በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ልዩ በሆነ መንገድ የተገኘ ድል

ልዩ በሆነ መንገድ የተገኘ ድል

ልዩ በሆነ መንገድ የተገኘ ድል

በእምነትህ ምክንያት ምናልባት በሥራ ቦታ፣ በትምህርት ቤት፣ በቤተሰብ ውስጥ ወይም መንግሥት በጣለው እገዳ ሳቢያ ተቃውሞ ያጋጥምሃል? በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ከሆንክ ተስፋ አትቁረጥ። ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች ተመሳሳይ ፈተና ቢደርስባቸውም በድል ተወጥተውታል። እስቲ የኤርና ሉዶልፍን ሁኔታ ተመልከት።

ኤርና የተወለደችው በ1908 በሉቤክ፣ ጀርመን ሲሆን ከቤተሰቧ ውስጥ ይሖዋን የምታመልከው እርሷ ብቻ ነበረች። ሂትለር ሥልጣን በያዘበት በ1933 የይሖዋ ምሥክሮች በርካታ ችግር ይደርስባቸው ጀመር። ኤርና “ሃይል ሂትለር” በማለት ሰላምታ ለመስጠት ፈቃደኛ ስላልነበረች የሥራ ባልደረቦቿ ተቃወሟት፤ በዚህም ምክንያት ናዚዎች አሰሯት። ስምንት ዓመታት በተለያዩ እስር ቤቶችና ሃምቡርግ-ፉልስቡተል፣ ሞሪንገን፣ ሊሽተንበርግ እና ራቨንስብሩክ በሚገኙ ማጎሪያ ካምፖች አሳልፋለች። ኤርና፣ ራቨንስብሩክ በነበረችበት ወቅት ድል እንድትነሳ ያስቻላት አንድ ሁኔታ ተከሰተ።

ልዩ የሆነች የቤት ሠራተኛ

ፕሮፌሰር ፍሬድሪኽ እና አሊሰ ሆልትስ የተባሉ በበርሊን የሚኖሩ ባልና ሚስት ነበሩ። እነዚህ ባልና ሚስት የናዚ ፓርቲ አባላት አልነበሩም፤ እንዲሁም ይህ ፓርቲ የሚያራምደውን ፖለቲካዊ ጽንሰ ሐሳብ አይደግፉም ነበር። ሆኖም በማጎሪያ ካምፕ ውስጥ የሚገኙ የተወሰኑ እስረኞች ተቆጣጣሪ የሆነ ከፍተኛ የናዚ ባለ ሥልጣን ዘመድ ነበራቸው። ይህ ባለ ሥልጣን ፕሮፌሰሩና ባለቤቱ የቤት ሠራተኛ እያፈላለጉ መሆናቸውን ሲረዳ ከሴት እስረኞች መካከል አንዷን እንዲመርጡ ፈቀደላቸው። በመሆኑም አሊሰ በመጋቢት ወር 1943 የቤት ሠራተኛ ለመምረጥ ወደ ራቨንስብሩክ አመራች። ማንን ትመርጥ ይሆን? ኤርና ሉዶልፍን መረጠች። ኤርና ከፕሮፌሰር ፍሬድሪክ ሆልትስ ቤተሰብ ጋር መኖር ጀመረች፤ እነርሱም ጥሩ አድርገው ይይዟት ነበር። ጦርነቱ ካበቃ በኋላም ከቤተሰቡ ጋር ዛለ ወንዝ አቅራቢያ ወደምትገኘው ሃለ የተባለች የምሥራቅ ጀርመን ከተማ አብራ ሄደች። በዚያም ከሶሻሊስት ባለ ሥልጣናት ተቃውሞ ይደርስባት ጀመር። በ1957 ቤተሰቡ ወደ ምዕራብ ጀርመን ተባረረ፤ በዚህ ጊዜም ኤርና አብራቸው ተጓዘች። በመጨረሻም ይሖዋን በነፃነት ማምለክ ቻለች።

ታዲያ ኤርና ልዩ በሆነ መንገድ ድል ያገኘችው እንዴት ነው? በመልካም ምግባሯ እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት በዘዴ በመስበኳ አሊሰ ሆልትስ እና አምስት ልጆቿ ተጠምቀው የይሖዋ ምሥክሮች ሆነዋል። ይህ ብቻ አይደለም፤ ከአሊሰ የልጅ ልጆች መካከል አሥራ አንዱ የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ ሁለቱ ዜልተርስ፣ ጀርመን በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ እያገለገሉ ናቸው። ዙዛነ የምትባለው አንደኛዋ የአሊሰ ልጅ “ቤተሰባችን በእውነት ውስጥ እንዲሆን ትልቁን ሚና የተጫወተው የኤርና መልካም ምሳሌነት ነው” በማለት ተናግራለች። ኤርና ጽናቷ የተትረፈረፈ በረከት አስገኝቶላታል። ያንተስ ሁኔታ ምን ይመስላል? አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙህ በታማኝነት መጽናትህ በተመሳሳይ መንገድ ሊክስህ ይችላል። አዎን፣ መልካም ምግባር ማሳየትህ እንዲሁም ምሥራቹን በዘዴ መስበክህ ልዩ በሆነ መንገድ ድል እንድታደርግ ያስችልሃል። a

[የግርጌ ማስታወሻ]

a እህት ኤርና ሉዶልፍ ይህ ተሞክሮ ለሕትመት በመዘጋጀት ላይ እያለ ታማኝነቷን እንደጠበቀች በ96 ዓመቷ በሞት አንቀላፍታለች።

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኤርና ሉዶልፍ (የተቀመጠችው) ከፕሮፌሰር ፍሬድሪክ ሆልትስ ቤተሰብ አባላት ጋር