በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትንሣኤ—በአንተ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር ትምህርት

ትንሣኤ—በአንተ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር ትምህርት

ትንሣኤበአንተ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር ትምህርት

“ጻድቃንና ኀጥአን ከሙታን እንደሚነሡ በእግዚአብሔር ተስፋ አለኝ።”—የሐዋርያት ሥራ 24:15

1. የሳንሄድሪን ሸንጎ አባላት ትንሣኤን በተመለከተ ውዝግብ ውስጥ የገቡት እንዴት ነበር?

 ሐዋርያው ጳውሎስ ሦስተኛውን ሚስዮናዊ ጉዞውን ባጠናቀቀበት በ56 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በኢየሩሳሌም ውስጥ ነበር። ሮማውያን በቁጥጥር ሥር አዋሉትና በአይሁዳውያን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሳንሄድሪን ፊት እንዲቀርብ ፈቀዱለት። (የሐዋርያት ሥራ 22:29, 30) በዚህን ጊዜ ጳውሎስ ከፊሎቹ የሸንጎ አባላት ሰዱቃውያን፣ የቀሩት ደግሞ ፈሪሳውያን እንደሆኑ አስተዋለ። እነዚህ ሁለት ቡድኖች አንድ ትልቅ ልዩነት ነበራቸው። ሰዱቃውያን በትንሣኤ አያምኑም ነበር፤ ፈሪሳውያን ግን በዚህ ያምኑ ነበር። ከዚያም ጳውሎስ “ወንድሞቼ ሆይ፤ እኔ ከፈሪሳዊ የተወለድሁ ፈሪሳዊ ነኝ፣ ለፍርድ የቀረብሁትም የሙታንን ትንሣኤ ተስፋ በማድረጌ ነው” በማለት ስለ ትንሣኤ ያለውን አቋም አሳወቀ። በዚህ ጊዜ ሸንጎው ትርምስምሱ ወጣ!—የሐዋርያት ሥራ 23:6-9

2. ጳውሎስ በትንሣኤ ላይ ላለው እምነት አጥብቆ ለመከራከር ዝግጁ የነበረው ለምንድን ነው?

2 ጳውሎስ ይህ ከመሆኑ ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ወደ ደማስቆ እየተጓዘ በነበረበት ወቅት የኢየሱስን ድምፅ የሰማበትን ራእይ አይቶ ነበር። በዚህ ጊዜ ኢየሱስን “ጌታ ሆይ፤ ምን ላድርግ?” ብሎ ጠየቀው። ኢየሱስም “ተነሥተህ ወደ ደማስቆ ሂድ፤ በዚያም ልታደርገው የሚገባህን ሁሉ ይነግሩሃል” በማለት መለሰለት። ደማስቆ እንደደረሰም ሐናንያ የተባለ አንድ ደግ ክርስቲያን ደቀ መዝሙር ፈልጎ አገኘው። ሐናንያም ጳውሎስን “የአባቶቻችን አምላክ ፈቃዱን እንድታውቅ፣ ጻድቁን [ከሞት የተነሳውን ኢየሱስን] እንድታይና ቃሉን ከአንደበቱ እንድትሰማ መርጦሃል” አለው። (የሐዋርያት ሥራ 22:6-16) ይህ ክስተት ጳውሎስ በትንሣኤ ላይ ላለው እምነት ጥብቅና ለመቆም እንዳስቻለው ምንም ጥርጥር የለውም።—1 ጴጥሮስ 3:15

ስለ ትንሣኤ ተስፋ በይፋ ማወጅ

3, 4. ጳውሎስ የትንሣኤ ትምህርት ታማኝ ደጋፊ መሆኑን ያረጋገጠው እንዴት ነበር? ከእርሱስ ምሳሌ ምን እንማራለን?

3 ጳውሎስ ቆየት ብሎ በአገረ ገዥው ፊልክስ ፊት ቀረበ። በዚህ ጊዜ ከሳሾቹን አይሁዳውያንን በመወከል የቀረበው ጠርጠሉስ የተባለ “ጠበቃ” ጳውሎስን ‘የአንድ ኑፋቄ መሪና ሕዝቡን ለሁከት የሚያነሳሳ ሰው ነው’ ብሎ ከሰሰው። ጳውሎስም ምንም ሳይጠራጠር “እነርሱ ኑፋቄ በሚሉት በጌታ መንገድ የአባቶቻችንን አምላክ አመልካለሁ” በማለት መልስ ሰጠ። ከዚህ በኋላ ዋነኛውን ጉዳይ በማንሳት እንዲህ አለ:- “እንደነዚህ ሰዎች ሁሉ፣ ጻድቃንና ኀጥአን ከሙታን እንደሚነሡ በእግዚአብሔር ተስፋ አለኝ።”—የሐዋርያት ሥራ 23:23, 24፤ 24:1-8, 14, 15

4 ከሁለት ዓመት ገደማ በኋላ፣ በፊልክስ እግር የተተካው ጶርቅዮስ ፊስጦስ በእስረኛው በጳውሎስ ላይ ምርመራ በሚያደርግበት ጊዜ ንጉሡ ሄሮድስ አግሪጳ አብሮት እንዲገኝ ጋበዘው። ፊስጦስ ‘ሞቶ የነበረው ኢየሱስ ሕያው ነው’ በሚለው የጳውሎስ ሐሳብ ከሳሾቹ እንደማይስማሙ ገለጸ። ጳውሎስም የመከላከያ ሐሳብ ሲያቀርብ “ለመሆኑ፣ እግዚአብሔር ሙታንን ማስነሣት እንደማይችል አድርጋችሁ የምትቈጥሩት ለምንድን ነው?” የሚል ጥያቄ አነሳ። ከዚያም እንዲህ አለ:- “የእግዚአብሔር ርዳታ እስከ ዛሬ ስላልተለየኝ፣ እነሆ፤ እዚህ ቆሜ ለትንሹም ለትልቁም እመሰክራለሁ፤ ነቢያትና ሙሴ ይሆናል ይፈጸማል ካሉት በስተቀር አንዳች ነገር አልተናገርሁም፤ ይኸውም ክርስቶስ መከራን እንደሚቀበልና ከሙታን ቀዳሚ ሆኖ በመነሣት ለሕዝቡና ለአሕዛብ ብርሃንን እንደሚሰብክ ነው።” (የሐዋርያት ሥራ 24:27፤ 25:13-22፤ 26:8, 22, 23) ጳውሎስ በእርግጥም የትንሣኤ ትምህርት ታማኝ ደጋፊ ነበር! እኛም እንደ ጳውሎስ ትንሣኤ እንደሚኖር አፋችንን ሞልተን መናገር እንችላለን። ይሁን እንጂ ሰዎች ምን ይሰማቸዋል ብለን መጠበቅ እንችላለን? ጳውሎስ የገጠመው ዓይነት ሁኔታ ሊከሰት እንደሚችል መገመት አለብን።

5, 6. (ሀ) ሐዋርያት ስለ ትንሣኤ ማስተማራቸው በሰዎች ዘንድ ምን ስሜት ፈጠረ? (ለ) ስለ ትንሣኤ ተስፋችን ለሰዎች የምንናገር በመሆኑ ምን ማድረጋችን የግድ አስፈላጊ ነው?

5 ይህ ከመሆኑ ቀደም ብሎ ጳውሎስ በሁለተኛው ሚስዮናዊ ጉዞው ወቅት (ከ49-52 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ) አቴናን ሲጎበኝ የተከሰተውን ነገር እንመልከት። ብዙ አማልክት የነበራቸውን የአቴና ነዋሪዎች አጥጋቢ ምክንያት እያቀረበ ያወያያቸው እንዲሁም አምላክ በመረጠው ሰው አማካኝነት በዓለም ላይ በጽድቅ የመፍረድ ዓላማ እንዳለው እንዲያስተውሉ ይረዳቸው ነበር። ጳውሎስ እዚህ ላይ የጠቀሰው ሰው ከኢየሱስ ሌላ ማንም ሊሆን አይችልም። ቀጥሎም አምላክ ኢየሱስን ከሞት በማስነሳት ዓላማው የሚፈጸም መሆኑን እንዳረጋገጠ ገለጸላቸው። አድማጮቹ ምን ተሰማቸው? መጽሐፍ ቅዱስ “እነርሱም ስለ ሙታን ትንሣኤ በሰሙ ጊዜ፣ አንዳንዶቹ አፌዙ፤ ሌሎች ግን፣ ‘ስለዚህ ጉዳይ ከአንተ ዳግመኛ ለመስማት እንፈልጋለን’ አሉት” በማለት ይነግረናል።—የሐዋርያት ሥራ 17:29-32

6 የሰዎቹ ሁኔታ ጴጥሮስና ዮሐንስ በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ፣ የጰንጠቆስጤ በዓል ተከብሮ ጥቂት ጊዜ እንዳለፈ ካጋጠማቸው ነገር ጋር ይመሳሰላል። በዚያን ጊዜም ቢሆን ሰዱቃውያን የሙግቱ ዋነኛ ተዋናዮች ነበሩ። የተፈጠረውን ሁኔታ በተመለከተ የሐዋርያት ሥራ 4:1-4 እንዲህ ይላል:- “ጴጥሮስና ዮሐንስ ለሕዝቡ እየተናገሩ ሳሉ፣ ካህናትና የቤተ መቅደሱ ጥበቃ ኀላፊ እንዲሁም ሰዱቃውያን ድንገት ወደ እነርሱ መጡ። እነርሱም ሐዋርያት ሕዝቡን በማስተማራቸውና በኢየሱስ ስለተገኘው ትንሣኤ ሙታን በመስበካቸው እጅግ ተቈጡ።” ይሁን እንጂ ጥሩ ዝንባሌ ያሳዩ ሰዎችም ነበሩ። “ቃሉን ከሰሙት መካከል ብዙዎቹ አመኑ፤ የወንዶቹም ቊጥር ወደ አምስት ሺህ ከፍ አለ።” ከዚህ በግልጽ ለመረዳት እንደምንችለው ስለ ትንሣኤ ተስፋ የምንነግራቸው ሰዎች የተለያየ ዝንባሌ ሊኖራቸው ይችላል። በመሆኑም በዚህ ትምህርት ላይ ያለንን እምነት ማጠናከራችን የግድ አስፈላጊ ነው።

እምነትና ትንሣኤ

7, 8. (ሀ) በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለቆሮንቶስ ጉባኤ በተላከው ደብዳቤ ላይ እንደተገለጸው እምነት ከንቱ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) ስለ ትንሣኤ ተስፋ ትክክለኛ ግንዛቤ ማግኘት እውነተኞቹን ክርስቲያኖች ለመለየት የሚያስችለው እንዴት ነው?

7 በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከነበሩት ክርስቲያኖች መካከል አንዳንዶቹ በትንሣኤ ተስፋ ለማመን ከብዷቸው ነበር። ከእነዚህም ውስጥ ጥቂቶቹ በቆሮንቶስ ጉባኤ ይገኙ ነበር። ጳውሎስ ለእነዚህ ክርስቲያኖች “እኔ የተቀበልሁትንና ከሁሉ በላይ የሆነውን ለእናንተ አስተላልፌአለሁ፤ ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚሉት ክርስቶስ ስለ ኀጢአታችን ሞተ፤ ተቀበረ፤ በቅዱሳት መጻሕፍት እንደ ተጻፈውም በሦስተኛው ቀን ተነሣ” በማለት ጻፈላቸው። ከዚያም ከሞት የተነሳው ክርስቶስ ‘ከአምስት መቶ በላይ ለሚሆኑ ወንድሞች እንደታየና’ ከተመለከቱትም መካከል አብዛኞቹ በወቅቱ በሕይወት እንዳሉ በመንገር ጉዳዩ እውነት መሆኑን አረጋገጠላቸው። (1 ቆሮንቶስ 15:3-8) አክሎም “ክርስቶስ ከሙታን እንደ ተነሣ የሚሰበክ ከሆነ፣ ከእናንተ አንዳንዶቹ እንዴት የሙታን ትንሣኤ የለም ይላሉ? የሙታን ትንሣኤ ከሌለማ ክርስቶስም አልተነሣም ማለት ነዋ! ክርስቶስም ካልተነሣ ስብከታችን ዋጋ ቢስ ነው፤ እምነታችሁም ከንቱ ነው” በማለት አስረዳቸው።—1 ቆሮንቶስ 15:12-14

8 አዎን፣ ትንሣኤ የማይኖር ከሆነ የክርስትና እምነት ከንቱ ይሆናል መባሉ ትንሣኤ መሠረታዊ የሆነ ትምህርት መሆኑን ያሳያል። ስለ ትንሣኤ ትክክለኛ ግንዛቤ ማግኘት እውነተኞቹን ክርስቲያኖች ከሐሰተኞቹ ለመለየት ያስችላል። (ዘፍጥረት 3:4፤ ሕዝቅኤል 18:4) ጳውሎስ ከክርስትና ‘የመጀመሪያ ትምህርቶች’ መካከል የትንሣኤ ትምህርት አንዱ መሆኑን የገለጸው ለዚህ ነው። በበኩላችን ‘ወደ ብስለት ለመሄድ’ ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ ያለብን ሲሆን ጳውሎስም “እግዚአብሔር ቢፈቅድ ይህን እናደርጋለን” በማለት ምክር ሰጥቷል።—ዕብራውያን 6:1-3

የትንሣኤ ተስፋ

9, 10. በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ “ትንሣኤ” ተብሎ የተገለጸው ቃል ትርጉም ምንድን ነው?

9 በትንሣኤ ላይ ያለንን እምነት ይበልጥ ለማጠናከር ‘መጽሐፍ ቅዱስ ትንሣኤ ሲል ምን ማለቱ ነው? የትንሣኤ ትምህርት የይሖዋን ፍቅር የሚያጎላው እንዴት ነው?’ እንደሚሉት ያሉ ጥያቄዎችን እንመረምራለን። ለእነዚህ ጥያቄዎች የምናገኘው መልስ ወደ አምላክ በይበልጥ እንድንቀርብ የሚያደርገን ከመሆኑም በላይ ለሌሎች ስለ ትንሣኤ እንድናስተምር ይረዳናል።—2 ጢሞቴዎስ 2:2፤ ያዕቆብ 4:8

10 “ትንሣኤ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ቀጥተኛ ፍቺው “እንደገና መነሳት” ማለት ነው። እንደገና መነሳት ምን ነገሮችን ይጨምራል? መጽሐፍ ቅዱስ ትንሣኤ ብሎ የሚጠራው አንድ የሞተ ሰው እንደገና ሕያው ይሆናል የሚለውን እምነት ነው። ከዚህም በላይ ሟቹ ምድራዊ ተስፋ ያለው ከሆነ ሥጋዊ አካል ለብሶ እንደሚነሳ፣ ሰማያዊ ተስፋ ያለው ከሆነ ደግሞ መንፈሳዊ አካል ይዞ እንደሚነሳ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። በዚህ ግሩም ተስፋ ላይ የተንጸባረቀው የይሖዋ ፍቅር፣ ጥበብና ኃይል በጣም እንድንደነቅ ያደርገናል።

11. የአምላክ ቅቡዓን አገልጋዮች ምን ዓይነት የትንሣኤ ተስፋ ከፊታቸው ይጠብቃቸዋል?

11 የኢየሱስና የቅቡዓን ወንድሞቹ ትንሣኤ፣ በሰማይ ለሚኖራቸው አገልግሎት አመቺ የሆነ መንፈሳዊ አካል እንዲያገኙ ያስችላቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 15:35-38, 42-53) ኢየሱስና ቅቡዓን ወንድሞቹ ምድርን ወደ ገነትነት የምትለውጠው መሲሐዊት መንግሥት ገዢዎች ይሆናሉ። ቅቡዓኑ በሊቀ ካህናቱ በኢየሱስ የበላይ ተቆጣጣሪነት፣ የንጉሥ ካህናት ሆነው ያገለግላሉ። እነዚህ ካህናት ጽድቅ በሰፈነባት አዲስ ምድር ላይ የሚኖሩት የሰው ልጆች ከክርስቶስ ቤዛ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስችሏቸዋል። (ዕብራውያን 7:25, 26፤ 9:24፤ 1 ጴጥሮስ 2:9፤ ራእይ 22:1, 2) እስከ አሁን በምድር ላይ በሕይወት ያሉ ቅቡዓን ይህ እስኪፈጸም ድረስ ለአምላክ ታማኝ ሆነው መቆየት አለባቸው። እነዚህ ቅቡዓን ሲሞቱ “ተገቢውን ዋጋ” ይቀበላሉ፤ ይህም የሚሆነው በትንሣኤ አማካኝነት የማይሞት መንፈሳዊ ሕይወት በሰማይ በሚያገኙበት ጊዜ ነው። (2 ቆሮንቶስ 5:1-3, 6-8, 10፤ 1 ቆሮንቶስ 15:51, 52፤ ራእይ 14:13) ጳውሎስ “በሞቱ ከእርሱ ጋር እንደዚህ ከተባበርን፣ በትንሣኤው ደግሞ በእርግጥ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን” በማለት ጽፏል። (ሮሜ 6:5) በምድር ላይ እንደገና ለመኖር ሥጋዊ አካል ለብሰው ስለሚነሱት ሰዎችስ ምን ማለት ይቻላል? የትንሣኤ ተስፋ ከአምላክ ጋር ይበልጥ እንዲቀራረቡ የሚረዳቸው እንዴት ነው? ከአብርሃም ታሪክ በርካታ ትምህርቶችን ማግኘት እንችላለን።

ትንሣኤና ከይሖዋ ጋር መወዳጀት

12, 13. አብርሃም በትንሣኤ ለማመን ጠንካራ መሠረት የሆነለት ነገር ምንድን ነው?

12 “የእግዚአብሔር ወዳጅ” ተብሎ የተገለጸው አብርሃም ታላቅ የእምነት ሰው ነበር። (ያዕቆብ 2:23) ጳውሎስ በዕብራውያን ምዕራፍ 11 ላይ ታማኝ ስለነበሩ ወንዶችና ሴቶች ሲናገር ስለ አብርሃም እምነት ሦስት ጊዜ ገልጿል። (ዕብራውያን 11:8, 9, 17) በሦስተኛው ላይ የጠቀሰው፣ አብርሃም በታዛዥነት ልጁን ለመሠዋት በተዘጋጀ ጊዜ ያሳየውን እምነት ነው። አብርሃም፣ ይሖዋ የተስፋው ዘር በይስሐቅ በኩል እንደሚመጣ የገባለትን ቃል እንደሚፈጽም እምነት ነበረው። እንዲሁም ይስሐቅ መሥዋዕት ሆኖ ቢሞት እንኳን “እግዚአብሔር ሙታንን [ይስሐቅን] ሊያስነሣ እንደሚችል ተገንዝቦ ነበር።”

13 ይሖዋ የአብርሃምን እምነት ጥንካሬ ከተመለከተ በኋላ በምትኩ የእንስሳ መሥዋዕት እንዲያቀርብ ዝግጅት አደረገለት። የሆነ ሆኖ የይስሐቅ ሁኔታ ለትንሣኤ ተምሳሌት እንደሆነ ጳውሎስ ሲገልጽ “አብርሃም . . . ይስሐቅንም ከሞት የመነሣት አምሳያ ሆኖ አገኘው” ብሏል። (ዕብራውያን 11:19) በይበልጥ ደግሞ አብርሃም ከዚህ ቀደም ሲል ያጋጠመው ሁኔታ በትንሣኤ እንዲያምን ጠንካራ መሠረት ሆኖለት ነበር። ይሖዋ አብርሃምና ሣራ በስተርጅናቸው ይስሐቅን እንዲወልዱ ባደረገ ጊዜ የአብርሃምን የመውለድ ችሎታ እንደገና ሕያው አላደረገም?—ዘፍጥረት 18:10-14፤ 21:1-3፤ ሮሜ 4:19-21

14. (ሀ) በዕብራውያን 11:9, 10 ላይ እንደተገለጸው አብርሃም ሲጠባበቅ የነበረው ምንድን ነው? (ለ) አብርሃም መንግሥቲቱ የምታመጣቸውን በረከቶች ለመቅመስ ምን ማግኘት አለበት? (ሐ) እኛስ ከመንግሥቲቱ በረከቶች ተቋዳሽ መሆን የምንችለው እንዴት ነው?

14 ጳውሎስ፣ አብርሃም በባዕድ አገር እንዳለ መጻተኛ ሆኖ በድንኳን እየኖረ “መሠረት ያላትን፣ እግዚአብሔር የሠራትንና የፈጠራትን ከተማ ይጠባበቅ” እንደነበር ጽፏል። (ዕብራውያን 11:9, 10) ከተማዋ ቃል በቃል የአምላክ ቤተ መቅደስ እንደሚገኝባት እንደ ኢየሩሳሌም ያለች ሳትሆን ምሳሌያዊት ናት። ይህች ከተማ በኢየሱስና በ144,000 ተባባሪ ገዢዎች የተመሠረተችው ሰማያዊት መንግሥት ነች። ሰማያዊ ውርሻቸውን ያገኙ የ144,000ዎቹ አባላት “ቅድስቲቱ ከተማ፣ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም” እና የክርስቶስ “ሙሽራ” ተብለው ተገልጸዋል። (ራእይ 21:2) ይሖዋ በ1914 ኢየሱስን የመሲሐዊቷ መንግሥት ንጉሥ አድርጎ ከመሾሙም በላይ በጠላቶቹ መካከል እንዲገዛ አዝዞታል። (መዝሙር 110:1, 2፤ ራእይ 11:15) “የእግዚአብሔር ወዳጅ” የሆነው አብርሃም ይህች መንግሥት የምታመጣቸውን በረከቶች ማግኘት እንዲችል እንደገና በሕይወት መኖር አለበት። እኛም በተመሳሳይ ከመንግሥቲቱ በረከቶች መቋደስ እንድንችል በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ለመገኘት አርማጌዶንን በሕይወት ከሚያልፉት እጅግ ብዙ ሰዎች መካከል መሆን አለብን፤ አሊያም ደግሞ ከሞት ከሚነሱት ውስጥ መሆን ይኖርብናል። (ራእይ 7:9, 14) ታዲያ ለትንሣኤ ተስፋ መሠረት የሆነው ነገር ምንድን ነው?

ለትንሣኤ ተስፋ መሠረት የሆነው የአምላክ ፍቅር

15, 16. (ሀ) በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሰው የመጀመሪያው ትንቢት ለትንሣኤ ተስፋችን መሠረት የሚጥለው እንዴት ነው? (ለ) በትንሣኤ ላይ ያለን እምነት ከይሖዋ ጋር ይበልጥ እንድንቀራረብ የሚያደርገን እንዴት ነው?

15 ከአፍቃሪው ሰማያዊ አባታችን ጋር የቀረበ ወዳጅነት ካለን፣ የአብርሃም ዓይነት ጠንካራ እምነት ካዳበርንና ለአምላክ ሕግጋት ከታዘዝን ይሖዋ እንደ ጻድቅ ሊቆጥረንና እንደ ወዳጆቹ አድርጎ ሊያየን ይችላል። ይህም መንግሥቲቱ ከምታስገኛቸው ጥቅሞች ተካፋይ ለመሆን ያስችለናል። በእርግጥም በአምላክ ቃል ውስጥ በዘፍጥረት 3:15 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው የመጀመሪያው ትንቢት፣ ለትንሣኤ ተስፋና ሰዎች ከአምላክ ጋር ለሚመሠርቱት ዝምድና መሠረት ጥሏል። ትንቢቱ የሰይጣን ራስ እንደሚቀጠቀጥ ብቻ ሳይሆን የሴቲቱ ዘር ተረከዝም እንደሚቀጠቀጥ ጭምር ገልጿል። ኢየሱስ በእንጨት ላይ ተሰቅሎ መገደሉ በምሳሌያዊ ሁኔታ ተረከዙ መቀጥቀጡን የሚያሳይ ነው። በሦስተኛው ቀን ከሞት መነሳቱ ደግሞ የቁስሉን መዳንና ‘በሞት ላይ ኀይል ያለው ዲያብሎስ’ መደምሰሱ የማይቀር መሆኑን ያረጋግጣል።—ዕብራውያን 2:14

16 ጳውሎስ “ገና ኀጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞተ፤ ይህም እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያሳያል” በማለት አሳስቦናል። (ሮሜ 5:8) እንዲህ ላለው የማይገባን ደግነት አመስጋኝ መሆናችን ወደ ኢየሱስና ወደ አፍቃሪው ሰማያዊ አባታችን እንድንቀርብ ይገፋፋናል።—2 ቆሮንቶስ 5:14, 15

17. (ሀ) ኢዮብ የገለጸው ስለ የትኛው ተስፋ ነው? (ለ) ኢዮብ 14:15 ስለ ይሖዋ ምን ይገልጻል? ይህን በተመለከተ አንተስ ምን ይሰማሃል?

17 ከክርስትና ዘመን በፊት የኖረው ታማኙ ኢዮብም በትንሣኤ ያምን ነበር። ሰይጣን በኢዮብ ላይ ከባድ ሥቃይ አድርሶበታል። ወዳጅ ተብዬዎቹ ስለ ትንሣኤ አንድም ነገር ባይጠቅሱለትም እንኳ ኢዮብ ይህ ተስፋ የብርታት ምንጭ ሆኖለት ስለነበር “ሰው ከሞተ በኋላ ተመልሶ በሕይወት ይኖራል?” የሚል ጥያቄ አንስቷል። ከዚያም “እድሳቴ እስከሚመጣ ድረስ፣ ተጋድሎ የሞላበትን ዘመኔን ሁሉ እታገሣለሁ” በማለት ለጥያቄው ራሱ መልስ ሰጥቷል። ለአምላኩ ለይሖዋም “ትጠራኛለህ፤ እኔም እመልስልሃለሁ” በማለት በእርግጠኝነት ተናግሯል። ከዚያም ኢዮብ “የእጅህንም ሥራ ትናፍቃለህ” በማለት አፍቃሪው ፈጣሪያችን ምን እንደሚሰማው ገልጿል። (ኢዮብ 14:14, 15) አዎን፣ ይሖዋ ታማኝ የሆኑ ሰዎች በትንሣኤ አማካኝነት ሕይወት የሚያገኙበትን ጊዜ በጉጉት ይጠብቃል። ፍጹም ባንሆንም እንኳን ይሖዋ ፍቅርና የማይገባ ደግነት አሳይቶናል፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ማሰላሰላችን ወደ እርሱ እንድንቀርብ ይገፋፋናል!—ሮሜ 5:21፤ ያዕቆብ 4:8

18, 19. (ሀ) ዳንኤል እንደገና ስለመኖር ምን ተስፋ ነበረው? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን እንመረምራለን?

18 የአምላክ መልአክ “እጅግ የተወደድህ ሰው” ብሎ የጠራው ነቢዩ ዳንኤል የሕይወት ዘመኑን በሙሉ ታማኝ ሆኖ በማገልገል አሳልፏል። (ዳንኤል 10:11, 19) ዳንኤል በግዞት ከተወሰደበት ከ617 ከክርስቶስ ልደት በፊት ጀምሮ በፋርሱ ንጉሥ በቂሮስ ሦስተኛ የግዛት ዘመን ይኸውም በ536 ከክርስቶስ ልደት በፊት ራእይ ከተመለከተ ከጥቂት ጊዜ በኋላ እስከሞተበት ጊዜ ድረስ ለይሖዋ ያለውን ታማኝነት አላጓደለም። (ዳንኤል 1:1፤ 10:1) ዳንኤል በሜዶናዊው ዳርዮስ ሦስተኛ የግዛት ዓመት፣ በታላቁ መከራ ስለሚደመደመው የዓለም ኃያላን መንግሥታት መፈራረቅ ራእይ አይቶ ነበር። (ዳንኤል 11:1-12:13) ራእዩን በሚገባ መረዳት ስላልቻለ መልእክቱን ይዞለት የመጣውን መልአክ “ጌታዬ ሆይ፤ የዚህ ሁሉ ፍጻሜ ምንድነው?” ብሎ ጠየቀው። በዚህን ጊዜ መልአኩ ‘ጠቢባን ስለሚያስተውሉበት የፍጻሜ ዘመን’ ገለጸለት። የዳንኤልስ የወደፊት ተስፋ ምንድን ነው? መልአኩ “ታርፋለህ፤ በቀኖቹ መጨረሻም ተነስተህ የተመደበልህን ርስት ትቀበላለህ” በማለት አረጋገጠለት። (ዳንኤል 12:8-10, 13) ዳንኤል በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ዘመን በሚከናወነው ‘የጻድቃን ትንሣኤ’ እንደገና ሕያው ይሆናል።—ሉቃስ 14:14

19 መጀመሪያ ካመንበት ጊዜ ይልቅ አሁን ወደ መጨረሻው ዘመንና የክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ወደሚጀምርበት ወቅት በጣም ቀርበናል። በመሆኑም ‘ከአብርሃም፣ ከኢዮብ፣ ከዳንኤልና ከሌሎች ታማኝ ወንዶችና ሴቶች ጋር በአዲሲቱ ዓለም ውስጥ አብሬ እገኝ ይሆን?’ እያልን ራሳችንን መጠየቅ ይገባናል። ከይሖዋ ጋር ያለን ወዳጅነት እንደተጠበቀ ከቆየና የእርሱን ትእዛዛት ማክበራችንን ከቀጠልን በዚያ የማንገኝበት ምንም ምክንያት የለም። በሚቀጥለው ጥናታችን ላይ እነማን ትንሣኤ እንደሚያገኙ ለማወቅ የሚያስችሉንን የትንሣኤን ተስፋ የሚመለከቱ ተጨማሪ ማብራሪያዎች እንመረምራለን።

ታስታውሳለህ?

• ጳውሎስ በትንሣኤ ተስፋ ላይ ስላለው እምነት በተናገረ ጊዜ ምን ዓይነት ምላሽ አጋጠመው?

• የትንሣኤ ተስፋ እውነተኛ ክርስቲያኖችን ከሐሰተኞቹ ለመለየት ያስችላል የምንለው ለምንድን ነው?

• አብርሃም፣ ኢዮብና ዳንኤል በትንሣኤ ላይ እምነት እንደነበራቸው እንዴት እናውቃለን?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጳውሎስ በአገረ ገዢው በፊልክስ ፊት በቀረበበት ወቅት ስለ ትንሣኤ ተስፋ በእርግጠኝነት ተናግሯል

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አብርሃም በትንሣኤ እንዲያምን ያስቻለው ምንድን ነው?

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢዮብ የትንሣኤ ተስፋ የብርታት ምንጭ ሆኖለት ነበር

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዳንኤል ጻድቃን ትንሣኤ በሚያገኙበት ጊዜ እንደገና ሕያው ይሆናል