ተስፋ አስቆራጭ በሆኑ ሁኔታዎች ሥር ተስፋ ማግኘት—በስደተኞች መጠለያ ካምፕ ውስጥ የተደረገ ስብሰባ
ተስፋ አስቆራጭ በሆኑ ሁኔታዎች ሥር ተስፋ ማግኘት—በስደተኞች መጠለያ ካምፕ ውስጥ የተደረገ ስብሰባ
የካኩማ የስደተኞች መጠለያ ካምፕ በሰሜን ኬንያ በሱዳን ጠረፍ አቅራቢያ ይገኛል። በዚህ ቦታ ከ86,000 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ይኖራሉ። አካባቢው በጣም ደረቅ ሲሆን ቀን ቀን ሙቀቱ 50 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ይደርሳል። በካምፑ ውስጥ በስደተኞች መካከል የሚነሳው ግጭት የተለመደ ነገር ነው። ለአብዛኛው ስደተኛ የካምፑ ሕይወት ተስፋ አስቆራጭ ቢሆንም በተስፋ የሚኖሩ ስደተኞችም አሉ።
ከስደተኞቹ መካከል የመንግሥቱን ምሥራች በቅንዓት የሚያውጁ በርከት ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ይገኛሉ። እነዚህ ምሥክሮች ከካምፑ በስተ ደቡብ 120 ኪሎ ሜትር ርቆ ሎድዋር በሚባል ቦታ በሚገኘው አነስተኛ ጉባኤ ሥር ናቸው። ከዚህ ቀጥሎ ቅርብ የሚባለው ጉባኤ ለመድረስ በመኪና ለስምንት ሰዓታት መጓዝ ያስፈልጋል።
ስደተኞቹ ከካምፑ ወጥተው በነፃነት መንቀሳቀስ ስለማይችሉ ከመካከላቸው ብዙዎቹ የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጓቸው የልዩ፣ የወረዳና የአውራጃ ስብሰባዎች ላይ መገኘት አይችሉም። በዚህ ምክንያት በካምፑ ውስጥ ልዩ ስብሰባ መደረግ እንዲችል አንዳንድ ዝግጅቶች ተደረጉ።
ወደ ሰሜን መጓዝ
ለዚህ ልዩ ስብሰባ እገዛ ለማድረግ ከካምፑ በስተ ደቡብ 480 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው በኤልዶሬት ከተማ የሚኖሩ 15 የይሖዋ ምሥክሮች አድካሚውን መንገድ ተጉዘው በስተ ሰሜን ወደሚገኘው ወደዚህ በረሃማ አካባቢ ለመሄድ ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቀረቡ። ከእነሱ በተጨማሪ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ሚኒባሱን ከነሹፌሩ በማቅረብ አብሯቸው ተጓዘ። ወንድሞቻቸውን ለማበረታታትና ለማጠናከር በጣም ጓጉተው ነበር።
ከተራራማው የምዕራባዊ ኬንያ አካባቢ በማለዳ ተነስተው ጉዟቸውን ሲጀምሩ አየሩ ቀዝቃዛ ነበር። ወደ በረሃማውና ሞቃታማው አካባቢ ከመድረሳቸው በፊት አባጣ ጎርባጣ በሆነው መንገድ እርሻዎችን እንዲሁም ጫካውን እያቋረጡ አቀበቱን ተያያዙት። የፍየልና የግመል መንጋዎች ጠፍ በሆነው መሬት ላይ ተሰማርተዋል። በአካባቢው ያሉ ጎሣዎች የባሕል ልብሳቸውን ለብሰው ከዘራ፣ ደጋንና ቀስት ይዘው ይጓዛሉ። ከ11 ሰዓታት ጉዞ በኋላ ምሥክሮቹ ሞቃታማና አቧራማ ወደሆነችውና 20,000 ሰዎች ወደሚኖሩባት ሎድዋር ደረሱ። ቤታቸው የተቀበሏቸው ወንድሞች በደንብ ካስተናገዷቸው በኋላ ተጓዦቹ በቀጣዩቹ ቀናት ለሚጠብቃቸው ሥራ ዝግጁ እንዲሆኑ ወደ መኝታቸው ሄዱ።
በሚቀጥለው ቀን 15ቱ የይሖዋ ምሥክሮች በአካባቢው የሚገኙ ማራኪ ቦታዎችን ለማየት ወጣ አሉ። በኬንያ በትልቅነቱ የአንደኝነትን ስፍራ የያዘው የቱርካና ሐይቅ ጎብኚዎች ቅድሚያ ሰጥተው ሊያዩት የሚገባ ቦታ ነው። ብዙ ኪሎ ሜትሮች በሚሸፍን የበረሃ ቁጥቋጦ የተከበበው
ይህ ሐይቅ በዓለም ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አዞዎች መኖሪያ ነው። ጨዋማ የሆነው የቱርካና ሐይቅ በአካባቢው ለሚኖሩት ጥቂት ሰዎች መተዳደሪያ ሆኗቸዋል። ጎብኚዎቹ ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤትና የአገልግሎት ስብሰባ አቅራቢያው በሚገኘው ጉባኤ በመካፈል ምሽቱን በጥሩ ሁኔታ አሳለፉ። ጉባኤው የገንዘብ አቅማቸው ውስን ለሆኑ አገሮች በ2003 የይሖዋ ምሥክሮች ባዘጋጁት የግንባታ ፕሮግራም አማካኝነት የተሠራ በጣም የሚያምር የመንግሥት አዳራሽ አለው።የልዩ ስብሰባው ቀን
ልዩ ስብሰባው ሊደረግ የታሰበው እሁድ ቀን ሲሆን የሎድዋር ጉባኤና ሊጎበኟቸው የመጡት ወንድሞች ከጠዋቱ በ2:00 ካምፑ ውስጥ ለመግባት ፈቃድ ስላገኙ ምሥክሮቹ ጉዟቸውን በጠዋት ለመጀመር ጓጉተው ነበር። ጠመዝማዛው መንገድ ጠፍ በሆነው ምድር አቋርጦ ወደ ሱዳን ጠረፍ ወሰዳቸው። በመንገዱ ላይ የሾሉ ተራራዎች ይታዩ ነበር። ወደ ካምፑ እየቀረቡ ሲሄዱ የካኩማ መንደር ከሩቅ ትታይ ጀመር። ዝናብ ጥሎ ስለነበር ወደ ካምፑ የሚወስደው ጥርጊያ መንገድ በብዙ ቦታዎች ላይ በጎርፍ ተጥለቅልቋል። አብዛኞቹ ቤቶች በጭቃ ጡቦች የተሰሩ ሲሆኑ በቆርቆሮ ወይም ውኃ በማያስገቡ ነገሮች ጣሪያ ይደረግላቸዋል። ኢትዮጵያውያን፣ ሶማሌዎች፣ ሱዳኖችና ሌሎችም በቡድን በቡድን ሆነው በየራሳቸው አካባቢ ይኖራሉ። ስደተኞቹ እንግዶቹን ሞቅ ባለ ስሜት ተቀበሏቸው።
ስብሰባው የተካሄደው በአንድ የማሠልጠኛ ማዕከል ውስጥ ነበር። በማሠልጠኛው ማዕከል ግድግዳዎች ላይ የተሳሉት ሥዕሎች የስደተኞቹን የሥቃይ ሕይወት የሚያሳዩ ቢሆንም በዚያን ቀን አዳራሹ ውስጥ የነበሩት ሰዎች
ግን ልባቸው በተስፋ ተሞልቶ ነበር። ሁሉም ንግግሮች የቀረቡት በእንግሊዝኛና በስዋሂሊ ቋንቋ ሲሆን ሁለቱንም ቋንቋ በደንብ አድርገው የሚያውቁ አንዳንድ ተናጋሪዎች ንግግራቸውን በሁለቱም ቋንቋዎች አቅርበዋል። ከሱዳን የመጣ ስደተኛ ወንድም “ምሳሌያዊውን ልባችንን መመርመር” የሚለውን የመክፈቻ ንግግር አቀረበ። ጎብኚዎቹ ሽማግሌዎች ደግሞ ሌሎቹን ንግግሮች አቀረቡ።በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ትልቅ ቦታ ከሚሰጣቸው ክንውኖች አንዱ ጥምቀት ነው። ከጥምቀት ንግግሩ በኋላ እጩ ተጠማቂው ከመቀመጫው ሲነሳ የሁሉም ዓይኖች በእርሱ ላይ አረፉ። ዚልበር የተባለው ይህ ተጠማቂ በ1994 በተፈጸመው የዘር ጭፍጨፋ ምክንያት ከአባቱ ጋር ሆኖ ከትውልድ አገሩ ሸሸ። በመጀመሪያ በብሩንዲ ጥበቃ የሚያገኙ መስሏቸው ነበር፤ ብዙም ሳይቆይ ግን በአደጋ ላይ እንዳሉ ተገነዘቡ። ስለዚህ ዚልበር አንዳንድ ጊዜ በጫካ ውስጥ እየተደበቀ ወደ ዛየር፣ ከዚያም ወደ ታንዛኒያ በመጨረሻም ወደ ኬንያ ተሰደደ። ተናጋሪው በጉባኤው ውስጥ እንደ አንድ ወንድማችን እንደምንመለከተው ሲነግረው ብዙዎች ዓይናቸው እንባ አቀረረ። ተናጋሪው በ95ቱ ተሰብሳቢዎች ፊት ሁለቱን ጥያቄዎች በጠየቀው ጊዜ ዚልበር በሙሉ ልብና ጥርት ብሎ በሚሰማ ድምጽ በስዋሂሊ “ንዳዮ!” ወይም “አዎ!” በማለት መለሰ። እጩ ተጠማቂውና አንዳንድ ወንድሞች ትንሽ ጉድጓድ ቆፍረው ከዚህ በፊት መኖሪያውን ለመሸፈን ይገለገልበት የነበረውን ላስቲክ በማንጠፍ ትንሽ የመጠመቂያ ገንዳ ሠሩ። ዚልበር ለመጠመቅ በጣም ከመጓጓቱ የተነሳ የዚያን ዕለት በጠዋት ተነስቶ በባልዲ ውኃ እያመላለሰ ገንዳውን ብቻውን ሞላው!
በከሰዓት በኋላው ፕሮግራም ላይ ከነበሩት ንግግሮች መካከል በካምፑ ውስጥ የሚኖሩት የይሖዋ ምሥክሮች የሚያጋጥሟቸውን ለየት ያሉ ሁኔታዎች የሚያሳዩ ተሞክሮዎች የቀረቡበት ክፍል ጎላ ብሎ የሚጠቀስ ነው። አንድ ወንድም በዛፍ ሥር ጋደም ብሎ ላገኘው ሰው እንዴት ብሎ እንደመሠከረለት ተናገረ።
ወንድም “ምንም ሳንፈራ ዛፍ ሥር መቀመጥ የምንችለው ሁልጊዜ ይመስልሃል?” በማለት ጠየቀው።
ሰውየው “አዎ” ብሎ ከመለሰ በኋላ አክሎ “በማታ ግን ያስፈራል” አለው።
ወንድም ሚክያስ 4:3, 4ን አነበበለት። ጥቅሱ “እያንዳንዱ ሰው በገዛ ወይኑ ሥር፣ ከገዛ በለሱም ሥር ይቀመጣል፤ የሚያስፈራቸው አይኖርም” ይላል። ከዚያም “አየህ በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ሁልጊዜ ያለፍርሃት መኖር ይቻላል” ብሎ አብራራለት። ሰውየው መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዳ ጽሑፍ ወሰደ።
ወደ ካኩማ የመጣች አንዲት እህት በቅርቡ ሦስት የቅርብ ዘመዶቿን በሞት አጥታ ነበር። በካምፑ ውስጥ ስላሉ ወንድሞች ስትናገር እንዲህ ትላለች፦ “ይህ ካምፕ በጣም አስቸጋሪ ቦታ ቢሆንም ወንድሞች ጠንካራ እምነት አላቸው። የሚኖሩበት ቦታ ደስ የማያሰኝ ቢሆንም ይሖዋን በደስታ ያገለግሉታል። ከአምላክ ጋር ሰላማዊ የሆነ ዝምድና አላቸው። ሰላሜን ጠብቄ እንድኖርና ይሖዋን እንዳገለግል አበረታተውኛል። የምማረርበት ምንም ምክንያት የለኝም!”
ቀኑ እንዴት እንደሄደ ሳያውቁት የልዩ ስብሰባው ፕሮግራም ወደ ማብቂያው ደረሰ። የመደምደሚያውን ንግግር ያቀረበው ወንድም ስምንት የተለያዩ አገሮችን ወክለው የመጡ ልዑካን እንዳሉ ተናገረ። አንድ ስደተኛ ወንድም ይህ የልዩ ስብሰባ ቀን በዚህ በተከፋፈለ ዓለም ውስጥ በይሖዋ ምሥክሮች መካከል አንድነትና ፍቅር እንዳለ የሚያረጋግጥ መሆኑን ተናገረ። በይሖዋ ምሥክሮች መካከል እውነተኛ የክርስቲያን ወንድማማችነት ይታያል።—ዮሐንስ 13:35
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የጠፉት የሱዳን ልጆች
በ1983 በሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ጀምሮ አምስት ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ከቤታቸው ተፈናቅለዋል። ከእነዚህ መካከል 26,000 የሚሆኑ ከቤተሰቦቻቸው የተለያዩ ልጆች ይገኙበታል። በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች በኢትዮጵያ ወደሚገኙ የስደተኞች መጠለያ ካምፖች የሸሹ ሲሆን እዚያም ለሦስት ዓመታት ያህል ቆይተዋል። በኋላ ግን ከካምፖቹ ውስጥ ለመውጣት ስለተገደዱ በሱዳን በኩል አቋርጠው ለአንድ ዓመት ያህል በእግራቸው በመጓዝ ወደ ሰሜን ኬንያ አቀኑ። በዚህ ከባድ ጉዞ ላይ በበሽታ ከመጠቃታቸውም በላይ ወታደሮች፣ ሽፍቶች እንዲሁም የዱር አራዊት ጥቃት ያደርሱባቸው ስለነበር በሕይወት የተረፉት ግማሽ የሚሆኑት ልጆች ብቻ ነበሩ። ከጊዜ በኋላ እነዚህ ልጆች የካኩማ ካምፕ ዋነኛ አባላት ሆኑ። የእርዳታ ድርጅቶችም የጠፉት የሱዳን ልጆች የሚል ስም ሰጧቸው።
በአሁኑ ጊዜ የካኩማ የስደተኞች መጠለያ ካምፕ ከሱዳን፣ ከሶማሊያ፣ ከኢትዮጵያና ከሌሎች አገሮች የመጡ ስደተኞች ይገኙበታል። ስደተኞቹ ልክ ካምፑ እንደደረሱ ለቤት መሥሪያ የሚሆን አንዳንድ መሠረታዊ ቁሳቁሶችና ለጣሪያ የሚሆን ሽፋን ይሰጣቸዋል። በወር ሁለት ጊዜ ለእያንዳንዱ ስደተኛ 6 ኪሎ ግራም ያህል ዱቄት፣ 1 ኪሎ ግራም ባቄላ እንዲሁም ጥቂት ዘይትና ጨው ይሰጠዋል። ብዙዎቹ ስደተኞች ከተሰጣቸው ውስጥ የተወሰነውን በመሸጥ ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን ይገዙበታል።
ከጠፉት የሱዳን ልጆች አንዳንዶቹ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለመገናኘት ችለዋል፤ አሊያም በሌላ አገር እንዲሰፍሩ ተደርገዋል። ሆኖም ስደተኞችን በሌላ አካባቢ የሚያሰፍረው ቢሮ፦ “ገና በሺህ የሚቆጠሩ ስደተኞች በአቧራ በተሸፈነውና በዝንብ በተወረረው የካኩማ የስደተኞች መጠለያ ካምፕ ምግብና ትምህርት ለማግኘት ይዋትታሉ” ብሏል።
[ምንጭ]
Courtesy Refugees International
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ካርታ]
ኬንያ
የካኩማ ካምፕ
የቱርካና ሐይቅ
ሎድዋር
ኤልዶሬት
ናይሮቢ
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በካምፑ ውስጥ መኖር አስቸጋሪ ነው
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በካኩማ ካምፕ ውኃ ሲከፋፈል
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በኬንያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ወንድሞቻቸውን ለማበርታት ወደ ሰሜን ያደረጉት አስቸጋሪው ጉዞ
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአገሩ ነዋሪ የሆነ ልዩ አቅኚ የሚሰጠውን ንግግር አንድ ሚስዮናዊ ሲያስተረጉም
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የመጠመቂያው ገንዳ
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
ውኃ ሲከፋፈልና የካኩማ የስደተኞች መጠለያ ካምፕ፦ Courtesy Refugees International