እምነትህ ለሥራ ያነሳሳሃል?
እምነትህ ለሥራ ያነሳሳሃል?
መቶ አለቃው ሽባ የሆነው አገልጋዩን ኢየሱስ ሊፈውሰው እንደሚችል እርግጠኛ ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ሰው ብቃት እንደሌለው ተሰምቶት አሊያም አረማዊ ስለሆነ ሊሆን ይችላል ኢየሱስን ወደ ቤቱ እንዲገባ አልጋበዘውም። ከዚህ ይልቅ አንዳንድ የአይሁድ ሽማግሌዎችን ልኮ ኢየሱስን “ጌታ ሆይ፤ ወደ ቤቴ እንድትገባ የሚገባኝ አይደለሁም፤ ነገር ግን ከዚሁ ሆነህ አንዲት ቃል ብቻ ተናገር፤ አገልጋዬም ይፈወሳል” አለው። ይህ መቶ አለቃ ኢየሱስ ወደ እርሱ መምጣት ሳያስፈልገው እንኳ መፈወስ እንደሚችል እምነት እንዳለው ኢየሱስ በመገንዘቡ ይከተሉት ለነበሩት ሰዎች እንዲህ አላቸው:- “እውነት እላችኋለሁ፣ ከእስራኤል መካከል እንኳ እንዲህ ያለ እምነት ያለው አንድ ሰው አላገኘሁም።”—ማቴዎስ 8:5-10፤ ሉቃስ 7:1-10
ይህ አጋጣሚ አስፈላጊ በሆነ በአንድ የእምነት ገጽታ ላይ ትኩረት እንድናደርግ ይረዳናል። እውነተኛ እምነት በተግባር መደገፍ አለበት። የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊው ያዕቆብ “ሥራ የሌለው እምነት በራሱ የሞተ ነው” ሲል ገልጿል። (ያዕቆብ 2:17) እምነት በሥራ ሳይደገፍ ሲቀር ምን እንደሚከሰት የሚያሳይ አንድ እውነተኛ ምሳሌ መመርመራችን ይህን ሐቅ ይበልጥ ግልጽ ያደርግልናል።
በ1513 ከክርስቶስ ልደት በፊት፣ የእስራኤል ብሔር በሕጉ ቃል ኪዳን አማካኝነት ከይሖዋ አምላክ ጋር ዝምድና መሠረተ። ሙሴ የዚያ ቃል ኪዳን ዘፀአት 19:3-6) አዎን፣ የእስራኤላውያን ቅድስና የተመካው በመታዘዛቸው ላይ ነበር።
መካከለኛ እንደመሆኑ የአምላክን ቃል ለእስራኤላውያን እንዲህ በማለት አስተላልፏል:- “በፍጹም ብትታዘዙኝና ቃል ኪዳኔን ብትጠብቁ . . . የተቀደሰ ሕዝብ ትሆናላችሁ።” (ከብዙ ዘመናት በኋላ አይሁዳውያን ሕጉ የሚያዘውን ነገር ተግባራዊ ከማድረግ ይልቅ ሕጉን ለማጥናቱ ጉዳይ ይበልጥ ትኩረት ይሰጡ ጀመር። አልፍሬድ ኢደርሻይም ዘ ላይፍ ኤንድ ታይምስ ኦቭ ጂሰስ ዘ መሳያ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ “‘የዓለም ታላላቅ ሰዎች የሆኑት’ ማለትም [ረቢዎች] ከሥራ ይልቅ ጥናት የላቀ ቦታ ሊሰጠው ይገባል ወደሚል መደምደሚያ ላይ ደርሰው ነበር” ሲሉ ጽፈዋል።
እውነት ነው፣ የጥንት እስራኤላውያን አምላክ ያወጣቸውን ሕግጋት በትጋት እንዲያጠኑ ታዘው ነበር። አምላክ ራሱ “ዛሬ የምሰጥህን እነዚህን ትእዛዛት በልብህ ያዝ። ለልጆችህም አስጠናቸው፤ በቤትህ ስትቀመጥ፣ በመንገድም ስትሄድ፣ ስትተኛና ስትነሣም ስለ እነርሱ ተናገር” ብሏቸዋል። (ዘዳግም 6:6, 7) ይሁንና ይሖዋ ከሕጉ ጋር ተስማምቶ ከመኖር ወይም ሕጉ የሚያዘውን ነገር ከማድረግ ይልቅ ሕጉን ማጥናት ይበልጣል ማለቱ ነበር? እስቲ ይህንን ጥያቄ እንመርምር።
መቋጫ የሌለው ጥናት
አይሁዳውያን አምላክ ራሱ ሕጉን በማጥናት በየቀኑ ሦስት ሰዓት ያጠፋል የሚል ወግ ስለነበራቸው እስራኤላውያን ሕጉን ለማጥናቱ ጉዳይ የላቀ ትኩረት መስጠታቸው ምክንያታዊ ሊመስላቸው ይችላል። በዚህም የተነሳ አንዳንድ አይሁዳውያን ‘አምላክ እንኳ በየቀኑ ሕጉን የሚያጠና ከሆነ ምድራዊ ፍጡራኖቹማ ሙሉ በሙሉ በዚያ መጠመድ አይኖርባቸውም?’ የሚሉበትን ምክንያት መረዳት አያዳግትም።
በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ ረቢዎቹ ሕጉን በመሰነጣጠቅና ማብራሪያ በመስጠት ሥራ ተጠምደው የነበረ ሲሆን ይህም አስተሳሰባቸውን ሙሉ በሙሉ አዛብቶታል። ስለዚህ ኢየሱስ ‘የኦሪት ሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን እንደሚናገሩት አያደርጉም’ ካለ በኋላ “ለመሸከም የማይቻል ከባድ ሸክም ማቴዎስ 23:2-4) እነዚህ ሃይማኖታዊ መሪዎች በተራው ሕዝብ ላይ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ሕጎችና ደንቦች የጫኑባቸው ሲሆን እነርሱ ግን በግብዝነት እነዚያኑ ሕጎች ላለመጠበቅ ማምለጫ ቀዳዳ አበጅተዋል። ከዚህም በላይ እነዚህ ከልክ በላይ በጥናት ላይ ያተኮሩት ግለሰቦች ‘በሕጉ ውስጥ ዋነኛ የሆኑትን ማለትም ፍትሕን፣ ምሕረትንና ታማኝነትን ንቀዋል።’—ማቴዎስ 23:16-24
አስረው በሰዎች ትከሻ ላይ ይጭናሉ፤ ራሳቸው ግን በጣታቸው እንኳ አይነኩትም” ብሏል። (ጸሐፍትና ፈሪሳውያን የራሳቸውን ጽድቅ ለማቆም ሲፈልጉ እናከብረዋለን የሚሉትን ሕግ ማፍረሳቸው እርስ በርሱ የሚጋጭ ነገር ነበር! በሕጉ ቃላትና በሌሎች ጥቃቅን ነገሮች ላይ ለዘመናት ያደረጉት ክርክር ወደ አምላክ እንዲቀርቡ አላደረጋቸውም። የዚህ ውጤት ሐዋርያው ጳውሎስ ‘ከንቱ ልፍለፋ፣’ ‘ተቃውሞ’ እና የውሸት “ዕውቀት” ብሎ የገለጻቸው ነገሮች ከሚያስከትሉት ጉዳት ጋር ተመሳሳይ ሲሆን ይህም ከእምነት መንገድ መውጣት ነው። (1 ጢሞቴዎስ 6:20, 21) ሌላው ከባድ ችግር ደግሞ ማለቂያ የሌለው ምርምራቸው የሚያሳድርባቸው ተጽዕኖ ነው። ይኸውም ለትክክለኛ ተግባር የሚያንቀሳቅስ እምነት እንዲያዳብሩ አላደረጋቸውም።
በእውቀት የተሞላ አእምሮ፤ እምነት የለሽ ልብ
የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ያላቸው አስተሳሰብ ከአምላክ አስተሳሰብ ጋር እንዴት የተራራቀ ነው! እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ከመግባታቸው ከጥቂት ጊዜ በፊት ሙሴ እንዲህ ብሎ ነግሯቸው ነበር:- “የዚህን ሕግ ቃሎች ሁሉ በጥንቃቄ ይጠብቁ ዘንድ ልጆቻችሁን እንድታዟቸው፣ እኔ ዛሬ በግልጥ የምነግራችሁን ቃሎች ሁሉ በልባችሁ አኑሩ።” (ዘዳግም 32:46) ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው የአምላክ ሕዝቦች የሚጠበቅባቸው ነገር ሕጉን በትጋት ማጥናት ብቻ ሳይሆን በሥራ ማዋልም ነበር።
ይሁን እንጂ የእስራኤል ብሔር ለይሖዋ ታማኝ አለመሆኑን በተደጋጋሚ አሳይቷል። እስራኤላውያን መልካም ሥራዎችን መሥራት ሲገባቸው እነርሱ ግን ‘እርሱን አልታመኑበትም፤ አልታዘዙትምም።’ (ዘዳግም 9:23፤ መሳፍንት 2:15, 16፤ 2 ዜና መዋዕል 24:18, 19፤ ኤርምያስ 25:4-7) በመጨረሻም አይሁዳውያን የኢየሱስን መሲህነት ለመቀበል እምቢተኞች በሆኑ ጊዜ ከሁሉ የከፋውን የእምነት የለሽነት ተግባር ፈጸሙ። (ዮሐንስ 19:14-16) ከዚህም የተነሳ ይሖዋ አምላክ እስራኤላውያንን በመተው ትኩረቱን ወደ አሕዛብ አዞረ።—የሐዋርያት ሥራ 13:46
እኛም በእውቀት በተሞላ አእምሮ ሆኖም እምነት የለሽ በሆነ ልብ አምላክን ማምለክ እንደምንችል በማሰብ እነርሱ በተያዙበት ወጥመድ ላለመያዝ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልገናል። በሌላ አባባል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን የአእምሮ እውቀት ከማካበት የበለጠ ነገር ይጠይቃል። ትክክለኛ እውቀት በሕይወታችን ላይ በጎ ተጽዕኖ እንዲያሳድር ልባችንን መንካት ይገባዋል። አትክልት ስለ መንከባከብ ብናጠናና ነገር ግን እውቀቱን ባንሠራበት የሚያስገኝልን ጥቅም ይኖራል? እርግጥ ነው፣ ስለ አትክልት አያያዝ የተወሰነ እውቀት እናገኝ ይሆናል፤ ሆኖም የምንሰበስበው ምርት አይኖርም! በተመሳሳይም አምላክ የሚፈልግባቸውን ብቃቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አማካኝነት የሚማሩ ሰዎች የእውነት ዘር ልባቸውን እንዲነካውና ዘሩም ፍሬ አፍርቶ ለሥራ እንዲያንቀሳቅሳቸው ሊፈቅዱለት ይገባል።—ማቴዎስ 13:3-9, 19-23
“ቃሉ የሚናገረውን አድርጉ”
ሐዋርያው ጳውሎስ “እምነት የሚገኘው መልእክቱን ከመስማት ነው” ሲል ተናግሯል። (ሮሜ 10:17) የአምላክን ቃል መስማታችን ከዚያም በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እምነት ማሳደራችን የዘላለም ሕይወት ተስፋ እንዲኖረን ያስችለናል። አዎን፣ ‘በአምላክና በክርስቶስ አምናለሁ’ ብሎ ከመናገር የበለጠ ነገር ያስፈልጋል።
ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ለሥራ የሚያንቀሳቅስ እምነት እንዲኖራቸው እንዲህ ሲል አሳስቧቸዋል:- “ብዙ ፍሬ በማፍራት ደቀ መዛሙርቴ መሆናችሁን ብትገልጡ፣ በዚህ አባቴ ይከብራል።” (ዮሐንስ 15:8) ከጊዜ በኋላ ደግሞ፣ የኢየሱስ ግማሽ ወንድም የሆነው ያዕቆብ ‘ቃሉ የሚናገረውን አድርጉ እንጂ ሰሚዎች ብቻ አትሁኑ’ ብሏል። (ያዕቆብ 1:22) ታዲያ ምን ማድረግ እንዳለብን እንዴት ማወቅ እንችላለን? አምላክን ለማስደሰት ከፈለግን ምን ማድረግ እንዳለብን ኢየሱስ በቃልም ይሁን በተግባር አሳይቶናል።
ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት የአምላክን መንግሥት ለመስበክና የአባቱን ስም ለማስከበር በትጋት ሠርቷል። (ዮሐንስ 17:4-8) በምን መንገድ? ብዙ ሰዎች ኢየሱስ የታመሙትንና ሽባዎችን መፈወሱ ትዝ ይላቸው ይሆናል። ሆኖም የማቴዎስ ወንጌል ዋናውን መንገድ እንዲህ በማለት ይገልጻል:- “ኢየሱስ በምኲራቦቻቸው እያስተማረ፣ የእግዚአብሔርን መንግሥት የምሥራች እየሰበከ . . . በከተሞቹና በመንደሮቹ ዞረ።” በግልጽ እንደሚታየው፣ የኢየሱስ አገልግሎት ለጥቂት ጓደኞቹና በቅርብ ለሚያውቃቸው ሰዎች ወይም ለጎረቤቶቹ ብቻ ምሥራቹን በአጋጣሚ በመንገር የተወሰነ አልነበረም። ይልቁንም ራሱን ሳይቆጥብ፣ ያገኘውን አጋጣሚ ሁሉ ተጠቅሞ ሰዎችን ለማነጋገር “በመላው ገሊላ” ተዘዋውሯል።—ማቴዎስ 4:23, 24፤ 9:35
ኢየሱስ ተከታዮቹም ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ተሳትፎ እንዲኖራቸው አዟቸዋል። በእርግጥም ሊኮርጁት የሚገባ ፍጹም ምሳሌ ትቶላቸዋል። (1 ጴጥሮስ 2:21) ኢየሱስ ለታማኝ ደቀ መዛሙርቱ “ስለዚህ ሂዱና ሕዝቦችን ሁሉ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ አስተምሯቸው” ብሏቸዋል።—ማቴዎስ 28:19, 20
በእርግጥም በስብከቱ ሥራ መካፈል በጣም ያታግላል። ኢየሱስ ራሱ እንዲህ ብሏል:- “እንደ በጎች በተኲላዎች መካከል እልካችኋለሁ።” (ሉቃስ 10:3) ተቃውሞ በሚያጋጥመን ጊዜ ተፈጥሮአዊ ዝንባሌያችን አላስፈላጊ የሆነ መከራ ወይም ጭንቀት እንዳይደርስብን በመፍራት ወደ ኋላ ማፈግፈግ ነው። ኢየሱስ በተያዘበት ሌሊት የታየው ነገር ይኸው ነው። ሐዋርያቱ በፍርሃት በመሸነፋቸው ትተውት ሸሹ። በዚያው ምሽት ትንሽ ቆየት ብሎ ጴጥሮስ ኢየሱስን አላውቀውም ብሎ ሦስት ጊዜ ካደ።—ማቴዎስ 26:56, 69-75
በተጨማሪም ሐዋርያው ጳውሎስ እንኳ ምሥራቹን ለመስበክ ትግል እንደነበረበት መናገሩን ማወቅህ ያስገርምህ ይሆናል። በተሰሎንቄ ለነበረው ጉባኤ “ብርቱ ተቃውሞ ቢደርስብንም እንኳ የእግዚአብሔርን ወንጌል ለእናንተ እንደምናበሥር በአምላካችን ድፍረት አገኘን” ሲል ጽፏል።—1 ተሰሎንቄ 2:1, 2
ጳውሎስም ሆነ አብረውት የነበሩት ሌሎች ሐዋርያት ፍርሃትን አስወግደው ስለአምላክ መንግሥት ለሌሎች እንደሰበኩ ሁሉ አንተም እንዲሁ ማድረግ ትችላለህ። ፍርሃትን እንዴት ማስወገድ ይቻላል? በጣም አስፈላጊ የሆነው እርምጃ በይሖዋ ላይ መታመን ነው። በይሖዋ ላይ ሙሉ በሙሉ ከታመንን፣ ይህ እምነት ለሥራ ስለሚያንቀሳቅሰን ፈቃዱን መፈጸም እንችላለን።—የሐዋርያት ሥራ 4:17-20፤ 5:18, 27-29
የድካማችሁን ዋጋ ታገኛላችሁ
ይሖዋ እርሱን ለማገልገል የምናደርገውን ጥረት በትኩረት ይከታተላል። ለምሳሌ ስንታመምም ሆነ ስንደክም ያውቃል። ጭንቀታችንንም ይረዳልናል። ገንዘብ ነክ የሆኑ ችግሮች ሲያስጨንቁን ወይም ጤንነታችን አሊያም ስሜታችን በመጎዳቱ ተስፋ ስንቆርጥ ይሖዋ ያለንበትን ሁኔታ ይረዳልናል።—2 ዜና መዋዕል 16:9፤ 1 ጴጥሮስ 3:12
ይሖዋ አለፍጽምናና የተለያዩ ችግሮች እያሉብንም እንኳ እምነታችን ለሥራ ሲያንቀሳቅሰን ሲመለከት በጣም ይደሰታል! እንዲያውም ተስፋ በመስጠት ታማኝ ለሆኑ አገልጋዮቹ ያለውን አሳቢነትና ስሜት በተግባር ያሳያል። ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ አነሳሽነት እንዲህ ሲል ጽፏል:- “እግዚአብሔር ዐመፀኛ አይደለም፤ እርሱ ሥራችሁን እንዲሁም በፊትም ሆነ አሁን ቅዱሳንን በመርዳት ስለ ስሙ ያሳያችሁትን ፍቅር አይረሳም።”—ዕብራውያን 6:10
መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋን “የማይሳሳት ታማኝ አምላክ” እንደሆነ እንዲሁም “ከልብ ለሚሹትም ዋጋ እንደሚሰጥ” አድርጎ በሚገልጸው ዘገባ ላይ እምነት ልንጥል ይገባናል። (ዘዳግም 32:4፤ ዕብራውያን 11:6) ለምሳሌ ያህል በዩናይትድ ስቴትስ፣ ካሊፎርኒያ የምትኖር አንዲት ሴት እንዲህ ስትል ታስታውሳለች:- “አባቴ ቤተሰብ ከመመሥረቱ በፊት ለአሥር ዓመት ያህል በሙሉ ጊዜ አገልግሎት አሳልፏል። በአገልግሎቱ ይሖዋ እንዴት እንደረዳው ታሪኩን በሚነግረኝ ጊዜ በጣም ደስ ይለኝ ነበር። አገልግሎት ለመውጣት ሲል በእጁ የነበረውን ጥቂት ገንዘብ የመኪና ነዳጅ ለመግዛት ያዋለባቸው ብዙ ጊዜያት ነበሩ። ከአገልግሎት ወደ ቤት ሲመለስ አብዛኛውን ጊዜ ያልጠበቀው ስጦታ በራፍ ላይ ይጠብቀው ነበር።”
ከቁሳዊ እርዳታ በተጨማሪ “የርኅራኄ አባት፣ የመጽናናትም ሁሉ አምላክ” ስሜታዊና መንፈሳዊ እርዳታ ይሰጠናል። (2 ቆሮንቶስ 1:3) ለዓመታት በተለያዩ መከራዎች የጸናች አንዲት እህት “በይሖዋ ላይ መታመን የእፎይታ ስሜት እንዲሰማህ ያደርጋል” ብላለች። “በይሖዋ ላይ እንድትታመን አጋጣሚውን ከመስጠቱም በተጨማሪ እንዴት እንደሚረዳህ ለማየትም ትችላለህ” በማለት አክላ ተናግራለች። “ጸሎት ወደሚሰማው” አምላክ በትሕትና ስትቀርብ በግል ላሉብህ ችግሮች ትኩረት እንደሚሰጥ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ።—መዝሙር 65:2
በመንፈሳዊው የመከር ሥራ የሚካፈሉ ሠራተኞች የሚያገኙት በረከትና ሽልማት ብዙ ነው። (ማቴዎስ 9:37, 38) ብዙዎች በአገልግሎት መካፈላቸው ለጤንነታቸው እንደጠቀማቸው ሁሉ ላንተም ሊጠቅምህ ይችላል። ከሁሉ በላይ ግን ለሌሎች መመሥከር ከአምላክ ጋር የመሠረትነውን ጥሩ ዝምድና ለማጠናከር ይረዳናል።—ያዕቆብ 2:23
መልካም ማድረጋችሁን ቀጥሉ
አንድ የአምላክ አገልጋይ ባለበት የጤና እክል ወይም በዕድሜ መግፋት ምክንያት በአገልግሎቱ መሥራት የሚፈልገውን ያህል እንዳልሠራ ቢሰማውና በዚህም ይሖዋ ያዝንብኛል ብሎ ቢያስብ ተገቢ አይደለም። በተመሳሳይም ጥሩ ጤንነት የሌላቸው፣ የቤተሰብ ኃላፊነት ያለባቸው ወይም በሌሎች አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሥር ያሉ ሁሉ እንዲህ ዓይነት መደምደሚያ ላይ ቢደርሱ ትክክል አይደሉም።
ሐዋርያው ጳውሎስ አካላዊ ጉዳት ወይም አንድ ዓይነት እንቅፋት ሥራውን ከባድ ባደረገበት ወቅት ችግሩ ‘እንዲወገድለት ጌታን ሦስት ጊዜ መለመኑን’ አስታውስ። ይሖዋም ጳውሎስን ፈውሶ በአገልግሎቱ ይበልጥ መሥራት እንዲችል ከማድረግ ይልቅ እንዲህ አለው:- “ጸጋዬ ይበቃሃል፤ ኀይሌ ፍጹም የሚሆነው በድካም ጊዜ ነውና።” (2 ቆሮንቶስ 12:7-10) ስለዚህም ያሉብህን ማናቸውንም አስቸጋሪ ሁኔታዎች ተቋቁመህ የእርሱን ፈቃድ ለመፈጸም የምታደርገውን ጥረት በሰማይ የሚኖረው አባትህ እንደሚያደንቅ እርግጠኛ ሁን።—ዕብራውያን 13:15, 16
አፍቃሪው ፈጣሪያችን ከአቅማችን በላይ እንድንሰጠው አይፈልግም። ከእኛ የሚጠብቀው ነገር ለሥራ የሚያነሳሳ እምነት እንዲኖረን ብቻ ነው።
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሕጉን ማጥናት ብቻውን በቂ ነው?
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እምነታችን በሥራ የተደገፈ መሆን ይኖርበታል