በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወላጆች፣ ውድ ለሆኑት ስጦታዎቻችሁ ጥበቃ አድርጉላቸው

ወላጆች፣ ውድ ለሆኑት ስጦታዎቻችሁ ጥበቃ አድርጉላቸው

ወላጆች፣ ውድ ለሆኑት ስጦታዎቻችሁ ጥበቃ አድርጉላቸው

‘ጥበብ ጥላ ከለላ ናት፤ የባለቤቷን ሕይወት ትጠብቃለች።’—መክብብ 7:12

1. ወላጆች ልጆቻቸውን እንደ ስጦታ መመልከት የሚኖርባቸው ለምንድን ነው?

 ወላጆች በአካላዊ ገጽታና በባሕርይ እነርሱን የሚመስሉ ልጆች ይወልዳሉ። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ያሉትን ልጆች “የእግዚአብሔር ስጦታ” በማለት ይጠራቸዋል። (መዝሙር 127:3) ዋነኛው የሕይወት ምንጭ ይሖዋ ስለሆነ ንብረቱ የሆኑትን ልጆች ለወላጆች በአደራ ሰጥቷቸዋል። (መዝሙር 36:9) ወላጆች፣ እነዚህን የመሰሉ ውድ ስጦታዎች ከአምላክ በማግኘታችሁ ምን ይሰማችኋል?

2. ማኑሄ ልጅ እንደሚወልድ በተነገረው ጊዜ ምን አደረገ?

2 ወላጆች እንዲህ ያለውን ስጦታ በትሕትናና በአድናቆት መቀበል እንደሚኖርባቸው ምንም ጥርጥር የለውም። ከ3,000 ዓመታት በፊት እስራኤላዊው ማኑሄ፣ አንድ መልአክ ልጅ እንደሚወልዱ ለሚስቱ በነገራት ጊዜ እንዲህ ያለ ስሜት አሳይቶ ነበር። ማኑሄ ምሥራቹን ሲሰማ “ጌታ ሆይ፤ የሚወለደውን ልጅ እንዴት አድርገን ማሳደግ እንዳለብን እንዲያስተምረን ያ ወደ እኛ የላክኸው የእግዚአብሔር ሰው እንደ ገና እንዲመጣ ታደርግ ዘንድ እለምንሃለሁ” በማለት ጸልዮአል። (መሳፍንት 13:8) ወላጆች ከማኑሄ ምሳሌ ምን ትምህርት ማግኘት ትችላላችሁ?

በዛሬው ጊዜ መለኮታዊ እርዳታ ያስፈለገበት ምክንያት

3. በተለይ በዛሬው ጊዜ ልጆችን ለማሳደግ የአምላክ እርዳታ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

3 በዛሬው ጊዜ ያሉ ወላጆች ልጆቻቸውን ለማሳደግ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የይሖዋ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ሰይጣን ዲያብሎስና መላእክቱ ከሰማይ ወደ ምድር ስለተጣሉ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ምድርና ባሕር . . . ወዮላችሁ! ምክንያቱም ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን ብቻ እንደ ቀረው ስላወቀ፣ በታላቅ ቊጣ ተሞልቶ ወደ እናንተ ወርዶአል” በማለት ያስጠነቅቃል። (ራእይ 12:7-9, 12) በተጨማሪም ሰይጣን “የሚውጠውን በመፈለግ እንደሚያገሣ አንበሳ” በመዞር ላይ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (1 ጴጥሮስ 5:8) አብዛኛውን ጊዜ አንበሳ ማደን የሚፈልገው ራሳቸውን የመከላከል አቅም የሌላቸውን በተለይ ደግሞ ትንንሽ እንስሳትን ነው። በመሆኑም ክርስቲያን ወላጆች ልጆቻቸውን ለመጠበቅ የሚያስችል መመሪያ ለማግኘት ወደ ይሖዋ ዞር ማለታቸው በጣም አስፈላጊ ነው። ታዲያ ልጆቻችሁን ለመጠበቅ ምን ያህል ጥረት እያደረጋችሁ ነው?

4. (ሀ) ወላጆች በሰፈራቸው ውስጥ አንበሳ እንደተለቀቀ ቢሰሙ ምን እርምጃ ለመውሰድ ይነሳሳሉ? (ለ) ልጆች ራሳቸውን እንዲጠብቁ ምን ማግኘት ያስፈልጋቸዋል?

4 በሰፈራችሁ ውስጥ አንበሳ እንደተለቀቀ ብትሰሙ ከምንም በላይ የሚያሳስባችሁ ልጆቻችሁን ከአደጋ የመጠበቁ ጉዳይ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። ሰይጣን ልክ እንደ አዳኝ አውሬ ነው። የአምላክ ሕዝቦች አቋማቸውን አጉድፈው የአምላክን ሞገስ እንዲያጡ ለማድረግ ይፈልጋል። (ኢዮብ 2:1-7፤ 1 ዮሐንስ 5:19) ለዚህ ጥቃት ይበልጥ የተጋለጡት ደግሞ ልጆች ናቸው። ልጆች በዲያብሎስ ወጥመድ እንዳይያዙ ይሖዋን ማወቅና እርሱን መታዘዝ ይኖርባቸዋል። የመጽሐፍ ቅዱስን እውቀት ማግኘታቸው በጣም አስፈላጊ ነው። ኢየሱስ “እውነተኛ አምላክ የሆንኸውን አንተንና የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 17:3) ከዚህም በላይ ልጆች ጥበብ ማለትም የተማሩትን የመረዳትና ተግባራዊ የማድረግ ችሎታ ያስፈልጋቸዋል። ‘ጥበብ የባለቤቷን ሕይወት ስለምትጠብቅ’ ወላጆች በልጆቻችሁ ልብ ውስጥ እውነትን መትከል ያስፈልጋችኋል። (መክብብ 7:12) ይህን ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው?

5. (ሀ) ጥበብን ማስተማር የሚቻለው እንዴት ነው? (ለ) የምሳሌ መጽሐፍ ጥበብ ምን ጥቅም እንዳላት ይገልጻል?

5 ለልጆቻችሁ የአምላክን ቃል ልታነቡላቸው ትችላላችሁ፤ ደግሞም እንደዚያ ማድረግ ይኖርባችኋል። ይሁን እንጂ ልጆች ይሖዋን እንዲወዱትና እንዲታዘዙት ለማድረግ ከዚህም የበለጠ ነገር ያስፈልጋል፤ ልጆቹ የሚማሩትን መረዳት ይኖርባቸዋል። ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ አንድ ልጅ ግራና ቀኝ ሳይመለከት የመኪና መንገድ እንዳያቋርጥ ይነገረው ይሆናል። ሆኖም አንዳንድ ልጆች እንደታዘዙት አያደርጉም። ለምን? በመኪና መገጨት የሚያስከትለው አደጋ በሚገባ ስለማይገለጽላቸው ወይም የአደጋው ውጤት በደንብ እንዲታያቸው ስለማይደረግ ሊሆን ይችላል። በዚህ መንገድ ትምህርት ቢሰጣቸው ግን ለአደጋ የሚያጋልጥ ‘የሞኝነት’ እርምጃ ከመውሰድ ሊቆጠቡ ይችላሉ። ጥበብን ለሌሎች ለማስተማር ጊዜና ከፍተኛ ትዕግሥት ይጠይቃል። ይሁንና ጥበብ እጅግ ጠቃሚ ናት! መጽሐፍ ቅዱስ “መንገዷ ደስ የሚያሰኝ ነው፤ ጐዳናዋም ሁሉ ሰላም ነው። ለሚያቅፏት የሕይወት ዛፍ ናት፤ የሚይዟትም ይባረካሉ” ይላል።—ምሳሌ 3:13-18፤ 22:15

ጥበብ የሚሰጥ ትምህርት

6. (ሀ) ልጆች ብዙውን ጊዜ ስህተት የሚፈጽሙት ለምንድን ነው? (ለ) ምን ዓይነት ጦርነት በመካሄድ ላይ ነው?

6 ብዙውን ጊዜ ልጆች ስህተት የሚሠሩት ትክክል የሆነውን ስላልተማሩ ሳይሆን ትምህርቱ ልባቸውን ስላልነካ ወይም ውስጣቸው ስላልዘለቀ ሊሆን ይችላል። ዲያብሎስ የልጆችን ልብ ለመቆጣጠር ፍልሚያ እያካሄደ ነው። የሚፈልገው በእርሱ ቁጥጥር ሥር ያለው ዓለም ለሚያሳድረው መጥፎ ተጽዕኖ ሲጋለጡ ማየት ነው። ከዚህም በላይ ከአዳም በወረሱት ኃጢአት የመሥራት ዝንባሌ ተገፋፍተው መጥፎ ነገሮችን እንዲፈጽሙ ለማድረግ ይጥራል። (ዘፍጥረት 8:21፤ መዝሙር 51:5) ወላጆች፣ የልጆቻቸውን ልብ ለመማረክ መጠነ ሰፊ ጥቃት እንደተከፈተ መገንዘብ ይኖርባቸዋል።

7. ለአንድ ልጅ ትክክል ወይም ስህተት ስለሆኑ ነገሮች ብቻ መንገሩ በቂ የማይሆነው ለምንድን ነው?

7 ወላጆች ለልጃቸው አንድ ዓይነት የሥነ ምግባር መመሪያ ለማስተማር ሲሉ ብዙውን ጊዜ ትክክልና መጥፎ ስለሆኑ ነገሮች ይነግሩታል። ለምሳሌ ያህል መዋሸት፣ መስረቅ ወይም ካላገቡት ሰው ጋር የጾታ ግንኙነት መፈጸም ትክክል እንዳልሆነ ለልጁ ይነግሩት ይሆናል። ይሁን እንጂ የተሰጠውን ትእዛዝ የማክበር ብርቱ ፍላጎት እንዲያድርበት ሌላም ነገር ማወቅ ያስፈልገዋል። ትእዛዙን የሰጡት ወላጆቹ ቢሆኑም ሕጉን ያወጣው ይሖዋ እንደሆነ ማወቅ ይኖርበታል። ልጁ የአምላክን ትእዛዛት መጠበቅ የጥበብ መንገድ መሆኑን መማር ይገባዋል።—ምሳሌ 6:16-19፤ ዕብራውያን 13:4

8. ልጆች የጥበብ እርምጃ የሚወስዱት ምን ከተማሩ ነው?

8 አንድ ልጅ ውስብስብ ስለሆነው አጽናፈ ዓለም፣ ስለተለያዩ ሕያዋን ፍጥረታት፣ ስለ ወቅቶች መፈራረቅና እነዚህን ስለመሳሰሉ ነገሮች ማወቁ ለጥበቡ አቻ የሌለው ፈጣሪ መኖሩን እንዲገነዘብ ያደርገዋል። (ሮሜ 1:20፤ ዕብራውያን 3:4) ከዚህ በተጨማሪ አምላክ እንደሚወደው፣ ልጁን ቤዛዊ መሥዋዕት አድርጎ በመስጠት የዘላለም ሕይወት የሚያገኝበትን መንገድ እንደከፈተለትና የአምላክን ትእዛዛት በመጠበቅ እርሱን ማስደሰት እንደሚችል መማር ይኖርበታል። ልጁ እንዲህ ያለውን ትምህርት ማግኘቱ፣ ዲያብሎስ እንቅፋት ሊሆንበት ቢጥርም እንኳ ይሖዋን ለማገልገል እንዲወስን ሊያደርገው ይችላል።—ምሳሌ 22:6፤ 27:11፤ ዮሐንስ 3:16

9. (ሀ) ሕይወት አድን የሆነውን ትምህርት መስጠት ምን ይጠይቃል? (ለ) አባቶች ምን እንዲያደርጉ ታዘዋል? ይህስ ምን ማድረግን ይጨምራል?

9 አንድ ልጅ ራሱን ከክፉ እንዲጠብቅም ሆነ ትክክል የሆነውን የማድረግ ፍላጎት እንዲያድርበት የሚያስችለውን ትምህርት ማስተማር ጊዜ፣ ትኩረትና እቅድ ማውጣት ይጠይቃል። ወላጆችም የአምላክን አመራር ማግኘት ያስፈልጋቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ “አባቶች ሆይ፤ እናንተም ልጆቻችሁን . . . በጌታ ምክርና ተግሣጽ አሳድጓቸው” ይላል። (ኤፌሶን 6:4) ይህ ምን ማለት ነው? እዚህ ጥቅስ ላይ “ተግሣጽ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “አስተሳሰብን መክተት” የሚል ሐሳብ ያስተላልፋል። በመሆኑም አባቶች በልጆቻቸው አእምሮ ውስጥ የይሖዋን አስተሳሰብ መክተት አለባቸው ማለት ነው። ይህም ለልጆች ትልቅ ጥበቃ እንደሚሆንላቸው እሙን ነው! የአምላክ አስተሳሰብ በልጆች አእምሮ ላይ መቀረጹ ከመጥፎ ድርጊት እንዲጠበቁ ያደርጋቸዋል።

ፍላጎታችሁ ከፍቅር የመነጨ መሆን አለበት

10. ልጆቻችሁን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማስተማር ምን ማወቅ ያስፈልጋችኋል?

10 ይሁን እንጂ ልጆቻችሁን በጥሩ ሁኔታ ለማሳደግ ያላችሁን ፍላጎት ከግብ ለማድረስ የምታደርጉት ጥረት፣ ከፍቅር የመነጨ መሆን ይኖርበታል። ለዚህ አንዱ አስፈላጊ ነገር ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት ማድረግ ነው። በልጆቻችሁ ሕይወት ውስጥ ምን እየተከሰተ እንዳለና ምን አመለካከት እንዳላቸው ለመገንዘብ ጥረት አድርጉ። ዘና እንዲሉ በማድረግ በዘዴ የልባቸውን አውጥተው እንዲናገሩ አድርጓቸው። አንዳንድ ጊዜ የሚያስደነግጥ ነገር ይነግሯችሁ ይሆናል። ሆኖም ስሜታችሁ እንዳይለዋወጥ ጥንቃቄ አድርጉ። ከዚህ ይልቅ በአዘኔታ ስሜት አዳምጧቸው።

11. አንድ ወላጅ የአምላክን አስተሳሰብ በልጁ አእምሮ ውስጥ መቅረጽ የሚችለው እንዴት ነው?

11 እርግጥ ነው፣ ለልጆቻችሁ የጾታ ብልግና መፈጸም የሚከለክለውን የአምላክ ሕግ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ደጋግማችሁ አንብባችሁላቸው ይሆናል። (1 ቆሮንቶስ 6:18፤ ኤፌሶን 5:5) እንደዚህ ማድረጋችሁ ልጆቻችሁ ይሖዋን ምን እንደሚያስደስተውና እንደሚያሳዝነው በሚገባ እንዲገነዘቡ አድርጓቸው ይሆናል። ይሁን እንጂ የይሖዋን አስተሳሰብ በልጆች አእምሮ ውስጥ መቅረጽ ከዚህ የበለጠ ነገር ማድረግን ይጠይቃል። ልጆች የይሖዋ ሕግ ያለውን ጠቀሜታ እንዲያገናዝቡ መረዳት ያስፈልጋቸዋል። ሕጎቹ ትክክልና ጠቃሚ ስለመሆናቸው እንዲሁም ሕጎቹን መታዘዝ ተገቢና አስደሳች ስለመሆኑ አሳማኝ ትምህርት ማግኘት ያስፈልጋቸዋል። የአምላክን አስተሳሰብ በልጆቻችሁ አእምሮ ውስጥ ቀርጻችኋል ሊባል የሚችለው፣ ልጆቹ የአምላክን አመለካከት እንዲቀበሉ መጽሐፍ ቅዱስን ተጠቅማችሁ በሚገባ ካስረዳችኋቸው ብቻ ነው።

12. አንድ ወላጅ ልጁ ስለ ጾታ ግንኙነት ተገቢ አመለካከት እንዲኖረው መርዳት የሚችለው እንዴት ነው?

12 ከልጃችሁ ጋር ስለ ጾታ ጉዳይ ስትነጋገሩ “አንድ ሰው፣ ይሖዋ ከጋብቻ በፊት የጾታ ግንኙነት እንዳይደረግ የሰጠውን ሕግ መከተሉ ደስታ የሚያሳጣው ይመስልሃል?” ብላችሁ ልትጠይቁት ትችላላችሁ። ልጁ ሐሳቡን እንዲገልጽ አበረታቱት። ልጅ ለመውለድ ስለሚያስችለው አስደናቂ የአምላክ ዝግጅት ከነገራችሁት በኋላ “አፍቃሪ የሆነው አምላካችን ሕግ የሚያወጣው ለምን ይመስልሃል? እኛን ደስታ ለማሳጣት ነው ወይስ ደስተኛ እንድንሆንና ከክፉ እንድንጠበቅ?” ብላችሁ ልትጠይቁት ትችላላችሁ። (መዝሙር 119:1, 2፤ ኢሳይያስ 48:17) ልጃችሁ ስለዚህ ጉዳይ ምን አመለካከት እንዳለው ለማወቅ ጥረት አድርጉ። ከዚያም የጾታ ብልግና መፈጸም ሐዘንና ችግር እንደሚያስከትል የሚያሳዩ አንዳንድ ምሳሌዎችን ልትነግሩት ትችላላችሁ። (2 ሳሙኤል 13:1-33) ልጁን በጥሩ ሁኔታ በማስረዳት የአምላክን አመለካከት እንዲገነዘብና እንዲቀበል የምታደርጉ ከሆነ የአምላክን አስተሳሰብ በአእምሮው ውስጥ ለመቅረጽ የሚያስችለውን ትልቅ እርምጃ ወስዳችኋል ለማለት ይቻላል። ይሁን እንጂ ሌላም ልታደርጉ የምትችሉት ነገር አለ።

13. አንድ ልጅ ይሖዋን የመታዘዝ ፍላጎት እንዲያድርበት ምን መማር ይኖርበታል?

13 ይሖዋን አለመታዘዝ የሚያስከትለውን መዘዝ ብቻ ሳይሆን አኗኗራችን ይሖዋን እንዴት እንደሚነካው ጭምር ለልጆቻችሁ ማስተማራችሁ በጣም አስፈላጊ ነው። ይሖዋ ፈቃዱን ሳናደርግ ስንቀር ሊያዝንብን እንደሚችል የሚያሳይ ማስረጃ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አሳዩት። (መዝሙር 78:41) ልጃችሁን “ይሖዋን ማሳዘን የሌለብህ ለምንድን ነው?” ብላችሁ ልትጠይቁትና “የአምላክ ጠላት የሆነው ሰይጣን ይሖዋን የምናገለግለው ስለምንወደው ሳይሆን ለግል ጥቅማችን ብለን እንደሆነ ይከራከራል” በማለት ልታስረዱት ትችላላችሁ። ከዚያም ኢዮብ ከአቋሙ ፍንክች ባለማለት የአምላክን ልብ እንዳስደሰተ፣ በዚህም ሰይጣን ላነሳው የሐሰት ክስ መልስ እንዳስገኘ ልትገልጹለት ትችላላችሁ። (ኢዮብ 1:9-11፤ 27:5) ልጃችሁ በሚያንጸባርቀው ባሕርይ ይሖዋን ሊያሳዝን ወይም ሊያስደስት የሚችል መሆኑን ማወቅ ይገባዋል። (ምሳሌ 27:11) ከታላቁ አስተማሪ ተማሩ (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ተጠቅማችሁ ይህንንና ይህን የመሳሰሉ ሌሎች በርካታ ጠቃሚ ትምህርቶችን ለልጆቻችሁ ማስተማር ትችላላችሁ። a

አርኪ ውጤቶች

14, 15. (ሀ) ከታላቁ አስተማሪ ተማሩ ከተባለው መጽሐፍ ውስጥ ልጆችን ለተግባር ያነሳሱት አንዳንዶቹ ትምህርቶች የትኞቹ ናቸው? (ለ) መጽሐፉን መጠቀምህ ምን ጥሩ ውጤቶች አስገኝቶልሃል? (በገጽ 18ና 19 ላይ ያለውን ሣጥን ተመልከት።)

14 ከታላቁ አስተማሪ ተማሩ የተባለውን ይህን መጽሐፍ ከሰባት ዓመት የልጅ ልጃቸው ጋር ያነበቡ በክሮኤሺያ የሚኖሩ አንድ አያት “እማዬ አንድ ነገር እንድሠራ አዝዛኝ ነበር፤ ሆኖም መጀመሪያ ላይ ያለችኝን ማድረግ አልፈለግሁም ነበር። ከዚያም ‘ታዛዥነት ይጠብቅሃል’ የሚለው ምዕራፍ ትዝ ሲለኝ ተመልሼ ሄድኩና እንደምታዘዛት ነገርኳት” በማለት ልጁ እንደነገራቸው ጽፈዋል። በፍሎሪዳ፣ ዩ ኤስ ኤ የሚኖሩ አንድ ባልና ሚስት “መዋሸት የሌለብን ለምንድን ነው?” የሚለውን ምዕራፍ በሚመለከት እንዲህ ብለዋል:- “ይህ ምዕራፍ ልጆች የልባቸውን አውጥተው እንዲናገሩና ሌላ ጊዜ ቢሆን ኖሮ የሚክዱትን ጥፋት እንዲያምኑ የሚያደርጉ ጥያቄዎችን ያነሳል” በማለት ተናግረዋል።

15 ከታላቁ አስተማሪ ተማሩ የተባለው መጽሐፍ ከ230 የሚበልጡ ሥዕሎች ያሉት ሲሆን ለእያንዳንዱ ሥዕል ለማለት ይቻላል መግለጫ ተሰጥቷል። አንዲት እናት እንዲህ በማለት የተሰማትን አድናቆት ገልጻለች:- “ብዙውን ጊዜ ልጄ አንድ ሥዕል ትኩር ብሎ ስለሚመለከት ገጹን ቶሎ አይገልጥም። ሥዕሎቹ ማራኪ ከመሆናቸውም በላይ ትምህርት ይሰጣሉ፤ ወይም ደግሞ ቢያንስ ቢያንስ ልጆች ጥያቄ እንዲጠይቁ ያነሳሷቸዋል። ልጄ አንድ ትንሽ ልጅ ጨለምለም ባለ ክፍል ውስጥ ቁጭ ብሎ ቴሌቪዥን ሲመለከት የሚያሳየውን ሥዕል ሲያይ፣ ትክክል ያልሆነ ነገር እያደረገ መሆኑን እንደተገነዘበ በሚያሳይ የድምፅ ቃና ‘እማዬ ይህ ልጅ ምን እያደረገ ነው?’ ሲል ጠየቀኝ።” ለሥዕሉ የተሰጠው መግለጫ “የምናደርገውን ሁሉ ማን ያያል?” ይላል።

ለዘመናችን የሚሆን በጣም አስፈላጊ ትምህርት

16. በዛሬው ጊዜ ልጆችን ስለ ምን ጉዳይ ማስተማር ያስፈልጋል? ለምንስ?

16 ልጆች የአካል ክፍሎቻቸውን ተገቢ በሆነ መንገድ እንዴት ሊጠቀሙባቸው እንደሚገባና በምን ዓይነት መንገድ ቢጠቀሙባቸው ደግሞ ተገቢ እንደማይሆን ማወቅ ያስፈልጋቸዋል። ሆኖም ስለ እነዚህ ነገሮች መነጋገር ሁልጊዜ ቀላል አይደለም። የአንድ ጋዜጣ ዓምድ አዘጋጅ የሆነች አንዲት ሴት የጾታ ብልቶችን በስም መጥራት እንደ ነውር ይታይ በነበረበት ዘመን እንዳደገች ገልጻ “የሚሰማኝን የሃፍረት ስሜት ማሸነፍ ይኖርብኛል” በማለት ልጆቿን ስታስተምር ያጋጠማትን ጽፋለች። በእርግጥም ወላጆች ሃፍረት ተሰምቷቸው ስለ ጾታ ጉዳዮች የማያነሱ ከሆነ ልጆቹ ከአደጋ ሊጠበቁ አይችሉም። አንድ ልጅ ስለ ጾታ ጉዳይ ምንም የማያውቅ መሆኑ በጾታ ለሚያስነውሩ ሰዎች ምቹ ሁኔታ ይፈጥርላቸዋል። ከታላቁ አስተማሪ ተማሩ የተባለው መጽሐፍ ይህን ርዕሰ ጉዳይ በትክክለኛና ጨዋነት በሚንጸባረቅበት መንገድ ያነሳል። ልጆችን ስለ ጾታ ጉዳይ ማስተማር የማያውቁትን ነገር አውቀው እንዲበላሹ አያደርጋቸውም፤ እንዲያውም እንዲበላሹ የሚያደርጋቸው አለማወቃቸው ነው።

17. ከታላቁ አስተማሪ ተማሩ የተባለው መጽሐፍ ወላጆች ልጆቻቸውን ስለ ጾታ ጉዳይ እንዲያስተምሩ የሚረዳቸው እንዴት ነው?

17 መጽሐፉ በምዕራፍ 10 ላይ ወደ ምድር ወርደው ልጅ ስለወለዱ ክፉ መላእክት በሚገልጽበት ጊዜ “ስለ ጾታ ግንኙነት ምን የምታውቀው ነገር አለ?” የሚል ጥያቄ ያነሳል። ከዚያም ለዚህ ጥያቄ ቀላልና ጨዋነት የተንጸባረቀበት መልስ ይሰጣል። በምዕራፍ 32 ላይ ደግሞ ልጆች ወሲባዊ ጥቃት ሊፈጽሙባቸው ከሚፈልጉ ሰዎች እንዴት ራሳቸውን መጠበቅ እንደሚችሉ ይናገራል። ለዚህ መጽሐፍ አዘጋጆች የደረሱት በርካታ ደብዳቤዎች እንዲህ ያለው ትምህርት በጣም አስፈላጊ መሆኑን ይገልጻሉ። አንዲት እናት “ባለፈው ሳምንት ልጄን ጄቫንን ሐኪም ቤት ይዤው ሄጄ በነበረበት ወቅት ዶክተሯ ስለ አካል ክፍሎቹ ተገቢ የሆነ አጠቃቀም አስተምረነው እንደሆነ ጠየቀችኝ። አዲሱን መጽሐፍ ተጠቅመን እንዳስተማርነው ስታውቅ በጣም ተገረመች” በማለት ጽፋለች።

18. መጽሐፉ ለባንዲራ ሰላምታ መስጠት ጣዖት አምልኮ መሆኑን የሚያስረዳው እንዴት ነው?

18 ሌላው ምዕራፍ ደግሞ የባቢሎንን መንግሥት ለሚወክለው ምስል ለመስገድ ፈቃደኛ ስላልሆኑ ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ ስለተባሉ ዕብራውያን ወጣቶች የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ይዟል። (ዳንኤል 3:1-30) ከታላቁ አስተማሪ ተማሩ የተባለው መጽሐፍ እንደሚጠቁመው አንዳንዶች በጣዖት አምልኮና ለባንዲራ ሰላምታ በመስጠት መካከል ያለውን ግንኙነት በግልጽ አያውቁ ይሆናል። ይሁን እንጂ ኤድዋርድ ጋፍኒ የተባሉ ደራሲ ዩ ኤስ ካቶሊክ ከተባለ መጽሔት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ላይ የተናገሩትን ልብ በል። ሴት ልጃቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ትምህርት ቤት ውላ ስትመለስ “በትምህርት ቤት አንድ አዲስ ጸሎት” እንደተማረች ትነግራቸዋለች፤ እርሳቸውም ጸሎቱን እንድትደግምላቸው ይጠይቋታል። ጋፍኒ ልጅቷ ያደረገችውን አስመልክተው ሲናገሩ “እጅዋን በደረቷ ላይ አደረገችና ኮስተር ብላ ‘ለባንዲራችን ታማኝ ለመሆን ቃል እገባለሁ . . .’ በማለት መዘመር ጀመረች” ብለዋል። አክለውም “ወዲያውኑ አንድ ነገር ብልጭ አለልኝ። ለካስ የይሖዋ ምሥክሮች ትክክል ናቸው። በትምህርት ቤቶቻችን ውስጥ የብሔራዊ ስሜት አምልኮ በልጆች አእምሮ ላይ የሚቀረጸው ገና በለጋ ዕድሜያቸው ነው፤ ከምንም በላይ ለአገራቸው ታማኝ እንዲሆኑ ትምህርት ይሰጣቸዋል” በማለት ተናግረዋል።

ቢደከምለት የሚያስቆጭ አይደለም

19. ልጆችን ማስተማር ምን ውጤት ያስገኛል?

19 በእርግጥም ልጆቻችሁን ማስተማር ምንም ያህል ቢደከምለት የሚያስቆጭ አይደለም። በካንሳስ፣ ዩ ኤስ ኤ የምትኖር አንዲት እናት ከልጅዋ ደብዳቤ ደርሷት ስታነብ እንባዋን መቆጣጠር አልቻለችም። ደብዳቤው እንዲህ የሚል ነበር:- “በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ የተረጋጋና ሚዛናዊ የሆነ ስሜታዊ አቋም እንዲኖረኝ አድርጋችሁ ስላሳደጋችሁኝ የታደልኩ ሰው እንደሆንኩ ይሰማኛል። አንቺም ሆንሽ አባዬ በእርግጥ ልትመሰገኑ ይገባችኋል።” (ምሳሌ 31:28) ከታላቁ አስተማሪ ተማሩ የተባለው መጽሐፍ ሌሎች በርካታ ወላጆች ውድ ለሆኑ ስጦታዎቻቸው አስፈላጊውን ትምህርት በመስጠት ሊደርስባቸው ከሚችለው አደጋ እንዲጠብቋቸው ሊረዳቸው ይችላል።

20. ወላጆች ሁልጊዜ ምን ማስታወስ ይኖርባቸዋል? ይህስ ምን ያስከትልባቸዋል?

20 ለልጆቻችን የቻልነውን ያህል ጊዜና ትኩረት ልንሰጣቸው፣ እንዲሁም ልንደክምላቸው ይገባል። በልጅነት የሚያሳልፉት ዕድሜ በጣም አጭር ነው። በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ በተቻላችሁ መጠን አብራችኋቸው ለመሆንና እነርሱን ለመርዳት ጥረት አድርጉ። እንዲህ በማድረጋችሁ ፈጽሞ አትጸጸቱም። የኋላ ኋላ ይወዷችኋል። ምንጊዜም ቢሆን ልጆቻችሁ የይሖዋ ስጦታዎች መሆናቸውን አስታውሱ። በእርግጥም እንዴት ያሉ ውድ ስጦታዎች ናቸው! (መዝሙር 127:3-5) ስለዚህ እንዴት እንዳሳደጋችኋቸው አምላክ እንደሚጠይቃችሁ በማሰብ ጥሩ እንክብካቤ አድርጉላቸው፤ በእርግጥም በኃላፊነት ትጠየቁበታላችሁ!

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ። “አምላክን ማስደሰት የምንችለው እንዴት ነው?” የሚል ርዕስ ያለውን ምዕራፍ 40ን ተመልከት።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ወላጆች በተለይ በዛሬው ጊዜ ልጆቻቸውን መጠበቅ የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?

• ጥበብ የሚያስገኘው ምን ዓይነት ትምህርት ነው?

• ከልጆች ጋር ልትወያዩባቸው የሚገቡ በጣም አስፈላጊ ጉዳዮች የትኞቹ ናቸው?

ከታላቁ አስተማሪ ተማሩ የተባለው መጽሐፍ ወላጆች ልጆቻቸውን እንዲያስተምሩ የረዳው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 18, 19 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ሁሉንም ሰው የሚጠቅም መጽሐፍ

ከታላቁ አስተማሪ ተማሩ (እንግሊዝኛ) የሚል ርዕስ ያለው መጽሐፍ የተዘጋጀው ወላጆችና ሌሎች ትልልቅ ሰዎች፣ የኢየሱስ ክርስቶስን ትምህርቶች ለልጆች እንዲያነቡላቸውና እንዲያወያዩአቸው ለመርዳት ታስቦ ነው። ይሁን እንጂ መጽሐፉን ያነበቡ ትልልቅ ሰዎችም ላገኙት ትምህርት የተሰማቸውን ልባዊ አድናቆት ገልጸዋል።

በቴክሳስ፣ ዩ ኤስ ኤ የሚኖሩ አንድ ሰው እንዲህ ብለዋል:- “ቀላል በሆነ መንገድ የቀረበው ከታላቁ አስተማሪ ተማሩ የሚል ርዕስ ያለው መጽሐፍ፣ የ76 ዓመት አዛውንት የሆንኩትን እኔን ጨምሮ የሁሉንም ሰው ልብ የሚነካና ለተግባር የሚያንቀሳቅስ ነው። በጣም አመሰግናችኋለሁ፣ ከወጣትነቱ ጀምሮ ይሖዋን ካገለገለ ሰው።”

በለንደን፣ እንግሊዝ የሚገኙ አንዲት አንባቢ “ውብ የሆኑት ሥዕሎች የልጆችንም ሆነ የወላጆችን ቀልብ ይማርካሉ። ጥያቄዎቹ የቀረቡበት መንገድና የጽሑፉ አዘገጃጀት ወደር የለውም፤ ‘ኢየሱስ ጥበቃ ያገኘው እንዴት ነው?’ የሚል ርዕስ ባለው ምዕራፍ 32 ላይ እንደተገለጸው ያሉ አሳሳቢ ጉዳዮች የተብራሩበት መንገድ በጣም ድንቅ ነው” ብለዋል። ሲደመድሙም “ይህ መጽሐፍ ለይሖዋ ምሥክሮች ልጆች ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑ ባያጠራጥርም አስተማሪዎችና ሌሎች ሰዎች መጽሐፉን ቢያገኙ እጅግ በጣም እንደሚደሰቱ ይሰማኛል። በዚህ መጽሐፍ ወደፊትም እጠቀምበታለሁ” ብለዋል።

በማሳቹሴትስ፣ ዩ ኤስ ኤ የሚኖሩ አንዲት ሴት “በጣም ታስቦባቸው የተዘጋጁትን ሥዕሎች በተመለከተ” አስተያየት ሰጥተዋል። “መጽሐፉ ለልጆች ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን ባስተውልም፣ በመጽሐፉ ላይ የተብራሩት ጉዳዮች አዋቂ የሆንነው ጭምር ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና በተመለከተ እንድናስብ ይረዱናል” ብለው ጽፈዋል።

በሜይን፣ ዩ ኤስ ኤ የሚገኙ ሴት “እንዴት ያለ አስደናቂ መጽሐፍ ነው! ይህ መጽሐፍ ለልጆች ብቻ ሳይሆን የአምላክ ልጆች ለሆንነው ለሁላችንም የሚጠቅም ነው። የያዘው ትምህርት ወደ ልቤ ሰርጾ የገባ ከመሆኑም በላይ ስሜቴን ቀስቅሶታል እንዲሁም አጽናንቶኛል፤ በመሆኑም ውስጣዊ ሰላም አግኝቻለሁ። ይሖዋን እንደ አባቴ አድርጌ በጣም እንደቀረብኩት ይሰማኛል። ይሖዋ ለዓመታት ሲደርስብኝ የነበረውን ሥቃይ አስወግዶልኛል፤ ዓላማውንም ግልጽ አድርጎልኛል” በማለት ተናግረዋል። ሐሳባቸውን ሲደመድሙ “ሁሉንም ሰው ‘እባካችሁ አንብቡት’ በማለት እያበረታታሁ ነው” ብለዋል።

በኪዮቶ፣ ጃፓን የሚኖሩ አንዲት ሴት ለልጅ ልጆቻቸው መጽሐፉን በሚያነቡላቸው ጊዜ ልጆቹ “ይህ ልጅ ምን እየሠራ ነው? ይህች ትንሽ ልጅ ተግሣጽ የሚሰጣት ለምንድን ነው? ይህች እናት ምን እየሠራች ነው? ይሄ አንበሳ ምን እያደረገ ነው?” እንደሚሉት ያሉ ጥያቄዎችን ይጠይቋቸው እንደነበር ተናግረዋል። “መጽሐፉ ማወቅ ስለምንፈልጋቸው ጉዳዮች ትምህርት የሚሰጥ በመሆኑ በቤተ መጻሕፍት ከማገኛቸው ከሌሎች መጻሕፍት ይበልጥ እወደዋለሁ” በማለት ሐሳባቸውን ገልጸዋል።

በካልጋሪ፣ ካናዳ የሚኖር አንድ አባት ልክ መጽሐፉን እንዳገኘ ለስድስት ዓመት ሴት ልጁና ለዘጠኝ ዓመት ወንድ ልጁ ማንበብ እንደጀመረ ተናግሯል። “ወዲያውኑ ሁኔታቸው መለወጥ ጀመረ። ልጆቼ በትኩረት ይከታተሉና ከልባቸው ለጥያቄዎቹ መልስ ይሰጡ ነበር። ጥናቱ በቀጥታ እነርሱን እንደሚመለከት ስለሚሰማቸው ሐሳባቸውን በደንብ አድርገው ይገልጻሉ። ልጆቼ በጥናቱ በጣም ስለተደሰቱ በተለይ ሴቷ ልጄ አዲሱን መጽሐፍ ሁልጊዜ ማታ ማታ ማጥናት እንደምትፈልግ ገልጻለች” ብሏል።

ይህ አባት አንድ ቀን ከጥናታቸው በኋላ የሆነውን እንዲህ ብሎ ገልጿል:- “ከወንዱ ልጄ ጋር ስለ ይሖዋና ስለ ዓላማዎቹ ለሰዓታት ተነጋገርን። በመጽሐፉ ላይ የተመሠረቱ በርካታ ጥያቄዎችን ያነሳ ነበር። ደህና እደር ካለኝ በኋላ ‘አባዬ፣ ሌላም ቀን ልክ እንደዛሬው እንነጋገራለን? ብዙ ጥያቄዎች አሉኝ፤ ስለ ይሖዋም ሁሉን ነገር ማወቅ እፈልጋለሁ’ ሲለኝ እንባ በዓይኔ ግጥም አለ።”

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወላጆች፣ ከማኑሄ ምን ትምህርት ማግኘት ትችላላችሁ?

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ልጆች፣ ከሦስቱ ዕብራውያን ምን ትማራላችሁ?

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ከታላቁ አስተማሪ ተማሩ” በተባለው መጽሐፍ ውስጥ ያሉት ሥዕሎችና መግለጫዎቻቸው ውጤታማ የማስተማሪያ መሣሪያዎች ናቸው

ሐናንያ ጴጥሮስን ምን ብሎ እየዋሸው ነው?

የምናደርገውን ሁሉ ማን ያያል?