በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ስለ ሁሉም ነገር ማወቅ እንችል ይሆን?

ስለ ሁሉም ነገር ማወቅ እንችል ይሆን?

ስለ ሁሉም ነገር ማወቅ እንችል ይሆን?

ሚስዮናውያን የሆኑ አንድ ባልና ሚስት በምዕራብ አፍሪካ በሚገኝ የባሕር ዳርቻ አካባቢ አረፍ ብለው ጨረቃዋን እየተመለከቱ ነበር። በዚህ ወቅት ባልየው “የሰው ልጅ ስለ ጨረቃ የሚያውቀው ምን ያህል ነው? ምን ያህልስ ይቀረው ይሆን?” የሚል ጥያቄ አነሳ።

ባለቤቱም መልሳ እንዲህ አለች:- “ልክ አሁን ጨረቃን እንደምናያት ምድርም ስትዞር ማየት ብንችል ኖሮስ? የሰው ልጆች በአሁኑ ጊዜ ስለ ምድር ምን ያህል ያውቃሉ? ገና የምንማረውስ ምን ያህል ይቀራል? ደግሞም እስቲ አስበው:- በፀሐይ ዙሪያ የምትሽከረከረው ምድር ብቻ አይደለችም፤ እኛ ያለንበት ሥርዓተ ፀሐይ በአጠቃላይ በእንቅስቃሴ ላይ ነው። ይህን ስንል ደግሞ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ምድራችን አሁን ባለችበት ቦታ ላይ እንደገና ተመልሳ የመገኘቷ አጋጣሚ በጣም ጠባብ ይሆናል ማለታችን ነው። ለነገሩ በሕዋ ውስጥ አሁን ያለንበትን ቦታም ማወቅ የቻልነው በሰማይ ላይ ካሉ ከምናውቃቸው ግዑዝ አካላት አንጻር ነው። ስለ አንዳንድ ነገሮች ብዙ ብናውቅም በአጽናፈ ዓለም ውስጥ በትክክል የት ቦታ ላይ እንደምንገኝ ግን አናውቅም።”

እነዚህ ሐሳቦች አንዳንድ መሠረታዊ እውነቶችን ያጎላሉ። የምንማረው በጣም ብዙ ነገር ያለ ይመስላል። እርግጥ ነው ሁላችንም በየዕለቱ አዳዲስ ነገሮችን እንማራለን። ይሁን እንጂ የቱንም ያህል እውቀት ብንቀስም መማር ከምንፈልገው አንጻር ሲታይ ገና ብዙ የሚቀረን ይመስላል።

አዳዲስ መረጃዎችን ለመሰብሰብ ከመቻላችንም በላይ እውቀት የማከማቸት ችሎታችን በከፍተኛ መጠን ማደጉ አይካድም። በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች በመታገዝ የሰው ዘር ይህ ነው የማይባል እውቀት ማከማቸት ችሏል። ኮምፒውተሮች መረጃ የማከማቸት አቅማቸው በጣም በመጨመሩ አንድ ኮምፒውተር ምን ያህል መረጃ መያዝ እንደሚችል ለመግለጽ አዳዲስ ቃላት መፍጠር የግድ ሆኗል። አንድ ሲዲ እጅግ በጣም ብዙ መረጃ ማስቀመጥ ይችላል፤ መያዝ የሚችለው መረጃ መጠን የሚገለጸው በሜጋባይት ሲሆን 680 ሜጋባይት ወይም ከዚያ በላይ መረጃ የማከማቸት አቅም አለው። ዲቪዲ ደግሞ የዚህን ሰባት ጊዜ እጥፍ የሚሆን መረጃ መያዝ የሚችል ሲሆን ከዚህም በላይ መረጃ ማከማቸት የሚችሉ ዲቪዲዎች እየተሠሩ ነው።

በዘመናችን ለመረዳት ከምንችለው በላይ በተራቀቁ መሣሪያዎች መረጃ መለዋወጥ ተችሏል። ሮታሪ ተብለው የሚጠሩት የማተሚያ መሣሪያዎች ለማመን በሚያዳግት ፍጥነት ጋዜጣዎችን፣ መጽሔቶችንና መጽሐፎችን ማተም ይችላሉ። በኢንተርኔት የሚጠቀም ሰው ደግሞ አንዲት የኮምፒውተር ቁልፍ በመጫን ብቻ ሥፍር ቁጥር የሌለው መረጃ ማግኘት ይችላል። በእነዚህና በሌሎች በርካታ መንገዶች አማካኝነት አንድ ሰው ሊማር ከሚችለው በላይ በጣም ብዙ መረጃ ይቀርባል። አንዳንድ ጊዜ ሥፍር ቁጥር የሌለው ይህ የእውቀት ክምችት ከባሕር ጋር ተመሳስሎ ተገልጿል፤ በጣም ብዙ በመሆኑ በምሳሌያዊ አነጋገር በውስጡ ለመዋኘት እንጂ ሙሉውን ለመጠጣት መሞከር እንደሌለብን ይነገራል። እጅግ ከፍተኛ መጠን ያለው የእውቀት ስብስብ መኖሩ ለማወቅ በምንፈልገው ነገር ረገድ መራጮች እንድንሆን የግድ ይለናል።

መራጮች እንድንሆን የሚያደርገን ሌላው ምክንያት ደግሞ ከሚቀርብልን መረጃ አብዛኛው ጠቃሚ አለመሆኑ ነው። እንዲያውም የተወሰነው ነገር የማይፈለግና ልናውቀው የማይገባ ነው። እውቀት ሲባል ጥሩም ይሁን መጥፎ፣ ጠቃሚም ይሁን ጎጂ ማንኛውንም መረጃ እንደሚያካትት አስታውስ። ይባስ ብሎ ደግሞ ብዙዎች እውነት እንደሆኑ አድርገው የሚቀበሏቸው አንዳንድ መረጃዎች ፈጽሞ ስሕተት ናቸው። ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸው ባለ ሥልጣናት የተናገሯቸው ነገሮች እንኳ ቆየት ብለው ሲታዩ ብዙውን ጊዜ ስሕተት ወይም ውሸት ሆነው ይገኛሉ። በጥንቷ ኤፌሶን የከተማዋ ዋና ጸሐፊ የነበረውን ባለ ሥልጣን እንደ ምሳሌ እንመልከት። አዋቂ እንደሆነ ተደርጎ ይታይ የነበረው ይህ ሰው “የታላቋ የአርጤምስ ቤተ መቅደስና ከሰማይ የወረደው ምስሏ ጠባቂ የኤፌሶን ከተማ ሕዝብ መሆኑን የማያውቅ ማን አለ?” በማለት ተናግሮ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 19:35, 36) ብዙዎች የአርጤምስ ምስል ከሰማይ የወረደ መሆኑን ማንም ሰው የሚያውቀውና የማይካድ ሐቅ ነው ቢሉም ነገሩ ፍጹም ውሸት ነበር። እንግዲያው መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖች “በውሸት ዕውቀት ከተባለ” ትምህርት እንዲርቁ ማስጠንቀቁ ተገቢ ነው።—1 ጢሞቴዎስ 6:20

የሕይወት ዘመናችን በጣም አጭር መሆኑ እውቀት በመቅሰም ረገድ መራጮች እንድንሆን የሚገፋፋን ጠንካራ ምክንያት ነው። ወጣትም ሆንክ አረጋዊ ልታጠናው የምትፈልገው በርካታ የእውቀት መስክ እንደሚኖር ጥያቄ የለውም። ሆኖም ይህንን ሁሉ ለማድረግ የምትኖርበት የሕይወት ዘመን እንደማይፈቅድልህ ትገነዘባለህ።

ይህ መሠረታዊ ችግር የሚቀረፍበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? ሕይወትን ለረጅም ጊዜ አልፎ ተርፎም ለዘላለም ለማራዘም የሚያስችል የእውቀት መስክ ይኖር ይሆን? እንዲህ ያለው እውቀት በአሁኑ ጊዜ አለ? ከሆነስ ይህንን እውቀት ለሁሉም ሰው ማዳረስ ይቻል ይሆን? የሚቀርብልን እውቀት ሁሉ እንደምንጠብቀው እውነት የሚሆንበት ጊዜ ይመጣል? በመግቢያው ላይ የተጠቀሱት ባልና ሚስት ለእነዚህ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ አግኝተዋል፤ አንተም መልስ ልታገኝ ትችላለህ። ለዘላለም እውቀት የመቅሰም አጋጣሚ እንዳለህ የሚገልጸውን የሚቀጥለውን ርዕስ እንድታነብብ እንጋብዝሃለን።