንዲህ ያሉ ወላጆች የይሖዋን ወይም የልጁን ዓይነት ባሕርይ አያንጸባርቁም። (መዝሙር 27:10፤ ኢሳይያስ 49:15) በተቃራኒው ግን ኢየሱስ ምን ያህል ለልጆች አሳቢ እንደነበረ ተመልከት። ሰው ሆኖ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት ማለትም ኃያል መንፈሳዊ ፍጡር ሆኖ በሰማይ ይኖር በነበረበት ወቅት እንኳ ‘በሰው ልጆች ደስ ይሰኝ’ እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ምሳሌ 8:31) ለእኛ ለሰው ልጆች ታላቅ ፍቅር ስለነበረው የዘላለም ሕይወት ማግኘት እንድንችል ሕይወቱን በፈቃደኝነት ቤዛ አድርጎ ሰጥቷል።—ማቴዎስ 20:28፤ ዮሐንስ 10:18

8. ኢየሱስ ለወላጆች ምን ግሩም ምሳሌ ትቷል?

8 ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት ወላጆች ሊከተሉት የሚችሉት ግሩም ምሳሌ ትቶላቸዋል። እስቲ ምን አድርጎ እንደነበር እንመልከት። በጣም ሥራ በበዛበትና ውጥረት ውስጥ በነበረበት ጊዜም እንኳ ከልጆች ጋር ጊዜ አሳልፏል። ልጆች ገበያ ውስጥ ሲጫወቱ ተመልክቶ ሲያደርጉት የነበረውን ነገር ሌሎችን ለማስተማር ምሳሌ አድርጎ ተጠቅሞበታል። (ማቴዎስ 11:16, 17) ለመጨረሻ ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም በተጓዘበት ወቅት መከራ እንደሚደርስበትና እንደሚገደል አውቆ ነበር። በዚህ ጊዜ ሰዎች ልጆቻቸውን ይዘው ወደ ኢየሱስ ሲመጡ ደቀ መዛሙርቱ ተጨማሪ ውጥረት እንዳይፈጥርበት በማሰብ ሳይሆን አይቀርም ልጆቹን ሊያባርሯቸው ሞከሩ። ኢየሱስ ግን ደቀ መዛሙርቱን የገሠጻቸው ከመሆኑም በላይ “ሕፃናት ወደ እኔ ይምጡ፤ አትከልክሏቸው” በማለት በልጆች ‘ደስ እንደሚሰኝ’ አሳይቷል።—ማርቆስ 10:13, 14

9. ከቃል ይልቅ ድርጊት ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው ለምን ሊሆን ይችላል?

9 ኢየሱስ ከተወው ምሳሌ ትምህርት ማግኘት እንችላለን። ሥራ ቢበዛብን እንኳ ልጆች ወደ እኛ ሲመጡ የምንቀበላቸው እንዴት ነው? ልክ እንደ ኢየሱስ ነው? ኢየሱስ በፈቃደኝነት ካደረገው ነገር እንደምንገነዘበው ልጆች በተለይ የወላጆቻቸውን ጊዜና ትኩረት ይሻሉ። “እወድሃለሁ ወይም እወድሻለሁ” እንደሚሉት ያሉ ቃላትን መናገር አስፈላጊ እንደሆነ አይካድም። ይሁን እንጂ ከቃላት ይልቅ ተግባር የጎላ ድምፅ አለው። ፍቅራችሁ የሚገለጸው በቃል ብቻ ሳይሆን ይበልጡኑ በድርጊታችሁ ነው። ለልጆቻችሁ ያላችሁ ፍቅር በምትሰጧቸው ጊዜና ትኩረት እንዲሁም በምታደርጉላቸው እንክብካቤ መጠን ይለካል። ይሁን እንጂ ይህን ሁሉ አድርጋችሁም እንኳ እናንተ እንደምታስቡት ወዲያውኑ ተጨባጭ ውጤት አታገኙ ይሆናል። ትዕግሥት አስፈላጊ ነው። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን የያዘበትን መንገድ የምንኮርጅ ከሆነ ትዕግሥት መማር እንችላለን።

ኢየሱስ ያሳየው ትዕግሥትና ፍቅር

10. ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ትሕትና ያስተማራቸው እንዴት ነበር? መጀመሪያ ላይ ተሳክቶለት ነበር?

10 ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ትልቅ ቦታ ለማግኘት እርስ በርሳቸው በተደጋጋሚ እንደሚፎካከሩ ያውቅ ነበር። አንድ ቀን ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ቅፍርናሆም ከደረሱ በኋላ “በመንገድ ላይ የምትከራከሩት ስለ ምን ነበር?” ብሎ ጠየቃቸው። “እነርሱ ግን በመንገድ ላይ የተከራከሩት ከሁሉ የሚበልጥ ማን ነው በሚል ስለ ነበር ዝም አሉ።” ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እያመናጨቀ ከመገሠጽ ይልቅ ህያው የሆነ ምሳሌ በመጠቀም በትዕግሥት ትሕትናን አስተማራቸው። (ማርቆስ 9:33-37) ምሳሌው የሚፈልገውን ውጤት አስገኝቶለት ይሆን? ወዲያውኑ አላስገኘም። ከስድስት ወራት ገደማ በኋላ ያዕቆብና ዮሐንስ በአምላክ መንግሥት የላቀ ቦታ እንዲሰጣቸው ኢየሱስን በእናታቸው በኩል ጠየቁት። በዚህ ጊዜም ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ አስተሳሰባቸውን እንዲያስተካክሉ በትዕግሥት ረድቷቸዋል።—ማቴዎስ 20:20-28

11. (ሀ) የኢየሱስ ሐዋርያት የማለፍን በዓል ወደሚያከብሩበት ቤት ከደረሱ በኋላ ሳያከናውኑ የቀሩት የአካባቢው ልማድ ምን ነበር? (ለ) ኢየሱስ ምን አደረገ? ጥረቱስ ወዲያው ተሳክቶለት ነበር?

11 ከዚያ ብዙም ሳይቆይ በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ የሚከበረው የማለፍ በዓል ሲደርስ ኢየሱስና ሐዋርያቱ በዓሉን ለብቻቸው ለማክበር ተሰባሰቡ። አንድ ፎቅ ላይ ባለ ክፍል ውስጥ በደረሱበት ወቅት ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት መካከል አንዳቸውም እንኳ በአካባቢው ልማድ መሠረት የጓደኞቻቸውን አቧራ የለበሰ እግር ለማጠብ በፈቃደኝነት አልተነሱም። እግር ማጠብ በአገልጋዮች ወይም በሴቶች መከናወን ያለበት ዝቅተኛ ሥራ ተደርጎ ይታይ ነበር። (1 ሳሙኤል 25:41፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:10) ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ትልቅ ሥልጣን ወይም ቦታ ለማግኘት የሚያደርጉትን ፉክክር እንዳልተዉ የሚያሳይ ሁኔታ ሲመለከት በጣም አዝኖ መሆን አለበት! በመሆኑም ኢየሱስ የእያንዳንዳቸውን እግር በማጠብ እነርሱም ሌሎችን በማገልገል ምሳሌውን እንዲኮርጁ አጥብቆ አሳሰባቸው። (ዮሐንስ 13:4-17) ታዲያ ምሳሌውን ተከትለው ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ “ደግሞም ከመካከላቸው ማን እንደሚበልጥ በእነርሱ ዘንድ ክርክር ተነሣ” በማለት በዚያው ምሽት ትንሽ ቆየት ብሎ ስለተከሰተው ሁኔታ ይናገራል።—ሉቃስ 22:24

12. ወላጆች ልጆቻቸውን ለማሠልጠን በሚያደርጉት ጥረት ረገድ ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ መኮረጅ የሚችሉት እንዴት ነው?

12 እናንተ ወላጆች፣ ልጆቻችሁ የሰጣችኋቸውን ምክር ተግባራዊ ሳያደርጉ ሲቀሩ ኢየሱስ እንዲህ ያለ ሁኔታ ባጋጠመው ጊዜ ምን ተሰምቶት ሊሆን እንደሚችል ለማሰብ ትሞክራላችሁ? ኢየሱስ ሐዋርያቱ ስህተታቸውን ለማረም ጊዜ ቢወስድባቸውም እንኳ ተስፋ እንዳልቆረጠ አስታውሱ። ያሳየው ትዕግሥት ውሎ አድሮ ፍሬ አፍርቷል። (1 ዮሐንስ 3:14, 18) ወላጆች፣ ልጆቻችሁን ለማሠልጠን በምታደርጉት ጥረት ረገድ ፈጽሞ ተስፋ ባለመቁረጥ ኢየሱስ ያሳየውን ፍቅርና ትዕግሥት መኮረጅ ይኖርባችኋል።

13. አንድ ወላጅ ልጁ ጥያቄ ሲጠይቀው ተቆጥቶ ማባረር የማይገባው ለምንድን ነው?

13 ልጆች ወላጆቻቸው እንደሚወዷቸውና እንደሚያስቡላቸው ሊሰማቸው ይገባል። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ምን እንደሚያስቡ የማወቅ ፍላጎት ስለነበረው ጥያቄ ሲጠይቁት ያዳምጣቸው ነበር። እንዲሁም ስለ አንዳንድ ጉዳዮች ምን እንደሚሰማቸው ይጠይቃቸው ነበር። (ማቴዎስ 17:25-27) አዎን፣ ውጤታማ ከሆኑት የማስተማሪያ ዘዴዎች መካከል በትኩረት ማዳመጥና ልባዊ አሳቢነት ማሳየት ይገኙበታል። አንድ ወላጅ ልጁ ጥያቄ ሲጠይቀው “ሂድ ከዚህ! ሥራ ላይ መሆኔ አይታይህም?” በማለት ተቆጥቶ ማባረር የሚቀናው ከሆነ ማስተካከል ይኖርበታል። በእርግጥ ሥራ በዝቶበት ቢሆን እንኳ ጉዳዩን በኋላ እንደሚነጋገሩበት ለልጁ ሊነግረው ይገባል። ከዚያም ወላጆች ቃላቸውን አክብረው ልጁን ማነጋገር አለባቸው። እንዲህ የሚያደርጉ ከሆነ ልጁ ወላጆቹ በእርግጥ እንደሚያስቡለት ስለሚሰማው ይበልጥ ይተማመንባቸዋል።

14. ወላጆች ለልጆቻቸው ፍቅር ማሳየትን በሚመለከት ከኢየሱስ ምን መማር ይችላሉ?

14 ወላጆች እጃቸውን በልጆቻቸው ትከሻ ላይ ጣል በማድረግና በማቀፍ ፍቅራቸውን መግለጻቸው አስፈላጊ ነው? ወላጆች በዚህም ረገድ ኢየሱስ ከተወው ምሳሌ ትምህርት መቅሰም ይችላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ “ሕፃናቱንም ዐቀፋቸው፤ እጁንም ጭኖ ባረካቸው” በማለት ስለ ኢየሱስ ይናገራል። (ማርቆስ 10:16) ሕፃናቱ ምን የተሰማቸው ይመስልሃል? ከልብ ደስ እንዳላቸውና ኢየሱስንም በጣም እንደወደዱት ምንም ጥርጥር የለውም! በእናንተ በወላጆችና በትንንሽ ልጆቻችሁ መካከል ልባዊ ፍቅርና መዋደድ ካለ ልጆቻችሁ የምትሰጧቸውን ተግሣጽና ትምህርት መቀበል አይከብዳቸውም።

ከልጆችህ ጋር ምን ያህል ጊዜ ማሳለፍ ይኖርብሃል?

15, 16. የልጆችን አስተዳደግ በሚመለከት ሰፊ ተቀባይነት ያገኘው ጽንሰ ሐሳብ የትኛው ነው? የመነጨውስ ከምን ሊሆን ይችላል?

15 ይሁን እንጂ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ብዙ ጊዜ ማሳለፋቸውና ፍቅራዊ አሳቢነት ማሳየታቸው ያን ያህል አስፈላጊ እንዳልሆነ የሚሰማቸው ሰዎች አሉ። የልጆችን አስተዳደግ በሚመለከት ‘ከልጆች ጋር ጥሩ ጊዜ ማሳለፍ በቂ ነው’ የሚል በረቀቀ ዘዴ የተሰራጨ አንድ ጽንሰ ሐሳብ አለ። የዚህ ጽንሰ ሐሳብ አቀንቃኞች ልጆች ከወላጆቻቸው ጋር የሚያሳልፉት ጊዜ ትርጉም ያለው፣ በሚገባ የታሰበበትና ጥሩ እቅድ የወጣለት እስከሆነ ድረስ ሰፊ መሆን እንደማያስፈልገው ይናገራሉ። ይሁን እንጂ ይህ አስተሳሰብ ትክክል ነው? እውነት የልጆችን ደኅንነት ግምት ውስጥ ያስገባ ጽንሰ ሐሳብ ነው?

16 በርካታ ልጆችን ያነጋገሩ አንድ ጸሐፊ ልጆች “ከወላጆቻቸው በጣም የሚፈልጉት ሰፊ ጊዜ” እና “ያልተከፋፈለ ትኩረት” እንደሆነ ተናግረዋል። አንድ የኮሌጅ ፕሮፌሰር ይህ ጽንሰ ሐሳብ “ወላጆች ከሚሰማቸው የሕሊና ወቀሳ የመነጨ ነው። ከልጆቻቸው ጋር ብዙ ጊዜ ላለማሳለፍ የፈለጉ ሰዎች የፈጠሩት ሰበብ ነው” በማለት የሰነዘሩት አስተያየት ልብ ሊባል የሚገባው ነው። ታዲያ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ምን ያህል ጊዜ ማሳለፍ ይኖርባቸዋል?

17. ልጆች ከወላጆቻቸው የሚፈልጉት ምንድን ነው?

17 መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ያህል ጊዜ አይልም። ይሁን እንጂ እስራኤላውያን ወላጆች በቤት ሲቀመጡ፣ በመንገድ ላይ ሲሄዱ፣ ሲተኙና ሲነሱ ከልጆቻቸው ጋር እንዲነጋገሩ ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸው ነበር። (ዘዳግም 6:7) ይህ ሲባል ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር መቀራረብና በየዕለቱ የሚያገኟቸውን አጋጣሚዎች ሁሉ ተጠቅመው እነርሱን ማስተማር ይኖርባቸዋል ማለት እንደሆነ ግልጽ ነው።

18. ኢየሱስ ያገኘውን አጋጣሚ ደቀ መዛሙርቱን ለማሠልጠን የተጠቀመበት እንዴት ነው? ወላጆች ከዚህ ምን ትምህርት ማግኘት ይችላሉ?

18 ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር የሚበላበትንና የሚጓዝበትን፣ አልፎ ተርፎም አረፍ የሚልበትን ጊዜ ተጠቅሞ በሚገባ አሠልጥኗቸዋል። በዚህ መልኩ፣ ያገኘውን አጋጣሚ ሁሉ እነርሱን ለማስተማር ጥሩ አድርጎ ተጠቅሞበታል። (ማርቆስ 6:31, 32፤ ሉቃስ 8:1፤ 22:14) በተመሳሳይ ክርስቲያን ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ጥሩ ግንኙነት ለመመሥረት፣ ግንኙነቱ ቀጣይነት እንዲኖረው ለማድረግ እንዲሁም እነርሱን በይሖዋ መንገድ ለማሠልጠን የሚያገኙትን አጋጣሚ ሁሉ ጥሩ አድርገው ሊጠቀሙበት ይገባል።

ልጆች መማር የሚኖርባቸው ምንድን ነው? እንዴትስ?

19. (ሀ) ከልጆች ጋር ጊዜ ከማሳለፍ በተጨማሪ የሚያስፈልገው ምንድን ነው? (ለ) ወላጆች ልጆቻቸውን በዋነኝነት ማስተማር የሚኖርባቸው ምንድን ነው?

19 ይሁን እንጂ ልጆችን በጥሩ ሁኔታ ለማሳደግ የሚያስፈልገው ነገር የተወሰነ ጊዜ ከእነርሱ ጋር ማሳለፍና ማስተማር ብቻ አይደለም። ልጆች ‘የሚማሩት ምንድን ነው’ የሚለውም ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። ምን መማር እንዳለባቸው መጽሐፍ ቅዱስ የሚገልጸውን ልብ በል። “ዛሬ የምሰጥህን እነዚህን ትእዛዛት . . . ለልጆችህም አስጠናቸው [“በልጆችህ ልብ ውስጥ ቅረጻቸው፣” NW]” ይላል። ልጆች መማር የሚያስፈልጓቸው ‘እነዚህ ትእዛዛት’ ምንድን ናቸው? በቁጥር 5 ላይ “አምላክህን እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ኀይልህ ውደድ” ተብሎ የተገለጸው ትእዛዝ እንደሆነ ግልጽ ነው። (ዘዳግም 6:5-7) ኢየሱስ ይህ ትእዛዝ አምላክ ከሰጣቸው ትእዛዛት ሁሉ እንደሚበልጥ ተናግሯል። (ማርቆስ 12:28-30) ስለዚህ ወላጆች በፍጹም ነፍስ ሊወደድና ሊመለክ የሚገባው እርሱ ብቻ የሆነው ለምን እንደሆነ ለልጆቻቸው በማስረዳት በዋነኝነት ስለ ይሖዋ ማስተማር ይኖርባቸዋል።

20. አምላክ በጥንት ዘመን የነበሩ ወላጆች ልጆቻቸውን ምን እንዲያስተምሩ አዟቸው ነበር?

20 ይሁን እንጂ ወላጆች ለልጆቻቸው ማስተማር የሚጠበቅባቸው ‘እነዚህ ትእዛዛት’ አምላክን በፍጹም ልብ መውደድን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ነገሮችንም ይጨምራሉ። ሙሴ በዘዳግም ምዕራፍ 5 ውስጥ አምላክ በጽላት ላይ ጽፎ የሰጠውን አሥርቱን ትእዛዛት በድጋሚ እንደጠቀሳቸው ሳትገነዘብ አትቀርም። ከእነዚህ ሕግጋት ውስጥ አትዋሽ፣ አትስረቅ፣ አትግደል፣ አታመንዝር የሚሉት ትእዛዛት ይገኙበታል። (ዘዳግም 5:11-22) በመሆኑም በዚያ ዘመን የነበሩት ወላጆች የሥነ ምግባር እሴቶችን ለልጆቻቸው ማስተማሩ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ጠበቅ ተደርጎ ተገልጾላቸዋል። በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያን ወላጆችም ልጆቻቸው ወደፊት አስተማማኝና ደስታ የሰፈነበት ሕይወት እንዲመሩ ለመርዳት የሚፈልጉ ከሆነ ተመሳሳይ ትምህርት መስጠት ይኖርባቸዋል።

21. የአምላክን ቃል በልጆች ልብ ውስጥ ‘መቅረጽ’ ሲባል ምን ማለት ነው?

21 ወላጆች “እነዚህን ትእዛዛት” ለልጆቻቸው እንዴት እንደሚያስተምሩም እንደተነገራቸው ልብ በል። ‘በልጅህ ልብ ውስጥ ቅረጸው’ ተብለው ታዝዘዋል። ‘መቅረጽ’ ተብሎ የተተረጎመው ኢንከልኬት የተባለው የእንግሊዝኛ ቃል “ደግሞ ደጋግሞ በመናገር ወይም በማሳሰብ ማስተማርና ማስገንዘብ፤ ማበረታታት ወይም በአእምሮ ውስጥ እንዲተከል ማድረግ” የሚል ፍቺ አለው። ስለዚህ አምላክ፣ ወላጆች በልጆቻቸው አእምሮ ውስጥ መንፈሳዊ ጉዳዮችን የመትከል ግብ ይዘው በሚገባ የታሰበበት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ፕሮግራም ማዘጋጀት እንደሚኖርባቸው ማሳሰቡ ነበር።

22. እስራኤላውያን ወላጆች ልጆቻቸውን ለማስተማር ምን እንዲያደርጉ ተነግሯቸው ነበር? ይህስ ምን ትርጉም አለው?

22 እንዲህ ያለው የታሰበበት ፕሮግራም የወላጆችን ተነሳሽነት ይጠይቃል። መጽሐፍ ቅዱስ “[እነዚህን ትእዛዛት] በእጅህ ላይ ምልክት አድርገህ እሰራቸው፤ በግንባርህም ላይ ይሁኑ። በቤትህ መቃኖች በግቢህም በሮች ላይ ጻፋቸው” ይላል። (ዘዳግም 6:8, 9) ይህ ሲባል ግን ወላጆች የአምላክን ሕግጋት ቃል በቃል በቤታቸው መቃንና በግቢያቸው በር ላይ ይጽፋሉ ወይም ሕጎቹን ገልብጠው በልጆቻቸው እጅ ላይ ያስራሉ እንዲሁም በዓይኖቻቸው መካከል ያደርጋሉ ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ በዋነኝነት ለማሳሰብ የተፈለገው ወላጆች የአምላክን ትእዛዛት ዘወትር ለልጆቻቸው እንዲያስተምሩ ነው። አዘውትረው ልጆቻቸውን የማስተማሩ ጉዳይ በቋሚነት መደረግ የሚገባው በመሆኑ የአምላክ ትምህርት ሁልጊዜ ከልጆቹ ፊት እንደማይጠፋ ነገር ነበር።

23. የሚቀጥለው ሳምንት ጥናት በየትኞቹ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ይሆናል?

23 ወላጆች ልጆቻቸውን ሊያስተምሯቸው ከሚገቡት በጣም አስፈላጊ ነገሮች መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው? ልጆች ራሳቸውን ከጥቃት መከላከል እንዲችሉ ትምህርትም ሆነ ሥልጠና ማግኘታቸው በተለይ በዛሬው ጊዜ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ወላጆች ልጆቻቸውን ውጤታማ በሆነ መንገድ ማስተማር እንዲችሉ ለመርዳት ምን ጠቃሚ ዝግጅት ተደርጎላቸዋል? በርካታ ወላጆችን የሚያሳስቡ እነዚህና ሌሎች ጥያቄዎች በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ ማብራሪያ ይሰጥባቸዋል።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ወላጆች ልጆቻቸውን እንደ ውድ ነገር መመልከት የሚኖርባቸው ለምንድን ነው?

• ወላጆችም ሆኑ ሌሎች ከኢየሱስ ምን መማር ይችላሉ?

• ወላጆች ለልጆቻቸው ምን ያህል ጊዜ መመደብ ይኖርባቸዋል?

• ልጆች መማር የሚኖርባቸው ምንድን ነው? ትምህርቱ መሰጠት ያለበትስ እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወላጆች ኢየሱስ ከተጠቀመበት የማስተማሪያ ዘዴ ምን ትምህርት ማግኘት ይችላሉ?

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እስራኤላውያን ወላጆች ልጆቻቸውን ማስተማር ያለባቸው መቼና እንዴት ነበር?

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወላጆች የአምላክን ትእዛዛት ዘወትር ለልጆቻቸው ማስተማር አለባቸው