በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

አንድ ክርስቲያን አንድ የመንግሥት ሠራተኛ ለሚሰጠው አገልግሎት ጉርሻ ወይም ሌላ ስጦታ ቢሰጥ እንደ ጉቦ ይቆጠራል?

በየትኛውም ቦታ የሚኖሩ ክርስቲያኖች፣ በአንድ አገር ተቀባይነት ያለውና ሕጋዊ የሆነ ጉዳይ በሌላ አገር ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለውና ሕገ ወጥ ሊሆን እንደሚችል በማስታወስ በአካባቢው የተለመዱ አንዳንድ ሁኔታዎች ሲያጋጥሟቸው ማስተዋል የታከለበት እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋቸዋል። (ምሳሌ 2:6-9) እርግጥ ነው፣ አንድ ክርስቲያን ‘በይሖዋ ድንኳን ውስጥ ማደር’ የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ከጉቦ መራቅ እንዳለበት ሁልጊዜ ማስታወስ ይገባዋል።—መዝሙር 15:1, 5፤ ምሳሌ 17:23

ጉቦ ምንድን ነው? ዘ ዎርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒዲያ እንደሚገልጸው “የሕዝብ አመኔታ የተጣለባቸው ባለ ሥልጣናት ኃላፊነታቸውን ወይም ሕጉን ችላ ብለው ሰጪውን እንዲጠቅሙ ለማድረግ . . . ስጦታ መስጠት ጉቦ ይባላል።” ስለዚህ አንድ ሰው የሚኖረው የትም ይሁን የት፣ ዳኛ ወይም ፖሊስ ፍርድ እንዲያጣምምለት ወይም ደግሞ ተቆጣጣሪ የሆነ ሰው ስህተት ሲፈጠርና ሕግ ሲጣስ አይቶ እንዳላየ እንዲያልፍ ሲል ገንዘብ ወይም ሌላ ስጦታ መስጠት ጉቦ ነው። በተጨማሪም ያለወረፋ ጣልቃ ለመግባት ወይም ወረፋ የያዙ ሰዎችን ቀድሞ አንድ ጉዳይ ለማስፈጸም ሲባል ስጦታ መስጠት ጉቦ መስጠት ነው። ከዚህም በላይ እንዲህ ያለው ተግባር አንድ ሰው ለሌሎች ፍቅር እንደሌለው ያሳያል።—ማቴዎስ 7:12፤ 22:39

ይሁን እንጂ ሕጋዊ አገልግሎቶችን ለማግኘት ወይም አድልዎ እንዳይፈጸም ለመከላከል ለሕዝብ አገልጋዮች ስጦታ ወይም ጉርሻ መስጠት እንደ ጉቦ ይቆጠራል? ለምሳሌ ያህል በአንዳንድ አገሮች ያሉ ባለ ሥልጣናት ጉርሻ ካልተሰጣቸው በስተቀር ልጆችን ትምህርት ቤት ለመመዝገብ፣ ለሕመምተኞች አልጋ ለመስጠት ወይም የኢሚግሬሽን ፈቃዶችን ለመስጠት አይፈልጉ ይሆናል። ወይም ደግሞ እንደ ንግድ ፈቃድ ያሉ ሰነዶችን ለማደስ ዛሬ ነገ እያሉ ያጓትቱ ይሆናል።

ጉርሻ መስጠትና ከዚህ ጋር የተያያዙ ልማዶች ከቦታ ቦታ ይለያያሉ። እነዚህ ድርጊቶች በጣም በተለመዱባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች ሕግ እስካልተጣሰ ድረስ አንድ ባለ ሥልጣን ግዴታውን እንዲወጣ ሲባል ጉርሻ መስጠት የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓት መጣስ መስሎ አይታያቸው ይሆናል። እንዲያውም በአንዳንድ ቦታዎች ጉርሻ መስጠት ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ሕዝባዊ አገልግሎት የሚሰጡ ሰዎች እንደ መደጎም ይቆጠራል። ይሁን እንጂ ሕጋዊ አገልግሎት ለማግኘት ሲባል ስጦታ መስጠትና ሕገወጥ በሆነ መንገድ ለሚደረግ ውለታ ጉቦ መስጠት የተለያዩ ነገሮች መሆናቸውን ማስታወስ ይገባል።

በሌላ በኩል ደግሞ ጥቅምን ለማስጠበቅ ሲባል ስጦታ መስጠት በተለመደባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮች ሕጋዊ የሆኑ አገልግሎቶችን ለማግኘት ጥያቄ በሚያቀርቡበት ጊዜ ለተቆጣጣሪዎች፣ ለጉምሩክ ባለ ሥልጣናት ወይም ለሌሎች ሰዎች ጉርሻ ለመስጠት ፈቃደኞች አይሆኑም። እንዲያውም በሚኖሩበት ቦታ በዚህ አቋማቸውና በታማኝነታቸው ስለሚታወቁ አንዳንድ ጊዜ ሌሎች ሰዎች በክፍያ ብቻ ሊያገኟቸው የሚችሏቸውን አገልግሎቶች በነፃ ያገኛሉ።—ምሳሌ 10:9፤ ማቴዎስ 5:16

ነገሩን ለማጠቃለል ያህል፣ እያንዳንዱ የይሖዋ አገልጋይ ሕጋዊ መንገድ የተከተለ አገልግሎት ለማግኘት ወይም በደል እንዳይፈጸምበት ለመከላከል ሲል ጉርሻ መስጠት ይኑርበት አይኑርበት ራሱ ሊወስን ይገባል። ከሁሉም በላይ ግን ኅሊናውን የሚያቆሽሽ፣ በይሖዋ ስም ላይ ነቀፋ የሚያመጣና ሌሎችን የሚያደናቅፍ ነገር እንዳያደርግ መጠንቀቅ ይገባዋል።—ማቴዎስ 6:9፤ 1 ቆሮንቶስ 10:31-33፤ 2 ቆሮንቶስ 6:3፤ 1 ጢሞቴዎስ 1:5