በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

ጳውሎስ አንዲት ክርስቲያን ሚስት “ልጅ በመውለድ ትድናለች [“ጥበቃ ታገኛለች፣” NW]” ሲል የጻፈው ለምንድን ነው?—1 ጢሞቴዎስ 2:15

በዚህ ጥቅስ ዙሪያ ያለው ሐሳብ ጳውሎስ ምን መናገር እንደፈለገ እንድንገነዘብ የሚረዳን እንዴት ነው? ጳውሎስ ክርስቲያን ሴቶች በጉባኤ ውስጥ ስላላቸው ድርሻ በመንፈስ ተገፋፍቶ ምክር እየሰጠ ነበር። “እንዲሁም ሴቶች በጨዋነትና ራስን በመግዛት ተገቢ የሆነ ልብስ ይልበሱ እንጂ በሹሩባ ወይም በዕንቊ ወይም ዋጋቸው ውድ በሆኑ ልብሶች አይሽቀርቀሩ፤ ነገር ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን የሚሉ ሴቶች ሊያደርጉ እንደሚገባ በመልካም ተግባር ይዋቡ” በማለት ጽፏል። (1 ጢሞቴዎስ 2:9, 10) እዚህ ላይ ጳውሎስ ክርስቲያን ሴቶች ጨዋ ወይም ልከኛ እንዲሆኑ፣ በግል ማጋጌጫ ረገድ ሚዛናቸውን እንዲጠብቁና በመልካም ምግባር ‘እንዲዋቡ’ እያሳሰባቸው ነበር።

ቀጥሎ ጳውሎስ በጉባኤው ውስጥ ስላለው የራስነት ሥልጣን ሲናገር “ሴት ዝም እንድትል እንጂ እንድታስተምር ወይም በወንድ ላይ ሥልጣን እንዲኖራት አልፈቅድም” ብሏል። (1 ጢሞቴዎስ 2:12፤ 1 ቆሮንቶስ 11:3) ከዚያም በሰይጣን “የተታለለችውና ኀጢአተኛ የሆነችው” ሔዋን እንጂ አዳም እንዳልሆነ በመናገር የዚህ ዝግጅት መሠረት ምን እንደነበረም ገልጿል። ታዲያ አንዲት ክርስቲያን እንደ ሔዋን ዓይነት ስህተት ከመፈጸም መቆጠብ የምትችለው እንዴት ነው? ጳውሎስ ሲመልስ “ይሁን እንጂ ሴት በእምነትና በፍቅር፣ በቅድስናም ራሷን እየገዛች ብትጸና ልጅ በመውለድ ትድናለች [“ጥበቃ ታገኛለች፣” NW]” ብሏል። (1 ጢሞቴዎስ 2:14, 15) ጳውሎስ እንዲህ ሲል ምን ማለቱ ነበር?

አንዳንድ ተርጓሚዎች የአንዲት ሴት መዳን የተመካው ልጅ በመውለዷ ላይ እንደሆነ አስመስለው ተርጉመውታል። ለምሳሌ ያህል አዲሱ መደበኛ ትርጉም “ሴት . . . ልጅ በመውለድ ትድናለች” ይላል። ሆኖም ጳውሎስ የተናገራቸውን ቃላት በዚህ መልኩ መተርጎሙ ስህተት ነው። አንድ ሰው ለመዳን የግድ ይሖዋን ማወቅ፣ በኢየሱስ ማመን፣ እምነት ማዳበርና ያመነበትን በተግባር ማሳየት እንዳለበት በርካታ ጥቅሶች ያሳያሉ። (ዮሐንስ 17:3፤ የሐዋርያት ሥራ 16:30, 31፤ ሮሜ 10:10፤ ያዕቆብ 2:26) በተጨማሪም ጳውሎስ አማኝ የሆኑ ሴቶች ካለምንም ችግር ልጅ ሊወልዱ እንደሚችሉ ዋስትና መስጠቱ አልነበረም። ክርስቲያኖች ሆኑም አልሆኑ በርካታ ሴቶች በሰላም መውለድ ችለዋል። በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንዶች አማኞች ሆኑም አልሆኑ ልጅ በሚወልዱበት ጊዜ ሕይወታቸውን አጥተዋል።—ዘፍጥረት 35:16-18

ቆየት ብሎ በዚሁ ደብዳቤ ላይ ጳውሎስ ለሴቶች የሰጠው ተጨማሪ ምክር ለመናገር የፈለገው ነገር ምን እንደነበር ለመረዳት ያስችለናል። አንዳንድ ወጣት መበለቶችን አስመልክቶ “ሥራ መፍታትንና ከቤት ቤት መዞርን ይለምዳሉ፤ ሥራ ፈት መሆን ብቻ ሳይሆን፣ የማይገባውን እየተናገሩ ሐሜተኞችና በሰው ጒዳይም ጣልቃ የሚገቡ ይሆናሉ” በማለት አስጠንቅቋል። የጳውሎስ ምክር ምን ነበር? በመቀጠል “ስለዚህ ባል የሞተባቸው ወጣት ሴቶች እንዲያገቡ፣ ልጆች እንዲወልዱ፣ ቤታቸውን እንዲያስተዳድሩ፣ ጠላትም የሚነቅፍባቸውን ነገር እንዳያገኝ እመክራለሁ” ሲል ጽፏል።—1 ጢሞቴዎስ 5:13, 14

ጳውሎስ ሴቶች በቤተሰብ ዝግጅት ውስጥ የሚያበረክቱትን ጠቃሚ ድርሻ ጎላ አድርጎ ገልጿል። ‘ልጆችን መውለድንና ቤቷን ማስተዳደርን’ በመሳሰሉ እንቅስቃሴዎች የምትጠመድ አንዲት ሴት “በእምነትና በፍቅር፣ በቅድስናም ራሷን አየገዛች ብትጸና” ወደ መጥፎ ድርጊት አትሳብም። ያላትን መንፈሳዊነት ጠብቃ ትኖራለች ወይም ለመንፈሳዊነቷ ‘ጥበቃ ይሆንላታል።’ (1 ጢሞቴዎስ 2:15 NW) ወጣት ሴቶች እንዲህ ማድረጋቸው በሰይጣን ወጥመድ እንዳይያዙ ይረዳቸዋል።

ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ የጻፈለት ይህ ደብዳቤ ወንዶችም ሆንን ሴቶች ሁላችንም ጊዜያችንን በተገቢው ሁኔታ መጠቀም እንዳለብን ያስገነዝበናል። የአምላክ ቃል ለሁሉም ክርስቲያኖች “ጥበብ እንደ ሌላቸው ሳይሆን እንደ ጥበበኞች እንዴት እንደምትኖሩ ተጠንቀቁ” ሲል ይመክራል።—ኤፌሶን 5:15