በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለትርጉም ሥራ የሚረዳ ጠቃሚ መሣሪያ

ለትርጉም ሥራ የሚረዳ ጠቃሚ መሣሪያ

ለትርጉም ሥራ የሚረዳ ጠቃሚ መሣሪያ

የመጽሐፍ ቅዱስ ባለቤት የሆነው ይሖዋ አምላክ የመንግሥቱ ምሥራች “ለሕዝብ፣ ለነገድ፣ ለቋንቋና ለወገን ሁሉ” እንዲሰበክ ይፈልጋል። (ራእይ 14:6) በጽሑፍ የሰፈረውን ቃሉን ማንም ሰው በቀላሉ እንዲያገኘው ይሻል። ይህንን ዓላማ ከግብ ለማድረስ መጽሐፍ ቅዱስ በዓለም ላይ ካለ ከማንኛውም ሌላ መጽሐፍ በበለጠ በብዙ ቋንቋዎች ተተርጉሟል። በሺህ የሚቆጠሩ ተርጓሚዎች የአምላክን ቃል በተለያዩ ልሳናት ለመተርጎም ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን አፍስሰዋል።

ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ መተርጎሙ ለአንባቢዎች ከሚያስገኘው ጥቅም በተጨማሪ ለተርጓሚዎችም ያበረከተው አስተዋጽኦ አለ። በተደጋጋሚ ጊዜያት መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ ሌሎች ጽሑፎችን ለመተርጎም የሚረዳ መሣሪያ ሆኖ ሲያገለግል ቆይቷል። ብዙ ተርጓሚዎች አንዳንድ ቃላትን በተሻለ መንገድ ለመተርጎም ሲሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ቃላት በተለያዩ ቋንቋዎች ምን ተብለው እንደተተረጎሙ ይመለከታሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ለትርጉም ሥራ የሚረዳ መሆኑ ኮምፒውተር እንዲተረጉም ለማድረግም ጥቅም ላይ ውሏል።

ኮምፒውተር ራሱ በራሱ ጥሩ የትርጉም ሥራ እንዲሠራ ማድረግ አዳጋች ነው። እንዲያውም አንዳንድ ባለሙያዎች የትርጉም ሥራ ኮምፒውተር መሥራት የሚችለው ነገር እንዳልሆነ ይሰማቸዋል። ለምን? ምክንያቱም ቋንቋ ማለት ዝም ብሎ የቃላት ስብስብ ብቻ አይደለም። እያንዳንዱ ቋንቋ የራሱ የሆነ የቃላት ቅንብር፣ ራሱን የቻለ ሕግ፣ ፈሊጣዊ አነጋገሮችና ውስጠ-ወይራ የሆኑ አባባሎች አሉት። እነዚህን ሁሉ ለኮምፒውተር ለማስተማር የተደረጉት ጥረቶች አመርቂ ውጤት አላስገኙም። ኮምፒውተር እንዲተረጉማቸው የተደረጉ ጽሑፎች በአብዛኛው ለመረዳት የሚከብዱ ናቸው።

አሁን ግን የኮምፒውተር ሳይንቲስቶች አዳዲስ ዘዴዎችን እየቀየሱ ነው። በኮምፒውተር ትርጉም ታዋቂ የሆኑት ስፔሽያሊስቱ ፍራንትስ ጆሴፍ ኦኽ “በጣም ተቀራራቢ የሆነውን የእንግሊዝኛ ትርጉም ለማግኘት ስታትስቲካዊ ዘዴዎችን እንጠቀማለን” ብሏል። ከሂንዲ ወደ እንግሊዝኛ ለመተርጎም ፈለግህ እንበል። በቅድሚያ በሁለቱም ቋንቋዎች የሚገኝ ጽሑፍ መምረጥ ይኖርብሃል። ቀጥሎም ኮምፒውተር ውስጥ ታስገባቸዋለህ። ከዚያም ኮምፒውተሩ እነዚህን ጽሑፎች ያወዳድራቸዋል። ለምሳሌ በሂንዲ የተጻፈ አንድ ቃል በተደጋጋሚ ቢያጋጥመውና ተዛማጅ በሆነው የእንግሊዝኛ ዓረፍተ ነገር ውስጥ ደግሞ “ቤት” የሚለውን ቃል ቢያገኝ በሂንዲ ቋንቋ በተደጋጋሚ ያገኘው የዚያ ቃል ትርጉም “ቤት” እንደሆነ አድርጎ ይደመድማል። ከፊትና ከኋላ የሚገኙት ቃላት እንደ “ትልቅ፣” “ትንሽ፣” “አሮጌ” ወይም “አዲስ” የሚሉት ገላጭ ቅጽሎች ሊሆኑ ይችላሉ። በዚህ መንገድ ኮምፒውተሩ አቻ ቃላትን እና የማይነጣጠሉ ቃላትን እያጠራቀመ ይሄዳል። ይህን መሰሉ “ሥልጠና” የተወሰኑ ቀናት ወይም ሳምንታት ሊወስድ ይችላል። ከዚያ በኋላ ኮምፒውተሩ ያገኘውን “ትምህርት” አዲስ ጽሑፍ ለመተርጎም ይጠቀምበታል። በዚህ መንገድ የተተረጎመ ጽሑፍ ሰዋስዋዊ ሕግንና የአጻጻፍ ዘይቤን የተከተለ ባይሆንም እንኳ በአብዛኛው ሐሳቡን የሚያስተላልፍ እንዲሁም አስፈላጊ ዝርዝር ጉዳዮችን የሚያስቀምጥ በመሆኑ ለመረዳት የማያዳግት ነው።

የትርጉም ሥራው ጥራት ባብዛኛው የተመካው በመጀመሪያ ኮምፒውተሩ ውስጥ ባስገባናቸው ቃላት ብዛትና ጥራት ላይ ነው። ለዚህ ደግሞ ጠቃሚ ሆኖ የተገኘው መጽሐፍ ቅዱስ ነው። በብዙ ቋንቋዎች በጥንቃቄ ከመተርጎሙም ሌላ መጽሐፉን በቀላሉ ማግኘት ይቻላል እንዲሁም በዛ ያሉ ቃላት ይዟል። ስለዚህም ተመራማሪዎች ኮምፒውተርን አዲስ ቋንቋ ለማስለመድ በመጽሐፍ ቅዱስ ለመጠቀም መርጠዋል።