የትንሣኤ ተስፋ—ለአንተ ምን ትርጉም አለው?
የትንሣኤ ተስፋ—ለአንተ ምን ትርጉም አለው?
“አንተ እጅህን ትዘረጋለህ፤ የሕያዋን ፍጥረታትንም ሁሉ ፍላጎት ታረካለህ።”—መዝሙር 145:16
1-3. አንዳንዶች ምን የወደፊት ተስፋ አላቸው? ምሳሌ ስጥ።
የዘጠኝ ዓመቱ ክሪስተፈርና ታላቅ ወንድሙ አንድ ቀን ጠዋት ከአጎታቸውና ከአክስታቸው ጋር ሆነው በእንግሊዝ አገር በማንቸስተር አቅራቢያ ከቤት ወደ ቤት ሲያገለገሉ ቆዩ፤ የአጎታቸውና የአክስታቸው ሁለት ልጆችም አብረዋቸው ነበሩ። ንቁ! መጽሔት ምን እንደተከሰተ እንዲህ በማለት ዘግቧል:- “በዚያን ዕለት ከሰዓት በኋላ አንዳንድ ቦታዎችን ለማየት በባህር ዳርቻ ላይ ወደምትገኘው ብላክፑል የመዝናኛ ከተማ አብረው ሄዱ። በከፍተኛ ፍጥነት በሚነዳበት አውራ ጎዳና ላይ እየተጓዙ ሳለ በደረሰባቸው የመኪና አደጋ እነዚህን 6 ሰዎች ጨምሮ በአጠቃላይ 12 ሰዎች ሕይወታቸውን አጡ፤ ፖሊስ ይህንን አደጋ ‘ታላቅ እልቂት’ ብሎ ጠርቶታል።”
2 ይህ አሳዛኝ አደጋ ከመድረሱ በፊት በነበረው ምሽት ቤተሰቡ በጉባኤ የመጽሐፍ ጥናት ላይ የተገኘ ሲሆን በስብሰባው ላይ ሞትን በተመለከተ ውይይት ተደርጎ ነበር። የክሪስተፈር አባት ሁኔታውን በማስታወስ እንዲህ ብሏል:- “ክሪስተፈር በጣም አስተዋይ ልጅ ነው። በዚያ ምሽት ስለ አዲሱ ዓለምና ስለ ወደፊት ተስፋው በግልጽ ሲናገር ነበር። በውይይቱ መሃል ‘ሞት አሳዛኝ ቢሆንም እንኳ በምድር ላይ በድጋሚ እንደምንገናኝ የምናውቅ መሆናችን የይሖዋ ምሥክር መሆናችን ካስገኘልን ጥቅሞች አንዱ ነው’ በማለት ክሪስተፈር በድንገት ተናገረ። በወቅቱ ማናችንም ብንሆን እነዚህ ቃላት ፈጽሞ የማይረሱ ይሆናሉ ብለን አላሰብንም ነበር።” a
3 ይህ ከመሆኑ ከበርካታ ዓመታት በፊት ማለትም በ1940፣ ፍራንትስ የተባለ ኦስትሪያዊ የይሖዋ ምሥክር ለይሖዋ ያለውን ታማኝነት ባለማጓደሉ ምክንያት አንገቱ ተቆርጦ እንዲገደል ተፈረደበት። ፍራንትስ ከታሰረበት በበርሊን የሚገኝ ወህኒ ቤት እንዲህ የሚል ደብዳቤ ለእናቱ ጽፎ ላከላት:- “[ወታደራዊ] ቃለ መሐላ ብፈጽም ሞት የሚገባው ኃጢአት መሥራቴ እንደሚሆን አውቃለሁ። ይሄ ደግሞ ታማኝነቴን ማጓደል ይሆንብኛል። ትንሣኤም አይኖረኝም። . . . ውድ እናቴ እንዲሁም ወንድሞቼና እህቶቼ ዛሬ ፍርዴን ሰምቻለሁ፤ አትፍሩ። የተፈረደብኝ ሞት ነው፤ ነገ ጠዋት እገደላለሁ። አምላክ ባለፉት ዘመናት ለነበሩት ክርስቲያኖች እንዳደረገው ሁሉ ለእኔም ጥንካሬ ሰጥቶኛል። . . . እስከ ሞት ታማኝ ከሆናችሁ በትንሣኤ እንገናኛለን። . . . በድጋሚ እስክንተያይ ድረስ ደህና ሁኑ።” b
4. እነዚህ ተሞክሮዎች ምን ስሜት አሳድረውብሃል? ከዚህ ቀጥሎ ምን እንመረምራለን?
4 ለክሪስተፈርና ለፍራንትስ የትንሣኤ ተስፋ ትልቅ ትርጉም ያለውና እውን የሆነ ነገር ነበር። ታሪካቸው በእርግጥም ልብን የሚነካ ነው! ለይሖዋ ያለንን ፍቅርና አመስጋኝነት ከፍ ለማድረግ እንዲሁም በትንሣኤ ላይ ያለንን እምነት ለማጠናከር እንድንችል ትንሣኤ ለምን እንዳስፈለገና ይህንን ማወቃችን በግለሰብ ደረጃ እንዴት ተጽዕኖ እንደሚያደርግብን እንመልከት።
በምድር ላይ ስለሚከናወነው ትንሣኤ የተገለጠ ራእይ
5, 6. ሐዋርያው ዮሐንስ በራእይ 20:12, 13 ላይ ያሰፈረው ራእይ ስለ ምን ይገልጻል?
5 ሐዋርያው ዮሐንስ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ራእይ ባየበት ወቅት በምድር ላይ ስለሚከናወነው ትንሣኤም ተመልክቶ ነበር። እንዲህ አለ:- “ሙታንን፣ ታላላቆችንና ታናናሾችን . . . አየሁ፤ . . . ባሕርም በውስጡ የነበሩትን ሙታን ሰጠ፤ ሞትና ሲኦልም በእነርሱ ውስጥ የነበሩትን ሙታን ሰጡ።” (ራእይ 20:12, 13) የሞቱ ሰዎች ሁሉ ምንም ዓይነት ማዕረግ ቢኖራቸው ማለትም ‘ታላላቆችም’ ይሁኑ ‘ታናናሾች’ ምርኮኛ አድርጎ ከያዛቸው ሲኦል ወይም መቃብር ነጻ ይወጣሉ። ባሕር የበላቸው ሰዎችም እንዲሁ በዚያን ጊዜ ዳግም ሕያው ይሆናሉ። ይህ አስደናቂ ክንውን ከይሖዋ ዓላማዎች መካከል አንዱ ነው።
6 የክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት የሚጀምረው በሰይጣን መታሰርና ጥልቁ ውስጥ መጣል ነው። በዚያን ጊዜ ሰይጣን ምንም መሥራት ስለማይችል ትንሣኤ ያገኙትንም ሆነ ታላቁን መከራ በሕይወት ያለፉትን ሰዎች አያሳስታቸውም። (ራእይ 20:1-3) አንድ ሺህ ዓመት ረጅም ዘመን መስሎ ይታይህ ይሆናል፤ በይሖዋ ዓይን ግን “እንደ አንድ ቀን” ነው።—2 ጴጥሮስ 3:8
7. በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ዘመን ለሚሰጠው ፍርድ መሠረት የሚሆነው ምንድን ነው?
7 በራእዩ ላይ እንደተገለጸው የክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ዘመን፣ የፍርድ ጊዜ ይሆናል። ሐዋርያው ዮሐንስ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “ሙታንን፣ ታላላቆችንና ታናናሾችን በዙፋኑ ፊት ቆመው አየሁ፤ መጻሕፍትም ተከፈቱ። ሌላም መጽሐፍ፣ እርሱም የሕይወት መጽሐፍ ተከፈተ፤ ሙታንም በመጻሕፍቱ ተጽፎ በተገኘው መሠረት እንደ ሥራቸው መጠን ተፈረደባቸው። . . . እያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን ተፈረደበት።” (ራእይ 20:12, 13) አንድ ሰው የሚፈረድበት ከመሞቱ በፊት በፈጸመው ድርጊት እንዳልሆነ ማስተዋል ይኖርብናል። (ሮሜ 6:7) ከዚህ ይልቅ እዚህ ላይ የተጠቀሱት “መጻሕፍት” ወደፊት የሚከፈቱ ናቸው። አንድ ሰው ‘በሕይወት መጽሐፍ’ ላይ ስሙ መስፈሩን ወይም አለመስፈሩን የሚወስነው የመጽሐፎቹን ይዘት ካወቀ በኋላ የሚፈጽመው ድርጊት ነው።
‘የሕይወት ትንሣኤ’ ወይም ‘የፍርድ ትንሣኤ’
8. ትንሣኤ የሚያገኙ ሰዎች ምን ሁለት ዓይነት ዕጣ ይጠብቃቸዋል?
8 ዮሐንስ ከዚህ ቀደም ብሎ በተመለከተው ራእይ ላይ ኢየሱስ “የሞትና የሲኦል መክፈቻ” እንዳለው ተገልጾ ነበር። (ራእይ 1:18) ኢየሱስ “በሕያዋንና በሙታን” ላይ ለመፍረድ በይሖዋ ሥልጣን የተሰጠው በመሆኑ “የሕይወት መገኛ” ሆኖ ያገለግላል። (የሐዋርያት ሥራ 3:15፤ 2 ጢሞቴዎስ 4:1) ይህንን የሚያደርገው እንዴት ነው? በሞት ላንቀላፉት ሰዎች እንደገና ሕይወት በመስጠት ነው። ኢየሱስ እየሰበከላቸው ለነበሩት ሰዎች “በዚህ አትደነቁ፤ መቃብር ውስጥ ያሉ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ጊዜ ይመጣል፤ መልካም የሠሩ ለሕይወት ትንሣኤ፣ ክፉ የሠሩ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉ” ብሏቸዋል። (ዮሐንስ 5:28-30) ታዲያ ጥንት የነበሩ ታማኝ ሰዎች ወደፊት ምን ተስፋ ይጠብቃቸዋል?
9. (ሀ) በርካታ ሙታን ትንሣኤ በሚያገኙበት ጊዜ ስለ ምን ነገር ያውቃሉ? (ለ) ምን ሰፊ የትምህርት መርሃ ግብር ይኖራል?
9 በጥንት ጊዜ የነበሩት ታማኝ ሰዎች ትንሣኤ ሲያገኙ፣ ሲያምኑበት የነበረው ተስፋ እውን መሆኑን ይገነዘባሉ። በዘፍጥረት 3:15 ላይ በሚገኘው የመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ላይ የተገለጸውን የሴቲቱን ዘር ማንነት ለማወቅ እንደሚጓጉ የታወቀ ነው! እንደሚመጣ አስቀድሞ የተነገረለት መሲሑ ኢየሱስ እስከ ሞት ድረስ ታማኝ በመሆን ሕይወቱን ቤዛዊ መሥዋዕት እንዳደረገ ሲያውቁ እንዴት ደስ ይላቸው! (ማቴዎስ 20:28) ትንሣኤ ያገኙትን የሚቀበሉት ሰዎችም እንዲሁ፣ የቤዛው ዝግጅት የይሖዋ የማይገባ ደግነትና ምሕረት መግለጫ መሆኑን ከሞት የተነሱት ሰዎች እንዲገነዘቡ መርዳት በመቻላቸው ይደሰታሉ። ትንሣኤ ያገኙት ሰዎች ደግሞ ይሖዋ ለምድር ያለው ዓላማ እንዲፈጸም የአምላክ መንግሥት እያከናወነ ስላለው ነገር ሲያውቁ ልባቸው በአድናቆት ከመሞላቱ የተነሳ ይሖዋን ለማወደስ እንደሚገፋፉ ምንም ጥርጥር የለውም። ለአፍቃሪው ሰማያዊ አባታቸውና ለልጁ ያላቸውን ታማኝነት ለማሳየት የሚችሉበት ሰፊ አጋጣሚ ያገኛሉ። ከሞት የሚነሱት በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አምላክ ያደረገውን የቤዛ ዝግጅት አምነው መቀበል ያስፈልጋቸዋል፤ በዚያን ጊዜ የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ እጅግ በጣም ሰፊ በሆነው እነዚህን ሰዎች በማስተማሩ ሥራ በመካፈል ደስታ ማግኘት ይችላሉ።
10, 11. (ሀ) በምድር ላይ የሚኖሩ ሁሉ በሺሁ ዓመት ግዛት ወቅት ምን አጋጣሚዎች ይከፈቱላቸዋል? (ለ) ይህ እኛን እንዴት ይነካናል?
10 አብርሃም ትንሣኤ በሚያገኝበት ጊዜ፣ ሲጠባበቃት በነበረችው “ከተማ” አገዛዝ ሥር የሚኖረውን እውነተኛ ሕይወት በማየት ታላቅ ደስታ ያገኛል። (ዕብራውያን 11:10) በጥንት ጊዜ ይኖር የነበረው ታማኙ ኢዮብ፣ የእርሱ አኗኗር ንጹሕ አቋማቸውን በመጠበቅ ረገድ ፈተና ያጋጠማቸውን የይሖዋ አገልጋዮች እንዳጠነከራቸው በሚሰማበት ጊዜ ደስ ይለዋል! ዳንኤልም ቢሆን በመንፈስ አነሳሽነት የጻፋቸውን ትንቢቶች ፍጻሜ ለማወቅ ምንኛ ይጓጓ!
11 ትንሣኤ አግኝተውም ይሁን ታላቁን መከራ በሕይወት አልፈው ጽድቅ በሰፈነበት አዲስ ዓለም ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ፣ ይሖዋ ለምድርና በእርሷ ላይ ለሚኖሩ ያለውን ዓላማ በተመለከተ ብዙ የሚማሩት ነገር እንደሚኖር የተረጋገጠ ነው። ይሖዋን ለዘላለም እያወደሱ የመኖሩ ተስፋ፣ በሺህ ዓመት ውስጥ የሚከናወነውን የትምህርት መርሃ ግብር በጣም አስደሳች ያደርገዋል። ይሁን እንጂ በጣም አንገብጋቢ የሆነው ነገር፣ ከመጻሕፍቱ ላይ የተማርናቸውን ነገሮች በግለሰብ ደረጃ በሥራ ላይ የማዋሉ ጉዳይ ነው። የተማርናቸውን ነገሮች በሥራ ላይ እናውል ይሆን? ሰይጣን ለእውነት ጀርባችንን እንድንሰጥ ለማድረግ የሚያቀርበውን የመጨረሻ ፈተና ለመቋቋም የሚያስችል ጥንካሬ የሚሰጡንን በጣም አስፈላጊ የሆኑ ትምህርቶች እናሰላስልባቸውና እንተገብራቸው ይሆን?
12. እያንዳንዱ ሰው በማስተማሩና ምድርን ወደ ገነትነት በመለወጡ ሥራ ላይ ሙሉ በሙሉ እንዲካፈል የሚያስችለው ምንድን ነው?
12 የክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት የሚያስገኝልንን አስደናቂ በረከቶችና ጥቅሞች መዘንጋት አይገባንም። ትንሣኤ የሚያገኙ ሰዎች በአሁኑ ጊዜ እንዳለው የመሰለ የአካል ጉዳት አይኖርባቸውም። (ኢሳይያስ 33:24) በአዲሱ ዓለም ውስጥ የሚኖሩ ሁሉ ሙሉ አካልና ፍጹም ጤንነት የሚኖራቸው መሆኑ፣ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ትንሣኤ የሚያገኙ ሰዎችን ስለ ሕይወት መንገድ በማስተማሩ ሥራ በሙሉ ኃይላቸው እንዲካፈሉ ያስችላቸዋል። እንዲሁም በጭራሽ ተሞክሮ በማያውቀውና ይሖዋን በሚያስከብረው መላዋን ፕላኔታችንን ወደ ገነትነት በመለወጡ ታላቅ ሥራ እነዚህ የምድር ነዋሪዎች ይካፈላሉ።
13, 14. ለመጨረሻ ጊዜ በሚቀርበው ፈተና ወቅት ሰይጣን የሚፈታው ለምንድን ነው? ፈተናው በግለሰብ ደረጃ ምን ውጤት ለያስከትልብን ይችላል?
13 ሰይጣን የመጨረሻውን ፈተና ለማቅረብ ከጥልቁ በሚወጣበት ጊዜ እንደ በፊቱ ሰዎችን ለማሳሳት ይሞክራል። በራእይ 20:7-9 ላይ እንደተገለጸው በሰይጣን መጥፎ ተጽዕኖ በመሸነፍ ‘የሳቱት ሕዝቦች’ ወይም ቡድኖች የጥፋት ፍርዳቸውን ያገኛሉ፤ ‘እሳት ከሰማይ ወርዶ ይበላቸዋል።’ ከሚስቱት መካከል በሺሁ ዓመት የግዛት ዘመን ከሞት የተነሱ ሰዎች ይገኙበታል፤ የእነዚህ ትንሣኤ የጥፋት ፍርድ ትንሣኤ ይሆናል። በተቃራኒው ከሞት ከተነሱት ውስጥ በአቋማቸው የጸኑት የዘላለም ሕይወት ሽልማት ይቀበላሉ። የእነዚህ ሰዎች ትንሣኤ በእርግጥም ‘የሕይወት ትንሣኤ’ ይሆናል።—ዮሐንስ 5:29
14 በአሁኑ ጊዜም ቢሆን የትንሣኤ ተስፋ የሚያጽናናን እንዴት ነው? ወደፊት ከትንሣኤ የሚገኘውን ጥቅም ለመቋደስ እንድንችል ምን ማድረግ ይገባናል?
በአሁኑ ጊዜ የምናገኘው ትምህርት
15. በትንሣኤ ማመን በአሁኑ ጊዜም ቢሆን ሊጠቅም የሚችለው እንዴት ነው?
15 አንተም ምናልባት ወዳጅህን ወይም ዘመድህን በቅርብ ጊዜ በሞት አጥተህ ይሆናል፤ እንዲሁም በተከሰተው አሳዛኝ ሁኔታ ምክንያት የተፈጠረውን ክፍተት ለማስተካከል እየታገልክ ሊሆን ይችላል። የሆነ ሆኖ የትንሣኤ ተስፋ፣ ስለዚህ ተስፋ የማያውቁ ሰዎች የሌላቸውን ውስጣዊ መረጋጋትና ጥንካሬ እንድታገኝ ይረዳሃል። ጳውሎስ የተሰሎንቄ ሰዎችን ሲያጽናናቸው “አንቀላፍተው ስላሉ ሰዎች ሳታውቁ እንድትቀሩ አንፈልግም፤ ደግሞም ተስፋ እንደሌላቸው እንደ ሌሎች ሰዎች እንድታዝኑ አንሻም” ብሏቸው ነበር። (1 ተሰሎንቄ 4:13) በአዲሱ ዓለም ውስጥ ተገኝተህ ሙታን ሲነሱ ስትመለከት በዓይነ ኅሊናህ ይታይሃል? እንዲህ ከሆነ ወዳጆችህን ወይም ዘመዶችህን በድጋሚ ስለማግኘቱ ተስፋ በማሰላሰል መጽናናት ትችላለህ።
16. በትንሣኤ መነሳት ምን ዓይነት ስሜት የሚያሳድርብህ ይመስልሃል?
16 የአዳም ዓመጽ ባስከተለው መዘዝ ሳቢያ በአንድ ዓይነት ሕመም እየተሰቃየህ ይሆናል። ይህ ሁኔታ የሚያስከትልብህ ጭንቀት፣ ጥሩ ጤና ይዘህና ጠንካራ ሆነህ ትንሣኤ እንደምታገኝ ያለህን አስደሳች ተስፋ እንድትዘነጋው እንዲያደርግህ አትፍቀድለት። በዚያን ጊዜ ዓይንህን ገለጥ አድርገህ ትንሣኤ በማግኘትህ ምክንያት በጣም የተደሰቱ ሰዎችን በዙሪያህ ስታይ፣ አምላክን ለፍቅራዊ ደግነቱ እንደምታመሰግነው ምንም ጥርጥር የለውም።
17, 18. ምን ሁለት አስፈላጊ ቁምነገሮችን ማስታወስ ይገባናል?
17 እስከዚያው ድረስ ግን ልናስታውሳቸው የሚገቡ ሁለት ቁምነገሮች አሉ። የመጀመሪያው በአሁኑ ጊዜ ይሖዋን በሙሉ ነፍስ የማገልገሉ አስፈላጊነት ነው። መሪያችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በመምሰል የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ የሚንጸባረቅበት ሕይወት የምንመራ ከሆነ ለይሖዋና ለሰዎች ፍቅር እንዳለን እናሳያለን። በተቃውሞና በስደት ሳቢያ መተዳደሪያችንን ወይም ነጻነታችንን በማጣታችን ምክንያት ምንም ዓይነት ችግር ቢያጋጥመን በእምነት ጸንተን ለመቆም ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ ይገባናል። ተቃዋሚዎች እንደሚገድሉን ቢዝቱብን እንኳ የትንሣኤ ተስፋችን ለይሖዋና ለመንግሥቱ ታማኝ ሆነን እንድንቀጥል ብርታት ይሰጠናል፣ ያጠነክረናል። የምሥራቹን በመስበኩና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ በቅንዓት መካፈላችን፣ ይሖዋ ለጻድቃን ያዘጋጀውን ስፍር ቁጥር የሌለው በረከት የመውረስ ተስፋ እንዲኖረን ያስችለናል።
18 ሁለተኛው ደግሞ ኃጢአተኛ በመሆናችን ምክንያት የሚመጡብንን መጥፎ ምኞቶች መቋቋም ከምንችልበት መንገድ ጋር የተያያዘ ነው። ስለ ትንሣኤ ተስፋ ያለን እውቀትና ይሖዋ ላሳየን የማይገባ ደግነት ያለን አድናቆት፣ በእምነት ለመጽናት ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ ያጠናክርልናል። ሐዋርያው ዮሐንስ “ዓለምን ወይም በዓለም ያለውን ማናቸውንም ነገር አትውደዱ፤ ማንም ዓለምን ቢወድ፣ የአብ ፍቅር በእርሱ ዘንድ የለም፤ ምክንያቱም በዓለም ያለው ሁሉ:- የሥጋ ምኞት፣ የዐይን አምሮትና የኑሮ ትምክሕት ከዓለም እንጂ ከአብ የሚመጣ አይደለም። ዓለምና ምኞቱ ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚፈጽም ግን ለዘላለም ይኖራል” በማለት አስጠንቅቋል። (1 ዮሐንስ 2:15-17) ዓለም ማራኪ አድርጎ የሚያቀርባቸውን ቁሳዊ ነገሮች ‘ከእውነተኛው ሕይወት’ ጋር ስናወዳድራቸው እዚህ ግቡ የሚባሉ አይደሉም። (1 ጢሞቴዎስ 6:17-19) የጾታ ብልግና ለመፈጸም ብንፈተን በጽናት እንቋቋመዋለን። አርማጌዶን ከመምጣቱ በፊት ይሖዋን የሚያሳዝን ባሕርያችንን ሳናስተካክል ብንሞት፣ የትንሣኤ ተስፋ ከሌላቸው ሰዎች ጋር እንደምንፈረጅ እንገነዘባለን።
19. ልንዘነጋው የማይገባን ዋጋ የማይተመንለት መብት ምንድን ነው?
19 ከሁሉም ይበልጥ ግን የይሖዋን ልብ አሁንም ሆነ ለዘላለም የማስደሰት በዋጋ የማይተመን መብት ማግኘታችንን መዘንጋት አይገባንም። (ምሳሌ 27:11) እስክንሞት ድረስ ታማኝ መሆናችን ወይም ይህ ክፉ ሥርዓት እስከሚጠፋበት ጊዜ ድረስ በአቋማችን መጽናታችን፣ የጽንፈ ዓለም ሉዓላዊነትን በተመለከተ በተነሳው ጥያቄ ረገድ ከማን ጎን እንደቆምን ይሖዋን ያስገነዝበዋል። ታላቁን መከራ በሕይወት በማለፍ ወይም ደግሞ ተአምር በሆነው ትንሣኤ አማካኝነት ገነት በሆነች ምድር ላይ መኖር ምንኛ ያስደስታል!
ፍላጎታችንን ያረካልናል
20, 21. ትንሣኤን በተመለከተ መልስ ያላገኘንላቸው ጥያቄዎች ቢኖሩንም ታማኝ ሆነን ለመጽናት የሚረዳን ምንድን ነው? አብራራ።
20 ትንሣኤን በተመለከተ የመረመርናቸው ሐሳቦች ለሁሉም ጥያቄዎቻችን መልስ የሚሰጡ አይደሉም። ካገቡ በኋላ ለሞቱ ሰዎች ይሖዋ ምን ዝግጅት አለው? (ሉቃስ 20:34, 35) ሰዎች ትንሣኤ የሚያገኙት በሞቱበት አካባቢ ነው ወይንስ በዘመዶቻቸው መኖሪያ አቅራቢያ? ትንሣኤን በተመለከተ መልስ ያላገኙ ሌሎችም በርካታ ጥያቄዎች አሉ። የሆነ ሆኖ “እርሱን ተስፋ ለሚያደርጉት፣ ለሚፈልገውም ሰው እግዚአብሔር መልካም ነው። ሰው የእግዚአብሔርን ማዳን፣ ዝም ብሎ ተስፋ ቢያደርግ መልካም ነው” የሚሉትን የኤርምያስ ቃላት ማስታወስ ይገባናል። (ሰቆቃወ ኤርምያስ 3:25, 26) ይሖዋ በፈቀደ ጊዜ ለጥያቄዎቻችን ሁሉ አጥጋቢ መልስ እናገኛለን። እንደዚህ ብለን በእርግጠኝነት መናገር የምንችለው ለምንድን ነው?
21 እስቲ መዝሙራዊው በመንፈስ አነሳሽነት ለይሖዋ ስለዘመራቸው ስለሚከተሉት ቃላት አስብ:- “አንተ እጅህን ትዘረጋለህ፤ የሕያዋን ፍጥረታትንም ሁሉ ፍላጎት ታረካለህ።” (መዝሙር 145:16) ዕድሜያችን እየገፋ ሲሄድ ፍላጎታችንም እየተቀየረ ይመጣል። በልጅነታችን እንፈልገው የነበረውን ነገር አሁን አንመኘውም። ያሳለፍነው ተሞክሮና ተስፋ የምናደርገው ነገር ስለ ሕይወታችን ባለን አመለካከት ላይ ተጽዕኖ ያደርጋል። በአዲሱ ዓለም ውስጥ እንዲኖረን የምንመኘው ምንም ይሁን ምን ይሖዋ ሙሉ በሙሉ ፍላጎታችንን ያረካልናል።
22. ይሖዋን የምናመሰግንበት ምን ጥሩ ምክንያት አለን?
22 በአሁኑ ጊዜ እያንዳንዳችንን የሚያሳስበን ትልቁ ነገር ታማኝ የመሆኑ ጉዳይ ነው። “ባለ ዐደራዎችም ታማኝ ሆነው መገኘት አለባቸው።” (1 ቆሮንቶስ 4:2) ክቡር የሆነው የአምላክ መንግሥት ምሥራች በአደራ ተሰጥቶናል። ይህንን የምሥራች ለምናገኛቸው ሰዎች ሁሉ በትጋት መስበካችን ወደ ሕይወት በሚወስደው ጎዳና ላይ መጓዛችንን እንድንቀጥል ይረዳናል። “ጊዜና አጋጣሚ” ሁላችንንም እንደሚገናኘን መቼም አንዘንጋ። (መክብብ 9:11 NW) በሕይወትህ ውስጥ የሚያጋጥሙህ አስተማማኝ ያልሆኑ ሁኔታዎች የሚፈጥሩብህን አላስፈላጊ ጭንቀት ለመቀነስ እንድትችል በክብራማው የትንሣኤ ተስፋ ላይ ያለህን እምነት አጥብቀህ ያዝ። የክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት እስከሚጀምር በሕይወት እንደማትቀጥል የሚያሳይ ሁኔታ ከተከሰተ፣ የእድሳት ጊዜ በእርግጥ እንደሚመጣ ማወቅህ ያጽናናሃል። ይሖዋ ባቀደው ጊዜ አንተም፣ “ትጠራኛለህ፤ እኔም እመልስልሃለሁ” በማለት ኢዮብ ለፈጣሪ የተናገረውን ቃል መድገም ትችላለህ። በአእምሮው ውስጥ ያሉትን ሰዎች ሁሉ እንደገና ሕይወት ለመስጠት የሚናፍቀው ይሖዋ ይመስገን!—ኢዮብ 14:15
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በይሖዋ ምሥክሮች የታተመውን የሐምሌ 8, 1988 ንቁ! (እንግሊዝኛ) መጽሔት ገጽ 10 ተመልከት።
b የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች (እንግሊዝኛ) የተባለውን በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ መጽሐፍ ገጽ 662 ተመልከት።
ታስታውሳለህ?
• ሰዎች በሺሁ ዓመት ግዛት ወቅት የሚፈረድባቸው በምን መሠረት ነው?
• አንዳንዶች ‘የሕይወት ትንሣኤ’ ሌሎች ደግሞ ‘የፍርድ ትንሣኤ’ የሚያገኙት ለምንድን ነው?
• የትንሣኤ ተስፋ በአሁኑ ጊዜ የሚያጽናናን እንዴት ነው?
• በመዝሙር 145:16 ላይ የተጠቀሰው ሐሳብ፣ ስለ ትንሣኤ መልስ ያልተገኘላቸውን ጥያቄዎች በተመለከተ ተገቢው አመለካከት እንዲኖረን የሚረዳን እንዴት ነው?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በትንሣኤ ላይ ያለን እምነት በአሁኑ ጊዜ የሚጠቅመን እንዴት ነው?