በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

ሐዋርያው ጳውሎስ በሳንሄድሪን ፊት “ፈሪሳዊ ነኝ” ብሎ መናገሩ ክርስቲያናዊ አቋሙን እንዳላላ አያስቆጥረውም?

በሐዋርያት ሥራ 23:6 ላይ የሚገኘውን የጳውሎስን ንግግር ለመረዳት በጥቅሱ ዙሪያ ያለውን ሐሳብ መመልከት ይኖርብናል።

በኢየሩሳሌም ያሉ አይሁዶች ሕዝቡን አነሳስተው ጳውሎስን ከደበደቡት በኋላ ለሕዝቡ ንግግር የማድረግ አጋጣሚ አግኝቶ ነበር። በዚህ ጊዜ “የአባቶቻችንን ሕግ [ኢየሩሳሌም ውስጥ] በገማልያል እግር ሥር ተቀምጬ በሚገባ ተምሬአለሁ” አላቸው። የተሰበሰበው ሕዝብ ለተወሰነ ጊዜ ያህል ሐዋርያው ያቀረበውን የመከላከያ መልስ ቢያዳምጥም እያደር ግን በቁጣ መገንፈል ጀመረ። በዚህ ጊዜ ጳውሎስን ይዞት የነበረው የጦር አዛዥ ወደ ጦር ሰፈሩ አስገባው። ከዚያም ሊገርፉት ሲሉ ጳውሎስ “አንድን የሮም ዜጋ ያለ ፍርድ ለመግረፍ ሕግ ይፈቅድላችኋልን?” አላቸው።—የሐዋርያት ሥራ 21:27 እስከ 22:29

በማግሥቱ አዛዡ ጳውሎስን በአይሁድ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ማለትም በሳንሄድሪን ፊት አቀረበው። ጳውሎስ ሸንጎውን በትኩረት ሲመለከት ከሳንሄድሪን አባላት ከፊሎቹ ሰዱቃውያን ከፊሎቹ ደግሞ ፈሪሳውያን መሆናቸውን ተገነዘበ። ከዚያም “ወንድሞቼ ሆይ፤ እኔ ከፈሪሳዊ የተወለድሁ ፈሪሳዊ ነኝ፣ ለፍርድ የቀረብሁትም የሙታንን ትንሣኤ ተስፋ በማድረጌ ነው” ብሎ ተናገረ። “ሰዱቃውያን የሙታን ትንሣኤ የለም፤ መላእክትም መናፍስትም የሉም የሚሉ ሲሆኑ፣ ፈሪሳውያን ግን በእነዚህ ሁሉ መኖር የሚያምኑ ነበሩ።” በዚህም ምክንያት በፈሪሳውያንና በሰዱቃውያን መካከል ከፍተኛ ጠብ ተነሣ። ከፈሪሳውያን ወገን የሆኑ አንዳንዶች “በዚህ ሰው ላይ ምንም ጥፋት አላገኘንበትም” በማለት አጥብቀው ተከራከሩ።—የሐዋርያት ሥራ 23:6-10

ጳውሎስ ቀናተኛ ክርስቲያን መሆኑ የታወቀ ስለነበር የሳንሄድሪንን አባላት ፈሪሳዊ ነኝ ብሎ አሳምኗቸው ሊሆን አይችልም። በቦታው የነበሩት ፈሪሳውያን በሁሉም ትምህርቶቻቸው የማያምንን ሰው እንደ ፈሪሳዊ አድርገው አይቀበሉትም ነበር። ስለዚህ ጳውሎስ ፈሪሳዊ እንደሆነ ሲናገር በፈሪሳውያን ትምህርቶች ሙሉ በሙሉ እንደሚያምን መናገሩ አልነበረም፤ በቦታው የነበሩት ፈሪሳውያንም አባባሉን በዚህ መንገድ ተረድተውት መሆን አለበት።

ጳውሎስ ለፍርድ የቀረበው በሙታን ትንሣኤ ተስፋ በማድረጉ እንደሆነ ሲናገር በዚህ ረገድ እንደ ፈሪሳውያን መሆኑን ማመልከቱ እንደነበረ ግልጽ ነው። በዚህ ርዕስ ዙሪያ በሚነሳ ውዝግብ ላይ ጳውሎስ በትንሣኤ ከማያምኑት ከሰዱቃውያን ይልቅ ከፈሪሳውያን ወገን ሊመደብ ይችላል።

ትንሣኤን፣ መላእክትን እንዲሁም በሕጉ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ጉዳዮችን በተመለከተ ፈሪሳውያን ያላቸው እምነት ጳውሎስ ከሚያምንበት የክርስትና ትምህርት ጋር የሚጋጭ አልነበረም። (ፊልጵስዩስ 3:5) ስለዚህ ጳውሎስ በዚህ ረገድ ከፈሪሳውያን ጋር እንደሚመሳሰል ሊናገር ይችላል፤ በቦታው የነበሩት የሳንሄድሪን አባላትም የጳውሎስን አነጋገር የተረዱት ከዚህ አንጻር ብቻ ነበር። ጳውሎስ ፈሪሳዊ እንደሆነ በመናገር ቀደም ሲል የነበረውን ሕይወት የጠቀሰው የአይሁድ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በእርሱ ላይ የነበረውን ጭፍን ጥላቻ ለማርገብ ነበር።

ይሁን እንጂ ጳውሎስ አቋሙን አለማላላቱን የሚያሳየን ዋናው ማስረጃ ከዚያም በኋላ ቢሆን የይሖዋ ድጋፍ ያልተለየው መሆኑ ነው። ጳውሎስ ጥያቄ ያስነሳውን ሐሳብ በተናገረበት ዕለት ምሽት ላይ ኢየሱስ “አይዞህ! በኢየሩሳሌም እንደ መሰከርህልኝ፣ በሮምም ደግሞ ልትመሰክርልኝ ይገባሃል” ብሎታል። ጳውሎስ የአምላክ ድጋፍ ያልተለየው በመሆኑ ክርስቲያናዊ አቋሙን አላላላም ብለን መደምደም እንችላለን።—የሐዋርያት ሥራ 23:11