አስደሳች የሆነው የትንሣኤ ተስፋ
አስደሳች የሆነው የትንሣኤ ተስፋ
በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በርካታ ሰዎች በትንሣኤ ያምናሉ። የሙስሊሞች ቅዱስ መጽሐፍ የሆነው ቁርዓን ስለ ትንሣኤ የሚያብራራ ሙሉ ምዕራፍ ይዟል። ሱራህ 75 በከፊል እንዲህ ይላል:- “በትንሣኤ ቀን እምላለሁ። . . . ሰው አጥንቶቹን አለመሰብሰባችንን ያስባልን? . . . የትንሣኤው ቀን መቼ ነው? ሲል ይጠይቃል። ይህ (ጌታ)፣ ሙታንን ሕያው በማድረግ ላይ ቻይ አይደለምን?”—ሱራህ 75:1-6, 40
ዘ ኒው ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ እንደሚናገረው “የዞራስተር ሃይማኖት ክፋት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንደሚወገድ፣ አጠቃላይ ትንሣኤና የመጨረሻ ፍርድ እንደሚኖር እንዲሁም ምድር እንደገና ጸድታ ጻድቃን እንደሚኖሩባት ያስተምር ነበር።”
ኢንሳይክሎፒዲያ ጁዳይካ ትንሣኤ “የሞቱ ሰዎች ሥጋዊ አካላቸውን ይዘው በመነሳት እንደገና በምድር ላይ ይኖራሉ የሚል እምነት ነው” ሲል ፍቺ ሰጥቶታል። ይኸው የማመሳከሪያ ጽሑፍ አይሁዶች የሰው ልጅ የማትሞት ነፍስ አለችው የሚለውን እምነት መቀበላቸው ግራ መጋባት እንደፈጠረ አክሎ ተናግሯል። “በመሠረቱ ትንሣኤና ነፍስ አትሞትም የሚሉት ሁለት እምነቶች ይጋጫሉ” በማለት አምኗል።
የሂንዱ እምነት ሪኢንካርኔሽን ወይም ሰው ከሞተ በኋላ እንደገና ይወለዳል የሚል ትምህርት ያስተምራል። ይህ እውነት ከሆነ ሰው ከሞተ በኋላ በሕይወት የምትቀጥል ነፍስ የግድ ያስፈልገዋል ማለት ነው። የሂንዱዎች ቅዱስ መጽሐፍ ባገቫድ ጊተ “በሁሉም የሰውነት ክፍል ውስጥ የምትገኘው ነፍስ አትጠፋም። ይህችን ዘላለማዊ ነፍስ ማንም ሊያጠፋት አይችልም” በማለት ይገልጻል።
ቡድሂዝም ከሂንዱይዝም የሚለየው ዘላለማዊ ነፍስ መኖሯን ባለመቀበሉ ነው። ሆኖም በዛሬው ጊዜ በሩቅ ምሥራቅ የሚኖሩ በርካታ ቡድሂስቶች አንድ ሰው ሲሞት ወደ ሌላ አካል የምትሸጋገር የማትሞት ነፍስ አለችው ብለው ያምናሉ። a
የትንሣኤን ትምህርት በተመለከተ ያለው ግራ መጋባት
አብዛኛውን ጊዜ ክርስቲያን ነን በሚሉ ሰዎች የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ነፍስ ከሞት በኋላ ሕያው ሆና እንደምትቀጥል ይገለጻል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ትንሣኤ እንዳለም ይነገራል። ለምሳሌ ያህል የአንግሊካን ቤተ ክርስቲያን ቀሳውስት የሚከተሉትን ቃላት ሲደግሙ መስማት የተለመደ ነው:- “ሁሉን የሚችል አምላክ በታላቅ ምሕረቱ፣ በሞት የተለየንን የውድ ወንድማችንን ነፍስ ለራሱ ወስዷል፤ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የሚገኘውና ወደ ዘላለም ሕይወት የሚያደርሰው እውነተኛና እርግጠኛ የትንሣኤ ተስፋ ስላለን አስከሬኑን በመቅበር ምድርን ወደ ምድር፣ አመድን ወደ አመድ፣ አፈርን ወደ አፈር እንመልሳለን።”—ዘ ቡክ ኦቭ ኮመን ፕሬየር
ይህ አነጋገር ‘መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው ስለ ትንሣኤ ነው? ወይስ የማትሞት ነፍስ አለች ስለሚለው ትምህርት?’ የሚል ጥያቄ ያስነሳል። እንዲያውም ፈረንሳዊው ፕሮቴስታንት ፕሮፌሰር ኦስካር ኩልማን የሰጡትን
ሐሳብ ልብ በል። ኢሞርታሊቲ ኦቭ ዘ ሶል ኦር ሬዘሬክሽን ኦቭ ዘ ዴድ? በሚለው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ብለዋል:- “ሙታን በትንሣኤ ይነሳሉ በሚለው የክርስቲያኖች ተስፋና ነፍስ አትሞትም በሚለው የግሪካውያን እምነት መካከል ፍጹም ልዩነት አለ። . . . ክርስትና የኋላ ኋላ ሁለቱን እምነቶች ቀላቅላ በማስተማሯ በአሁኑ ጊዜ አንድ ክርስቲያን በሁለቱ ትምህርቶች መካከል ያለው ልዩነት ባይገባውም እንኳ እኔና አብዛኞቹ ሊቃውንት እውነት ነው ብለን የምናምነውን ነገር የምንደብቅበት ምክንያት አይታየኝም። . . . የአዲስ ኪዳን አጠቃላይ ይዘት በትንሣኤ እምነት ላይ ያተኮረ ነው። . . . አምላክ አንድን የሞተ ሰው እንደ አዲስ ሲፈጥረው እንደገና ሕያው ይሆናል።”በአጠቃላይ ሲታይ ሰዎች ስለ ሞትና ስለ ትንሣኤ በሚሰጡት ትምህርቶች ግራ መጋባታቸው አያስደንቅም። ይህን ግራ መጋባት ለመፍታት የሰው ልጅ ፈጣሪ የሆነው ይሖዋ አምላክ የገለጠው እውነት የሚገኝበትን መጽሐፍ ቅዱስን መመርመር ያስፈልገናል። መጽሐፍ ቅዱስ ጥቂት የትንሣኤ ዘገባዎችን ይዟል። ስለ ትንሣኤ ግልጽ የሆነ ግንዛቤ ለመጨበጥ ከእነዚህ መካከል አራቱን እንመርምር።
“ሴቶች ሙታናቸውን በትንሣኤ ተቀበሉ”
ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ክርስትና ለተለወጡት አይሁዳውያን በጻፈው ደብዳቤ ላይ የእምነት ሴቶች “ሙታናቸውን በትንሣኤ ተቀበሉ” በማለት ተናግሯል። (ዕብራውያን 11:35 የ1954 ትርጉም) ከእነዚህ ሴቶች መካከል አንዷ የምትኖረው በሜዲትራኒያን የባሕር ዳርቻ ላይ ለምትገኘው ለሲዶና ቅርብ በሆነችው በከነዓናውያን ከተማ በሰራፕታ ነበር። ይህች ሴት የአምላክ ነቢይ የነበረውን ኤልያስን በእንግድነት የተቀበለችው ሲሆን ጽኑ ረሃብ ተከስቶ በነበረበት ወቅት ጭምር ምግብ በመስጠት አስተናግዳዋለች። የሚያሳዝነው የዚህች ሴት ልጅ ድንገት ታምሞ ሞተ። ኤልያስም ወዲያውኑ ልጁን እርሱ ወደሚያርፍበት ሰገነት ወሰደውና እንደገና ሕያው ይሆን ዘንድ ይሖዋን ተማጸነ። በዚህ ጊዜ ተአምር ተፈጥሮ ‘ልጁ ዳነ።’ ኤልያስ ልጁን ወደ እናቱ በመውሰድ “እነሆ፣ ልጅሽ በሕይወት ይኖራል” አላት። የሰጠችው ምላሽ ምን ነበር? በደስታ ስሜት ተሞልታ “የእግዚአብሔር ሰው እንደ ሆንህ፣ የእግዚአብሔርም ቃል በአፍህ እውነት እንደ ሆነ አሁን አወቅሁ” አለችው።—1 ነገሥት 17:22-24 የ1954 ትርጉም
ከሰራፕታ በስተ ደቡብ 100 ኪሎ ሜትር ያህል ርቀት ላይ የሚኖሩ ለጋስ ባልና ሚስት ነበሩ፤ እነዚህ ባልና ሚስት በኤልያስ እግር የተተካውን ነቢዩ ኤልሳዕን ይንከባከቡት ነበር። ሚስትየዋ ሱነም ውስጥ የታወቀች ሴት ነበረች። ከባለቤቷም ጋር ተማክረው ኤልሳዕ በቤታቸው ላይ ባለ ሰገነት ውስጥ እንዲያርፍ ዝግጅት አደረጉ። ሴትየዋ ወንድ ልጅ በወለደች ጊዜ ልጅ ስላልወለዱ ይሰማቸው የነበረው ሐዘን በደስታ ተተካ። ልጁ ካደገ በኋላ ብዙ ጊዜ አባቱና አጫጆቹ ወደሚሠሩበት ማሳ ይሄድ ነበር። አንድ ቀን አሳዛኝ ሁኔታ ተፈጠረ። ልጁ ራሴን አመመኝ እያለ ይጮኽ ጀመር። በዚህ ጊዜ አንድ አገልጋይ ቶሎ ብሎ ወደ ቤት ከወሰደው በኋላ እናቱ አቅፋ ጭኗ ላይ አስቀመጠችው፤ ሆኖም ትንሽ እንደቆየ የልጁ ሕይወት አለፈ። በጭንቀት የተዋጠችው እናት እርዳታ ለመግኘት ኤልሳዕን መጥራት እንዳለባት ወሰነች። ከአንድ አገልጋይ ጋር በመሆን በስተ ሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ ኤልሳዕ ወደሚገኝበት ወደ ቀርሜሎስ ተራራ አቀናች።
ነቢዩም አገልጋዩ ግያዝ የልጁን መሞት እንዲያረጋግጥ አስቀድሞ ላከው። እርሱ እዚያ ሲደርስ በእርግጥም ሁለተኛ ነገሥት 4:32-37 ሁኔታውን እንዲህ በማለት ይዘግባል:- “ኤልሳዕ ወደ ቤት ሲገባም ልጁ ሞቶ በዐልጋው ላይ ተጋድሞ ነበር። ወደ ውስጥም ገባ፤ ከዚያም በሩን በራሱና በልጁ ላይ ዘግቶ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ። በዐልጋው ላይ ወጥቶም በልጁ ላይ ተጋደመና አፉን በአፉ፣ ዐይኑን በዐይኑ፣ እጁን በእጁ ላይ አደረገ። ሙሉ በሙሉ እንደተዘረጋበትም፣ የልጁ ሰውነት መሞቅ ጀመረ። ኤልሳዕም ተነሥቶ በቤቱ ውስጥ ወዲያና ወዲህ ከሄደ በኋላ ወደ ዐልጋው ወጥቶ እንደ ገና በልጁ ላይ ሙሉ ለሙሉ ተዘረጋበት፤ ልጁም ሰባት ጊዜ አስነጠሰውና ዐይኖቹን ከፈተ። ኤልሳዕም ግያዝን ጠርቶ፣ ‘ሱነማዪቱን ጥራት፤’ አለው፤ እርሱም ጠራት። እንደመጣችም፣ ‘በይ ልጅሽን ውሰጂ’ አላት። እርሷም ገብታ በእግሩ ላይ ወደቀች፤ በምድርም ላይ ተደፋች፤ ልጇንም ይዛ ወጣች።”
ልጁ ሞቶ ነበር። ኤልሳዕና ሴትየዋም ተከትለውት ሄዱ፤ ይሁን እንጂ ሱነም ሲደርሱ ምን ተከሰተ?በሰራፕታ ትኖር እንደነበረችው መበለት ሁሉ ሱነማዊቷም ሴት ይህ ሁኔታ የተከናወነው በአምላክ ኃይል እንደሆነ ታውቅ ነበር። እነዚህ ሁለት ሴቶች አምላክ ልጆቻቸውን እንደገና ሕያው በማድረጉ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቷቸዋል።
በኢየሱስ አገልግሎት ዘመን ከሞት የተነሱ ሰዎች
ከ900 ዓመታት ገደማ በኋላ ከሱነም በስተ ሰሜን ትንሽ ራቅ ብላ በምትገኘው ናይን በምትባል መንደር አቅራቢያ አንድ ሰው ከሞት ተነሳ። ኢየሱስ ክርስቶስና ደቀ መዛሙርቱ ከቅፍርናሆም ተነስተው ወደ ናይን መግቢያ በር ሲደርሱ ቀብር የሚሄዱ ሰዎች አጋጠሟቸው፤ በዚህ ጊዜ ኢየሱስ አንድ ልጇን ያጣችውን መበለት ተመለከተና ማልቀሷን እንድታቆም ነገራት። ከዚያ በኋላ የሆነውን ሐኪሙ ሉቃስ እንዲህ በማለት ዘግቧል:- “ቀረብ ብሎም ቃሬዛውን ነካ፤ የተሸከሙትም ሰዎች ቀጥ ብለው ቆሙ፤ ኢየሱስም፣ ‘አንተ ጐበዝ፤ ተነሥ እልሃለሁ!’ አለው። የሞተውም ሰው ቀና ብሎ ተቀመጠ፤ መናገርም ጀመረ። ኢየሱስም ወስዶ ለእናቱ ሰጣት።” (ሉቃስ 7:14, 15) ይህን ተአምር የተመለከቱ ሰዎች ለአምላክ ክብር ሰጥተዋል። ኢየሱስ ሰውን ከሞት እንዳስነሳ የሚገልጸው ወሬ በስተ ደቡብ በሚገኘው በይሁዳና በዙሪያው ባሉ ወረዳዎች ሁሉ ተሰማ። የመጥምቁ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርትም ስለዚህ ተአምር ሰምተው ስለነበር ለዮሐንስ ነገሩት። ዮሐንስም ወደ ኢየሱስ ሄደው እንደሚመጣ የሚጠበቀው መሲሕ እሱ መሆን አለመሆኑን እንዲጠይቁት ላካቸው። ኢየሱስ “ሄዳችሁ ያያችሁትንና የሰማችሁትን ለዮሐንስ ንገሩት፤ ዐይነ ስውራን ያያሉ፤ ዐንካሶች በትክክል ይራመዳሉ፤ ለምጻሞች ነጽተዋል፤ ደንቈሮዎች ይሰማሉ፤ ሙታን ተነሥተዋል፤ ለድኾችም ወንጌል ይሰበካል” በማለት ነገራቸው።—ሉቃስ 7:22
ኢየሱስ የሞቱትን በማስነሳት ከፈጸማቸው ተአምራት መካከል በብዙዎች ዘንድ የሚታወቀው የጓደኛው የአልዓዛር ትንሣኤ ነበር። በዚህ ወቅት ኢየሱስ በቦታው ዮሐንስ 11:39) የአልዓዛር በድን መበስበስ መጀመሩ ኢየሱስ ከሞት እንዳያስነሳው አላገደውም። ኢየሱስ አልዓዛርን እንዲወጣ ባዘዘው ጊዜ “የሞተውም ሰው እጅና እግሩ በቀጭን ስስ ጨርቅ እንደ ተጠቀለለ፣ ፊቱም በሻሽ እንደ ተጠመጠመ ወጣ።” በኋላ ላይ የኢየሱስ ጠላቶች የወሰዷቸው እርምጃዎች ዳግም ሕይወት ያገኘው ሰው በእርግጥ አልዓዛር እንደሆነ ማስረጃ ይሆናሉ።—ዮሐንስ 11:43, 44፤ 12:1, 9-11
የተገኘው አልዓዛር ከሞተ ከተወሰኑ ቀናት በኋላ ነበር። ቢታንያ ሲደርስ አልዓዛር ከሞተ አራት ቀናት ሆኖታል። መቃብሩ የተገጠመበትን ድንጋይ እንዲያነሱ በተናገረ ጊዜ ማርታ “ጌታ ሆይ፤ አሁንማ አራት ቀን ስለ ቈየ ይሸታል” በማለት አከላከለች። (ሙታን ትንሣኤ እንዳገኙ ከሚዘግቡት ከእነዚህ አራት ታሪኮች ምን እንረዳለን? ትንሣኤ ያገኘው እያንዳንዱ ግለሰብ ማንነቱ አልተቀየረም። በጣም ቅርብ የሆኑት ዘመዶቻቸው እንኳ በደንብ ለይተዋቸዋል። ከተነሱት ሰዎች መካከል አንዳቸውም ቢሆኑ ሞተው በቆዩበት ጥቂት ጊዜ ውስጥ ምን እንዳጋጠማቸው የተናገሩት ነገር የለም። ወደ ሌላ ዓለም ሄዶ እንደነበረ የተናገረም አልነበረም። ሁሉም በጥሩ ጤንነት እንደተነሱ እሙን ነው። ከኢየሱስ አነጋገር መረዳት እንደምንችለው ከሞት የተነሱት ሰዎች ለጥቂት ጊዜ አንቀላፍተው የተቀሰቀሱ ያህል ነበር። (ዮሐንስ 11:11) እርግጥ ነው ሁሉም ከተወሰነ ጊዜ በኋላ እንደገና በሞት አንቀላፍተዋል።
ከምንወዳቸው ሰዎች ጋር እንደገና የመገናኘት አስደሳች ተስፋ
በፊተኛው ርዕስ ላይ የተጠቀሰው ኦወን በአሳዛኝ ሁኔታ ከሞተ ከጥቂት ጊዜ በኋላ አባቱ ወደ አንድ ጎረቤቱ ቤት ይሄዳል። እዚያም በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ የሕዝብ ንግግር መጋበዣ ወረቀት ጠረጴዛ ላይ አገኘ። “ሙታን የት ናቸው?” የሚለው የንግግሩ ርዕስ ትኩረቱን ሳበው። ይህ ጥያቄ በአእምሮው ውስጥ ሲጉላላ ቆይቷል። በዚህ የሕዝብ ንግግር ላይ በመገኘቱ ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛ መጽናኛ ማግኘት ቻለ። በዚህ ስብሰባ ላይ ሙታን እንደማይሰቃዩ ተምሯል። ኦወንን ጨምሮ በሞት ያንቀላፉ ሰዎች እሳታማ በሆነ ሲኦል ስቃይ አያገኛቸውም፤ ወይም መልአክ እንዲሆኑ አምላክ ወደ ሰማይ አልወሰዳቸውም። ከዚህ ይልቅ በትንሣኤ አማካኝነት ከሞት የሚነሱበት ጊዜ እስኪደርስ በመቃብር ይቆያሉ።—መክብብ 9:5, 10፤ ሕዝቅኤል 18:4
በቤተሰብህ ላይ አሳዛኝ ሁኔታ ተከስቶ ያውቃል? አንተም እንደ ኦወን አባት ‘በሞት የተለዩን የምናፈቅራቸው ሰዎች በአሁኑ ጊዜ የት ናቸው? እንደገና ልናገኛቸው የምንችልበት አጋጣሚ ይኖር ይሆን?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ትንሣኤ የሚሰጠውን ተጨማሪ ትምህርት እንድታነብ እንጋብዝሃለን። ምናልባትም ‘ሙታን ትንሣኤ የሚያገኙት መቼ ነው? ሙሉ በሙሉ ከትንሣኤ ተጠቃሚ የሚሆኑት እነማን ናቸው?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። የእነዚህንም ሆነ የሌሎችን ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት እባክህ የሚቀጥሉትን ርዕሶች አንብብ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የሰው ዘር አምላክን ለማግኘት ያደረገው ፍለጋ (እንግሊዝኛ) የተባለውን በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ መጽሐፍ ገጽ 150-154 ተመልከት።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኤልያስ ልጁ ወደ ሕይወት እንዲመለስ ይሖዋን ለምኗል
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ በኤልሳዕ አማካኝነት የሱነማዊቷን ልጅ ከሞት አስነስቷል
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ በናይን ትኖር የነበረችውን መበለት ወንድ ልጅ ከሞት አስነስቷል
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሰዎች ከሚወዷቸው ዘመዶቻቸው ጋር በትንሣኤ እንደገና ይገናኛሉ