በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋን አምላክህ አድርገው

ይሖዋን አምላክህ አድርገው

ይሖዋን አምላክህ አድርገው

በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን አንዳንድ ሰዎች አምላካቸው ተብሎ እስኪጠራ ድረስ ከይሖዋ ጋር ጥብቅ ዝምድና መመሥረት ችለው ነበር። ለምሳሌ ያህል በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ይሖዋ “የአብርሃም አምላክ፣” “የዳዊት አምላክ” እንዲሁም “የኤልያስ አምላክ” እንደሆነ ተገልጿል።—ዘፍጥረት 31:42፤ 2 ነገሥት 2:14፤ 20:5

እነዚህ ሰዎች ከአምላክ ጋር ይህንን ዓይነት ጥብቅ ዝምድና መመሥረት የቻሉት እንዴት ነው? ከፈጣሪ ጋር የግል ዝምድና መመሥረትና ዝምድናውን ጠብቆ ማቆየት እንድንችል ከእነርሱ ምን እንማራለን?

አብርሃም ‘ይሖዋን አመነ’

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በይሖዋ እንዳመነ የተነገረለት የመጀመሪያው ሰው አብርሃም ነው። አብርሃም በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ ያስቻለው ከሁሉ የላቀ ባሕርይ እምነት ነበር። እንዲያውም አብርሃም የይሖዋን ሞገስ አግኝቶ ስለነበር ፈጣሪ ቆየት ብሎ ራሱን ለሙሴ ባስተዋወቀ ጊዜ ‘የአብርሃም አምላክ’ እንዲሁም የልጁ የይስሐቅና የልጅ ልጁ የያዕቆብም አምላክ መሆኑን ተናግሯል።—ዘፍጥረት 15:6፤ ዘፀአት 3:6

አብርሃም እንዲህ ዓይነት እምነት በይሖዋ ላይ ማሳደር የቻለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ደረጃ፣ አብርሃም እምነቱን በጠንካራ መሠረት ላይ ገንብቷል። በዚህ ረገድ የአምላክን ማዳን በዓይኑ የተመለከተው የኖኅ ልጅ ሴም የይሖዋን መንገዶች ለአብርሃም ሳያስተምረው አልቀረም። በጊዜው ሴም ይሖዋ “የጽድቅ ሰባኪ የነበረውንም ኖኅን ከሌሎች ሰባት ሰዎች ጋር አድኖ ለቀድሞው ዓለም ሳይራራ በኃጢአተኞች ላይ የጥፋት ውሃ” ሲያዘንብ የዓይን ምሥክር ነበር። (2 ጴጥሮስ 2:5) ስለዚህ አብርሃም ይሖዋ ቃሉን የሚጠብቅ አምላክ መሆኑን ከሴም መማር ችሎ መሆን ይኖርበታል። ያም ሆነ ይህ አብርሃም ራሱ አምላክ ቃል በገባለት ወቅት የተደሰተ ከመሆኑም በላይ የተሰጠው ተስፋ ፍጻሜ ማግኘቱ እንደማይቀር እርግጠኛ መሆኑን በሚያሳይ መንገድ ኖሯል።

በጽኑ መሠረት ላይ የተገነባ እምነት የነበረው አብርሃም ያመነበትን ነገር በሥራ ላይ ማዋሉ እምነቱን ይበልጥ አጠንክሮለታል። ሐዋርያው ጳውሎስ “አብርሃም ርስት አድርጎ ወደሚቀበለው ስፍራ እንዲሄድ በተጠራ ጊዜ በእምነት ታዘዘ፤ ወዴት እንደሚሄድ ባያውቅም፣ እሺ ብሎ ሄደ” በማለት ጽፏል። (ዕብራውያን 11:8) እንዲህ ዓይነቱ ታዛዥነት አብርሃም በነበረው እምነት ላይ ሲታከልበት ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ እንዳለው “እምነት ከሥራው ጋር አብሮ ይሠራ እንደነበር ታያለህ፤ እምነትም በሥራ ፍጹም ሆነ።”—ያዕቆብ 2:22

ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ የአብርሃም እምነት እንዲፈተን መፍቀዱ እምነቱን ይበልጥ አጠንክሮለታል። ይህንን አስመልክቶ ጳውሎስ “አብርሃም እግዚአብሔር በፈተነው ጊዜ፣ ይስሐቅን መሥዋዕት አድርጎ በእምነት አቀረበ” በማለት ጽፏል። ፈተና እምነትን በማጥራትና በማጠናከር ‘ከወርቅ ይልቅ እጅግ የከበረ’ ያደርገዋል።—ዕብራውያን 11:17፤1 ጴጥሮስ 1:7

አብርሃም በሕይወት ቆይቶ ይሖዋ ቃል የገባለት ነገሮች ፍጻሜያቸውን ሲያገኙ መመልከት ባይችልም እንኳ ሌሎች የእርሱን አርዓያ ሲከተሉ በማየቱ ተደስቷል። ሚስቱን ሣራን ጨምሮ ሌሎች ሦስት የቤተሰቡ አባላት ማለትም ይስሐቅ፣ ያዕቆብና ዮሴፍ ግሩም የእምነት ምሳሌ ተደርገው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተገልጸዋል።—ዕብራውያን 11:11 (የ1954 ትርጉም), 20-22

በዛሬው ጊዜ የአብርሃምን ዓይነት እምነት ማዳበር

ይሖዋን አምላኩ ለማድረግ የሚፈልግ ማንኛውም ሰው እምነት በጣም ያስፈልገዋል። ጳውሎስ “ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም” በማለት ጽፏል። (ዕብራውያን 11:6) ታዲያ በአሁን ጊዜ ያሉ የአምላክ አገልጋዮች የአብርሃምን ዓይነት እምነት ማዳበር የሚችሉት እንዴት ነው?

ልክ እንደ አብርሃም የእኛም እምነት በጠንካራ መሠረት ላይ መገንባት ይኖርበታል። ይህን የምናደርግበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስንና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን ዘወትር በማጥናት ነው። መጽሐፍ ቅዱስን ማንበባችንና ባነበብነው ላይ ማሰላሰላችን ይሖዋ ቃል የገባልን ተስፋዎች እንደሚፈጸሙ እርግጠኞች እንድንሆን ያደርገናል። ይህ ደግሞ ሕይወታችንን በዚህ የተረጋገጠ ተስፋ እንደምናምን በሚያሳይ መንገድ እንድንመራ ይገፋፋናል። በአገልግሎት በቅንዓት መሳተፍንና በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘትን በመሳሰሉ ጉዳዮች ታዛዥነት ማሳየታችን እምነታችንን ይበልጥ ያጠነክረዋል።—ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20፤ ዕብራውያን 10:24, 25

እምነታችን ምናልባትም በተቃውሞ፣ በከባድ ሕመም፣ የምንወደውን ሰው በሞት በማጣት ወይም በሌላ ዓይነት መንገድ እንደሚፈተን የታወቀ ነው። በፈተና ወቅት ለይሖዋ ታማኝ ሆነን መቀጠላችን ከወርቅ ይልቅ እጅግ የከበረ ጠንካራ እምነት ያስገኝልናል። በሕይወት ቆይተን ይሖዋ የገባልን ተስፋዎች በሙሉ ሲፈጸሙ መመልከት ሳንችል ብንቀር እንኳ እምነታችን ወደ እሱ ይበልጥ እንድንቀርብ ይረዳናል። በተጨማሪም ምሳሌነታችን ሌሎች እምነታችንን እንዲኮርጁ ያነሳሳቸዋል። (ዕብራውያን 13:7) የወላጆቹን እምነት ተመልክቶ ምሳሌያቸውን የተከተለው የራልፍ ሁኔታም ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ነው። ራልፍ እንዲህ በማለት ይናገራል:-

“ከወላጆቼ ጋር በኖርኩባቸው ጊዜያት መጽሐፍ ቅዱስን አብረን ማንበብ እንድንችል ወላጆቻችን ማለዳ እንድንነሳ ሁላችንንም ያበረታቱን ነበር። በዚህ ሁኔታ መጽሐፍ ቅዱስን ከዳር እስከ ዳር አንብበን ለመጨረስ ችለናል።” ራልፍ አሁንም በየዕለቱ ጠዋት ጠዋት መጽሐፍ ቅዱስን ያነባል፤ ይህም ቀኑን በጥሩ መንፈስ እንዲጀምር ያስችለዋል። በተጨማሪም በየሳምንቱ ከአባቱ ጋር የማገልገል ልማድ ነበረው። “ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግና የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምራት የተማርኩት በዚያን ጊዜ ነበር” ብሏል። በአሁኑ ወቅት ራልፍ አውሮፓ ውስጥ ባለ አንድ የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ በፈቃደኝነት በማገልገል ላይ ይገኛል። በእርግጥም ይህ ወላጆቹ ላሳዩት እምነት ትልቅ ወሮታ ነው!

ለይሖዋ እንደ ልቡ የሆነለት ሰው

አብርሃም ከኖረበት ዘመን 900 ዓመታት ገደማ በኋላ የተወለደው ዳዊት በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ከተጠቀሱት የይሖዋ አገልጋዮች መካከል ጎልቶ የሚታይ ነው። ይሖዋ ዳዊትን የወደፊት ንጉሥ እንዲሆን መምረጡን አስመልክቶ ነቢዩ ሳሙኤል ሲናገር “እግዚአብሔር እንደ ልቡ የሚሆንለትን ሰው አግኝቶአል” ብሏል። በይሖዋና በዳዊት መካከል የነበረው የወዳጅነት መንፈስ ጥልቅ ስለነበር ትንሽ ቆየት ብሎ ነቢዩ ኢሳይያስ ከንጉሥ ሕዝቅያስ ጋር በሚነጋገርበት ወቅት ይሖዋን “የአባትህ የዳዊት አምላክ” በማለት ጠርቶት ነበር።—1 ሳሙኤል 13:14፤ 2 ነገሥት 20:5፤ ኢሳይያስ 38:5

ዳዊት ከይሖዋ ልብ ጋር ተስማምቶ የኖረ ቢሆንም ለሥጋዊ ምኞቶቹ የተሸነፈባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ። ሦስት ጊዜ ከባድ ስህተቶችን ፈጽሟል:- የቃል ኪዳኑን ታቦት ወደ ኢየሩሳሌም ለመውሰድ ትክክለኛ ባልሆነ ማጓጓዣ እንዲጠቀሙ ፈቅዷል፣ ከቤርሳቤህ ጋር ምንዝር ከመፈጸሙም በላይ ለባሏ ለኦርዮ ጉድጓድ ምሶለታል፤ እንዲሁም ይሖዋ ሳያዝዘው በእስራኤልና በይሁዳ የሕዝብ ቆጠራ አካሂዷል። በእነዚህ ጊዜያት ሁሉ ዳዊት የይሖዋን ሕግ ተላልፏል።—2 ሳሙኤል 6:2-10፤ 11:2-27፤ 24:1-9

ሆኖም ዳዊት ኃጢአት መሥራቱ በሚነገረው ጊዜ በሌሎች ለማመካኘት ከመሞከር ይልቅ መሳሳቱን አምኖ በመቀበል ኃላፊነቱን ይወስድ ነበር። የቃል ኪዳኑ ታቦት በትክክል እንዳልተጓጓዘ አምኗል፤ እንዲሁም “ምን ማድረግ እንዳለብን በታዘዘው መሠረት [ይሖዋን] አልጠየቅነውም” በማለት ተናግሯል። ነቢዩ ናታን ምንዝር መፈጸሙን ባጋለጠ ጊዜ የዳዊት ምላሽ “እግዚአብሔርን በጣም በድያለሁ” የሚል ነበር። እንዲሁም ሕዝቡ እንዲቆጠር ማድረጉ የሞኝነት ድርጊት መሆኑን ሲረዳ “ባደረግሁት ነገር ታላቅ ኀጢአት ሠርቻለሁ” በማለት ጥፋቱን አምኗል። ዳዊት ከኃጢአቱ ንስሐ በመግባት ከይሖዋ ጋር ያለውን ወዳጅነት ጠብቆ ማቆየት ችሏል።—1 ዜና መዋዕል 15:13፤ 2 ሳሙኤል 12:13፤ 24:10

ስህተት በምንሠራበት ጊዜ

ይሖዋን አምላካችን ለማድረግ ስንጥር የዳዊት ምሳሌነት ማበረታቻ ይሆነናል። ለይሖዋ እንደ ልቡ የሆነለት ሰው ከባድ ኃጢአቶችን ከፈጸመ፣ እኛም ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት አንዳንድ ጊዜ ብንሳሳት ወይም ከባድ በደል ብንፈጽም ተስፋ መቁረጥ አይኖርብንም። (መክብብ 7:20) ዳዊት ንስሐ በመግባቱ ምክንያት የፈጸመው ኃጢአት ይቅር እንደተባለለት ማወቃችን ብርታት ይጨምርልናል። ከጥቂት ዓመታት በፊት ዩዊ ላይ የደረሰው ሁኔታም ተመሳሳይ ነው። a

ዩዊ በአንድ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ውስጥ ሽማግሌ በመሆን ያገለግል ነበር። በአንድ ወቅት ግን መጥፎ ለሆኑት ፍላጎቶቹ በመሸነፍ ኃጢአት ሠራ። በመጀመሪያ ላይ ልክ ንጉሥ ዳዊት እንዳደረገው ምናልባት ነገሩን ይሖዋ በቸልታ ያልፈው ይሆናል በማለት በድብቅ ለመያዝ ሞክሮ ነበር። ሆኖም ውሎ አድሮ ኅሊናው እረፍት ስለነሳው አብሮት ለሚያገለግል አንድ ሽማግሌ ኃጢአቱን ተናዘዘ፤ ከዚያም ካጋጠመው መንፈሳዊ አደጋ ዩዊን ለመታደግ አንዳንድ እርምጃዎች ተወሰዱ።

ከዚህ በኋላ ዩዊ ንስሐ በመግባት ከይሖዋና ከጉባኤው ጋር ያለውን ቅርርብ ጠብቆ ለመኖር ችሏል። ከጥቂት ሳምንታት በኋላ እርዳታ ለሰጡት ሽማግሌዎች የተሰማውን ከልብ የመነጨ ጥልቅ አድናቆት ሲገልጽ “በይሖዋ ስም ላይ ያመጣሁትን ነቀፌታ እንዳስወግድ ረድታችሁኛል” በማለት ጽፏል። ዩዊ ከይሖዋ ጋር የነበረውን ግንኙነት ማደስ በመቻሉ ባለበት ጉባኤ ውስጥ በድጋሚ አገልጋይ ሆኖ ለመሾም በቅቷል።

“እንደ እኛ ሰው ነበረ”

ዳዊት ከሞተ ከመቶ ዓመት በኋላ የኖረው ኤልያስ በእስራኤል ተነስተው ከነበሩት ታላላቅ ነቢያት ውስጥ አንዱ ነው። ይህ ነቢይ ምግባረ ብልሹነትና የሥነ ምግባር ዝቅጠት በተስፋፋበት ዓለም ውስጥ ይኖር የነበረ ቢሆንም ለእውነተኛው አምልኮ ጥብቅና በመቆም ለይሖዋ ያለውን ታማኝነት አስመስክሯል። እርሱን የተካው ኤልሳዕ ይሖዋን “የኤልያስ አምላክ” ብሎ መጥራቱ አያስደንቅም።—2 ነገሥት 2:14

ዳሩ ግን ኤልያስ ከሰው የተለየ ኃይል አልነበረውም፤ እንዲያውም ያዕቆብ “ኤልያስ እንደ እኛ ሰው ነበረ” ሲል ጽፏል። (ያዕቆብ 5:17) ለምሳሌ ያህል የበአል አምላኪዎች በአሳፋሪ ሁኔታ እንዲሸነፉ ማድረጉን የሰማችው ንግሥት ኤልዛቤል እንደምትገድለው ዛተች። ይህን ሲሰማ ምን አደረገ? ከመፍራቱ የተነሳ ወደ በረሃ ሸሸ። እዚያም በአንድ የክትክታ ዛፍ ሥር ተቀምጦ:- “በቅቶኛል፤ እኔ ከቀደሙት አባቶቼ አልበልጥምና ነፍሴን ውሰዳት” በማለት ለይሖዋ ጸለየ። ኤልያስ በነቢይነት ከመቀጠል ይልቅ ሞትን መረጠ።—1 ነገሥት 19:4

ያም ሆኖ ይሖዋ የኤልያስን ስሜት ተረድቶለታል። ኤልያስ ብቻውን እንዳልሆነና ለእውነተኛው አምልኮ ታማኝ የሆኑ የእምነት አጋሮች እንዳሉት በመግለጽ አበረታቶታል። ከዚህም በላይ በኤልያስ ላይ እምነት በማሳደር ተጨማሪ ሥራ ሰጥቶታል።—1 ነገሥት 19:5-18

ኤልያስ ያጋጠመው የስሜት መረበሽ የይሖዋን ሞገስ ማጣቱን የሚያመለክት አልነበረም። ከ1,000 ዓመታት በኋላ ኢየሱስ ክርስቶስ በጴጥሮስ፣ በያዕቆብና በዮሐንስ ፊት በተለወጠ ጊዜ ይሖዋ ከኢየሱስ ጋር እንዲታዩ የመረጠው እነማንን ነበር? ሙሴንና ኤልያስን ነበር። (ማቴዎስ 17:1-9) በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው ይሖዋ ኤልያስን ምሳሌ አድርጎ ተመልክቶታል። ኤልያስ ‘እንደ እኛ ያለ ሰው የነበረ’ ቢሆንም እውነተኛውን አምልኮ መልሶ ለማቋቋምና ለስሙ መቀደስ ያደረገውን ከፍተኛ ጥረት አምላክ ትልቅ ግምት ሰጥቶታል።

ከስሜታችን ጋር የምናደርገው ትግል

በአሁኑ ጊዜ ያሉ የይሖዋ አገልጋዮችም ቢሆኑ አንዳንድ ጊዜ የስሜት መረበሽ ሊያጋጥማቸው እንዲሁም የተስፋ መቁረጥ ስሜት ሊሰማቸው ይችላል። ኤልያስ ተመሳሳይ ሁኔታ አጋጥሞት እንደነበር ማወቁ እንዴት ያጽናናል! ይሖዋ ለኤልያስ እንዳደረገው ሁሉ እኛም ከስሜታችን ጋር የምናደርገውን ትግል ይረዳልናል።—መዝሙር 103:14

በአንድ በኩል አምላክንና ሰዎችን እንወዳለን እንዲሁም የመንግሥቱን ምሥራች በማወጅ የይሖዋን ሥራ ለማከናወን እንተጋለን። በሌላ በኩል ደግሞ ሰዎች ለምንሰብከው ምሥራች ግድየለሾች መሆናቸው ያሳዝነን አለዚያም የእውነተኛው አምልኮ ጠላቶች የሚሰነዝሩት ዛቻ ያስጨንቀን ይሆናል። ሆኖም ይሖዋ ኤልያስ በሥራው መቀጠል እንዲችል እንደረዳው ሁሉ በዛሬው ጊዜ ያሉ አገልጋዮቹንም ይደግፋቸዋል። ለምሳሌ ያህል የኸርበርትንና የጌርትሩትን ሁኔታ ተመልከት።

ኸርበርትና ጌርትሩት በቀድሞው ጀርመን ዲሞክራቲክ ሪፑብሊክ ትገኝ በነበረችው ሌፕሲግ ከተማ በ1952 ተጠምቀው የይሖዋ ምሥክሮች ሆኑ። በዚያን ወቅት በአገሪቷ ውስጥ የስብከቱ ሥራ በእገዳ ሥር ስለነበር ለአምላክ አገልጋዮች ሕይወት ቀላል አልነበረም። ከቤት ወደ ቤት ስለሚያካሂዱት ምሥክርነት ኸርበርት ምን ተሰምቶት ይሆን?

“ከቤት ወደ ቤት ስናገለግል ፖሊሶች በድንገት መጥተው ያስሩን ይሆናል በማለት በጣም የምንፈራባቸው ጊዜያት ነበሩ” በማለት ተናግሯል። ሆኖም ኸርበርትና የእምነት አጋሮቹ ፍርሃታቸውን እንዲቋቋሙ የረዳቸው ምን ነበር? “የተጠናከረ የግል ጥናት ነበረን። እንዲሁም በስብከቱ ሥራ መጽናት እንድንችል ይሖዋ ብርታት ሰጥቶናል” ብሏል። ኸርበርት ለሕዝብ በሚሰጠው የምሥክርነት ሥራ በመካፈሉ ብዙ አስደሳች እንዲሁም ብርታት የሚጨምሩ ተሞክሮዎችን ማግኘት ችሏል።

በአንድ ወቅት ኸርበርት ለመጽሐፍ ቅዱስ ፍላጎት ያሳየች በመካከለኛው ዕድሜ ላይ ያለች ሴት አገኘ። ከትንሽ ቀናት በኋላ ተመልሶ ሊጠይቃት ወደ ቤቷ በሄደ ጊዜ አንድ ወጣት ቀረብ ብሎ ውይይታቸውን ያዳምጥ ጀመር። ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ኸርበርት አንድ አስደንጋጭ ነገር ተመለከተ። በቤቱ ማዕዘን አካባቢ ይገኝ ከነበረ ወንበር ላይ የፖሊስ ባርኔጣ ተቀምጧል። ይህ ባርኔጣ የወጣቱ ሲሆን እርሱም ኸርበርትን ለማሰር ወስኖ ነበር።

ወጣቱ በቁጣ “የይሖዋ ምሥክር ነህ አይደል! እስቲ መታወቂያህን አምጣ” አለው። ኸርበርትም መታወቂያውን ሰጠው። በዚህ ወቅት ያልተጠበቀ ሁኔታ ተከሰተ። ሴትየዋ ወደ ፖሊሱ በመዞር “በዚህ የአምላክ ሰው ላይ አንድ ነገር ቢደርስበት ካሁን በኋላ እዚህ ቤት ድርሽ ማለት አትችልም” ስትል አስጠነቀቀችው።

ወጣቱ ለትንሽ ጊዜ ቆም ብሎ ካሰበ በኋላ ለኸርበርት መታወቂያውን በመመለስ በነፃ አሰናበተው። ኸርበርት በኋላ እንደተረዳው ፖሊሱ የሴትየዋ ልጅ ወዳጅ ነበር። ስለዚህ ኸርበርትን በማሰር ከልጅቷ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማበላሸት አለመፈለጉ ግልጽ ነበር።

ይሖዋን አምላካችን እናድርገው

ከዚህ ሁሉ ምን እንማራለን? እንደ አብርሃም ሁሉ እኛም ይሖዋ በገባልን ተስፋዎች ላይ ጽኑ እምነት ሊኖረን ይገባል። ዳዊት እንዳደረገው ሁሉ በምንሳሳትበት ወቅት እውነተኛ ንስሐ በመግባት ወደ ይሖዋ መመለስ ይኖርብናል። እንዲሁም ልክ እንደ ኤልያስ ጭንቀት በሚሰማን ጊዜ ጥንካሬ እንዲሰጠን በይሖዋ ላይ መታመን ያስፈልገናል። ይሖዋ ‘ለሰዎች ሁሉ በተለይም ለሚያምኑት አዳኝ የሆነ ሕያው አምላክ’ ስለሆነ አሁንም ሆነ ለዘላለም እርሱን አምላካችን ማድረግ እንችላለን።—1 ጢሞቴዎስ 4:10

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ስሙ ተቀይሯል።

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አብርሃም መታዘዙ እምነቱን አጠናክሮለታል

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እንደ ዳዊት ሁሉ እኛም ኃጢአት ከሠራን ንስሐ መግባት ይኖርብናል

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ የኤልያስን ስሜት እንደተረዳ ሁሉ የእኛንም ስሜት ይረዳል