እያንዳንዱን ቀን በሚገባ መጠቀም የሚቻለው እንዴት ነው?
እያንዳንዱን ቀን በሚገባ መጠቀም የሚቻለው እንዴት ነው?
“ጥበብን የተሞላ ልብ ይኖረን ዘንድ፣ ዕድሜያችንን መቊጠር አስተምረን።” (መዝሙር 90:12) ይህንን ትሕትና የተንጸባረቀበት ልመና ያቀረበው የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ሙሴ ነው። ሙሴ ምን እየጠየቀ ነበር? እኛስ እንደዚህ ብለን መጠየቅ ይኖርብን ይሆን?
ሙሴ በቁጥር 10 ላይ የሰው ልጅ የሕይወት ዘመን ምን ያህል አጭር እንደሆነ በአዘኔታ ገልጿል። በሌላ አጋጣሚም “ከሴት የተወለደ ሰው፣ ዘመኑ አጭርና በመከራ የተሞላ ነው” በማለት ኢዮብ የተናገረውን ጽፏል። (ኢዮብ 14:1) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ሙሴ፣ ፍጹም ያልሆኑ የሰው ልጆች ዕድሜ አጭር የመሆኑን አሳዛኝ እውነታ በጥልቅ ተገንዝቦ ነበር። ስለሆነም በሕይወት የኖረበትን እያንዳንዱን ቀን እንደ ውድ ሀብት ይቆጥረው ነበር። ሙሴ ከላይ የተጠቀሰውን ልመና ለአምላክ ሲያቀርብ፣ ቀሪ ሕይወቱን በማስተዋል ይኸውም ፈጣሪውን በሚያስደስት መንገድ ለመኖር እንደሚመኝ መግለጹ ነበር። እኛስ በሕይወት የምንኖርበትን እያንዳንዱን ቀን ትርጉም ባለው መንገድ መጠቀም አንፈልግም? አሁን የአምላክን ሞገስ ማግኘት ከፈለግን ሕይወታችንን በዚህ መንገድ ለመጠቀም ቁርጥ ውሳኔ እናደርጋለን።
ሙሴም ሆነ ኢዮብ እንዲህ እንዲሰማቸው ያደረጋቸው ሌላም ምክንያት ነበረ፤ ይህ ምክንያት እኛም ተመሳሳይ ስሜት እንዲያድርብን ሊያደርገን ይገባል። እነዚህ ፈሪሃ አምላክ የነበራቸው ሰዎች ወደፊት ሽልማት እንደሚያገኙ ማለትም መልካም ሁኔታዎች በሰፈኑበት ምድር ላይ እንደሚኖሩ ተስፋ ያደርጉ ነበር። (ኢዮብ 14:14, 15፤ ዕብራውያን 11:26) በዚያን ጊዜ መልካም የሠራ ማንም ሰው በአጭሩ በሞት አይቀጭም። የፈጣሪያችን ዓላማ ታማኝ ሰዎች ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም እንዲኖሩ ነው። (ኢሳይያስ 65:21-24፤ ራእይ 21:3, 4) ‘ጥበብን የተሞላ ልብ እንዳለህ በሚያሳይ መንገድ ዕድሜህን ከቆጠርክ’ ይህ ተስፋ ለአንተም ተዘርግቷል።