መጥፎ ሁኔታ ሲያጋጥማችሁ ‘ትዕግሥተኛ ሁኑ’
መጥፎ ሁኔታ ሲያጋጥማችሁ ‘ትዕግሥተኛ ሁኑ’
“የጌታም አገልጋይ ሊጣላ አይገባውም፤ ይልቁን ለሰው ሁሉ ገር፣ . . . ትዕግሥተኛም መሆን ይገባዋል።”—2 ጢሞቴዎስ 2:24
1. በአገልግሎት ላይ እያለን አንዳንድ ጊዜ ክፉ ቃል የሚናገሩ ሰዎች የሚያጋጥሙን ለምንድን ነው?
ለአንተ ወይም ለምታከናውነው ሥራ በጎ አመለካከት የሌላቸው ሰዎች ሲያጋጥሙህ ምን ታደርጋለህ? ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ መጨረሻው ዘመን ሲናገር ሰዎች “ተሳዳቢዎች፣ . . . ሐሜተኞች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች” እንደሚሆኑ ተንብዮአል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5, 12) በአገልግሎት ላይ ሆነህ ወይም ሌሎች ነገሮች ስታከናውን እንዲህ ዓይነት ሰዎች ያጋጥሙህ ይሆናል።
2. ክፉ ቃል የሚሰነዝሩብንን ሰዎች በጥበብ እንድንይዝ ሊረዱን የሚችሉት የትኞቹ ጥቅሶች ናቸው?
2 ክፉ ቃል የሚናገር ሰው ሁሉ መልካም ነገር አይወድም ማለት አይደለም። ሰዎች የደረሰባቸው ከባድ መከራ ወይም ብስጭት ባገኙት ሰው ላይ በቁጣ እንዲገነፍሉ ሊያደርጋቸው ይችላል። (መክብብ 7:7) ብዙዎች እንዲህ ዓይነት ዝንባሌ የሚታይባቸው ኃይለ ቃል መናገር የተለመደ በሆነበት አካባቢ ስለሚኖሩ ወይም ስለሚሠሩ ነው። ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን እንዲህ ዓይነቱን አነጋገር ለመጠቀም ይህ ምክንያት ሊሆነን አይችልም፤ ሆኖም ሰዎች ክፉ ቃል የሚናገሩት ለምን እንደሆነ እንድንገነዘብ ያስችለናል። ክፉ ቃል ሲሰነዘርብን ምላሻችን ምን ሊሆን ይገባል? ምሳሌ 19:11 “ጥበብ ሰውን ታጋሽ ታደርገዋለች” ይላል። ሮሜ 12:17, 18 ደግሞ “ለማንም ክፉን በክፉ አትመልሱ፤ . . . ቢቻላችሁስ በበኩላችሁ ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ” የሚል ምክር ይሰጠናል።
3. የምንሰብከው መልእክት ሰላማዊ መሆንን የሚያካትተው እንዴት ነው?
3 በእርግጥ ሰላማውያን ከሆንን ይህ በሁኔታችን ላይ መታየቱ አይቀርም። በምንናገረውና በምናደርገው ምናልባትም ፊታችን ላይ በሚነበበው ስሜትና በድምፃችን ቃና ይንጸባረቃል። (ምሳሌ 17:27) ኢየሱስ ሐዋርያቱን እንዲሰብኩ ሲልካቸው ይህን ምክር ሰጥቷቸው ነበር:- “ወደ ማንኛውም ሰው ቤት ስትገቡ ሰላምታ አቅርቡ [“ሰላም ለዚህ ቤት በሉ፣” ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል]። ቤቱም የሚገባው ሆኖ ከተገኘ፣ ሰላማችሁ ይድረሰው፤ የማይገባው ከሆነ ግን ሰላማችሁ ወደ እናንተ ይመለስላችሁ።” (ማቴዎስ 10:12, 13) ለሰዎች የምናደርሰው መልእክት ምሥራች ነው። መጽሐፍ ቅዱስ መልእክቱን ‘የሰላም ወንጌል፣’ ‘የእግዚአብሔር የጸጋ ወንጌል’ እና “ይህ የመንግሥት ወንጌል” ብሎ ይጠራዋል። (ኤፌሶን 6:15፤ የሐዋርያት ሥራ 20:24፤ ማቴዎስ 24:14) ዓላማችን የሌላውን ሰው እምነት መንቀፍ ወይም እርሱ ባለው አመለካከት ላይ መከራከር ሳይሆን በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን ምሥራች ማካፈል ነው።
4. የመጣችሁበትን ዓላማ ለመናገር እንኳ ዕድል ሳታገኙ አንድ ሰው “አልፈልግም” ቢላችሁ ምን ማለት ትችላላችሁ?
4 አንድ የቤት ባለቤት መልእክታችንን ገና ሳይሰማ “አልፈልግም” ይል ይሆናል። አብዛኛውን ጊዜ “ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አንድ ጥቅስ ላነብልዎት ፈልጌ ነበር” ማለት እንችላለን። በዚህ ሐሳብ ሊስማማ ይችላል። በሌሎች አጋጣሚዎች ደግሞ እንዲህ ማለቱ ጥሩ ሊሆን ይችላል:- “የመጣሁት ወደፊት የፍትሕ መጓደል የሚወገድበትና ሰዎች ሁሉ እርስ በርስ የሚዋደዱበት ጊዜ እንደሚኖር ልነግርዎት ነበር።” በዚህ ጊዜ የቤቱ ባለቤት ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ጥያቄ ካላቀረበ “አሁን አይመችዎትም መሰለኝ” ማለት ትችላላችሁ። የቤቱ ባለቤት በሰላም ባያናግረን እንኳ “የማይገባው” ሰው ነው ብለን መደምደም ይኖርብናል? ምላሹ ምንም ይሁን ምን መጽሐፍ ቅዱስ “ለሰው ሁሉ ገር፣ . . . ትዕግሥተኛም” እንድንሆን የሰጠንን ምክር አስታውሱ።—2 ጢሞቴዎስ 2:24
ባለማወቅ ዓመፀኛ የሆነ ሰው
5, 6. ሳውል በኢየሱስ ተከታዮች ላይ ምን አደረሰባቸው? እንዲህ ያደረገውስ ለምን ነበር?
5 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖረው ሳውል የተባለ ሰው ንቀት በተሞላበት ንግግሩ ብሎም በኃይለኝነቱ የታወቀ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ‘የጌታን ደቀ መዛሙርት ለመግደል ይዝት’ እንደነበር ይናገራል። (የሐዋርያት ሥራ 9:1, 2) “ተሳዳቢ፣ አሳዳጅና ዐመፀኛ” እንደነበር ከጊዜ በኋላ አምኗል። (1 ጢሞቴዎስ 1:13) ምንም እንኳ አንዳንድ ዘመዶቹ ክርስቲያኖች የነበሩ ሊሆኑ ቢችሉም “በቊጣም ተሞልቼ በውጭ አገር እስከሚገኙ ከተሞች ድረስ ተከታትዬ አሳደድኋቸው” በማለት ለክርስቶስ ተከታዮች የነበረውን አመለካከት ገልጿል። (የሐዋርያት ሥራ 23:16፤ 26:11፤ ሮሜ 16:7, 11) ሳውል እንደዚህ በሚያደርግበት ወቅት ደቀ መዛሙርቱ በአደባባይ ከእርሱ ጋር እንደተከራከሩ የሚያሳይ ምንም ማስረጃ የለም።
6 ሳውል እንዲህ ያደርግ የነበረው ለምንድን ነው? ከብዙ ዓመታት በኋላ እንደጻፈው ይህንን ያደረገው “ባለማወቅና ባለማመን” ነበር። (1 ጢሞቴዎስ 1:13) ሳውል ‘የአባቶቹን ሕግ በሚገባ የተማረ’ ፈሪሳዊ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 22:3) የሳውል አስተማሪ ገማልያል ሰፋ ያለ አመለካከት የነበረው ቢሆንም ሳውል በቅርብ ይገናኘው የነበረው ሊቀ ካህኑ ቀያፋ ግን አክራሪ ነበር። ቀያፋ ለኢየሱስ ክርስቶስ መገደል ምክንያት በሆነው ሴራ ውስጥ ዋና ተዋናይ ነበር። (ማቴዎስ 26:3, 4, 63-66፤ የሐዋርያት ሥራ 5:34-39) ከዚያ በኋላ፣ ቀያፋ የኢየሱስ ሐዋርያት እንዲገረፉ ያደረገ ከመሆኑም ሌላ በኢየሱስ ስም መስበካቸውን እንዲያቆሙ በጥብቅ አዟቸዋል። የቁጣ ስሜት ሰፍኖበት የነበረውን የሳንሄድሪንን ሸንጎ ስብሰባ የመራው ቀያፋ ሲሆን እስጢፋኖስ ተወስዶ በድንጋይ እንዲወገር የተፈረደበት በዚህ ወቅት ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 5:27, 28, 40፤ 7:1-60) ሳውል፣ እስጢፋኖስ ሲወገር ተመልክቷል። ከዚያም በደማስቆ የሚገኙትን የኢየሱስ ተከታዮች በማሳሰር እንቅስቃሴያቸውን ለማዳከም የሚደረገውን ጥረት እንዲያስፈጽም ቀያፋ ሥልጣን ሰጠው። (የሐዋርያት ሥራ 8:1፤ 9:1, 2) ሳውል የቀያፋን ሁኔታ በማየት አድራጎቱ ለአምላክ መቅናቱን እንደሚያሳይ አስቦ ነበር። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ትክክለኛ እምነት አልነበረውም። (የሐዋርያት ሥራ 22:3-5) ከዚህም የተነሳ ኢየሱስ እውነተኛው መሲሕ መሆኑን ሳያስተውል ቀረ። ሆኖም ወደ ደማስቆ እየተጓዘ በነበረበት ወቅት ከሞት የተነሳው ኢየሱስ በተአምራዊ መንገድ ሲያናግረው ወደ ልቦናው ተመለሰ።—የሐዋርያት ሥራ 9:3-6
7. ሳውል ወደ ደማስቆ እየተጓዘ በነበረበት ወቅት ከኢየሱስ ጋር በመገናኘቱ ምን አደረገ?
7 ከዚህ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ደቀ መዝሙሩ ሐናንያ ለሳውል እንዲመሠክርለት ተላከ። አንተ ብትሆን ኖሮ ለእርሱ ለመመሥከር ትጓጓ ነበር? ሐናንያ ነገሩ አስጨንቆት የነበረ ቢሆንም ሳውልን በደግነት አናገረው። ሳውል ወደ ደማስቆ እየተጓዘ ሳለ ከኢየሱስ ጋር በተአምራዊ ሁኔታ መገናኘቱ አመለካከቱን እንዲለውጥ አድርጎታል። (የሐዋርያት ሥራ 9:10-22) ከጊዜ በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ በሚል ስም የታወቀ ሲሆን ቀናተኛ ክርስቲያን ሚስዮናዊ ለመሆንም በቅቷል።
የዋህ ሆኖም ደፋር
8. ኢየሱስ መጥፎ ነገር ለሠሩ ሰዎች የአባቱ ዓይነት ዝንባሌ ያሳያቸው እንዴት ነው?
8 ኢየሱስ ቀናተኛ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪ የነበረ ሲሆን ከሰዎች ጋር ባለው ግንኙነት የዋህ ሆኖም ደፋር ነበር። (ማቴዎስ 11:29) ኃጢአተኞች ከክፉ መንገዳቸው እንዲመለሱ የሚያሳስበውን የሰማዩ አባቱን አስተሳሰብ አንጸባርቋል። (ኢሳይያስ 55:6, 7) ኢየሱስ ከኃጢአተኞች ጋር በነበረው ግንኙነት ያደረጉትን መሻሻል ያስተውል የነበረ ከመሆኑም ሌላ እንዲህ ዓይነቶቹን ግለሰቦች አበረታቷቸዋል። (ሉቃስ 7:37-50፤ 19:2-10) ኢየሱስ ውጪያዊ ሁኔታቸውን አይቶ በሌሎች ላይ ከመፍረድ ይልቅ ወደ ንስሐ ሊደርሱ እንደሚችሉ ተስፋ በማድረግ የአባቱን ደግነት፣ ቻይነትና ትዕግሥት ኮርጆዋል። (ሮሜ 2:4) ይሖዋ ሰዎች ሁሉ ንስሐ እንዲገቡና እንዲድኑ ይፈልጋል።—1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4
9. ኢሳይያስ 42:1-4 በኢየሱስ ላይ ከነበረው ፍጻሜ ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?
9 ወንጌል ጸሐፊው ማቴዎስ ይሖዋ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ያለውን አመለካከት ሲገልጽ የሚከተለውን ትንቢት ጠቅሶ ተናግሯል:- “እነሆ የመረጥሁት፣ የምወደውና በእርሱ ደስ የሚለኝ አገልጋዬ፣ መንፈሴን በእርሱ ላይ አኖራለሁ፤ እርሱም ለአሕዛብ ፍትሕን ያውጃል። አይጨቃጨቅም ወይም አይጮኽም፤ ድምፁም በአደባባይ አይሰማም። ፍትሕን ለድል እስኪያበቃ ድረስ፣ የተቀጠቀጠውን ሸምበቆ አይሰብርም፤ የሚጤሰውንም የጧፍ ክር አያጠፋም። አሕዛብ በስሙ ተስፋ ያደርጋሉ።” (ማቴዎስ 12:17-21፤ ኢሳይያስ 42:1-4) ኢየሱስ በእነዚህ ትንቢታዊ ቃላት ላይ እንደተገለጸው የጦፈ ንትርክ ውስጥ አልገባም። አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ባለበት ጊዜም እንኳ እውነትን ይናገር የነበረው ልበ ቅን የሆኑ ሰዎችን በሚማርክ መንገድ ነበር።—ዮሐንስ 7:32, 40, 45, 46
10, 11. (ሀ) ኢየሱስ ፈሪሳውያን በጣም ይቃወሙት የነበረ ቢሆንም እንኳ ለአንዳንዶቹ የመሠከረላቸው ለምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ አንዳንድ ጊዜ ለተቃዋሚዎቹ ምን ዓይነት መልስ ይሰጥ ነበር? ሆኖም ምን ከማድረግ ተቆጥቧል?
10 ኢየሱስ አገልግሎቱን ባከናወነበት ወቅት ከበርካታ ፈሪሳውያን ጋር ተነጋግሯል። አንዳንዶቹ በንግግሩ ሊያጠምዱት የሞከሩ ቢሆንም እንኳ ኢየሱስ ሁሉም መጥፎ ዝንባሌ አላቸው ብሎ አልደመደመም። በተወሰነ መጠን የነቀፋ አመለካከት የነበረው ፈሪሳዊው ስምዖን ኢየሱስን በቅርብ ለማወቅ ስለፈለገ ሳይሆን አይቀርም ቤቱ ምግብ ጋበዘው። ኢየሱስ ግብዣውን የተቀበለ ከመሆኑም ሌላ በዚያ ለነበሩት ሰዎች መሠከረላቸው። (ሉቃስ 7:36-50) በሌላ ወቅት ደግሞ ኒቆዲሞስ የሚባል የታወቀ ፈሪሳዊ ጨለማን ተገን አድርጎ ወደ ኢየሱስ መጣ። ኢየሱስ እስኪጨልም ድረስ ጠብቆ በመምጣቱ አልነቀፈውም። ከዚህ ይልቅ አምላክ እምነት ለሚያሳዩ ሰዎች የመዳንን መንገድ ለመክፈት ሲል ልጁን በመላክ ስላሳየው ፍቅር ለኒቆዲሞስ መሠከረለት። በተጨማሪም ኢየሱስ ለአምላክ ዝግጅት የመታዘዝን አስፈላጊነት በደግነት ነገረው። (ዮሐንስ 3:1-21) በሌላ ጊዜ ስለ ኢየሱስ የቀረበውን ጥሩ ሪፖርት ሌሎች ፈሪሳውያን ሲያጣጥሉት ኒቆዲሞስ ለኢየሱስ ተሟግቷል።—ዮሐንስ 7:46-51
11 ኢየሱስ እርሱን ለማጥመድ ይሞክሩ የነበሩ ሰዎች ግብዝ መሆናቸውን ማስተዋል አልተሳነውም ነበር። ተቃዋሚዎች እርባና ቢስ ወደሆነ ክርክር እንዲያስገቡት አልፈቀደም። ይሁን እንጂ ተገቢ ሆኖ ሲያገኘው የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓትና ጥቅስ በመጥቀስ እንዲሁም ምሳሌ በመጠቀም አጭርና ኃይለኛ መልስ ይሰጥ ነበር። (ማቴዎስ 12:38-42፤ 15:1-9፤ 16:1-4) በሌሎች ጊዜያት ደግሞ መልስ መስጠቱ የሚያስገኘው አንዳች ፋይዳ እንደሌለ ከተገነዘበ ዝም ማለትን ይመርጥ ነበር።—ማርቆስ 15:2-5፤ ሉቃስ 22:67-70
12. ኢየሱስ ሰዎች ቢጮሁበትም እንኳ እነርሱን መርዳት የቻለው እንዴት ነው?
12 ክፉ መንፈስ የተቆጣጠራቸው ሰዎች በኢየሱስ ላይ የጮኹበት ወቅትም ነበር። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥመው ትዕግሥት ያሳየ ከመሆኑም ሌላ አምላክ በሰጠው ኃይል ተጠቅሞ ሰዎቹን ከነበረባቸው ችግር አላቋቸዋል። (ማርቆስ 1:23-28፤ 5:2-8, 15) በአገልግሎት ላይ እያለን አንዳንድ ሰዎች ቢናደዱና ቢጮሁብን እኛም እንደ ኢየሱስ ትዕግሥተኛ መሆን ያለብን ሲሆን እንዲህ ዓይነቱን ሁኔታ በደግነትና በዘዴ ለመያዝ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል።—ቈላስይስ 4:6
በቤተሰብ ክልል ውስጥ
13. አንዳንድ ጊዜ ሰዎች የቤተሰባቸው አባል ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ሲጀምር የሚቃወሙት ለምንድን ነው?
13 አብዛኛውን ጊዜ የኢየሱስ ተከታዮች ትዕግሥተኛ እንዲሆኑ የሚጠይቅ ሁኔታ የሚያጋጥማቸው በቤተሰብ ክልል ውስጥ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ልቡ በጥልቅ የተነካ ሰው ቤተሰቡም ተመሳሳይ ምላሽ እንዲሰጥ ይጓጓል። ሆኖም ኢየሱስ እንደተናገረው የቤተሰቡ አባላት ጥላቻ ያሳዩ ይሆናል። (ማቴዎስ 10:32-37፤ ዮሐንስ 15:20, 21) ለዚህ መንስኤ የሚሆኑ የተለያዩ ምክንያቶች አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ሐቀኞች፣ ኃላፊነት የሚሰማንና ሰው አክባሪ እንድንሆን ሊረዳን ቢችልም በየትኛውም ዓይነት ሁኔታ ሥር ቢሆን በዋነኝነት ኃላፊነት ያለብን ለፈጣሪያችን እንደሆነ የአምላክ ቃል ይናገራል። (መክብብ 12:1, 13፤ የሐዋርያት ሥራ 5:29) አንድ የቤተሰባችን አባል ለይሖዋ ታማኝ በመሆናችን ምክንያት በቤተሰቡ ውስጥ ያለውን ተደማጭነት እያጣ እንደሆነ ከተሰማው ቅር ሊሰኝ ይችላል። በዚህ ዓይነቱ ጉዳይ ላይ ስንነጋገር ኢየሱስ ያሳየውን የታጋሽነት ባሕርይ መኮረጃችን በጣም አስፈላጊ ነው!—1 ጴጥሮስ 2:21-23፤ 3:1, 2
14-16. በፊት የቤተሰብ አባሎቻቸውን ይቃወሙ የነበሩ አንዳንዶች እንዲለወጡ ያደረጋቸው ምንድን ነው?
14 በአሁኑ ጊዜ ይሖዋን እያገለገሉ ያሉ ብዙዎች መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት በጀመሩበት ወቅት ያደርጓቸው በነበሩት ለውጦች የተነሳ የትዳር ጓደኛቸው ወይም ሌላ የቤተሰባቸው አባል ይቃወማቸው ነበር። ተቃዋሚዎቹ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች መጥፎ ነገር ሰምተው ምናልባትም በቤተሰቡ ውስጥ መጥፎ ሁኔታ እንደሚፈጠር ስጋት አድሮባቸው ሊሆን ይችላል። አመለካከታቸውን እንዲለውጡ ያደረጋቸው ምንድን ነው? በአብዛኞቹ ሁኔታዎች በአማኙ ላይ የሚያዩት መልካም ባሕርይ ትልቅ ድርሻ ያበረክታል። አማኙ ምንም ዓይነት ስድብ ቢሰነዘርበትም ትዕግሥት በማሳየት በቤተሰብ ውስጥ ያሉትን ኃላፊነቶች ሳያጓድል፣ ዘወትር በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘትንና በአገልግሎት መሳተፍን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ምክር በታማኝነት ተግባራዊ ማድረጉ ከቤተሰቡ የሚደርስበት ተቃውሞ እንዲለዝብ ሊያደርግ ይችላል።—1 ጴጥሮስ 2:12
15 ተቃዋሚ የሆነ ሰው ካደረበት ጭፍን ጥላቻ ወይም ኩራት የተነሳ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚሰጠውን ማንኛውንም ማብራሪያ ለማዳመጥ ፈቃደኛ ያልነበረበት ጊዜም ይኖራል። በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖር ከፍተኛ የአገር ፍቅር ስሜት እንደነበረው የሚናገር የአንድ ሰው ሁኔታ እንዲህ ይመስል ነበር። በአንድ ወቅት ሚስቱ የአውራጃ ስብሰባ ላይ ሳለች ልብሶቹን በሙሉ ጠቅልሎ ቤቱን ጥሎ ሄደ። በሌላ ጊዜ ደግሞ መሣሪያ ይዞ ከቤት ወጥቶ በመሄድ ራሱን እንደሚገድል ዛተ። ተገቢ ያልሆነ ነገር የሚያደርገው በእርሷ ሃይማኖት ምክንያት እንደሆነ ይናገር ነበር። እርሷ ግን መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ምክር በሥራ ለማዋል ጥረት ማድረጓን ቀጠለች። እህት የይሖዋ ምሥክር ከሆነች ከ20 ዓመታት በኋላ እርሱም የይሖዋ ምሥክር ሆነ። በአልባኒያ አንዲት እናት ሴት ልጅዋ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ በማጥናቷና ከዚያም በመጠመቋ በጣም ተናደደች። በተለያዩ 12 ወቅቶች እናትየው የልጅቷን መጽሐፍ ቅዱስ ቀዳደደችባት። ከዚያም አንድ ቀን ልጅቷ ጠረጴዛ ላይ ትታ የሄደችውን አዲስ መጽሐፍ ቅዱስ ገለጠች። እንደ አጋጣሚ ሆኖ የከፈተችው ማቴዎስ 10:36 ላይ ሲሆን እናትየው ጥቅሱ የሚናገረው ነገር የእርሷን ሁኔታ እንደሚገልጽ ተገነዘበች። ይሁንና ልጅቷ የአውራጃ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ከሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች ጋር ወደ ኢጣሊያ ስትሄድ እናትየው የልጅዋ ደኅንነት ስላሳሰባት እስከ ጀልባው ድረስ ሸኘቻት። እናትየው በመካከላቸው ያለውን ፍቅርና ፈገግታቸውን እንዲሁም እርስ በርሳቸው ሲተቃቀፉና በደስታ ሲስቁ ስታይ የነበራት አመለካከት ተለወጠ። ከዚህ በኋላ ብዙም ሳይቆይ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ተስማማች። በዛሬው ጊዜ ተቃዋሚ የሆኑ ሰዎችን ለመርዳት ጥረት ታደርጋለች።
16 በአንድ ወቅት፣ አንድ ባል ሚስቱ ወደ መንግሥት አዳራሹ እየመጣች ሳለ ቢላዋ ይዞ በቁጣ እየደነፋ ፊቷ ላይ ተደቀነባት። እርሷ ግን በረጋ መንፈስ “ወደ መንግሥት አዳራሹ ገብተህ ሁኔታውን በገዛ ዓይንህ መመልከት ትችላለህ” አለችው። ወደ አዳራሹ ገብቶ ትምህርቱን የተከታተለ ከመሆኑም ሌላ ከጊዜ በኋላ የጉባኤ ሽማግሌ ሆነ።
17. በክርስቲያን ቤት ውስጥ አንዳንድ ጊዜ ውጥረት የነገሠበት ሁኔታ ቢፈጠር የትኛው ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ሊረዳ ይችላል?
17 የቤተሰባችሁ አባላት በሙሉ ክርስቲያኖች ቢሆኑም እንኳ ከሰብዓዊ አለፍጽምና የተነሳ ውጥረት የሰፈነበትና ክፉ ቃላት የሚሰነዘሩበት ሁኔታ ሊከሰት ይችላል። በጥንቷ ኤፌሶን ይኖሩ የነበሩ ክርስቲያኖች “መራርነትን ሁሉ፣ ቊጣና ንዴትን፣ ጭቅጭቅና ስድብን ከማንኛውም ክፋት ጋር ከእናንተ ዘንድ አስወግዱ” ተብለው መመከራቸው ሊስተዋል የሚገባው ጉዳይ ነው። (ኤፌሶን 4:31) ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው የኤፌሶን ክርስቲያኖች በአካባቢያቸው የነበረው ሁኔታ፣ የራሳቸው አለፍጽምናና በአንዳንድ ሁኔታዎች ደግሞ በፊት የነበራቸው ሕይወት ተጽዕኖ አሳድሮባቸው ነበር። ለውጥ እንዲያደርጉ ሊረዳቸው የሚችለው ምንድን ነው? ‘በአእምሯቸው መንፈስ መታደስ’ ያስፈልጋቸው ነበር። (ኤፌሶን 4:23) የአምላክን ቃል ማጥናታቸው፣ ቃሉ በሕይወታቸው ውስጥ ሊያሳድረው ስለሚገባ ተጽዕኖ ማሰላሰላቸው፣ ከክርስቲያን ባልንጀሮቻቸው ጋር መሰብሰባቸውና ከልብ መጸለያቸው በሕይወታቸው ውስጥ የአምላክ መንፈስ ፍሬ ይበልጥ በተሟላ መልኩ እንዲታይ ያስችላል። በዚህ መንገድ “እግዚአብሔር በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ፣ እናንተም ይቅር ተባባሉ፤ እርስ በርሳችሁ ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ” የሚለውን ምክር መፈጸም ይችላሉ። (ኤፌሶን 4:32) ሌሎች የፈለጉትን ቢያደርጉም እኛ ግን ደግ፣ ርኅሩኅና ይቅር ባይ በመሆን ትዕግሥት ማሳየት ይኖርብናል። በእርግጥም፣ ‘ለማንም ክፉን በክፉ መመለስ’ የለብንም። (ሮሜ 12:17, 18) አምላክን በመምሰል እውነተኛ ፍቅር ማሳየት ምንጊዜም ልናደርገው የሚገባ ትክክለኛ ነገር ነው።—1 ዮሐንስ 4:8
ለሁሉም ክርስቲያኖች የሚሆን ምክር
18. በ2 ጢሞቴዎስ 2:24 ላይ የሚገኘው ምክር በጥንቷ ኤፌሶን ይኖር ለነበረ አንድ ሽማግሌ ተገቢ የነበረው ለምንድን ነው? ክርስቲያኖችን በሙሉ ሊጠቅም የሚችለውስ እንዴት ነው?
18 መጥፎ ሁኔታ ሲያጋጥማችሁ ‘ትዕግሥተኛ ሁኑ’ የሚለው ምክር ለሁሉም ክርስቲያኖች ይሠራል። (2 ጢሞቴዎስ 2:24) ይህ ምክር በመጀመሪያ የተሰጠው ለጢሞቴዎስ ሲሆን በኤፌሶን ሽማግሌ ሆኖ ሲያገለግል ትዕግሥተኛ መሆን አስፈልጎት ነበር። በዚያ በሚገኘው ጉባኤ ውስጥ የነበሩ አንዳንዶች የግል አመለካከታቸውን በይፋ ያራምዱ የነበረ ሲሆን የተሳሳተ ትምህርትም ያስተምሩ ነበር። የሙሴ ሕግ ዓላማ ሙሉ በሙሉ ስላልገባቸው የእምነትን፣ የፍቅርንና የበጎ ሕሊናን አስፈላጊነት መገንዘብ ተስኗቸው ነበር። የክርስቶስን ትምህርት ዋና ቁም ነገርና ለአምላክ ያደሩ የመሆንን አስፈላጊነት ባለመገንዘባቸው በቃላት ላይ ሲከራከሩ በውስጣቸው ያለው የኩራት መንፈስ ለጠብ ዳረጋቸው። ጢሞቴዎስ ይህን ሁኔታ ለማስተካከል ለቅዱስ ጽሑፋዊ እውነት ጥብቅ መሆን የነበረበት ቢሆንም ከወንድሞቹ ጋር ባለው ግንኙነት ገር መሆን ነበረበት። በዛሬው ጊዜ እንዳሉት ሽማግሌዎች ሁሉ ጢሞቴዎስም መንጋው የእርሱ ንብረት እንዳልሆነና ከሌሎች ጋር ያለው ግንኙነት ክርስቲያናዊ ፍቅርና አንድነት እንዲሰፍን የሚያበረታታ መሆን እንዳለበት ያውቅ ነበር።—ኤፌሶን 4:1-3፤ 1 ጢሞቴዎስ 1:3-11፤ 5:1, 2፤ 6:3-5
19. ሁላችንም ‘ትሕትናን መፈለጋችን’ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
19 አምላክ ሕዝቦቹን “ትሕትናን ፈልጉ” በማለት አሳስቧቸዋል። (ሶፎንያስ 2:3) “ትሕትናን” ለማመልከት የተሠራበት የዕብራይስጥ ቃል አንድ ሰው የሚደርስበትን ሥቃይ ምንም ሳያማርርና አጸፋውን ሳይመልስ በትዕግሥት ችሎ እንዲያሳልፍ የሚረዳውን ዝንባሌ ያመለክታል። ይሖዋ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ሥር እንኳ ሳይቀር ትዕግሥት ማሳየትና እርሱን በትክክል መወከል እንድንችል እንዲረዳን አጥብቀን እንለምነው።
ምን ትምህርት አግኝተሃል?
• ክፉ ቃል ሲሰነዘርብህ የትኞቹ ጥቅሶች ሊረዱህ ይችላሉ?
• ሳውል ዓመፀኛ የነበረው ለምንድን ነው?
• ከማንኛውም ዓይነት ሰው ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖረን የኢየሱስ ምሳሌ የሚረዳን እንዴት ነው?
• በቤተሰብ ክልል ውስጥ በአንደበት አጠቃቀማችን ራሳችንን የምንገዛ መሆናችን ምን ጥቅሞች አሉት?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሳውል መጥፎ ስም የነበረው ቢሆንም እንኳ ሐናንያ በደግነት አነጋግሮታል
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንድ ክርስቲያን ኃላፊነቶቹን በታማኝነት መወጣቱ ከቤተሰቡ የሚደርስበትን ተቃውሞ ሊያለዝብ ይችላል
[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ክርስቲያኖች ፍቅርና አንድነት ያስፋፋሉ